ከሰው ወይ ከአምላክ ፤ ተምሮ የረቀቀ
ቀለም ብዙ የጠጣ ፤ ከባሕር እየጠለቀ
ተለይቶ የወጣ ፤ በርቶለት የራቀ
አንጥሮ አብጠርጥሮ ፤ መርምሮ የላቀ
በአዎንታዊ እሴቶች ፤ ጌጦ ያሸበረቀ
ደግነትን ከሸር ፤ ልማትን ከጥፋት ፤ ለይቶ የጠበቀ
የሚያሰነካክለውን ፤ የት እንዴት እንደሆን ፤ ነቅቶ የጠነቀቀ
ነበር ምሁር ማለት ፤ መሻል መብለጣቸውን ፤ አጣጥሞ ያወቀ
አዬ ድንቄም አያ ii ፤
ምሁሩ ሊቅ ዐዋቂ
የሀገር አደራ ጠባቂ
በአረጋዊያን ተመራቂ
በታናናሾቹ ተደናቂ
ትውልድን አናጭ አምጣቂ
አብእናን ቀራጭ አላቂ
በዕውቀት በጥበብ አርቃቂ
ለችግር መፍትሔን አፍላቂ
የሥልጣኔን ብርሃን ፈንጣቂ
ለሀገር ለወገን መከታ
ለትውልድ ተስፋ አለኝታ
መመኪያ ደጀን ስጦታ
አይደለም ? ትርጉሙ ሲፈታ ?
አዪ … እ !!
ድንቄም ዐዋቂ የመጠቀ
የእንስቷን ተስፋ የደመቀ
በወላጅ አዝማዷ የተጠበቀ
ደርሳ እንድትታይ ያስቋመጠ
ስንት ፈተና አልፎ እያስማጠ
ለዛ የደረሰችውን ማኅቶት
ያችን ኮረዳ የነገን እናት
የቤተሰብ ያገርን መሠረት
ፍቅርን መግባ በጸጋ
ልጆችን ኮትኩታ አሳድጋ
ሀገር ተረካቢውን ዜጋ
የበቁ የነቁ አድርጋ
ይሄንን ያህል ሚና ዋጋ
ያላትን እኅት ድንቅ ሸጋ
ፈጥርቆ የሚበላ ፤ አማራጭ አሳጥቶ
ቅስሟን የሚሠብር ፤ የሚያደቅ አጥቅቶ
ብርሃን የሚያጨልም ፤ ድርግም አርጎ አጥፍቶ
የወገንን ተስፋ ፤ ያገርን ዐይን ወግቶ
ደም እንባ የሚያስለቅስ ፤ ሕዝብን አስከፍቶ
የወላጅ አንጀት ቆራጭ ፤ በሐዘን ምጥ መትቶ
በዚህ ሁሉ ሸክም ፤ የዕዳ ማዕበል ውስጥ ፤ ተንፈራግጦ ዋኝቶ
ቅንጣት ሳይሰማው ፤ ደስታን የሚያጣጥም ፤ ስሜቱን አርክቶ
ይሄ ነው እንዴ ታዲያ ፤ ሊቅ ምሁር የጎላ
ሀገር የምትኮራበት ፤ የትውልዱ ባላ ?
ምሳሌ አርዓያችን ፤ መፍትሔ አዳይ መላ ?፡፡
ለሥጋ ፈቃዱ ፤ ለሚያልፈው ከኋላ
ለዋልጌነት ዐመል ፤ ለቅጽበታዊ ተድላ
ሕግ ወግ ባሕልን ፤ ተላልፎ መሐላ
ያገር የወገንን ፤ አደራ የሚበላ ፡፡
ምንድን ነው ምሁርነት ፤ ሊቅነት ዐዋቂ ?
መማር መንቃት ማለት ፤ ሁሉንም ጠንቃቂ ?
ሰብእናን መቅረጽ ፤ መታነጽ ካልሆነ
ሥነ-ምግባር ሞልቶ ፤ ልብ ካላሳመነ
አርዓያነት ያለው ፤ መዓዛ ካላጠነ
ከዋልጌ ስድነት ፤ ከዓመል ካላዳነ
ግብረ-ገባዊውን ፤ ዘውድ ካላስጫነ
ማሰብ ከተሳናቸው ፤ መለየት ካልቻለ
የሰው እንስሳነትን ፤ ግብር ካልከለከለ
አቅል ማስተዋልን ፤ ብስለት ካላደለ
ለሕሊና አሳድሮ ፤ ፍንክች ካላስባለ
ለእውነት ካላስገዛ ፤ ሐሰት ካላስጣለ
ጅብነትን ገትቶ ፤ ትሕሩም ካላረገ
ከአሕያ አስተሳሰብ ፤ በዕውቀት ካልታደገ
ምንድን ነው ምሁርነት ? መማር ማወቅ ማለት ?
ከደናቁርት ማኅበር ፤ በማወቅ መለየት ? ፡፡
እኮ በል ምንድን ነው ? ምንድን ነው ምሁርነት ?
ጠንቅቆ መገንዘብ ፤ መማር ማወቅ ማለት ? ፡፡
እነኝህን ሀብቶች ፤ ሀብትህ ካላደረክ
ምሁር ነኝ ለማለት ፤ በልኮ እንዴት ደፈርክ ?
የመማር የማወቅ ፤ ጥቅም እና ፋይዳው
እንዴት ነው የሚገባህ ፤ አንተ የምትረዳው ?
እንቅፋት መሆን ነው ? ለሀገር ስኬት ተድላ ?
በሽታ መሆን ነው ? እሾህ አሜኬላ ?
ነቀርሳ መሆን ነው ? በሱስ ማጥ ተዘፍቆ ?
ባንዳነት ማደር ነው ? ለጠላት ጥቅም ታጥቆ ?
በል እኮ ንገረኝ ፤ መልስ እሻለሁ ካንተ
ይሄንን ማለት ነው ? በቃ ተከተተ ? ፡፡
እንደዚህ ነው ዕውቀት ? ዘቅጦ እየተሞተ ?
ሀገር ስታስተምርህ ፤ በድህነት አቅሟ
እንዲህ እንድትሆን ነው ? እንዲሠበር ቅስሟ ?
ሥሯን እንድትነቅል ፤ ልትደፋት ባፍ ጢሟ
በል እኮ በል ለምን ? ምክንያትህ ምንድን ነው ?
ጥቅም ምንዳ ጉርሻህ ? ከዚህ የምታገኘው ?
ምንድን ነው ? ለምን ነው ?
·ረ ለምን ከማን ፤ እባክህ ምንድን ነው ?
ምን አተረፈልን ፤ ከቶ ምን ፈየደ ?
ያንተ ምሁርነት ፤ ምን ሲሳይ ወለደ ?
ከማን ምን አምጥቶ ፤ ምን ጥቅም አዋሐደ ?
የቱን ከምኑ ጋር ፤ አስማምቶ አዋደደ ?
ከተሰቀሉብን ፤ ምኑን አወረደ ?
የገዛ ሀብታችንን ፤ የባዕድ ከማድረግ ሌላ
ምን ተከረ ዕውቀትህ ፤ ምን ጎደሎ ሞላ ?
ከማውደም በስተቀር ፤ የነበረንን ጸጋ
ለምታመልካቸው ሁሉ ፤ ጨለማቸውን ያነጋ
ይሄ ነው የተረፈልን ፤ ከአንተ ምሁርነት
የራስን እየጣሉ ፤ የሩቁን መመኘት
ባዕድ መቀላወጥ ፤ የሩቅ ሆኖ መቅረት
ሥር ተነቅሎ መውደቅ ፤ መስጠም በምማዔ
ደሞ ቀና እንዳንል ፤ እንዳይኖር ትንሣኤ ፡፡
Leave a Reply