ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 ዓመተ ዓለም አንድ የነጻነት መሪ ነበር። በዘመናዊ የማኔጅመንት ትምህርት ውስጥ የስራ ክፍፍልን የፈጠረና መሰረት የጣለ ትልቅ ሰው ነው። ይህ ሰው የተወለደው በጭንቅ ሰዓት ነበር። እስራዔላውያን በግብጽ ምድር በባርነት ቀንበር ስር ባሉበት ሰዓት። ንጉስ ፈርዖን የእስራዔላውያንን የጥበብ ስራዎች፣ የሚሰሯቸውን ጡቦች ቢወድም ነገር ግን በቁጥር እየበዙ ከመጡ መንግስቴን ይነጥቁኛል ብሎ ስለፈራ ህጻናትን ሁሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ የተላለፈበት የጨለማ ዘመን ነበር። በዚህ ወቅት የተወለደው ይህ ሰው ወላጅ እናቱ በዓባይ ወንዝ ላይ በእንዲት ቅርጫት ኣሳፈረችው። መደበቋ ነው። በርግጥም ከወታደሮች ሰይፍ መትረፍ ችሏል። ለሶስት ወራት በዚህ ሁኔታ ወላጅ እናቱ ደበቀችው። ታዲያ ከእለታት ኣንድ ቀን ልእልት እየችው። ልእልት ይህን ህጻን ስታየው ያማረ ነበርና ቤተመንግስት ያድግ ዘንድ ተደረገ። እድለኛ ነው ቢባልም ከፍ ሲል እብራዊነቱን ኣጥብቆ ያዘ።ሙሴ በንጉስ ቤት ከሚኖረው ኑሮ ይልቅ የወገኖቹ የባርነት ኑሮ ያንገበግበው ነበርና የፈርዓን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢኝ ኣለ።
ሙሴ በአካልም በመንፈስም ከጠነከረ በሁዋላ የእብራውያን ከግብጽ መውጣት ጉዳይ በጣም በራለት። መውጣት አለብን አለ….ዘ-ፀዓት ልቡን ሞላው። የዓያቶቹን የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ናፈቀ። ወተትና ማር የምታፈልቀው የአባቶቻቸው ምድር ከነዓን ወለል ብላ ታየችው። ቅስቀሳዎችን ጀመረ…እብራውያን የዓያቶቻቸውን ምድር ማሰብ …ማሰላሰል ጀመሩ። ከነዓንን ያቺን የተስፋይቱን ምድር…
እብራውያን የግብጽ ባርነት ኣሰቃይቷቸው ነበርና የተስፋ ምድራቸውን ናፈቁ—ናፈቁ ያለ ልክ። ሙሴ ወገኖቹን በመወከል ብዙ ጊዜ በንጉስ ፍርዖን ፊት ቆመላቸው…..ሽንጡን ገትሮ ተሟገተላቸው። ይሁን እንጂ ፈርዖን የነዚህ ጥበበኞች ጥበብና ጉልበት ጥሞት ነበርና እምቢኝ ኣለ። እግዚአብሄር የግብጻውያንን የበኩር ልጆች ሁሉ መግደል ሲጀምር ፈርዖን እጅ ሰጠ። ከዚህ በሁዋላ ሙሴ ኣንድ ቀን ህዝቡን ይነሱና ግብጽን ለቀው ይወጡ ዘንድ ጥሪ ሲያደርግ በእብራውያን ዘንድ ፈንጠዝያ ሆነ። እስራዔላውያን የተስፋ ምድራቸውን ለማየት እጅግ ቋምጠው ነበር። ከዚህም የተነሳ የውጡ (exodus) ደወል ሲመታ ሊጋግሩት ያቦኩትን የዳቦ ሊጥ እንኳን በዚያ የባርነት ኣገር ውስጥ ሊያበስሉት ኣልፈለጉም። ጨርቃቸውን እያንጠለጠሉ ከነሊጣቸው ወጡ። ለነጻነት ቸኩለው ነበርና። ለከነዓን ለተስፋ ምድራቸው ቸኩለው ነበርና ነው። ሙሴ የወገኖቹ ብሶት የገባው ቆራጥ መሪ ስለነበር ንቅናቄውን መርቶ ጉዞ ጀመሩ። እነዚህ ባለ ተስፋ ህዝቦች ተስፋን ሰንቀው ወደ ከነዓን ጉዞ በጀመሩ ለታ በነጻነት ኣየር ውስጥ ናቸው። ይሁን እንጂ ግን ወደ አገራቸው ገብተው ተረጋግተው ለመኖር ገና በጉዞ ላይ ናቸው። ታዲያ ግን ጉዞው የሚፈጀው ሁለት ሳምንት ገደማ ቢሆንም በሚገርም መልኩ አርባ አመት ፈጀባቸው።
በርግጥ ሙሴ እጅግ ግልጽ የሆነ መድረሻ ቢኖረውም፣ ከባርነት ሰፈር በመውጣቱ ጉዳይ ላይ የማይናወጥ ኣቋም ቢኖረውም ፣ ግልጽ መነሻ ቢኖረውም ወደዚያ ወደ ተስፋቸው ምድር በሚወስደው ካርታ (Road-map) ላይ ግን የተጨነቀ ኣይመስልም። ምን ኣልባትም ከመነሻውም መነሻና መድረሻውን ቢያውቅም በመሃል ወደዚያ በሚወስደው መንገድ ላይ ግልጽ መረጃ ያለው ኣይመስልም። መድረሻውና መነሻው መስጠውታል:: የግብጽ ኑሮ ወገኖቹን ያለ ልክ ጎድቷልና የመውጣቱ ጉዳይ ብዙውን ሃይሉን ሳይወስድበት ኣይቀርም ይሆናል። እናም የኣስራ ኣንድ ቀን ጉዞ ኣርባ ኣመት ፈጀና ብዙ ትውልድ ከነዓንን ሳያይ ቀረ።
ይሁን እንጂ ግን ነጻነታቸውን በጉዞ ላይ ሳሉም ቢሆን ተቀዳጅተው ነበር። እብራውያን በጉዞው ተሰላችተው ወደ ግብጽ መልሰን ብለው ሙሴን የጠየቁት በርግጥ የግብጽን ኑሮ ናፍቀው ኣይደለም። ሙሴን እልህ ውስጥ በማስገባት ቶሎ ካርታውን ኣስተካክሎ ኮምፓሱን ኣስተካክሎ ወደ ኣባቶቻቸው ምድር እንዲያስገባቸው ነው እንጂ እብራውያን ከግብጽ ኑሮ ሞትን መርጠዋል።ወደ ግብጽ ከመመለስ በዚያው በምድረ በዳ የእምላካቸውን መና እየበሉ ቢኖሩ እጅግ ይሻላቸዋል። ይሁን እንጂ ሙሴ እንዴት ወደከነዓን መግባት እንደሚቻል አምላኩንም ሲጠይቅ ስለ ካርታው ሲጨነቅ ኣይታይም። ያንን በምድረ በዳም ቢሆን ያገኙትን ነጻነት እያየ ረክቶ ተዘናጋ ይሆን፣ ከሰማይ የሚወርደውን መና እያየ ቶሎ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመግባቱ ጉዳይ ላይ ብዙ ሳይጨነቅ ቀረ ይሁን ኣይታወቅም። ብቻ ግን አዘገያቸው።
የሙሴ ታሪክ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ኣስተማሪ ሆኖ ኣየሁትና ነው ይህን ኣሳብ ያስቀደምኩት እንጂ ስብከት ኣምሮኝ እውቀቱ ኖሮኝም ኣይደለም። መጽሃፉን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች እንዴት እንደሚገልጹት ኣላወቅም። የሆነ ሆኖ ግን ለዛሬው የኢትዮጵያ የነጻነት መሪዎችና ለኛም ይህ ታሪክ ተምሳሊታዊ ኣስተማሪነት ኣየሁበት። ውጣ (exodus) የሚለው ቃልም በርግጥ መሰጠኝ። ወቅታዊ ጥሪ መስሎ ተሰማኝ።
የኢትዮጵያ ዘ-ፀዓት
አገራች ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጊዜ ሳትወስድ ልትወጣባቸው የሚገባት ጉዳዮች ኣሉ። ትውልዱ የውጣ ስሜትን ሊያመጣ የሚገባበት ዘመን ላይ ነን። ውጣ ሲባል ከምን ከምን ልንል እንችላለን። ኣንደኛው ከጎሰኝነት እስራት፣ ሌላው ከጥላቻ ፖለቲካ፣ ሌላው ከድህነት፣ ሌላው ከአምባገነኖች ጭቆና፣ ከኣደገኛ ባህሎች ሁሉ ነው የውጣ ክተት ኣዋጅ መትተን ልንወጣ የሚገባው። ነገር ግን መውጣት ብቻ ኣይደለም። ከጎሰኝነት ወጥተን በምን ኣይነት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ እንደምንገባ ግልጽ የሆነ መድረሻ ሊኖረን ይገባል። ሙሴ መድረሻው ግልጽ ነበር። የኛ ፖለቲካ ችግር ሁላችን መውጣት እንዳለብን ብናይም በመድረሻችን ላይ ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ኣሉ። መድረሻችንን በሚገባ ሳናውቅ ከቀረንና “የሚጋጩ ህልሞች” ካሉን በርግጥ ለመውጣት እንቸገራለን።
ሌላው የፖለቲካችን ችግር ደግሞ ወደ ለውጥ የሚወስደንን መንገድም እንዲሁ ግልጽ ሆኖ ያለማየት ችግር ነው። ለመውጣት (exodus) ሶስት ነገሮች ያሻናል። ኣንደኛው የመውጣት ኣዋጅ፣ ግንዛቤ፣ ህዝባዊ ንቅናቄ ነው። ይህን ንቅናቄ ደግሞ ወደ ተሻለች የኣዲስ ኪዳን ኢትዮጵያ ቤት ውስጥ የሚወስድ መሆን ኣለበት። ኣዲሲቱን ኢትዮጵያን በኣይምሯችን ስለን ሲስተሙን በተግባር ኣይተነው ልንቋምጥለት ይገባል። ያ ነው የመውጣታችን ሃይል የሚሆነው። እስራዔላውያን ስለተስፋ ምድራቸው ሲሰሙ፣ ኣገር የሌላቸው ሳይሆኑ ነገር ግን ከሁሉ የበለጠ ምድር እንዳላቸው ሲገነዘቡ ለመውጣት ትልቅ ሃይልን እንዲሰንቁ ኣድርጓቸዋል። ኣገር እንደሌለው እንዴት እንደዚህ እንሆናለን፣ ጥበብ እያለን እንዴት እንዲህ ባሪያ እንሆናለን የሚለው ስሜት እብራውያንን ጨርቅ ያስጣለ፣ ከነሊጣቸው እንዲወጡ ያደረገ ትልቅ የለውጥ ሃይል ነበር።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ሃገራችንም ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የቡድኖችን ማንነት ሳትጨፈልቅ፣ ቋንቋዎችንና ባህልን ኣክብራ የምትኖርበትን ስርዓተ-መንግስት ሰርታ ስታሳይ ወጣቱ ለለውጥ ይነሳል። ያ ትውልድ የሚባለው ወጣት ቀልቡን የሳበው ኣንድ ጉዳይ ኣንድ ያየው መድረሻ ስለነበር ነው። የሶሻሊዝም ትምህርት የሚፈጥረው ስእል (image) በወጣቱ ኣይምሮ ውስጥ ተስሎ ነበር። ገነት የሆነች ኢትዮጵያን ሳያዩ ኣይቀሩም። ለነገሩ ሶሻሊዝም የዓለምን ወጣቶች በየኣገሩ ኣሳብዶ ነበር። የሚያሳየው ዓለም ያማልላል። መንግስተ ሰማያትን እዚህ መሬት ላይ ኣምጥቶ ያሳያል። እኩልነት የሰፈነባት ዓለም፣ የኔ የኔ የሌለባት ዓለም፣ ድሃና ሃብታም የማይባልባት ዓለም፣ ሰላም የሰፈነባት የበለጸገች ኣለምን በጥሩ የስነ ጽሁፍ ቋንቋ ያሳያል። ነገር ግን ያ ዓለም ምናባዊ በመሆኑና ወደዚያ የሚያደርሰው መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ ሩቅ ሳይሄድ ሰዎች እየተገነዘቡት ቀዝቀዝ ኣሉ። ስለሆነም ወደ ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የመውጣት ንቅናቄ ለማድረግ መጀመሪያ ተጨባጭ የሆነች የተሻለች ኢትዮጵያን በተለይ መሪዎች ሊያዩልን ይገባል።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት ዙሪያ መለስ ችግሮች ለመውጣትና የተሻለ ዓለም ለማየት ፖለቲካዊ ለውጥ ብቻውን ኣይበቃትም። ፖለቲካዊ ለውጥ ብቻውን ይጠባል። የግድ ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ መግባት ኣለብን። ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ መግባት ኣለብን። ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ምርት መጨመር ብቻ ሳይሆን የሪሶርስ ኣጠቃቀሟንም ልታሻሽል ይገባል። ያሉብን ችግሮች ማህበራዊ ሲደመር ፖለቲካዊ በመሆኑ የግድ ማህበረ ፖለቲካችን ኣካባቢ ልንወጣ የሚገባን ጉዳዮች ኣሉ። ልክ እስራዔላውያን አንድ ተራራ እየዞሩ የሁለት ሳምንቱ መንገድ ኣርባ ኣመት እንደፈጀባቸው የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ ኣርባ ኣመት በላይ ፈጅቷል። የመሬት ላራሹ ጥያቄ ከሌላው ዓለም በተለየ ሁኔታ ከኣርባ ኣመት በላይ ፈጅቷል። ኢትዮጵያ ከፊውዳሉ ስርዓት ከተላቀቀች በሁውላ በፍጥነት ልታሻሽለው የሚገባውን ይህን መሰራታዊ ጉዳይ ኣርባ ኣመት ሙሉ ይህን ተራራ ስንዞር ይታያል። ህወሃት ኢህዓዴግ ወደስልጣን ከመጣ በሁዋላ የገባንበት ስስታም ፖለቲካ ደግሞ ኣንዱ ኢትዮጵያውያን የውጣ ክተት ልናውጅበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ከእኔ እኔ እኔ ከሚል ራስወዳድና ጠባብ ኣስተሳሰብ ወጥታ ወደ እኛ ኣስተሳሰብ መግባት ያስፈልጋታል። ከዚህ በፊት ደጋግመን እንዳልነው ኣገር በእኔ … እኔ … እኔ… ኣይቆምም። የግድ ከዚህ የወጡና ለመስዋእትነት የተዘጋጁ ቡድኖችን ይጠይቃል። ያለንን የቡድን ሃብት ኣጥብቀን ይዘን ደግሞ ኣገር የሚባል ነገር ናፍቆን ኣይሆንም። መውጣት ኣለብን። በሌላ በኩል ትምክህተኝነት ኣስተሳሰብም ከዚሁ ከጠባብነት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ስሜት በመሆኑ ወጣቶች የመውጣት (exodus) ኣዋጅ ሊያውጁበት ይገባል። በነገራችን ላይ exodus ማለት የግሪክ ቃል ሲሆን በእንግሊዘኛ mass departure ወይም የህዝቡ መነሳትና መውጣት ማለት ነው። ታላቅ ህዝባዊ ውሳኔ የሚጠይቅ ንቅናቄ ነው። የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ለሃገር የሚቆረቆሩ ሁሉ ወደዚህ ቆፍጣና ስሜት ውስጥ ገብተው ካልተሻገርን አገራችን የተቀመጠችበት ወለል ጥሩ ኣይደለም። የራሷ ኣኩሪ ታሪክ ያላት ኣገር እንዴት በኛ ዘመን እንዲህ ትሆናለች? ብሎ መቆጨት ያስፈልጋል።
አንድ ጊዜ ፌስ ቡክ ላይ ኣንድ ነገር ኣየሁ። የላሊበላን ውቅር ቤተክርስቲያን ያየሰው እንዲህ ይላል። ይህ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያዊ ሊሰራ ኣይችልም ምናልባት የሚሆነው ኣንድ የውጭ ኣገር ዜጋ መጥቶ ሰርቶላቸው ሄዶ ነው ይላል። ይህ ሰው እንዲህ እንዲል ያደረገው ነገር ኣሁን ያለንበትን ድህነትና ዓለም ከደረሰችበት ኣንጻር እኛ ወደ ሁውላ መቅረታችን ነው። ዛሬ ላይ ስንታይ ያንን የመሰለ ጥበብ የነበረን ሰዎች ኣንመስልም ማለት ነው። ለነገሩ ግን ይህ ሰው መገንዘብ ያለበት ያ የውጭ ኣገር ዜጋ ይህን መስራት ከቻለ ለምን ራሱ ኣገሩ ላይ ኣልሰራውም ነበር? ይህን የሚመስል ወይም የተሻለ የመስራት ጥበብ ከነበረው በሃገሩ ከዚህም የተሻለ ተሰርቶ ባየን። ነገር ግን ይህ ጥበብ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተገኘው፣ ለዚህም ነው የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበው። በትክክልም የኛው ኣባቶች ስራ ነበር። በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ስንዞር ኣሰደናቂ ጥበቦች ይታያሉ። የኣባቶች ስራ ነው። የራስ ፈደል መኖር ትልቅ የስልጣኔ መሰረት ነው። ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የነበረች የሰለጠነች እንደነበረች እነዚህ ጥበቦች ህያው ምስክር ናቸው። ይሁን እንጂ ኣሁን ያለው ትውልድ በብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ ዙሪያ ኣንድ ተራራ ኣርባ ኣመት ሙሉ ይዞራል። ዞሮ ዞሮ ተመልሶ ትናንት ያደረበት ቦታ ሲያድር ኧረ ይሄ ቦታ ትናንት መጥተንበት ነበር ተሳስተናል ኣይልም። ዝም ብሎ ይዞራል። ከዚህ ነው መውጣት ያለብን። ወጣቶች በልበ ህሊናቸው የመውጣትን ስሜት ካልጻፉ፣ ከባርነት መቼም ኣንወጣም።
አብያተ ክርስቲያናትና የባህል መሪዎችም ኣዋጅ ሊያሰሙ ይገባል። ዘ-ጸኣት ሊያውጂ ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በኣንዳንድ ቡድኖች ኣካባቢ ከፍተኛ የሆነ የኔጌቲቭ ሶሻል ካፒታል ክምችት ኣለ። ያልጠረግነው ብዙ ጎታች ባህል ኣለ። በህጻናት፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ብዙ ባህል ነክ ወንጀል ኣለ። ሰዓትን የማክበር ፈጣን የመሆን ባህል ማዳበር ያስፈልጋል። ፓርቲዎች ህብረትን ሊያጓትቱ ኣይገባም። ኣሳማኝ ምክንያት ለሌለው ነገር ጊዜ መግደል ኣንድ ትልቅ ችግር ነው። በነጻነት ትግል ውስጥ ትልቁ ቁም ነገር ጊዜ ነው። ብዙ እስራዔላውያን ከነዓን ያልገቡት ረጅም ጊዜ እንድ ተራራ በመዞር ስለፈጁ ነው። ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበረሰብ ኣካላት በየፊናቸው የዘጸዓት ኣዋጅ ነጋሪት ሊመቱ ይገባል። በጎጂ ባህል ማስወገድ ኣካባቢ የሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ዘጸዓት ሊሉ ይገባል፣ ድህነትን የሚዋጉ ድርጅቶች ዘጸዓት ሊሉ ይገባል፣ የተጨቆኑ ህዝቦችን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ የሚጥሩ ፓርቲዎች ዘጸዓት ሊያውጁ ይገባል። ዘጸዓት የፖለቲካ ርእዮት ኣይደለም። ኢትዮጵያውያን ከከበባቸው ዙሪያ መለስ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሁሉ ለመውጣት የሚሰንቁት የሞራል ስንቅ ነው።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።
geletawzeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply