• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የረዳት አብራሪ ሐይለመድህን አበራ ጉዳይና የአንድ አመት ጉዞው ባጭሩ

March 4, 2015 07:07 am by Editor 1 Comment

እለተ ሰኞ  ፌብሯሪ 17  ቀን 2014  ዓ/ም ማለዳ

አንድ  ንብረቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነና በበረራ ቁጥር ET 702 የተመዘገበ ቦይንግ 767  የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላን በጣሊያን በኩል አድርጎ ወደ ስዊዘርላንድ የአየር ክልል ይገባል። የስዊዝ የአየር ክልል ጠባቂዎችም በጧት የመጣባቸውን  ጥቁር እንግዳ ማንህ ወዴት ነህ ማለት። የአውሮፕላኑን የበረራ ሂደት ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት የተቆጣጠረው ረዳት አብራሪ ሃይለመድህን አበራም ቆፍጠን ብሎ አኔ ነኝ ! ማለት። አንተ ማን? ምነው ምን ፈልገህ ነው ወደ አየር ክልላችን የገባኸው?  የአየር ክልል ተቆጣጣሪዎቹ ቀጣይ ጥያቄ ነበር ። የበርካታ ወገኖቹን የብሶትና የግፍ መልዕክት ይዞ በስዊዝ  አየር ላይ የሚያንዣብበው ሃይለመድህንም  “ለጊዜው  የምፈልገው  የስዊዝ  መንግስት የፖለቲካ  ጥገኝነት እንዲሰጠኝ ፣ ለኢትዮጵያ መንግስትም  ተላልፌ እንዳልሰጥና  አውሮፕላኑን ጄኔቫ  ላይ በሰላም  ማሳረፍ ነው” የምትል ቅልብጭ ያለች ቃል ነበረች። በሁለቱም በኩል የተለያዩ መረጃዎችን ከተለዋወጡ በዃላ አውሮፕኑን ማሳረፍ እንደሚችል የተፈቀደለት ሃይሌም በተካነው ልዩ የማብረር ችሎታ ካለምንም ኮሽታ አውሮፕላኑን ጄኔቫ ክዋንትራን አየር ማረፊያ  202 መንገደኞችንና የበረራ ሠራተኞችን እንደያዘ በሰላም አሳርፎ ፤ እሱም “ያልጠረጠረ”  የምትለዋን ብሂል ቋጥሮ  ይዟት ነበርና  በመስኮት  በኩል  በገመድ  በመውረድ ለስዊዝ የደህንነትና ፖሊስ አባላት እጁን በሰላም በመስጠትና ቃሉንም  ለማስመዝገብ ወደሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት  አመራ።

ሃይለ መድህን የአውሮፕላኑን የበረራ ሃላፊነት በብቸኝነት ከተቆጣጠረ ጀምሮ ከስዊዝ ፖሊሶች ጋር በአካል አስገተገናኘበት ጊዜ ደረስ ያደረጋቸውን በሙሉ በአፅንኦት የተከታተሉ አንድ አሜሪካዊ የቀድሞ ፓይለትና አሁን ደግሞ የግል የበረራ ተቋም ባለቤትን እንዳስደመማቸው እንደገለፁለት ወዳጄ ጋዜጠኛ አበበ ገላው አጫውቶኛል።

ከዚያስ ፧ ከዚያ በኳላማ የአለም ታላላቅና ታናናሽ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዋና ዜና ሃይለመድህንና የተጠለፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሆነ። የቴሌቪዥን መስኮቶች በሃይለመድን ምስሎች ተሞሉ ፣ ሬድዮኖች ደጋግመው ደጋግመው ስሙን ያነሳሉ፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች እነ ፌስቡክና ትዊተር ስለ ሃይለመድህን በሚያወሱ ወሬዎች ኮሜንት ፣ ላይክ ፣ ሼር እና  ሪትዊት ስራ በዝቶባቸው ነበር።

በአራቱም መአዘን የሚገኙ የጦቢያ ልጆች ቀፏቸው እንደተነካባቸው ንቦች ተነሱ። ሃይለመድህን ነፃ ይሁን የሚሉ ድምፆች ማስተጋባት ጀመሩ። ” ነፃ ሃይለመድህን ” የሚል አለም አቀፍ አስተባባሪ ግብረ ሃይል ተቋቋመ ፣ ሰላማዊ ሰልፎች በመላው አለም  በከፍተኛ ድምቀት ተካሄዱ ፣ በሃይለመድን ስም  ድረ ገፅና የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ተከፈቱ ፣ “ሀይለመድህን ብሔራዊ ጀግናችን ነው” የወቅቱ መሪ መፈክርም ሆነ።

አዎ!  ሕወሓት በሚከተለው ዘረኝነትንና ጠባብነትን መርህ ባደረገው የፖለቲካ አመራሩ ምክንያት ሠርቶ መብላት ላልቻለው ፣ በስደት ምክንያት በበረሃ አውሬና በባህር አሣ ለሚበላው ፣ ከሐገር ቤት አልፎ የሌሎች ሐገራትን ወህኒ ቤቶችን ለሚያጨናንቀው፣ የእምነት ተቋሙ ተደፍሮ ሲኖዶስና መጅሊስ ለሚመረጥለት፣ የእምነት አባቶችም በአባይ ፀሐዬ በኩል ለሚሾምለት፣ በሃገር ቤት ለመኖር ለመረጠም በገዛ ሀገሩ የሁለተኛና ሦስተኛ ዜግነትን ተቀብሎ እንዲኖር ለሚገደደውና ከፈጣሪ የተሰጠውና በአለም አቀፍ ተቋማት የተደነገገውን  ኢትዮጵያም የተቀበለቻቸውንና የፈረመችባቸውን  ሰብአዊ መብቶቹን ለተገፈፈው ኢትዮጵያዊ እንደ ሀይለመድህን አይነት ብሶቱን በአለም አደባባይ የሚያሳይለትና የሚያጋልጥለት ሲያገኝ እንዴት ብሔራዊ ጀግናው አያደርገው!

እንደ መንግታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ዋና መስሪያ ቤት  (UNHCR) መረጃ በፈረንጆቹ 2013 ዓ/ም አጋማሽ ድረስ ብቻ ከአርባ ሁለት ሺህ (42,000) በላይ ኢትዮጵያውያን ስደት ጠይቀዋል ።

በውጭ መንግተስታት ዘንድ በተለይም እርዳታ በሚለግሱት ምእራባውያን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት አክባሪ መስሎ ለመታየት የሚዳዳው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት የደረሰበትን ፖለቲካዊ ኪሳራ ሂሳብ ለማወራረድ  “ሀይለ መድህን የአእምሮ በሽተኛ ነው” የሚል ዘመቻ ቢጀምርም ወንዝ ሊያሸጋግረው አልቻለም።

በመቀጠል ህወሓት የወሰደው ርምጃ የመንግሥት ባለስልጣናትን ወደ ስዊዝ በመላክ የስዊዝ ባለሥልጣናትን አግባብቶና አሳምኖ ሀይለመድህንን ወደ ኢትዮጵያ ለመውሰድ መሞከር ነበር (የየመን መንግሥት በነፃነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ያደረገውን እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ነው) የስዊዝ ባለሥልጣናት ግን በፍፁም አይሞከርም የሚለው ቃል መልሳቸው ነበር።

ከዚህም በኋላ ሕወሓት የስዊዝ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለማስፈራራት ይመስላል አንድ ከፍተኛ የህወሓት አባልና የመንግሥት ባለሥልጣን በድጋሜ ወደ ስዊዝ ላከ። የተላኩትም ሰሞኑን ከአንዲት የ14 አመት በአውስትራሊያ ነዋሪ ከሆነች ትውልደ ኢትዮጵያዊት “በሽልማት ያገኘችውን ” 20 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ተረከብኩ ያሉት የፌስቡክና ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ  ቴድሮስ አድሐኖም ነበሩ   ፌብሩዋሪ 28 ቀን 2014 ዓ/ም። ስዊዞቹም እንኳን አንተና ባለራእዩ መሪያችሁ አፈሩን አራግፎ ቢመጣም ወይ ፍንክች አሏቸው መሰለኝ የፌስቡክ ሚንስትሩ ወደመጡበት ለመመለስ ሻንጣቸውን ከሸከፉ፣ ጠባቂዎቻቸውና አጃቢዎቻቸውን በቦታቸው መኖራቸውን ካረጋገጡ በኋላ ለመውጣት ሲዘጋጁ ከፕሮቶኮላቸው አንዱ ጠጋ ብሎ አንድ ነገር ሹክ አላቸው ። ቴድሮስ አድሐኖም የስዊዝ ባለሥልጣናትን ከሚያነጋግሩባት የስዊዝ የመንግሥት መቀመጫ በሆነችው በርን ከተማ ላይ ከሚገኘው መሥሪያ ቤት በቅርብ ርቀት ለጀግናው ሀይለመድህን ፍትህና ነፃነትን  የሚጠይቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፈኞች ስላሉ ፣ ከመሥሪያ ቤቱ ሲወጡ እንዳያገኟቸው ጥንቃቄ እንዲደረግ ነበር የፕሮቶኮሉ መልእክት።

ሰኔና ሰኞ የተገጣጠሙባቸው የማርክ ዙከርበርግ ቋሚ ደንበኛ (valued customer)  ቴዲ በከፍተኛ አጀባና ጥንቃቄ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በሌሉበት አቅጣጫ አፈተለኩ። መቼም የፌስቡክ ደንበኛ ሆኖ መስራቹንና ባለቤቱን አሜሪካዊውን ማርክ ዙከርበርግን የማያውቅ የለም። ይኸው ለነ ቴድሮስ አድሐኖም ምስጋና ይግባና በያዝነው ሳምንት ፎርብስ መጽሔት ይፋ ባደረገው የአለማችን ሀብታሞች ደረጃ መሠረት ዙከርበርግ በዚህ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሃያዎቹ ቱጃሮች ውስጥ በመግባት የአለማችን 16ኛው ሃብታም ለመሆን ሲችል የሀብቱም መጠን 33.4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ። ድሮስ የተሰጣቸውን ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ገፋ በማድረግ አብላጫ  ጊዜያቸውን ፌስቡክ ላይ ፎቶ ሲለጥፉ የሚውሉና የሚያድሩ እንደ ቴድሮስ አይነት ደንበኞችን ይዞ  እንዴት ገቢው አያድግ!

የስዊዘርላንድ መንግሥት ተወካዮች ከህወሓት ባለሥልጣናት ጋር ስላደረጉት ተደጋጋሚ ውይይት ፣ ከኢትዮጵያውያንና ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እንዲሁም ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለሚደርሷቸው ጥያቄዎች ጠቅለል ያለ መልሰ ለመስጠት ያስችላቸው ዘንድ ሜይ 9 ቀን 2014  ዓ/ ም ለመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ። በመግለጫቸውም:  የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ረዳት አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ተላልፎ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ፣ ወደፊትም ተላልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ እንደማይኖር ፣ የፍርድ ሒደቱን በስዊዝ ፍርድ ቤቶች ችሎት እንደሚታይ፣ የስዊዝ መንግስትም የህግ ከለላ እንደሚያደርግለት፣ ያቀረበውም የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ከፍርድ ሂደቱ መጠናቀቅ በኋላ እንደሚታይና አዎንታዊ መልስም እንደሚኖረው ( በስዊዝ ረዘም ላለ ጊዜ ለመኖር የሚያስችለውን ፈቃድ እንደሚያገኝ)  አስረግጠው ተናገሩ ።  በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የሀይለመድህን ጠበቆች ቡድን መሪ ዶ/ር ፊሊፕ ኩራ ( እሳቸው እንኳን ይችን ዶክተር መባል አይፈልጓትም የተገዛች ስላልሆነች ነው የተጠቀምኩባት) የስዊዝ መንግሥት ያሳለፈው ውሣኔ ተገቢ የሆነና ትክክለኛ መሆኑን ገልፀው አንድ ተከሳሽ በተመሳሳይ ክሶች በሁለት የተለያዩ ሃገሮች ችሎት ፊት ይቅረብ የሚል አለም አቀፍ ሕግም እንደሌለ ተናግረዋል።

በድፕሎማሲው መንገድ እንዳልተሳካላቸው የተረዱት እነ ጭር ሲል አልወድም አዲስ ነገር ይዘን ብቅ ብለናል አሉ። ይሄኛውስ ምንድነው?  ይሄኛውማ  ሀይለመድህን ባይኖርም በሌለበት ( in absentia) ሞት፣ የእድሜ ልክ እስርና ሌሎችንም ጠንካራ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አለም አቀፍ ዝናን ባተረፈው ፍርድ ቤታችንና የፍትሕ ስርአታችን አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበት እንዲያስፈርድበት እናደርጋለን የሚል ነበረ።

hailemedinፍትሕ ሚኒስቴር በረዳት አብራሪ ኃይለመድን አበራ ላይ  በከፍተኛው ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ሁለት ሲሆን፤ የመጀመሪያው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 507/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፡-

‹‹…በዋና አብራሪ ፓትዮዝ ባርቤሪ አማካኝነት ከአዲስ አበባ በሱዳን በኩል ወደ ጣሊያን ሀገር ሮም ከተማ መንገደኞችን ለማድረስ በማጓጓዝ ላይ እንዳለ ዋናው አብራሪው የበረራ መቆጣጠሪያውን ክፍል ከውስጥ በመቆለፍ፣ ያለፍቃድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ አውሮፕላኑን በቁጥጥር ሥር በማድረግ የአውሮፕላኑ የበረራ ቡድን አባላት በሩን እንዲከፍት ሲጠይቁት አርፋችሁ የማትቀመጡ ከሆነ በአውሮፕላኑ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ በማስፈራራት፤ እንዲሁም የአውሮፕላኑን የመዳረሻ አቅጣጫ ያለአግባብ በማስቀየር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈቃድ ውጭ ወደ ስዊዘርላንድ አየር ክልል ውስጥ በመግባት ተሳፋሪዎች እና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት እና ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎ በመጨረሻ በጄነቭ ከተማ ውስጥ ያለመዳረሻው እንዲያርፍ በማድረጉ እና ተሳፋሪዎችን ለአደጋ በማጋለጡ በፈፀመው በሕገ-ወጥ መንገድ በጉዞ ላይ ያለን አውሮፕላን መያዝ ወይም ማገት›› የተከሰሰ መሆኑን ያትታል፡፡

በሁለተኛነት ክስ ደግሞ በዚሁ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 508/1/ ላይ ያለውን መተላለፍ የሚል ሲሆን፤ ክሱም በአጭሩ እንዲህ ይላል፡-

‹‹…ያለፍቃድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ አውሮፕላኑን በቁጥጥር ሥር በማድረግ የአውሮፕላኑ የበረራ ቡድን አባላት በሩን እንዲከፍተው ሲጠይቁት አርፋችሁ የማትቀመጡ ከሆነ በአውሮፕላኑ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በማለት በማስፈራራት አውሮፕላኑን በድንገት እና በፍጥነት ሁለት ጊዜ ከፍ እና ዝቅ (dive) በማድረግ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያሉትን የመንገደኞች ምግብ ማቅረቢያ ቁሳቁሶች እንዲገለባበጡ በማድረግ፣ የአውሮፕላኑን የመዳረሻ አቅጣጫ ያለአግባብ በማስቀየር፣ ከአትዮጵያ አየር መንገድ ፈቃድና እውቅና ውጭ ስዊዘርላንድ አየር ክልል ውስጥ በመግባት ስዊዘርላንድ ከተማ ጀኔቭ በመግባት አየር ላይ በማንዣበብ ከቆየ በኋላ እንዲያርፍ በማድረግ በፈፀመው በሕገ-ወጥ መንገድ በጉዞ ላይ ያለን አውሮፕላን አስጊ ሁኔታ ላይ መጣል ወንጀል ተከሷል፡፡›› ይላል።

በፌ/አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ ፊርማ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ማመልከቻ ከስ ቻርጁን ጨምሮ አስራ አንድ ገፅ ሲሆን፤ የዋና አብራሪው፣ የአምስት የበረራ አስተናጋጆች እና የአራት ሰዎች ስም ዝርዝር በመስክርነት ተገልፆአል፡፡ በሰነድ ማስረጃነት ደግሞ አየር መንገዱ በ27/06/2006 ዓ.ም ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የጻፈው አራት ገጽ እና ሲቪል አቬየሽን በ21/06/2006 ኃይለመድንን በተመለከተ የጻፈው ማብራሪያ ከነአባሪው ሁለት ገጽ ቀርቧል፡፡

የኃይለመድን አበራን የጤንነት ሁኔታ በተመለከተ አየር መንገዱ ለፌደራል ፖሊስ በላከው ደብዳቤ በስድስት ወር ውስጥ አምስት ጊዜ ያህል ለቀላል ሆድ ቁርጠት፣ ራስ-ምታት፣ ጉንፋንና ተቀማጥ ወደ ድርጅቱ ክሊኒክ ከመሄዱ ያለፈ ምን ችግር የሌለበት ጠኔኛ እንደሆነ ገልፆአል፡፡ ሲቪል አቬሽንም በተመሳሳይ መልኩ በላከው ደብዳቤ አብራሪው አመታዊ የጤና ምርምራ አድርጎ እ.ኤ.አ. እስከ 22/02/2014 ዓ.ም ድረስ ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን አድሶ እንደሰጠው አስታውቋል፡፡

(እዚህ ላይ በመጀመሪያ መንግሥት ኃይለመድህን የአእምሮ በሽተኛ ነው ብሎ እንደነበር ልብ ይሏል)

አየር መንገዱ ከዚሁ ጋር አያይዞ ሁለት መቶ ሀምሳ ሶስት ሺህ፣ ሶስት መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአራባ ሁለት ሳንቲም (253,336.42) ዩሮ ኪሳራ እንደደረሰበት እና በቀጣይም ተጨማሪ ክፍያዎች እንደሚኖሩበት አሳውቋል፡፡

ህወሓት/ ኢሕአዴግ ራሱ ከሣሽ ራሱ ፈራጅ ሆኖ በሚተውንበት የፍርድ ቴአትር ቤት መታየት የጀመረው ድራማ የተጠበቀውን ተመልካች ማግኘት ካለመቻሉም በላይ የክሱም ስክሪፕት በጥሩ ፀሀፈ ተውኔት ስላልተፃፈ ቴአትሩን ለማየት ለታደሙትም ታማኝና ጥቂት የስርአቱ ልማታዊ ደጋፊዎችና ጋዜጠኞች የእንቅልፍ መድኃኒት ሆነባቸው ፣ አለም አቀፍም፣ ሐገር አቀፍም፣ ልማት አቀፍም ትኩረት አጣ።

አዲሱ ትኩረት መሳቢያ ቴአትር

ባሳለፍነው ሳምንት አውሮፕላን የተጠለፈበትን አንደኛ አመት ለማሰብም ይመስላል ሕወሓት አዲስ ዘዴ አግኝቻለሁ ይላል።

አዲሱ ዘዴ የተባለው ምንድነው ቢሉ፣ ኢንተርፖል በሚባል የአለም አቀፍ ፖሊስ ተቋም  በኩል “ሀይለመድህን አበራ የሚባል ረዳት  አውሮፕላን አብራሪዬ ጠፍቶብኛልና እባካችሁ ያያችሁ” የሚል የተማፅኖ ጥሪ ማሰማት ነው። በዚያውም የኢንተርፖል አባል መሆኔን እወቁልኝ ነው።  “የኢንተርፖል አባል መሆን ብርቅ ነው እንዴ?  ” አለ አሉ ይህን የሰማው ኮንስታብል ዶክሌ። ወደው አይስቁ !

ለማንኛውም “ረዳት አብራሪዬን ያያችሁ” ለሚለው በኢንተርፖል በኩል ለተሰራጨው ቀይ ማዘዣ( Interpol red notice) የመጀመሪያውን መልስ የሰጠችው ስዊዝ ነች ” አዎ እኔ አይቻለሁ እንቁልልጬ አይነት መልስ ።

ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 27 ቀን 2007 ዓ/ም በፈረንሳይኛ ቋንቋ ለሚታተመው “ለ ማታ”  (Le Matin) ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የሀይለመድህንን ጉዳይ የሚያየው የኮንፌዴሬሽኑ አቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ ጃኔት ባልመር “ለኢንተርፖል ተላልፎ ይሰጣል ወይ?  ለሚለው ጥያቄ በፍፁም አይሆንም አይሞከርም ነው መልሴ ብለዋል ።

ጃኔት ባልመር ይቀጥላሉ ” የ31 አመቱ ሀይለ መድህን በአሁን ጊዜ ስዊዝ ውስጥ በሕግ ጥላ ስር ይገኛል። በፍርድ ቤትም ጉዳዩ እየታየ ነው። በኢትዮጵያም ከአለም አቀፍ የሕግ ሂደት ባፈነገጠ ሁኔታና በስዊዝ ችሎት መቅረቡ እየታወቀ ክስ እንደተመሠረተበት ፣ እኛም አሳልፈን እንደማንሰጠው አሳውቀናል ። ኢንተርፖልም የቀይ መያዣ( ማሳሰቢያ) ጥሪውን ያስተላለፈው በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ መሆኑን አሳውቋል” ይላሉ።

የሀይለመድህን ጠበቃ ፊሊፕ ኩራም ለዚሁ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ” የኢትዮጵያ መንግሥት ሀይለመድህንን በይፋ ” ከሐዲ ” ብሎ ፈርጆታል ። በመሠረታዊውን የፍትህ ስርአት  (fundamental rule of law)  “አንድ ሰው በተመሳሳይ ክስ በሁለት የተለያዩ ችሎቶች መቆም የለበትም” የሚለውን በመፃረር ከኛም እውቅና ውጪ  በሌለበት ለመክሰስ ወስኗል ። በምን አይነት መልኩ ነፃ በሆነ የፍርድ ሂደት ጉዳዩ እየታየ እንደሆነም እኔ በበኩሌ የማውቀው ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ ውጤት አልባ የማሰናከያ ቀመሮችን  እየፈጠረ ነው ” ይላሉ።

የአቃቤ ሕጉ ቃል አቀባይ ጃኔት ባርመር “ለኢትዮጵያ መንግስት የአፀፋ መልስ የለንም። ለመንግስታችን የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ያቀረበው  የሀይለመድህን አበራ  የፍርድ እጣ እዚሁ በጥሩ ሁኔታ ይወሰናል ። በርግጥ የፍርድ ሂደቱ ብዙም አልገፋም። ክፍት ችሎቶች የሉም። ምርመራዎች እንደቀጠሉ ናቸው ። ጉዳዩ ገና በምርመራ ላይ ያለ ስለሆነ ከዚህ በላይ ብዙ መናገር አልችልም” ብለዋል ።

ጠበቃ ፊሊፕ ኩራም “ሀይለ መድህን  በጣም ደህና ነው ። ስለ ፍርድ ሂደቱም  መናገር የምችለው:  እንዲህ መጓተቱ የተለመደ ባይሆንም ከንብረት ጋር የተያያዙ የተለያዩ መረጃዎችን ከተለያዩ ሐገሮች ለማግኘት ስንሞክርና መልስ ለማግኘት ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ ነው። ልዩ ወደሆኑት  ቴክኒካዊ መረጃዎች  ስንመጣ ይህም ራሱን የቻለ የቴክኒክና የሳይንስ ምርመራ ይጠይቃል። በመጨረሻም የኮንፌዴሬሽኑ የህዝብ አቃቤ ሕግ  በመርህ ደረጃ 202 መንገደኞችን በሙሉ የሚያነጋግር ሲሆን አሁንም ከተሳፋሪዎቹ ስለራሳቸው  መረጃዎችን እየጠበቀ ይገኛል ። ” ብለዋል

የረዳት አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ጉዳይ ከፌብሩዋሪ 17 ቀን 2014 ዓ/ም  እስከ ፌብሩዋሪ 28 ቀን 2015 ዓ/ም ድረስ የነበረውን የአንድ አመት ጉዞ ባጭሩ ይሄን ይመስላል።

ሀይለመድህን አበራ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ኦገስት 30 ቀን 1983 ዓ /ም  በጣና ሃይቅ ዳርቻ በምትገኘው ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 03 ተወልዶ ያደገ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በመጋቢት 28 ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ባህርዳር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል።

ከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርክቴክቸር  ትምህርት ክፍል በመከታተል ላይ እያለና ለማጠናቀቅም አንድ ሴሚስተር ብቻ ሲቀረው በማቋረጥ ከልጅነት ጀምሮ ይመኘው የነበረውን የበረራ ትምህርት ለመከታተል የኢትዮጵያ አየር መንገድን የበረራ ት/ቤት ተቀላቅሏል። ፌብሩዋሪ 17 ቀን 2014 ዓ/ም አውሮፕላኑን ጠልፎ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ እስካሳረፈበት ጊዜ ድረስ በአየር መንገዱ በረዳት አብራሪነት አገልግሏል። ከከጠለፋውም በኋላ የአየር መንገዱ የበረራ ክፍል ሃላፊ የነበሩት ካፒቴን ደስታ ዘሩ ከሥራቸው መልቀቃቸው ይታወቃል።

በመጨረሻም በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር ሐይል አባላት የሆኑ መኮንኖችና የበረራ ቴክኒሺያኖች በተለያዩ አቅጣጫዎች ሥርአቱን እየከዱ በመጥፋት ላይ መሆናቸውን እያየን ነው። በተለይም ወደ ጎረቤት ሐገር የኮበለሉት አንድ ተዋጊ ሄሊኮፕተር ይዘው መሆኑንም ራሱ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎቹ  አረጋግጦልናል።

ከ25 እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን ሄሊኮፕተር እና ለስልጠና ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸውን የበረራ ባለሙያዎችን ያጣውና በማጣት ላይ ያለው ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይና አመራሮቹ ረዳት አብራሪ ሀይለ መድህን አበራ ብቻ ገበናቸውን የገለጠባቸው  ለማስመሰል ወደ ምእራባውያን ሐገሮች ባለሥልጣናቱን መላክና ኢንተርፖልን ደጅ መጥናት ውሀ አያነሳላቸውም።

ምነው ዶ/ር ቴድሮስ በነካ እጅዎ ወዳደጉባትና ወደተማሩባት ኣስመራ ጎራ ብለው የሄሊኮፕተሯንና የበረራ ባለሙያዎቿን ጉዳይንም ቢመክሩባትስ?

ከስዊዝስ  ኣስመራ አትቀርብዎትም?

……………………………………………………

www.freeabera.com
Facebook: Free Hailemedhin Abera
Email: ashenafikb@yahoo.com
ተፃፈ የካቲት 23  ቀን 2007 ዓ /ም

በሀገረ ስዊዘርላንድ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Comments

  1. dij mj says

    March 5, 2015 11:22 pm at 11:22 pm

    በተመቸዉ ሀይለመድህን !!እንኩን ደሰ አልክ

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule