ቫላንታይንስ ዴይ (ፍቅረኞች ቀን) ከወደ ምዕራቡ ከተዋስናቸው ወይም ከተጫናቸው በዓላት አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል በእኛ ዘንድ አሁን ያገኘውን ያህል ተቀባይነት እንዲያገኝ ከማድረግ አንጻር የብዙኃን መገናኛዎች በተለይም የኤፍ ኤም ሬዲዮዎች(ነጋሪተ ወጎች) ዐቢዩን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የብሔራዊው የብዙኃን መገናኛውና ሌሎች የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ጣቢያዎችም እንደዚያው ቁምነገሬ ብለው ይዘውታል፡፡ የብዙኃን መገናኛዎች በተለይም የኤሌክትሮኒክሱ (በአየር ሞገድ የሚሠራጨው) በመልካም ጎንም ይሁን በመጥፎ ጎን ለሚመጣ ውጤት ታላቅ ጉልበት አላቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ባጠቃላይ ለደረሰብን የባሕል ወረራና ጥቃት በዚህ የብዙኃን መገናኛ ከበጣም ጥቂቶቹ በስተቀር “የመዝናኛ ዝግጅት” በሚል ሥያሜ የአየር ሰዓት የወሰዱ እንደዜጋ የሀገርንና የሕዝብን እሴት ሀብት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸውና እንዴትም እንደሚጠበቅ ምንም የማያውቁ ወይም መጠበቅ የማይፈልጉ ከመናኛ የግል ጥቅማቸው ባለፈ ይሄንን ከባድ ኃላፊነት ለመረዳት የአቅም ውስንነት የገደባቸው አዘጋጆች ይሄንን ዕድል ለነሱ ከሰጧቸው አካላት ቀጥሎ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦች ጀርባም ደግሞ ጨርሶ ኃላፊነት የማይሰማቸው የተለያዩ ስግብግብ የንግድ ወይም የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ፡፡
ቫላንታይንስ ዴይ (የፍቅረኞች ቀን) ከባሕላችን አንጻር እንዴት ይታያል?
ቫላንታይንስ ዴይ ይጠቅማል አይጠቅምም ወደ ሚለው ከመሔዴ በፊት ይሔንን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ባሕላችን በነገራችን ላይ “ባሕላችን” ብየ ስል ንጥሩን(ኦሪጂናሉን) ማለቴ እንጅ ለምሳሌ አሁን አዲስ አበቤ ነን የምንለው እየኖርነው ያለውን በዘመናዊነት ሽፋን በባዕዳን ባሕል የተበከለውን ወጥነት ያጣውን ባሕል ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር ስናየው ሲጀመር ባሕላችን ፍቅረኝነትን ማለትም ከጋብቻ ውጪ ወይም በፊት የሚደረግን ፆታዊ ወዳጅነትን የሚያውቅና የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በእኛ ባሕል የፍቅር ሕይዎት የሚኮመኮመው በትዳር ውስጥ ነው፡፡ በእርግጥ ባሕላችን እጮኝነትን ያውቃል፡፡ ይሁን እንጂ የእጮኝነት ወቅት እሷ የሱ እሱ የእሷ መሆናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የፍቅር ሕይዎት ሊባል በሚችል ደረጃ ፍቅር የሚኮመኮምበት አይደለም፡፡ በመታቀብ ውስጥ ሆነው አንድ የሚሆኑበትን ቀን የሚጠብቁበት ወቅት ነው እንጂ፡፡
ይህ ቁጥብነት የተሞላበት ክቡር ባሕላችን ምን ያህል ክብርን፣ አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ንጽሕናን የጠበቀ እንደሆነ ከጋብቻ በፊት በሚደረጉ ፆታዊ ግንኙነቶች ከሚፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች የጸዳ እንደሆነ መረዳት የሚሳነው ሰው ይኖራል ብየ መገመት እቸገራለሁ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከባሕላችን ጋር ተቃርኖና ተጻርሮ ያለውን ግላዊና ማኅበራዊ ሕይዎታችንን አደጋ ላይ የሚጥልን ምዕራባዊ ባሕል ለማዋሐድ መሞከር ምን ያህል የተሳሳተ ብቻ አይደለም ኃላፊነትና ማስተዋል የጎደለው እንደሆነ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ይህንን የምዕራባዊያን ድርጊት ወይም ባሕል መዋሱ ትክክል ይሆን የነበረው ከላይ የገለጽኩት ባሕላችን የተገለጸውን ዓይነት መሆኑ ከሞራል (ከግብረ-ገብ)፣ ከሥነ-ምግባር፣ ከላቀ ሰብእና እነፃ፣ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ወዘተ. አንጻር ችግር ያለበትና ነውረኛ ቢሆን ነበር፡፡ እንደምናየው ግን ያለው እውነታ የሚያሳየው ይህንን አይደለም፡፡ ከጋብቻ ውጪ ፆታዊ መወዳጀትን መቀበላችን የሰውን ክቡርነት፣ የሕይዎትን ዋጋ ውድነትና ልዕልና ተቀብሎ ከተቀረጸው የጸዳና ኃላፊነት የተሞላበት ወይም የሚሰማው ባሕላችን መተዋችን የዚህን ተቃራኒ ውጤት ወደሚያመጣ መሔዳችን መውረዳችንን መዝቀጣችንን እንጂ ከፍ ማለታችንን መላቃችንን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ያለንን የነበረንን ባሕል ልንንቅ ልንለቅና ልንለውጥ የምንችልበት አንድም አመክንዮ የለም ማለት ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ይሄንን የባዕድ ባሕል ወደ ባሕላችን ስንቀላቅል እጅግ መሳሳትና መውረድ መሆኑ እርግጥ ነው ማለት ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን በአመክንዮ ያልደገፍነው ወይም ልንደግፈው ያቃተን አስተሳሰብ ሥራ ላይ ስናውል ችግር ማጋጠሙ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ይሆናል፡፡ ምናልባት ይህ የጸዳው ባሕላችን የኑሮ ዘይቤ ጊዜ ያለፈበትና በዚህ ዘመን የሚኖረውም የሌለ ተደርጎ ይታሰብ ይሆናል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ነገር ግን ፍጹም የተሳሰተና ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ እንደሆነ አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85% በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖርና ይህ የእኛ ባሕል ነው ብየ የገለጽኩትን የኑሮ ዘይቤ የሚኖር ነው፡፡ በባሕል መበረዝ እየተበከለ ያለው ሕዝብ በተቀረው 15% ከተማ ነዋሪ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ያም ቢሆን ሁሉም የከተማ ነዋሪ ለባሕል መበረዝ እጁን የሰጠ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ስለዚህ ባሕላዊ እሴታችን መጠበቅ መከበር ማንሰራራት ለማውራት መምሸት አይደለም ገናም አልረፈደም፡፡
አንድ ጊዜ ምን ገጠመኝ መሰላቹህ ከፌስ ቡክ (ከመጽሐፈ-ገጽ) ጓደኞቸ አንዱ አንድ ፎቶ(ምስለ አካል) ለጥፎ ዐየሁ፡፡ በምስለ አካሉ ላይ ላሊበላ ቤተ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ የባሕል ልብስ የለበሱ ወንድና ሴት ሆነው ወንድየው ከሴቷ ፊት ተንበርክኮ የጋብቻ ቀለበቱን እያሳያት እሷ በድንገቱ በመገረም አፏን በእጇ ጭና ያሳያል፡፡ በዚህ ምስለ አካል በርካታ የመጽሐፈ ገጽ ተጠቃሚዎች ደስ በመሰኘት ምስለ አካሉን ተጋርተው በየራሳቸው መጽሐፈ ገጽ ለጥፈውት ነበር፡፡ እኔ ግን ነገሩ አልተመቸኝም ነበርና ከስሩ ይሄንን አስተያየት አሰፈርኩ፡፡
ወንድሜና እኅቴ በቅድሚያ ለዚህ ስላበቃቹህ እንኳን ደስ አላቹህ፡፡ ስቀጥል የተሰማኝን እንድገልጽ ከፈቀዳቹህልኝ እኔ በዚህ ምስለ አካል ላይ አልተደሰትኩም፡፡ ምናልባት የባህል ልብስ ባታደርጉና ቦታውም ሌላ ቦታ ቢሆን ትንሽም ቢሆን መከፋቴን በቀነሰልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የባሕል ልብሳችንን ግጥም አድርጋቹህ እንዲህ አምሮባቹህ በዚህ በተቀደሰውና የኢትዮጵያዊነትን ልዕልና በሚመሰክረው ቦታ ላይ ከምዕራቡ ዓለም የተወሰደን ድርጊት መፈጸምህ ምን ያህል እንዳመመኝ ለመግለጽ እቸገራለሁ፡፡ እንደምታውቀው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያዊ የሆኑ እሴቶችን ሁሉ በመቅረጽ በመጠበቅና በመንከባከብ ትታወቃለች፡፡ ይሄንን ተግባር ስትፈጽምም ሌላ ፈጻሚ አካል ኖሮ ሳይሆን እኛው ልጆቿ አባቶቻችንን ፊት አውራሪ አድርገን ነበር ይሄንን ከባድ ኃላፊነት ስንወጣ የኖርነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሳለ ታዲያ እንዳለፉት ትውልዶች ሁሉ ማንነቱን ይጠብቅ ዘንድ ይልቁንም አሁን ካለብን በሉላዊነት(globalization) ከተሸፈነ ጫናና የባሕል ወረራ አንጻር ካለፉትም ትውልዶች በተሻለ ብቃትና ጥንካሬ ማንነቱን ለመጠበቅ ከባድ የታሪክ ኃላፊነት ከተጣለበት ከዚህ ትውልድ አካል የሆናችሁት ከባሕላችን ውጭና ባዕድ የሆነን ድርጊት የኢትዮጵያዊነትን ልዕልናና ድል በሚመሰክረው ሥፍራ ላይ ስታደርጉት ሳይ በጦርነት ድል ተደርገን በግዛታችን ላይ የጠላት ሰንደቅ ቢውለበለብ ሊሰማህ የሚችለውን ዓይነት የሚተናነቅ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡
በእኛ ባሕል እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ቦታ የለውም ሲጀመርም አንተ እሷን እሷም አንተን ስትቀራረቡ በምን ዓይነት አቀራረብ ለምን ዓይነት ጉዳይ እንደሆነ ማለትም ለትዳር መሆኑን ተማምናቹህ አስቀድሞ የጨረሳቹህት ወይም እንደምትጨርሱት የሚጠበቅ የሚታሰብ በመሆኑ ይህ ድርጊትህ ከባሕላችን አንጻር በጣም የራቀና የተሳሳተ ነው፡፡
ወደ ምዕራቡ ዓለም ዜጎች ስትሔድ ግን አንድ ወንድና ሴት በፍቅር መጎዳኘት ሲያስቡ ሦስት አማራጮች ክፍት በሆኑበት ሁኔታ ነው፡፡ ምን ማለቴ መሰለህ ትዳር የሚለው ነገር ከፊት ለፊት ያለ አማራጭ ሳይሆን መጨረሻ ደረጃ ላይ ያለ አማራጭ ነው፡፡ በየደረጃው አንደኛውን አማራጭ እየኖሩ ግንኙነታችን ተመችቶናል ወደሚቀጥለው ደረጃ ይደግ እያሉ ነው መጨረሻ ላይ ትዳር ላይ የሚደርሱት፡፡ ትዳር ብለው የሚሉትም የእኛ ባሕል ለትዳር እንደሚሰጠው ትርጉምና ክብር ክብደት ዓይነት እንዳይመስልህ፡፡ በተመሠረተ በቀናት ልዩነት ሁሉ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ትዳራቸው ጣጣውና ችግሩ ብዙ ነው ይሄን ለመዘርዘር ጊዜ የለኝም ዋነኛው ችግሩ የሚመነጨው ግን አስቀድሞ በነበረው ግንኙነት ወቅት ፍቅራቸውን አጣጥመው ጨርሰው አርጅቶ ስለሚገቡበት ትዳር ውስጥ አዲስ ነገር በማጣት በቀላሉና ወዲያው የመሰለቻቸት ችግር ከማጋጠሙ የተነሣ ነው፡፡
ከእነዚህ ሦስት አማራጮች የመጀመሪያው አማራጭ ላልተወሰነ ጊዜ በመሀከላቸው ጥል ተፈጥሮ እስኪራራቁ ጊዜ ድረስ ወሲብን ጨምሮ በፍቅር ውስጥ ልንፈጽማቸው ይገባናል የሚሏቸውን ነገሮች ሁሉ እየፈጸሙ የሚኖሩበት አማራጭ ነው፡፡ ግንኙነቱ የፍቅር ጓደኝነት (love friendship) ይባላል፡፡ በዚህ ሕይዎታቸው ደስተኞች ከሆኑ ልክ አሁን አንተ እንዳደረከው ወንድየው ተዘጋጅቶበት ይቆይና በድንገት የጋብቻ ቀለበቱን በማውጣት ግርምት ወይም ድንቀት(surprise) በመፍጠር ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ ሴቲቱ ያሳለፉት ሕይዎት ለሷም ከተመቻት ፈቃደኛነቷን በመግለጽ በእሽታ ትቀበለውና ለጋብቻ ይበቃሉ ማለት ነው፡፡ ከሁለቱ አማራጮች መሀል ደግሞ አንድ ሌላ አማራጭ አላቸው እድሜአቸው ገፋ ሲል ወይም ደግሞ ፍቺ የፈጸሙ የሚኖሩት ኑሮ ነው እሱም ልክ ትዳር እንደመሠረቱ ጥንዶች ሁሉ ወንዱና ሴቷ ትዳር ሳይመሠርቱ በአንድ ቤት የሚኖሩበት አማራጭ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሕይዎት ሲኖሩ ግንኙነቱን የወሲብ አጋርነት(sexual partnership) ይሉታል ወንዱ ሴቷን አጋሬ ሲላት ሴቷም ወንዱን እንደዚያው፡፡ ሲበቃቸውም የሚቀደድ ሰማኒያ ሳይኖር በቅተሽኛል በቅተኸኛል ሳይባባሉ እንደወጡ የሚቀሩበት የግንኙነት ዓይነት ነው፡፡
ወንድሜ ከእነዚህ ደረጃዎች ጀርባ ከሃይማኖትና ከባሕል አንጻር የሚወገዙ ስንት አስተሳሰቦች አሉ መሰለህ፡፡ እንዱንና ዋነኛውን ብነግርህ “መጣጣምን” ለማወቅ ሲባል እንደሆነ ያወራሉ፡፡ እንግዲህ ከነዚህ ከነዚህ ጉዳዮች አንጻር ነው ይህ አሁን አንተ ያደረከው ድርጊት ያልተመቸኝ፡፡ ከጀርባው እንዲህ ያለ ከእኛ ባሕልና ሃይማኖት አንጻር የሚቃረን የሚወገዝ የማይበረታታ የሕይዎት ጉድ ያለበት በመሆኑ ይህ ያደረከው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ምናልባት ግን ይህ ያደረከው ነገር ምንም እንኳ የምዕራባዊያኑ እንጂ የእኛ ባይሆንም ቅሉ በገለጽኩት ዓይነት የምዕራባዊያን የፍቅር ሕይዎት ሳታልፉ ማለትም ከጋብቻ በፊት በግብር ሳትተዋወቁ (ወሲብ ሳትፈጽሙ) ቆይታቹህ በእግዚአብሔር ቤት እንዲህ ዓይነቱን ቃል የተቀደሰ ጥያቄ ባቀርብ ተገቢ ነው ብለህ አስበህ ጥያቄውን አቅርበህ ከሆነ ይቅርታህ ይድረሰኝ፡፡ ነገር ግን እሱም ቢሆን አሁንም በባሕላችን በሃይማኖታችንም ቀለበት የሚታሠረው በካህን ቡራኬ በመሆኑ ይህ የገለጽክበት መንገድ ትክክል አይደለም ማለት ነው፡፡ እናም ወንድሜ ግድ የለህም ይህ ምስለ አካል(ፎቶ) በተለይ ደግሞ በእግዚአብሔር ቤት የባሕል ልብሳችንን በለበሳቹህ ምእመናን መፈጸሙ ምን ያህል ለምዕራቡ ዓለም የባሕል ወረራ መንበርከካችንን መሸነፋችንን መማረካችንን እጅ መስጠታችንን ነውና የሚያሳየው እባክህን አንሣው? ብየ አስተያየቴን አሠፈርኩ፡፡ እሱም እግዚአብሔር ይስጠውና ጥፋት መሆኑን ተረዳ መሰለኝ ያንን ምስለ አካል ወዲውኑ አነሣው፡፡
እንግዲህ ቫላንታይንስ ዴይ ተብሎ እየተከበረ ያለው የምዕራባዊያኑ በዓል በእንዲህ ዓይነት “የፍቅር” ገጽታና ቅኝት ስለሆነና እዚህም እየተከለ ያለው ተመሳሳዩን ገጽታና ቅኝት በመሆኑ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሠረቱ ካደረገው ባሕላችን ጋር ፍጹም የማይስማማና የማይጠቅምም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለነገሩ በምዕራቡም ዓለም ቢሆን ይህ በዓል ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ያለው በዓል አይደለም፡፡ የዚህ በዓል ታሪካዊ ዳራ የካቶሊኮች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፕሮቴስታንቶች አይቀበሉትም፡፡ እነዚህ ሁለቱ እምነቶች “በሃይማኖት” ልዩነት ምክንያት በተለያየ ጊዜ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አውሮፓ ጦርነት ወይም ግጭት እስከማድረግ የደረሱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አንደኛው ለሌላኛው እሴት አክብሮት የለውም፡፡ በመሆኑም ፕሮቴስታንት የሆኑ ሀገራት ቦታ የሚሰጡትና የሚያስቡት በዓል አይደለም፡፡ ጨርሶም የማያውቁት አሉ፡፡
የአበባ ስጦታና ባሕላችን ያላቸው ግንኙነትና ቁርኝት?
ከቫላንታይንስ ዴይ ጋራ ተያይዘው ከሚከወኑ ኩነቶች ውስጥ የስጦታ ልውውጥ በተለይም የአበባ ስጦታ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እኛ ኢትዮጵያዊያን የአበባ ስጦታ የማበርከት ባሕል እንደሌለን አድርገው ያስባሉ፡፡ እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ እንዲያውም ሲመስለኝ ሲመስለኝ ፈረንጆቹ አበባን የማበርከት ባሕል የወሰዱት ከእኛ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ በባሕላችን ምድረ አውሮፓ ከነመፈጠሩ እንኳ በማይታወቅበት ዘመን ለተለያዩ ጉዳዮች አበባን የማበርከት ልማድ ወይም ባሕል ስንፈጽም እንደኖርን ታሪካችን ያስረዳናልና፡፡ በቤተክርስቲያናችን ማለትም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አበባ እጅግ የከበረ ስጦታ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ባሕል ወይም እሴት ነው ተብሎ የሚታወቀውን ባሕልና እሴት በመቅረጽ በኩል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሚና ጎልቶ ይታያል፡፡ ያሉንን ኢትዮጵያዊ መገለጫ ያላቸውን ባሕላዊ በዓላትና ኩነቶችን መለስ ብለን ብናጤን ሃይማኖታዊ አሻራ የሌለበት አንድም እንኳን አታገኙም፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አበባ ለየት ያለ ሥፍራና አግልግሎት አለው፡፡ ለአብነት ያህል ሦስቱን እጠቅሳለሁ፡-
- ቤተክርስቲያን ካሏት አጽዋማት ውስጥ ዋነኛ በሆነው በዐቢይ ፆም መጨረሻ በሕማማት ሳምንት የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በሚታሰብበት ቀን በመስቀሉ ስር ላይ ጽጌረጋ አበባ በመነስነስ ለክርስቶስ እንዲበረከት “ግብረ ሕማማት” የሚባለው መጽሐፍ በሚያዘው መሠረት በየዓመቱ ይህ ይፈጸማል፡፡
- “ጽጌ” ፆምን የተመለከተው ነው፡፡ የጌታንና የተወዳጅ እናቱን ወደ ግብጽ መሰደድ ለማሰብ የሚፆም ፆም ነው፡፡ የዚህች ፆም ሥያሜ “ጽጌ” የሚለው ቃል ሲተረጎም አበባ ማለት ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ቅዱሳን አባቶቻችን በመጻሕፍቶቻቸው እመቤታችንን በአበባ ስለመሰሏት አንዱ ምክንያት ሲሆን ልላኛው ምክንያት ደግሞ ወቅቱ የአበባ ወቅት ስለሆነ በወቅቱ ሲጠራ ነው፡፡
- ሌላኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድ ዓመታዊ በዓል አለ መስከረም 10 ይውላል፡፡ ሥያሜው “ተቀጸል ጽጌ” (አበባን ተቀዳጅ) ይባላል፡፡ ቤተክርስቲያን ንጉሡን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ የምትልበት በዓል ነው፡፡ የጸሎቱና የቅዳሴው ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ካህናት በደመቀ የዝማሜ፣ የማስረገጥ፣ የወረብ፣ የሽብሻቦ፣ መዝሙር ታጅቦ ንጉሡንና ንግሥቲቷን እንኳን አደረሳቹህ በማለት አበባ የሚያበረክቱበት በዓል ነበር፡፡
በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆኑ ባሕላዊ ከሆኑትም በዓላቶቻችን ሁለቱን ስጠቅስ አንደኛው ድርጊቱ ከንግሥተ ሳባ ና ከእንቁጣጣሽ ታሪክ ጋራ ተያይዞ ይጠቀስ እንጂ ከዚያ አስቀድሞም ይፈጸም እንደነበረ ይገመታል፡፡ እሱም ልጃገረዶች የአበባየሁሽን ጭፈራ እየጨፈሩ የአበባ ስጦታን ለወላጅ ለጎረቤት ለዘመድ አዝማድ እንኳን አደረሳቹህ እያሉ የሚያበረክቱበት በዓል ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የመስቀል በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል ሲከበር ደመራው የእኛ ብቻ በሆነውና ሌላ ቦታ ጨርሶ በማይበቅለው ሁሌም አዲስ ዓመትን በሚያበስረን አደይ አበባችን አጊጦ የሚደመረው በዓል ነው፡፡ እናም እነኝህ እነኝህ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የአበባና የሐበሻ ቁርኝት ቀደምቱና ጥንታዊው ታሪካችን ከሚጀምርበት አንሥቶ የነበረ በመሆኑ ከማንኛውም ሀገር የላቀና ለሌሎቹ አርአያ እንደሆነ በቀላሉ መታዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ ዘመን ሰው ግን እንዲህ ዓይነት ታሪኮቻችንን ስለማያውቅ የአበባ ስጦታ ወይም አበባን ማበርከት የእኛ ባሕል ያልሆነ ከባእድ የመጣ ይመስለዋል፡፡ እውነቱ ግን ከላይ እንደተገለጸው ነው፡፡ እናም አበባ ስታበረክቱ የእኛን የራሳችንን ባሕል እየፈጸማቹህ እንደሆነ በማሰብ እንጅ ከፈረንጅ በተውሶ የመጣን ባሕል እየፈጸማቹህ እንደሆነ ተደርጎ እንዳይታሰብ መጠንቀቅ ያሻል፡፡
ይህ “ቫላንታይንስ ዴይ” ባዕዳዊ በዓል ከማኅበራዊ ሕይዎት አንጻር እንዴት ይታያል?
ይህንን በዓል ከማኅበራዊ ሕይዎትም አንጻር ስናየውም የምንጎዳበት ወይም የምናጎልበት እንጂ የምናተርፍበት ሆኖ አናገኘውም፡፡ ብዙዎቻችን እንደታዘብነው ሁሉ በዚህ በዓል ቀን ወላጅና ልጅ ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ለአቅመ ሔዋን ባልደረሱ ሴቶች እኅቶቻችን ላይ ነው፡፡ በዚህ የእድሜ ደረጃ ያሉ ልጆችን በዓሉ በዚያ ሳቢና አባባይ ድምቀት ሲከበር ሲያዩ በሚፈጥርባቸው መነሣሣትና ጉጉት ያለ ወንድ ጓደኛ መሆናቸው ባዶነትና ወደ ኋላ መቅረት ወይም ያለመሠልጠን ሆኖ እየታያቸው ያለ ዕድሜያቸው የወንድ ጓደኛ እንዲይዙ ከባድ ጫና እያሳደረባቸውና ችግር ላይ እየጣላቸው ይገኛል፡፡ ጓደኛ ከያዙም በኋላ በሌሎች ጊዜያትም ሆነ በበዓሉ ቀንም በዓሉን ለማክበር በሚል ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር በሚሔዱባቸው ቦታዎች ላልጠበቁትና ላልፈለጉት ችግር መዳረጋቸው የተለመደ ዜና ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኤድስን ጨምሮ በሚከሰቱ የተወሳሰቡ ተያያዥ ችግሮች ቅድመ ጋብቻ ምንም ዓይነት ግንኙነት አለመጀመር መፍትሔ መሆኑ በታመነበት ዘመን ይሄንን መግባባት አፍርሶ እንደገና ወደ ኋላ የሚመልስን አፍራሽ ተግባር መከወን እውነት ያለመብሰል ብቻ ሳይሆን የለየለት ጠላትነትም ነው፡፡
በመጨረሻም ይሄንን ጣጣ ላመጡብን ምን እየሠሩ እንደሆነ በውል ለይተው ለማያውቁት “የመዝናኛ ዝግጅት” አዘጋጆች ማስገንዘብ የምሻው ጉዳይ አለ፡፡ አንድን ነገር ከሌላ አምጥታቹህ ከመዘርገፋቹህ በፊት እባካቹህ ከተለያየ አቅጣጫ ለመመርመር ሞክሩ፡፡ ይህን በማድረጋቹህ የምትጠቀሙት ነገር ቢኖርም እንኳ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ችግር የእናንተም መሆኑ አይቀርምና አስፍታቹህ ለማሰብ ሞክሩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይሄንን ዕድል የሰጧቹህን አካላት ከመለመን ከማሳሰብ ከማስገንዘብ ይልቅ እናንተን መለመኑ ማሳሰቡ ሳይሻል አይቀርም፡፡ አነሱ እዛ ላይ ቁጭ ብለው ምን እንደሚሠሩ እንደሚውሉ አልገባ ብሎኝ በጣም ተቸግሬያለሁ፡፡ እናም ወደናንተው ልመለስና እንዲሁ ስታስቡት የቸገረን ነገር ይሄና መሰል ድርጊቶች ናቸውን? ከዚህ ይልቅ ምናለ በቸገረንና ሊኖረን በሚገባው ነገር ላይ ብታተኩሩ ብትተጉ ብትረባረቡ? እንዲህ እንደቀላል የሚወራ ወሬ ስታጡ የአየር ሠዓት ለመሙላት ብቻ ቀበጣጥራቹህት የምትወጡት ነገር ለእናንተ ቀላል መስሎ ቢታያቹህም ሀገርን ማፈራረስ የሚያስችል አቅም አለው እያፈራረሰንም ይገኛል፡፡ እንደዜጋና እንደሚያስብ ሰው ይሄንን ላትረዱ የምትችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት ይኖር አይመስለኝም፡፡ ከስሜታዊነት ይልቅ ዕውቀትን ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን የማስቀደም የሐሳብ መሠረት ላለው ሰው ይህ ፈጽሞ የሚቸግር ጉዳይ አይሆንም፡፡
ልጆች በተለይም ሴቶች በትምህርት ላይ እያሉ ወደ እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት እንዲገቡ የማይመከረው ያለወቅቱ ወሲብ በመጀመራቸው ምክንያት ከወሲብ ጋራ ተያይዘው ተግተልትለው ከሚመጡት ዓይነተ ብዙ ሕይዎትን ከሚያሰነካክሉ ከባባድ ችግሮች ባሻገር ትኩረታቸው ሙሉ በሙሉ ስለሚሰርቅ አቅጣጫውን ስለሚያስተው ነው፡፡ ትምህርት በራሱ የሙሉ ጊዜ ሥራ ነው ሙሉ ጊዜን ለትምህርት አትኩሮት ሰጥተውትም ከስኬት ለመድረስ ስንት ፈተናዎች አሉት በዚህ ላይ ያለጊዜው ያለ ቦታው ፍቅር ውስጥ ከተገባ ለትምህርት ልንሰጠው የሚገባው ትኩረት ከመሰረቁ ጋር በተያያዘ ምን ያህል የብቃት መውረድ መንሸራተት መጎዳት ሊያጋጥም እንደሚችል በሁሉም ሰው ግንዛቤ ውስጥ ያለጉዳይ ነው፡፡ ፍቅር ቀናተኛ ነው ሙሉ ትኩረት ስጡኝ ባይ ነው፡፡ እንቅልፍና ምግብ እስከመከልከል ከዚያም አልፎ እስከማሳበድም ይደርሳል፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ ተገብቶ ትምህርን ያህል ከባድ ሥራና ኃላፊነት ወይም ጥናት እንደምን በብቃት መወጣት ይቻላል? ይሄም በመሆኑ ነው በተለይ ሴቶቻችን በየከፍተኛው የትምህርት ተቋማቱ የገቡትን ያህል ሳይሆን ለመጥቀስ በሚያሳፍር እጅግ በጣም እጅ ብቻ ለመመረቅ የሚበቁት፡፡ ከዚህ ችግር አምልጦ በትምህር መስክ ለስኬት ለመብቃት ያለው ብቸኛ አማራጭ ይደረስበታል የራሱ ጊዜ አለው በሚል የበሰለና አርቆ ማሰብ የታከልበት ውሳኔ ፍቅርን ከትምህርት ወይም ከምረቃ በኋላ መቅጠሩ ብቻ ነው፡፡ እንደምናየውም ትምህርታቸውን በብቃት ተወጥተው በግሩም ነጥብ የሚመረቁት እራሳቸውን ከእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ የቆጠቡት ናቸው፡፡
ወጣቱ ከዚህ የበሰለ ውሳኔ ደረጃ ላይ እየደረሰ በላቀ ብቃት ህልሙን እንዲያሳካ ለማስቻል የሁሉም ርብርቦሽ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የብዙኃን መገናኛው እጅግ ከባድ ኃላፊነት አለበት፡፡ እዚያ ላይ የተቀመጡ የየዝግጅቱ አዘጋጆች ባለሞያዎች ለመልካም ሰብእና ምሳሌና አርአያነት ያላቸው ሊሆኑ የግድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚታዩ ካልሆኑም ሁለተኛው አማራጭ ካሳለፉት ከየግል የሕይዎት ተሞክሮዎቻቸውና ከውድቀት ጥንካሬዎቻቸው ወጣቱ እንዲማር የማድረግ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን እኛንም የበላ ጅብ ይብላቹህ በሚል የደነቆረና እጅግ ኃላፊነት የጎደለው የምቀኝነት ፈሊጥ ምኑንም የማያውቀውን ወጣት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲነጉድና እንዲጠፋ ማድረግ ቃል ሊገልጸው የማይችለው ድንቁርናና ከጠላትነት የከፋ ጠላትነት ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ የተገለጹት ቁም ነገሮች ለማይዋጡለትና መናኛ የግል ጥቅሙ የሚበልጥበት የጥፋት ዓላማ ላለው የመከነ ዜጋ ግን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ልብ ይስጥልን ልብ የማይገዙና ሰይጣን ያገበራቸው ከሆኑ ግን ሳያጠፉን በፊት ይቅደምልን ጉልበታቸውን ቀጤማ ያድርግልን ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻላል ወገን?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Sanyii says
I swear before I knew who wrote this article I was thinkin this guy an hypocrit like Amsalu and surprise surprise I found to be Amsalu. Thank God it is not anohter perosn with a backward and hypocritical view as that of you.
Please widen your view, Ethiopianism is not being following Orthodox, speaking Amharic, having Amhara’s culture, etc. . That system has been defeteated by non-Amharic speaking people of Ethiopia. Ethiopia is no more “island of Christianity/Orthodos”. Go to Afar, Somali, Harari, Beneshangul, Oromiya, South, Wello, etc. and you may be stonned to death. You are writing the article for Ethiopians (Protestants, Muslims, Waaqqeefataa, and Orthodox) and you are not writing on Sm’a Tsidk or some conseravtive Orthodox magazine or paperI hoping EPRDF to change Federal working language to English and then you get what you deserve.
Ke’Egziabher belay ye’Egziabhern mebt lemaskeber atmokr. Yane antem endene ISIS t’honaleh.
Egziabher lbona yist’h!