ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአፍሪካውያንን ህልውና እየተፈታተኑ ካሉ ጉልህ ችግሮች መካከል ኣሸባሪነት ዋና ጉዳይ ሆኗል። ISIL በሊቢያ፣ ኣልሸባብ በምስራቅ ኣፍሪካ፣ ቦኮሃራም በምእራብ ኣፍሪካ በከባድ ፍጥነት እያደጉ ነው። አፍሪካውያን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሽብር ስራዎች ላይ የተባበረ ክንዳቸውን ሊያነሱ የሚገባበት፣ ህዝቦች ግንዛቤያቸውን በማስፋትና የዚህን ኣሸባሪ መንፈስ ሊዋጉ የሚገባበት ሰዓት ላይ ነንና እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ ላይ በጽኑ መወያየት ያሻናል። በተለይ ወጣቱ በኣህጉራችን ስላለው የሽብር እንቅስቃሴ በሚገባ ሊረዳ ይገባዋል:: መምህራን አፍሪካ ውስጥ ስላጠላው የሽብር ጥላ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ኖሯቸው ተማሪዎቻቸውን ሊያስተምሩ ይገባል።
ወደ ዋናው ውይይታችን እናምራ። ስለ ሽብርተኞች ሲነሳ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ይኖራሉ። ለመሆኑ እነዚህ ኣሸባሪ ቡድኖች ምንድነው ወደ ጫካና ጭካኔ የሚመራቸው? ሽብርተኛነት እንዴት በፍጥነት በአህጉራችን ሊያድግ ቻለ? ኣሸባሪነት በተለይ በኣፍሪካ ክፍለ ዓለም ውስጥ ያለው ኣደጋና የስጋት ደረጃው ምን ያህል ነው?እውን ሳናውቀው ወይም በስህተት ለኣሸባሪነት መፈልፈል የፈጠርነው ምቹ ሁኔታ ኣለ ወይ? እንዴትስ ነው ይህንን ኣሁን በፍጥነት እያደገ ያለ ኣሸባሪነት የምንገታውና ኣፍሪካን ከኣሸባሪነት ነጻ የምናደርገው? የሚሉት ጥያቄዎች የኛ የዜጎች ሁሉ የመወያያ ኣጀንዳዎች መሆን ኣለባቸው። ዜጎች በኣሸባሪዎች ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ይዘው መንግስታቸው በኣሸባሪዎች ላይ ንቁ ካልሆነና መመከትና ማቆም ከተሳነው ውረድ ሊሉት ይገባል። የኣሸባሪዎች ጉዳይ ከሁሉ በላይ የሃገርና የህዝብ ጉዳይ ነውና። ይህ የኣሸባሪነት ጉዳይ ከፖለቲካ ልዮነቶች ሁሉ በላይ በመሆኑ ከፖለቲካ ኣመለካከቶቻችንና ከውስጥ ችግሮቻችን ከፍ ብለንና ከላይ ከኣህጉር ማማ ላይ ቆመን በጋራ ልንዋጋው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ከፍ ሲል ለመወያያ ማጠንጠኛ ይሆናሉ ያልኳቸውን ነጥቦች ወደ ሁዋላ ወደ ፊት እየተንሸራሸርን እንወያይባቸው። በኣጠቃላይ በዓለማችን ያሉ ቀንደኛ ኣሸባሪዎች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሲሆን አፍሪካ ውስጥ የተፈለፈሉትን እንደ ኣልሸባብና ቦኮሃራም ያሉትን የሽብር ቡድኖች ተፈጥሮና ፍላጎት እንዲሁም ስነ ልቦና ነጥለንእናንሳ። ለምሳሌ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም ናይጀሪያ ውስጥ የተፈጠረውን ቦኮ ሃራምን ስናይ ይዞት የተነሳውና ጫካ የሰደደውን ነገር በሚገባ መመረመር ጥሩ ነው። ይህ ቡዳን ከፋኝ ብሎ የሚለውና በእስልምና ሃይማኖት ሃራም (ውጉዝ) ያለው የምእራቡን ዓለም ትምህርት ነው። ቦኮ ሃራም ማለትም የምእራብን ትምህርት ውጉዝ ከመ አርዮስ እንደማለት ነው። ይህ ቡድን የተቋቋመው አንድ መሃመድ የሱፍ በተባለ የሽብር ስሜት በተጠናወተው ሰው ነው።
በርግጥ ድርጅቱን ከመሰረተ ከጥቂት አመታት በሁዋላ በናይጀሪያ የጸጥታ ሃይሎች ተገድሏል። ይሁን እንጂ መሃመድ የሱፍ የጠነሰሰው የምእራብን ትምህርት ውግዘት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ኣላማውን ተቀብለው በፍጥነት ኣድጎ ይታያል። በአሁኑ ሰዓት ቦኮ ሃራም ከኣሸባሪ ድርጅቶች ሁሉ በጀሃድ ርምጃው ብዙ ሰዎችን በመግደል የሚደርስበት ኣልተገኘም። ቦኮ ሃራም ናይጀሪያ ውስጥ ይጠንሰስ እንጂ በቅርብ ጊዜ። “ራእዩን” ሰፋ ኣድርጎ ምእራብ ኣፍሪካን የሚያካልል ISWA (Islamic State West Africa) የተባለ ስያሜን ለራሱ ሸልሟል። የእንቅስቃሴ ዞኑን ኣስፍቶ በቻድ፣ በካሜሩን፣ በኒጀርና በሌሎችም የምእራብ ኣፍሪካ ሃገራት እየተንቀሳቀሰ ነው። እ.አ.አ. በ2014 ሚያዝያ ወር ላይ 276 ሴት ተማሪዎችን ሰርቆ የጠፋባለም ያልታየ የሴቶች ሌባ ነው። ይህ ቡድን የሚያመጣው ትምህርትና እንቅስቃሴ ሁሉበተለይበተለይ ለአፍሪካ ሴቶች ትልቅ ስጋት ነው። የሚከተለው ዶክትሪን ከተለያዩ ጎጂ ልማዶችና ከጭቆና ለመላቀቅ ደፋ ቀና የሚሉትን የአፍሪካን ግማሽ ህዝብ ሴቶችን ወደ ባሰ ጭቆና ሊመልስ የተነሳ ኣደገኛ ቡድን ነው።
ስለዚህ ኣሸባሪ ቡድን ስናስብ ጠልቀን መመራመር መፈለጋችን አይቀርም።መቼምኣንድን ሰው ጫካ የሚከተው ከባድ በደል መኖር ኣለበት። የመረረው፣ ከፍተኛ ብሶት ያለበት ሰው ጫካ ይገባል። ይሸፍታል። ቦኮ ሃራምን ጫካ የከተተውና ያስከፋው የምእራብ ትምህርት ጉዳይ ነው ይላል። በርግጥ ይህ ጥያቄ ዋና ጥያቄው ነው ወይ? ብለንም መደመም ኣለብን:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የቦኮ ሃራም መስራች የነበረው መሃመድ የሱፍ የምእራቡን ኣለም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኣጣጥሞ ይጠቀም የነበረ ሰው ነበር። ዘመናዊ መኪና ይነዳ የነበረ፣ ዘመናዊ ላብታፕ የነበረው፣ የአለምን የምግብ ኣይነቶች እያማረጠ የሚበላጥሩ ጥሩ ጫማዎችን የሚያደርግ ሰው ነበር። ቴክኖሎጂውን ይደሰት የነበረ ሰው ነበር። የምእራቡን ኣለም የበረከት እጅ በዚህ በኩል ወዶታል ወይም በረከት ነው ብሎታል ማለት ነው። በርግጥ ቲሸርትና ጂንስ መልበስ ከልክሏል። ይህ እንግዲህ በራሱ ጫካ የሚከተ ነው ወይ ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ቦኮ ሃራም የምእራብ ትምህርት ከሚላቸው ውስጥ ኣምርሮ የጠላውከምእራብ የተነሳውን የዴሞክራሲ ባህል ነው። ምርጫን፣ የህዝቦች ልእልና ጉዳይን ሃራም ብሎታል። እነዚህ እሴቶች በርግጥ ከምእራብና ከአሜሪካ ኣካባቢ የተነሱና የዳበሩ ቢሆኑም ዛሬ ዘመን ግን በመላው ዓለም ተቀባይነት ያገኙ የዓለምእሴቶች ሆነዋል።
የሰው ልጆች የስልጣኔ ደረጃዎች በመሆናቸው አንዳንዶች ቀደም ብለው ሌሎች ዘግየት እያሉም ቢሆን ዓለሞች ወደነዚህ እሴቶች እየተዘረጉ ነው። ሃይማኖት ሳይለይ የዓለም ህዝብ ተካፍሏቸዋልና ቦኮ ሃራም ይህንን ባህል ሃራም ሲል ሃራም ያለው ምእራቡን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ህዝቦች እሴቶች ነው። ለዚህም ነው ሽብረተኝነት ኣለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ያደረገው። ከሁሉ በላይ ቦኮ ሃራምም ይሁን ኣልሸባብ ወይም ኣልቃይዳ ወይም ኣይሲስ ከዴሞክራሲ ባህል ጋር መጋጨታቸውና ይህንን ባህል ለመቀልበስ መሞከራቸው ከማንም በላይ ከምእራብም በላይ ጠላትነቱ ለራሳቸው ለአፍሪካ ሃገራት ነው። ለምሳሌ ቦኮ ሃራምን ብንወስድ ቦኮ ሃራም የምእራብን ትምህርት ሃራም ካለ በሁዋላ ሊያመጣ የፈለገው ዓለም የተለየ ነው። የትምህርት ካሪኩለሙ ምን ሊሆን እንደሚችል ባናውቅም ነገር ግን በሸሪያ ህግ የምትመራ እስላማዊት ሃገር ፈልጓል። ይህቺ ኣገር ደግሞ ከኣንድ መቶ ሃምሳ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ በህዝብ ብዛቷ ከኣፍሪካ ኣንደኛ የሆነች፣ከሃይማኖት ኣኳያ ሃምሳ በመቶ የሚሆነው ክርስቲያን በሆነበትና ኣርባ ሶስት በመቶ ገደማ ሙስሊም በሆነባት ኣገር ናይጀሪያ ነው። ቦኮ ሃራም ለኣፍሪካ ከማንም በላይ ኣደገኛ ነው የሚያሰኘን ይህንን የሸሪያ ህግ ተግባራዊ ሊያደርግ ያሰበው እንደናጀሪያ ባለ ክርስቲያን በሚበዛበት ኣገር፣ እንደ ካሜሩን ባለ ሰባ በመቶ የሚሆነው ህዝብክርስቲያን በሚሆንበት ኣገር ውስጥ መሆኑ ነው። ቦኮ ሃራም ይህንን ኣላማውን ተግባራዊ ለማድረግና እስላማዊ መንግስት ካሜሩንን ለመመስረት ሰባ በመቶ የሚሆነውን ሙስሊም ያልሆነውን ህዝብ ማረድ ሊኖርበት ነው ማለት ነው።
ናይጀሪያ ውስጥ ግማሽ በላይ የሚሆነውን ህዝብ በጅሃድ ሊጨርስ ነው ማለት ነው። ምእራብ ኣፍሪካን እስላማዊ ግዛት ለማድረግ ሚሊዮኖችን ሊያጠፋ ነው ማለት ነው። ይሄ ነው ኣንዱ የቦኮ ሃራም ትልቅ ኣሸባሪነት። ኣሸባሪነት ለዚያ ቀጠና ከሁሉ በላይ ኣስጊ የሚያደርገው የህዝቡ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ብዝሃነት ነው። በርግጥ እስላማዊ መንግስት እንመሰርታለን የሚሉ ኣሸባሪ ቡድኖች እንደ ሊቢያ ባሉ ህዝባቸው መቶ በመቶ ሙስሊም በሆነበትም መረጋጋትን አላመጡም። ይህ የሚያሳየው ኣይሲስ በዓለም ላይ የሙስሊሙ ጥያቄ ኣለመሆኑንና መርሆዎቹ የሙስሊሙን ሃይማኖት የጣሰ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ግን በፍጥነት ያድጋል። አልሸባብ በሁለት ሺህ ኣራት ኣካባቢ ሲመሰረት ከነበረው ኣቅም ዛሬ ጠንክሯል። በዚህ ቀጣናአሸባሪነትየቦኮ ሃራምን መንፈስ ተከትሎ በቅርቡ Jahba East Africa (የምስራቅ ኣፍሪካ ግንባር) የተሰኘ እስላማዊ ሚሊሺያ የተቋቋመ ሲሆን አሸባሪነት ኣፍሪካን በምእራብና በምስራቅ ለማመስ ተዘጋጅቷል።
እንደሚታወቀው ጽንፈኝነት በአፍረካ ቀንድ አካባቢ ረዥም ታሪክ አለው። አክራሪነት ለዚህ ቀጣና አዲስ አይደለም። በ15ኛው ክፍለ ዘመን አንድ አህመድ ግራኝ የተባለ ጽንፈኛ ተነስቶ ኣይ ኤስን (IS) በአፍሪካ ቀንድ ለመመስረት ሞክሯል። ጅቡቲን፣ ሶማሊያን፣ኢትዮጵያንና ኤርትራንና ጠቅልሎ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ብዙ ጥሯል። በዚህ ጊዜም በኢትዮጵያ ውስጥ ከትግራይ ጀምሮ ጎጃም፣ ጎንደር ወሎ ሸዋ ድረስ እጅግ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ኣቃጥሏል፣ እጅግ ብዙ ክርስቲያኖችን የመስቀሉ ተከታዮች እያለ ገድሏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም የግራኝ ኣህመድ አልጋዚአይ ኤስ እንቅስቃሴ መቼም የማይረሳ ግዙፍ ታሪክ ነው። ግራኝ አህመድ ኣስቦት የነበረው የእስልምና መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ሳይሳካ ቢቀርም ይህ መንፈስ ግን ኣልተመታም ነበርና ዛሬ ከመቶዎች አመታት በኋላ በተለያየ ስም ተከስቷል። ወጣቱ አህመድ ግራኝ የሚመስጣቸው አንዳንድ ወጣቶች የዚህን ሰው ህልም እውን ለማድረግ የወጣቶች ንቅናቄ ወይም አልሸባብ የሚል ድርጅት መስርተው ጅሃድ አውጀዋል።
ዘመናዊዎቹ የኣይ ኤስ ተከታዮች አፍሪካን ምን ሊያደርጓት ነው ካልን ኣንዱ ትልቁ ጉዳይ ኣፍሪካን ከምርጫ ስርአት ማውጣት ወይም ወደዚያ የምታደርገውን ግስጋሴ ማቆም ይፈልጋሉ። ኣፍሪካን ወደ እስላማዊ ግዛትነት የመቀየር ፍላጎት ኣላቸው። ይህ ሙከራ ኣደገኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዚህ የኣይ ኤስ መንፈስ ራሱ ከስልጣኔ ከሰው ልጆች ገስጋሽ ተፈጥሮ ጋር የተጋጨ ነው። አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት ከሚያስችሉዋት መሳሪያዎች ኣንዱና ትልቁ ጉዳይ ትምህርት ሲሆን በተለይ ከምእራቡ ኣለም የምታገኘው ተጨባጭ የሆኑ የማቴሪያል ባህሎችና ተጨባጭ ያልሆኑ የኣስተዳደር ባህሎች ወሳኝ ናቸው። በርግጥ ኣፍሪካ ራሷ ያሏት ግሩም ባህሎችም ካለችበት ዝቅተኛ የድህነት ወለል እንድትነሳ ኣቅም ይሰጡዋታል። ገስጋሽ እንድትሆን የተውጣጡ ጥበቦችን በተግባር እያዋለች ነው የምታድገው። ወደ ኣነሳነው ጉዳይ እንመለስና ቦኮ ሃራምና ኣልሸባብ የዴሞክራሲ ባህልን ሲዋጉ መጥፎ እና ሃራም ባህል ሲሉ የሚገርመው ግን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጥፎ ስራ በመጠቀም ለጅሃድ ተግባር ማዋል ጀምረዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በቅርቡ ኬንያ ውስጥ የተሞከረው የኣንትራክስ ስነ ህይወታዊ የሽብር ስራ ነው። ኬንያ ውስጥ የተያዘው ይህ የአንትራክስ ቫይረስን በመጠቀም ሊሰራ የነበረ ወንጀል ያጋለጠው ነገር ቢኖር ይህ ቡድን መልካም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየረገመ ነገር ግን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ደግሞ ለግድያ ስራ ይጠቀማል ማለት ነው። ሃራም መባል የነበረበት እንዲህ ኣይነት ባህልን ማዳበር ነበር። የዘመኑን የቴክኖሎጂ ውጤቶች የማህበራዊ ድረገጾችንም እንደዚሁ ወንጀል የሚሰሩባቸው በመሆኑ ይህ ቡድን በእስልምናም ሆነ በሰው ልጆች የሞራል መለኪያ በየትኛውም እምነት ሃራም ነው። ጅንስ መልበስን ሃራም እያለ በአንትራክስ ቫይረስ ጅሃድ መፈጸምን ቅዱስ ካደረገው ይህ ቡድን በርግጥ ሰይጣናዊ ነው።
ዝንባሌ ወደ ሚስብ ጥያቄ እንመለስ። ተመልከቱ ይህ ቡድን ከሙስሊሙ፣ ከስልጣኔ፣ ከክርስቲያኑ፣ ከዓለም ሁሉ የተጣላ ነው። ግን ደግሞ ኣፍሪካ ውስጥ ያድጋል። ኣንድ ጊዜ ብቅ ብሎ እልም እንደሚል ሽፍታ ኣይደለም። ለምን እንደዚህ ሆነ? ምን ምቹ ሀኔታ ኣግኝቶ ነው ሽብርተኝነት የሚያድገው የሚለው ጥያቄ በጣም መሳጭ ነው። አፍሪካ በተለይ ለሽብርተኞች ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን የፈጠረችበት ሁኔታ ኣለ። ከነዚህ ምቹ ሁኔታ መገለጫዎች መካከል አንዱ የማህበራዊ ፍትህ መጓደል፣ ሌላው ደግሞ ከፍተኛ ስራ ኣጥነትና ድህነት፣ ሌላው ደግሞ የአፍሪካ ሰኪዩሪቲ አቅም ውሱንነት፣ የትምህርት አለመዳበር፣ ምቹ መልክአምድራዊ ሁኔታዎች (ያልዳበረ ኢንፍራስትራክቸር) ተደማምረው ነው። ኣሸባሪን የሚረዱ ቡድኖች በተለያየ ገንዘብ ድሃውን ወጣት መያዝ የሚችሉባት ኣህጉር በመሆኑዋ ለኣሸባሪነት ማደግ ኣስተዋጾ ያደርጋል። መሄጃ ያጡና የመረራቸውን ወጣቶች በትንሽ ጥቅም ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ የኣፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ የሆነ የመብት ረገጣ ያለ በመሆኑ ግፍ የበዛበት ወጣት ኣለምን ጠልቶ የኣሸባሪነት መንፈስ ቢጠናወተው ብዙ ኣይገርምም። ሌላው ጉዳይ የትምህርት ማነስና የዋህነትም ይኖራል። ኣንዳንድ ለሃይማኖታቸው በጣም ቅንዓት ያላቸውን የዋህ ሙስሊሞች እየመለመሉ ኣሸባሪ ሊያደርጓቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ኣፍሪካ ውስጥ ይሰፋል። የመንግስታት ኣምባገነናዊ ባህርያት በራሳቸው በኣንድም በሌላም መንገድ ጽንፈኛ ዜጎችን ሊያፈራ ይችላል። በሌላ በኩል በኣፍሪካ ውስጥ በግልጽም ይሁን በህቡእ በማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ኣመለካከት ካለ ኣክራሪነት እንዲያድግ ያደርጋል። የቡድን ጭቆናዎች ኣክራሪዎች እንዲበዙ ስለሚያደርግ ይህ ሁኔታ ኣሸባሪነትን እንዲያድግ ያደርገዋል።
ስለ ኣሸባሪዎች ስናስብትልቁ ስጋት ያላቸው ዓላማብቻ አይደለም። ወደዚያ ህልም ኣይደርሱም። ነገር ግን ወደ ህልማቸው የሚወስደው ስትራተጂ ነው ለኣፍሪካ በጣምኣደገኛው ነገር። ለማይደርሱበት ህልም የሚሄዱበት ጎዳና ብዙ ችግሮችን ያመጣል። ወደ ኣላማቸው የሚወስደው የትግል ስትራተጂ ደግሞ ጅሃድ በተለይም ኣጥፍቶ መጥፋት ነው። በብሄር ላይ ወይም በፖለቲካ ርእዮት ላይ የሚደረግ ልዩነት የቱንም ያህል ቢከር ኣጥፍቶ ጠፊነት ኣይኖረውም። ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ግን ይህን ስትራተጂ ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰኑ የዋህ ሰዎችን ያስገኛቸዋል። ከሞት ወዲያ ለሚኖር ኣዲስ ህይወት እንዲቋምጡ በማድረግ፣ በጅሃድ ስራቸው ከአምላክ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው በማሳመን የዋሆች በኣጥፍቶ ጥፋት ስራ ላይ እንዲሰማሩ ያደርጋል። ታዲያ ከሙስሊሙ አካባቢ እንዲህ አይነት አንዳንድ አሸባሪዎች ቢነሱም አብዛኛው የሙስሊሙ ማህበረሰብ በየትም አለም ዴሞክራሲን ፈልጓል። እነሆ ዛሬ የአረብ ሃገራትም በዴሞክራሲ ትግል ላይ ይገኛሉ።
በቅርብ አምታት የተነሳውን የአረብ ስፕሪንግ በሚመለከት አስተያየቶች ይሰጣሉ። አንዳንዶች የአረብ ስፕሪንግ ውጤታማ ኣልሆነም ይላሉ። ነገር ግን ኣይደለም። ትግል እኮ ነው የተያዘው። ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት በኣንድ ሰሞን ተቃውሞ መንግስትን በመጣል የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት ይከብዳል። የኣረብ ኣገራት ከነበሩበት ኣስተዳደር ዘየ ወጥተው ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት የሚጠይቋቸው ዋጋዎች ይኖራሉ። መውደቅ መነሳት ይኖራል። የሚያስደስተው ነገር ግን የአረብ ህዝቦች ልባቸው በዴሞክራሲ ኣሳቦች ተማርኳል። አረብ ላይ የተነሳው የለውጥ ባቡር ይዘገይ ይሆናል እንጂ ወደ ሁዋላ አይመለስም። በርግጥ ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ለመግባት የህዝቦች ትግል እንዳለ ሆኖ የዴሞክራሲውን ስርዓት የሚመሩ የበሰሉ ፓርቲዎችና ለዴሞክራሲ ምቹ የሆነ ሲስተም ይሻሉ። ለምሳሌ ግብጽ ውስጥ የነበረውን የህዝቡን የዴሞክራሲ ትግል ስናይ ኣስደናቂ ነበር። ህዝቡ ለውጥና ዴሞክራሲ ፈልጓል። በመሆኑም ታገለና ሙባረክን ከጣለ በሁዋላ ስልጣን ላይ የወጣው መንግስት ግን በሃይማኖት ማንነት ላይ የቆመ የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ነበር። ይህ ድርጅት ጽንፈኛ ባይባልም ነገር ግን ጥርት ያለ ዴሞክራቲክ ድርጅት ኣይደለም። ከማህበራዊ የኢኮኖሚ ተቋምነት ወደ ፖለቲካ የመጣ በመሆኑ ከፓለቲካ ስራው በመረዳጃ ሥራው የተሻለ መስራት የሚችል ነበር።
ይህ ድርጅት ዴሞክራት የሆነ በመርህ ላይ የቆመ ባለመሆኑ ሃገሪቱን ቶሎ ብሎ ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ኣልቻለም። ግብጽ በዚህ በአረብ ስፕሪንግ ንቅናቄ ሰአት ያጣችው ዴሞክራሲን ሊቀበል የሚችል ሲስተም ነበር። ግብጽአዲስ ዴሞክራሲ የሚባል ስርዓት መቀበል ስትሻ አዲስ አቁማዳ ያስፈልጋት ነበር።አዲሱንየወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ አያስቀምጡምና። ስለዚህ ለዴሞክራሲ ታገለች ግን ፓለቲካዋና ስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ ገና ከማንነት ፓለቲካ አልተላቀቀም ነበር። የግብጽን ዴሞክራሲ ሊያራምድ የሚችል ሲስተም መጀመሪያ ያስፈልጋል። አለዚያ ከፈረሱ ጋሪው ይቀድምና ቁጭ ይላል። ኣሁንም ግብጽ ገና ዳዴ እያለች ነው። ሌሎች የኣረብ ስፕሪንግ ያናወጣቸው ኣገሮችም ብዙ ስኬታማ ባይሆኑም ግን ርምጃ ጀምረዋል። ትግላቸው ቀጥሎም ብዙ ኣመት ሳይወስዱ ወደ ዴሞክራሲ ባህል ይገባሉ። እንደነ አልሸባብ ያሉና ቦኮሃራም ያሉ ኣሸባሪዎች የሚታገሉት ኣንድ ጉዳይ ይህን የኣረብ ስፕሪንግ ነውና ኣደገኝነታቸው ለተባበረችው ኣሜሪካ ወይም ለምእራብ ኣገሮች ብቻ ሳይሆን በዋናነት የሙስሊሙ ማህበረሰብና የኣፍሪካ ስጋቶች ናቸው።
የራሳችንን ቀጣና ጉዳይ ስናይ እ.አ.አ. በ 2004 ዓ.ም ኣልሸባብ ከተመሰረት በሁዋላ ከበባድ ወንጀሎችን ፈጽሟል ኣሁንም ለቀጣናው ስጋትነቱ ቀጥሏል። የኣልሸባብ ኣንዱ ትልቅ ህልም ወጣቱን ወይም ኣዲሱን ትውልድ መያዝ ነው። በተለይ ሶማሊያ መንግስት ኣልባ ሆና በመቆየቷ ተስፋ የቆረጠውንና ስደት ያልተሳካለትን ወጣት እየመለመለ የተጠናከር ድርጅት ነው። ከኣልቃይዳ፣ ኣይሲስና ቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው ይህ የቀጠናችን ኣሸባሪ በወጣቶች ላይ የሚሰራውን የምልመላ ስራ ለማስቆም የዚህ ቀጣና ወጣቶች የተደራጀ ስራ ሊሰሩ ይገባል። የምስራቅና ምእራብ አፍሪካ ወጣቶች አልሸባብ ሃራም፣ ቦኮሃራም ሃራም፣ አልቃይዳ ሃራም፣አይሲስ ሃራም የሚል ድርጅት መስርተው አሳቡን በአሳብ ሊዋጉት ይገባል። ይህ ነው አንዱ የጸረ ሽብር ትግል ታክቲክ። አክራሪነት የአንድ ወቅት የሚሊተሪ ትግል ብቻ አይደለም። ሁልጊዜም አሳብና .መንፈሱን መዋጋት ያስፈልጋል። የስልጣኔ የዴሞክራሲ የሴቶች መብትና ነጻነትን የሚታገል አሳብ ለመዋጋት ረዘም ያለ ጊዜን ይወስዳል። አሸባሪነት እንደሌላው ሽፍትነት ቦግ ብሎ ቶሎ የማይጠፋበት ምክንያት ሃይማኖታዊ ካባ ስለለበሰ ነው። ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማትም ትልቅ የጸረ አክራሪነት ትምህርት መስጠት አለባቸው። ስለዚህ አጠቃላይ ትግሉ ሁለት አቅጣጫ ያለው ሲሆን አንዱ የታጠቀን አሸባሪ ቡድን የተባበረ የሚሊተሪ አክሽን ሌላው ደግሞ የህዝባዊ ኢንተለጀንስ ስራና የጸረ ጽንፈኛነት ትምህርቶች ናቸው።
አልሽባብ በምስራቅ አፍሪካ የሚያልመው የእስልምና መንግስት ህልም መቼም ባይሳካም ነገር ግን ብዙ ወንጀል እየፈጸመ ኣገር ሊበጠብጥ መቻሉ ጥያቄ የለውም። ሶማሊያም ሆነች ሌሎች የቀጣናው ኣገራት ለኣልሸባብ የሚመቹ ሁኔታዎችን መቀነስ ኣለባቸው። በዌስት ጌት ሾፒንግ ሞል ውስጥ በመስከረም 2013 እ. አ. አ. ኣልሸባብ ባደረሰው ጥቃት ወደ ስልሳ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል እጅግ ብዙ ቆስለዋል። በሚያዝያ 2015 እ.አ.አ. በጋሪሳ ዮኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ወደ ኣንድ መቶ ኣርባ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ቆስለዋል። ከሁለት አመታት በፊት ጂቡቲ ውስጥ በኣንድ ምግብ ቤት ውስጥ ይህ ኣሸባሪ ቡድን ጥቃት ፈጽሟል። ኣልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሁል ጊዜም ማሰቡ ኣይቀሬ ነው። በአጠቃላይ የቀንዱ ሃገራት ለዚህ ኣሸባሪ ቡድን ሁልጊዜም ተጋላጭ ናቸው። አልሸባብ እየተጠናከረ የዔደን ባህረ ሰላጤና የቀይ ባህር ሰላም ሊያገኙ ኣይችሉም። የዓለም ህዝቦች ያለ ኣሳብ በዚህ ቀጣና ሊዘዋወሩ የሚችሉት የዚህ ቀጣና ስጋቶች ሲጠፉ ነውና እንደ ኣልሸባብ ኣይነቱን ኣሸባሪ ለመምታት ትልቅ ኣለማቀፋዊ ድጋፍ ኣለ።
ስለ ኣሸባሪዎች ማውራቱ ብቻ ሳይሆን መፍትሄዎች ኣምጡ ተብሎ መጠየቅም ይኖራል። የኣፍሪካ ሃገራት መንግስታት ይህን የኣሸባሪነት መንፈስና ስሜት ምን ያህል መምታትና ማንበርከክ ችለዋል የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው ጥረቱ ቢታይም ነገር ግን ስትራተጂዎቹ በሚገባ መጠናት ኣለባቸው። ኣንደኛ ኣፍሪካ መረዳት ያለባት ነገር ኣሸባሪነትን ብቻዋን ተዋግታ የምትጨርሰው ባለ መሆኑ ከተባበሩት መንግስታትጋርና ከተባበረችው ኣሜሪካ ጋር ጠንካራ ህብረት መፍጠር ኣስፈላጊ ነው። እነዚህ ሁለት ኣካላት በተለይ በኣሸባሪነት ላይ ያላቸው አቋም ጠንካራ በመሆኑና አቅሙም ስላላቸው በጋራ መስራት ኣፍሪካውያን ለሚያደርጉትየጸረ ሽብር ዘመቻ ይረዳቸዋል። ይህ ትብብር በሚሊተሪ አክሽን ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ግንዛቤንም እንደ አንድ ጸረ ሽብር ኦፐሬሽን የያዘ ቢሆን መልካም ነው። የትብብሩ አንድ መሰረት ኣሸባሪነት በባህርይው ኣለማቀፋዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ነው። እንደነ ቻድና ኒጀር ሶማሊያ ያሉ በኢኮኖሚ የደከሙ ኣገራት እነ ቦኮ ሃራምንና አልሸባብን በራሳቸው ተዋግተው ኣይጨርሱትም። ያላቸው የሰኪዩሪቲ ኣቅም ውሱንነት ጸጥታን ለማስከበር ያስቸግራቸዋል ወይም እጅግ ብዙ ዋጋ ያስከፍላቸዋልና ይህንን ሃይል ለመዋጋት ጥምረት ወሳኝ ነው።
ኣፍሪካውያን ጥምረት ሲመሰርቱ ይህን የኣሸባሪነትን ችግር ከላይ ከኣህጉር ችግር ኣንጻር ኣይተው ክብደት ሊሰጡት ይገባል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ኣሸባሪነት የሚለውን ስያሜ መጫወቻ ሊያደርጉት ኣይገባም። በኣለም ኣቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ኣሸባሪዎችን እንዋጋ በጋራ እንታገል ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎቹን ከነዚህ ቡድኖች ጋር እንዲመዘገቡለትና ኣብረው እንዲመቱለት ማስላቱ በጣም ርካሽነት ነው። ስሌቱ ራሱ የሽብርተኝነትን ብያኔ ያወርዳል። በመሆኑም ክብደት ያለው የጸረ ሽብር ኣካል ተቋቁሞ በጋራ ክንድ አሸባሪነትን መዋጋት ያስፈልጋል። እነ ግንቦት ሰባትና ኦነግ ጋዜጠኞች ከነኣልሸባብ ጋር ካልተመዘገቡልኝ ኣልሸባብን ኣልዋጋም ካለ በርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት የዚህ ኣሸባሪ መንፈስ ኣልገባውም ማለት ነው ወይም ከልቡ የኣሸባሪዎች ተዋጊ ኣይደለም ማለት ነው። ሌላው ጉልህ ጉዳይ ደግሞ ኣሸባሪነት በቀጥታ በጦርነት ብቻ ሊጠፋ የማይችል ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ነው። ኣሸባሪነት መሪዎች ሲመቱ ቢጠፋ ኦሳማ ቢላደን ሲሞት ኣልቃይዳ ደብዛው በጠፋ ነበር። ስለዚህ ኣፍሪካውያን ያለብን ውጊያ የሚሊተሪ ኦፐሬሽን ብቻ ኣይደለም። በርግጥ የሚሊተሪ ኣክሽኖች በስፋት ካልተካሄዱ ይህ ኣሸባሪ ቡድን ኣይመታም።
ይሁን እንጂ ኣሸባሪነትን እስከ ሃቹ ለመምታት ኣፍሪካ ልታደርግ የሚገባት ትልቁ ውጊያ ኣሳብን መዋጋት መሆኑን ተረድታ ይህንን ተግባራዊ ስታደርግ ነው። ኣሸባሪነት ኣሳብ ነው። ኣሳብ የሚመታው ደግሞ በኣሳብ ነውና የኣሸባሪዎችን ትምህርት በማጋለጥና ኣሳቡን በተለይም ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በማስረዳት የዋህ ደጋፊዎችን ማዳን ኣሸባሪነት መቆሚያ መሰረት እንዳይኖረው ያደርጋል። የሪጅን ትብብር ያስፈልጋል። ኬንያና ሶማሊያ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ከዓለም ኣቀፉ ማህበረሰብ ጋር መስራት ኣለባቸው። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ኣሸባሪ ቡድኖች እንዲመቻቸው የሚያደገውን ከባቢ መስበር ነው። ከዚህ ውስጥ ኣንዱ የማንነት ፖለቲካ ድባብን መስበር ነው። ኢትዮጵያ በብሄር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዋ በኣንድም በሌላም መንገድ ሰው በቡድናዊ ማንነቱ ላይ የፖለቲካ ቤት እንዲሰራ የሚያበረታታ በመሆኑና ለጽንፈኝነት ቦታ ያለው በመሆኑ ቶሎ መውጣት ኣለባት። ኬንያ ምንም እንኳን በብሄር ላይ የቆመ ፖለቲካ ቢከለከልምና በብሄር ላይ መደራጀት በህግ የሚያሰቀጣ ወንጀል ቢሆንም ነገር ግን የቡድነኝነት ስሜት በህቡእ ያለ በመሆኑ ቡድኖች ከዚህ ስሜት መውጣት ይጠበቅባቸዋል። የሶማሊያ ሁኔታም በጣም ተሻሽሎ ሰኪዩላር መንግስት መመስረትና በመርህና ዴሞክራሲ ላይ መመስረት በዚህ ቀጣና ኣሸባሪነት እንዳይቀጥል ያደርጋል።
ማህበራዊ ፍትህን ማሻሻል ተስፋ ቆርጦ ወደ ኣልሸባብ የሚጎርፈውን ወጣት ያነጥፋል። በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ መስራት ወጣቱን ለስደትና ለኣሸባሪነት እንዳይጋለጥ ያደርገዋል። የማህበራዊ ፍትህ መጓደል፣ የመብት መታፈን፣ የደሞክራሲ እጦትና ድህነት በቀጥታ ለኣሸባሪነት ጥሩ ከባቢዎች በመሆናቸው ኣሸባሪነት ከዚህ ቀጣና እስከ ሃቹ ይመታ ዘንድ የኣፍሪካ ሃገራት ኣልሸባብንና ቦኮሃራምን ወይም ኣልቃይዳን በሚሊተሪ ኣክሽን ለመምታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የሃሳብ ውጊያያስፈልጋል። የጽንፈኝነትን ስሜት ለጊዜው በጠመንጃ እየመከትን ብንቆይም እስከ ሃቹ ጽንፈኝነትን የሚያጠፋልን ግን የዴሞክራሲን ባህል ስናዳብር ነው። ይህ ባህል በራሱ ጽንፈኝነትን ኣስወግዶ ከኣሸባሪነት ነጻ ያደርገናል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወንዶችና ሴቶች ወጣቶች መወያየት ግንዛቤ መያዝ ኣንዱ የትግል ስልት ነው። ጠንካራ ኣህጉራዊ ጸረ ኣሸባሪነት ትብብር ማድረግ ኣፍሪካውያን ይጠበቅብናል። ወጣቱ ትውልድ የኣሸባሪዎች ትምህርት ሃራም መሆኑን በሚገባ ሊረዱት ይገባል። ኣልሸባብ፣ ኣልቃይዳ፣ ኣይሲስና ሌሎችም ተመሳሳይ ድርጅቶች የያዙት ኣስተምህሮ በሙስሊሙ፣ በክርስቲያኑ፣ በቡድሂስቱ፣ በሰው ልጆች የሞራል መለኪያ፣ በኣለም ኣቀፍ የሰባዊ መብት መስፈርቶች ሁሉ ሃራም ነውና።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply