እንደ ዶክተር ጌታቸው በጋሻው አባባል ጤንነታቸው ከታወኩት ውስጥ ልደባለቅ እንጂ ከምዬ ኢትዮጵያ አንፃር ዛሬም ወያኔና ሻቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። እብድ ልባል እንጂ ሁለቱም የኢትዮጵያ ሕዝብና ሀገር ላይ የተጫወቱና እየተጫወቱ ያሉ ናቸው። ወያኔን ቤተመንግስት ደጃፍ ድረስ ሸኝቶ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ የሰጠን ሻቢያ ገና “77 ዓመት ይቀረዋል”። ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት ከቶም እንዳያንሰራራ የሻቢያን የቤት ሥራ እያከናወነ ያለው ወያኔ ቢንገዳገድ ቀሪውን የሚቀጥል እየተዘጋጀልንና እየተደገሰልን ነው። አዎ ሻቢያን በኤርትራ፣ ወያኔን በኢትዮጵያ ለሥልጣን ያበቃቸው ከጋለባቸው ጋር እየተጋለቡ፣ ዛሬ ያሉትን ነገ እየካዱ፣ ትላንት የጣሉትን ዛሬ እያነሱ፣ ዛሬ ያቀፉትን ነገ እያረዱ፣ ሀገር ኢትዮጵያን እንዳሻቸው ሊጋልቡ፤ ሊታመን ከሚገባው በላይና ያለ ይሉኝታ እየተገለባበጡ ሀገርና ሕዝብ እያሳረሩ ይገኛሉ።
ድሮ ዕድሜ ደጉ ይባል ነበር ዛሬ ግና ዕድሜ ዘልዛላው በጉድ ተናጋሪዎች ጉድ ያሳየናል፣ ጉድ ያሰማናል። ዛሬ የኢትዮጵያዊነት ባህል መበረዝ ብቻ አይደለም፣ ጠፍቶ፣ ከሀገር ይልቅ እራስ ወዳድነት ተንሰራፍቶ፣ ነገ ሀገሬ ብሎ ሚጮህላት ትውልድ ይደነዝዝ ዘንድ የተሸረበው ሴራ፣ ለኃያላን ዘራፊዎች አልጋ በአልጋ የሆነችው ሀገራችን ልጆቿ በመላው ዓለም ከመበተን አልፈው እየታረዱ ይገኛሉ። ለወያኔና ሻቢያ ሀገር ማለት ተረት ተረት ናት። ልማት ማለት የሕዝብ ስቃይ ነው። አባይ ሊገነባ የሠፈሩን ቧንቧ ውሃ ሁሉ የወሰደው ይመስል ዛሬ የውኃ ጀሪካን ይዞ ሚንከራተተውን ቤቱ ይቁጠረው። መብራቶች ሁሉ ጭለማን እያስተናገዱ በሚገኝባት ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ያለች እየተባለ ይቀለድብናል፤ ይሾፍብናል።
መብትና ነፃነት በትንሹ ለአርባ ዓመት የናፈቀው ሕዝባችንን ዛሬም አደባባይ አውጥተው ይቀጠቅጡታል። እኛ ካልንህ ሌላ እንዳትናገር፣ እንዳትሰማ፣ እንዳታይ ብለው አንድ ለአምስት ጠፍረውታል። ጊዜ የሰጠው ወያኔ ሀገር እየሰባበረ ይገኛል። ትውልድ እያኮላሸ ይነጉዳል። በአሸባሪነት ስም ሀገርና ሕዝብ እያሸበረ ይገኛል። የወያኔ የጀርባ አጥንት የሆነው ሻቢያ በተመሳሳይ መልኩ የኤርትራን ልጆች በመሰሪ ጅራፉ እየገረፈ ይገኛል። ስደትና እስር ቤት የመገንጠል ውጤታቸው ሆኗል። ሁለት አምባገነኖች አሥመራና አዲስ አበባ መሽገው በጋራ ሕዝብ ያምሳሉ፣ ከእኛ ሌላ ብለው ይኸው 24 ዓመት ሀገርን እረግጠው ይገኛሉ። “ምርጫ” እያለ የሚያላግጥብን ወያኔና በብቸኛ አምባገነንነት የቀጠለው የኢሳያስ መንግስት የመቶ ዓመት ታሪክ ብለው የሚያላግጡባትን ሀገራችንን ለመበታተን የጋራ አጀንዳ ይዘው እየተጓዙ በአለበት በአሁኑ ወቅት አወቅን ተማርን ባዮች እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ቀጣይ አደንቋሪ ለመሆን ሲዘጋጁ ያሳዝናል፤ ያሳፍራል።
ለሀገርና ለህዝብ መታገል ማለት ጨዋታ አይደለም። መብትና ነፃነት በበርካታ መስዋዕትነት የሚገኝ፣ በቆራጦች ደምና ሕይወት ሕዝቦች ነፃ የሚወጡበት ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የኖረችው በአድዋና በማይጨው በመቶ ሺዎች ክቡር ሕይወታቸውን ለሰንደቅ ዓላማቸውና ለሀገራቸው በአበረከቱት ነው። የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ የተመከተው በብርቅዬ አርበኞቿና ጀግና ልጆቿ ያላሳለሰ ጥረትና ተጋድሎ ነው። ዛሬ እኛ ሀገሬ የምንላት ኢትዮጵያ እነሱ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። ሰው ሊኖር ሰው ሞቷል። ሀገር እንድትኖር የጀግና ሕይወት ታቅፋለች። ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በርካታዎች አሸልበዋል። አይሳካለት አይስመርለት እንጂ ሀገሬና ሕዝቤ ያለ ያ ትውልድ ለዴሞክራሲ መብትና ለሕዝብ መንግስት ሊከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በሀገሩ ምድር ከፍሎ አልፏል። ይህ ነው እንግዲህ ከሞላ ጎደል ከብዙው በጥቂቱ የሀገራችን የነፃነትና የመብት ትግል። ከዚህ የተማርነው በስደት ጎራ ተወሽቆ ማሾፍን፣ ሐምበርገር እየገመጡ መስዋዕትነትን መስበክ አልነበረም። ሀገሬን ያለው ሀገሩ ነው የታገለው።
“የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” እንዲሉ የዛሬው ታጋይ ነኝ ባይና ፖለቲከኛና ምሁር እንደ መንግስት በሀገር ዱለታውና በአትናገሩኝ ባይነት ንቀቱ “አይ! አንቺ ሀገር ገና ስንቱ ይጠብቅሻል” ያሰኛል። “አይ! አንተ ሕዝብ ገና መከራህን ሊያራዝመው ስንቱ አሰፍስፏል” ያሰኛል። ዕድሜአቸው እየገፋ የቤተ መንግስቱ ደጃፍ ምኞት ብቻ የሆነባቸው ሌላው ቢቀር የትግሉ ባለቤት በመሆን መታየትን ከፈለጉ ሰንበትበት ብለዋል። ስንቱን አሉት፣ ስንቱን ቀባጠሩት፣ ስንቱን እረገጡት፣ አማራጩ ይህ ብቻ ነው እያሉ ከድጡ ወደ ድጡ ሲዘፍቁ “ይበላቸው” ተብሎ መተዉ ትግሉን እየጎዳ ነው። የሥልጣን ምኞታቸው ማንነታቸውን እየቀያየረ ምንም ከማድረግ እንደማይመለሱ እያሳዩን እየነገሩን ነው። እፍረትና ይሉኝታ እርቀዋቸዋል።
በትንሹ ከሰባት ዓመት በፊት AFD ብለው በሻቢያ አቀነባባሪነት በኢትዮጵያ ላይ የዶለቱትን ነው ዛሬ “የአቶ ኢሳያስን መግለጫ ሰምቶ ያልተደሰተ ጤንነቱ ያጠያይቃል” የምንባለው። አዎ! አቶ ኢሳያስን አቅፎ በሀገር ላይ ከመዶለት ዕብደት ከሆነ በጽናት ቆሞ ሻቢያንም ወያኔንም በጋራ በመታገል አብዶ መሞት ይመረጣል። ከጊዜ ጋር እራስን በመገለባበጥ የተመኟት የሥልጣን በር ስትጠብ ገደል መግባት አማራጭ አይደለም። የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የአረቡ አብዮት ሲቀጣጠል ቤተመንግስት በር ወለል ብሎ የታያቸው ጊዜው የወጣት ነው ብለው “በቃ!” ብለው ያዜሙትና ሊነግዱበት የተዘጋጁትን ወጣት ዛሬ ወደ ዳር ገፍተው ከሻቢያ ጋር ከበሮ ሲደልቁ ያላሳፈረ ምን ያሳፍራል? የጥፋት አማራጭ፤ አማራጭ ሊሆን ከቶም አይችልም። መብት ለአንድ ብሔር ብቻ በመስጠት ያቆም ይመስል ለኦነግ በሪፈረንደም ስም እስከ መገንጠል መብት ይሰጠው ብለው በግንቦት 7ና ኦነግ መሃል የተሰኩ ምሁር ዛሬ ደግሞ ግንቦት 7ና ኢሳያስ መሃል ሲወተፉ ማየት ለህሊና ያላሳፈረ ምን ያሳፍራል? “ፍቅር ሳይሆን ሥልጣን ዕውር ነው” ያሰኛል። “የትም ፍጪው ሥልጣኑን አምጪው” ይሉታል ይህ ነው። ዕድሜ ይስጠን እንጂ ገና የትላንቱ ፋሺስት መንግሥቱ ኃ/ማርያምና ግንቦት 7 መሀል እንደሚወተፉ ሽታውም ያለ ይመስለኛል።
“አማራጩ የለንም” ይባላል። ትግል መጀመሪያ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ከየካቲት 66 ሕዝባዊ አብዮት እንደፈነዳ ሀገሬና ሕዝቤ ብለው ከተለያየ ዓለማት ሥራቸውንና ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው የገቡት ወገኖች ምቾታቸውንና ድሎታቸውን ለሀገርና ለህዝብ በመስጠት ያስተማሩ የትግል ዋልታዎች ነበሩ። ትግል ያለው ሀገር ቤት ነው። በሰላማዊ በሉት በትጥቅ የትግሉ ሜዳ ሀገር ቤት ከወገን ጋር ነው። ይህ ባለመሆኑ ነው በትንሹ ለአለፉት 24 ዓመታት ለወያኔና ለሻቢያ የተመቻቸነው። ወያኔ ሀገርን እንደፈለገ እንዲጋልብ እርቀን ተመችተነዋል። “አላዋቂ ሳሚ..” እንደሚባለው እርቀውም ትግሉን ሲያንቦራጭቁ፣ ትግሉን ሲያሽመደምዱ ይታያሉ። የትግላቸው ውጤት ጥፋት ቢሆንም የወያኔ ደደቢት እኮ ሱዳን አይደለም፣ ትግሉ ለፍሬ ባይበቃም የኢሕአፓው አሲምባ እኮ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ነው። እናማ ትግል ያለ እዚያው ሀገር ቤት ምሽጉን በመፍጠር ነው። የነፃነት ታጋይ ምሽጉና ከለላው የሀገሩ ሕዝብ ነውና። የመብት ታጋይ የሕዝቡን ስቃይ፣ የሕዝቡን ጥሬ እየቆረጠመ፣ የምንጭና የወንዝ ውኃውን እየጠጣ የዕለት ተለት እንግልቱ እራሱ የትግሉ አካል ነው። ትግል ይህ ነው። “ትግል ድሮ ቀረ” እንዲሉ ሐምበርገር እየገመጡ ወጣቱ ምነው ፈዘዘ፣ ሞራል የለውም እያሉ ውጭ ሆኖ ማላገጥ ለእንደኛ ዓይነቱ በአሁኑ ጊዜ የሞራል ብቃት የለንም። ውጭ ተቀምጠን በሌላው ላይ መፍረድ የለብንም። ያውም የትግል ተመክሯቸውን ለማስተማር ሳይሆን ሀገርና ሕዝብን ከበተነ ሻቢያ ለመተቃቀፍ፣ እንገንጠል ባዮችን በርቱ እንበላቸው ዲስኩር ህሊናን ሸጦ እየሰበኩ አልነበረም። እኛ የድርሻችንን ተወጥተናል ታግለንና መከራ ከፍለን ሞክረናል አሁን ሀገርን የልጆቿ የማድረግ ድርሻው የአሁኑ ትውልድ ነው ካልንም ምናለ በሀገሩ መሬት በሀገሩ ላይ እራሱ በራሱ ትግሉን ያካሂድ ይመራ ዘንድ ብንተውለት። ኸረ ስንቱን እረገጡት! ኸረ ስንቱን አሉት!
ሰሞኑን ጐልቶ ቢወጣም የግንቦት 7ና የሻቢያ ትቅቅፍ በትንሹ ከAFD ምሥረታ ጀምሮ ይወስደናል። ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመበታተን ወያኔና ሻቢያ ሥልጣን ከጨበጡ ጀምሮ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ኤርትራ የመገንጠል መብቷ ተረጋግጧል። የኤርትራ ጉዳይ ዛሬ 24 ዓመት ያስቆጠረ አዲስ ትውልድ ኤርትራንና ኢትዮጵያን በሁለት ሀገርነት እያወቀ ያደገበትን ጉዳይ ለማየትና የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊት ግንኙነት ምን መሆን አለበት? የሚለው እራሱን የቻለ ጥናትን የሚጠይቅ ቢሆንም በመንግስት ደረጃ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሻቢያ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ቆሞም አያውቅ። ሀገራችን ኢትዮጵያን እንደበደለኛ በመቁጠር፣ ኢትዮጵያ ቅኝ አርጋናለች ብሎ ግንጠላውን በመሳሪያው ያስከበረው ሻቢያ ዛሬም እያደራጀና እየተንከባከበ ያለው “ቅኝ ከያዘችን አቢሲኒያ ነፃ መውጣት አለብን” የሚሉትን ኦነግና ኦብነግ ዓይነት የአንድነት ጠንቆችን መሆኑን እያየን “ሻቢያን አማራጭ ማድረግ አለብን” የሚሉ ሰባኪዎች ለስልጣን ጥማታቸውና ፍላጎታቸው ምንም ከማድረግ ውደኋላ እንደማይመለሱ እየተረዳን ነው።
ወያኔ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ወያኔና ሻቢያ በጋራ “ጉሮ ወሸባዬ” ብለው ሀገሪቷን ዝርፊያ ጀመሩ። የቤተመንግስቱ ጥበቃ ጀምሮ የሀገሪቷ ቁልፍ ቦታዎችን ሻቢያ ተቆጣጠረ። ሻቢያ ኤርትራን “በሕጋዊነት” በመንግስትነት ይዞ ኢትዮጵያን ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ማስተዳደር ጀመረ። ሻቢያ ወያኔን ጠፍጥፎ እንደሰራው ሁሉ ከሥልጣን በኋላም እየጋለበ ሊነዳው እቅዱ ነበር። “ሌባ ሲካፈል እንጂ ሲሰርቅ አይጣላም” ሆነና የሁለቱ ዘራፊዎች ፀብ “እኔ እብስ እኔ” ከሚለው የዘለለ አልነበረም። ወያኔ በሀገራችን የትግራይን ዘረኝነት የበላይነት ለማስፈን ካለው ምኞት አንፃር ለሻቢያ አልተመቸውም። ሻቢያም ከቶም ባልጠበቀውና ባልገመተው መንገድ የወያኔ የረቀቀ ተንኮል ሰለባ በመሆን እንዳሰበው ኢትዮጵያን ሊቆጣጠር ተሳነው። ይህ አዲስ አበባው ቤተመንግሥት ደጃፍ ደርሶ የተባረረው ሻቢያ ቁጭትና ምሬት የባድመን ጦርነት አስነስቶ ለበርካታ ወገኖቻችን እልቂት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በቀጣይነትም ሻቢያ መልሶ እንደፈለገው የሚቆጣጠራትን ኢትዮጵያ መፍጠር አለያም እንደ ሱማሌ መንግስት አልባ ሆና ትበታተን ዘንድ ምኞቱ ነው። ለዚህም ነው መገንጠል አጀንዳቸው የሆነ ሁሉ ምሽጋቸው ሻቢያ የሆነው።
ትጥቅ ትግልን በአማራጭ የትግል ስልትነት ያካተቱ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የትጥቅ ትግሉ መነሻ መሠረቱ በማያጠራጥር መልኩ እዚያው ሀገር ቤት መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ለትጥቅ ትግል የተመረጠው አካባቢ ከወታደራዊ ጠቀሜታው አንፃር ጂዎግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የአካባቢው ሕዝብ ባህልና አኗኗር፣ ከተቻለ ለመሣሪያም ሆነ ለአንዳንድ አቅርቦት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የመገናኛ መስመሮች አመቺነትና ሌላም ሌላም ተጠንቶ እንቅስቃሴው ይጀምራል። ሊጀመር የታሰበው የትጥቅ ትግል የተራዘመ ነውና ለዚህም ነው “የትግሉ ነው ሕይወቴ” የሚባለው። ትግሉን መስመር አስያዦችና ጀማሪዎች መሠረቱን ጥለው ለቀጣዮች ያስተላልፋሉ እንጂ የድሉ ፍሬ ተቋዳሾች ላይሆኑ ይችላሉና ነው ገና ሲጀምሩ ቃል ኪዳን የሚገቡት። እንቅስቃሴውም ከጀመረ ቀስ እያለ በአለው አገዛዝ የተንገፈገፈውንና መብትና ነፃነት የተጠማውን ኃይል ከዚያው ከሀገሪቷ ምድር እያሰባሰቡና እያደራጁ ትግሉ ሲመር ሲጠነክር የሚያሳዩት። ትንሽም ቢሆን የትግል ተመክሮ ላለው ምሁር ይህ ይጠፋል ማለት ዘበት ነው።
ታዲያ ሻቢያ በመገንጠልና በመበታተን አባዜ የተጠናወታቸውን መንከባከብ ለምን አስፈለገው? ቢባል መልሱ አጭርና አንድ ነው። የኢትዮጵያን መበታተን ይፈልጋልና። የመቶ ዓመት የቤት ሥራው መደምደሚያው ይህ ነውና። በሌላ በኩል እንደ ግንቦት 7ና ሌሎችም ለሻቢያ አመቺ ኃይሎች ናቸው። ሻቢያ ከወያኔ ጋር ባለበት ጊዜያዊ ፀብ ቂሙን መወጣት የሚፈልገው ወያኔን ጠልቶ ሳይሆን ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ለማሽመድመድ ካለው ትልሙ ነው። በአሁኑ ወቅት ፀብ ጭሮ በሀገሪቷ ላይ እንደበፊቱ ጦርነት ሊያስነሳ የሚችልበት ወቅት ላይ አይደለም። የኢሳያስ መንግስት በኃያላኑ ከአሸባሪዎች መመደብ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ማዕቀብም የተጣለበት ነውና ጦርነት አሁን አዋጪው አይደለም። ግና በትግል ስም እግረኛ ሠራዊቱን አስገብቶ ወረራ ሊያካሂድ ይችላል። የሚሰማሩትም ተዋጊዎች በግንቦት 7 ስምና በትግራይ ተወላጅ ተዋጊዎች ስም የሻቢያ ሠራዊት ከተሳካለት ወረራውን ይገፋበታል። በሌላ በኩልም ወያኔ ተንገዳግዶ ሊፈጠር በሚችለው ግብታዊ እንቅስቃሴ በሀገር ቤት በስውር ከተከማቹት የሻቢያ ወገኖችና በሀገር ላይ ካነጣጠሩ ጣምራ ጠላቶች ጋር እራሱን እየሸጠ ያለው ግንቦት7 እስከተመቸው ድረስ ይጠቀምበታል። ይህ ነው እንግዲህ ለዶክቶሮቻችን የተሳነው። ሊሰግዱለት የፈለጉትን አሞራ ጅግራ ሳይሆን በግ ባይ ደፋሮች ናቸው።
ውድ የኢትዮጵያ ወገኖች! ሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ አደጋ ላይ ከወደቀች በርካታ 10ተ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእኛ ዕድሜ ቢያንስ ሦስት መንግስታት ዓይተናል። የዓፄ ኃ/ሥላሴ አገዛዝ በደርግ ቀጥሎም በወያኔ ቢተካ “ትሻልን ትቼ ትብስን አመጣሁ” እንዲሉ ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ ልጆች መብትና ዕድገት ለሀገሪቷ ብልጽግና አላመጡም። ዘላለማዊነት አይታሰብምና የወያኔም መንግስት ያበቃለታል ግና ማነው አራተኛው መንግስት? ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያና ሕዝባችን ዛሬ የተጠሙት የአምባገነን መቀያየር አይደለም። ሕዝባችን በቅድሚያ በሀገሩ፣ በመንደሩ፣ በቀዬው መብቱን፣ እፎይ ብሎ መኖሩን ይፈልጋል። ስለሀገርና ሰንደቅ ዓላማ እየጮኸ መብቱን እረግጦ የቀበረውንማ አይቷልና አይናፍቀውም። የብሔር ብሔረሰቦች መብት እያለ ሀገሪቷን በዘር ፖለቲካ ዘፍቆ ኢትዮጵያዊነትንና ብሔራዊ ስሜትን ሊቀብር የተዘጋጀ መንግስትም አይቷልና አይመኘውም። እኛ ካልነው በቀር ሌላ የሚያስብ አይኑርብን፣ የሀሳብ ልዩነት አናስተናግድም፣ አትናገሩን፣ ብቸኛ አማራጭ እኛ ብቻነን ባዮችንም በተደጋጋሚ አይቷልና ተንገፍግፏል። የዴሞክራሲያ መብትን ለማታገያ ተጠቅመው እነሱ ሥልጣን ከያዙ የሕዝብና የሀገር ጥያቄ ምላሽ እንዳገኘ ቆጣሪዎችም ከስቃይና መከራው አያላቅቁምና ለቀጣይ መንግሥትነት እየቋመጡ ያሉትን፣ ከሀገራችን ጠላት ሻቢያ ጋር የሥልጥኑን በር ሊያንኳኩ የቋመጡትን ዝናብ አይፈሬ ታጋዮች በሚገባ በማጤን የመከራው ብሶትና ገፈት ቀማሽ ከሆናችሁት ውስጥ እንደ ጥንቱ ትግሉን ፍጠሩት። አማራጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ትግልና አዲሱ ትውልድ ነው።
በቀጣይ ጽሁፌ እስክንገናኝ በቅርቡ ዶክተር ጌታቸው በጋሻው በኢሳት ቴሌቪዥን ስለ ሻቢያው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የሰጡትን ሙገሳና ከአራት ዓመት በፊት ምን ብለው ነበር በማድመጥ ለሳቸውም ሆነ ለግንቦት 7 ሁላችንም አጉል ነው! አጉል ነው! እንበላቸው። ማን እንደፈለገ እየተገለባበጠ እንዳለ የሦስት ደቂቃውን ቅጂ በማድመጥ ፍርዱን ስጡ።
እሳቸው አንዴ እረጥበዋልና ዝናብ ባይፈሩም ሕዝብ ግና ሊያውቃቸው ይገባል።
ዶክተር ጌታቸው የፈለጉትን የማለት መብት ቢኖራቸውም እሳቸው ያሉትን ተጠራጣሪና ተቃዋሚ አዕምሮው ያጠራጥረናል መልዕክታቸው ንቀት የወለደው ይመስለኛል። “ለኢሳያስ አፈውርቂ ካላጨበጨባችሁ ታማችኋል” ድምዳሜአቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ ነው። እውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሻቢያንና ወያኔ ስቃይና መከራ መሆናቸውን ሞፈርና ቀንበር ዕውቀቱ የሆነው አርሶ አደር ያስረዳቸዋል። ለሕዝብ ያቀረቡትን “በኢሳያስ ተደሰትኩ” መልዕክታቸውን አደገኝነቱን አጉል ነው! እያልኩ እኔም ጽሁፌ ሕዝብ ጆሮ ይደርስ ዘንዳ አቅርቤሃለሁ። በሀገር ላይ እያሾፈና እየቀለደ ያለው ወያኔ ከበቂ በላይ ነውና ዝናብ አይፈሬ ታጋዮች ማስተዋሉን ይስጣችሁ እላለሁ።
ቸር ይግጠመን
አሉላ (alulla2@yahoo.com)
ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.
አሜሪካ ቨርጅኒያ
Leave a Reply