• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የኢትዮ – ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ጉዳይ እና የህወሓት መጨረሻ

July 4, 2018 02:06 pm by Editor 1 Comment

ለረዥም ዓመታት በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የዘለቀው ግንኙነት ወጥ የሆነ መልክ ያለው አልነበረም። የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ከመጽናቱ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ነገሥታትና የጦር አበጋዞች በኢትዮ – ሱዳን ጠረፍ አካባቢ ከግብጽ ተስፋፊ ኃይልና ከሱዳን የንቅናቄ (መሃዲስት) ኃይል ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት ተፈጥሮ ያውቃል።

በአፄ ኢያሱ ብርሃነ ሰገደ የንግስና ዘመን የኢትዮጵያ ድንበር “ገዳሪፍ”ን አልፎ ከሚገኘው “ስናር” እስከተባለው (ሱዳን ውስጥ ያለ የቦታ ስም ነው) ቦታ ድረስ ነበር (ተከለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ “ከአፄ ልብነ – ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ” የሚለውን መጽሃፍ ያስታውሷል) የሚለዉን የታሪክ ጭብጥ እናቆየውና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ዋዜማ የካሳ ኃይሉ (ኋላ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ) የአባቱ ልጅ የሆነው ደጃች ክንፉ በ1829 “ወድ ከልተቡ” በተባለ ሥፍራ በሱዳን በኩል የመጣውን የግብጽ ተስፋፊ ጦር ድል መትቶ ሰዷል። ይህ ክስተት የግዛታዊ ቅርፅ አንዴ እየጠበበ ሌላ ጊዜ እየሰፋ ረዥም ዓመታት ባስቆጠረችው ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ምዕራብ በኩል ስለግዛት ሉዓላዊነት ከተካሄዱ ጦርነቶች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።

ካሳ ኃይሉ በሽፍትነት ዘመኑም ሆነ በንግሥና ጊዜው የሰሜን ምዕራብን ጠረፍ አካባቢ በአትኩሮት ይከታተለው ነበር። በሽፍትነት ዘመኑ ከግብፆች ጋር መጋጨት የጀመረውም በዚሁ ጠረፍ አካባቢ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ሌላው ቀርቶ እርሱ “ቱርክ” ብሎ ከሚጠራቸው ኃይሎች ጋር ያደረገው የዕድሜ ልክ ፍልሚያና ኢየሩሳሌምን ከነሱ ነፃ አወጣለሁ የሚለው ሕልምም የተፀነሰው ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ ነው። (በይበልጥ የተክለፃዲቅንና የባህሩ ዘውዴን ሥራዎች ያጤኗል)። የዚህ ገፊ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆንም መተማ ላይ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ አሳዛኝ የጦር ሜዳ ህልፈትም ስለ አገር ግዛት ሉዓላዊነት የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑን ታሪክ ሲያወሳው የሚኖር ጉዳይ ነው።

በጥቅሉ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ በረዥሙ ታሪካችን ውስጥ የበዛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ዐቢይ የታሪካችን ምዕራፍ ነው። የድንበር ውዝግቡ ረዘም ያለ የታሪክ መነሻ ቢኖረውም የቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ መሰሪ እጅ አለበት። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት እንግሊዝ ሱዳንን በቅኝ ገዥነት ከመያዟ በፊት የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን “ጓንግ” ተብሎ የሚጠራው ወንዝ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በዳግማዊ ምኒልክ የንግሥና ጊዜ (ድህረ – አድዋ) ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ገዥነት በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን እንዲካለል ከእንግሊዝ በቀረበው ጥያቄ መሰረት በአፄ ምኒልክ ተቀባይነት አግኝቶ ግንቦት 8፣ 1894 ዓ.ም.  ዉል ተፈረመ።

ይሁንና ስምምነቶቹ በአፈፃፀም ላይ ችግሮች ነበሩባቸው። ካርታ ዘርግቶ ድንበር ከመከለል ባሻገር በቦታው ተገኝቶ ድንበሩን በምልክት መለየት አልተቻለም ነበር (በይበልጥ ባህሩ ዘውዴን ያጤኗል) ይህም ሆኖ ከዳግማዊ ምኒልክ ኅልፈት በኋላ የልጅ ኢያሱን አጭር የንግሥና ዘመናት ተሻግረን “… በንግሥት ዘውዲቱና በልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጊዜ የኢትዮጵያ ወሰን ጓንግ ወንዝ ድረስ መሆኑ ስለታመነበት፣ ሱዳኖች የጓንግ ወንዝ እንዳይሻገሩና ከተሻገሩም ለሚያገኙት ጥቅም ሁሉ የግጦሽ ሳርን ጨምሮ ግብር እንዲከፍሉ በተደረገው ስምምነት መሰረት ከፍተኛ ጎደቤና መተማ ላይ ጉምሩክ ተቋቁሞ ይህን ህግ የሚያስከብሩ የአካባቢው ተወላጆች በጠረፍ ኃላፊነት ተመድበው ነበር። ለጠረፍ መጠበቂያ 160 ያህል የጦር መሳሪያ ተመድቦ እንደነበርም ይነገራል (ነገዱ አባተ፣ “የጠረፍ ጀግኖች”)”።

በሰማያዊ ፓርቲ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ፕ/ር መስፍን ስለድንበሩ ሲያስረዱ

ይህ አሠራር በየጊዜው እየተደራጀና የጉምሩክ ሥራው እየዘመነ ከሞላ ጎደል በረዥሙ የአፄ ኃይለሥላሴ 44 የንግሥና ዘመናት ተፈፃሚ ሆኗል። በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ አልፎ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከሱዳን ገበሬዎች (ዘላኖች ጭምር) ግጭት የነበረ ቢሆንም ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። በአፄው የንግስና ዘመን መገባደጃ ላይ 1965 ዓ.ም. የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ ገበሬዎች ጓንግ ድረስ ማረሳቸውን በግልጽ ተቃውሞ ለንጉሱ የወሰን ማካለሉ ሥራ እንግሊዝ በሠራችው የቅኝ ግዛት ካርታ መሠረት እንዲሆን ጠየቀ።

በጊዜው በለውጥ ትናጥ የነበረችው ኢትዮጵያ የድንበሩን ጉዳይ በይደር ይዛ የማታ ማታ በደርግ የተጠለፈውን አብዮት አስተናገደች። የድንበር ማካለል ዳግም ጥያቄው ተንከባሎ የደርግ ትከሻ ላይ አረፈ። በ1970 ዓ.ም. በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም የሚመራ የታሪክ ምሁራን የተካተቱበት የወሰን ኮሚሽን  ተቋቁሞ ጉዳዩን አጥንቷል። የሱዳን ቅኝ ገዥ የነበረችው እንግሊዝ፣ ሎንደን ድረስ በመሄድ መረጃዎችን በማሰባሰብ የሱዳን መንግሥት የሚያቀርበው የወሰን ጥያቄ መሠረታዊ መነሻ የሌለው መሆኑንና ጉዳዩ የቅኝ ግዛት ውርስ ዕዳ እንደሆነ የወሰን ኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል።

ከዚህ መግለጫ በመነሳት የሱዳን መንግሥት የደርግን የአገር ግዛት ሉዓላዊነት ቀናዒ ስሜት በወራሪው የሶማሊያ ኃይል ያሳረፈውን ክንድ አይቷልና ጥያቄውን ደግሞ ደጋግሞ ከማንሳት ተቆጠበ። ይልቁንስ ህወሓትን በመርዳትና ነፃ መሬት በመስጠት ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት እንደአማራጭ ፖሊሲ ያዘ። የደርግ አፀፋም ከዚህ የተለየ አልነበረም። የዛሬዋን ደቡብ ሱዳን እንደአገር ለመመሥረት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘውን የኮሎኔል ዶ/ር ጆን ጋራንግን አማፂ ቡድን በመርዳት ተጠመደ። በመሀል ቤት የድንበሩ ጉዳይ ተዘነጋ። ድህረ – ደርግን ተከትሎ የሱዳን መንግሥት አርሶ አደሮቹንና ዘላኖችን ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያ ለም መሬት ማስፋፋቱን ተያያዘው። መንግሥታዊ ድጋፍ ያለው ይሄው ተስፋፊነት በአካባቢው የሚኖሩ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን ቢያስቆጣም ማዕከላዊ “መንግሥቱን” የተቆጣጠረው ህወሓት ጉዳዩን በቸልታ ሲያልፈው ቆይቷል።

(ፎቶ ቅንብር፤ አባይ ሚዲያ)

በ1995 ዓ.ም መተማ አካባቢ የሱዳንና የኢትዮጵያ ወታደሮች ግጭት ፈጠረዉ ነበር። በወቅቱ በቅጡ ባልተካለለ ድንበር የግዛት ባለቤቱን የመበየንን ስሜት በሚያንፀባርቅ መልኩ መለስ ዜናዊ “የእኛ ያልሆነን መሬት የመንጠቅ እርምጃ” ሲል አደናጋሪ ግን ተንበርካሪ የሆነ ንግግር ማድረጉ ይታወሳል። ይህን አደናጋሪ ንግግር ተከትሎ የሱዳን መንግሥት በ1996 ዓ.ም እንደገና የመሬት ይገባኛል ጥያቄውን አነሳ። ጉዳዩ በገዥው ኃይል ውስጥ በከፍተኛ አመራሮች ብቻ ሲታይ ቢቆይም ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ ሳይሆን ተድበስብሶ ቆይቷል።

ከዚህ ጊዜ በኋላ በተለየ መልኩ ከ1998 ዓ.ም. ታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የሱዳን መንግሥት ግልጽ የሆነ የመስፋፋት ወረራውን ቀጠለ (ነገዱ አባተ፣ ያለፈውን ምንጭ)። በዚህ ጊዜ ህወሓትና ጀሌዎቹ ከምርጫ 97 በኋላ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ተሸብሮ የነበረ በመሆኑ በመሀል አገር ፖለቲካ ተጠምዶ ለጉዳዩ ቸልታ አሳይቷል። የሱዳን መንግሥትን የመስፋፋት ድርጊት በመከላከያና በሲቪል ደኅንነቱ በኩል ሳይደርስበት ቀርቶ ሳይሆን አገዛዙ ለግዛት ሉዓላዊነት ደንታ ቢስ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። በአናቱም እጅግ እየከረረ ከመጣው የዘውግ ፖለቲካ አረዳድ አኳያ የህወሓት የፖለቲካ ሊሒቃን ጉዳዩን ከአገር ግዛት ሉዓላዊነት ይልቅ “ክልላችን እስካልነኩ ድረስ . . .” የሚል ምልከታ እንደያዙ ጥቁምታ ይሰጣል። ከትግራይ የላይኛው ጫፍ እስከ አባይ ወንዝ መሻገሪያ ያለውን የድንበር ወሰን የሚጋራው የሱዳን መንግሥት የግዛት መስፋፋቱን እያጠናከረ የመጣበት ቦታ በቋንቋ ተኮሩ ፌዴራሊዝም መሰረት የአማራ ክልል ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነው።

የሱዳን ገበሬዎች፣ ዘላኖች፣ በማህበራት የሚያርሱ ቡርዣዎች ሳይቀር በማን አለብኝነት ስሜት በአልበሽር መንግስት እየተደገፉ በመተማ የጠረፍ ግንባር “ደለሎ” በተባለው ሰፊ የእርሻ መሬት “የዘለቀ እርሻ ልማት” ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ፣ የኢትያጵያ ገበሬዎችን አፈናቅለው ከቁጥር 3 እስከ ቁጥር 6 ያለውን የእርሻ ቀጠና ተቆጣጥረውታል (ነገዱ አባተ፣ ያለፈው ምንጭ)። ሱዳናዊያን በመተማ በኩል ከሚያደርጉት መስፋፋት በተጨማሪ በአርማጭሆ በኩል ተያይዘውት ያለው መስፋፋት በኢትዮጵያ ገበሬዎች በኩል የመረረ ተቃውሞ አስነስቶ ተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተፈጥረዋል። ይህም ሆኖ የመንግሥታዊ መዋቅር ድጋፍ ያለው የሱዳን ገበሬዎች ተስፋፊነት በማየሉ በአሸናፊነት የሚከተሉትን አካባቢዎች ተቆጣጥረዋል።

  1. ሙሽራ ቀለም         8. ማዶ ከረደም
  2. ስልዱስ                9. ሆርሁመር
  3. ወዳሐሩድ            10. ወድ ከውቢት
  4. ገላሉባን              11. አፍቴራ
  5. ሸጋታምስ            12. መርበጣ
  6. አቦኪርና             13. ምድርያ
  7. ሀምዳይት            14. ግንባር ኑሬ

ከዚህ በላይ የተመለከቱ የአካባቢ ሥሞች በቀደሙት የኢትዮጵያ መንግሥታት በኢትዮጵያ ግዛተ – ሉዓላዊነት ስር የነበሩ ናቸው። እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ አለ፤ ይኸውም “ወድ ከውቢት/ውድ ከውሊ” የሚባለው ቦታ ላይ የአፄ ቴዎድሮስ ወንድም (ቴዎድሮስ ከመንገሱ በፊት) ደጃች ክንፉ በ1829 ዓ.ም. በሱዳን በኩል ከመጣው የግብጽ ኃይል ጋር ጦርነት ገጥሞ ድል ያደረገበት ቦታ ነው። (ባህሩ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 ገጽ 27 ለቦታ ማገናዘቢያ ይመልከቱ)። አሁን ይህ ቦታና ሌሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሱዳን ተስፋፊ ኃይል ቁጥጥር ስር ዉለዋል። ቅድመ 1983 ዓ.ም ከነበረዉ ወሰን በአማካይ 89 ኪሎ ሜትር ተሻግረዉ አካባቢዉን ተቆጣጥረዉታል። ይህም ሆኖ “ከኢትዮጵያ ገና ተጨማሪ መሬት አለን” በሚል የሱዳን መንግሥት ጥያቄ ማንሳቱን አላቆመም።

የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያንና የሱዳን አዋሳኝ ድንበር ጉዳይን ፍቱን እልባት (የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምልክት) አለመስጠታቸው አንድ ክፍተት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ በአካባቢው ካነበረችው ስውር ደባ በተሻገረ መልኩ የታሪክ ማስረጃዎችን መነሻ ያደረገ የግዛት ሉዓላዊነት ማስከበር የአሁኑ የኢትዮጵያ “መንግሥት” የታሪክ ኃላፊነት ነበር። አልሆነም እንጂ። መለስ ዜናዊ ከማለፉ በፊት ከጉዳዩ አሳሳቢነት አኳያ ከገዥው ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከመተማና ከአርማጭሆ ጠረፍ አካባቢ ገበሬዎች ውጪ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለ ጉዳዩ ከተባራሪ ወሬ በስተቀር የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

የድንበር ውዝግቡ በስፋት ወደ አደባባይ ከወጣ በኋላም በውዝግቡ መካረር የተነሳ የያኔው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ያለ ጊዜው ከኃላፊነቱ ተነስቶ ራቅ ባለ መልኩ በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እንዲቀመጥ መደረጉ ይታወሳል። ምክትሉ የነበረዉ ደመቀ መኮንንም ባሳየዉ የፖለቲካ ታማኝነት የተነሳ በከፍተኛ ሹመት ወደ ማዕከላዊ “መንግሥት” መምጣቱ ከዚሁ ከድንበር ዉዝግቡ ጋር የተያያዘ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነዉ። ማዕከላዊ “መንግሥቱን” ያለ ከልካይ የተቆጣጠረው ህወሓት፣ ከኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የሚያከናውናቸው ተግባራት ግልጽነት የሚጎድላቸው ናቸው። አማራ ክልል ላይ አያሌው ጎበዜ ተነስቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተተካበት የፖለቲካ ውሳኔ ጊዜውን ጠብቆ በድህረ – መለሱ ህወሓት ውስጥ ገዱና ካቢኔው ለህወሓት የእግር እሳት ሆነው ተገኝተዋል።

የድንበር ማካለሉ ይፋ በሆነ መንገድ ባይነገርም የሱዳናዊያን መስፋፋት በኢትዮጵያ “መንግሥት” ቸልተኝነትና አድፋጭነት “ፍሬ” አፍርቶላቸዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ በነጠቁት መሬት ላይ በእርሻ፣ በግጦሽ፣ በዕጣን ለቀማ፣ በማዕድን ፍለጋ ተጠቃሚ ሆነዋል። አንጀታቸውን ከአካባቢዉ ለም መሬት ጋር ያስተሳሰሩት የጠረፍ አካባቢ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ዛሬም ድረስ ተስፋ ባልቆረጠ ስሜት በእርሻ ወራት ጊዜ ከሱዳናዊያን ጋር ብረት አከል መተናነቅ ያደርጋሉ። ይህን መተናነቅ በግንባር ቀደምትነት ይመራው የነበረው ባሻ ጥጋቡ ነበር። ብርቱው አዛውንት በአርማጭሆ ሱዳን ጠረፍ አካባቢ ተሰሚነት የነበረው በመሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር በየጊዜው ፍልሚያ ያደርግ ነበር። ሆኖም ግን ባሻ ጥጋቡ 2005 ዓ.ም. ላይ በህመም የተነሳ ህይወቱ አልፏል። ኃይል አልባው ኃይለማሪያም ደሳለኝ “እየመራሁት ነው” የሚለው “መንግሥት” በጠረፍ አካባቢ በቻሉት መጠን የሱዳንን መስፋፋት ለመከላከል የሞክሩትን የአካባቢዉን ገበሬዎች “ሽፍታ” ሲል ፈርጇቸዋል። በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች በአቅም ማጣት የተነሳ በሱዳን ተስፋፊነት እየተገፉ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ የኢትዮጵያ መሀል ዳር ሲሆን፤ በአንፃሩ የሱዳን ዳር እየሰፋ መሀል ሆኗል።

የትግራይና የሱዳን ተወካዮች በመቀሌ ውይይት ሲያደርጉ (ፎቶ ፋና)

ብዙዎችን የጉዳዩ ተከታታዮች ግራ በሚያጋባ እና ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት መልኩ በጥር፣ 2009 ዓ.ም. “18ኛው የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ልማት ኮሚሽን ጉባኤ” በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። ጉባኤውን በተመለከተ “የኢትዮ – ሱዳን የጋራ ድንበር ልማት ኮሚሽን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች የጀመሩትን የትብብር ግንኙነት አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ” የሚል የዜና ሽፋን ቢሰጠውም ዜናውን ገልብጦ መረዳት አይከብድም።

በጉባኤው ላይ “በፖለቲካና ፀጥታ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በድንበር አካባቢ የሚካሄድ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የወንጀል ድርጊቶችና ወንጀለኞችን መከላከል ላይ በትብብር መሥራት፣ . . . በህገ – ወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በጋራ ለመከላከል በሚቻልበት አግባብ ሰፊ ውይይት ተካሄደ” የሚል የዜና ሽፋን የተሰጠው ጉባኤ “ለስምምነቱ ተፈፃሚነት” ኢትዮጵያን በመወከል የህወሓትና የትግራይ ክልል ሊቀመንበር አባይ ወልዱ፣ በሱዳን በኩል ደግሞ የገዳሪፍ ግዛት አስተዳዳሪ ሚርቀኒ ሳልሕ ሱዳንን በመወከል ተፈራርመዋል።

ይህን ጉባኤ በተመለከተ ለሱዳን ብሔራዊ ስሜት ተግቶ የሚሰራው ሱዳን ትሪቢውን “የሱዳን ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ አቻወቻቸው ጋር የድንበር ማካለሉንና የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ከሱዳን የወሰዱትን መሬት ስለሚመልሱበት ሁኔታ ውይይት ተካሄደ” ሲል በድረ- ገጹ ላይ ዘግቧል። ዜና ዘገባው እውነትነት ቢኖረውም እንኳ ፍሬ ሃሳቡ የሱዳን ወፍ ገልብጣ ነፋች ያስብላል።

በ2008 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በአማራ ክልል ከተፈጠረው ብረት አከል ህዝባዊ አመፅ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል አመራሮች የውስጠ – ፓርቲ መተጋገልና በሁለቱ ክልሎች መካከል እንደ ሕዝብ እየተስተዋለ ካለው ቅራኔ አኳያ ጉባዔው(የሱዳንና የኢትዮጵያ) በመቀሌ ከተማ መካሄዱ ከዚህም አልፎ በመንግስታዊ መዋቅር ደረጃ ከትግራይ ክልል ውጪ ህጋዊ ውክልና የሌለው የህወሓትና የትግራይ ክልል ሊቀመንበር የሆነዉ አባይ ወልዱ ኢትዮጵያን ወክሎ መፈረሙ ጉዳዩን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል። (ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ያተመው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)።

ህወሓትና ሱዳን ውስጥ ውስጡን እያደረጉ ያለው የትራንስፖርት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ … ስምምነቶች ጉዳዩን በቅርበት በሚያውቁት ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጤና የማይታይ የወደፊቷን “ታላቋ ትግራይ” አገር ምስረታ መንገድ ጠራጊ ሂደት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ይህን ጥርጣሬ የህወሓት ሰዎች “ጥሩ ድርሰት ነው” በማለት የሚሳለቁበት ቢሆንም የድርጅቱን የበረሃ ላይ ማኒፌስቶ ይዘት እና ቅጥ ያጣውን የጥላቻ ፖለቲካ አካሄዱን ለሚያስተውሉ ወገኖች ጥርጣሬውን ለእውነት የቀረበ ያደርገዋል። ዞረም ቀረም ከጥርጣሬው ባሻገር ያለው ተጨባጭ እውነታ ድህረ – 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያ አልቦ – ሉዓላዊነት የሚንፀባረቅባት አገር ለመሆኗ ከኤርትራ ቀጥሎ የሱዳን መጠነ ሰፊ ተስፋፊነት ሁለተኛው ማሳያ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጀመሩት የመደመር እና የኅብረት ፖለቲካ ያልጣማቸው የህወሓት “ጸጉረ ልውጦች” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየፈጸሙ ያሉት ሤራ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ይህ የህወሓት አካሄድ አዋጭ አለመሆኑን በመመልከት ለመደመር የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል ጽንፈኛ አቋም የያዙ እንዳሉ የሰሞኑ ሁኔታዎች አመላካች ናቸው። ከዚህ ሌላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በመደመር መስመር ላይ መሆኗ በህወሓት ውስጥ የልዩነት አጀንዳ ፈጥሯል። የኤርትራን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ “ከእኛ በላይ ላሳር” የሚሉ የህወሓት “የቀን ጅቦች” አጀንዳቸው ስለተነጠቀባቸውና በሰሜን በኩል ያለው “ማኩረፊቸው” ስለተወሰደባቸው ዳር ዳሩን በመሄድ በኢትዮጵያ የጠረፍ ቦታዎች ላይ ግጭቶችን በማስነሳት የዐቢይን አስተዳደር ለማዳከም ዘላቂነት የሌለውን ጥረታቸውን ቀጥለውበታል። የሰሞኑ የመተማ ግጭት ባለፉት ሳምንታት በውስጥና በድንበር አካባቢ ከተነሱት ግጭቶች ጋር አብሮ የሚጠቀስ አንዱ ነው።

ለ27 ዓመታት እና በሽፍትነት ዘመናቸው ሱዳንን ቤታቸው አድርገው የኖሩት ህወሓቶች የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አካሄድ ዕቅዳቸውን ሁሉ በማክሸፍ “ታላቋ ትግራይ”ን የመመሥረት የበረሃ ምኞታቸውን እንዳመከነው የተረዱት ረፋፍደው ነው። ጠ/ሚ/ሩ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉትን አገራት በመጎብኘት በፍጥነት የፈጸሙት ዲፕሎማሲያዊ ተግባር የህወሓትን ቀዳዳ የደፈነ ተግባር ነው። ከሱዳኑ አልበሽር ጋር ብቻ ሳይሆን ከግብጹ አልሲሲ ጋር ያካሄዱት የወዳጅነት ጉብኝት፤ ከሁሉ በላይ ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነትና ፈጣን ግንኙነት የመመሥረት አካሄድ ለህወሓት የመጨረሻው መጀመሪያ ሆኖበታል። ይህ የዐቢይ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ በዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍና ማበረታቻ የሚሰጠው በመሆኑ ህወሓት የቀረው አማራጭ መደመር ብቻ ነው። ለዚህም ከውስጡ የሚወጡና የትግራይን ሕዝብ የሚታደጉ ደማሪ የለውጥ ኃይሎች ያስፈልጉታል። ይህ ካልሆነ ግን በዓለምአቀፉ የአሸባሪዎች ባሕረ መዝገብ ላይ በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኘው ህወሓት ሌሎችን “አሸባሪ” በማለት ሲወነጅል የኖረው ዘመን አክትሞ መጨረሻው እንደመሪው ዳግም ላያንሠራራ ወደ አለመኖር መሄድ ይሆናል።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News, Politics Tagged With: border, ethio-sudan, Full Width Top, Middle Column, tplf

Reader Interactions

Comments

  1. Bilusuma says

    July 5, 2018 04:24 pm at 4:24 pm

    Kesew jib Buda ye ken jib yishalal

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule