ከዝግጅት ክፍሉ፤ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ አቶ ዳንኤል ክብረት የራሳቸውን አስተያየት የሰጡ ሲሆን ይህንንም አስተያየት ተከትሎ ፕ/ር መስፍን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱንም አስተያየቶች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡
መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ
በዳንኤል ክብረት
ከጥቂት ቀናት በፊት ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ አንድ አነጋጋሪ፣ አከራካሪና አመራማሪ መጽሐፍ አውጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ሃሳባቸውን በአደባባይ፣ ሕዝብ በሚረዳው መንገድና ቋንቋ ከሚገልጡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ልሂቃን አንዱ ናቸው፡፡ በሦስት የመንግሥት ሥርዓት ፕሮፌሰር መስፍን ሃሳባቸውን ሲገልጡ፣ ሲጽፉ፣ ሲከራከሩና፣ መልካም የመሰላቸውን ሁሉ ለሕዝብ ሲያቀርቡና ሲሞግቱ የኖሩ የአደባባይ ምሁር ናቸው፡፡
አብዛኞቹ ልሂቃን በጆርናሎችና በዐውደ ጥናቶች ላይ ከሚያቀርቧቸው ጽሑፎች ባለፈ ለሀገር ሕዝብ ዕውቀታቸውን በሀገር ቋንቋ አያቀርቡም፡፡ በዚህ የተነሣም ታዋቂነታቸውም ሆነ ተሰሚነታቸው በዚያው አካዳሚያዊ በሆነው ክልል ብቻ የታጠረ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን በአማርኛችን ከጣት ቁጥር በላይ የሆኑ መጻሕፍትን አቅርበዋል፡፡ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በሀገራዊ መድረኮች እየተገኙ ያላቸውን ለግሰዋል፡፡
ይህንን መጽሐፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ከራሴም ጋር ሆነ ከሌሎች ጋር ተወያይቼበታለሁ፡፡ ተምሬበታለሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮችንም አንሥቼበታለሁ፡፡ ለመጻፍ ግን ጥቂት ቀናትን መውሰድ አስፈልጓል፡፡ ስለ ሦስት ምክንያት፡፡ ምናልባትም ከእኔ የተሻለ ሰው በጉዳዩ ላይ ይጽፍና ሃሳቤን፣ ያነሣው ይሆናል ብዬ፤ በሌላም በኩል ምናልባትም በሕይተወትና በጤና ያለው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አንድ ነገር ይል ይሆናል ብዬ፣ እንዲያም ባይሆን እነዚህ ሊቃውንትን ያፈራውና እነርሱም ያፈሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል ምልከታውን ያቀርብ ይሆናል ብዬ፡፡ ግን የሆነ አልመሰለኝም፡፡
ይህ አሁን የቀረበው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የኢትዮጵያን ታሪክ የሞገቱበት መጽሐፍ ነው፡፡ ጉዳዩ ገና ከርእሱ ይጀምራል፡፡ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ሲል፡፡ አነጋጋሪ፣ አመራማሪና አከራካሪነቱንም አሐዱ ይላል፡፡ ለመሆኑ ታሪክ ይከሽፋል? የክሽፈት ታሪክ ሊኖር ይችላል እንጂ የከሸፈ ታሪክ ሊኖር ይችላል? የስኬት ታሪክ ይኖራል እንጂ የተሳካ ታሪክ ይኖራል?
ፕሮፌሰር መስፍን ራሳቸው በመጽሐፋቸው ከገጽ 34 ጀምረው ስለ ታሪክ ምንነት ብያኔ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ብያኔያቸውም ታሪክን ‹ዘገባ› ‹መዝገብ› ‹ውለታ› ‹ሰንሰለት› እያሉ ነው የገለጡት፡፡ ይህ ገለጣቸው ደግሞ ታሪክ የማይቋረጠውን የሰው ልጆች ጉዞ የሚያሳይ ዘገባ፣ የትናንቱን የሰው ልጅ ሂደትና አስተዋጽዖ የምናነብበት መዝገብ፣ የትናንቱ ማኅበረሰብ ያቆየልን ውለታ ነው፡፡ የትናንቱንና የዛሬውንም የሚያስተሣሥር ሰንሰለት ነው፡፡
እንዲያ ከሆነ ደግሞ ታሪክ የአንድን ማኅበረሰብ የስኬትም ሆነ የክሽፈት፣ የድልም ሆነ የሽንፈት፣ የውጤትም ሆነ የኪሳራ፣ የልዕልናም ሆነ የተዋርዶ ጉዞ የሚያሳየንና የምናጠናበት፣ የምንመዘግብበትና የምናይበት ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ክሽፈቱ እናይበት ይሆናል እንጂ ራሱ የሚከሽፍ አይመስለኝም፤ ስለ ስኬቱ እናጠናበታለን እንጂ ራሱ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ ሰው የስኬት ታሪክ ይኖረዋል እንጂ ታሪኩ አይሳካለትም፡፡ የሽንፈት ታሪክም ይኖረዋል እንጂ ታሪኩ አይሸነፍበትም፡፡ ለዚህ ነው አከራካሪነቱ፣ አነጋጋሪነቱና አመራማሪነቱ ከርእሱ የሚጀምረው፡፡
ያንን ብንሻገረውና ታሪክ ይከሽፋል ብንል እንኳን መከራከራችንንና መመራመራችንን አናቆምም፡፡ ‹እውነት የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል? አንድን ታሪክ ከሽፏል ወይም ተሳክቷል የሚያሰኘው ምን ምን ሲሆን ነው? የሚሉትን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የምናጣው ታላቁ ነገር ይኼ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለታሪካችምን መክሸፍ ማሳያ ናቸው ያሏቸውን ነገሮች ከማንሣታቸው በቀር ይህንነ ነገር አላብራሩልንም፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ያጣሁት ታላቅ ነገር የሚመስለኝ ይኼ ነው፡፡ የታሪክን ‹ክሽፈትና› ስኬት› መበየኛ ነገሮችን አስቀድመው በማሳየት፤ አንድ ታሪክ ‹ከሸፈ. ወይም ‹ተሳካ› የሚያሰኙትን መመዘኛዎች በመተንተን፣ በዚያም መሠረት የኢትዮጵያን ታሪክ እየገመገሙ እዚህ እዚህ ላይ እንዲህ ስለሆንን፣ በዚህ መመዘኛ መሠረት ከሽፈናል ይሉናል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን ሌላ አካሄድ መርጠዋል፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ዋናውን ቦታ የያዙት ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ከእነርሱ በፊት ሌሎች የታሪክ ሰዎችም እየቀረቡ ሂሳቸውን ተቀብለዋል፡፡ እኔ እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍንን መጠየቅ የምፈልገው ሁለት ጥያቄ ነው፡፡
የመጀመርያው የታሪክ ክሽፈትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንዴት ነው የተገናኙት? የታሪክ ክሽፈትን ለማሳየት የታሪክን ሂደት ተከትሎ አንድን ሁነት ከየት ተነሥቶ የት እንደደረሰ በመተንተን፣ ያም ሁነት ከሽፎ ከሆነ የከሸፈበትን ምክንያት ማቅረብ ሲገባ ታሪካችን ከሽፏል ብንል እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?
ለእኔ ይህ አካሄድ አንድ ሰው ሌላ ሰውን የገደለበትን ዜና የሠራውን፣ ለዜናው ትንታኔ ዜና ያቀረበውን ጋዜጠኛና ተንታኝ የግድያው ወንጀል አባሪ ተባባሪ፣ ወይም ደግሞ ለግድያው ምክንያትና መነሻ አድርጎ እንደማቅረብ ነው፡፡ ዘጋቢውን ‹ወንጀለኛ› ማለትና ዘገባውን ‹የወንጀል ዘገባ› በማለት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ዘጋቢው ወንጀለኛ የሚባለው የሠራው ዘገባ ሕግን የተላለፈ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ዘገባውን የወንጀል ዘገባ የሚያደርገው ግን ስለ አንድ ስለተፈጠረ ወንጀል የቀረበ ዘገባ ከሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ጥናት ለብቻው ቢተነትኑትና ያም ትንተና የታሪክ አጻጻፋችንና አተናተናችን የተሳካ ነው ወይስ ያልተሳካ? አስመስጋኝ ነው ወይስ አስነቃፊ? ተመስጋኝ ነው ወይስ ተነቃፊ? የሚለውን ቢተነትኑት እስማማ ነበር፡፡
አንድ ኦዲተር የአንድን ድርጅት ሂደት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ያ ድርጅት ከስሮ ከሆነ የኪሳራውን መጠንና የኪሳራውንም ምክንያት ያቀርባል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ያ ኦዲተር የራሱ ሕፀፆች ይኖሩበታል፡፡ ሁለቱ ነገሮች ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ የድርጅቱ ኪሳራና የድርጅቱን የኪሳራ ሪፖርት የሠራው ባለሞያ ሕፀፅ፡፡ የዚህን ድርጅት ታሪክም አንድ የታሪክ ባለሞያ ሊዘግብ፣ ሊተነትንና የኪሳራውንም መነሻና ሂደት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ የታሪክ ባለሞያ ይህንን ታሪክ ሲዘግብና ሲተነትን ድክመቶች ሊኖሩበት ይችላል፡፡ የሁለቱ መገምገሚያ ግን ይለያያል፡፡ የድርጅቱ መክሰርና የታሪክ ባለሞያውም የከሰረ ድርጅትን ታሪክ መዘገቡና መተንተኑ ‹የከሰረ የታሪክ ባለሞያ› አያሰኘውም፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ላይ የተተቹት የታሪክ ባለሞያዎችም በፕሮፌሰር ሐሳብ ብንስማማ እንኳን ‹የከሸፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ በየአንጻራቸው ዘገቡ፣ ተነተኑ› እንጂ እነርሱ ራሳቸው የከሸፉ የታሪክ ባለሞያዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል ቢባል እንኳን ለዚያ ለከሸፈው ታሪክ ማጣቀሻ ይሆኑ ይሆናል እንጂ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ ሥር የእነርሱ ሥራ መተንተን አልነበረበትም፡፡ ምንልባት ፕሮፌሰር ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ› የሚል ርእሰ ጉዳይ ቢያነሡ ኖሮ የማርያም መንገድ ባገኙ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ በርግጥ ከሽፏል? በሚለው ከተስማማን ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብ ችግሮችና የአተያየይ ሳንካዎች ማንሳታቸውና በዚያ ላይ ትችት ማቅረባቸው አልነበረም ችግሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱን አስችለውና ደረጃውን ጠብቀው ደግመው ደጋግመው ቢሄዱበት ለሁላችንም የዕውቀት በረከት የሚሆን ነው፡፡ ነገር ግን ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርእስ ታሪክ ጸሐፊዎቹን ከታሪኩ ጋር አብሮ መውቀጥ ‹ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ› ዓይነት ይሆናል፡፡ ‹ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ይዘንባል› ያለውን የሜትሮሎጂ ባለሞያ ‹ለምን ዘነበ› ብሎ እንደመውቀስ ነው፡፡
ሌላው ሁለተኛው ጥያቄዬ የተነሡትን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የሚመለከት ነው፡፡ በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ ላይ በዋናነት ተነሥተው የተተቹ አምስት ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሊቃውንት አሉ፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይና ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፡፡ ከእነዚህ ሊቃውንት መካከል ከፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴና ከፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በቀር ሌሎቹ ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ በሕይወት ከሚገኙት ከሁለቱ ሊቃውንት መካከልም ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ታምመው በድካም ላይ ነው የሚገኙት፡፡
ምንም እንኳን በአንድ መጽሐፍ ላይ የሚደረግ ክርክርና ሂስ ሰዎቹ መልስ ሊሰጡበት፣ ሂሱንም ሊቀበሉበት ዘመን ብቻ መሆን አለበት ባይባልም፣ ይህ ዕድል ካለና ከነበረ ግን ይመረጣል፡፡ ቢያንስ ስለ ሦስት ነገር፡፡ አንደኛ እነዚህ ሊቃውንት ሂሱን ተመልክተው እንዲሻሻሉ፤ ሁለተኛም እነዚህ ሊቃውንት የእነርሱንም አተያይ የማቅረብ ዕድል እንዲያገኙ፤ ሦስተኛ ደግሞ ነገሩ ፍትሐዊ እንዲሆን፡፡ አንድን አካል መልስ ለመስጠት በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ ማሄስና መውቀስ ከሞራል አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ የሀገሬ ሰው ‹ሙት ወቃሽ አትሁን› የሚለው ሙት መወቀስ ስለሌለበት ሳይሆን ‹መልስ ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ› ማለቱ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የነ ፕሮፌሰር ታደሰ፣ የነ ዶክተር ሥርግውና የነ ፕሮፌሰር መርዕድ ዘመነኛ ናቸው፡፡ ይህ ዛሬ የሰጡት ትችት በዚያ በዘመነኛነታቸው ወቅት ቢሆን ኖሮ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚኖር ክርክር ታላቅ ዕውቀት በተገበየ ነበር፡፡ በርግጥ ልዩ ልዩ መዛግብትን ስናገላብጥ አንዳንድ ክርክሮች እንደነበሩ ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ኅትመቶች ሲወጡም ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ የፕሮፌሰር መስፍን ሐሳብ ቀርቦ ክርክር አልተደረገበትም፡፡
የፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት church and state in Ethiopia የሚለው መጽሐፍ የታተመው በ1964 ዓም ነው፡፡ የዛሬ 41 ዓመት፤ የዶክተር ሥርግው Ancient and medieval Ethiopian History to 1270 የታተመው በ1964 ዓም የዛሬ 41 ዓመት ነው፡፡ የፕሮፌሰር መርዕድ ጽሑፍ political geography of Ethiopia at the beginning of 16thc. የታተመው በ1966 ዓም ነው፡፡
አንግዲህ ይህንን ሁሉ ዘመን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ትችቱ መቅረቡ ነው ለእኔ የሞራል ጥያቄ እንዳነሣ ያደረገኝ፡፡ እነዚህን ሰዎች በዘመን ያላገኘናቸው፤ ‹ጥንት› በምንለው ዘመን የነበሩ ቢሆኑ ኖሮ የሞራል ጥያቄው ሊነሣ ባልቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእኛው ጋር የነበሩ፤ መልስ ሊሰጡበትና ትችቱን ሊቀበሉበት በሚችሉት ዘመንም ሊጻፍላቸውም፣ ሊጻፍባቸውም የሚቻል፣ ነበርና ምነው? ያሰኛል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያን ጥንታዊና የመካከለኛው ዘመን በማጥናትና በመተንተን እንደ ሥርግው፣ እንደ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትና እንደ ፕሮፌሰር መርዕድ ያለ ሰው ዛሬ አላገኘንም፡፡ በየመድረኩም ሆነ በየመዛግብቱ እንደ ብሉይና ሐዲስ የሚጠቀሰው የእነዚሁ ቀደምት አበው ሥራ ነው፡፡ የእነዚህን ቀደምት አበው ሥራዎች በማይመለከታቸው ርእስና ጉዳይ ላይ ማንሣትም ሆነ ማሄስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለቡድኑ መሸነፍ ተጨዋቾቹንና አሠልጣኙን፣ ፌዴሬሽኑንና ኮሚሽኑን መጠየቅ ሲገባ የጨዋታውን ዘጋቢና ተንታኝ ጋዜጠኛ መውቀስ ይመስላል፡፡
ከቀድሞ ጀምሮ በልሂቃኑ ዘንድ ከዕውቀት ክርክር የዘለለ ሌላ የጎንዮሽ መጎሻሸምና መነካካት እንደነበረ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ምሁራን ታሪክ የሚያጠና ሁሉ የሚደርስበት ነው፡፡ አንድ ማሳያ ብቻ ላንሣ፡፡ አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህራንና በሌሎች መካከል ‹ጠብ› ተፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም ለአብዮቱ እንቀርባለን የሚሉ ምሁራን እነዚህን የታሪክ ክፍል መምህራን ‹ደብተራዎች› እያሉ መውቀስና እንደ አድኅሮት ኃይላት መመልከት ያዘወትሩ ነበር፡፡
ይህ ነገር እየከረረ መጣና አንድ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ምሁር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ ሄደው እነዚህን የታሪክ መምህራን በፀረ አብዮትነት ከሰሱ፡፡ በወቅቱም ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ቤተ መንግሥት እንዲመጡ ተጠሩ፡፡ እኒህ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዶክተር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ በማን በኩል እንደ ሄዱ ፕሮፌሰር መስፍን ያውቃሉ፡፡
ፕሮፌሰር ታደሰ ከሌሎቹ ምሁራን ጋር በጉዳዩ መክረው ወደ ቤተ መንግሥት ተጓዙ፡፡ አንዳች ክፉ ነገር እየጠበቁ ነበር የገቡት፡፡ መንግሥቱ በክብር ተቀበላቸውና የአብዮቱን ታሪክ እንዲጻፍ መፈለጉን ነገራቸው፡፡ ፕሮፌሰርም ልባቸው መለስ አለች፡፡ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ሞያዊ ሥራ ለመሥራት እንደሚቻል ገለጡ፡፡ መንግሥቱም ፕሮፖዛል እንዲያዘጋጁ ነግሮ በክብረ ሸኛቸው፡፡ ከመሸኘቱ በፊት ግን ‹ከዶክተር እገሌ ጋር ቅሬታ አላችሁ መሰል፣ አንዳንድ ነገር ነግሮኝ ነበር፤ እዚያው ተነጋግራችሁ ፍቱት› አላቸው፡፡ እርሳቸውም እንፈታዋለን ብለው ከቤተ መንግሥት ወጡ፡፡
አሁን እዚህ መጽሐፍ ላይ ቤተ መንግሥቱን አየሁት፡፡
ምንጭ፤ የዳንኤል ክብረት እይታዎች
የፕ/ር መስፍን ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የዳንኤል ክብረት ክሽፈት
መስፍን ወልደ-ማርያም
አቶ ዳንኤል ለመናገርና ለመጻፍ ያለው ፍጥነት በሚናገርባቸው ጉዳዮች ላይ ካለው እውቀት ጋር አይመጣጠንም፤ እንዲያውም ያውቃል እንዲባል የሚጽፍ አንጂ አውቆ የሚጽፍ አይመስልም፤ አቶ ዳንኤል ሳላውቀው በጻፈው ላይ አስተያየት ስሰጥ ይህ ሁለተኛዬ ነው፤ ከዚህ በፊት በአንድ ጋዜጣ ላይ በጣም የታወቀውን የአየርላንድ ችጋር በ150 ዓመታት ያህል አቅርቦት በማየቴ አስተያየት ሰጥቼበት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ስለመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ በጻፈው ላይ አጭር አስተያየት ልስጥ፤ እንዲያው እንትንን እንትን ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል የሚባለውን በመከተል እንጂ ትርፍ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፤ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ካድሬዎች ደብተራዎችም ጭምር ማነብነብን እንደተናጋሪነት ሠልጥነውበታል፤ ስለዚህም ሰውም ማነብነባቸውን እንደእውቀት እየወሰደው ይወናበዳልና በጊዜው መልስ መስጠት ግዴታ ይመስለኛል፤ የሰው ልጅ በምን ይታፈራል? በወንበር፤ በወንበር አይደለም በከንፈር፤ ይባላል፡፡
ነገር ሳላበዛ ጥቂት ነጥቦችን በማንሣት የአቶ ዳንኤልን የማንበብ ችሎታና የተንኮል ክህነት ብቻ ለአንባቢዎች ላሳይ፤ ስለአስተያየቱ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡
አንደኛ፣ ደጋግሜ እንብቤዋለሁ ይላል፤ ይህንን ባይነግረን ጥሩ ነበር፤ በመናገሩ ብቻ እንዳናምነው ማስረጃ ይሰጠናል፤ ያላነበበውን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ ማለት ያስፈለገበት አስገዳጅ ምክንያት ምንድን ነው? አውቃለሁ ብሎ በመነሣት ለማሞኘት ወይም ለማታለል ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት ያለ አይመስለኝም፤ እንደአቶ ዳንኤል ያለውን ለማስጠንቀቅ ደጋግሜ አነበብሁት በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የዩኒቨርሲቲን ዓለም የማያውቁ ሰዎች ሌላ ትርጉም በመስጠት እንዳይሳሳቱ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአካል በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው ልባቸው ከደብተራ ተንኮል ላልጸዳም ቀናውን የእውነት መንገድ እንዲያመለክታቸው እመኛለሁ፤›› የሚል ተጽፎ ነበር፤ ይህንን አቶ ዳንኤል አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡፡
ሁለተኛ፤ ‹‹ለመሆኑ ታሪክ ይከሽፋል? የክሽፈት ታሪክ ሊኖር ይችላል እንጂ የከሸፈ ታሪክ ሊኖር ይችላል? የስኬት ታሪክ ይኖራል እንጂ የተሳካ ታሪክ ይኖራል? አንድን ታሪክ ከሽፏል ወይም ተሳክቷል የሚያሰኘው ምን ምን ሲሆን ነው? … በመጽሐፉ የምናጣው ታላቁ ነገር ይሄ ነው፤›› በዚህ ትርጉም የማይሰጥ የቃላት ድርደራ ላይ ምንም አስተያየት መስጠት አይጠበቅብኝም፤ ይቀጥልና ‹‹.. የታሪክን ክሽፈትና ስኬት መበየኛ ነገሮችን አስቀድመው በማሳየት አንድ ታሪክ ከሸፈ ወይም ተሳካ የሚያሰኙትን መመዘኛዎች …›› ይላል አቶ ዳንኤል፤ ካላነበበው ‹ደጋግሜ አንብቤዋለሁ› በማለት ብቻ ጭንቅላቱ ውስጥ አይታተምለትም፤ የሚከተለው እንደሚነበብ ሆኖ የተጻፈ ነበር፤ ‹‹መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው፤›› ይህ ተጽፎአል! አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡፡
ሦስተኛ፤ ‹‹ታሪክ ጸሐፊዎቹን ከታሪኩ ጋር አብሮ መውቀጥ ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ዓይነት ይሆናል››! ይላል፤ ይህ ሰው አንብቤአለሁ፤ አውቃለሁ፤ ሲል በመሃይም ድፍረት ነው፤ የሚከተለው ተጽፎአል፤ ‹‹አንድ ሰው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ከጻፈ ‹‹ማንም ዜጋ በጉዳዩ ላይ የመሳተፍና ሀሰቡን በሙሉ ነጻነት የመስጠት መብት አለው፤ አለዚያ በየጓዳችን በሐሜት ብቻ እየተዘላዘልን እውነትን አንጥሮ በአደባባይ የማውጣቱን ዘዴ ሳንማር ሌላ ሦስት ሺህ ዓመታት እንቀጥላለን፤›› ይህንን አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡፡
አራተኛ፤ በራሱ ላይ ሲፈርድ ቶሎ ሳይጽፍ መቆየቱን ለማስረዳት ምናልባት ከእሱ የተሻለ ሰው ቢጽፍ፣ ምናልባት ፕሮፌሰር ባሕሩ ቢጽፍ፣ ምናልባት የታሪክ ሊቃውንትቱ ተማሪዎች ቢጽፉ፣ ምናልባት የታሪክ ክፍሉ ቢጽፍ በማለት ጠብቆ እንደነበረ ይገልጻል፤ እነዚህ ሁሉ የሱን ምኞት እሱ በፈለገው ፍጥነት ሳያሙዋሉለት ቀሩና እነፕሮፌሰር ባሕሩን ላጨበት ሥራ ራሱን አቀረበ፤ የሱ ድፍረት የሌሎቹን እውቀት የሚበልጥ ለማስመሰል ጻፈ፤ ድፍረቱን ልናደንቅለት ይገባል፤ በማያውቁት ጉዳይ ደረትን ገልብጦ በሙሉ እምነት ማነብነብ የካድሬዎች ባሕርይ ሆኖ በቤተ እግዚአብሔርም ገብቶአል፡፡
አምስተኛ፤ አቶ ዳንኤል ከአዋቂነት ወደመንፈሳዊነት ይሸጋገርና ‹‹አንድን አካል መልስ ለመስጠት በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ መሄስና መውቀስ ከሞራል አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም፤ የሀገሬ ሰው ‹ሙት ወቃሽ አትሁን››› እዚህ ደግሞ ጭራሽ ሊወጣበት ከማይችለው የአለማወቅ ማጥ ውስጥ በድፍረት ገባ! ‹‹ሞራል›› ስለሚለው ነገር ምንም እንደማያውቅ ሳያውቅ አወጀ፤ ድፍረት ብቻውን በምንም መንገድ እውቀት አይሆንም፤ ለመራቀቅ ፈልጎ ራሱን በአለማወቅ አዘቅት ውስጥ ከተተ፡፡
ስድስተኛ፤ በጽሑፉ መደምደሚያ ላይ የደብተራ ተንኮል አፈትልኮ ይወጣል፤ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ያነሣና በደብተራ ተንኮል አንዱን ‹‹ዶክተር›› የሚለውን መልክ የሌለውና ስም የሌለው የደብተራ ምሥጢር ያደርግና፤ ‹‹እኒህ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዶክተር ወደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ በማን በኩል እንደሄዱ ፕሮፌሰር መስፍን ያውቃሉ፤›› ብሎ ይለጥፍብኛል፤ እግዚአብሔር ያሳያችሁ ስሙን ያልጠቀሰውንና የማላውቀውን ሰው የእኔን ስም ጠርቶ እንደማውቀው አድርጎ ሌላ ስሙን ያልጠቀሰውንና እኔ የማላውቀው ‹‹ዶክተር›› ወደመንግሥቱ ያቀረበ እያለ ውሸት ሲያጠነጥንና ሲፈትል ጊዜ ያጠፋበት ምክንያት አልገባኝም፤ ተንኮሉ እዚህ ላይ አያበቃም፤ ታደሰ ታምራትን ‹‹መንግሥቱ ከመሸኘቱ በፊት ግን ‹ከዶክተር እገሌ ጋር ቅሬታ አላችሁ መሰል፤ አንዳንድ ነገር ነግሮኝ ነበር፤ እዚያው ተነጋግራችሁ ፍቱት፤ አላቸው፤›› ይልና የመጨረሻዋን የደብተራ ተንኮል ጣል አድርጎ ይደመድማል፤ ‹‹አሁን እዚህ መጽሐፍ ላይ ቤተ መንግሥቱን አየሁት፡፡›› ምን እንዳየ፣ የት እንዳየ፣ ምንና ምን እንደተገናኘ የደብተራ ምስጢር ነው፤ ያቀረበውን ሁሉ የማን ባለሙዋል ሆኖ ያገኘው እንደሆነም አይናገርም፤ እንዲህ ያለ ሞላጫነት! ስለእውቀት ከተጻፈ መጽሐፍ ተነሥቶ ወደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጓዳ ገብቶ፣ ስሙ የማይጠራ ዶክተርን መነሻ አድርጎ፣ ይህን ሁሉ እኔ እንደማውቅ ተናግሮ በድንቁርና ምርጊት ይደፍነዋል! እንዲህ ያለ ሰው ስለእውቀት ለማውራት ለምን ይነሣል? ከበሽታ በቀር ምን ሌላ ይገፋፋዋል?
Dawit says
‹‹.. የታሪክን ክሽፈትና ስኬት መበየኛ ነገሮችን አስቀድመው በማሳየት አንድ ታሪክ ከሸፈ ወይም ተሳካ የሚያሰኙትን መመዘኛዎች …›› ይላል አቶ ዳንኤል፤ ካላነበበው ‹ደጋግሜ አንብቤዋለሁ› በማለት ብቻ ጭንቅላቱ ውስጥ አይታተምለትም፤ የሚከተለው እንደሚነበብ ሆኖ የተጻፈ ነበር፤ ‹‹መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው፤›› ይህ ተጽፎአል! አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡
Mike says
The worst article by Professor Mesfin. Professor Mesfin usually writes in articulative way but in his response to Daniel’s critisism of his recent work he resorts to personal attack. This is very unprofessional.
Gemoraw says
interesting in both side ,but I still can’t get the answer from the professor in its critics about the “moral” issues on the fitth underlined question by Dnieal ?.I wander why professor prefer to jump it and use much rough words and show him self as if, that he is more pure in mind than the critisizer ?some of the readers still share some facts from Danieal k ,becuase during the dergue rigim there was a lot rumors about professor mesfin how that he was thirsty of political power ,by divide and rule the campass atmosphere .he was even very attached to the regim by the time on determine ethiopians political issues ,for instance , on the fate of those 60th ministers in prison, and, on the regional autonomy political issues,and on ethio eritreans politics .and some of us read the book that was telling the biograpy of Mengistu Hailemariam and in this book the name of the professor Mesfin and his political involvement was clearily adressed by colonel mengistu H ,so I dought that Danieal K critics are not coming from no where!
Abcd says
As I thought, The comment of Prof. Mesfin is unusual whether the comment of Daniel Kibret is right or not. He commented what he saw as one person on his blog, it has negative as well as positive side. The things that all he said do not have to be true. Just this is a comment. But in the case of prof. undoubtdly he has a right to oppose or accept any thing based on his book. However, the words that, was used by prof. to show how the idea of Daniel is wrong, is the same as insult. He has a right to oppose in a proper manner. but the words do not give a comfort for any one who read it. Personaly, I respect both of them. the comment of the prof. seems revenge for the comment of daniel instead of answer.
inkopa says
“ነገር ሳላበዛ ጥቂት ነጥቦችን በማንሣት የአቶ ዳንኤልን የማንበብ ችሎታና የተንኮል ክህነት ብቻ ለአንባቢዎች ላሳይ፤ ስለአስተያየቱ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡”
yihenen leb yelual !!!
black dove says
Look how the Professor clearly addresses his idea, this one is also another floor for the so called decon Daniel and for the rest of us. This is how we could bring changes, “think before you speak” , i think daniel has not get the right truck to run…he was close to the Ethiopian Ortodox Church through MahberKidusan, they admire him first and the kick his ass when they get Know him and now his playing the back and forth arround there! Daniel please wake up and break up with the blogs , this is the time to make change please get learn…then you could speak proudly and write on the blogs ….may be you fell that your followers admiration as a hood of covenant but that’s not the truth , do u consider the damage of misleading or biasing the crowd? i don’t have to say much the professor has told u much if have got the heart for change ..i belive that’s enough!
Nebiyu Sirak says
ፕሮፌሰር መስፍንን እጂግ በጣም የማከብራቸው ምሁር ናቸው፡፡ ለሰው ልጅ ሰባዊ መብትና ለኢትዮጵያዊነት ክብርን ያደረጉትንና እያደረጉት ያለውን ድፍረት የተሞላበት ትግልም አድናቂ ከመሆን ባለፈ በአባቱ ምሁር እኮራባቸዋለሁ፡፡ አዲሱ መጽሃፋቸውን ሳላነበር ከዳናኤል ጋር የተለዋወጡጥን እሰጣ ገባ ምላሽ ተመልክቸ ግን በፕሮፌሰር አዝኛለሁ ! አመላለሳቸው ከመስመር ያለፈ መስሎኝላና ነው ቅያሞቴ !
ነቢዩ ሲራክ
kaleb says
ታዘብኩዎት !
የርስዎ ታሪክ ራሱ – አንድ የክሽፈት ታሪክ እንደሆነ ይህ የኑዛዜ ጽሁፍዎት ያሳያል።
girum says
The worst article by Professor Mesfin. Professor
Mesfin usually writes in articulative way but in his
response to Daniel’s critisism of his recent work
he resorts to personal attack. This is very
unprofessional.