ስድስት:- ቃል ኪዳን፤ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ
እንግዲህ ኢሳት በነገረኛነትም ሆነ በጠመንጃ-ያዥነት በኩል ከሎሌነት ጠባይ ጋር የተያያዘውን ኢትዮጵያውያን ያለንን አጉል ባህል ሁሉ እየነቀስን እየጣልን በዘመናዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መሠረት ለመጣል ዋና መሣሪያ ሊሆነን ይችላል ብሎ ማመን መነሻ ይሆናል፤ ይህ እምነት ከሌለ የእምቧይ ካብ ነው፤ ይህ እምነት ራስን ማጽዳትንም ይጠይቃል።
ማክሸፍ እንደምንችልበት ከማመን እንጀምር፤ ስለዚህም ኢሳት ሊከሽፍ የሚችልበትን እያንዳንዱን መንገድ ማጥናትና በቅድሚያ ፈውሱን ማዘጋጀት የሚጠቅም ይመስለኛል፤ ይህንን ጉዳይ በትጋት ለመከታተል የኢሳትን አማራጭ የማይገኝለት የአገር ጥቅም በእውነትና በትክክል መገንዘብ ያሻል፤ ዘመን-አመጣሽ ነገር ብቻ አድርጎ መመልከቱ ለወረት ይዳርገዋል፤ ወረትን ማክሸፍ ቀላል ነው፤ ከከሸፈ በኋላ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በጣም ከባድ ሥራን ይጠይቃል፤ ስለዚህ ከወዲሁ ኢሳት ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲተከል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ዘለቄታ እንዲኖረው ማረጋገጫ ይሆናል።
የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ አንፈራጥጠው ከላይ ቤት እታች ቤት እየቀላወጡ አካላቸውን፣ አእምሮአቸውንና መንፈሳቸውን የሚያባልጉ ሰዎችን ያበራክታል፤ የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የጸዳውን ከአደፈው፣ ሳይለዩ ለሚያወሩት ደካሞች ሜዳውን ያሰፋላቸዋል፤ የወያኔ/ኢሕአዴግን ፍርሃት ወደመርበድበድ ይለውጠዋል፤ የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም።
ንስሐ ለመግባት ወኔ ለሌላቸው፣ በሠሩት ጥፋት አገርን ወይም ወገንን በመበደላቸው ዛሬም ለመኩራራት ለሚፈልጉት፣ አርበኛውንና ባንዳውን ባንድ ሚዛን አስቀምጠው ለሚተቹት፣ የኢትዮጵያውያንን ሰውነት አራክሰው ጊዜያዊ ጥቅማቸውን ለሚያከማቹ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በተንኮል እየመነዘሩ የሥልጣን መሰላል ለሚያበጁ ሁሉ ፊት-ለፊት ቆሞ ለሚጋፈጣቸው ኢሳት መድረክ ይሆናል፤ የኢሳት ዋና ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው፤ ይህንን ተግባር ለመፈጸም ኢሳት የኢትዮጵያ፤ ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲሆን መንገዱን እንጥረግ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባለቤትነት የሚመራውና የሚያካሂደው እናድርገው፤ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሳት ላይ ያለው መብት ነው ከተባለ፣ ግዴታውንም አብሮ መቀበል ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ግዴታውን በቃል ኪዳን መቋጨት ከቻለ ኢሳት ከቀፈፋና ለመክሸፍ ይድናል።
የእኔ ምኞት ኢሳት በኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን ተገንብቶ በሕገ ኀልዮት እየተመራ አዲስ ዓላማ፣ አዲስ የአሠራር ዘዴ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ጉድለቶችን ሁሉ አውቆ በጥንቃቄ እየነቀሰ አዲስ የመተማመንና የመተባበር ባህል ይፈጥራል የሚል ነው፤ (እኔ ቃል ኪዳን የምለው ሁለት ቁም-ነገሮችን የያዘ ነው፤ በአንድ በኩል እውነትን አለመፍራት (ወይም በጥሩ መልኩ ለእውነት መቆም፣) በሌላ በኩል ለአንድ የጋራ ዓላማ የራስን ግዴታ ሳያስተጓጕሉ ለመወጣት በቆራጥነት መቆም፤ ስንት ልጆች አሉህ ተብሎ ሲጠየቅ ሁለት ወይም ሦስት እያለ አጥር ላይ ተንጠልጥሎ የሚመልስ ለቃል ኪዳን አይበቃም፤) ከሩቅ እንደማየው ጥቂት ሰዎች ኢሳትን በቃል ኪዳን ተይዘው ሲጥሩ አብዛኛው ደግሞ በአጋጣሚ እንደተመቸውና እንደፈለገ የተቻለውን የሚያደርግ ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን የሌለው ነው፤ ከተሳሳትሁ ደስ ይለኛል፤ አስተያየቴ ትክክል ከሆነ ኢሳት አይዘልቅም፤ መክሸፍ ዕጣ-ፋንታው ይሆናል።
ዓላማውን ሳይመታ እንዳይከሽፍ ኢሳት በቃል ኪዳን መታሰር አለበት፤ እንዴት? ቢባል፣ አንድ ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በአማካይ በወር አሥር ዶላር ለመስጠት ቃል ኪዳን ቢገቡና የየዓመቱን ግዴታቸውን በአንዴ ቢወጡ፣ በወር አሥር ሚልዮን ዶላር (በዓመት አንድ መቶ ሃያ ሚልዮን ዶላር) ኢሳትን ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር የሰላምና የፍቅር፣ የብልጽግናና የተስፋ መድረክ ሊያደርገው ይችል ነበር፤ አብዛኛዎቹ ችሎታው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለኢሳት የሚገቡት ቃል ኪዳን ለጥሬ ሥጋና ለመጠጥ የገቡትን ቃል ኪዳን ካላሸነፈ ታማኝ በየነን በያገሩ እየላከ በሚያደርገው ዓመታዊ ቀፈፋ ኢሳት ይገነባል ብዬ ለማመን ያሰቸግረኛል፤ በኢሰመጉ አይቼዋለሁ።
ቀፈፋ ወይም ልመና አንዱና ዋናው የባህል ሕመም ነው፤ እያንዳንዳችን ከዚህ ሕመም ለመዳን በራሳችን ላይ መዝመት የሚያስፈልገን ይመስለኛል፤ በተለይ በአገር ጉዳይ፣ በወገን ጉዳይ ማን ነው ለማኝ? ተለማኙስ ማን ነው? ስለአገሩና ስለወገኑ ችግር የማያውቅ አለ? ለማወቅ የማይፈልግ ይኖራል እንጂ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ችግር ገሀድ ነው፤ በአስከፊ መልኩ ለመረዳት የሚፈልግ በመረረ ቋንቋ የተጻፈውን የዶር. በድሉ ዋቅጅራን ሀገሬ ገበናሽ (ክፍል አንድ፣ ክፍል ሁለትና ክፍል ሦስትን) ያንብብ። አንብቦ ካላለቀሰ፣ አልቅሶ ‹‹ምን ላድርግ!›› የሚል ቁርጠኛነት ያላደረበት በዓመት አንድ ጊዜ በታማኝ ቀፈፋ አገሩንና ወገኑን መርዳት አይችልም፤ እምነቱ ካለ፣ ስሜቱ ካለ በገንዘብ የሚደረግ ማናቸውም እርዳታ የመጨረሻው፣ መናኛው ነው፤ መናኛ የሚያደርገው የገንዘቡ መብዛት ወይም ማነስ አይደለም፤ ለአገርና ለወገን ከዚያ በጣም የበለጠ የሚከፈል ዋጋ በመኖሩ ነው፤ አያቶቻችንና ቅምአያቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በገንዘብ አይመነዘርም፤ እነሱ በሕይወታቸው ያስገኙልንንና እኛ በገንዘብ የሸጥነውን ኩራትና ክብር በገንዘብ ብቻ አናስመልሰውም፤ ቃል ኪዳን እንግባ!
አምስት:- ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ፤ ነገረኛነትን እንዴት እንገራዋለን?
ሳይንሳዊ ውይይትም ወይም ክርክር የሚመራው በሕገ-ኀልዮት ወይም በእንግሊዝኛ ‹‹ሎጂክ›› በሚባለው የአስተሳሰብ መመሪያ ነው፤ ይህንን አዚህ ለመዘርዘር ከባድ ነው፤ ግን ሁለት መሠረታዊ ቁም-ነገሮችን ማንሣት እንችላለን፤ አንደኛው የሕገ-ኀልዮት መንገድ ከዝርዝር ተነሥቶ ወደማጠቃለል የሚሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር የሚወርድ ነው፤ (የትና መቼ እንደሆነ አላስታውስም እንጂ ከዚህ በፊት በጻፍሁት ከታች-ወደላይና ከላይ-ወደታች በማለት እነዚሁኑ መንገዶች ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፤ከታች ወደላይ ከዝርዝር መነሣቱን ሲሆን፣ ከላይ ወደታች ያልሁት ከአጠቃላይ የሚነሣውን ነው፤) በቀላል ምሳሌ ላስረዳ፤ ከበደ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ወርዶፋ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ዘነበች ሁለት ዓይኖች አሏት፤ …. እንዲህ እያልን በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ሁሉ አንድ በአንድ (በዝርዝር) ከገለጽን በኋላ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ወደሚል ትክክለኛ መደምደሚያ (ማጠቃለያ) እንደርሳለን፤ በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ማዳረስ አንችልም፤ ከምናገኛቸው ሰዎች ዘጠና አምስት ከመቶው ሁለት ዓይኖች ያሏቸው ከሆኑ አልፎ አልፎ ያጋጠሙንን ዓይን የሌላቸውን ሰዎች በመጥቀስ ማጠቃለያው አይፈርስም ወይም አይሻርም፤ ከተጠኑት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑት ሁለት ዓይኖች እንዳሏቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው የሚለውን ማጠቃለያ እንደእውነት ተቀብለነው እያንዳንዱን ሰው በተናጠል ሁለት ዓይኖች አሉት ለማለት እንችላለን፤ ይህ ሳይንስ እውቀትን ለማስፋፋት የሚጠቀምበት መንገድ ነው።
ማጠቃለያው ተረጋግጦ ከተቀመጠ በኋላ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር በሚወርደው መንገድም መጠቀም አንችላለን፤ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ከደረስንበት ማጠቃለያ እንነሣና ከበደም፣ ዘነበችም፣ ወርዶፋም ሰዎች በመሆናቸው ሁለት ሁለት ዓይኖች አሏቸው፤ እያልን ከማጠቃለያው ወደዝርዝሩ እንደርሳለን፤ ልብ በሉ ማጠቃለያው የቆመው እያንዳንዱን እውነት በማስተዋል ላይ ነው፤ ከማጠቃለያው የምንነሣው ግን ከሀሳብ ነው፤ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ሀሳብ ተነሥተን ከበደ ሰው ነውና ሁለት ዓይኖች አሉት … እያልን ስለእያንዳንዱ ሰው እንናገራለን።
በሁለቱም የአስተሳሰብ መንገዶች ብዙ ጊዜ አስከፊ ስሐተቶች ይፈጸማሉ፤ አንድ ወይም ሁለት ምሳሌዎችን በመያዝ ቶሎ ወደማጠቃለያ አንዘላለን፤ ሁለት ወንዶች ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ትደርሳለች፤ ወይም ሁለት ሴቶች ያታለሉት ወንድ ሴቶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ይደርሳል፤ በዓለም በሙሉ ያሉ ስንትና ስንት ሚልዮን ሴቶችን በሁለት በሚያውቃቸው ሴቶች ወክሎ መናገር የማሰብ ውጤት ሊሆን አይችልም፤ ማጠቃለያው ከስሜት የመነጨ እንጂ ትክክለኛ አስተሳሰብን ተከትሎ የተገኘ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ሰው የራሱን ስሜት ብቻ እየተናገረ ወደስምምነት ለመድረስ በፍጹም አይቻልም፤ እንዲሁም እውነተኛነቱ ከአልተረጋገጠ ማጠቃለያ ተነሥቶ እያንዳንዱን እዚያ ውስጥ መክተት ወደፍጹም ስሕተት የሚያገባ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል የተሳሳተ ማጠቃለያ ደረሰች፤ ያንን የተሳሳተ ማጠቃለያ ይዞ ሌሎችም ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ማለት አለማሰብ ነው፤ ቀደም ሲል እንደተባለው ወደትክክለኛ ማጠቃለያ ለመድረስ ሰፊ ጥናት ተደርጎ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶው የሚሆኑት ወንዶች አታላዮች መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ብቻ ወንዶችን ሁሉ አይወክሉም።
ብዙ ጊዜ በችኮላና በጅምላ የሚነገሩ ነገሮች ስሕተት አለባቸው፤ በቶሎ ካልታረሙ ክርክር ሲገጥማቸው እየጠነከሩ ይሄዳሉ፤ ለምሳሌ ቀሚስ የሚለብስ ሁሉ ሴት ነው፤ ወይም ሴቶች ሱሪ አይታጠቁም፤ እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች በእውነት ላይ የተፈናጠጠ ሐሰትን የያዙ ናቸው፤ ይህንን ለማፍታታት አልሞክርም፤ ለአንባቢው እተወዋለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜም ንግግራችን የጅምላ ነው፤ ከጅምላ አነጋገር ፈጽሞ ለመውጣት አንችልም፤ ግን አእምሮአችን ማበጠርና ማጣራት እንዲችል፣ ቀጥሎም ተቃውሞ ሲመጣ ለመታረም እንዲዘጋጅ ማስለመድ ይጠቅመናል።
አእምሮው በአንድ ዓይነት ጥላቻ የተመረዘ ሰው ከሱ ዘር፣ ወይም ከሱ ጎሣ፣ ወይም ከሱ ቋንቋ፣ ወይም ከሱ ሃይማኖት … የተለየውን ሰው ሁሉ በስሜት ብቻ እያጠቃለለ በጅምላ ይጠላል፤ ይንቃል፤ ይሰድባል፤ ያዋርዳል፤ እያንዳንዱንም ሲያገኝ በአእምሮው ውስጥ ያስቀመጠውን ምስል እያየ ሰውዬውን ይገምተዋል፤ ሰውዬውን የሚገምተው እሱ ራሱ አእምሮው ውስጥ ባስቀመጠው ምስል ነው እንጂ ሰውዬው በሚናገረው ወይም በሚሠራው አይደለም፤ አንዳንድ ወንዶችም አንዲት ሴት ክፉኛ ስላቃጠለቻቸው ሴትን በሙሉ ይጠላሉ፤ ከአንድ ተነሥቶ ወደጅምላ መዝለል በጣም ከባድ ስሕተት ነው።
ሳይንስ በአብዛኛው የሚጠቀምበት በመጀመሪያው፣ ከዝርዝር ወደማጠቃለያው በሚወስደው የአስተሳሰብ መንገድ ነው፤ የሳይንስ ሕጎች ሁሉ የተገነቡት በዚህ ከዝርዝር ወደአጠቃላይ በሚወስደው አስተሳሰብ ነው፤ እያንዳንዱ ካልታወቀ ሁሉም በአጠቃላይ ሊታወቅ አይችልም፤ የተረጋገጠ እውቀት የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ነገር ነው አንጂ ከጅምላ አይደለም።
በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ንግግር ዋናው ጅምላው ነው፤ ለሰነፍ አእምሮ በጅምላ ማሰቡ በጣም ይቀላል፤ አንዳንዱን እያገላበጡ ከማጣራት ጅምላውን በሩቁና በግርድፉ መፈረጅ ቀላል ቢመስልም ስሕተት ነው፤ ከለመደም አእምሮን ያባልጋል፤ በፖሊቲካ በተለይ የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብና አነጋገር አገርንና ሕዝብን ወደከፋ አደጋ ውስጥ የሚጨምር ይሆናል፤ ለዚህ ነው የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብን በጥንቃቄ ማገላበጥ የሚያስፈልገን፤ ኢሳት በዚህ በኩል ትክክልና በጎ አስተሳሰብን ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አራት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ
እንደሚመስለኝ ከነፍጠኛነት ይልቅ ነገረኛነት ጥሩ የዴሞክራሲ መሠረት ሊሆን ይችላል፤ በእርግጥ ነገረኛነት ለኢትዮጵያውያን የባህል መሠረት አለው ቢባልም በነፍጠኛነት ስር እየታሸ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከነፍጠኛነት ጫና ስር ሲያመልጡና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመደራጀት ሲሞክሩ ሁሌም ነገረኛነት ያይላል፤ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያውያን ማኅበሮች መሀከል ሕግንና ሥርዓትን ተከትሎ የተዋጣለት ማኅበር ብርቅ ነው፤ አብዛኛዎቹ እየተነታረኩ ሲከፋፈሉና ሲዳከሙ የሚታዩ ናቸው፤ የችግሩ መነሻም ሁልጊዜም ሥልጣን፣ ገንዘብና ዝና ናቸው፤ ከነዚህ ሲያልፍም በኢትዮጵያዊነት መሠረት ላይ ብቻ የቆመውን ማኅበር የፖሊቲካ እምነት ወይም የጎሣ ቀለም ለመቀባት በመሞከር ነው፤ በኢትዮጵያውያን ማኅበሮች ላይ ሲታይ የቆየው ኋላ-ቀር አስተሳሰብ በውጭ በተቋቋሙ ቤተ ክርስቲያኖችም ላይ መታየት ጀመረ፤ ባህል ነዋ።
በዘመናችን የተከሰተው ነገረኛነት ከባህላዊው እሰጥ-አገባ ክርክር በጣም የራቀና የዘቀጠ ነው፤ ‹‹ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ከመጠምጠም መማር ይቅደም፤ ነገር ሳያውቁ ሙግት፣ ሳይጎለብቱ ትዕቢት…›› ወዘተ. በሚሉ የሕገ ኀልዮት መመሪያዎች የሚገዛ ሙግትም ሆነ ክርክር፣ ወይም ወግና ጨዋታ ከነገረኛነት የተለየ ነው ለማለት ይቻላል።
የዛሬው ነገረኛነት የአእምሮ ሥርዓተ-ቢስነት አለበት፤ እኩልነትን በትክክል ካለመረዳት የሚገኝ የአእምሮ ብልግና አለበት፤ ዱላ ከያዘ ጋር ነገረኛነት አይኖርም፤ ፍርሃት ያጠፋዋል፤ ሥርዓት የሚመጣው በዱላ ብቻ ነው ከተባለ ውርደት ነው፤ በአንድ በኩል በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በስደተኛነት እኩል ናቸው ከሚል መነሻ፣ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጭቁን አቅመ-ቢሶች በመሆናቸው እኩል ናቸው ከሚል መነሻ ይጀምርና ሌላው ልዩነት ሁሉ ድራሹ ይጠፋል፤ ስለዚህ ማንም በምንም ጉዳይ ቃላትን እየፈተለ እንደዘመኑ ዳንስ ብቻ ለብቻ መንቦጫረቅ የኢትዮጵያውያን የነገረኛነት ባህል ሆኖአል፤ በቅርቡ አንደሰማሁት በዚህ የቃላት መንቦጫረቅ (ፓልቶክ) አንደኛ ሶማሌያውያን፣ሁለተኛ ኢትዮጵያውያን፣ ሦስተኛ ኤርትራውያን ሲሆኑ ሌሎች አፍሪካውያን የሉበትም አሉ፤እውነት ካልሆነ እንርሳው፤ እውነት ከሆነ ግን ብዙ የምንማርበትና ራሳችንን የምናስተካክልበት ምክንያት ሊሆነን ይችላል፤ በቃላት መንቦጫረቅ ለጊዜው በእኩልነት ጸዳል የሚያሞቅ ቢመስልም የኋላኋላ ራስንም፣ማኅበረሰቡንም ይጎዳል።
የሶማልያውያኑንና የኤርትራውያኑን ባላውቅም ስለኢትዮጵያውያኑ ባጭሩ ምስክርነት መስጠት እችላለሁ፤ አብዛኛዎቹ የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ፊደል ከቆጠሩ ራሳቸውን አዋቂዎችና ፈላስፋዎች አድርገው በአደባባይ ለማቅረብ አያፍሩም፤ ግን ያሳፍራሉ፤ ለአንባቢው ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ራሳቸው ሳያውቁት ጀምረው ሳያውቁት ይጨርሱታል፤ በእንግሊዝኛ መጻፍ የማይችሉ ቢሆንም በአማርኛ ጽሑፋቸው እንግሊዝኛ የሚያውቁ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት ሀሳቡንም አጻጻፉንም ያወላግድባቸዋል፤ ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን ከየጋዜጣው ማሳየት ይቻላል፤ ግን አስፈላጊ አይደለም፤ ምክንያትም አለኝ፤ ካላበዙት አንድ ጥሩ ባሕርይን ያመለክታል፤ በድንቁርናም ቢሆን በጣም የሚያስደንቅ በራስ መተማመንን ያሳያል፤ እኔ አምስተኛ ክፍል ሆኜ (የዚያ ክፍል ጓደኛዬ የዓየር መንገዱ ግርማ መኮንን አሁንም አለ) አንድ የሳይንስ አስተማሪ የካቶሊክ መነኩሴ መሬት ትዞራለች ብለው ማስረጃዎቻቸውን ሲደረድሩ እኔ እጄን አውጥቼ ‹‹መሬት አትዞርም፤ ዳዊት ወአጽንአ ለምድር ዲበ ማይ ይላል፤ ብዬ ድርቅ አልሁ፤ እግዚአብሔር ያሳያችሁ፤ እኔ ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፤ አስተማሪዬ ያላቸው እውቀት ለእኔ እሳቸው ከመጡበት አገር ከካናዳም ይርቃል፤ በዚያ ላይ እሳቸው መነኩሴ ናቸው፤ ዳዊትን በየቀኑ ይደግማሉ፤ ስለሃይማኖትም ቢሆን እኔ ከሳቸው ጋር አልወዳደርም ነበር፤ አስተማሪዬ ዝም ብለው ይስቁብኝ ነበር፤ በፈተና ጊዜ ግን ዳዊትን ጠቅሼ አልመለስሁም! ባልለወጥ የትምህርት ነገር በአምስተኛ ክፍል አብቅቶልኝ ነበር፤ እንዲህ ያለውን አጉልና ባዶ በራስ መተማመን በቶሎ ካልቀጩት አእምሮን ያባልጋል፤ በጥሩ መልኩም ቢሆን ነገረኛነት አይወደድም፤ ዳኛቸው ወርቁ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የወጣው ክርክሩን ሊቀበሉት ያልፈለጉ ሰዎች ‹‹ነገረኛ›› (እንደአቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ጉዱ ካሣ››) ተብሎ ነበረ።
አፍ ዳገት አይፈራም ሲባል የአነጋገሩን ትክክለኛነት ለመለካት ሳይሆን የተናጋሪውን አለመፍራትና አለማፈር ለመግለጽ ነው፤ አሽከር በአንደበቱ ውሻ በጅራቱ ሲባልም መናገር ወደላይ እያዩ ለመቀባባት ወይም ለማረጋገጥ ነው እንጂ ይዘቱ ከእውነት ጋር የማይገናኝ ይሆናል፤ ነገረኛ ማለት ደረቅ፣ እውነቱን ለቅቆ ለስለስ የማይል፣ ችኮ-መንቻካ ማለትም ይሆናል፤ ባለሥልጣኖቹ ለመስማት የሚፈልጉትን ብቻ እየመረጠና እያዋዛ ሳይሆን ለሱ የሚታየውን ደረቁን እውነት ይዞ የሚናገር ማለት ነው፤ በግልምጫ፣ በቁጣ፣ በጥቅም፣ ሳይሸነፍ የሚኖረው ነገረኛ ይባላል፤ ባህላችን ነገረኛነትን የሚያጥላላው ለኔ እንደሚመስለኝ ጠመንጃ-ያዥነትን ለማስከበር ነው፤ ሎሌ የሚኖረው መሣሪያ ወይ አንደበት ወይ ጠመንጃ ነው፤ ሎሌ በአንደበቱ ሲናገርም ሆነ በጠመንጃው ሲተኩስ ለጌታው ሲል ለመግደል ወይም ለማቁሰል ነው፤ የራሱ ዓላማም ሆነ ኢላማ የለውም።
ጠመንጃ-ያዥና ጠመንጃ-ያዥ ሲጫረሱ የሚያደርሱት ከባድ ጥፋት ለሰላማዊው ሕዝብም፣ ለአገርም ይተርፋል፤ ነገረኛነት የዚያን ያህል አይጎዳም፤ በተጨማሪም ወደሠለጠነና ሥርዓት ወዳለው እሰጥ-አገባ ክርክር ለመድረስ ከጉልበተኛነት ከመነሣት ይልቅ ከነገረኛነት መነሣቱ መንገዱን ቀና የሚያደርገው ይመስለኛል፤ ነገረኛነት በአጉል እኩልነት ላይ የቆመ ቢሆንም የዱላ ፍርሃት የለበትምና ይሻላል፤ ደግሞም ትምህርት እየተስፋፋ ሲሄድ አጉል ነገረኛነት ለዝናብ እንደተጋለጠ ጨው እየቀለለ ይሄዳል፤ ስለዚህም አጉል ነገረኛነት የሚያስጠላ ቢሆንም ብንታገሠውና ብናርመው ከመደባደብ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ይጠቅመናል፤ እየተራረምን በዚህ መንገድ ብንሄድና ብንለምደው፣ የእውቀትን ጎዳና አገኘነው ማለት ነው፤ ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሔዎችን ማግኘት እንችላለን ማለት ነው።
ሦስት:- ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ
እስካሁን ድረስ ያሳየነው ችሎታ የማጥፋት ወይም የማክሸፍ እንጂ አዲስ ነገርን ወይም አዲስ ሥርዓትን የመፍጠር አይደለም፤ በአለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ሦስት የአስተዳደር ሀሳቦች መቅረባቸውን አውቃለሁ፤ አንዱ በአቶ ሀዲስ አለማየሁ፤ ሁለተኛው በኤንጂኒር-የሕግ ባለሙያ ደመቀ መታፈሪያ፣ ሦስተኛው የኔ ናቸው፤ አእምሮአቸውና ልባቸው በማርክሳዊ-ሌኒናዊ ጦር ተቀስፎ የተያዘባቸው ወጣቶች ሌላ ሀሳብን የማይሰሙበት ጊዜ ነበር፤ ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ጥራዝ-ነጠቅነት ብቻ የሁሉም ዓይነት የእውቀት ምንጭ ነው ብለው በጭፍን የሚያምኑ ወጣቶች በተለይም ከኢትዮጵያዊ የፈለቀ ሀሳብን ለማጥላላት ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን አይቆጥቡም ነበር፤ የሌኒን የጡት ልጆች እርስበርሳቸው ተፋጁና ያሸነፉት ዛሬም ከፋፍለው ይገዙናል፤ የት እንደሚያደርሱን ገና አላወቅንም።
ለኢትዮጵያ ለዘለቄታው ይበጃል የምንለውን የፖሊቲካ እምነትና ሥርዓት እኛው ራሳችን አምጠን ብንወልደው መልካም መሆኑ አይጠረጠርም፤ ግን ከላይ እንደገለጽሁት የኛ ችሎታ ማጨናገፍ ነው እንጂ ወላድና አዋላጅ መሆን አይደለም፤ እሰከዛሬ ለሁሉም የሚሆን መድረክ አልነበረምና መተባበሩ ችግር ሊሆን ይችል ነበር ይሆናል፤ አሁን ግን ኢሳት ሁሉንም ዓይነትና እምነት በእኩልነት ያስተናግዳል፤ ወይም ለማስተናገድ የሚችል ይመስለኛል፤ አሁን በኢሳት የሚሰማው የከሸፈ ቀረርቶና የተስፋ ቀረርቶ ነው፤ የከሸፋን ቀረርቶ እንደታሪክ ትምህርት እንዳንወስደው ጠያቂና ተጠያቂ ሆነው የሚቀርቡት ተጠያቂው አዋቂ ጠያቂው የማያውቅ ሆነው ነው፤ ለዚህም ነው የከሸፈ ቀረርቶ የሚሆነው፤ የተስፋው ቀረርቶም እንዲሁ ነው፤ በኢሳት መድረክ ላይ የሚናገሩት ሰዎች ከአወያዩ ወይም ከጠያቂው ሌላ ሁለት ወይም ሦስት ቢሆኑ አንዱ ሌላውን እያፋጠጠ እውነቱ ሊነጥርና ሀሳብ ሊበጠር ይችል ነበር፤ በውይይት ወይም በክርክር ስላለፈው ለመማር ስለወደፊቱ ለማቀድ ምቹ ይሆን ነበር፤ ለየብቻ ሜዳ እየሰጡ የፉከራ ወይም የማቅራሪያ መድረክ ማድረጉ ግን ብዙ አያራምድም፤ ሁሉም እንደታማኝ ተጨባጭ የምስል ማስረጃዎቹን ይዞ መቅረብ የሚችል ቢሆን እንኳን አንዱን የቀረርቶ ዓይነት ያስቀረዋል ለማለት ይቻላል፤ በተረፈ ግን በቀረርቶ አንማርም፤ በቀረርቶ አናቅድም።
መድረኩን ለየብቻቸው የሚፈልጉት ሰዎች ያለጥርጥር በውስጣቸው አምባ-ገነንት ለመኖሩ ምልክት እያሳዩ ነው፤ የሚሞግታቸው ወይም በጥያቄ የሚወጥራቸው ሰውን የማይፈልጉ ከሆነ ለምን ይጠቅሙናል? እንደዚህ ያሉ ሰዎችንስ መቼ አጣን? በቴሌቪዥኑ ጸዳል ለመሞቅ ብቻ የሚፈልገውን ማስተናገድ ለሌላው አይጠቅምም፤ ከባህላችን የወረስነውን ድካም እያስተነገድን ነው፤ ይህ ለአጠቃላይ ለውጥ እንደማይበጅ የተረጋገጠ ይመስለኛል፤ ይህ ካልተረጋገጠ የኢሳት ልፋት ለምንድን ነው? በኢሳት ላይ የሚቀርበው ሁሉ ስለዴሞክራሲ ይሰብካል፤ ነገር ግን በተግባር ዴሞክራሲ የሚገለጥበትን መንገድ ውይይትና ክርክር አያሳዩም፤ ለምሳሌ ሁለቱ ኦነጎች፣ ሁለቱ ኢሕአፓዎች፣ የጎሣ ድርጅትን እንደፖሊቲካ ፓርቲ የሚቀበሉና የማይቀበሉ፤ ለኢትዮጵያ የሚበጀው ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሆነ የተለያየ አቅዋም ያላቸው ሁሉ ፊት-ለፊት እየገጠሙ ሲከራከሩ አናይም፤ መድረኩን ለየብቻ ካልያዙት በቀር አንደበታቸው አይፈታም፤ በአጭሩ እየተሰበከ ያለው ዴሞክራሲ በኢሳት መድረክ ላይ አይታይም፤ መቼ ሊጀምር ታስቦ ነው?
እኛው ራሳችን በፈጠርነው መሠረት ላይ አብዛኞቻችንን ኢትዮጵያውያን የማይጎረብጥ ሥርዓት ለመገንባት ፍላጎት ያደረብን ይመስላል፤ ኢሳት ከአንድ ባህላዊ ችግር ሰብሮ የወጣ አስተሳሰብ ላይ የቆመ ነው ለማለትም ሳይቻል አይቀርም፤ የጉልበተኛነትን ባህል በነገረኛነት ባህል እንተካው የሚል ይመስላል፤ ከላይ ስጀምር ኢሳት የባህል ይዘት አለበት ያልሁት ነገረኛነትን ነው፤ ኢሳት የጠምንጃ-ያዥነትንና የጉልበተኛነትን ትምክህት ‹‹አከርካሪውን ሰብሮ›› የነገረኛነትን ባህል ስር ለማጠናከር የሚጥር ይመስላል፤ ይመስላል ከምል ነው ብል ደስ ይለኝ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ወሬዎች ይሰማሉ።
ኢሳት አንድ ልዩ ተልእኮ ያለው ቡድን የሚጋልበው ፈረስ ነው ይባላል፤ ኢሳት እንደተለመደው የጥቂት ሰዎችን ኑሮ ለማመቻቸት ገንዘብ መሰብሰቢያ ነው ይባላል፤ ጨረቃንና ጸሐይን ምሥጢር ማድረግ ባህላችን ነው፤ ለማናቸውም ዓይነት ሙከራ የተለየ ዓላማ መስጠት ባህላችን ነው፤ ኢሳትን የፈጠረውን ዓይነት ጉልህ የመተባበር ውጤት ለማስተጓጎል ባህላዊ መሰናክሎች እንደሚፈጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እነዚህን መሰናክሎች ማስወገድ የምንችለው ሌሎች የዴሞክራሲ ባሕርዮችን፣ ማለትም ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የአሠራር ልምድ በማድረግ ብቻ ነው፤ የማሞኘትና የብልጣብልጥ መንገዶች ሁሉ ተሞክረው ወደገደል አፋፍ የሚያመሩ ኮረኮንች መሆናቸውን ሁሉም አውቆታል፤ ጥርጣሬዎች የሚነሡትም በሁለት ምክንያቶች ነው፤ አንዱ ግልጽነትና ተአማኒነት ሲጎድል ነው፤ ሁለተኛው ቀደም ሲል በተለያዩ ቡድኖች የተተለሙትንና የከሸፉትን ሙከራዎች በማስታወስ ነው፤ በዚያ ላይ ጥርጣሬን የሚሰብከው ባህላችን አለ።
የኢሳት ልዩ ዓላማ ምንም ይሁን ምን የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አጠቃላይ ዓላማ የሚያራምድ ከሆነና ለማናቸውም ኢትዮጵያዊ አመለካከት በሩን ክፍት አድርጎ ካስተናገደ ከዚህ በላይ የሚጠበቅበት ተግባር ያለ አይመስለኝም፤ ማናቸውም ዓይነት ሀሳብ፣ ማናቸውም ዓይነት አመለካከት፣ ማናቸውም ዓይነት የፖሊቲካ እምነት በነጻነት የሚነገርበት መድረክ ከሆነ፣ ማናቸውም ዓይነት ሀሳብ፣ አመለካከትና የፖሊቲካ እምነት ያላቸው ሰዎች በግልጽና በነጻነት የሚወያዩበት ወይም የሚከራከሩበት መድረክ ከሆነ ሌላ ምን ይፈለጋል? ወያኔ/ኢሕአዴግ የዘጋው ይህንን ነው፤ ኢሳት ይህንን በር ለሁሉም ከከፈተ ኢትዮጵያውያን ከመታፈን ዳኑ ማለት ነው፤ ስለዚህም የባለቤትነቱ ጉዳይ ችግር ሊፈጥርብን አያስፈልግም።
የኢሳት ዋና ጥቅሙ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወያኔ/ኢሕአዴግ አፈና ለማዳን ብቻ አይደለም፤ ከዚያ በጣም የበለጠና ለዘለቄታው ጠቃሚ የሆነ ነገር አለ፤ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲን ባህል ማስተማር ነው፤ እኔ የዴሞክራሲ ባህል የምለው በነጻነት ላይ ቆሞ ነጻነትን እያራገበ በልበ-ሙሉነት የሌሎችን ነጻነት የሚያከብርና የሚያስከብር ቃልና ተግባር የተስማሙበትና በሕግ ልዕልና የሚዳኙበት ሁኔታ ውስጥ መሆንን ነው፤ ይህንን ባህል በኢትዮጵያ ሕዝብ ኅሊና ውስጥ ለመትከል ቀላል አይደለም፤ በመጀመሪያ በኢሳት ውስጥ የሚሠሩት ሰዎች ለዚህ ጥሩ አርአያ ሆነው መታየት አለባቸው (ጓደኛቸው የተለየ ሀሳብ ሲያቀርብ ግር የሚላቸው በኢሳት ውስጥ እንዳሉ ከአንዴም ሁለቴ ታዝቤአለሁ፤)፤ የተለየ ሀሳብን ለመስማት የማንፈራ ለመሆን መማር ያስፈልገናል፤ አቶ መለስ ዜናዊ የተለየ ሀሳብን የመስማት ችሎታ ቢያዳብር በአበበ ገላው ውርጅብኝ አንገቱን ለዘለዓለም አይደፋም ነበር፤ መቻቻልና መከባበር በዴሞክራሲ የሚመጣ ልዩ ችሎታ ነው፤ ይህ ችሎታ እንደሌለን አውቀንና አምነን ከተነሣን ኢሳት ድንቅ መሣሪያ ይሆንልናል፤ እኛም ኢሳት እንዲከበርና ድምጹ ዋጋ ያለው እንዲሆን ለማድረግ እንችላለን፤ ኢሳት የኢትዮጵያን ሕዝብ በዴሞክራሲ ሲያበለጽግና ሲያጎለብት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ኢሳትን ማበልጸግና ማጎልበት የሚጠበቅበት ይመስለኛል።
ሁለት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ
ልክ ወያኔ/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን መገናኛ ዘዴዎች ሁሉ ለአንድ የወያኔ ዓላማ ብቻ እንዲውል እንዳደረገው ኢሳትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለአንድ ቡድን ዓላማ ተገዢ ለማድረግ የታሰበ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፤ እስቲ ማስረጃ ቁጠሩ ሲባሉ ከስሜትና ከጥርጣሬ በቀር ምንም ተጨባጭ ነገር አይወጣቸውም፤ የተለያዩ ቡድኖች፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ነን ከሚሉ ጀምሮ በሰላማዊ የፖሊቲካ ትግል ተወስነናል የሚሉና በተገኘው በማናቸውም መንገድ ወያኔ/ኢሕአዴግን እንታገላለን የሚሉ ሁሉ በኢሳት መድረክ እንዳገኙ ይታያል፤ ኢሳት የራሱ የፖሊቲካ እምነት የለውም፤ ወይም ሁሉንም የፖሊቲካ እምነቶች ይደግፋል ማለት ይቻል እንደሆነ አላውቅም፤ ዝም ብሎ እምነት የሌለው መድረክ ነው እንዳይባል ወያኔን ተቃዋሚነቱ ጎልቶ የወጣ ነው፤ ኢሳት የጸዳ የዴሞክራሲ መድረክ ነው ከተባለ ጸረ-ዴሞክራሲ አቅዋም ያላቸውን፣ ወያኔንም ጨምሮ ማስተናገድ የሚኖርበት ይመስለኛል፤ ይህ ግን ጎልቶ እየታየ አይደለም።
ዋናው የዴሞክራሲ ችግር ዴሞክራሲ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ዋናው የነጻነት ችግር ነጻነት ነው፤ ዴሞክራሲንና ነጻነትን አልፈልግም የሚል ሰው የለም፤ በቅርቡ ከወጣው የመርስዔ ኀዘን ትዝታዬ የሚል መጽሐፍ ውስጥ አንድ እንቊ የሆነ ነገር አገኘሁ፤ እንደተጻፈ ልጥቀሰው፡-
በአእላፍ ሰገድ ኢያሱ ዘመን፣ በ1672 ዓ.ም. ጥቅምት 10 ቀን የሃይማኖት ጉባኤ ቆሞ ነበርና የቅብዓቶች አፈ ጉባኤ አባ አካለ ክርስቶስና የተዋሕዶዎች አፈ ጉባኤ አባ ኒቆላዎስ በየበኩላቸው ከመጻሕፍት እየጠቀሱ በንጉሡ ፊት በብዙ ተከራከሩ፡፡ በክርክሩም ላይ አባ አካለ ክርስቶስ ተረትቶ ጳጳሱና እጨጌው አወገዙት፡፡ ንጉሡ አእላፍ ሰገድ ዮሐንስም የተዋሕዶዎችን መርታት የቅብዓቶችን መረታት አይተው ‹‹ከበረ ሥጋ በተዋሕዶ›› ተብሎ ዐዋጅ እንዲነገር አደረጉ፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ግን የግል እምነታቸውን ሲገልጡ ‹‹እኔ ራሴ በተረቺዎቹ በኩል ነኝ›› ብለው ተናገሩ ይባላል፡፡
አእላፍ ሰገድ ኢያሱ ከሦስት መቶ ሠላሳ ዓመታት በፊት ሦስት ቁም-ነገሮችን ያስተማረናል፤ አንደኛ ፍትሕ-ርትዕ ከሥልጣን ነጻ መሆኑን የሁለት ወገኖችን ክርክር አዳምጦ፣ የጳጳሱንና የእጨጌውን በውግዘት የተገለጸ ውሳኔ ተቀበለ፤ ሁለተኛ የግል እምነት ከዳኝነት ነጻ መሆኑን ሲያሳይ አሸናፊው ተዋሕዶ መሆኑን አወጀ፤ ሦስተኛ ሃይማኖት የግል መሆኑን ለማሳየት ‹‹እኔ ራሴ በተረቺዎቹ በኩል ነኝ፤›› በማለት የራሱን እምነት አሳወቀ፤ እነዚህ ሁሉ ቁም-ነገሮች ከሽፈው ዛሬ፣ በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. ከሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላ ከባድ ችግሮቻችን ሆነው ለተዋሕዶውም ለእስላሙም ተደንቅረውብናል! ይህ ባለህበት ሂድ! አይደለም፤ ቀኝ-ኋላ ዙር! ነው።
ከላይ ዋናው የዴሞክራሲ ቸግር ዴሞክራሲ፣ ዋናው የነጻነት ችግር ነጻነት መሆኑን ገልጬ ነበር፤ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት በአጼ አእላፍ ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተወሰነም ቢሆን የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ነጻነት በመኖሩ በአደባባይ በሙሉ ነጻነት ክርክር ተደርጎ አሸናፊና ተሸናፊ በይፋ ተለዩ፤ ዛሬ ግን ያንን ያህል የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ነጻነት ስለሌለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተሰንጥቃለች፤ የኢትዮጵያ እስልምናም የመሰንጠቅ አደጋ እያንዣበበበት በመሆኑ እንዳይሰነጠቅ አጥብቆ እየታገለ ነው።
ከዴሞክራሲና ከነጻነት የሚወለደው ችግር በውይይትና በክርክር፣ በሕጋዊ ሥርዓትና በሕግ ልዕልና ይፈታል፤ በአምባ-ገነን አገዛዝ ያለው አፈና ነው፤ ነገር ግን ዴሞክራሲንና ነጻነትን የሚያፍኑ አምባ-ገነኖችና ሎሌዎቻቸው ሁሉ አፈናቸውን የሚያከናውኑት በዴሞክራሲና በነጻነት ስም ነው፤ በደቡብ አፍሪካ አፓርቴይድ መሠረት የነበረው ለነጮቹና ለጥቁሮቹ ለየብቻ ዴሞክራሲና ነጻነት ይበጃል በሚል ነበር፤ ማነው ይበጃል ብሎ የሚወስነው? ሲባል መልሱ ነጮቹ ናቸው ነው፤ ነጮቹ በዴሞክራሲና በነጻነት ለነጮች ብቻ ሳይሆን ለጥቁሮችም ይወስናሉ! ኢትዮጵያም ውስጥ እነአሜሪካ ባርከው የተቀበሉት ክልል-በዘር ከተመሠረተ ሃያ ዓመታት አለፉ፤ ውጤቱ እያቆጠቆጠ ነው፤ ዴሞክራሲንና ነጻነትን እየደፈጠጠ ነው፤ ኢትዮጵያም እየደበዘዘች ነው፤ ከዚህ የአንድ አገር ውርደት የሚጠቀሙት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ እነዚህም ሰዎች ቢሆኑ ለሢሶ ዕድሜያቸው አንኳን አይጠቀሙም፤ ለልጆች የሚተላለፍ ጥቅምም አይኖራቸውም፤ ከኢትዮጵያ ውጭ እንደልብ ተንደላቅቀው የሚኖሩበት አገርም መኖሩ ያጠራጥራል፤ ዛሬ እየተጠቀሙ እንዳሉት ነገም እንጠቀማለን ብለው ማሰባቸው ቂልነት ነው፤ ነገ ራሱን የቻለ ጣጣ ይዞ ይመጣል።
አንድ ፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ
በአለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ እንደኢሳት (የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥንና ራዲዮ) ያለ ኃይል የትኛውንም የኢትዮጵያ አገዛዝ አጋጥሞት አያውቅም፤ በመሠረቱ የኢሳት መሣሪያነት ከባህል ውጭ ቢሆንም የባህል ይዘት አለበት፤ ይህንን ወደኋላ አመለክታለሁ፤ ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ታሪክ በመሠረቱ ሁሌም በኃይል ላይ ቆሞ በኃይል የሚሽከረከር ነው፤ በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ የመጡት አብዮተኞች ሁሉ ይህንን በመሠረታዊነት የመክሸፍ ምንጭ የሆነውን የጉልበት አምልኮት እንደዓላማም እንደመሣሪያም ይዘው የተነሡ ናቸው፤ ዛሬም ቢሆን ተሸናፊዎችም ሆኑ አሸናፊዎች አብዮተኞች የሚያወሩትና የሚጽፉት ከጉልበተኛነት ከረጢታቸው ሳይወጡ ጥፋታቸውን እንደልማት፣ አላዋቂነታቸውን እንደብልህነት በማድረግ ራሳቸውን አታልለው ሌላውን ለማታለል እየሞከሩ ነው፤ አንድም የከሸፈ አብዮታዊ መሪ ያለጠዋሪ ልጅ የቀሩትን እናቶችና አባቶች፣ የብልጣብልጦች መሣሪያ ሆነው እንደወጡ የቀሩትን ወጣቶች በኃላፊነትን ተቀብሎ በእውነት የሚዘክራቸው የለም፤ እነዚያ በየሜዳው በጥይት ነደው ጅብና አሞራ የበላቸው ወጣቶች እንደማንም ሰው ሕይወትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ሌሎች ዓላማዎች ነበሩአቸው፤ ዛሬ ‹‹መስዋእት ሆኑ›› እየተባለ ይነገርላቸዋል፤ ዶሮን ሲያታልሏት ዓይነት ነው፤ ይህንን የሚሉት የራሳቸውን ሕይወት እየሳሱለት ጠብቀው በሌሎች ሕይወት ጉልበተኞች ለመሆን የተመኙት ናቸው፤ በወጣቶቹ አጥንት ላይ ጉልበተኛነታቸውን የተከሉት አጥንቱ እየቆረቆራቸው ይባንናሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፤ በወጣቶቹ አጥንት ላይ ከአሜሪካ የመጣ ድርብርብ ፍራሽ ስላነጠፉበት አጥንቱ መኖሩንም አያስታውሱትም፤ ዛሬም የሚሳሱለትን ሕይወታቸውን በሰፊ ግምብና በታጠቁ ወጣቶች አጥር ይጠብቃሉ፤ በአንጻሩ በምኞት የቀሩት ከንፈራቸውን እየነከሱ ከጠርሙስ ጋር ይታገላሉ፤ ከምኞት ባርነት ወጥተው ለንስሐና ለነጻነት ገና አልበቁም፤ ለንስሐ ሳይበቁ የሞቱም አሉ፤ የመክሸፍ ክፉነት እውነትን ፊት-ለፊት የመጋፈጥ ወኔ ሳያገኙና ንስሐ ሳይገቡ ከነኃጢአት በወጣቶች ደም ተጨማልቆ መሞት ነው፤ የከሸፈውን እንዳልከሸፈ፣የከሰረውን እንዳልከሰረ፣ተሸንፎ የተንኮታኮተውን እንዳልተሸነፈ እያደረጉ የሬሳ ቀረርቶ ማሰማት የማይሰለቻቸው ሞልተዋል፤ ወደፊት መግፋት የሚቻለው ሬሳ ሬሳን ተሸክሞ ሳይሆን፣ ስሕተትን አርሞ የሞተውን ቀብሮ ነው።
በሃይማኖታዊ ቋንቋ ንስሐ አለመግባት ማለት ጥፋትንና ስሕተትን አለማመንና በቅብብሎሽ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ማስተላለፍ ነው፤ ጥፋቱንና ስሕተቱን የማይቀበል ከነጥፋቱና ከነስሕተቱ ዕድሜውን ይጨርሳል፤ ለልጆቹም የሚያወርሰው ያንኑ ጥፋቱንና ስሕተቱን ነው፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ይህንን የጥፋት ውርስና ቅርስ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ወስነን ካየነው ጉዳቱ በጣም የሚያንስ ይመስላል፤ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ ካየነው ግን ጉዳቱ ከባድ ነው፤ ከኋላችን የሚመጡት ሁሉ የሚቀድሙን በሌላ ምክንያት አይደለም፤ ከሃምሳና ስድሳ ዓመታት በፊት ከናይጂርያ፣ ከጋና፣ ከማላዊ፣ ከታንዛንያ፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ እየመጡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ወጣቶች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ አገሮቻቸውን ሲያገለግሉ ነበሩ፤ በኬንያ እንደሮበርት ኡኮ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበረ፤ በታንዛንያ እንደጆርጅ ማጎምቤ ለብዙ ዘመናት በተለያዩ አገሮች አምባሳደር ነበር፤ በዚያን ዘመን ለነዚህ የአፍሪካ አገሮች የተረፈችው ኢትዮጵያ ዛሬ ከእነሱ በታች መሆንዋ ቆሞ ከመቅረት የመጣ ነው፤ ቆሞ መቅረቱ ደግሞ ስሕተትንና ጥፋትን እያዘሉና እሹሩሩ እያሉ ከመንከባከብ የሚመጣ ነው፤ እውነተኛ መልካችንን የምናይበት መስታዋት ሳይኖረን ብዙ ምዕተ-ዓመታት አለፉ፤ አቧራ ሲጠራቀም ከጊዜ ብዛት ተራራ ይሆናል፤ ትንሽ ጉድጓድ ከጊዜ ብዛት ረጅም ገደል ይሆናል፤ ትንሹ ቁስል ከዋለ ካደረ የቆላ ቁስል ይሆንና እንቅልፍ ይነሳል፤ በአንድ ቦታ ላይ አንድ እንቅፋት ደጋግሞ የሚመታው ሰው ረዳት ያስፈልገዋል፤ አለዚያ አንድ ቀን ያው እንቅፋቱ ይገድለዋል።
ኢሳት ለኢትዮጵያ አዲስና ኢትዮጵያዊ አብዮትን የሚያውጅ ይመስላል፤ እስከዛሬ አብዮት የምንለው ሁሉ የተለያዩ አገሮችን የታሪክ ውራጅ በግድ ኢትዮጵያን ለማልበስ የሚሞክር ነው፤ በ1967 ሶሺያሊዝም አዲሱ ሃይማኖት መሆን ሲጀምር በጎንደር በማኅበረ ሥላሴ ኅብረተሰባዊነት (ሶሺያሊዝም) አለ ብዬ ብናገር ውራጅ ሶሺያሊዝምን የሚያመልኩ ብዙ ዘለፋ አወረዱብኝ፤ አሁንም ቢሆን ውራጅ ከመዋስ ገና አልወጣንም፤ የልመና ስልቻችንን ተሸክመን አንዴ በአሜሪካ በር፣ አንዴ በሩስያ በር፣ አንዴ በቻይና በር ላይ እንቅለሰለሳለን፤ ልመና ባህል ነው፤ ለጌታ ማደርም ባህል ነው፤ ሆኖም ሁለቱም ዘዴዎች እድገትንና መሻሻልን አያመጡም፤ መሻሻልን የሚያመጡ ቢሆኑም የሚያስከትሉት ጉዳት ከሚሰጡት ጥቅም የበዛ ነው፤የሚገኘው ግዑዝ ጥቅም የአእምሮና የመንፈስ ውድቀትን በማስከተል ዋጋን ያስከፍላል፤ ይህ ሁሉ ጉዳይ በነጻነትና በሙሉ ልብ ክርክርን የሚጋብዝ ነው፤ ኢሳት ለዚህ ጥሩ መድረክ ሊሆን ይችላል፤ ይሆናል ለማለት ብችል ደስ ይለኝ ነበር።
Teddy says
ክቡር ፕሮፌሰር፤ ውሳጣዊ ስሜትን ኮርኳሪ፣የምናደርገውን ቆም ብለን እንድናስብ መሪ ለሆነው ጽሑፍዎ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር እንዲህ አይነቱን ችግር ነቃሽ፣ አቅጣጫ መሪ እና መፍትሄ ፈላጊ የሆኑትን አባት ይጠብቅልን።
አንባቢዎች ሆይ፤ የክቡር ፕሮፌሰርን መነሻ ሃሳብ (አንድ ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በአማካይ በወር አሥር ዶላር ለመስጠት ቃል ኪዳን ቢገቡና የየዓመቱን ግዴታቸውን በአንዴ ቢወጡ) ለመደገፍ እንወስን፤ ወስነንም ወደ ተግባር እንቀይረው። ውሳኔአችንንም ለኢሳት ቀጥታ በውስጥ ስልካቸው፤ ወይም በጽሑፍ እንግለጽ፤ ገንዘቡንም እናስገባላቸው።
የኢሳት ሃላፊዎችና ባልደርቦችም፤ የሬድዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ቢያዘጋጁ። የፕሮግራሙንም መሪ ቃል፤ ዘመቻ መስፍን ወልደማሪያም-ኢሳትን እንደ ብረት ለማጠንከርና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለስልጣን ለማብቃት እልህ አስጨራሽ ትግል ከ …እስከ… ቀን (የሚል አይነት ነገር ቢሆን)፤ ለዚህ ምላሽ የሰጡትን የኢትዮጵያውያን ወገኖች ለደህንነታቸው ሲባል ቁጥራቸውን ብቻ እንዲሁም የገባውን የገንዘብ መጠን በየጊዜው ኢትሳት ይፋ ቢያደርግ ፤ ፕሮፌሰሩ የጠቆሙት መፍትሄ እውን ይሆናል የሚል እምት አለኝ። እባካችሁ እንሞክረው። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ።