የጣሊያን ፖሊስ በሕገ-ወጥ መንግድ ወደ አዉሮጳ ያሸጋግራሉ በማለት የተጠረጠሩ 10 የኤርትራ ተወላጆችን በቁጥጥር ሥር አዋለ። የካታኒያ-ሲሲሊ ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ስደተኞችን ወደ አዉሮጳ የሚያሸጋግር ሕብረ-ሐገራት መረብ መኖሩን የሚጠቁም መረጃ ከደረሰዉ በኋላ ባደረገዉ አሰሳ ነዉ። በፖሊስ መግለጫ መሠረት ስደተኞቹን የሚያሻግረዉ መረብ ኤርትራ፤ ሊቢያ፤ ሌሎች ሰሜን አፍሪቃ ሐገራት እና ኢጣሊያ ድረስ የተዘረጋ ነዉ። ለአሸገጋሪዎቹ ገንዘብ እየከፈሉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ በርካታ ስደተኞች ሜድትራንያን ባሕር ዉስጥ እየሰመጡ ሞተዋል።
ፖሊስ ሰሞኑን የያዛቸዉን ተጠርጣሪ አሸጋጋሪዎች ካለፈዉ ግንቦት እስከ መስከረም ድረስ 23 የባሕር ላይ ጉዞዎችን አቀነባብረዋል በማለት ከሷቸዋል። ከተጓዦቹ ቢያንስ 240 ስደተኞች ሞተዋል። ከአስሩ ተጠርጣሪዎች ዘጠኙ ኅዳር 16 ቀን ኢጣሊያ ውስጥ የተያዙ ሲሆን አስረኛውና የቡድኑ መሪ ነው ተብሎ የሚጠረጠረው መዓሾ ተስፋማርያም ማክሰኞ ዕለት ጀርመን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ በተለይ ባለፈው ሰኔ ወር ከሊቢያ የሰሜን አፍሪካ ወደብ በበርካታ ተጓዦች ተጨናንቆ የተነሳውንና በኋላ በመስጠሙ ለ224 ስደተኞች ሞት ምክንያት የሆነውን ጀልባ የባህር ላይ ጉዞውን ሲጀምር መዓሾ ተስፋማርያም በአካል በመገኘት ሲቆጣጠር እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የካንታኒያ ሲሲሊ ፖሊስ ዘጠኝ ሶማሌዎችን በሕገወጥ መንገድ በማስተላለፍ ሥራ ላይ የነበረ 11ኛ የኤርትራ ተወላጅ ከዚሁ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ ሶማሌዎቹ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ የተቆለፈ ቤት የነበሩ ሲሆን ስምንቱ ለአቅመአዳም/ሔዋን ያልደረሱ መሆናቸውን የዜናው ዘገባ ጨምሮ ገልጾዋል፡፡ (ዜናው የተገኘው ከዶቸቨለ እና በእንግሊዝኛ ከሚታተም The Local የተሰኘ የጣሊያን የዜና መረብ ነው – Photo-Giovanni-Isolino-AFP)
Leave a Reply