በግልጽ መታወቅ ያለበት የግለሰቡ ማንነትና ያደረገው አስተዋፅዖ
ዓመቱ ፲፱፻፷፫ ነበር። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፤ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነበርኩ። በዚያ ጊዜ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ፤ በስተግራ ከነበረው የፋሲካ ሆቴል፤ ከሆቴሉ በስተሰሜን ገባ ብሎ በረባዳው በኩል፤ ተከራይቶ የሚኖር፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ነበር። ይህ መምህር አቶ ክብረት ተስፋሁን ይባላል። የሻምበል ሞገስ ወልደሚካዔል የናቱ ታናሽ ወንድም ነው። አራት ሆነን ምሳ ስንበላ፤ ሞገስና እኔ በዩኒቨርሲቲው የምናደርገው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃመወያየት ጀመርን። ለኮንግሬስ ( የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር – አዩተማ University Students Union of Addis Abeba – USUAA – ኡዙዋ) የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ለመወከል እንደምወዳደር ቀደም ብዬ ነግሬው ስለነበር ያውቃል። ከጎኔ ውድ ጓደኛዬ፤ የሞገስ ወልደሚካዔልየአክስቱ ልጅ፤ አሊ ፈረጅ ነበር። በወቅቱ የመቶ አለቃ የነበረው ሞገስ፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ፤ የኢኮኖሚክስ ዲግሪውን በማታ ትምህርት እየወሰደ፤ ሊጨርስ ተቃርቦ ነበር። እናም የተማሪውን እንቅስቃሴ በደንብ ይከታተላል። ከመምህሩ ከዶክተር እሸቱ ጮሌ ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበረው።
አንዳንድ ሰዎች በዓለም ላይ በሕይወት ለመኖራቸው ትርጉም ሠጥተውት ያልፋሉ። ሕይወታቸውን እቅድና ግብ አበጅተውለት፤ ለዚሁ ግባቸው ሙሉ ጥረታቸውን ያበረክቱለታል። አንዳንዶች ቁጥር ሆነው፤ በድምሩ ነበሩ ተብለው ይላተማሉ። አንዳንዶች ደግሞ ዱካ እንደሌለው መንገደኛ፣ ጥላ እንዳልጣለ ዛፍ፣ መኖራቸው ሳይታወቅ ያልፋሉ። ሞገስ ወልደሚካዔል በመጀመሪያው ከተገለጹት ወገን ነው። ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ሕይወቱን ትርጉም አበጅቶለት፤ ለዚሁ ዓላማው፤ ቤተሰቡን፣ ዘመዱን፣ ንብረቱን ሁሉ ለዓላማው አራግፎ አልፏል።
“ስማ አንዱዓለም” ሲል ጀመረ ሞገስ። “አንተ በተማሪዎች እንቅስቃሴ የምታደርገውን ተስትፎ ብደግፈውም፤ ሌላ አማራጭ እንዳለ ልታውቅ ይገባሃል። እኒህ ሰውዬ በጣም አርጅተዋል። እንዲህ በደከሙበት ጊዜ፤ የሚከተለውን መተንበይ አይቻልም። በርግጥ ግን የምነግርህ፤ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አይኖርም። እሳቸው በሕይወት እያሉም ሆነ በሞት ተለይተው፤ ወደው ሥልጣን አይለቁም። በተማሪ እንቅስቃሴ የሀገራችንን ሂደት መወሰን አትችሉም። ያ አይቀሬ ቀን ሲመጣ አንተ አንድ የመቶ እየመራህ ብትገኝ፤ ልትጫወት የምትችለው ሚና ከፍተኛ ይሆናል። አባ ተፈራ ወታደር እንዳትሆን ታግሎሃል። አውቃለሁ። አዘዞ አባቶቻችን ወታደሮች ሆነው እያገለገሉ አድገናል። እሱ እንድትማርለት ይፈልጋል። አውቃለሁ። እኔንም ደጋግሞ ልጄን ወታደር እንዳታስገባብኝ ብሎኛል። አየህ፤ እኛና አባቶቻችን አንድ አይደለንም። የኛ ጊዜ የተለየ ነው። ታውቀዋለህ። ለውጥ ያንጃበበበት ጊዜ ነው። ጠቃሚ የሆነ አስተዋፅዖ ለማድረግ ከፈለግህ፤ አሁንም ደግሜ የምነግርህ፤ ሐረር የጦር አካዳሚ እንድትገባ ነው።” በማለት በኋላ ዞሬ ሳጤነው፤ ምን ያህል አርቆ አሳቢና አስተዋይ እንደነበር የተረዳሁትን ነገረኝ። በወቅቱ ግን፤ አባቴ ወታደር አትሆንም፤ መሐንዲስ ነው የምትሆነው ብሎ ከሕፃንነቴ ጀምሮ በተደጋጋሚ ያሳሰበኝ አጥቅቶም ይሁን አባቴን በመፍራት፤ የተማሪውን እንቅስቃሴ ያለልኩ ለጥጬ አክብጄ አይቼውም ይሁን የሱን ምክር አቅልዬ፤ “ተማሪውና መምህራን ተደራጅተናል፣ ሠራተኛው እየተደራጀ ነው፣ የኑሮ ውጥረቱ አይሏል፣ እኔ ሐረር አካዳሚ ሄጄ እስክመለስ የሚጠብቅ አብዮት የለም፤ በማለት ተከራከርኩት።
በአንጻሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪና አብረን አንድ ክፍል እንወስድ የነበረው ሻምበል አጥናፉ አባተ፤ በተደጋጋሚ የምናደርገውን የተማሪዎችእንቅስቃሴ በመቃወም፤ “ተው እናንተ ልጆች። ንጉሰ ነገሥቱ ምን አደረጉ? ይልቁንስ ብትማሩ አይሻላችሁም?” ይለኝ ነበር። እኔም፤ “አንተ ሙሉ ደሞዝክን እየበላህ፤ ሙሉ ተማሪ ሆነህ፤ ምን ጎሎህ! እዚህ መረጃ አቀባይ እንድትሆን ነው የተላክኸው። ሂደና ቤተመንግሥቱን ጠብቅ!” በማለት መልሼለት ነበር። እንግዲህ እኔ እዚህ ላይ የማሰፍረው፤ በምርምር ያገኘሁትን ወይንም ሰው የነገረኝን አይደለም። የራሴን ተመክሮ ነው። በቅርብ የወጡትን መጽሐፍት በማነብበት ጊዜ፤ ሻምበል ሞገስ ወልደሚካዔልን፤ አንድም አባቱ ከኤርትራ በመሆናቸው የኤርትራ ተገንጣዮች ደጋፊ፤ ሌላም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ( የኢሕአፓ ) አባል ስለነበር ፀረ-ደርግ አድርገው የሚስሉትን ተረድቻለሁ። እናም እኔ፤ የሞገስ ወልደሚካዔልን ማንነት ከማውቀው በመነሳት፤ ግልጽ ማድረግ ግዴታዬ ስለሆነ፤ እነሆ እውነቱ!
ሞገስ ወልደሚካዔል ተወልዶ ያደገው አዘዞ ነው። አዘዞ ከጎንደር አጠገብ የምትገኝ ትንሽ የወታደር ሰፈር ነች። ሞገስም እኔም የተወለድነው፤ ጠቅላይ ሰፈር እየተባለ ይጠራ በነበረው የሰባት ቁጥር ቅርጽ በያዙት ሁለት መደዳ ቤቶች ውስጥ ነበር። እነሱ በምዕራብ በኩል ባለው ቤት ሲኖሩ፤ እኛ ደግሞ በሰሜን በኩል ባለው ቤት ነበርን። በኋላ ከዓለማያ ኮሌጅ ተመርቆ፤ አርሲ የጭላሎ ፕሮጀክት ተቀጥሮ ሲሰራ ሕይወቱ ያለፈው ታናሽ ወንድሙ ዮሐንስ ወልደሚካዔል ሲሆን፤ የዮሐንስ ታናሽና አንድ ክፍል በትምህርት ቤት የምበልጠው የኔ ጓደኛ መላኩ ወልደሚካዔል ነው። የሱ ተከታዮች ክፍሌና ሙሉጌታ ናቸው። በትምህርቱ ጎበዝ የነበረው ሞገስ፤ አዘዞ የአፄ ፋሲል አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ ባኋላ፤ ወደ ጎንደር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄዶ፤ ከዚያም ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ በመሄድትምህርቱን ቀጠለ። አባቱ የሻምበል ባሻ ወልደሚካዔል በጡሮታ ጊዜያቸው፤ በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ፤ በበረንቱ የምክትል ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾመው፤ ወደዚያ ሄደዋል። እናቱ የጎንደርና የጎጃም ተወላጅ ሲሆኑ፤ ገና በወጣትነቱ ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። እኔ ያኔ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በመጀመር ላይ ነበርኩ። እናቱ የተቀበሩት አዘዞ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስትያን ነው። የናቱ እናት እሙሃይ ማማ አልጋነሽ፤ አዘዞ መንኩሰው ሲኖሩ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፤ ሞገስ በተገደለበት ሰሞን ነው። እሳቸውም የተቀበሩት አዘዞ ነው።
ለመንደርደሪያ ይኼን ካቀረብኩ በኋላ፤ ወደሞገስ የፖለቲካ ተሳትፎ ላቅና። ሞገስ ከሐረር የጦር አካዳሚ በከፍተኛ ውጤት ከተመረቀ በኋላ፤ በቀጥታ አዲስ አበባ ተመድቦ፤ በአራተኛ ክፍለ ጦር ያገለግል ነበር። በዚያን ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ማታ ማታ በመማር የኢኮኖሚክስ እውቀቱን ለማጎልበት ገፋ። ያኔ ነበር እኔን ሐረር የጦር አካዳሚ ገብቼ የመቶ አለቃ በመሆን፤ የበለጠ አስተዋፅዖ ሊኖረኝ እንደሚችል የመከረኝ። ገና የካቲት ፷፮ ከመምጣቱ ከሶስት ዓመት በፊት፤ ሊከተል የሚችለውን ጉዳይ ተገንዝቦት ነበር። በወቅቱ ተራማጅ ከነበሩት ግለሰቦች ጋር ግንኙነቱን ቀጠለ። ገና ሃያ ዓመት ሊሞላኝ በመንደርደር ላይ የነበርኩና ሁሉን አውቃለሁ ባይ የወጣት ትዕቢት የወጠረኝ ስለነበርኩ፤ የኔን መልስ አክብዶ እንዳልወሰደው የነገረኝ በኋላ ነው። ሞገስና እኔ በቀጥታ ስለፖለቲካ በዝርዝር መነጋገር የጀመርነው፤ የካቲት ባንዣበበበት ወቅት ነበር። አቃቂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሊያድግ፤ ዘጠነኛ ክፍል ተከፍቶ ነበር። እዚያ አስተምር ነበር። የምኖረው አዲስ አበባ ሆኖ፤ በየዕለቱ እየተመላለስኩ ሙሉ አስተማሪና፤ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሙሉ ተማሪ ነበርኩ። ሞገስ ላከብኝና፤ ገነት ሆቴል አጠገብ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሄድኩ።ከሱ በኩል የማውቀው ምንም ነገር አልነበረም። እኔን ግን ስለተማሪው እንቅስቃሴና ሂደቱ በየዕለቱ እንድነግረው ይጠይቀኝ ነበር። እኔም ከኔ በኩል የማውቀውን ከመዘላበድ በስተቀር፤ እሱን ምንም ጠይቄው አላውቅም። በዚህ ደረጃ እያለን፤ የካቲት ፈነዳ። ያኔ ሞገስ እኔን የመፈለጉን ያህል እኔም እፈልገው ነበር። የትም ተጽፎ ያላየሁት፤ ሞገስ ለደርግ መፈጠርና ማደግ ያደረገውን አስተዋፅዖ ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ሞገስ የደርግ አስኳል የሆነውን ቡድን በማሰባሰብ በኩል ያደረገውን ሩጫ፤ በየጊዜው ይነግረኝ ነበር። ሞገስ ያኔ የዕለት ተዕለት ሥራው አድርጎ የያዘው ይኼኑ ነበር። በአራተኛ ክፍል ጦር ውስጥ፤ የሚደረገውን የሚስጢር ስብሰባ ይነግረኝ ነበር። ማን ማን እንደሆኑ በዝርዝር አውቅ ነበር። የያንዳንዳቸውን የፖለቲካ እውቀት ደረጃና ብስለታቸውን ይነገረኝ ነበር።
ደርግ ጎልብቶ ሲወጣ፤ ሞገስ የኢኮኖሚክስ ክፍሉ ኃላፊ ሆነ። ንጉሠ ነገሥቱን ለማውረድ የተደረገውን የመረጃ ስብሰባ የመራ ሞገስ ነበር። ይህን በሙሉ እምነት ለመናገር ያስቻለኝ፤ በወቅቱ አንዳንድ መረጃዎችን እንድሰበስብለት ብዙ ቦታ ልኮኝ ስለነበር ነው። በጠቅላላ መስከረም አንድ ቀን ማታ የታወጀውን የንጉስ ነገሥቱን ከሥልጣን መውረድና የቀረቡትን መረጃዎች ያጠናቀረው ሞገስ ነበር። የመሬቱን አዋጅ በተመለክተ፤ በዝርዝር ያደረገውን ጥረትበሌላ ጊዜ አቀርበዋለሁ። ላሁኑ ግን፤ ሙሉ መረጃውን ያሰባሰበውና ያጠናቀረው ሞገስ ነበር በማለት አልፈዋለሁ። ያኔ ከሁለት የደርግ አባሎች ጋር አስተዋወቀኝ። የመጀመሪያውና በቀጥታ ከፍተኛ እምነት እንዳሳድርበት ያደረገኝ፤ ጁኒየር ኤክማን ዮሐንስ ፍትዊ ነበር። ሁለተኛው ወጣት የመቶ አለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ነበር። ስለመቶ አለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ሲነግረኝ፤ “ይህ ወጣት የመቶ አለቃ ተስፋ አለው። ምንም የፖለቲካ እውቀት የለውም። ሆኖም ግን፤ እንደሌሎቹ ላለፈው ሥርዓት የጠበቀ ፍቅር የለውም። የማርክሲዝም ሌሊንዝም እውቀት ባይኖረውም፤ ሊማር የሚችልና ከኛ ወገን ልናደርገው የምንችል ስለሆነ፤ ትንሽ ገረፍ ገረፍ እንድታደርገው እፈልጋለሁ።” አለኝ። ምንም እንኳ እኔ ያኔ ኢሕአፓን ከመሠረቱት የአንዱ ቡድን አባል ብሆንም፤ ሞገስ የድርጅትአባል ይሁን ወይንም አይሁን አስቤበትም አላውቅም። ነውም አይደለምም የሚል ግምት አልነበረኝም። የነበረኝ እምነት፤ ሞገስ ወንድሜ ነው። የኔ ስኬት ለሱ፤ የሱ ስኬት ለኔ ነው የሚል ብቻ ነበር። እናም ይህ ነበር ያሯሯጠኝ። በዚያ ወቅት እኔ የነበረኝ ፍላጎት፤ የነበረው አድሃሪ ሥርዓት ፈርሶ፤ ከሁሉም የተደራጁ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ተሰባሰቦ፤ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋሙ ነበር። እናም የጠየቀኝን በሙሉ አደርግለት ነበር። እኔ የጠየቅሁት ነገር አልነበረም። እሱ የሚነግረኝ የደርግ የዕለት ተዕለት የውስጥ ሂደት፤ ለኔ በቂ ነበር። አብሬያቸው የምኖረው የኢሕአፓ አባላት፤ ከፍተኛውን መስዋዕትነት ከፍለው ያለፉት ሠይፉ ጠናና እዮብ ጠና፤ ከሞገስ የማመጣውን ዜና በጉጉት ይከታተሉ ነበር። ከዚያ በተረፈ፤ ከሞገስ ጋር፤ ድርጅታዊ ተልዕኮም ሆነ ግንኙነት አልነበረኝም። ሞገስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለማነጋገር ከመጡት የደርግ አባላት አንዱ ነበር። በወቅቱ አራት ኪሎ ከሚገኘው ግቢ ውስጥ፤ በእግር ኳስ ሜዳው ደረጃዎች ላይ ተኮልኩለን ለተቀመጥነው ተማሪዎች የተናገረው አንድ አረፍተ ነገር ትዝ ይለኛል። “The military cannot defy history! – ወታደሩ ታሪክን ሊጠቀጥቅና ሊያልፍ አይችልም።” ያለው። ሞገስ ደርግ ከሌሎች ተራማጅ ኃይሎች ጋር በመተባበር፤ ሀገራችንን ወደ ትክክለኛ መንገድ እንደሚመራት ከፍተኛ እምነት ነበረው። የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነቱን ተማምነናል።
ካነበብኳቸው መጽሐፍት ውስጥ፤ የሞገስን የኤርትራዊ ትውልድ ትስስር አስመልክቶ፤ ከአማን አንዶም ጋር ሆኖ ተገንጣዮችን ደጋፊ አድርገው የወነጀኑትን አግኝቻለሁ። የማውቀውን ልንገራችሁ። አንድ ቀን ሞገስ በጣም ተበሳጭቶ አገኘሁት። “You know what he said? – ምን እንዳለ ታውቃለህ?” አለና በቀጥታ ዓይኖቼን ተመለከተ። ማን ወይንም የት ብዬ እስክጠይቅ ፋታ አልሠጠኝም። “He said: ‘I am not going to dance to the tune of hooligans! – ለማንም የዱርዬ ጥርቅም አታሞ፤ እስክስታ አልመታም!’ አይገርምህም!” በማለት አራገፈብኝ። ጀኔራል አማን አንዶምን ነበር። ጀኔራን አማን አንዶምን ለማግባባትና የያዘውን አቋም እንዲለውጥ ወደ አማን አንዶም ሲላክበት፤ ከላይ የሠፈረውን በመናገር ዘጋቸው። ሞገስ በአማን አንዶምና በደርግ አባላት መካከል እርቅ እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። አማን ይሄን ባለበት ወቅት ግን፤ የተበሳጨው ሞገስ፤ ፍጹም ተቃራኒው በመሆን፤ በአማን አንዶም ላይ ለተወሰነው ድንጋጌ አባሪ ነበር።
ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ፤ በኢሕአፓ በኩል፤ ከሞገስ ጋር የማደርገውን ግንኙነት እንዳቆም ተላከብኝ። እኔ ደግሞ ክፋቱን አላየሁትም ነበር። ሠይፉም፤ “ሞገስ የድርጅታችን አባል ስለሆነ፤ ልታጋልጠው ትችላለህና አቁም!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሠጠኝ። ያን በማቅማማበት ወቅት ነበር የጀኔራል አማን አንዶም ሁኔታ የተከሰተው። በሂደቱ እኔን በጣም ያስቆጣኝና ከሞገስ ጋርም ለመጨረሻ ጊዜ ያለያየኝ ክስተት ተፈጠረ። ከአማን ጋር የነበራቸው ፍጥጫ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ በአጣብቂኝ ላይ ባሉበት ደረጃ፤ በአማን ላይ አስቸኳይ እርምጃ ካልወሰዱ፤ መንግሥቱና ቡድኑ ሥልጣን ከጃቸው እንደሚያመልጥ ተረዱ። ፍራቻ ወረሳቸው። እናም በሱ ላይ እርምጃ መውሰዱን ተስማሙበት። በዚህ ሂደት፤ በቀጥታ በአማን ላይ እርምጃ መውሰዳቸው፤ በጦሩ ላይ የሚያስከትለው እንደምታ አስፈራቸው። እናም አዳብለው በቁጥጥራቸው ሥርየነበሩትን እስረኞች መደረቡን ተስማሙበት። በኔ እምነት፤ በስድሳዎቹ ላይ የተወሰደው አስቸኳይ እርምጃ፤ በአማን ላይ ሊወስዱ ከወሰኑት ጋር የተዳበለ የፍርሃት ጥቃት እንጂ፤ ራሱን የቻለ የፖለቲካ እርምጃ አልነበረም።
እግረ መንገዱን ግን፤ በመንግሥቱ ኃይለማርያም የፍርሃት መርበድበድ፤ አስቸጋሪ የሆነባቸውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመምራት የታሰሩ ጥቂት የደርግ አባላት፤ አብረው ተገደሉ። ከነዚህ መካከል ዮሐንስ ፍትዊ አንዱ ነበር። ያንን በሬዲዮ ስሰማ፤ በንዴት ተቃጠልኩ። ዮሐንስ የኢሕአፓ አባል እንደነበር ያወቅሁት በኋላ ነው። እኔ ያወቅሁትና የወደድኩት፤ ባጭር ጊዜ በነበረን ግንኙነት፤ ባየሁበት ባህሪው ነበር። ወጣት፣ እንደኔው ቅብጥብጥ፣ እንደኔው ችኩል፣ በጣም ምኞታችን ከተጨባጩ ሁኔታ ከንፎ የበረረ፣ ለሕዝብና ላገር ከፍተኛ ፍቅር ያለው ነበር። የሱ ሞት ከሞገስ ጋር አቆራረጠኝ። አንድ ፉልስካፕ (የአረብ ሉክ) የሚባል ዝርግ ወረቅት ሙሉ፤ የወንድም ቁጣ፣ የንዴትና የጉራ ሙሉ ጽሑፍ፤ ለሞገስ ላክሁለት። በውጡም፤ “ዛሬ አንተ ከመንግሥቱ ጋር ሆነህ ዩሐንስን ገደልክ። ነገ መንግሥቱ አንተን እንደሚገድልህ እወቅ። እሱ ባይገድልህ፤ እኔ ደሙን ካንተ እንደምበቀልና እንድምገድልህ እውቅ!” የሚል ይገኝበታል።
መንግሥቱ ኃይለማርያም ሞገስንና ሌሎችን ለምን ገደለ ብዬ አልጠይቅም። ምክንያቱን አውቀዋለሁ። ሥልጣኑን አጠቃሎ ለመውሰድና ሌሎችን ለመጨፍለቅ በሚያደርገው ሩጫ፤ ከፍተኛ ደንቃራ ሆነው ከቆሙበት አንዱ ሞገስ ነበር። አንድ ጊዜ ከሞገስ ጋር ስንገናኝ የነገረኝን አስታውሳለሁ። “አሁን አለቀለት!” በማለት ጀመረ። “ማን?” ስለው፤ “መንግሥቱ ነዋ! ምን መሰለህ፤ ብዙዎቹ አካሂያዱን ተረድተዋል። በቀጥታ እሱን ከሥልጣን ሩጫው ማቆም የምንችልበት መንገድ ተፈጥሯል። በኮሚቴው ውስጥ የሚኖረውን ሚና እያቀጨጭንበት ነው። አብዛኛው አባሎች የሱን ሂደት ስለተገነዘቡ፤ የደርግን መዋቅርና የመሪዎችን የሥልጣን ልክ ለማስተካከል፤ የድምጽ መሥጠት ሂደት ሊከተል ነው። እኛ የድምጽ የበላይነት አለን።” አለኝ። “ተው! ይሄ ተንኮለኛ ቀላል እንዳይመስልህ! ለምን ይልቁንስ እርምጃ አትወስዱበትም!” አልኩት። “ቀላል እንዳይመስልህ። ዋናው ነገር የአባላትን ድምጽ ማግኘቱ ነው። እና አሁን የበላይነት አለን።” በማለትና በልበ ሙሉነት ነገረኝ። እኔም ደስ ብሎኝ ተለያየን። ሞገስ በአባላት ሙሉ መብትና በድምጽ ብልጫ ያምን ነበር። የሰውን ቅንነት ይቀበል ነበር። ጥሩውን አጉልቶ ይመለከት ነበር። ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ማመን ብቻ ሳይሆን፤ መተግበር ከፍተኛ ጥረቱ ነበር።
እገረ መንገዴን አንድ ነገር ላስቀምጥ። አንዳንዶች ሻምበል ዓለማየሁን የኢሕአፓ ቀንደኛ አባል አድርገው ያቀርቡታል። እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ ይህ ትክክል አይደለም። እኔ ወደ አሲንባ ለመሄድ በምጠባበቅበት ወቅት፤ በሕቡዕ ከቦታ ወደ ቦታ እየተቀያየርኩ እኖር ነበር። አንድ ቦታ በተቀመጥኩበት ወቅት፤ የነበርኩበት ጓድ የአንድ መስሪያ ቤት ባለሥልጣን ነበር። ሻምበል ዓለማየሁ ጓደኛው ነበር። በዚያ ወቅት፤ ሻምበል ዓለማየሁ የድርጅቱ አባል እንዲሆን ተወስኖ፤ ይህ ግለሰብ ከዓለማየሁ ጋር ቀጠሮ አደረገ። ማታ ደስ ብሎት ስናወራ አመሸን። በነጋታው መንግሥቱ ኃይለማርያም እነ ጀኔራል ባንቲን፣ ሞገስንና ዓለማየሁን መረሸኑን ሰማን። ከፍተኛ ድንጋጤ ሆነብን። ዓለማየሁ የድርጅቱ አባል መሆኑ በቀጠሮ ቀረ። ምንም እንኳ በደርግ ውስጥ በከፍተኛ ንቀት የዴሞክራሲን ወረቀት እየያዘ፤“ልክህን ነገረህ!” እያለ በመንግሥቱ ላይ ቢፎክርበትም፤ እኔ እስከማውቅ ድረስ፤ ሻምበል ዓለማየሁ የኢሕአፓ አባል አልነበረም። ሞገስ ወልደሚካዔል የኢሕአፓ አባል እንደሆነ ከተነገረኝ በኋላ፤ ወደ ቤቱ መሄዴን አቆምኩ። ይህ የምስክርነት ቃሌ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
አርብ፤ ጥቅምት፲፪ ቀን፤ ፳፻፰ ዓመተ ምህረት ( 10/23/2015 )
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
ኃይለ says
አስመሳይ ሁላ ዛሬ ላይ ሆነህ ስለዛ ዘመን የበሰበሰ የሃገር ጠላት ፣ሃገርን እንደ ወያኔና ሻእቢያ ለመበታተን ተነስቶ የነበረ ነገረ ግን ምንም እንኳን ጨፍጫፊዎች ቢሆኑም ለሃገር አንድነት ፍቅር በቆሙ የደርግ አባላት በ ጓድ መንግስቱ ኃይለ ማርያም አመራር ሰጪነት የተመነጠረ ፣የኢትዮጵያን ስቃይ ከዛሬ አርባ አመት ጀምሮ ሊያስጀምር የነበረ ኢሕአፓ የተባለ ደነዝና መሰሪ ፓርቲ አታውራ፣ስለ ኢትዮጵያ ጠላቶች መስማት እኔም ሆንኩ ማንም ኢትዮጵያዊ/ት ሰልችቶናል።