ነገሩ ግራ የገባው ነው!
ለመሆኑ አሳባችን ምንድነው? እንዲሁ ስንጨቃጨቅና ስንነካከስ ምን ያህል ልንዘልቅ ነው? ንትርኩና መተላለፉ እጅ እጅ ብሎንና ሰልችቶን ሁሉን ትተን የእርቅ ያለህ! ለማለት ጊዜው ለመሆኑ መቼ ይሆን? ከጥል ወደ ፍቅር፤ ከመከፋፈል ወደ አንድነት፤ በስምምነት ለማደግ ቀጠሮ የያዝነው ለመቼ ነው?
በፖለቲካው ውድድር ውስጥ ያለንን የበላይነት ለማስከበር የሞት የሽረት ትግል ስለምናካሄድ፤ የጋራ የሆነውንና የሁላችንም ችግር የሆነውን ይህን የእርቅ ጥያቄ እንዲስተናገድ ማን ቦታ ይስጠው? ይህ የእርቅ ችግር ግን እንደ ድልድይ ሆኖ ሁሉንም ጎራ ያገናኝ ነበር። በራሱ ችግራችንን ሁሉ ባይፈታም እንደ ጥሩ መነሻ ያገልግላል።
ይህ የጋራ የሆነ የእርቅ ጉዳይ መደማመጥን ሊጠይቅ ነው። እኛ ደግሞ የለመድነው ሌላ ነው። ታዲያ ስንተላለፍና ስንዘላለፍ ችግራችንን አክርረነው እና ነገራችንን እጡዘነው የባሰ ተራርቀን እንታያለን። ሁላችንም ነገርን የምናየው በየራሳችን መነፅር ብቻ ስለሆነ ሌላው የሚናገረው አይገባንም። ስለዚህ ሁልጊዜ መተላለፍ ብቻ ሆኖብናል።
አይዞን!
እግዚአብሔር ስለ ተስፋው ቃል እንዲህ ሲል ይናገራል
“አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጥቅጠህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።”(መዝሙር 74፥14)። “የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር (አሞጽ9፥7) “ኢትዮጵያ ፈጥና እጆቿን ወደ አግዚአብሔር ትዘረጋለች። (መዝሙረ ዳዊት 68፡31)
ምድራችን የመሪዎቻችንን ክብር ስታስተናግድ ለዘመናት ኖራለች። እጃችንን ስንዘረጋ ደግሞ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔርን ክብር ታስተናግዳለች።
የእስራኤል ሕዝብ ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ያዕቆብ እስራኤል በመሆን የቃል ኪዳኑን ሕዝብ መሰረተ።
የኢትዮጵያ ጥሪ ግን በሕዝብ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እጆቿን በመዘርጋት የተስፋው ቃል ሕዝብ ትሆናለች። ለሕዝቡም ምግባቸውን ይሰጣቸዋል። ይህም ተጽፏል። ስለተጻፈም ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው።
እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ዓይናችንን ከሰው ላይ አንስተን ፈጣሪያችን ላይ እንድናደርግ ይጠራናል። የሚያስተሳስረንም በእግዚአብሔር ያለን እምነት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የማንኛውም አንድ ሃይማኖት አገር ሳትሆን በእግዚአብሔር ስር ያለች የፍቅር አገር ያደርጋት ዘንድ እናምናለን።
ምልክት ይሁነን!
ባንዲራችንን የቃል ኪዳን ምልክት እናድርገው።
መላ ከላይ ይምጣልን ስንል ለምልክት ባንዲራችን የተስፋችን አመልካች የሆነው የተዘረጉ እጆች ይኑርበት። ስሙኝና።
ባንዲራችን እኛን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ይታወቃል። በባንዲራችን ላይ ያለው አርማችን ግን መንግሥት በተቀየረ ቁጥር እየተቀየረ ዕድሜው በመንግሥታት ዕድሜ ልክ ብቻ የሚቆጠር መሆኑ ይታወቃል።
መላው ጠፍቶን እጆቻችንን እንደዘረጋን አምላክ ይወቅልን ስንል ኢትዮጵያ ከጥሪዋ ጋር የሚሄድ አርማ (የተዘረጉ እጆች) በባንዲራችን ላይ እንዲያርፍበት እናድርግ የሚል ምኞት አለኝ።
ይህ ዓርማ ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ቢቀመጥ ሊሰጠን ያለውን ምልክት በጥቂቱ እንመልከት።
1ኛ/ የተሰጠን ዓርማ ከአምላክ የተወሰነልንን የበረከት ጥሪ ለመቀበል እሺ በማለት እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንዲባርካት ፍቃደኝነታችንን ያሳያል።
2ኛ/ የተሰጠን ዓርማ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነት ያንፀባርቃል። የሰዎች ምኞት የሚያንፀባርቅ ሳይሆን የተስፋው ቃል ሕዝብ ለመሆናችን ምስክር ይሆናል።
3ኛ/ የተሰጠን ዓርማ ከማናቸውም መንግሥታት ጋር ስለማይወግን ዘላቂነት ይኖረዋል።
4ኛ/ የተሰጠን ዓርማ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ሃሳብ እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው የፈጠረው አይደለም። ስለዚህም ከአምላክ የተሰጠን ስጦታ ነው።
5ኛ/ የተሰጠን ዓርማ በሺህ የሚቆጠር ዘመን ታሪክ ያለው ታሪካዊ ነው። ስለዚህም ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ታሪካዊ ለሆነችው አገራችን ምቹ ነው።
6ኛ/ የተሰጠን ዓርማ ለኢትዮጵያ ብቸኛ መለያ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የብዙ አገሮች ባንዲራ ኮከብ አለበት።
7ኛ/ የተሰጠን ዓርማ ከማናቸውም ሃይማኖት ጋር አይወግንም። ከማናቸውም ሃይማኖት ምልክቶች ጋር አይያያዝም። ሃይማኖት እንደማይከፋፍለን ምልክት ይሆንልናል።
8ኛ/ የተሰጠን ዓርማ በፊት ለአፍሪካ ኩራት የነበረውን ባንዲራችንን ለዛሬ የአፍሪካ ተስፋ በማድረግ ይበልጥ ያከብረዋል።
9ኛ/ የተሰጠን ዓርማ ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች አገር ብትሆንም ቅሉ በሃይማኖት ሳንከፋፈል በመያያዝ እዲስ በሆነ መልክ የእግዚአብሔርን እርዳታ ጠይቆ ማግኘት ምን እንደሚመስል ለዓለም ያበስራል።
10ኛ/ የተሰጠን ዓርማ እግዚአብሔር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገፅታ ለውጦ የዓለም ሞዴል ሲያረጋት ለእግዚአብሔር ታማኝነትና ታላቅነት መታሰቢያ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ሆይ፡ ምርጫሽ የቱ ይሆን?
——
ዶ/ር ዘላለምን ለማግኘት በዚህ አድራሻ መጻፍ ይችላሉ፡ one@EthioFamily.com
Leave a Reply