ወቅቱ 1973 ዓ.ም ነበር፡፡ አገሪቱ ከተለያዩ የውስጥና የውጪ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ልጆቻቸውን ያለ አሳዳጊ ጥለው በየጦር ሜዳው ወድቀዋል፡፡ አሳዳጊና ተንከባካቢ ያጡት ህፃናት በየጎዳናው መውደቃቸው ያሳሰበው የደርግ መንግስት፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት መንግስቱ ኃይለማርያም ልዩ ትዕዛዝ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህፃናት አምባ ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ ሃገር ሀይቆችና ቡታጅራ አውራጃ፣ በአላባ ቁሊቶ ወረዳ፣ አላጌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወላጆቻቸውን በጦርነትና በሌሎችም ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ያጡ ህፃናትን ተቀብሎ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት፣ በትምህርትና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ የማሳደግን ዓላማ አንግቦ የተቋቋመው አምባው፤ “ሰብለ አብዮት”፣ “መስከረም ሁለት ኦጋዴን”፣ “ዘርዓይ ደረስ” እና “መንግስቱ ኃ/ማርያም” በተባሉ 5 መንደሮች የተከፋፈለ ነበር፡፡
አምባው ገና ከተወለዱ ህፃናት ጀምሮ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ተቀብሎ እያሳደገ ያስተምርና ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ (የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ) ከማሳደጊያው ይሰናበታሉ፡፡ ህፃናቱ አምባውን ለቀው በሚወጡ ጊዜ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑና በማህበራዊ ህይወታቸውም የመገለል ስሜት እንዳያድርባቸው ልዩ የምክር አገልግሎት ይሰጣቸው እንደነበር የቀድሞው የአምባው ልጆች ያስታውሳሉ፡፡ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች አንድም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገባሉ አሊያም ወደ ውጪ አገር (በአብዛኛው ኩባና ራሺያ) እየሄዱ ይማሩ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም የአምባው መስራችና ህፃናቱ ሁሉ ”አባታችን“ እያሉ የሚጠሯቸው የአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም አገር ጥለው መውጣት ለአምባው ህፃናትና ሰራተኞች ትልቅ ዱብ እዳ ነበር፡፡
የአምባው ህፃናት መሳጭና መልእክት አዘል በሆኑት ህብረ ዝማሬዎቻቸው በእጅጉ ይታወቁ ነበር፡፡ በታዋቂዋ ገጣሚ አለምፀሐይ ወዳጆ ክትትልና የጥበብ ስልጠና ይደረግላቸው የነበሩት የአምባው ልጆች፤ “የጀግና ፍሬ” በተሰኘ የኪነት ቡድን ታቅፈው በየጊዜው ለታዳሚዎች የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ቡድን ተዘጋጅተው ለአድማጭ ጆሮ ከበቁትና ተወዳጅነትን ካገኙት ስራዎቻቸው መካከል “ፀሐዬ”፣ “የጀግና ልጅ ጀግና” እና “እርግቢቱ ሂጂ” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በ1970ዎቹ መገባደጂያና በሰማንያዎቹ መጀመሪያ ላይ አብዛኛው ታዳጊ እኒህን መዝሙሮች ከህዝብ መዝሙር ባልተናነሰ ያውቃቸው ነበር፡፡ በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም መዝሙሮቹን በተደጋጋሚ መስማት አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ የደርግን ውድቀት ተከትሎ ግን መዝሙሮቹ ታሪክ ሆነው ተረሱ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላም በቅርቡ እኒህ ሥራዎች በከፊል የተካተቱበት ሲዲ ታትሞ መውጣቱ ተሰምቷል፡፡
እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም የሙዚቃ ሥራው አስተባባሪ የሆኑትንና የአምባው ልጆች የነበሩትን መቅደስ ተመስገን እና ጆኒ መርጊያ ስለ ህፃናት አምባው፣ ስለ አስተዳደጋቸው፣ በተለይ ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከአገር መውጣታቸውን ሲሰሙ ስለተፈጠረባቸው ስሜት እንዲሁም ስለ መዝሙሮቻቸው እንዲያወጉኝ ጠየቅኋቸው፡፡ በደስታ ፈቃደኝነታቸውን ገለፁልኝ።
የአምባ ህይወት ጅማሮ (ጆኒ መርጊያ)
“በወላጅ አባቴ የአዕምሮ ህመም ምክንያት ቤተሰባችን ሲበተን እኔ ገና ህፃን ልጅ ነበርኩ። እናታችን ሁኔታውን መቋቋም ተስኗት ጥላን ጠፋች፤ ስለዚህም አንድ ወንድሜና እህቴን ጨምሮ ሶስታችንም ጎዳና ወጣን፡፡ ወቅቱ ለእኛ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የሚላስ የሚቀመስ አጥተን በረሃብ ከመሞታችን በፊት ግን ከጎዳና ላይ ተለቅመን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ የህፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ እንድንገባ ተደረግን፡፡ በ1973 ዓ.ም መንግስት አባቶቻቸውን በጦርነት ያጡትን ህፃናት ሰብስቦ ለማሳደግና ለማስተማር በማሰብ የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ እንዲቋቋም አደረገ፡፡ የህፃናት አምባው ግንባታ ተጠናቆ በዚያው ዓመት አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ከየጎዳናው እየተለቀሙ በህፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉት ህፃናት እየተሰበሰቡ ወደ አምባው እንዲገቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ በዚህ መሰረትም እኔና አንድ ወንድሜ ወደ ህፃናት አምባው ገባን፡፡”
መቅደስ ተመስገን (10 ዓመታትን በአምባው ያሳለፈች)
“ወደ አምባው የገባሁት የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር፡፡ አባቴ ወታደር ስለነበር አስመራ ውስጥ በግዳጅ ላይ ህይወቱ በማለፉ፣ከልጆቹ መካከል ህፃናት አምባ የሚገባ ልጅ ሲጠየቅ፣ እኔ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ ወደ አምባው እንድገባ ተደረገ። ወደ አምባው ስገባ የነበረውን ሁኔታ ፈፅሞ አልረሳውም፡፡ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ ከጥቂት የቤተሰብ አባላት ጋር በአንድ ትሪ ትበላ ለነበረች ህፃን፣ በትልቅ የምግብ አዳራሽ እጅግ በተዋበ ገበታ ላይ ከብዙ ህፃናት ጋር እንድትበላ ስትደረግ የሚፈጠርባትን ስሜት ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ማታ ቴሌቪዥን ልናይ ወደ አዳራሽ ስንገባ፣ በእውኔ ሳይሆን በህልሜ ነበር የመሰለኝ፡”
የአምባው ትዝታ
“አምባው፤አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ማግኘት ያለበትን ደስታና ፍቅር አግኝተን ያለፍንበትና ለህይወታችን መሰረት የሆነን ዕውቀት የቀሰምንበት ቦታ ነው፡፡ ራሳችንን በአግባቡ መግለፅ የምንችል፣ በራሳችን የምንተማመን ልጆች ሆነን እንድናድግ ያደረገን አምባው ነው፡፡ የምግብ፣ መጠጥና አልባሳት ጭንቀት ሳይኖርብን፣ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ተሟልቶልን ነው ያደግነው፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ አሳዳጊዎቻችን ተገቢውን የቤተሰብ ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጡ አሳድገውናል፡፡ ይህ ቀረብን የምንለው ነገር ፈፅሞ የለም፡፡
“ክረምት ሲመጣ ቤተሰብ ያላቸው ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው ጋ በመሄድ፣ ሁለቱን ወራት የእረፍት ጊዜ እዚያ አሳልፈው ይመጡ ነበር፡፡ ይህ የሚደረገውም ከቤተሰቦቻችንም ሆነ ከማህበረሰቡ የራቀ ህይወት እንዳይኖረንና ውጪውን እንድንላመድ ነው፡፡ ቤተሰብ የሌላቸው ልጆችም ክረምቱን በጓደኞቻቸው ቤተሰቦች ቤት እየሄዱ ያሳልፉ ነበር። ህፃናቱ የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አምባው ሲመለሱ፣ ከአምባው 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቡልቡላ ከተማ ጊዜያዊ ፅ/ቤት ተቋቁሞ፣ የህፃናቱ የጤና ሁኔታ በባለሙያዎች እየተመረመረ ወደ አምባው እንዲገቡ ይደረግ ነበር።”
የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ ህፃናቱ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እየተሟላላቸው እንደሆነ ለማየት የቅርብ ክትትልና ድንገተኛ ጉብኝትም ያደርጉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የአምባው ህፃናት ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቅሬታ አንስተው “አባታችን ይጠራልን” በማለታቸው ፕሬዚዳንቱ ወደ አምባው ሄደው ልጆቹን አነጋግረው ተመልሰዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ እነ መቅደስ እንዲህ ያስታውሱታል፡-
“ፕሬዚዳንት መንግስቱ ለእኛ የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ እኛም እንደዚሁ እኛን ለመጐብኘት ወደ አምባው ሲመጣ በውስጣችን ይፈጠር የነበረውን ልዩ ስሜት ለመግለፅ ያዳግተናል፡፡ በየጊዜው እየመጣ ያዋራንና ያበረታታን ነበር፡፡ አሳዳጊዎቻችን እንኳን “እንዲህ አደረጉ… ጠገቡ” ብለው ሲነግሩት፤ “ተዉ ልጆቻችሁ ቢሆኑ እንዲህ አትሉም ነበር” ይላቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ በአምባው ውስጥ ከምግብ ጋር የተያያዘ ቅሬታ ተነሳና ረብሻ ተፈጠረ፡፡ ከእኛ በላይ ያሉ ተማሪዎች “አባታችን ይጠራና ያነጋግረን” ብለው ጠየቁ፡፡ በእሱ ምትክ ፍስሃ ደስታ ወደ አምባው መጡ፡፡ ማንም ግን ሊያነጋግራቸው አልፈለገም፡፡ “ራሱ አባታችን ይምጣ” ብለው ድርቅ አሉ፤ ተማሪዎቹ፡፡ በኋላም መንግስቱ መጣና ሊያነጋግረን ሰበሰበን፡፡ ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ከባድ ጦርነት ላይ እንደሆነና በየቀኑ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ለመሳሪያ ግዥ እንደሚያወጣ ነገረን፡፡ እናም ታገሱን፣ ተረዱን አለን፡፡ እኛንም አሳዳጊዎቻችንንም ለየብቻ አነጋግሮና አስማምቶን ሄደ፡፡ በየጊዜው ወደ አምባችን እየመጣ ያፅናናንና ያነጋግረን ነበር፤ በኋላ በኋላ ግን መምጣቱን ተወው፡፡”
ፕሬዚዳንቱ ከአገር ሲወጡ …
ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ከአገር የመውጣታቸው ዜና ለአምባው ህፃናትና ሰራተኞች ለመሸከም የሚያዳግት ክፉ መርዶ ነበር፡፡ ህፃናቱም ሆኑ አሳዳጊዎቻቸው ቀጣይ እጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ባለማወቃቸው በእጅጉ ተደናገጡ። በተለይ የአምባው ሰራተኞችና አሳዳጊዎቻቸው የተቋሙ ሰላምና የህጻናቱ ህይወት ያሳስባቸው ነበር። አምባው የተሰራበት ቦታ የአሩሲና አላባ ተወላጅ የሆኑ ወገኖችን የሚያወዛግብ ስለነበር በተፈጠረው ክፍተት አንዱ ወገን በህፃናቱ ላይ አደጋ እንዳይጥል ስጋት ነበረባቸው፡፡
“እናም ችግሩ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን መንገድ ለመፈለግ የአምባው ስራ አስኪያጅ በአገር ሽማግሌ ልመና ይዞ ነበር፡፡ እኛም በማንኛውም ጊዜ ለሚደርሰን ትዕዛዝ ዝግጁ ሆነን በተጠንቀቅ እንድንጠባበቅ ስለተነገረን፣ ራሳችንን ለጉዞ አዘጋጅነት ነበር፡፡ በኋላ ግን የኢህአዴግ ወታደሮች ወደ አምባው በመምጣታቸው ሊፈጠር የነበረው ችግር ተወግዶ ሰላማዊ ህይወታችንን ለመቀጠል ችለናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከአገር ወጥተዋል የሚለው ዜና በሬዲዮ ሲሰማ፣ ሁላችንም ሰማይ ምድሩ ነበር የዞረብን፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላስ?
ከደርግ ውድቀት በኋላ በአምባው ለሚኖሩ ህፃናትና ታዳጊዎች የሚደረገው እንክብካቤ በእጅጉ ቀንሶ ነበር፡፡ ልጆቹ እንደቀድሞው ዓይነት እንክብካቤ እንደማይደረግላቸውና አርፈው ትምህርታቸውን መማር እንደሚገባቸው በግልፅ ተነገራቸው፡፡
“መንግስት እንደተቀየረ ይደረግልን የነበረው እንክብካቤ ተቀየረ፡፡ አዳራሽ ሰብስበውን እንደ ድሮው እንደልብ ሆኖ መኖር የለም፡፡ አርፋችሁ ተማሩ አሉን፡፡ ይህ ለእኛ ምን አይነት ስሜት እንደሚፈጥርብን መገመት አያስቸግርም፤ ሁኔታው በትምህርት ውጤታችን ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል። አምባው ደርግ የወታደሮቹን ልጆች ለማሳደግ የከፈተው ነው በሚል እንዲፈርስ ተደረገ፡፡
አምባው እንዴት ፈረሰ?
የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ በአዋጅ እንዲፈርስ የተደረገው በ1989 ዓ.ም ነበር፡፡ ልጆቹ የክረምቱን የእረፍት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸውና ከየጓደኞቻቸው ጋር ለማሳለፍ አምባውን ለቀው የወጡበት ወቅት ነው፡፡ ምንም ቤተሰብና ጠያቂ የሌላቸው በርካታ ልጆችም በአምባው ውስጥ ክረምቱን እያሳለፉ ነበር፡፡ አምባው እንደሚዘጋና ልጆቹ እዚያ ባሉበት ቦታ ሆነው ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ መልእክት በሬዲዮ ተላለፈ፡፡ ይህ መልእክት የበርካታ የአምባው ልጆችንና ሕፃናትን የወደፊት ህይወት ያጨለመ እንደነበር ልጆቹ ይናገራሉ፡፡
“የአምባ ልጆች ማለት የውጪውን ዓለም እምብዛም የማያውቁ፣ ጠያቂ ዘመድና ቤተሰብ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ ይህንን መርዶ ለእነዚህ ልጆች መንገር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የደረሰበት ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ የራሳቸው ቤተሰብ የሌላቸው፣ ክረምቱን ጓደኞቻቸው ቤተሰቦች ቤት ለማሳለፍ የሄዱ ህፃናት አያሌ ነበሩ፡፡ እነዚህ ህፃናት መግቢያቸው የት ነው? ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ በአምባው ውስጥ ክረምቱን ለማሳለፍ በቆዩት ልጆች ላይ የተፈፀመው ነገር ነው፡፡
ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆኑትን ልጆች ሰብስበው ዝዋይ ከተማ ወስደው ሜዳ ላይ በተኗቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ለሞት፣ ለስደትና ለቡና ቤት ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ዕድሜያቸው አነስተኛ የሆኑትን አዲስ አበባ ቀጨኔና ሚኪሊላንድ ህፃናት ማሳደጊያ አስገቧቸው፡፡ በዚህ መንገድ ከአምባው የወጡት ልጆች ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው፣ በሰላም ተቀላቅለው ለመኖር ትልቅ ፈተናና ትግል ገጥሟቸው ነበር፡፡ ምንም ዓይነት የስነልቦና ዝግጅት ስላልነበረን ሁኔታውን መቋቋም ተስኖን ነበር። አምባው ስራውን ያቋረጠው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በድንገት ነበር፡፡”
የአምባው ፍሬዎችና አይረሴ መዝሙሮቻቸው
የአምባው ህፃናት ከ50 በላይ ህብረ መዝሙሮች የነበሯቸው ሲሆን ከእነዚያም ውስጥ ጥቂቶቹን አሰባስበው በቅርቡ በሲዲ በማስቀረጽ ለገበያ አቅርበውታል፡፡ “የህፃናት አምባ ልጅ ሆኖ መዝሙር የማይችል የለም፡፡ ታዋቂ ደራሲያንና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ወደ አምባ እየመጡ ያሰለጥኑን ነበር፡፡ የአምባ የጀግና ፍሬ በሚባለው የኪነት ቡድን ታቅፈን የሰራናቸው ከ50 በላይ ህብረ መዝሙሮች አሉን፡፡ አሁን አምባው ከፈረሰና ከተበተንን ከዓመታት በኋላ ባቋቋምነው “የአምባ አብሮ አደግ መረዳጃ እድራችን” ሙሉ ወጪው ተሸፍኖ መዝሙሮቻችን በሲዲ ታትመው ወጥተዋል፡፡ ሲዲውን ለመስራት ያነሳሳን የአምባ ልጆችን ሊያግባባና አንድ ሊያደርገን የሚችል በእጃችን ላይ የቀረ የድሮ ነገር መዝሙሮቻችን ብቻ መሆናቸው ነው፡፡
በዚህ ዘመን ደግሞ መሀል ላይ ላለው ትውልድ ማለትም ለታዳጊው የሚሆን መዝሙር የለም፤ ስለዚህ ለምን መዝሙሮቹን አውጥተን አናሳትምም ብለን ተነጋገርንና ውሳኔ ላይ ደረስን፤ መዝሙሮቹን በልጆቻችን ልናዘምረው ነበር ያቀድነው ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህም ከአራት ኪሎ ህፃናትና ወጣቶች ትያትር ሁለት ህፃናትን ወሰድንና ሰራነው፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“በሲዲ የወጣው ስራችን አሳዳጊዎቻችን ለነበሩ ሰዎችና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናችንን የምናቀርብበት እንዲሆን አድርገናል፡፡ አሁን እኛ ወላጆች ሆነን ስናየው፣ ልጆች ማሳደግ ምን ያህል ከባድና ፈታኝ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ስለዚህም አሳዳጊዎቻችን ሊመሰገኑና ሊከበሩ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡” ብለዋል የቀድሞ የአምባው ልጆች፡፡
የአምባው ልጆች ቅሬታ
“ህፃናት አምባው በጦርነትና በተፈጥሮአዊ አደጋዎች ወላጆቻቸውን ያጡ፣ አሳዳጊና ተንከባካቢ የሌላቸው ልጆች እንዲያድጉበት ታስቦ የተሰራና ህፃናት በስነ ምግባርና በትምህርት የሚታነጹበት ስፍራ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት አልነበረውም፡፡ አምባው በዚያ መንገድ መፍረሱ የሚያሳዝን ቢሆንም ከዚያ የበለጠ አሳዛኙ ጉዳይ ግን የአምባው ታሪክና ስራ ሁሉ እንዲጠፋ መደረጉ ነው፡፡
“ታሪካችን ብጥስጥስ ብሎ ወድቋል፤ ጠፍቷል። እኛ ስንወጣ ልጆች በመሆናችን ይዘነው የወጣነው ምንም ነገር የለም፤ ግን የአገር ታሪክ ነው፤ ትውልድ ቢማርበት ጥሩ ነበር፡፡ ይህ አልሆነም፤ ታሪካችን በታሪክነቱ እንዲቀመጥ ባለመደረጉ እናዝናለን፡፡” ሲሉ ልጆቹ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ (መታሰቢያ ካሳዬ፤ አዲስ አድማስ)
ከአዘጋጆቹ: በህጻናት አምባ የነበራችሁ ወይም ስለ አምባው የምታውቁት ነገር ያላችሁ ሁሉ በዚህ ኢሜይል አድራሻ (editor@goolgule.com) ጽሁፍ አዘጋጅታችሁ ብትልኩል በማለት ጥያቄያችንን ልናቀርብ እንወዳለን:: ከጽሁፎቻችሁ ጋር ፎቶዎችም ብትልኩልን ለህዝብ በማድረስ በኩል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን:: ቃለምልልስ ለማድረግ የምትፈልጉም ካላችሁ በዚሁ የኢሜይል አድራሻ ጻፉልን እናስተናግዳለን::
seashor boye says
ክብር እና ምስጋና እንደዚህ የተዳፈኑና የተቀበሩ እውነታዎችን ከየተዳፈኑበት እየፈነቀላችሁ ህዝብ ጀሮ ለምታደርሱ የህዝብም እና የታሪክ እምባ ጠባቂ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች የአምእሮ ልእልናውን ደርቦ ደራርቦ ያጎናፅፋችሁ ብያለሁ ይሄንን ፖስት ሳነብ ግን ከብዙ አመት በፌት ያነበብኩት ሰለ አምባ ልጆች የሚያወሳ የቢሆን አለም የሚል መፅሀፍ ትዝ አስባላችሁኝ
abyot bekele says
amebaw ketebetn bhula bezu bezu seqayoche dersewbegn neber ena esune benegerchu teru yemeslegnle