• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ!

October 20, 2014 08:24 pm by Editor 1 Comment

የጅዳ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት በተወሳሰበ የአሰራር፣ አመራር ሂደት ውስጥ በማለፍም ቢሆን የመማር ማስተማር ሒደቱን ከጀመረ ሁለት ወር ደፍኗል። በሁለት ወራት ልጆቻችን ተምረው ተመለሱ ብሎ ለጠየቀ ምላሹ ቆሽት ያሳርራል። በእስካሁኑ የትምህርት ቅበላ ባለው ከስድስት ያላነሰ ክፍለ ጊዜ የሚማሩት ከሁለትና ሶስት ክፍለ ጊዜ ሲሆን አልፎ አልፎ አራት ክፍለ ጊዜ ብቻ ተምረው ይመለሳሉ። ይህን እውነታ ልጆቹን እንደማዋያ ጥሎ ዘወር የሚለው ባይተዋር ወላጅ ከልጆቹ ይሰማዋል። የልጆቹን ደብተር አገላብጦ የሚመለከት የእኔ ቢጤ ብስጩ አባት ደግሞ ከልጆቹ ከመስማት አልፎ በማስረጃ ደብተሩን  ሲያገላብጥ የሚታዘበው እውነታ ነው።

በአንዳንድ ክፍሎች ዘመናዊውን ትምህርት ትምህርት የሚያሰኙት የእንግሊዝኛና የሒሳብን ጨምሮ ከፍ ሲል የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስ፣ የባዮሎጂና የኮምፒውተር ትምህርቶች መሰጠት የተጀመረው በያዝነው ሳምንት ነው። የሚያም እውነት ነው … ልጆች በተወለዱበት ሃገር ዜግነት ቀርቶ፣ ቅንጣት ልዩ መብት አይሰጣቸውም። ይህ በሆነበት የአረብ ሀገሩን ስደት መከራና የኑሮ ውጣ ውረድ ላገናዘበው፣ ማህበረሰቡ በራሱ ጥረት ት/ቤት መስርቶ አስፈላጊ ክፍያ ፈጽሞና ልጅን ትምህርት ቤት ሰዶ ያልተማረ ልጅን መቀበል ግፍ ነው፣ አመቱን ሙሉ ወደ ትምህት ገበታ ሳይሆን  ወደ ማዋያው ማመላለስ የለየለት ዝቅጠት ነውና ከዚህ መከራ ይሰውረን!

ዛሬ ማለዳ አንድ የፌስቡክ ወዳጀ ስለትምህርት ቤቱ መረጃ ያቀበሉኝ አዝነው ነው፣ ማምሻውን ደግሞ ብርቱ ውስጥ አዋቂ ወዳጀ ስልክ ደውሎ “ምነው የትምህርት ቤቱን ጉዳይ ረሳህውሳ? ቢያንስ ይጻፍ የሚሰማ ቢገኝ!” ሲል የውስጥ የውጩን የተተረማመሰ አሰራርና በየደቂቃው የምሰማውን የወላጁን ሮሮ አስተጋባልኝ … ገፋፍቶኝ ወደ ከሸፈው የኮሚኒቲ የአመታት የለውጥ መንፈስ ነጎድኩ … ተመለስኩና ሌላ የከሸፈ ታሪክ የአረቦች የጸደይ  አብዮት አቀናሁ … ከምናቡ ቅኝት ተመልሸ  የጅዳው ት/ቤታችን እንደ አረቡ አብዮት ከድጡ ወደ ማጡ  … ብየ ጀመርኩት፣ ህመሜን ልተንፍስ በሚል … ከቀደመው ልጀምር …

የተሻለ ይመጣ መስሎን በድክመቱ ላይ አተኩረን ሳናመሰግነው ያለፍነው የቀድሞው ኮሚኒቲ ትልቅ ስራ ሰርቶ ማለፉን ማስታወስ ግድ ይላል። የዛሬን አያድርገውና የጅዳ ኮሚኒቲ የውስጥ ችግሩ እንዳለ ሆኖ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ያደርግ የነበረው ትልቅ ድጋፍ የሚዘነጋ አይደለም። የቀድሞው አሁን ካለውና በድርጅት ሰዎች ጫና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ከሚነገረን ኮሚኒቲ የተሻለ ነው የምንለው በርካታ መምህራንን ከማስመጣት ባለፈ በመማር ማስተማሩ ጠንካራ አቋም ነበረውና ነው።

የቀድሞው ኮሚኒቲ ከአስር ያላነሱ መምህራንን ከሃገር ቤት አስመጥቶ ነበር … ግን አልበረከቱም። አለመበርከታቸው ፈርጀ ብዙ ምክንያት አለው። ድንቅ ድንቅ የሚባሉ መምህራን በትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ በኮሚኒቲ ጣልቃ ገብነትና በራሳቸው የግል ጉዳይ ሃገር ቤት ሄደው ላይመለሱ እዚያው ቀርተዋል … ለነገሩ የትምህርት ቤቱን ዳይሬክተርን ጨምሮ፣ ከሃገር ቤት መጥተው ከእኛ ጋር የከረሙትም ባለሙያ መምህራን ዛሬም አሉ፣ ከማስተማሩ ክልል ግን በሹመት ሰበብ ገለል እያሉ ነው። “በምርጫ” የትምህርት ቤቱን ዋና ዋና ኋላፊነት ቦታዎች ተቀዳጅተዋል፣ በውጭ ህይወታቸው ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በአብዮታዊው ዲሞክራሲያዊ የገዥው ፖለቲካ ፖርቲ አባልነት ሲመለመሉና ሲጠመቁ  አሁንም “በምርጫ” የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት ቁንጮ ባለስልጣናት ሆነዋል፣ በስራና ስብሰባም ተወጥረዋል። ጥቂት ወደ ውስጥ ገባ ካልን የምናገኘው ደስ አይልም። በዚህ ሁኔታ መምህር እያለ መምህር የማጣታችን እንቆቅልሽ ያማል …

የቀድሞው ኮሚኒቲው ከሃገር ቤት የኬሚስትሪ መምህር ቢያስመጣም መምህሩ ከላይ በግርድፍ የተጠቀሰው የአስተዳደር ሹመት እና ሌላም በድርጅት ስልጣን ተንበሽብሸዋል። “መሽ አላህ ብያለሁ፣ ሹመት ያዳብር ብያለሁ” የማልለው ታዳጊዎች እየተጎዱ ስለመሆኑ ዋቢ ጠቅሸ ማስረዳት እችላለሁና ነው።…

በቀድሞው ኮሚኒቲ በአንድ ወቅት አስመጥቷቸው የነበሩት የሒሳብ መምህር በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ወጣት ምሁርን ነበሩ፣ አለመታደል ሆኖ ንቃት፣ ትጋት፣ ተቆርቋሪነታቸው ለትምህርት ቤቱ የበላይ ሃላፊነት መመጠናቸው አደጋ ላይ ጣላቸው፣ ንቃት፣ ትጋት፣ የህዝብ ወገንተኛነታቸው አልተፈለገምና ተማሪ ቀጡ ተብሎ በረቀቀ መንገድ ከትምህርት ቤቱ በራሳቸው ፈቃድ እንደተሰናበቱ ተደርጎ ተወገዱ … ወደ ሃገር ቤት በአስቸኳይ ተሸኙ …

የኮምፒውተር መምህርም በቀድሞው ኮሚኒቲ በኩል ከሃገር ቤት አስመጥተን ነበር፣ ባለሙያውን በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ መምህሩ ሃገር ቤት ሄደው ቀሩ … እንበለው!

ቀጠለና ከአመታት በፊት የኮምፒውተር አስተማሪ እዚሁ በወጣ ማስታወቂያ ተገኘና ቅጥሩ ተፈጸመ። ከጥቂት አመታት በኋላ ግን ማለትም ካሳከፍነው አመት ጀመሮ በሙሉ ሃይላቸው ከማስተማሩ የሚገታቸው የትምህርት ቤቱ “ዩኒት ሊደርነት” ሃላፊነት ተሰጣቸው። እነሆ ዛሬ የኮምፒተሩ መምህር በተሰጣቸው ሹመት መሰረት ማስተማሩን ትተው መምህር የሌላቸው ተማሪዎችን ሲያሯሩጡ ይውላሉ! ይህስ አያምም፣ አያሳዝንም?students

በአሳር በመከራ ወላጅ ተጠርቶ ሲሰበሰብ ትውልድ የማነጹ ስራ ስለመጓተቱ፣ ስለ መምህራን እጥረት፣ ስለ ማስተማሪያ ቁሳቁስና ስለትምህርት ጥራት፣ ስለ ደመወዝ ማነስ፣ ስለ አጠቃላይ አሰራር መጓተት ሂደት መረጃ አጣቅሰው ትምህርት ቤቱ ያለበትን አደጋ ሲናገሩት መስማቱን ለምደነዋል። በዚህ ደረጃ እየተመራ ያለውና እየመሩን ያሉት የትምህርት ቤቱ ሹማምንት የሚሰሩትን ጠጋ ብለን ስንጠይቃቸው ሆድ የሚያሞላ ምላሽ አይሰጡንም፣ ብቻ … አንደበተ ርቱዕ የትምህርት ቤቱ እና ኮሚኒቲው ሹማምንት “ጎደለ” የሚሉትን ለማሟላት ስላለመስራታቸው አጥጋቢ የምለው ምክንያት አለኝ …

ትምህርት ቤቱ ከጀመረ ጀምሮ እንግሊዝኛ በማስተማር ትልቁን ክፍተት ይሸፍኑ የነበሩት ህንዳዊ መምህር ሚ/ር ሳንቱሽ ሲጓተት የተበለሻሸ የመኖሪያ ፈቃድ ማዛወር ሒደት አልተሳካም። ይህም ለጎደለው ትምህርት፣ ለማስተማሩ ክፍተት መሆኑ ብዙዎች መናገር የምንፈራው እውነት ነው። የኮሚኒቲው ሃላፊዎች የእውቁና ባለውለታ መምህሩን  የሚ/ር ሳንቶሽ ፈቃድ ቅየራ ባጓተቱበት እጃቸው የትምህርት ቤቱ ስም በሚሰጠው ፈቃድ የካፍቴሪያው ሰራተኞችን እንደ ባለሙያ አድርጎ ፈቃድ ማስተካከሉ ተሳልጦላቸዋል። ዛሬ ብርቱው መምህር ሁለመናው ከሽፎባቸው “ከቤት ውለዋል!” አሉ። እኛም ትጉህ መምህር አጥተናል! በትምህርት ቤቱ ዙሪያ በዘመድ አዝማድ በተሳሰረው አሰራር የሚታየውና የሚሰማውን ሁሉ ፍትሃዊ የአለመሆን ሂደት ውስጥን ያደማል፣ ቢያብከነክንም አይጠቅምምና ወደ ውስጥ ዘልቄ አልነካካውም … ሁሉን ተናግሬ ሆዴ ባዶ እንዳይቀር ቢስተካከል በሚል እሳቤ ከተጨበጠው መረጃ ግን ጥቂት ጥቂት ብቻ እየቆነጠርኩ መናገሬን ልብ በሉ …

የከሸፈው የጸደዩ አብዮት …

ዛሬ ዛሬ የእኛ ትምህርት ቤት ነገር እንደ አረብ ሃገሩ “የጸደይ አብዮት” ሆኖብናል። የጸደዩ የአረቦች አብዮት ማዕበል ሃይለኛ ነበር። የቱኒዝያ ንጉስ ፕሬዚደንት ቢን አሊ ገርስሶ፣ ሶስት ዓስርተ ዓመታት የተሻገረውን የግብጽን ፕሬዚደንት የሁስኒን አምባገነን መንግስት ደረማምሶታል። የማይመስል፣ አይሆንም ተብሎ የሚገመተው በአብዮቱ ማዕበል ተንጦና ተደረማምሶ አይተናል። የአብዮት ማዕበሉ ሊቢያ ላይ ሲያርፍ “የአፍሪካ ንጉሰ ነገስት ነኝ” ባዩን ፕሬዚደንት ጋዳፊን ከነምናምናቸው ደብዛቸውን አጥፍቷቸዋል። የየመኑን ፕሬዚደንት አሊ አብደላ ሳላህን አላስቀረላቸውም። ሳላህ ከተረጋጋውና በሳውዲ የሚደገፈው ወንበራቸው በማዕበሉ ተጠቅቶ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኛ መሆናቸውን በሹክሹክታም ቢሆን ሰምተናል። የመን ግን ከአንድ ሃገርነት ልትወጣ መከራዋን እያየች ነው … የቀድሞዋ ጥንታዊ አረብ ሃገር የሻሟ የአረቦች ቅምጥል ሃገረ ሶርያ የአብዮቱ ማዕበል ጎድቷት ከሃገር ተራ ወጥታለች … ሶርያ የሃያላኑ ምዕራባውያን የእነ አሜሪካና አጋሮቿ፣ የራሺያና፣ ቻይናና የኢራን ጉልበት መፈተሻ የጦርነት ቀጠና፣ የለየላቸው ጨካኝ አክራሪ ጽንፈኞች መፈንጫ የደም ምድር ሆናለች … ሶርያ!

ተጠልፏልና ያልጠቀመው አብዮት …

እነሆ አብዮቱ ለሁሉም አልበጃቸውም፣ ይህን የምለው ሃገራት ከሃገርነት ተርታ በሚያወጣ እሰጣ ገባ ቋፍ የመገኘታቸው እውነታን ማየታችን ዋቢ በማድረግ ነው። ብቻ አየሆነ ያለው በአብዮቱ የተገኘው የመልካም ለውጥ ትንሳኤ ምሳሌ ሳይሆን መልካሙ የለውጥ ጅምር በእኩዮች ተጠልፎ ለውጡ ውድቀት ዘመም መሆኑን ነው። “አብዮቱ ድሉን መትቷል!” እንዳንል አብዮቱ የተካሔደባቸው ሃገራት የገቡበት ከድጥ ወደ ማጥ የመሆኑን ሃቅ ስናጤነው ብቻ ነው … ይህ በመሆኑ ከአብዮቱ መባቻም የነዋሪው መከራ ካለፈው የከፋ ሆኗል! የሆነው የተፈለገው ሳይሆን ያልተጠበቀው ነውና …!

የተመሳሰለብኝ የእኛው ጉዳይ …

የማይገናኘውን ታላቅ የታሪክ ሂደት ከደቃቃው የእኛ ገጠመኝ ጋር ማመሳሰሉ አይገጥምምና ይገርማችሁ ይሆናል … ትልቁን ከትንሹ ማዛመዴ የለውጡን ፍላጎት፣ በለውጡ መባቻ በጀርባ የተጠለፈውን የለውጥ መንፈስ ተመሳሳይ ሂደት ለማጣቀስ ይረዳኝ እንደሁ ብየ ነው … ቢጨነቀኝ! በጅዳና አካባቢዋ ለማህበረሰቡ ጥቅም መከበር በማሰብ “የተሻለ ይመጣ” መስሎን በቀድሞው ኮሚኒቲ ድክመት ላይ አተኩረን ለለውጡ መረባረባችን እውነት ነው። ለውጥም መጥቶ ነበር፣ ለውጡ ግን በጉልበተኞች ተጠለፈ! የተረባረብንበት የደከምንበት ሁሉ ለዛሬው ፍዳ አደረሰን…

ምርጫው ተጠልፎ ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ እያዘገምን ያለው መንገድ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል … መፍትሔ ጠቁም እንዳትሉኝ! መፍትሔው ከሁላችንም ምክክር መምጣት ይገባዋል፣ ከሁሉም በላይ የ3000 (ሶስት ሺህ) ታዳጊ ተማሪዎችን የትምህርት ቅበላ በዋናነት የሚያገባቸው የጅዳ ቆንስልና በሳውዲ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች አደባባይ በሚታየው የገዘፈ አደጋ ሊመለከቱት ይገባል፣ የትውልድ ግንባታ አደጋ ላይ ወድቋልና “ያገባናል” ብለው ስላልመከሩ ቂም ይዘን አንወቅሳቸውም፣ አሁንም ለተቀመጡበት ወንበር፣ ለቆሙለት ዜጋ፣ ለሚከፈላቸው ክፍያ ሁሉ ቀርቶ ላስተማረቻቸው ሃገር ትንሳኤ ለተተኪው ትውልድ ሲሉ የ3000 (የሶስት ሺህ) ተማሪዎችንና የትምህር ማዕከሉን ሊታደጉት ይገባል! በዚህ ዙሪያ ገብ የጉዳዩ ባለቤቶችን ዜጎችን ማወያየት ከሹሞቻችን ይጠበቅባቸዋል! … እኛ የሚያገባን ግን፣ ይህ ሆነ አልሆነ ትናንትም ዛሬም እንደምናደርገው የሃገር ተረካቢ ልጆች ጉዳይ ስለሚያገባን ወላጅ በፍርሃት ተሸብቦ እንኳ ዝምታን ቢመርጥ እንናገር፣ እንመክር፣ እንጦምርበት ዘንድ ግድ ብሎናል! ጆሮ ያለው ይሰማል፣ ሰምቶ የዝሆን ጀሮን የተመኘ ጥቁር የታሪክ አሻራን መጣሉን ልብ ቢል መልካም ነው!

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Comments

  1. Ethiopian Hagere Jed Bewadi says

    October 21, 2014 03:27 pm at 3:27 pm

    ወዳጅ በት/ቤቱ ዙሪያ ያቀረብከውን መረጃ እንደ ወላጅ እኔንም ስለሚመለክተኝ ሳላመስግነህ አላላፈም ። የ3000 ህጻናተን የመማር ማስተማር ሂደት በማደናቀፍ የህጻናቱን የወደፊት ራዕይ ለማጨለም ሆን ተብሎ እይተፈጸመ ያለው ደባ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ ለአብዛኛው በጅዳ እ ና አካባቢው የምንኖር ኢትዮጵያውያን እንቆቅለሽ ሆኖብናል ። ት/ቤት ውስጥ ያሉትን ችገሮች በበላይነት መዳኘት የሚገባቸው የቆንስላው ሹማምንቶች ምንም እንዳልተፈጸመ ዳር ቆመው ማየታቸው ጤናም ባልሆነ የትምህረት አሰጣጥ ያለ እውቀት ክፍል እየቆጠሩ ትምሀረት መቀበያ እድሜያቸውን በከንቱ እየቀጩ ለሚገኙ ልጆቻችን በእውቀት አለመጎልበት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከተጠያቂ ነት ሊያመልጡ እንደማይችሉ ከወዲሁ ሊረዱት ይገባል። ወዳጅ በህጻናት ልጆቻችን እውቀት መገብያ የኮሚኒ ት/ቤት ዙሪያ እንደወላጅ ባለህ ሙያ ብዙ ለማለት መሞከርህ እንደተጠቀሱት ምርጥ መመህራኖች ስበብ ፈልገው ፡አነትንም መገፍተር ባይችሉም ………… አቅማቸው የሚችለውን ያህል ገን ከመፈጸም የቦዘኑበት አጋጣሚ እንደሌለ ለማወቅ አብነት መጥቀስ ግድ አይልም ። ብቻ ወዳጅ ህጻናት ልጆቻችን እውቀት የሚገበዩበት ማዕከል ለድርድር መቀረብ እንደሌለበት አምናለሁ ! ለዚህም እንደ ወላጅ ልጆቻችን ጥራት ያለው እውቀት እንዲገበዩ የማድረግ የእያንዳንዱ ወላጅ ሃልፊነት መሆኑ ይሰማኛል ። ለዚሀም የኮሚኒቴው ት/ቤቱ እይተፈጸሙ ያሉ ስረአት አልበኝነት በህጻናቱ የትመህረት ጥራት ላይ የሚያደርስው ተጸኖ በሃገር እና በህዝብ ላይ ከሚፈጸም ሸፍጥ ተለይቶ ስለማይታይ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይገበዋል ። በተለይ ጥቂቶች በ መምህራኖች ላይ የሚያሳያዩትን ግብረገብነት የጎደለው አሰራር ከመከላለክል አንስቶ ከወላጆች እጅ የወጣውን ት/ቤት ደንብ እና ስረአት ለማስያዝ ከጻናቱ ጥቀም ይለቅ ጭበጥ ለማትሞላ ከርሳቸው ህሊናቸውን የሸጡ ወገኖችን እንደ ወላጅ ከወዲሁ ሃይ ማለት ይገባናል ! ወዳጅ ጎረቤትህ ነኝ ከበዋዲ !

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

Recent Posts

  • ለሱዳንና ኤርትራ ሲከራከሩ የነበሩት አበባው ባለመመረጣቸው “በጣም ተድጃለሁ” አሉ June 26, 2026 12:29 am
  • “ትህነግ ወደ ዓለምአቀፍ ወንጀለኛነትና አሸባሪነት እየተምዘገዘገ ነው” June 25, 2026 01:00 am
  • አሜሪካ በሕገወጡ ትህነግ አመራሮች ላይ ጠንካራ የቪዛ እገዳ ጣለ June 18, 2026 10:29 am
  • እንደ ሌሊት ወፏ የሚንቀሳቀሰው ኢህአፓ/ትብብር   June 18, 2026 09:36 am
  • የታርጋ ጫጫታ June 15, 2026 05:16 pm
  • ፋንታኹን ዋቄ ከአሜሪካ የሃይማኖት እልቂት አወጁ June 15, 2026 02:12 am
  • ሕገወጡ ትህነግ ወጣቶችን ለዳግም ዕልቂት እያሰናዳ ለፈረንጆች “ኢትዮጵያን አውግዙልኝ” እያለ ነው June 11, 2026 12:57 am
  • በሐዘንና ግልፅ ደብዳቤ ስም የተሸፈነ የድህረ ምርጫ ሀገር የማተራመስ ስትራቴጂ June 10, 2026 12:19 am
  • የጽምዶ ልክፍት June 9, 2026 12:49 am
  • ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው? June 5, 2026 02:37 pm
  • ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም! June 5, 2026 01:47 pm
  • የትብብሩ “ብናሸንፍም ፓርላማ አንገባም” መግለጫ “ወንበር ስታጡ ነው” የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ June 4, 2026 12:04 am
  • አዲሱ የትራምፕ የምርጫ መመሪያ፡ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አፍ ያስዘጋ፤ ተቃዋሚዎች ተስፋ ያስቆረጠ June 3, 2026 08:50 pm
  • “ኢህአፓ ከምርጫው በኋላ ይሰነጠቃል” May 29, 2026 07:07 pm
  • ሪፖርተር፡ “ስውር ተልዕኮ” – በከባድ ወንጀል ሊከሰስ May 6, 2026 11:55 pm
  • የፋኖ ኃይል በደረሰበት ጉዳት ሃምሳ ሺህ የሚጠጋ ትጥቅ ጥሎ ጠፋ April 29, 2026 02:27 pm
  • አዲሱ የቴድሮስ ካሳሁን 888 ኮድ፤ እንደ 666?! April 15, 2026 05:53 am
  • ምኑ ነው ያሳቃችሁ፤ ያስደሰታችሁ? April 2, 2026 10:52 am
  • የጀዋር መሃመድ የፖለቲካ ማንነት እና የባዕዳን ተልዕኮ April 2, 2026 10:16 am
  • ከግብፅ በዳያስፖራ ትርምስ ጠማቂዎች በኩል ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የላከው “ስጦታ” March 27, 2026 09:14 am
  • “ሰላማዊ ታጋዮቹ” እነ ልደቱ ከአራጁ ሸኔ ጋር ተጣምረዋል March 25, 2026 01:04 pm
  • ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነው የሪፖርተር አዘጋገብ March 19, 2026 11:54 am
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ የኦሮሚያ የልማት ድርጅቶች March 18, 2026 10:48 am
  • የጃኖ ስጦታና የዶሮ ፖለቲካ በጎንደር March 10, 2026 09:24 am
Copyright © 2026 · Goolgule