በሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ለሁለትና ሶስት ሰዎች የክብር ዶክትሬት መስጠትን እንደ ልማድ መያዛቸው ከክብር ዶክትሬት መሰረታዊ አላማዎች ጋር የሚፃረርና ክብሩን የሚያራክስ ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ፡፡
የክብር ዶክትሬት የሚሰጥባቸው መስፈርቶች በመርፌ ቀዳዳ ግመል እንደ ማሽሎክ ያህል ናቸው ያሉት ምሁራኑ፤ በአሁን ወቅት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ፉክክር በሚመስል መልኩ ዶክትሬቱን የሚሰጡበት አካሄድ በአስቸኳይ ሊታረም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የክብር ዶክትሬቱ የተሰጠባቸው ግለሰቦችም ለስም መጠሪያነት መጠቀማቸው ተገቢ አይደለም ያሉት ምሁራኑ፤ መገናኛ ብዙኃን የክብር ዶክትሬት የተሰጠውን ግለሰብ፤ “የክብር ዶክተር” እያሉ መጥራታቸውም አግባብ ባለመሆኑ ማረም ይኖርባቸል ብለዋል፡፡
የቋንቋና ስነ ፅሁፍ ምሁሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት የሚሰጥበት ሁኔታ፤ ከማዕረጉ መሰረታዊ አላማ ጋር የተቃረነ መሆኑን አለማቀፍ ልምዶችን በማጣቀስ አስረድተዋል፡፡
በአሁን ወቅት በትምህርት በቅተዋል ተብለው ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጣቸው ምሁራን ምን ያህል ችግር ፈቺ ምርምር ሰርተዋል የሚለው ራሱ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የጠቆሙት ዶ/ር በድሉ፤ የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው አንድ ግለሰብ ተምረው ዶክተር ከሆኑት ባልተናነሰ ሁኔታ ማህበረሰባዊ አስተዋፅኦ ሲያበረክትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
“ማዕረጉ በመደበኛ ትምህርት ከሚገኘው ዶክትሬት ይበልጣል” ያሉት ምሁሩ፤ በዋናነት ከራሱ ማህበረሰብ ባለፈ ለዓለም ህብረተሰብ ያበረከተው አስተዋፅኦና በአለማቀፍ ደረጃ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከግምት ገብቶ ነው የክብር ዶክትሬቱ የሚሰጠው ብለዋል፡፡ “ማንም ሰው ከተማረ ዶክትሬቱን ያገኘዋል፤ ማንም ሰው ግን “የክብር ዶክትሬትን” ሊያገኝ አይችልም ያሉት ዶ/ር በድሉ፤ በኛ ሀገር ግን ክብሩን እንዲያጣ ተደርጎ እየተቀለደበት ነው ብለዋል፡፡
የክብር ዶክትሬት የሚሰጥባቸውን ዋነኛ መስፈርቶች የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ግለሰቡ ከትውልድ ሀገሩ አልፎ እንደ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ አበበ ቢቂላ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ምስረታና ከሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታ ጋር ተያይዞ ስማቸው የሚነሳው አፄ ኃይለ ሥላሴ አይነት አለማቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆኑና ለአለም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ለሌላው አርአያ ይሆናል ሲባል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው አካሄድ ግን ወደ አካባቢ ተወላጅነትና ጎሳ እየወረደ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ምን አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ በጉልህ ያልተገመገሙ ግለሰቦች ጭምር እየተሰጣቸው መሆኑ የክብር ዶክትሬቱን ከአላማና መርህ ውጪ አድርጎታል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸው ግለሰቦች ይገባቸዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የጠቆሙት ምሁሩ፤ በሙዚቃው ዘርፍ ከጥላሁን ገሰሰና ከአስቴር አወቀ ውጪ ሌላ ይገባዋል ብዬ የምቀበለው ሰው የለም ብለዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪ መርሃ ግብር የሌላቸው ዩኒቨርሲቲዎችም የክብር ዶክትሬት መስጠት እንደማይችሉ ዶ/ር በድሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የዶ/ር በድሉን ሃሳብ የሚጋሩት የህግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል ይላሉ፡፡ በሁለት መንገድ የክብር ዶክትሬት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ፕ/ር ጥላሁን፤ በስነ ፅሁፍና በኪነ ጥበብ አለማቀፍ ተፅዕኖ የፈጠሩና በአገር አቀፍና በአለማቀፍ ደረጃ በተሰማሩበት ሙያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎች ናቸው ለማዕረጉ የሚመረጡት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት ፀሐፊ ሆነው ማገልገላቸውን የሚያስታውሱት ፕ/ር ጥላሁን፤ በደርግ ዘመን የክብር ዶክትሬት መሰጠት ቆሞ እንደነበርና ዳግም ካስጀመሩት አንዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በስነ ፅሁፍ ለደራሲ ከበደ ሚካኤልና ኋላም ለደራሲ ሀዲስ አለማየሁ መሰጠቱን ያስታውሳሉ፡፡
የክብር ዶክትሬት የሚሰጠውን ግለሰብ ለመምረጥ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ እንደሚደክሙና ምናልባትም ለበርካት አመታት መስፈርቱን የሚያሟላ ግለሰብ ላይገኝ እንደሚችል የተናገሩት ፕ/ሩ፤ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳዩን የፉክክርና የባለስልጣናት እጅ መንሻ እያደረጉት ይመስላል ብለዋል፡፡ በአካባቢ ተወላጅነት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ምሁሩ፤ ከሰሞኑ እየተሰጡ ያሉ የክብር ዶክትሬቶች ፖለቲካ ፖለቲካ የሚሸቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መስፈርት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ግለሰቦች ማዕረጉን ፈፅሞ ለመጠሪያነት ሊጠቀሙበት እንደማይገባ ሲናገሩም፤ “የክብር ዶክተርም” ሆነ “ክቡር ዶክተር” የሚለው አጠራር ፈፅሞ ስህተት ነው ብለዋል – ፕ/ር ጥላሁን፡፡
በንጉሡ ዘመን እንደ ሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ሴዳል ሴንጎር ላሉት የነፃነት ታጋዮች የክብር ዶክትሬቱ መሰጠቱን ያስታወሱት ምሁሩ፤ በወቅቱ ክብሩ ተጠብቆ እንዲቆይ እንደ ብርቅ ነበር የሚታየው፤ የአሁኑ አካሄድ ግን ልጓም ያጣ ሆኗል፤ በአስቸኳይ ሊስተካከልና ሊታረም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ዩኒቨርሲቲ ማለት “ዩኒቨርሳል” ከሚለው ቃል እንደመሰየሙ አለማቀፍ ባህሪ እንጂ አካባቢያዊ ባህሪ እንደሌለው አውስተው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ዘርና ጎሳ እየወረደ መምጣቱ ክብሩን አሳጥቶታል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ለግለሰቡ ሲሰጥ ዩኒቨርሲቲውንም የሚያስከብር ይሆናል ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢያዊ በመሆናቸው ከዚሁ የአካባቢያዊ ስሜት በመነጨ ለየአካባቢያቸው ተወላጆች ለመስጠት መሽቀዳደማቸው አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡ ከክብር ዶክትሬት አሰጣጥ አላማና መርህ ጋርም ፈፅሞ የሚሄድም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በዛሬው እለት በተለያዩ የትምሀርት ዘርፎች ያስተማሯቸውን ተማሪዎች የሚያስመርቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ለተመረጡ ግለሰቦች የክብር ዶክትሬትን እንደሚሰጥ ጠቁሞ የክብር ዶክትሬትን ለመጠሪያነት መጠቀም አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጠውም አንድ ግለሰብ “እኔ የክብር ዶክትሬት ይገባኛል” ብሎ ሲያመለክት ወይም ሌላ አካል ጥቆማ ሲያቀርብ፤ የግለሰቡ አስተዋፅኦ ተገምግሞ መሆኑን የገለፀው ዩኒቨርስቲው፤ በተቋሙ ይገባቸዋል የሚባሉ ግለሰቦች ሊመለመሉና ማዕረጉ በሴኔት ውሳኔ ሊሰጣቸው ይችላል ብሏል፡፡
ሰሞኑን ተማሪዎቻቸውን ያስመረቁት የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ለአቶ አዲሱ ለገሰና ለሙዚቀኛዋ ማሪቱ ለገሰ የክብር ዶክትሬት ሠጥቷል፡፡ አክሱም ዩኒቨርሲቲም ለአቶ ስብሃት ነጋ የክብር ዶክትሬቱን ሲሰጥ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ፤ ለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ መስጠቱ ታውቋል፡፡ (አለማየሁ አንበሴ – አዲስ አድማስ)
ዩኒቨርስቲዎቻችን እባካችሁን አታሳፍሩን!
“ልፋ ያለው በልሙ ዳውላ ሲሸከም ያድራል” እንዲሉ ሆኖብን ሰሚና አድማጭ ያለ እየመሰለን የምንጮህ ብዙዎች ነን፡፡ ግን ያው እነመምሩ “ነባይ ነባይነ ከምዘይባይነ ኮነ” (ጮህን፣ ጮህን ግና እንዳልጮህን ተቆጠርን (ሰሚ አጣን)” እንዳሉት ዘመናችን የጥንቶቹ ባቢሎናውያን ዓይነት የመደነቋቆሪያ ጊዜ ሆነና እንዲሁ በከንቱ እንደቁራ እንጮሃለን፡፡ ቢሆንም ካለመጮኽ መጮኽ ይሻላል – ዝምታም አንዳንዴ ከሞት አንድ ነው፡፡
የመንግሥት ዩንቨርስቲዎች እየተበሻቀጡ መምጣታቸውን በሚመለከት አዲስ አድማስ ላይ የወጣውን ቆንጆ ጽሑፍ ላገር ተቆርቋሪ ድረገፆችም በሰሞኑ ልጠፋዎቻቸው ለንባብ አብቅተውታል፡፡ በዚያ ጉዳይ ላይ እኔም የበኩሌን ልጮህ ብዕሬን ላነሳ እጆቼን ሳሟሙቅ ነበር ይህን ግሩም ጽሑፍ ያነበብኩት፡፡ ሁለቱን ብርቅዬ ምሁራን ልጆቻችንን – ዶክተሮች ዳኛቸው አሰፋና በድሉ ዋቅጅራን ዋቢ በማድረግ የተሰናዳው ይህ የአዲስ አድማስ አጭር ሀተታ በጨዋ አቀራረብ በጣም ማለፊያ ቁም ነገሮችን አስፍሯል – ሰሚ ከተገኘ፡፡ ችግሩ ግን በአሁኒቷ ሀገራችን ውስጥ አፍ እንጂ ጆሮ የለም፤ ሆድ እንጂ ጭንቅላት ተደፍኗል፤ ዐይናቸው ግምባር የሆነባቸው የጨለማ ልጆች እንጂ ልበ-ብርሃን ዐይናማዎች ለጊዜው ብርቅ ሆነውብናል፡፡ ይህ ቀረሽ በማይባል አጠቃላይ ኪሣራ ውስጥ ተዘፍቀን እኛም ሀገራችንም ኤሎሄ እያልን እንገኛለን፡፡
ዩንቨርስቲዎቻችን መዋረድን ካልፈለጉ ደግሞ የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ይህን መጣጥፍ ከቁብ ሊጥፏቸው ይገባል፡፡ ሰሙንም አልሰሙንም እኛ የራሳችንን ተወጥተናልና አይቆጨንም፡፡ እናም እውነቱን ይዘን እንጮሃለን፡፡ አዳመጡ አላዳመጡ የነሱ ድርሻ ነው፡፡ ቢያዳምጡ ግን የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች እነሱ ናቸው፡፡ ባያዳምጡ ደግሞ በታሪክም ሆነ የታወረ ኅሊናቸው ሲበራ (ሊያውም የሚበራላቸው ከሆነ!) የሚጎዱትና ለጸጸት የሚዳረጉት እነሱው ናቸው፡፡ ጆሯቸውን ገርበብ ያድርጉና ይህን ነገሬን ይስሙ፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ለመጻፍ ሳስብ የክብር ዶክትሬት እንዴትና ለማን ወይም ለነማን መሰጠት እንደሚገባው በልምድ ካካበትኩት የራሴው “ዕውቀት” በመነሣት የኔ በምለው ጀማ ፊት እንዲህ እል ነበር፤ “አንድ የታወቀ ዩንቨርስቲ ይህን የክብር ዶክትሬት የሚባል ማዕረግ የሚሰጠው በአካዳሚያዊም ሆነ በማኅበረሰብኣዊ ልዩ አስተዋፅዖዋቸው በሕዝቡ ዘንድ አንቱታን ያተረፉ ሕዝባዊ ተምሣሌቶች (models/iconic figures) ሊሆኑ ይገባል፡፡ እነዚህን ዓይነት አርአያዎች ምንም እንኳን በቀለም ትምህርቱ ዲግሪውን ሊያገኙ ባይችሉ እንኳን አንድ የዶክትሬት ዲግሪ ከያዘ ሰው በተስተካከለ ምናልባትም በላቀ ደረጃ ዕውቀትና ችሎታቸውን በተግባር ካስመሰከሩ ከመሰል ተፎካካሪዎቻቸው ጋር ተወዳድረው ዲግሪው ይሰጣቸዋል፡፡…”
ይሁን እንጂ ሰሞኑን እንደምናየው በቲፎዞና በሀገር/በወንዝ ልጅነት፣ በጥቅም ትስስርና በእከክልኝ ልከክልህ፣ በጎሣና በብሔር፣ በእጅ መንሻነትና በመጎናበሻነት ይህ የተከበረ ዲግሪ ቢሰጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የታወቀ ነው፡፡ በሀገራችን እያስተዋልነው ያለነው ሁኔታም ይህንን የፈጠጠ እውነት የሚያሳይ ነው፡፡ በየካምፓሶቹ የሚገኙ የወያኔው መንግሥት አሽከሮች ዲግሪውን ከድግርም አሳነሱትና አዛባ ውስጥ ዘፍቀውት ይቀልዱበት ገቡ – ባለጌ ቤት የሚገኝ መልካም ነገር መቼም አያምርበትም፡፡ “‹ዳቦ›ና ሥጋ እባለጌ ቤት ርካሽ ነው” የሚባለውስ ለዚህም አይደል? ዳር ድንበር ያልተበጀበለት ብልግና አይጣል ነው፡፡
እኔ በሀገራችን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መናደድ የጀመርኩት የ110 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ድሃ አሮጊት – በጣም የጃጀች ባህላዊ ዘፋኝ – ከአልጋ አውርደው “ዶክተር ንጋቷ ከልካይ” ብለው የክፍለ ዘመኑን ኮሜዲ በደረሱ ጊዜ ነው፡፡ ከርሷ ይልቅ ለአባባ ተስፋዬ ሣህሉ ቢሰጧቸው ምን ነበረበት? (ለአባባ ተስፋዬ (እስካሁን ካልሰጡ) ያልሰጡበት ምክንያት ሊሆን የሚችለው ወያኔ የጠላውን ማክበር መዘዙ በቀላሉ የማይነቀል በመሆኑ ነው፡፡) ወያኔን ሳያውቅም ቢሆን ያስኮረፈ ሰው ሰማይና ምድርን የሚያስታርቅ ሒሣባዊ ቀመር ቢፈለስፍ እንኳንስ የክብር ዶክትሬት ሠርቲፊኬትም አይሰጠውም፤ የወያኔ አፋዳሽ ከሆነ ግን እንዳሞሌ ጨው ያቀለሉት የክብር ዶክትሬት ይቅርና “እውነተኛው” የፒኤችዲ ዲግሪም ታትሞ ይሰጠዋል፡፡
በመሠረቱ የሰው ግርድና አመሳሶ የለውም፤ በአርአያ ሥላሤ የተፈጠረ ሁሉ እኩል ሰው ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ግን የክብር ዶክትሬት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ ችግር አለ ነው፡፡ ለንጋቷ ከልካይ ይገባ የነበረው እንድትጦርበትና ከደሳሳ ጎጆ ወጥታ ቀሪ ዕድሜዋን ጥቂት ዘና ብላ እንድትኖር – ፅድቁ ቀርቶባት በቅጡ እንድትኮነን – የዶክትሬቱ ዲግሪ ቀርቶባት ጥቂት ሣንቲሞች ቢሰጧት ነበር፡፡ ለርሷም የማይገባትንና(የማትረዳውንና ማለቴ ነው) ለማስረዳትም ዓመት የሚፈጀውን ይህን ከባድ ማዕረግ ለዚህች ሴት መስጠት የዲግሪውን ክብርና ሞገስ እንዲሁም ምንነት ካለማወቅ የሚመነጭ ድንቁርና ነው፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ምን እየሠራ እንደሆነ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ አሁንና ሰሞኑን ደግሞ ሌሎች ማፈሪያ ዩንቨርስቲዎችም የትልቁን ማፈሪያ ተቋም ተከትለው መጃጃል ይዘዋል አሉ፡፡ እግዜር ያሳያችሁ፣ ክርስቶስ ያመላክታችሁ – አሁን በሞቴ ለአዲሱ ለገሠ እንዴት ተደርጎና በየትኛው መለኪያ ተመዝኖ ነው የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው? ዩንቨርስቲውን በቁሙ ለመግደል ካልሆነ በስተቀር እንዴት ለዚህ በእጁ የጠቀለለውን ምግብ እንኳን አስተካክሎ መጉረስ የማይችል ማይም ደንቆሮ፣ ለዚህ ከስፖርት መምህርነት የሜዳ ላይ ዝላይ በዘለለ ፊደል ላልቆጠረ ንፋሽ ገለባ በምን ሒሣብ ይህ ማዕረግ ይሰጣል? ወያኔ ከሰማይ በታች ሊፈጽመው የማይችለው ጀብድ እንደሌለው ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ይህን አካዳሚያዊ ግድያ እውን ሆኖ ማየት እጅግ አሣፋሪና ሀገሪቱን ለዓለም አቀፍ ትዝብት የሚዳርግ ነው፤ እኔ አፈርኩ፡፡እንዲያው ግን በምን መስክ ይሆን የሰጡት? ለመሆኑ በምን በምን መስክ ይህ ዲግሪ እንደሚሰጥስ ያውቁ ይሆን?
እርግጥ ነው – የክብር ዶክትሬት ለሙዚቃና ለኪነ ጥበብ ሥራዎችም እንደሚሰጥ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እጅግ ጎልተው የወጡና ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ባለው ሁኔታ ታላቅ አስተዋፅዖ ላበረከቱ እንጂ በስመ ተደናቂነት ጥሩ ድምፅ ላላቸውና ድንቅ ሽብሻቦ ላሳዩ ሁሉ ይህ የክብር ዲግሪ እንደቡና ቁርስ ለሁሉም አይታደልም – እንዲያ ከሆነ ብርቅነቱ ይቀርና ሁሉም አቀንቃኝና ደራሲ፣ ሁሉም ሰዓሊና ሯጭ፣ ሁሉም ስመጥር ነጋዴና ታዋቂ ግለሰብ እየተነሣ ሊዶከትር ነው ማለት ነው – ተመቅኝቼ አይደለም ፤ ግን ዓላማው ያ ስላልሆነ ነው፡፡ ዝርዝሩን ማወቅ ለሚፈልግ ከሥር በተቀመጡ አድራሻዎች ይጎልጉል፡፡
ከዚህ አንጻር ለማሪቱ ለገሠም ሆነ ለአስቴር ዐወቀ የተሰጠው የክብር ዶክትሬት ሚዛን አይደፋም፡፡ ለኃይሌ ገ/ሥላሤም የተሰጠው እንዲሁ፡፡ የክብር ዶክትሬት ያልታወቁትንና የተደበቁትን ማውጫና የምርምርና የማኅበራዊ በጎ ሥራዎቻቸውን ዕውቅና መስጫ እንጂ ባላቸው ላይ ዕዳ መቆለያ አይደለም፡፡ ቢል ጌትስን ከተሰቀለበት የዝና ሰማይ አውርደህ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የክብር ዶክትሬት መስጠት ምንም ትርጉምና ስሜት አይሰጥም – ለምሣሌ፡፡ ምሥጋናና ስድብ ከየትም አቅጣጫ ቢመጣ ማስደሰቱና ማናደዱ ስለማይቀር እርሱ መጥቶ ዲግሪውን ቢቀበልም እነሱ ግን ማፈር ነበረባቸው፡፡ ዳሩ ሀፍረትን መች ፈጠረባቸውና፡፡ የሽልማቱ ዳር ዳርታ ግን ግልጽ ነው – “አሻሮ ይዘህ ወዳለው ተጠጋ” ይላል ያገሬ ሰው፡፡
ድንቅ ድንቅ ዜጎችን ገንዘብ መሸለም፣ ኑሯቸው እንዲሻሻል ማድረግ፣ ሀውልት ማቆም፣ የማድነቂያና የማመስገኛ ምሽቶችን ማሰናዳት፣ ቴምብሮችን በምስላቸው ማዘጋጀት፣ በስማቸው አደባባዮችንና መንገዶችን መጥራት፣ ወዘተ. ይቻላል፡፡ የክብር ዶክትሬትን ግን ስትጠጣና ስትቅም ትዝ ላለህ አርቲስትና ፖለቲከኛ ወይም ነጋዴና ቱጃር ሀብታም ሁሉ መርጨት – በዚያም ተንጠላጥለህ አንዳች ጥቅምህን ለማስከበር መቋመጥ ትርፉ በሀገር ላይም ሆነ በተቋማቱ ላይ የማይሽር ጠባሳን ጥሎ ማለፍ ነው፡፡
ይህን ዲግሪ የሚሸለም ሰው ቢጠፋ እንዴት ፖል ካጋሜ ይሸለም? በዩንቨርስዎቻችን ያሉትን አመራሮች ምን ነካቸው? ለምን ድረገፆችን ከፍተው ስለዚህ ዲግሪ አሰጣጥ ሂደት ጥቂት አያነቡም? ለምን በስሜት ፈረስ ይጋልባ? ለወያኔ ጭፍሮች በጭፍን እየታዘዙ ሀገርን ለምን ያዋርዳሉ? ነገ እኮ “እነማን ነበሩ?” የሚል የታሪክ ጥያቄ ይከተላል፡፡ እነሱ ቢሞቱ ልጆቻቸውና ትውልዳቸው ያፍርባቸዋል፡፡ ስብሃት ነጋን መሸለም ምን ማለት ነው? “እየሰከራችሁ ከልጅ ልጆቻችሁ ጋር ከማገጣችሁና በቢሊዮኖች የሚገመት የሀገርና የድርጅት ብር ከመዘበራችሁ የክብር ዶክትሬት ትሸለማላችሁ!” የሚል መልእክት ለወጣቱ ለማስተላለፍ ይሆን የአክሱም ዩንቨርስቲ ዓላማ? ደግሞ ዶክተር በድሉ እንዳለው ይህ ተቋም የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም ሳይኖረው በምን ሥልጣኑ ነው ይህን ዲግሪ የሚሰጠው? እንደዚህ ከሆነማ የሰቆጣ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ለካሣ ተ/ብርሃን ይህን የፈረደበት የክብር ዶክትሬት መስጠት ሊኖርበት ነው፤ የላሊበላው የቅርጻ ቅርጽ ማሰልጠኛ ተቋም ለልደቱ አያሌው ይህን ዲግሪ ይስጠውና ጥቂት ያስቀን ደግሞ፤ ሆ! ኧረ እነዚህ ሰዎች ወዴት እየወሰዱን ነው እናንተዬ? እንዴት ነው ለይቶላቸው እንዲህ የተሞላፈጡት?
ለየት በሚል አገላለጽ ልድገመውና አሁንም የክብር ዶክትሬት የገና ዳቦ አይደለም፡፡ የሚሰጠው ሰው ከሙያዊ አስተዋፅዖው በተጓዳኝ በግል ሕይወቱ ጭምር ተምሣሌት መሆን አለበት፡፡ ለምሣሌ የኔ ቢጤው ሰካራምና ሰክሮ ተወላግዶ እየተለፋደደ ሠፈሩንና ቤቱን የሚረብሽ ሰው ጨለማንና ብርሃንን የማስታረቅ ጥበብና ተሰጥዖ ቢኖረው እንኳን የክብር ዲግሪ ሊያገኝ አይገባውም፡፡ ለአብነት ያህል ማንትስ ወርቃለማሁ የሚባል እንደኔ ቀበጥ ሽማግሌ በአርትና በማስተዋወቅ ሥራ ሺህ ጊዜ ቢጣበብና ሰማይ የደረሰ ዕውቀትና ችሎታ ቢኖረው ይህን ዲግሪ (ኢትዮጵያ ውስጥ ካልሆነ) በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም – መመዘኛዎቹ እጅግ ጥብቅ ናቸው፡፡ የዕለት ተለት ሕይወት፣ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ለወጣቱ ያለው አርአያነትና ሁለንተናዊ ፋይዳ፣ በሙያው ያበረከተው ታላቅ ማኅበረሰብኣዊ ትሩፋት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተወዳጅነትና ተፈቃሪነት፣ ሥሙር ቤተሰባዊ ሕይወት፣ ለሽልማት ባሳጨው ታላቁ ሥራው እየደከመ ያሳለፈው ረጂም ዕድሜ ወዘተ. ለዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት ዋና ዋና የብቃት መመዘኛ መሥፈርት ናቸው፡፡ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ የክብር ዲግሪ መጫን ካለማ እኔስ አንድም በትልቁ መንደር ማርካቶ መሀል ተወልጄ በማደጌ፣ ስምንት ልጆችን አፍርቼ ሥጋን፣ ወተትን፣ ጥሩ ጥሩ ልብስን፣ እንዲሁም አትክልትንና ፍራፍሬን ሣይጨምር አንድም ነገር ሳይቸግራቸውና ሳይጓደልባቸው በማሳደጌ፣ በአንዲት ሚስት ብቻ ተወስኜ ከ37 ዓመታት በላይ በመዝለቄ፣ ጠይም በመሆኔ… ይህ ዲግሪ ይገባኛልና እንዲሰጠኝ የትውልድ መንደሬን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመዳወላቡ ዩንቨርስቲን መጠየቅ አለብኝ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያችን ከወያኔ መቀለጃነት ነፃ ሆና የምናያት ጊዜ ከምንም በላይ ናፍቆኛል፡፡ ወያኔ ካልሆንክ አንተስ? ወያኒት ካልሆንሽ አንቺስ? … ለካንስ ዘመን ሲያረጅ ጣጣው ብዙ ኖሯል?
እንዲያው ለነገሩ ግን በወያኔ ዘመን መጫወቻ ያልሆነ ነገር ምን አለ? የዩንቨርስቲው አበዛዝ ሲታይ ሀገር የተመነደገች ትመስላለች፤ አንድም ነገር ያልተሟላላቸው እኮ ናቸው፤ እንኳን በየበረሃውና በየጫካው ያሉት ተቋማት ዱሮ በግሩም የሁለተኛ ደረጃነት ደረጃው የሚታወቀው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ራሱ ባዶ ነው – ቀፎ፡፡ መምህርም፣ የሙያ ብቃትና ፍቅርም፣ የማስተማር ችሎታና ፍላጎትም፣ የመማር “አፕታይትም”፣ የማስተማሪያ ግብኣትም፣ የሙያ ሥነ ምግባርም፣ ምንም ምናምንም … የለውም፤ ቤቱ ብቻ ተገትሮና በወያኔ ካድሬዎች ተሞልቶ እንደፀጉራም ውሻ ሞቷል ሲሉት በጣር ላይ ብቻ አለ፡፡
በተለይ ሌሎቹማ አስተማሪው ከተማሪው የማይለይባቸው ባዶ “ዩንቨርስዎች” ናቸው፤ የሁሉም ጽንሰ ሃሳቦች ፍቺና ምንነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ ዩንቨርስቲ ማለት እኮ የዕውቀት አምባ፣ የማኅበራዊ ዕሤቶች ማበልጸጊያ የሞራልና የመልካም ሥነ ምግባር ምንጭ ማለት ነው – የኞች ግን በተቃራኒው መሸራሞጫና የወሲብ ንግድ የሚጧጧፍባቸው፣ ከወላጆች የተለዩ ሕጻናት ልጆች የሚበለሻሹባቸው፣ የወሲብ ጥማተኞች የሆኑ የወያኔ ኢንቨስተሮችና ልማታዊ ባለሀብቶች የሚጎበኙዋቸው ጎጃም በረንዳና የቀድሞዋ ሠንጋተራዎች ናቸው (harems)፡፡ አዎ፣ በዕውቀትም፣ በሰውነት አቋምም፣ በዕድሜም፣ በአለባበስም፣ በጠባይና በሱስም ተማሪውን ከአስተማሪው የማትለይባቸው የማስመሰያው ዕቅድ ማሟያ ተቋማት መሆናቸውን በሚገባ እናውቃለን፡፡ አልሞትንም ብለን እንፎክራለን እንጂ አሣምረን ሞተናል፡፡ ይህን በወያኔ ተገንዞ የተቀበረ ትምህርት እንዴት ከሙታን ሠፈር ማንሳት እንደሚቻል እንደ አንድ ጤነኛ ዜጋ ሆናችሁ ስታስቡት እጅግ ማስጨነቁ አይቀርም – ለመጨነቅ ጊዜና ፍላጎት ካላችሁ ሊያውም፡፡
በነገራችን ላይ በዶክተር በድሉ አንድ ሃሳብ ላይ አልስማማም፡፡ ያም አንድ የክብር ዶክተር በማዕረጉ ሊጠራበት አይችልም ያለው ነው፡፡ በበኩሌ አሳምሮ ይጠራበታል ባይ ነኝ፡፡ የሴኔት አባላት ስንትና ስንት ተራኩተውና ተሟግተው ከነሙሉ ክብሩ ጥቅሙና ማዕረጉ የሚሰጥን የክብር ዶክትሬት ተሸላው ካተጠራበት ዱሮውንስ ምን ይሠራለታል? ከመነሻው የተሰጠው እኮ ብቃቱና ችሎታው በአቻ ግመታ ተረጋግጦ ዶክትሬት እንደሚገባው ታምኖበት ነው፡፡ ስለዚህ የክብር ቅብጥርስ ሳይባል በሌጣው “ዶክተር ታረቀኝ ሙጬ” ተብሎ ሊጠራበት ይችላል – “ማን ሊስምሽ ታሞጠሙጭ” እንዳትሉ እንጂ፡፡ ለዚህም ነው እኮ “ዶክተር አዲሱ ለገሠ” ዶክተር ሥብሃት ነጋ” ዶክተር ተፈራ ዋልዋ፣ ፕሮፌሰር ጄኔራል ሣሞራ የኑስ፣ ዶክተር አባዱላ …” ለማለት አንደበታችንን ከመክፈታችን በፊት ሣቃችን እየቀደመን ጥርሳችንን ሳንወቀር ሆዳችንን ይዘን የምንንፈራፈረው፡፡
ለግንዛቤ ያህል – ውድ ዩንቨርስቲዎቻችን ሆይ! እባካችሁን ይህን ተረዱ፡- ለገዳይ የክብር ዲግሪ አይሰጥም፤ ሕዝብን በአንድ ዐይን እኩል ለማያይ ዘረኛ ሰው የውርደት ካልሆነ የክብር ዲግሪ አይሰጥም፡፡ ለነጋዴና ለግል ጥቅም ሲል አቅሉን ስቶ ተራውጦ ሀብትና ንብረት ላበጀ አትራፊ ነጋዴ የክብር ዲግሪ አይሰጥም፤ ጉሮሮውን ለመሸፈን በየምሽት ክበቡ ሕዝበ አዳምን ለሚያስጨፍር አረሆና አዝማሪ የክብር ዲግሪ አይሰጥም … (ቴዲ አፍሮ ከነዚህ ስለሚለይ ሌሎች ተቋማት ባይሰጡት እንኳን እኔና ባለቤቴ ወ/ሮ ታንጉት ተማክረን የቤታችንን ሽልማት በአርት የክብር ማስተርስ ለመስጠት መወሰናችንን በዚህ አጋጣሚ ልግለጽ መሰለኝ)፡፡
ማድረግ ስለቻልን ብቻ ማድረግ የሌለብን ብዙ ነገር መኖሩን አንዘንጋ፡፡ ማድረግ መቻልን ከህግ፣ ከሞራል፣ ከባህልና ከመሰል ሰብኣዊና ኅሊናዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ተገቢ የአሠራር ሂደት ጋር ካላሰናሰልነው አምባገነንነትንና ወጥረገጥነትን ያስትላል፡፡ እንጂ ህግ ባይገዛን ኖሮማ ስንቱን ስንገድልና በስድብ ስንሞልች አንውልም ነበር? በጀመርነው የክብር ዲግሪ ሽልማት ረገድም እንዲሁ ነው፡፡ ለምሣሌ ኃይሌ ሮጦ ስለቀደመ ሣይሆን ሮጦ ባመጣው ገንዘብ ሀገርንና ሕዝብን በሚጠቅም የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ ቢያውል አንድ ቀርቶ ሠላሣ ዲግሪ ቢሰጠው ከመደሰት በቀር ምንም አንልም፡፡ የወያኔን ባንዲራ በማውለብለቡ ብቻ ግን ይሰጥ ከተባለ የዲግሪውን መቅለል ማወጅ ነው – በጥሩ ስኬት የሚታወቅ ሌላ ሰው እንዳይመኘውና እንዲያውም እንዲጠላውና አንዲጠየፈው እናደርጋለን፡፡ አላሙዲንም ሆነ ካረሎስ ስሊምና ቢልጌትስ የክብር ዲግሪ ሊያገኙ አስበውና ዐቅደው አይደለም ይህን ሁሉ ቢሊዮን ገንዘብ ያከማቹት፤ እንዲያውም ፍትሃዊነት በጎደለው የመጫወቻ ሜዳና በሸፋፋ ሚዛን፣ በድሆችም ላብ የሀብት ቆጥ ላይ በመውጣታቸው የክብር ሣይሆን የቅሌት ዲግሪ ነው ሊሰጣቸው የሚገባ – ለነዚህ መሰል ሀብታሞችና ደም መጣጭ ከበርቴዎች፡፡ የልባቸውን ካደረሱ በኋላ በጎ አድራት ቢከፍ ወይም ቢረዱ ምን ይሠራል? አታናግሩን እንጂ! “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…” የተባለው አሠራችንን አስቀድመን እንድናጤንና እንድንስተካከል ነው፡፡ ዘርፈን ዘርፈን ስናበቃ፣ ድሃን በድለን ስናበቃ፣ ሠራተኞቻችን አስፕሪን እንኳን ገዝተው ከራስ ምታታቸው እንዳይገላገሉ ሙልጭ አውጥተን ካደኸየናቸው በኋላ የምን በጎ አድራት ነው?
ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና የሚከተሉትን ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ጽሑፎች እንድታነቡ በመጋበዝ ልሰናበታችሁ፡፡ ወዳማርኛ ብተረጉማቸው ደስ ባለኝ፤ ግን ጊዜ አጣሁ፡፡ ጊዜ ያለው ሰው ተርጉሞ በድረገፆች የአስተያየት መስጫ ሥር ቢያሰፍርልኝ ቀን ሲክሰን ወሮታውን እከፍላለሁ፡፡ ቻው፡፡
Honorary degrees recognize those who have made profound and enduring contributions to scholarship, culture, and improved quality of life in society at large. Achievements of national or international significance deserve priority consideration. It is important that recipients be persons of great integrity, as the choices we make reflect our values as an institution.
In accordance with state statute, “No degree shall ever be conferred in consideration of the payment of money or the giving of property of whatsoever kind.” RCW 28B.20.130 (ibid)
Depending on the achievement, schools may present different types of honorary doctorate degrees. Some schools may offer only a Doctor of Philosophy degree, while others bestow a degree based on the accomplishment of the recipient. A few examples include:
Doctor of Humane Letters – acknowledging academic distinction
Doctor of Laws – awarded to professionals in the field of law
Doctor of Science – recognizing revolutionary scientific research and discovery
Doctor of Fine Arts – conferred primarily to musicians, actors, architects and artists
Doctor of Divinity – bestowed upon exceptional religious figures
By awarding honorary degrees, the University recognizes those individuals whose accomplishments are of such excellence that they provide inspiration and leadership to its graduates. As well, through its choice of honorary degree recipients, the University makes a public declaration of its values. In selecting candidates, the University should attempt to choose individuals of such a caliber that in honouring them, it too is honoured. The Honorary Degrees and Convocations Committee should attempt, through its recommendations of nominees, to reflect the cultural diversity of the country and the international character and diversity of the University itself. It should also attempt to honour those whose outstanding contributions to their fields or to society have not yet been widely recognized.
ታረቀኝ ሙጬ (tmuchie95@gmail.com)
በለው! says
—— ይህ የክብር ዶክትሬት ሳይሆን,,,”የዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዶክትሬት ተብሎ ይሰየም!”
ተሸላሚዎች የውጭ ዜጎች ሲሆኑ “የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ኒሻን መባል አለበት። ገና ፳፭ ቦታ የዩኒቨርስቲ ብሎኬት አቁመናል ተብሎ ካባ በተለያየ ቀለም እያዥጎረጎሩ መንጫጫት አፍ እንጂ ሥራ መክፈት አደለም ። አራት ነጥብ ።
**”የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ለአቶ አዲሱ ለገሰና ለሙዚቀኛዋ ማሪቱ ለገሰ የክብር ዶክትሬት ሠጥቷል፡፡ አክሱም ዩኒቨርሲቲም ለአቶ ስብሃት ነጋ የክብር ዶክትሬቱን ሲሰጥ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ፤ ለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ መስጠቱ ታውቋል፡፡”
*******
የክብር ዶክትሬት ሸፍጥ እና መንደሬነት
Posted on Monday, June 27, 2016 @ 7:20 pm by Nahusenay Belay
በርግጥ የሰው ልጅ ለሚያበረክተው የላቀ አስተዋፅኦ እዉቅናና ክብር መሰጠቱ ይበል እሚያስብል ነገር ነው። በተለይ እንደኛ ዓይነት ባለ ሃገሩንና ህዝቡን ለዘመናት ሲያገለግል የኖረን ዜጋ በቀላሉ አሽቀንጥሮ በሚጥል ማሕበረሰብ እዉቅና መስጠት መጀመሩ መበረታታት አለበት። ሆኖም በየዓመቱ የክብር እየተባለ እየተሰጠ ያለው የክብር ዶክትሬት ግን በብዙዎች ዘንድ እየተወገዘ ቢሆንም ኣሁንም ዩኒቪርሲቲዎቻችን በተለመደው መንገድ እየነጎዱ ነው።
ይሄ የክብር ዶክትሬት የሚባል ጉዳይ መቀለጃና ወዳጅ ማፍርያ እየሆነ ነው። የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው እጀግ የላቀ ሰብኣዊ ኣስተዋፅኦ ላደረገ ሰው ነው። አሁን እያያን ያለነው ግን እያንዳንዱ ዩኒቪርሲቲ የክልሉን ወይም ያካባቢዉን ተወላጅ የሚሸልምበት ኣሳፋሪ ድርጊት እየሆነ ነው። እያንዳንዱ ዩኒቪርሲቲ በየዓመቱ የኣንድ ወረዳ ህዝብ የሚሆን የሰው ብዛት የክብር ዶክትሬት ይሰጣል። Universal ፀጋዎች እና ክብሮች እንዲያስተምሩ የተቛቛሙት ዩኒቪርሲቲዎቻችን የመንደሬነት ማእክል፣ አመራሩም የመንደሬነት ባለሞያ፣ ድርጊቱም የወንዜነት ዶክትሬት መስጠት ሆኖ አረፈ። Universal ይቅርና የፌዴራል ተቛም መምሰል ኣቅትዋቸው የተራ መንደሬ ስራ መስራት ከጀመሩ ቆይተዋል። መንደሬነት ስብኣዊ ክብሮችን ስለማያቃቸው Universal መርሆዎችን አያከብራቸዉም።
ችግሩ የሚጀምረው ከኣመራር መረጣ ነው። ለምሳሌ መቐለ ወይም ባህርዳር ላይ የሚገኝ ዩኒቪርሲቲ የፈለገ ብቃት ያለው ሰው ቢሆን ያካባቢው ተወላጅ መሆን አለበት፤ ዩኒቪርሲቲ መሆኑ ይረሳና የክልሉ ፓርቲ መዋቅር ተቀጥያ በመሆን ያገለግላል፤ አስተማሪዎችም የተሻለ ታማኝ ለመሆን እንጂ የተሻለ ተመራማሪ ለመሆን የማይፈልጉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስንት ምርጥ ጭንቅላት በመንደሬ ኣመራርና በፓርቲ ጣልቃ ገብነት ይመክናል ወይም ይታፈናል። ይህ በሁሉም ዩኒቪርሲቲዎቻችን በተለያየ መጠን በስፋት ያለ ችግር ነው።እኔ እስከማዉቀው ድረስ ካዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ ዉጪ ሌሎች ዩኒቪሲቲዎች የሚመሩት ባካባቢው ሰው ነው፤ ባጭሩ ዩኒቪርሲቲዎቹ ዩኒቨርሳል ክብሮች ሳይሆኑ ባመራርም ባሰራርም መንደሬ ናቸው። አንደኛ በሽታቸው የፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነው፤ ለምሳሌ አስተማሪዎች ይህንን የጉልበት ጣልቃ ገብነት ባይፈልጉትም ምንም ማድረግ እንዳይችሉ ተደርገዋል። ቢናገሩ ምን እንደሚመጣ ከራሴው ዩኒቨርሲቲ በላይ ማሳያ የለም።
ዩኒቨርሲቲዎች ለስብኣዊ ክብር የላቀ ዋጋ የከፈሉና ዓይነተኛ ለዉጥ ያመጡ ሰዎችን እንጂ በግልባጩ የሰው ልጅን ነፃነት በሚነፍጉ ሂደቶች የተሳተፉ ግለ-ሰዎችን መሸለም ከጀመሩ የመጨረሻቸው መጀምርያ ነው። ይባስ ብሎ ምንም አንፃራዊ ነፃነት የሌላቸው ዩኒቪሲቲዎች ተሸላሚዎቹ ኣካላት ናቸው በእጅ አዙር ራሳቸዉን እየሸለሙ ያሉት። በመላው ዓለም ለምትመረቁ ተማሪዎች እንዃን ደስ ኣላቹህ እላለሁ። ዩኒቪርሲቲዎቻችንን ደግሞ ዩኒቪርሲቲ ምሰሉ፤ የምትሰሩትን እወቁ፣ በየዓመቱ አታሳፍሩን ማለት እወዳለሁ።