ዘመን ፊትሽ ተከምሮ
እየታዬ ስራሽ አምሮ
እንቁጣጣሽ አንድ ብለሽ
አርባ ድረስ እድሜ ቆጥረሽ
እንደ ቤቶች የሳቅ ተውኔት
እንደ ጨቤ ስካር ህይወት
ሞት ራሱን ያሾፍሽበት
ለምንድነው? በይ ንገሪኝ
እባክሽን አደብቂኝ
ባንቺው ቀዬ የተወለድኩ
ፊደል በጄ እዛው የያዝኩ
መስፍን ሜዳ የተራገጥኩ
በጨበጣ ብይ ያስቆጠርኩ
ቲቸር ታዬ ያስተማሩኝ
ገብሬ ኩርኩም ያቀመሰኝ
የሲሚንቶ ጭስ ያወዛኝ
ቅዱስ ያሬድ ተሳልሜ
ከሽፋ ቤት ተሰይሜ
ያቶ ማሞን ኪኒን ቅሜ
እዛው ኖሬ እዛው ያደኩ
የቃጠሎው ቀን የተረፍኩ
እኔ እማውቅሽ የማታውቂኝ
የሰፈርሽ አንድ ስው ነኝ
ይሄን ሁሉ ዘርዝሬልሽ
ጥያቄዬን ስጠይቅሽ
ዝም አትይም መቼም ከፍተሽ
ፊት ለፊትሽ ተስፋሽ ሞልቶ
እየታየ ዝናሽ ጎልቶ
እንደጸደይ ባገር ፈክተሽ
በህዝብ ፊት ደምቀሽ ታይተሽ
በአዲስ አመት በንቁጣጣሽ
በ´ለቱ ለት ምን ቀጠፈሽ
መታሰቢያነቱ ለአርቲስት ሰብለ ተፈራ ይሁንልኝ
sebhat says
ገጣሚው/ዋ ”ወለላዬ ‘ የሰፈሬ ልጅ ሰብለን ብቻ ሳይሆን የተማርኩበትን ትንሿን ትምህርት ቤቴን የተባበሩትን ከነመምህሮቿ አስታወሰኝ/ችኝ