የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር “ኢትዮጵያ ቅደሚ!” በይፋ (officially) ለህዝብ የተበሰረውና በ“አብዮት አደባባይ” የተዘመረው ልክ የዛሬ 40 አመት ቅዳሜ መስከረም 2 ቀን 1968 ዓ.ም ነበር!
በርካታ የቀድሞ ተማሪዎቼና ወዳጆቼ በተገናኘን ቁጥር “የምንወደው መዝሙር ግጥም እየተዘነጋን ነውና እባክህ ባመቸህ መንገድ እንደገና አውጣው” እያሉ ሲጠይቁኝና እኔም ቃል ስገባ ብዙ ጊዜ ሆነን።
40ኛ አመቱን ምክንያት በማድረግ ለታሪክ ማስታወሻ እንዲሆን እነሆ ግጥሙን በትህትና እያቀረብሁ፤ መዝሙሩ ብዙ ውጣ ውረድ ታሪክ ስላለው ወደፊት በሰፊው ይገለፃል።
፨ ፨ ፨
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንደነት ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሊሆኑ ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጅ ወደፊት በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለስራ ላገር ብልፅግና!
የጀግኖች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ!
፨ ፨ ፨
የሙዚቃው ደራሲ አቶ ዳንኤል ዮሃንስ ነው፤ የሙዚቃ ትምህርት ቡልጋሪያ ነው የተማረው።
ማሳሰቢያ፦ በግጥሙ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ቃላት አንዳንድ ሰዎች በማወቅ ለተንኮል ወይም ባለማወቅ በየዋህነት የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጡ ተደምጠዋል። ስለዚህ ማብራሪያ መስጠቱ ተገቢ ይመስለኛልና እነሆ!
- ኅብረሰባዊነት፡- ይህ ቃል በእንግሊዝኛው social democracy የሚባለው አቻ ነው እንጂ ኮሚኒዝም ወይም ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አይደለም! በ1967ዓ.ም የታወጀው የደርግ መንግሥት የመጀመሪያው ፖሊሲ መመሪያም “የኢትዮጵያ ኅብረተ-ሰብአዊነት – Ethiopian Socialism” እንደነበር ያስታውሷል! የገጣሚውም የቀድሞውም ይሁን የአሁኑ የፖለቲካ አቋም እንደ ስዊድን በመሳሰሉት አገሮች እንዳለው አይነት “ኅብረሰባዊነት social democracy” ነው!
- ጀግና፡- ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የጀግኖች አገር መሆኗ እየታወቀ አንዳንድ ተንኮለኞች “ደርጎችን ነው” የሚያሞግሰው ሲሉ ተደምጠዋል! በፊትም አሁንም ወደፊትም እምዬ ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር መሆኗን በፅኑ አምናለሁ።
- ጠላት፡- በኢትዮጵያውያን መካከል ብዙ ግጭቶችና ጦርነቶች ተካሂደዋል ከረጅሙ ታሪካችን እንደምንረዳው። ሆኖም የ“ጠላት” ጦርነት አይባልም! ምንም ጊዜ “ጠላት” የምንለው የውጨውን የባእድ ወራሪ ነው! ስለዚህ በግጥሙ ውስጥ “ጠላቶችሽ ይጥፉ!” ሲል ማንን እንደሆነ ግልፅ ነው። ከዚህም በቀር የኢትዮጵያ “ጠላቶች” – “ድርቅ፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ መሃይምነት፣ ስራ አጥነት…” ጭምር በመሆናቸው ድራሽ አባታቸው እንዲጠፋ ገጣሚው ምኞቱን መግለፁ ነው “ጠላቶችሽ ይጥፉ!” ሲል በመዝሙሩ ውስጥ!
- አንዳንድ ወዳጆቼ በየትኛውም አይነት ዴሞክራሲ የሚያምኑትን ሁሉ መዝሙሩ “እንዲያቅፍ” “በኅብረሰባዊነት ምትክ በዴሞክራሲ ሥርዓት ቢባል ጥሩ ነው፤ ሌላው እንዳለ ሆኖ” ይሉኛል። በበኩሌ ተቃውሞ የለኝም የትና ማን እንደሚዘምረው በበኩሌ ባላውቅም! እርግጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት ማኅበር አባሎች እዚህ ላስ ቬጋስና ዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ላይ “ኢትዮጵያ ቅደሚ”ን ሲዘምሩ አዳምጫለሁ፤ አብሬም ዘምሬአለሁ።
በተረፈ በዚሁ ልሰናበት! ላላነበቡ/ላልሰሙ በበኩላችሁ አካፍሉ ጎሽ!
(ሙዚቃውን ለመስማት እዚህ ላይ ይጫኑ)
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ (Assefa GMT) የ“ኢትዮጵያ ቅደሚ” ደራሲ ናቸው፡፡
wonchifu says
ጎሽ አሰፋዬ! እውነተኛውን ኢትዮጵያዊ መዝሙር በማስታወሴ ረጅም እድሜ ይስጥህ::
mahlet says
thx