ስንኖር በዚህ አለም • • • ቆመን ለመራመድ፣
ጫናውን ለመቻል • • • ግፊያውን ለመልመድ፣
አቀበት ለመውጣ • • • ቁልቁለት ለመውረድ፣
ጠንክሮ መጓዝ ነው • • • የለም መንገዳገድ።
እኛ ያምላክ ልጆች ~ ባምሳሉ የሰራን፣
እንደ ምድር አሸዋ ~ ምድርን የሞላን፣
ፈጣሪ ሲፈጥር ~ ከአፈር ሲሰራን፣
“ብዙ ተባዙ” እንጂ ~ መች ተጋፉ አለን?
እንደ ቃሉም ሆነ = እልፍ አእላፍ ሆንን፣
ላይ በላይ ተዋለድን = እንደ አሸን ፈላን፣
ምድር ተጥለቀለቀ = አለምንም ሞላን፣
መሬት ተጣበበች = ቦታ አልበቃ አለን፣
አንዱ ባንዱ አሴረ = እርስ በርስ ተጋፋን፣
መንገድ ለማስለቀቅ = ጥሎ ማለፍ ጀመርን።
ባምሳሉ የፈጠረን • • • እኛ ያምላክ ልጆች፣
ሰብእናው ጎሎን • • • ሆነን እንደ ጥጆች፣
ግጦሹን ለማግኘት • • • ሳሩን ለማሻመድ፣
ደካማውን ጥለን • • • ባናት ላይ መራመድ፣
ሆኗል የኛ ነገር • • • የዘመን ትሩፋት፣
እራስን ለማትረፍ • • • ከመንጋው መጋፋት፣
የት ያደርሰን ይሆን?• • • ምን ያህል ያስሄደን?
የከብት አስተሳሰብ • • • የጥጃ ራስ ይዘን?
ብሌን ከበደ 5/12/2014
Leave a Reply