የሃዘኑ ድባብ ከመብራቱ መቆራረጥ ጋር ተዳምሮ ጨለማውን አብሶታል። የአሁኑ መብራት መቋረጥ ግን ከወትሮ ፈረቃ ለየት ያለ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስላል። ከጥቂት ስፍራ በስተቀር ሁሉም ቦታ በአንዴ እንዲጠፋ ነው የተደረገው። ከሬድዋን ሁሴን እና ከሃይለማርያም የቴሌቭሽን ዲስኩር በኋላ ሃገሩ ሁሉ ጨለማ እንዲሆን አደረጉ። ይህንን ለማድረግም በቂ ምክንያት ነበራቸው። ሃዘን ያልወጣለት ህዝብ አደባባይ ወጥቶ በአረመኔ ወታደሮች ሲቀጠቀት በማህበራዊ ድረ-ገጽ እንዲታይ አልተፈለገም። ህዝቡ እርስበርስ መረጃ እንዲለዋወጥ መፍቀዱም አደጋ አለው። ስልኩም ጠፋ!
ለጥቂት ጉልበተኞች ግን ይህ መብራት ከቶውንም አይጠፋም። ግዜው እስኪደርስ፣ የሚመኩበት ጉልበታቸው እስኪፈታ ድረስ ይበራል። እስከዚያው ብዙሃኑ በጨለማ ይኖራሉ።
የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር ግን ከቴድሮስ አድሃኖም ጋር ትንሽ የሚጣረዝ ይመስላል። ድህነታችን ለስደት እንደዳረገን ነበር ሃይለማርያም በአደባባይ ይናገሩ የነበረው። ተሳስተው ነው? ወይንስ በጥድፍያው ምክንያት አልተናበቡ ይሆን? ልማታዊ መንግስት ድህነት የምትለዋን አይጠቀምም። ቴዎድሮስ አድሃኖም ግን በፌስ ቡክ ገጻቸው “ሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን። ወያኔነት ልማት፣ ኩራትና ዴሞክራሲ ነው።..ይህን ችግር የሚፈታውም ወያኔነት ነው!” ብለውናል። በመስቀል አደባባይ ወታደራቸውን አሰልፈው የሰላማዊውን ህዝብ ሃዘን በወያኔነት ሲመልሱትም አሳዩን። በሊቢያ፣ በየመን እና በደቡብ አፍሪካ በሰቆቃ ያሉ ወገኖች የሚሉትንም እየሰማን ነው። “የኛ የምንለው መንግስት የለንም! … ጨለማ ውስጥ ሆነን እየጸለይን ነው።” ይህ ነው የወያኔነት ወጤት።
አቶ ሃይለማርያም ተሳስተው አንድ እውነት ተናገሩ። አንድ ነገር ቢጨምሩበት ጥሩ ነበር። ለስደቱ መንስኤ የፍትሃዊ ስርዓት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መጥፋቱ መሆኑን። ለማንኘውም በውስጥ ግምገማ ላይ ይህችን ለምን እንደተናገሩ ያስረዱ ይሆናል።
ለሃዘን የወጣ ህዝብ በአረመኔ ወታደሮች ሲቀጠቀት ሮይተርስ ከአዲስ አበባ አሳይቶናል። ዜጎች ሲቀጠቀጡ የሚያሳዩ የቪድዮ ምስሎች በማህበራዊ ድረ-ገሶች በስፋት ተበትነዋልል። ሬድዋን ሁሴን ግን ወታደሮቹ አንድም ሰው እንዳልነኩ ነገሩን። ታድያ ዥጉርጉሩን የፌዴራል ልብስ ያጠለቀ አይሲስ ነበር እንዴ በመስቀል አደባባይ ህዝቡን ሲያሸብር የነበረው? ሃፍረት ያልፈጠረባቸው፤ የሰብአዊ ፍጡር ህሊና የሌላቸው ውሸታሞች ናቸውና ይህን ማለታቸው አይደንቅም። ኢውሮ ኒውስ ከአዲስ አበባ በቀጥታ ያሳይ የነበረው ትእይንት ዘግናኝ ነበር። አይሲስ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን የማይተናነስ ጭካኔ አሳዩን። ህጻን፤ ሴትና አዛውንት እንኳን ሳይለዩ ሁሉንም በጭካኔ ቀጠቀጡ። የህዝብ ወገን ቢሆኑ በወገን፤ ለዚያውም በሃዘን ላይ ያለ ህዝብ ላይ እንዲህ አይጨክኑም። በእውነቱ ባእዳንም እንዲህ ባዘነ ህዝብ ላይ አይጨክኑም። የ97ቱን ሰቆቃ አስታወሱን።
የታፈነው ህዝብ በአንድ ላይ ሆኖ ብሶቱን ሲገልጽ ሰማን። ሬድዋን ሁሴን እንደሚሉት ከዚህ ረብሽ ጀርባ ሰማያዊ ፓርቲ አለበት። ከጨርቆስ እስከ ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ ከቦሌ እስከ ኮልፌ፤ ከዘነበወርቅ እስከ ሽሮ ሜዳ … ያለ ህዝብ ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲ ከሆነ ህዝብ ከናንተ ጋር አይደለምና ስልጣኑን ለሰማያዊ ፓርቲ ማስረከብ ነው ያለባቸው። አይገባቸው ይሆናል እንጂ በተዘዋዋሪ እየነገሩን ያሉት ህዝብ በሙሉ እንደጠላቸው ነው። ጥቂት ያሉትንም የህዝብ ቁጥር በምስል አየነው።
ይህ የህዝብ መልእክት ትምህርት ካልሆናቸው አምሯቸው የታወረ ነው። ክስተቱ እንደፈርዖን በባርነት የያዙት ህዝብ ምን ያህል እንደተከፋ ያሳየናል። 23 አመታት በጫንቃው ላይ የተቀመጠው ስርዓት ምን ያህል እንዳንገፈገፈው የሚያሳይ ባሮ ሜትር ነው።
ለመሆኑ እነዚያ ባለስልጣናት ሲሞት ደረት የሚመቱት ልማታዊ አርቲስቶች የት ጠፉ? “ታላቁ መሪ” ባረፉ ግዜ ማቅ ለብሰው እዩኝ-እዩኝ ይሉ የነበሩ አርቲስቶች ነብስ እየመረጡ ነው የሚያለቅሱት? በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የተሰውት ወገኖች የሰብአዊ ፍጡራን አይደሉም እንዴ? ወይንስ ሃዘንም በትእዛዝ ሆነ? መቼም በዚህ ሰቆቃ ለማዘን የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን አያስፈልግም። ለማዘን ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። በዚህ የጨለማ ወቅት ከህዝብ ወገን ያልሆነ ሁሉ ለህሊናው ሳይሆን ለሆዱ የሚገዛ እንስሳ ብቻ ነው። መቼም የማያልፍ ነገር የለም ይህም ያልፍና ሁላችንንም ያስተዛዝበናል።
ክንፉ አሰፋ
Leave a Reply