የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ በእግሩ የተተካው ህወሓት ይኸው ሥልጣን ላይ ከወጣ 23 ዓመት ሊሆነው ነው። ህወሓት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ዲሞክራሲን አሰፍናለው፣ ሰብአዊ መብት አክብሬ አስከብራለው፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ይከበራል፣ ልማት ይመጣል የኢትዮዽያ ሕዝብ ስደት ያበቃል፣ በቀንም ሦስት ጊዜ ይበላል የሚሉት ዋንኞቹ ነበሩ። እስኪ አንድ በአንድ እንያቸው።
1. ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ ህወሓት ከበረሃ ወጥቶ ከተማ እንደገባ ዋንኛ ጩኸቱ ይሄ ነበር። በመጀመሪያ አካባቢ ነፃ ጋዜጦችን ማሳተም፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በፖለቲካ ፓርቲ መደራጀት የመሳሰሉት ነገሮች ጥሩ ጅማሮ ያሳዩ ቢሞስሉም ብዙም ሳይቆይ ግን የህወሓት ትክክለኛ ባሕሪ መገለጥ ጀመረ። ጋዜጠኞችን ማሰርና ማንገላታት፣ ነጻ የሙያ ማኅበራትን ማፍረስ፣ ተቃዋሚዎችን ማሰር ብሎም በስውር ማስገደል፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች ቀስ በቀስ እየተከለከሉ መጡ። በተለይ ሁላችንም እንደምናውቀው ከምርጫ 97 በኋላ በቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሰላማዊ ሰልፍና ከቤት ውጪ ስብሰባ ሙሉ ለሙሉ ተከለከለ። ጋዜጠኞች በግፍ ታሰሩ በርካታ ጋዜጦችም ተዘጉ። በምርጫ በኩልም ብናይ ባለፉት 23 አመታት ውስጥ ምንም አይነት ግልጽና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። በ97 ትንሽ ገርበብ ብሎ የነበረውን በርና የሕዝብ ተስፋ ለማጨለም ህወሓት ከ24 ሰዓት በላይ አልፈጀበትም። ምርጫውን አጭበርብሮ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን እስር ቤት አስገብቶ ከ200 የማያንሱ ሰላማዊ ዜጎችን ከገደለና ከ30 ሺህ የማያንሱ ወጣቶችን በተለያዩ እስር ቤቶች አጉሮ ካሰቃየ በኋላ ሀገሪቱ ይባስኑ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኋላ ነው የተመለሰቸው።
እንደ ደርግ ጊዜ ዛሬም ዜጎች ፍርድ ቤት ሳይቀረቡ ይታሰራሉ ይገደላሉ። በማዕከላዊና በእስር ቤቶች ውስጥ ዜጎች ይገረፋሉ። ቶርች ይደረጋሉ። በተለይ ሰዎች ከፖለቲካና ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከሆነ የታሰሩት የሚደርስባቸው በደል ከፍተኛ ነው። በብርቱካን፣ በበቀለ ገርባ፣ በአንዱ ዓለም አራጌ፣ በእስክንድር በርዮት ዓለሙ፣ በውብሸት ታዬ ላይ የደረሱትና እየደረሱ ያሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማየቱ በቂ ነው። በአጠቃላይ ለዲሞክራሲ አስፈላጊ የሆኑት ተቋማት ማለትም ነጻ ፍርድ ቤቶች የሉም፣ ነጻና ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም የለም ፣ በሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጏሚ መካከል ምንም አይነት የሥልጣን ክፍፍል የለም። ሁሉም ነገር በሕግ አስፈጻሚው በዋናነትም በህወሓት ከህወሓትም በጣም ጥቂት በሆኑ ግለሰቦች እጅ ያለው ነው። በአጭሩ ሁሉም ነገር የሚሰራው በባለስልጣናት በጎ ፍቃድ እንጂ በሕግ የበላይነት አይደልም።
2. የብሔር ብሔረሰቦች መብትና እራስን ማስተዳደር ህወሓት ከአጋሮቹ ጋር ሆኖ ያጸደቀው ሕገ መንግስት አንቀጽ 39 ብሔረሰቦች እራሳቸውን እንደሚያስተዳድሩና ከፈለጉም እስከመገንጠል መብት እንዳላቸው ደንግጏል። ክልሎችም ብሔርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ተዋቅረዋል። ልክ ነው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ። ነገር ግን በተግባር እንደምናየው ሥልጣኑን በማዕከል ጠቅልሎ የያዘው ህወሓት ነው። ለምሳሌ በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ በሚባሉት ክልሎች ውስጥ በሶማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል በሙስናና ሌሎች ሰበቦችን በማስቀመጥ የክልሎቹ መሪዎቹ ከቦታቸው ሲነሱ በቀጥታ የሚፈጸመው ከፌደራል መንግስት በሚሄዱት በአባይ ፀሐዬ በዶ/ር ሺፈራውና በመሳሰሉት ባለሥልጣናት ነበር። አሁንም እንደዚያው ነው። ለይስሙላ የክልሎቹ ምክር ቤቶች ተሰብስበው ቢወስኑም ስራው ግን አስቀድሞ ከመጋረጃው ጀርባ ነው የሚጠናቀቀው። ሌሎቹም ክልሎች ቢሆኑ ከዚያ የተለየ ነገር የላቸውም። ለምሳሌ የአቶ አባተ ኪሾ ከደቡብ ክልል ፕሬዚዳንትነት የተነሱትና የታሰሩት በእነ መለስ ዜናዊ ቡድን ነበር። አቶ አባ ዱላ ገመዳ ወደ ፌዴራል መንግስት ሲዛወሩ የኦ.ፒ.ዲ.ዮ. አባላትና ምክር ቤት ተቃውሞ ነበራቸው። በጉዳዩ ላይ መግባባት ስላልነበር በተደጋጋሚ ተሰብስቦ ነበር። በኋላም በእነ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በመተላለፉ እሳቸው ወደ ፌዴራል እንዲመጡ ተደረጎ ሟቹ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ነበሩ የተተኩት። በፌዴራል ደረጃ ያለውን አወቃቀርና የሥልጣን ክፍፍል ብናይ ሁሉም ቁልፍ ቦታዎች በህወሓት ቁጥጥር ናቸው።
ባለፉት 21 አመታት ውስጥ የጠ/ሚ ቦታ ከህወሓት እጅ ወጥቶ አያውቅም። አሁንም ለይስሙላ አቶ ሀይለማሪያም ይቀመጡ እንጂ ስልጣኑ ያለው በህወአቶቹ በእነ ደብረጽዮን እጅ ነው። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርነቱም ቦታ በመሀል ላይ ለ2 አመት ያህል በአቶ ሀ/ማሪያም ከመያዙ ውጪ አሁንም በህወሓት ቁጥጥር ስር ነው። በሠራዊቱ ውስጥ የኤታማዦርነት ቦታ ላለፉት 23 አመታት በህወሓት እጅ ነው። በጄነራል ማዕረግ ያሉት የሥልጣን ቦታዎች ከጥቂቶቹ በቀር በብዛት በህወሓት የተያዙ ናቸው። ከዚያም ወረድ ብሎ ያሉት የማዕረግ ቦታዎች ውስጥ የህወሓት አባላት ቁጥር ብዙ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ በህወሓት ቁጥጥር ሥር ነው። የኦሮሞ፣ አማራና የደቡብ ወይም የሌላ ብሔር አባላት ቁጥር በጣም ጥቂት ነው ወይም ከነጭራሹ የለም በሚባል ደረጃ ነው ያለው። ሁኔታው በዚህ ብቻ አያበቃም ለክልል ፕሬዝዳንቶች አማካሪ እየተደረጉ ይሾሙ የነበሩት ከህወሓት ሲሆን በሁሉም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ከህወሓት ቢያንስ አንድ ምክትል ሚኒስቴር አለ። የዚህ አላማው ደግሞ ከላይ የተቀመጡትን ከትግራይ ብሔር ውጪ ያሉትን ለመቆጣጠር ነው። በመሆኑም በአጠቃላይ ያለውን ነገር ስናይ ለስሙ በፌዴራል አወቃወር የተመሰረተ መንግስት አለ ቢባልም በተግባር ግን ሁሉ ነገር በማዕከላዊ መንግስት ብሎም በህወሓት ቁጥጥር ስር ነው ያለው። የብሔረሰብ ጥያቄ መልስ ስላላገኘ አሁንም በርካታ ብሔረሰቦች እራሳችንን እናስተዳድር ብለው ብቻ ሳይሆን እንገንጠል ብለው የትጥቅ ትግል እያካሄዱ ነው። የህወሓትም የብሔሮች እራስን የመስተዳደር ቃልና ተግባር ሳይገናኙ 23 አመታት አለፉ።
3. ልማት ይመጣል፣ በቀን ሦስት ጊዜ ትመገባላችሁ ስደት ይበቃል. . . ይሄ ሌላው ህወሓት-ኢህአዴግ ለሕዝብ ተስፋ ከሰጣቸው ነገሮች አንዱ ፍትሀዊ ልማት ማምጣትና ድህነት መቀነስ ነበር። ነገር ግን የተወሰኑ መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ውጪ ኢኮኖሚው ከግብርና ወጥቶ ወደ ኢንደስትሪው ሽግግር አላደረገም። ዛሬም ከ83% በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ በግብርና ነው የሚተዳደረው የሚኖረውም በገጠር ነው። ከ80% በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ ዛሬም መብራት አያገኝም። ከ65% በላይ የሚሆነው ደግሞ ንጹሕ የመጠጥ ውሀ አያገኝም። ከ35% በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው። አሁንም መንግስት ከ5 ሚሊዮን ለማያንሱ ዜጎች በየአመቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይለምናል። ዛሬ አብዛኛው ሕዝብ በቀን ሦስቴ መብላት አይደለም በቀን አንዴ ለመመገብ እየተቸገረ ነው።
በእርግጥ ሥርዓቱ ሀብታም ያደረጋቸውና ከገዢው ፓርቲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በአንድ ሌሊት ከድህነት ወጥተው ሀብታም እየሆኑ ነው። አልፎም ከሙሰኛ ባለሥልጣናት ጋር አብረው እየነገዱና እየዘረፉ በሀገር ውስጥም በውጪም እያጠራቀሙ ነው። ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከድህነትና ከነጻነት ማጣት የተነሳ በየአመቱ በአማካይ ከ250,000 በላይ ዜጎች በሕጋዊና ሕገ ወጥ መንገድ ይሰደዳሉ። ብዙዎቹም በመንገድ ላይ ይሞታሉ፣ የውስጥ አካላቸው ይሰረቃል፣ ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱት ደግሞ የሚደርስባቸው በደልና ግፍ ብዙ ነው። ዛሬ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያና በሱዳን የስደተኞች ጣቢያ ይገኛሉ። የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የንግድ ሥርአት የህወሓት ንብረት በሆነው በኤፈርት ተፅዕኖ ሥር ነው። የሀገሪቱን ጝዽጵ 40% የሚያክል ካፒታል ይዞ ግዙፍ የንግድ ኢምፓየር መስርቶ እንደፈለገው ኢኮኖሚን እያሽከረከረው ይገኛል። በንግድ ሥርአቱ ውስጥ ፍትሀዊ ውድድር የለም።
በአጠቃላይ ከ23 አምታት በኋላም ሀገሪቱ ከ1983 በፊት እንደነበረችው በአምባገነኖች ስር ነች። የሕግ የበላይነት የለም። ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ የማይታሰብ ነው። የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የመሳሰሉት መብቶች በገዢው ፓርቲ መልካም ፍቃድ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው። በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ዛሬም የሰው ሕይወት እስከማጥፋት የሚያደርሱ ግጭቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይከሰታሉ። የብሔረሰቦችም ሆነ የግለሰብ መብት አልተከበረም። ድህነትና ሥራ አጥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ ናቸው። ስንደመድመው በሁሉም አቅጣጫ የኢህአዴግ የተስፋ ቃላት ከሽፈዋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የትንሳኤ በአል ይሁንላችሁ
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Leave a Reply