በጥር 7/2007 ሐሙስ ዕለት በሐመር ወረዳ በ”ላላ” ቀበሌ በሐመር ብሔረሰብ አርብቶ አደሮችና ፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት የደረሰዉ ጉዳት የሚከተለዉን ይመስላል፤
ሀ/ የሞቱ–
1. ሻምበል ለማ አሸናፊ
2/ ወ/ር ሙሴ ማቱሳላ
3/ ወ/ር ደፋሩ ጦና
4/ ወ/ር ካሬ
5/ ወ/ር በኃይሉ
6/ ስሙ ለግዜዉ ያልታወቀ የልዩ ኃይል ባልደረባ
7/ ስሙዋ ለግዜዉ ያልታወቀ ሴት ባለሙያ
8/መምህር መሳይ ነሽ መርነህ
ለ/ የቆሰሉ
1/ አቶ ቹሜሬ የረር /የደቡብ ኦሞ ዞን ፍትህ ጸጥታና ደንብ ማስከበር ምክትል ሀላፊ
2/ ምክትል ሣጅን ጌታሁን ቶላ
3/ ወ/ር ተሰማ መሰረት
4/ ወ/ር ጌታቸዉ ጻንቃ
5/ ወ/ር ቱላ ኪያ
6/ ባሻ ወንድማገኝ ጨነቀ
7/ ወ/ር ሚልኪያስ ግራኝ
8/ ወ/ር ዘለቀ (አባታቸዉ ያልታወቀ)
9/ አቶ ደምሳሽ ሞላ (የዞኑ ሴቶችና ሕጻናት መምርያ ሾፌር)
የሐመር ወረዳ ፍትህ ጸጥታና ደንብ ማስከበር ሃላፊ ኮማንደር ቡራ ካሎ የኦፕሬሽኑ አዛዥ ሲሆኑ ትእዛዝ የሚሰጡት ዲመካ ሁነዉ መሆኑንም ከስፍራዉ ከነበሩ መረዳት ተችሏል፡፡ በአርብቶአደሩ በኩል ስለደረሰው ጉዳት መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፡፡
ከዞኑ መስተዳድር የውስጥ ምንጮች በደረሰን መረጃ መሰረት በነገው ዕለት የዞኑ ሲቪል ሠራተኞች ከስከሬን አንሺ የቀን ሠራተኞች ይዘው ወደ ቦታው በመሄድ አሰከሬኖችን ለማምጣት እንደሚንቀሳቀሱና በዚህ ጉዞም ወታደራዊ ኃይል እንዳይኖር/እንዳያጅባቸው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በሃመር ወረዳ ዋና ከተማ ዲመካ ምንም የፖሊስ ኃይል ለመኖሩና አንዳንድ የወረዳውና ከዞኑ የተንቀሳቀሱ ፖሊሶች የፖሊስ ልብሳቸውን በመቀየር/ከአካባቢው ሲቪል ሠራተኞች በመውሰድ/ በእግር ጫካ ለጫካ በመጓዝ ከዞኑ ከተማ ጂንካ መድረሳቸውንና የከተማው ነዋሪም ‹‹እንኳን ለቤታችሁ አበቃችሁ›› እያለ እየጠየቃቸው እንደሆነና እነርሱም ‹‹ በማናውቀው አስገብተውን ሊያስቸርሱን ነበር፣ የተፈጠረው ሁኔታና በወንድሞቻችን ላይ የደረሰው በእጅጉ አሳዛኝ ነው›› በሚል ቁጭታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችና ከቦታው ተመላሾች ኢሣት መረጃውን ለኢትዮጵያዊያን በማድረሱ ባለውለታችን ነው በማለት ሲያመሰግኑ ተደምጠዋል፡፡
የግጭቱ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም የሚከተሉት በስፋት በአርብቶ-አደሩ የሚነሱ ናቸዉ፤
ወቅታዊው/ኢሚዲየት/ መነሻው የወረዳው ፖሊስ በለመደው መንገድ የአካባቢውን ባህላዊ አባቶች በ‹‹ንቀት›› አልፎ የሀመር ወጣቶች ላይ ኃይሉን ለማሳየት ያደረገው ሙከራ ቢሆንም–
1/ በአካባቢዉ ስም ከመነገዱ ውጪ ያየነዉ ለዉጥ ባለመኖሩ ሐመር ከ23 አመት በፊት በነበርንበት መገኘታችን፤
2/ እኛን ባላማከሩበት የግጦሽና ውኃ ማጠጫ ቦታችንን ከፓርኩ ክልል አስገብተው ባለበት አርብቶ አደርነታችን እየታወቀ ለከብቶቻችን ዘመናዊ የግጦሽ ስፍራ ሳይዘጋጅልን በበጋ ወደ ፓርክ ለግጦሽና ለዉሃ እንዳናስገባ መደረጉ ሀብቶቻችንን እንድናጣ መገደዳችን፤
3/ የወረዳዉ ፖሊስ አዛዥ መቶ አለቃ ጋዲ በርቂ በመኪና ገጭተዉ በገደሉት ሀመር በህግ አለመጠየቃቸዉ፤በተመሳሳይ ወ/ር ዋዶ የተባሉ ሀመሩን ደረቱ ላይ ረግጠዉ ሲገሉ በህግ አለመጠየቃቸዉ፣በተቃራኒው ደግሞ በቂ ዕውቀትና መረጃ የሌለዉ የሀመር እረኛ ጎሽ ገደለ ተብሎ ወህኒ መወርወሩ፤ የኛ ሰውነት ከእንሰሳ/ጎሽ ያነሰ ተደርጎ በራሳችን ልጆች ጭምር መታየቱ፤…. የሚሉት በህዝቡ ውስጥ ይብላሉ የነበሩና በተደጋጋሚ ተነስተው ምላሽ የተነፈጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በተፈጠረው ሁኔታ በወረዳው ብቻም ሳይሆን በዞኑ ውጥረትና ያለመረጋጋት ነግሷል፣የተፈጠረው ችግር መቼና እንዴት መፍትሄ እንደሚያገኝ አይታወቅም፣የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት አገልግሎት አቋርጠዋል፡፡ አስቸኳይ አሳታፊ መፍትሄ ካለገኘም የመስፋትና መዛመት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅታችን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ባለፉት 23 ዓመታት በዞኑ ያለውን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንና ምስቅልቅል በአጠቃላይ፣ በተለይም በየጊዜው በዞኑ ነዋሪዎች የሚነሱ ጥያቄዎችንና እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ የአርብቶአደሩን ጥያቄዎችና በዞኑ ያለጥናት የሚደረጉ ሰፈራዎችን እንዲሁም ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሚደረጉ የህዝብ ማፈናቀሎችንና ይህንኑ ተከትሎ የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግሥት በአግባቡና የአካባቢውን ባህላዊና አካባቢያዊ ግጭት አፈታት ዘዴዎችን ባገናዘበ መንገድ መልስና መፍትሄ እንዲሰጠቸው፣በመሣሪያ ኃይል ጥያቄዎችን ለማፈን የሚደረገው ሙከራ ዘላቂ መፍትሄ ካለማስገኘቱም ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል በተደጋጋሚ ለዞኑ መንግሥት ባለሥልጣናት ስንገልጽ ለችግሮቹ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ጥያቄዎቹን በማንሳታችን ሊያስፈራሩና ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ተመልክተናል፡፡ የዚህ አካሄድና አስተሳሰብ የመጨረሻ ውጤቱ ይህ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ድርጅታችን መንግሥት–
1. በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት መጠንና ዓይነት/ የሰው ህይወት፣አካል ጉዳት…/፣የንብረት ውድመት፣…. ላይ በቂ መረጃ እንዲሠጥና የድርጊቱ አዛዞች፣ፈጻሚዎች….ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
2. በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖችና ለደረሰው የንብረት ውድመት ካሳ እንዲከፍል፤
3. ግጭቱ ከመጪው ምርጫ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ስለሆነ አፋጣኝ አሳታፊ መፍትሄው እንዲፈልግለት፤የፖሊስ ተግባራትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወደቦታቸው/ተግባራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ፣
4. ለችግሩ ሥረ-መንስኤዎች ሕብረተሰቡን ያሳተፈና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያለው አካባቢያዊ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅና ችግሩ እንዳይባባስና እንዳይስፋፋ አስቸኳይ የማረጋጋት እርምጃ እንዲወስድ፤
የማንአለብኝነት ኃይል እርምጃ መቼውንም መፍትሄ አይሆንምና ለቀጣይም መንግሥት ከዚህ ዓይነቱ አካሄድ እንዲታቀብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/
Leave a Reply