የጎርፉ፣ የዝናቡ፣ የምድሩና የሰማዩ ፈጣሪ እያለ የምንፈራው የለም፡፡ ዛሬ ጨዋታው ተቀይሯል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት መንግስት ተጫዋች ሕዝቡ ደግሞ ቲፎዞ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጨዋታውም ሜዳውም ተቀይሯል፡፡ አሰላለፉም ለየቅል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተጫዋቹ ሕዝቡ እንደሆነ የኢአህዴግ “መንግስት” ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው እያልሁ ወደ ትዝብቴ ላምራ፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልል በቢሮ ደረጃ ባሉ የመንግስት መ/ቤቶች በለውጥ ሥራዎች ዙሪያ ለአንድ ሳምንት ያህል ከሠራተኛው ጋር ተሃድሶ አይሉት ሥልጠና አልያም ውይይት በዉል ባልታወቀ ጉዳይ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ሥራ ፈተው ሲናቆሩ መሰንበታቸውን ስሰማ መንግስት ማለያውንና አሰላለፉን ቀይሮ ያለደጋፊ የጀመረው ጨዋታ እንደሆነ ከጅምሩ ታዝቤአለሁ፡፡
መሰንበቻውን ለመንግስት መ/ቤት ሠራተኞች በመልካም አስተዳደር፣ በውጤት ተኮር ስርዓት፣ በዜጎች ቻርተር ጽንሰ ሀሳብና አተገባበር፣ በለውጥ ሠራዊት ግንባታ፣ በለውጥ መሳሪያዎች ትስስር፣ በመንግስት ሠራተኞች ሥነ ምግባር ኮድ፣ በስብሰባ አፈጻጸምና ማኑዋል በሚሉ ባረጁና ባፈጁ ሰነዶች ዙሪያ በኃይልና በቡድን መድረክ ሲያላጉ መሰንበታቸው ሳያንስ ዓለም ላይ የሌለውን ገነት መሳይ መልካም አስተዳደርና ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ነን እያሉ ሲያደናቁሩ ሰንብተዋል፡፡ መሰንበቻውን ጆሮ ያልሰጣቸው ቢኖርም የየተቋሙ ኃላፊዎች በየተቋማቸው ያለውን ሲቪል ሰርቫንት ከአስቸኳይ ጊዜ ያልተናነሰ ማዕቀብ ሲጡሉበት፣ ሲደነፉበትና በግራሞት ሲቆዝም ሰንብቷል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ከልክ ያለፈ ንግድ ውስጥ በገቡበት፣ በማህበራዊ ፕሮግራሞች መቋረጥ ምክንያት በርካታ ዜጎች ለበለጠ ድህነትና ሲቃይ በተዳረጉበት፣ ቢሮክራቶች በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በተዘፈቁበት፣ ሲቪል ሰርቫንቱ ባረጁና ባፈጁ ህጎች፣ ደንቦችና የአሰራር ሰርዓቶች ውስጥ በታመሰበት፣ የሰው ሀብትና የፋይናንስ ስራ አመራሩና የቁጥጥር ስርዓቱ ፈር ባልያዘበት፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጡ ተገልጋይን መሠረት ያላደረገና ቅልጥፍናና ውጤታማነት በጎደለበት በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር ቀርቶ መልካም አስተዳደሪ በሌለበት ክልል መንግስት ከሠራተኛው ጋር ሆድና ጀርባ በሆነበት ወቅት ይህን አጀንዳ ዘርግቶ ተቀበል፣ አትቀበል … እያለ የሚፎላው የበላይ አመራር ሥራውን ዘንግቶት ይሆን ያስብላል፡፡
ዳንኤል ኩፍማን የተባለ የዘርፉ ተመራማሪ መልካም አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ ተጠያቂነት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ውጤታማነት፣ የህግ የበላይነትን ማስፈንና ሙስና በቁጥጥር ሥር ማዋል ሲቻል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ ሆነ በአማራ ክልል ያለው መልካም አስተዳደር ከተመራማሪው ሐሳብ በተቃራኒው እንደሆነ የግድ ጥናት የሚጠይቅ አይደለም፡፡
በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለማንሳት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ መልካም አስተዳደር ቀርቶ አስተዳደርም በአግባቡ የለም፡፡ ይልቁንም በሁሉም ዘርፍ ክልሉ እያሽቆለቆለና እንደ ሀገር በክልል የመቀጠል ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡
ሁሌም የምለው መንግስት በየዓመቱ ሲቪል ሰረቫንቱንና ሌላውን ሕዝብ ለማዘናጋት በሚል አጀንዳ እየቀረጸና መሪ ቃል እየፈበረከ የሚፈጥረው ትርምስ ኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች የሚያመላክት ነው። መንግስት እንደድሮው መግዛት ተስኖታል፡፡
ህዝቡም እንደድሮው መገዛት ታክቶታል፡፡ የመንግስትና የሕዝቡ ቋንቋም እንደባቢሎኖች የተለያየበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ከዚያም ብሶ ሚዲያው ታፍኗል። ትግሉን በተደራጀ መልክ ዳር የሚያደርስ ጠርቶ ባልወጣበት ሁኔታ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ከተሞችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ህዝባዊ ዓመጽ ሊፈነዳ ጫፍ ላይ መድረሱን ለማወቅ ሊቅነት የሚጠይቅ አልሆነም። በዚህ ሁኔታ ዐመጽ ከተነሳም የሚከተለው ትርምስና እልቂት ቀላል ስላይደለ ንፁህ ህሊና ያለው ሁሉ በግልፅ አይቶት መፍራት አለበት። ይህ ፍርሃት በጎ ፍርሃት ሊሆን የሚችለው ወደ መፍትሄው መሄድ ካስቻለን ብቻ ነው።
እኔን የሚገርመኝ በእንደዚህ ዓይነት ቀውጢ ወቅት ብቅ የሚሉ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በመንግስት ዳረጎት ስም ሕዝብን የሚያንገላቱ ተቆርቋሪ መሳዮች በድርጅት ስም ሸበጥ አልባ ታጋዮች ደካማነታቸውን መንግስት በለገሳቸው የሥልጣን ካባ በመሸፈን በሚያደርሱት የመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝብንና መንግስትን ለማለያየት እንደሚጥሩ ገዥው መንግስት ሊያስተውለው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
መንግስት በአገሪቱ መልካም አስተዳደር ይሰፈን የሚል ከሆነ በቅድሚያ በድርጅት ስም የተኮለኮሉትን አባላቱን ሊያጠራ ይገባዋል፡፡ የአባልነት መስፈርቱ በውል ሳይታወቅ እንደ ተራ ሻይ ቤት ማንም ልቅምቃሚ ድርጅቱን እየተጠጋ ቁጥር እንጂ ጥራት በሌለው የድርጅት አባል በአደባባይ አጀንዳ እየተቀረጸና ሀሳብ እየተወረወረ በስውር ደግሞ አባላቱ እርስ በርስ ጥላሸት እተቀባባ የድርጅቱን ምስጢር ገሀድ እያወጡ ደርጅቴ ቢሉን የምንሰማበት ጆሮ የለንም፡፡ በድርጅት አባልነት ስም አታስፈራሩን፡፡ መደራጀት ሕዝብን ለማገልገል፣ ድህነት ለማስወገድ፣ … እንጂ ሠራተኛውን ለመጨቆን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የሰሞኑ የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቫንቱ ተሃድሶ መድረክ ያሳየን የየተቋማቱ ኃላፊዎች በሠራተኛው ላይ ዛቻ አይሉት ጥላቻ ሲዘባበቱበትና ሲያስፈራሩት እንደሰነበቱ ታዝበናል፡፡ እየታደስን እንሠራለን እየሠራን እንታደሳለን የሚለውን መሪ ቃል ወደ ጎን በመተው እየዛትን እናሰራለን እያሰራን እናስራለን በሚመስል መልኩ መድረኩ መጠናቀቁን አውቀናል፡፡
በዚህም የክልሉ መንግስት ሊያገኝ ያሰበውን ተቀባይነትና አመኔታ በድርጅቱ ደረስጌዎች ዛቻ እንዳጣው በማወቅ ለቀጣዩ በየተቋማቱ ያሉ አመራሮችንና በድርጅቱ ከመሠረታዊ ድርጅት እስከ ሴል የተሰገሰጉትን አባላት ማንነትና የሙያ ብቃት በማጥራት ከድርጅቱ 37 ዓመት የድል በዓል ማግስት ሊያድሰው ይገባል እላለሁ፡፡
ጲላጦስ ከጣና ዳር (ummp4.20@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply