የወያኔ የግፍ ስርዓት በህዝብ ትከሻ ላይ ድሩን አድርቶ ፤ የማይጠረግ እስኪመስለን ድረስ ሁለት አስርት አመታቶችን በላያችን ላይ ዘልቋል ።በሰላማዊ መንገድ የግፉ ስርዓት ተቋጭቶ ፍትህና እኩልነት በሀገራችን ይሰፍን ዘንድ ብዙ ተሞክሯል ። ነገር ግን በወያኔ ስልጣን አልጠግብ ባይነት እና የሰላማዊው መንገድ ክርችም ብሎ በመዘጋቱ ባሩዷን ማሽተት ግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ከደረስን ከራርመናል ።ትግሉ ከኛ ምን ያህል የአላማ ጽናትን ይፈልጋል ? ምን ያህልስ መስዋእትነትን ያስከፍለናል ? እንዴትስ ብንታገል ካሰብነው የነጻነት ደጃፍ ባጭሩ ያደርሰናል ብለን ብንጠያየቅ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ይመስለኛል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊም በተለይም በወጣትነት የእድሜ ክልል ያለው የህብረተሰብ ክፍል ስልጣንን ከህወሃት መዳፍ ውጭ አይቶት ስለማያውቅ ፤ ሀገሪቱን እነሱ ብቻ እንዲመሩ መለኮታዊ የሆነ ፈቃድ ያላቸው እስኪመስለው ድረስ ውስጡ አምኖ ተቀብሎት ነበር ለማለት ይቻላል ።ዳሩ ቢያምንም አይፈረድበትም ፤ ምክንያቱም እድሜ ሙሉውን በገዢነት የሚያውቀው ወያኔን ብቻ ነውና ።ነገር ግን ከጥቂት አመታት ወዲህ ስንመለከት በሀገር ውስጥም ሆነ በባእድ ሀገራት በሚያስደንቅ ሁኔታ የወጣቱን አዲስ የሆነ የትግል መንፈስ በተለያዩ መድረኮች እየታየ ነው።እንደ እኔ ግምት ፤ የትግል መንፈሱን እንዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ካጦዙት አንዱ ስርዐቱ እጅግ ከፋ የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱና ሌላው የገዥው አምባገነን ቡድን በአፈሙዝ ወደ ስልጣን የመጣ ቡድን በመሆኑ ለሰላማዊ መንገድ ባይተዋርና በር የማይከፍት በመሆኑ ነው።
የወያኔ ስርዓት በርካታ የሆኑ ሰላማዊ ፣ ቡድኑን ከህዝብ የሚያስታርቁ እድሎችን በት እቢትና በተአብዮ በመወጠር ሳይጠቀምበት ቀርቷል።ሳይጠቀምበት ካመለጡት እድሎች መሃከል የግንቦት 1997 ምርጫ በዋናነት ይጠቀሳል ። በዚያ ወቅት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ በህወሃት መሪዎች ያለገደብ የተያዘው ስልጣን ህዝብ እጅ ይገባል ብሎ በጉጉት እየጠበቀ ያለበት ጊዜ ነበር ።በጊዜው ገዥው ፓርቲ በምርጫው ሙሉ በሙሉ የተሸነፈ ቢሆንም ሽንፈቱን መቀበል ተስኖት አፈሙዙን ወደ ህዝብ ሰድሮ ንጹሃንን በግፍ መጨፍጨፉ መቼም ከህሊናችን የሚፋቅ አይደለም ።በዚያ ወቅት በሰላም ስልጣናቸውን ለህዝብ ቢያወርዱት ኖሮ ላሳዩት ቀናኢነትና ህዝቡን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የስልጣን ባለቤት በማድረጋቸው ፤ ምናልባትም በ2002 ምርጫ ህዝቡ በድጋሚ እድሉን ሊሰጣቸው ይችል ነበር ብዬ እገምታለው።
በወቅቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹና ህዝቡ እውን ወያኔ ስልጣኑን ወደ ህዝብ ያወርደው ይሆን ? የሚለው ጥያቄ በአብዛኞቻችን አይምሮ ውስጥ የምርጫውን ውጤት እስክናውቅ ድረስ ልብ ያንጠለጠለ ጉዳይ ነበር ።እንደው ግን ድምጻችን ብቻ ሳይሆን ልባቸውም አሸንፏቸው በጉልበት ከያዙት የሃላፊነት ቦታ በሰላም ገለል ቢሉ ኖሮ፤ ህዝቡም ያሁኑን ያህል የከፋ ቂም በቀል በወያኔ ላይ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም ።ምክንያቱም የህዝቡ ሙሉ ትኩረት የስልጣን ባለቤትነቱ መረጋገጡ ላይ ስለነበረ ፤ በስልጣን ላይ በቆዩበት ጊዜያት ላጠፉት ጥፋትም የመጠየቅ አዝማሚያ አይስተዋልም ነበርና።
አሁን ግን ወያኔ መሽቶበታል ። ይቅር ከመባባያው ክልል በጣም እርቆ ተጉዟል ።በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም አቅጣጫ የአስከፊውን ስርዓት ገፈት ቀማሽ ያልሆነ ዜጋ ፈልጎ ማግኘት ከክምር ጭድ መሃል የወደቀን መርፌ እንደመፈለግ ይቆጠራል።
ችግር ብልሃትን እንደሚፈጥር ሁሉ አብዝቶ መበደልም የነጻነት ትግልን እውን ያደርገዋል ።የወያኔ ቡድን እንዴት ሊወገድ እንደሚችል በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ ምሁሮች ያስኬዳል ያሉትን ስልቶች ጠቁመዋል ።ከዚህም መካከል የትጥቅ ትግል አንዱ ነው ።በትጥቅ ትግል መንግስታቸውን ካወረዱ ሀገራት ልምድ በመነሳት ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ለአንድ ሀገር መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን የሚያስከትልና የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ አሳርፎ የሚሄድ ስለሆነ በሃገራችን ባይከሰት መልካም ቢሆንም ፤ ነገር ግን እንደ ወያኔ ያለ አስከፊና ጨቋኝ ስርዓት ለረጅም ጊዜያት ስልጣኑን የሙጥኝ ብሎ ህዝብን እየጨቆነ ፣ እያፈነ፣ እያሰረና እየገደለ መዝለቁም ፤ ይበል የሚያሰኝ ስላልሆነ የትጥቅ ትግሉን አስፈላጊነት እርግጥ ያደርገዋል።
እርግጥ ነው ባሩድ ሳናሸት የሚገኝ ነጻነት ቢኖር ማንም አይጠላም ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በገዥው መደብ በኩል በገሃድ የምናየው እብሪትና ትእቢት ፣ ህዝብን የመናቅና ያለማድመጥ ሁኔታ ትግሉን የግድ ያደርገዋል ። ምናልባት አንድ ቀን የባሩድ ሳይሆን የሽቶ መዐዛ ያሸትቱናል ብለን ለ23 ዓመታት በተስፋ ጠብቀን ነበር ። ግን አልሆነም ከዚህ በኋላም እንደማይሆን የአሁኑ አካሄዳቸው በራሱ እማኝ ነው ። ይህን አስከፊ እና በጥቂት አጉራ ዘለል የስርዓቱ ዋና አንቀሳቃሽ የሚከወነው እልህ ውስጥ የሚያስገባ ሀገራዊ በደል ማስቆም የእኛ ሃላፊነት ነው ።
የህወሃት መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ በጦር መሳሪያ ግዢ ስራ የተጠመደ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም።ቢሆንም የሚያስፈራንና አላማችንን አንዲት ጋትም ብትሆን ወደኋላ የሚያፈገፍግ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ለነጻነት ትግል ለመነሳት ብዙ ሃይል ወይም ብዙ የጦር መሳሪያ አይደለም የሚያስፈልገው የቆረጠ ልብ እንጂ ይሄንን ደግሞ ካሁኖቹ ጨቋኝ ገዥዎቻችን መማር እንችላላን ። የወያኔ ቡድን ለትግል ሲነሳ 11 ሆነው መነሳታቸውን ሁላችንም የምናውቀው ነው ።ቀጥሎ የነሱን ቆርጦ መነሳት የተመለከተው ወገናቸው የመሪዎቹን ፈለግ ተከትሎ ለድል በቃና በተራው ጨቋኝ ሆኖ ቁጭ አለ ። ወገኖቼ ! ታድያ ታግሎ ያታገላቸው የቁጥራቸው መበራከት አሊያም የጦር መሳሪያ ብዛት አልነበረም ትግራይን ነጻ የማውጣት የአላማ ጽናት እንጂ ፤ እኛም ከዚህ ምሳሌ በመነሳት ኢትዮጵያን ካለችበት የጭቆና ቀንበር ለማውጣት ቁርጠኛ ልብ ያስፈልገናል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ስርዓቱ ሞቷል ከኛ የሚጠበቀው ተገቢውን የቀብር ስነስርዓት ማስፈጸም ብቻ ነው!!!!
እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ !!
Leave a Reply