
በመጀመሪያ ደረጃ፤ ለነፃነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ትግል፤ ትክክለኛ መፍትሔ የሚሆነው፤ የማያወላውል ቆራጥ የዴሞክራሲ ጠበቆች ሆነው፤ ለዴሞክራሲ አሰራር ጽኑ ዕምነት ባላቸው ሀቀኛ ታጋዮች ሲመራ ብቻ ነው። የኒህ ታጋዮች የዴሞክራሲያዊ አሰራር እና የነፃነት ምንነት ግንዛቤ፤ እዚህ ቦታ ይሠራል እዚያ ቦታ ግን አይሠራም የሚባል የቦታና የጊዜ ክልል የለውም። ለጊዜያዊ ጥቅም ወይንም አንድን ወገን ጎድቶ ሌላውን ለሚረዳ ተግባር እጃቸውን አይዘረጉም። ለዴሞክራሲ ጥብቅና ለሚቆምና ለምትቆም ግለሰብ፤ ቦታ ሆነ ጊዜ አይከልላቸውም። ያንን በውስጥ የድርጅታቸው አሰራርና በውጭ ግንኙነታቸው ይገልጹታል። ተማሪ ሆኜ፤ ለፓሪስ ኮሚውን መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ትምህርት አቁመን ስንዘክር ትዝ ይለኛል። ከኔ የቀደሙት ደግሞ፤ የኢያን ስሚዝን የሮዴዥያ ነፃነት ማወጅ አውግዘው፤ የአፍሪቃ ሀገራት በትብብር እንዲያወድሙት ተማሪዎቹ መሰለፋቸውን ተገንዝቤአለሁ። አሜሪካ ከቪየትናም ትውጣ ብለን ትምህርት አቁመናል፤ ዘምረናል። ይኼን ሁሉ የምዘረዝረው ለምክንያት ነው።
ቀደም ሲል አንድ ሽምገል ያሉ ታጋይ ሰው፤ ትግሉን በኤርትራ ለማካሄድ፤ ወደ አስመራ እንደሚያመሩና ኢሳያስ አፈወርቂን እንደሚገናኙት ነገሩኝ። ትብብር እንዳደርግላቸውና እኔና መሰሎቼ አብረናቸው እንድንሰለፍ መከሩኝ። አስፈላጊነቱን ጠየቅኋቸው። “ምን ማለትህ ነው? ኤርትራ እኮ ልትረዳን ትችላለች። ደግሞ ኤርትራ ካልሆነ፤ ሌላ በየት በኩል ተገብቶ መታገል ይቻላል? ኢሳያስ እኮ የኢትዮጵያን አንድነት ይፈልጋል። ወያኔን ደግሞ ይጠላል። ስለዚህ፤ በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ ተጠቅመን፤ የራሳችንን ነፃነት ማግኘት እንችላለን።” አሉኝ። ሰፋ አድርገን ስለ ወያኔና ስለ ሸዓቢያ ተነጋገርን። ልንጣጣም አልቻልንም። በመጨረሻም፤ “ዓየህ አንዱዓለም፤ ሸዓቢያ ወያኔን ረድቶ አዲስ አበባ እንዳስገባው ሁሉ፤ እኛንም አዲስ አበባ እንድንገባ ከረዳን፤ በኋላ ዞር በል ማለት እንችላለን። ለምን ከሰይጣን ተባብረን ወያኔን አንጥልም?” አሉና አቋማቸውን ግልጽ አደረጉልኝ። ማን በማን ላይ ብልጥ መሆን እንደሚችልና የወደፊቱን እንዴት አድርገው እንዳስቀመጡት ስረዳ፤ ወጋችን ግምኛ መሆኑ ተሰማኝ። ከዚያ በኋላ ሲመለሱም ሆነ ሲመላለሱ ግንኙነታችን አልገፋም።
እዚህ አሜሪካ ተቀምጬ፤ ዶናልድ ትራምፕ የሚዘባርቀውን ሁሉ ሳወግዝ፤ ቻይና የምታደርገውን ስረግም፣ ፑትን የሚሸርበውን ሳውጠነጥን፤ ፍትኅ ደንበር የላትም ብዬ ነው። አይሲስ የኢትዮጵያዊያንን አንገት ሲቀላ፤ ደሜ አብሮ ፈላ። ኢሳያስ የኢትዮጵያ ወታደሮችን አስሮ እንደባሪያ ሲያሰራቸው፣ ልቤ አዘነ አብሯቸው። ደቡብ አፍሪቃ ኢትዮጵያዊያን በዱርዬዎች ሲጎዱ፣ አጅና እግሮቼ በንዴት አብረዋቸው ነደዱ። የትም ቦታ የሚደርስ በደል፣ በደል ስለሆነ መቃወሜን አላቋረጥኩም። ታዲያ ኢሳያስ በሀገሩ ላይ ምን እየሠራ ነው። ኤርትራዊያን አይደሉም እንዴ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በሜዲትራንያን ባሀር የሚሰጥሙት! ኤርትራዊያን አይደሉም እንዴ እንደ ኢትዮጵያዊያን ላንቃቸው ተዘግቶ፣ በየእስር ቤቱ እየማቀቁ ያሉት! እንዴት ተብሎ ነው አንድ ታጋይ ኢትዮጵያዊ ለኢሳያስ ጥብቅና የሚቆመው? ስብሃት ነጋ ኤርትራዊያን ባደረጉት ትግል የትግራይን ወጣቶች በመገበር “ኢትዮጵያን አቸነፍን!” እኮ ነው ያለው፤ ኢትዮጵያን ጥላቻው ያን ማድረግ አስችሎት ነው! ታዲያ አሁን የኢትዮጵያ ጥላቻ ነው ኢሳያስን ለመደገፍ ያስነሳችሁ? ኧረ ወዴት! ወዴት! ኢትዮጵያ ሌላ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሌላ! የኢትዮጵያ ጠላትና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጠላት ጊዜያዊ አንድነት ቢኖራቸውም፤ ቋሚ የሆነ ቁስል የለባቸውም። አንድ አይደሉም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጊዜያዊ እንደመሆኑ መጠን፤ ጠላቶቹም ጊዜያዊ ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ ዘለቂ እንደመሆኗ መጠን፤ ጠላቶቿም ከዚህ ሕልውናዋ ጋር የተያያዙ ናቸው። ኢሳያስ ሲነሳም ሆነ አሁን፤ እንደ የትግሬዎች ነፃ አውቺ ግንባር የኢትዮጵያ ጠላት ነው።
ኢሳያስ አፈወርቂ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ያለው ዝምድናና ጠብ ውስን ነው። ትናንት እጅና ጓንት ነበሩ። ዛሬ ደግሞ የሥልጣን ጥማቱ ለያይቷቸዋል። ነገ ሙርጣቸውን ሊገጥሙ ይችላሉ። አዎ! ኢሳያስ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ በበለጠ መንገድ ኢትዮጵያን እንዲጨፍርባት ለሚፈቅድለት አሽከሩ ይረዳል። ከዚያ በተረፈ ግን፤ ሎጅክን ባናቱ ደፍቶ የኔ ነው ለማለት ከመቃጣት በስተቀር፤ ከኢሳያስ ጋር ሆኖ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን መውጋት ቅዠት ነው። ደግሞ በዓለም አደባባይ እንዳይወቀስ የየግል ፈርማችንን መጠየቅ! አይጣል! በዚህ ተግባር የሚጠቀመው ማነው? ኢሳያስን ለማስደሰት የሚደረግ ሩጫ፤ አንድም በእውነት ለኤርትራ ዴሞክራሲያዊ መብት በሚታገሉ ኤርትራዊያን ዘንድ፤ አልፎም በጭቁኑ የኤርትራ ወገናችን ዘንድ ያስተዛዝበናል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሆነ የኢሳያሱ ሻዓቢያ፤ በየጎናቸው አንዱ የሌላውን ተቃዋሚ ሸጎጦ ማስፈራሪያና በሀገር ውስጥ ማተራመሻ መሳሪያ አበጅተዋል። እኒህ ከዚህ በላይ ሊያደርጉት የሚችሉት ሌላ ሙያ የሌላቸው ድርጅቶች፤ ከአሻንጉሊትነት በተረፈ ፋይዳ ቢስ ናቸው። በዚህ ኢሳያስን የተባበሩት መንግሥታት እንዳይቆጣብን ሩጫ የታዘብኩት፤ አሁንም ይሄኑ አሽከርነታቸውን ብቻ ነው።
ከላይ ለጠቀስኳቸው ሽማግሌ የሠጠኋቸውን መልስ እዚህ እደግመዋለሁ። ታጋይ ኢትዮጵያዊያን የጎደለን ነገር ቢኖር፤ ጠበንጃ ለመለመን ከግሩ ስር የምንወድቅለት የሀገር መሪና የሽምቅ ውጊያ ለማድረግ መቆናጠጫ የድንበር ቦታ አይደለም። ትግሉ የጎደለው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊ የሆነ የትግል ማዕከል ነው። ይሄን ስል፤ የነገዋን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ የሚያደላድል ነጥሮ የወጣ ራዕይ፣ ሰፊውን ኢትዮጵያዊ በአንድነት የሚያሰባስብ ድርጅትና፤ ራሳቸውን ለትግል የለገሱ ከራስ ወዳድነትና ከሥልጣን ብልግና የራቁ መሪዎችን ነው። በርግጥ እኒህ መሪዎች ከሰማይ እንደጉም አይዘገኑም፤ ራዕዩም ከሱቅ አይገዛም፤ ታጋዮችንም ኑ በማለት መሰብሰብ አይቻልም። ሆኖም ግን፤ አሁን ባለው የሀገራችን የኢትዮጵያዊያን የኑሮ ሁኔታ፣ በስደት ተበታትነን ከምንገኘው ኢትዮጵያዊያን የትግል ሩጫ፣ ይህን አንጥሮ ማውጣት አያዳግተንም። እንቅፋት የሆነብን፤ የራሴን ድርጅት የሚል የግለኝነት ፍቅር ነው። ይሄን ለመፍታት ደግሞ የሚያስፈልገን፤ ሀገራዊ ውይይት ነው። በዚህ መንገድ ወደ አንድ ልንመጣ የምንችልበትን መንገድ መንደፍ እንችላለን። በርግጥ በዝርዝር ይሄን ቢደረግ ያ ይከተላል ተብሎ አንድና አንድን እንደመደመር ቀላል አይደለም። ነገር ግን፤ ሀገራችን ባለችበት ሀቅ፤ ሀገር ውስጥ ያለውም ሆነ እየተሰደድ ያለው ኢትዮጵያዊ እየደረሰበት ያለው ስቃይ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለምንል ሁሉ፤ ቅደም ተከተሉን ረጋ ብለን እንድናይ ያስገድደናል። ያ ካልሆነ፤ ኢትዮጵያ ነኝ ማለታችን ምን ትርጉም አለው? የኔ ፓርቲና የኔ መሪ ብለው አባላት የሚነሱት እኮ፤ ሊያወዳድሯቸው የሚችሉ የተለያዩ ፓርቲዎች ኖረዋቸው፤ ከዚህ ያኛው ብለው ምርጫ ሲኖራቸው ነው።
አሁንኮ የሀገር ጉዳይ ነው የያዝነው! ሀገሪቱ ደግሞ የሁላችን ናት። የማንም የፖለቲካ ድርጅት የግል ሀብት አይደለችም። በኔ እምነት፤ አሁን እያንዳንዱ ድርጅት የሚታገላው ለራሱ ድርጅትና የትግሬዎችን ነፃ አውጭI ግንባር ለመተካት ነው። ሀገር ደግሞ በዚህ መንገድ ነፃ አትወጣም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወራሪ ድርጅት ነው። ከወራሪነቱ አልፎ ኢትዮጵያን እየበጣጠሰና አዘቅት አየከተተ ያለ ድርጅት ነው። እናም እያንዳንዳችን ኢትዮጵያን ሁሉ ይሄን ወራሪ ድርጅት ለማውደም አብረን በአንድነት መነሳት አለብን። ይሄን ለማድረግ ደግሞ በአንድነት በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ መነሳት ነው። የያዝነው የትናንት ትግል አይደለም። የያዝነው የአሁን፣ የሕልውና ትግል ነው። በምንም መንገድ ተደራጁ በምንም፤ እኒህ ድርጅቶች የሚያደርጉት ትግል የራሳቸው የድርጅታቸው ትግል እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አይደለም። ባሁኑ ሰዓት “ለጊዜው ይርዳን እንጅ በኋላ ዞር በል እንለዋለን!” ማለት፤ ከፖለቲካ ሽርሙጥናው ውጪ፤ አቋም የለሽ መሆን ነው። በራስ አለመተማመን ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ፍላጎትና አቅም አለመተማመን ነው። ሙልጭልጭነት ነው። እንደ ዕውነቱ ከሆነ፤ በጭቁኑ የኤርትራ ሕዝብ ላይ ማፌዝ ነው። ይሄን የሚያስብ፤ እንኳንስ ለዴሞክራሲ ሊቆምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምፁን ሊያሰማ ቀርቶ፤ በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ በኤርትራ አንገቱን ሊያቀና የሞራል ብቃት የለውም።
ይልቁንስ ባሁኑ ሰዓት መላ ታጋዩን ክፍል በአንድነት ለማሰባሰብ መደረግ ስላለት እርምጃ መነጋገሩ ግዴታ ነው። ትግሉ በምን መንገድ ይካሄድ የሚለው ከዚያ በኋላ ያ ስብስብ የሚተልመው ነው። በርግጥ ትግሉ እየተካሄደ ነው። እየተካሄደ ያለው ግን፤ ሀገር ውስጥ በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ እንጂ በውጭ አይደለም። በየቤቱ አባትና እናቱ በተወለዱበት ቦታና ማንነት የተነሳ፣ አሁን ባለበት ቦታ ምክንያት፣ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ባለመስገዱ የተነሳ፣ አንገቱን ለምን አልደፋም ተብሎ፤ በስራ አጥነት፣ በምግብ ማጣት፣ በበሽታ፣ በድርቅ፣ በድንቁርና፣ በማጣት እየተሰቃየ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተበታተነ መልክና የየራሱን በደል አንስቶ፤ እምቢ እያለ ነው። የሚገርመው፤ በውጭ አንጻራዊ ነፃነት ኖሮን፣ በኑሮም የተሻለ ሁኔታ ላይ ያለነው ለዚህ የሚታጋል ወገናችን አልደረስንለትም። አልፈን ተርፈን እኔ ነኝ ወኪሉ የለም እኔ ነኝ እያልን እንነታረካለን። በሚያስገርም ሁኔታ እርሰ በርሳችን ጠላታችን ከሆነው የበለጠ በመጠላላት ተናክሰናል። የወሬ ትግል ኒሻናችን፤ ደረታችንን አሳምሮታል። የሚገርመው፤ የትግሬዎች ነፃ አውቺ ግንባር የያዘውን አጀንዳ ፀረ-ኢትዮጵይ አጀንዳ የያዙ ድርጅቶች የትግሉን መስክ አጥለቅልቀውት፤ የሚቀጥለው ምን ሊመጣ ይችላል? የሚለውን አጨፍነውታል። እውነት ኢትዮጵያ ትኖር ይሆን የሚል ጥያቄ ባየሩ ተንሳፏል። በግልጽ እንነጋገር! የሚገባንን እያደርግን አይደለንም።
አንድ ጠላት፣ አንድ ትግል፣ የሕዝብና የሀገር አንድነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የያንዳንዷና የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግለሰብ መብት መከበር፣ ሀገራዊ ፖለቲካው ከክልልና ከሃይማኖት ነፃ እንዲሆን፣ ይሄን ገዥ ቡድን አስወግዶ ከሕዝቡ በቀጥታ የተውጣጣ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ብለን፤ መላ ታጋይ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስብ አጀንዳ ካልያዝን፤ አሁንም ዓመታት ቆጠራን ሙያ ማድረግ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ሰኔ ፮ ቀን፤ ፳፻፰ ዓመተ ምህረት
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply