በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በጣም ተወዳጁ ኤፍኤም ሬዲዮ ሸገር ነው ቢባል የሚያጣላን አይመስለኝም። ሸገር መፈክሩ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” የሚል ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፖለቲከኞችም ይህንኑ መፈክር የንግግራቸው ማሳረጊያ ዓረፍተ ነገር እያደረጉት ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ከመግለጫዎቹ ግርጌ “ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር” የሚል ዓረፍተ ነገር ያስቀምጣል። አዲሱ በእነሰይፉ ፋንታሁን እና ሠራዊት ፍቅሬ… የተከፈተው ኢትዮ ኤፍኤም ሬዲዮ “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ” የሚል መፈክር ይዞ መጥቷል። በቅርብ ጌዜ ከተከፈቱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ – ጄቲቪ – መፈክሩ “ኢትዮጵያዊነት መልካምነት” የሚል ነው። “ኢትዮጵያ” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ዘፈን የአገር ውስጥ ሽያጭ ሪከርድ ሰብሯል። የሐበሻ ቢራ ማስታወቂያ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለውን ቃል ማዕከል ያደረገ እና ስለኢትዮጵያ ‘ገናና ታሪክ’ የሚያወሳ ዓይነት ነው። ሐበሻ ቢራ ገና ከመተዋወቁ ገበያው ደርቶለት የነበረውን ዋልያ ተቀናቅኖ ወጣ። ገበያው ከማስታወቂያው ነው ብለው ይመስላል፣ ሌሎቹም ቢራዎች ተቀራራቢ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን ይዘው ብቅ-ብቅ ማለት ጀመረዋል። የቴሌቪዥን ትዕይንቶች፣ የግጥም ምሽቶች፣ ሌሎችም የጥበብ ሥራዎች ከመቼውም ግዜ በላይ ‘ኢትዮጵያዊነት’ን እያንቆለጳጰሱ ነው። በምላሹም ቀላል የማይባል ጭብጨባ ይቀበላሉ።
እነዚህ ሁሉ በተለምዶ “ኢትዮጵያዊነት” የሚባለው የአንድነት ኃይሉ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ማኅበራዊ መገለጫዎች ይመስላሉ። ነገር ግን እነዚህ ይፋዊ መፈክሮች “ንቅናቄው እያደገ መምጣቱን ያረጋግጣሉ ወይስ፣ የዘውግ ፖለቲካ ንቅናቄ እና ዕድገት ድንጋጤ የፈጠረው ግብረ መልስ ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ለዚህ ጥያቄ የግሌን መልስ በመስጠት ብቻ አይወሰንም፡፡ ይልቁንም፣ “ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ተቆርቋሪ ነን የምንለው ሰዎች እውን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ስሜት እና ፍላጎት ታማኝ ነን ወይ?” የሚለውንም ጥያቄ እግረ መንገዴን አንስቼ ለውይይት ክፍት ማድረግ ነው፡፡
ግን፣ ግን ‘ኢትዮጵያዊነት’ ራሱ ምንድን ነው?
“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ከሚለው መፈክር የምንረዳው ነገር ቢኖር ‘ኢትዮጵያዊነት’ መሠረቱ ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገረ መንግሥት መቀጠል አለባት የሚለውን ቁምነገር ያነገበ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ ግን አንድ ወጥ መልስ ያለው አይመስልም፡፡
‘ኢትዮጵያዊነት’ ከሚለው ቃል በፊት ‘ኢትዮጵያኒዝም’ የሚለው የእንግሊዝኛ ዕኩያው-መሳይ በጥቅም ላይ ውሎ ነበር። የእኛው ‘ኢትዮጵያዊነት’ እና የአፈ እንግሊዞቹ ‘ኢትዮጵያኒዝም’ ግን ለየቅል ናቸው። ‘ኢትዮጵያኒዝም’ የተባለው ንቅናቄ የተጀመረው በ1880ዎቹ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘ኢትዮጵያ’ የሚለው መጠቀሱ፣ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ቄሱም፣ ምዕመኑም ጥቁር መሆኑ ነበር መነሻቸው። በወቅቱ ክርስትና የነጩ ዓለም ጭቆና መሣሪያ ስለነበር ቄስ መሆን የሚችለው ነጭ እንጂ ጥቁር አልነበረም። ጥቁሮች ለመብታቸው መቆም ሲጀምሩ፣ ከፊሉ ክርስትናቸውን በእስልምና ሲተኩ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ‘ኢትዮጵያኒዝም’ የሚል ንቅናቄ ፈጥረው፣ ጥቁር የሚሰብክበት ‘የኢትዮጵያ’ የተባሉ ቤተ ክርስትያኖችን አቋቋሙ። ከዚያም የአድዋ ድል መከተሉ ለጥቁሮቹ ንቅናቄ ኃይል ስለሰጠው ከምዕራብ አገራት (በተለይም ከአሜሪካ) ወደ አፍሪካ፣ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት ኢትዮጵያኒዝም ተስፋፍቶና ተሟሙቆ በአፓርታይድ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብቻ 37ሺሕ ገደማ ‘ኢትዮጲያኒስት’ ቤተ ክርስቲያኖች ተፈጥረው ነበር።
በአገራችን ግን ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለው ቃል አጠቃቀም ከዚህ ሃይማኖታዊ-ፖለቲካዊ ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ብቻ ሆኖ ከመውጣቱም በላይ፣ አጠቃቀሙም መላውን የጥቁር ዘር ወክሎ ሳይሆን በኢትዮጵያ ድንበር የታጠሩትን ብቻ ወክሎ ነው። በዚያ ላይ ቃሉ በይፋ መደመጥ የጀመረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በብዛት የውጭ ሠራተኞችን ቀጥረው ያሠ፡ሩ የነበሩ የመንግሥት ተቋማትን በኢትዮጵያውያን መተካት እና ተቋማቱም ኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲይዙ ማድረግ ሲጀመር ነበር። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ‘ኢትዮጵያናይዝ’ የማድረግ ንቅናቄ ሲጀመር ኢትዮጵያዊ ሠራተኞችን (ከአብራሪ፣ እስከ በረራ አስተናጋጅ፣ እስከ ቢሮ ሠራተኞች) በፈረንጆቹ ምትክ የማሰማራት፣ የአማርኛ ቋንቋን መጠቀም፣ የባሕል ልብሶችን እንደ ዩኒፎርም መጠቀም የንቅናቄው አንድ አካል ሆነው ወጥተዋል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበረው የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ግንዛቤ “የአማራ እና የትግሬ”ን እሴቶች ብቻ ያቀፈ ተብሎ ተተችቷል። በዘር የሚተላለፈው፣ የገባር ስርዓት ላይ ሕዝባዊ አብዮት ሲነሳ፣ ስርዓቱ ከደረሱበት ውግዘቶች አንዱ ይህ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ግንባታ ሁሉንም ያማከለ አይደለም የሚለው ነበር። ‘ኢትዮጵያዊነት’ የተባለው ለሁሉም ዕኩል ገላጭ አልነበረም የሚለው ትችት እስካሁንም ድረስ ይደመጣል።
ቀድሞ በንጉሣዊው ስርዓት እና በገባር ስርዓቱ የከፉ ብሶቶች ታፍኖ የነበረው የአለመወከል ቅሬታ፣ ከአብዮቱ ጋር ሲፈነዳ፣ ‘ኢትዮጵያዊነት’ (በነባሩ አረዳድ) ይስማማቸው የነበሩ ሁሉ አገሪቷ ትፈርሳለች ብለው ደንግጠው ነበር። ከነዚህ ድንጉጦች ውስጥ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መፈክር ይዘው የመጡት ደርጎች ይገኙበታል። ደርጎች ኦሮሞውን ተፈሪ በንቲን እና ኤርትራዊውን አማን አንዶምን ርዕሰ ብሔር አድርገው የመረጡት በነባሩ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ውክልና ሳይሰማቸው የቀሩትን ሕዝቦች (አለመወከሉ በባሕልና እሴት ብቻ ሳይሆን በአገር አመራርም (ፖለቲካ ሥልጣንም) ጭምር ነበርና) ጥያቄያቸውን በከፊል ለመመለስ እንደነበር ጓድ መንግሥቱ ሳይቀሩ (ከገነት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ) አምነዋል። ነገር ግን የሥልጣን ሽኩቻው ከኢትዮጵያ ቀደመና ሁለቱም ሲወገዱ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ሳይቀድም ቀረ። ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ሥልጣን እስከጨበጠ ድረስ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ቢያንስ በመፈክር ደረጃ ይቀድም ነበር። በወቅቱ በዘውግ ለእድር እንኳ በይፋ መደራጀት አይፈቀድም።
ኢሕአዴግ ሲመጣ ግን ነባሩን የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ትርክት ተጠያፊ ሌላ የአደባባይ ትርክት ይዞ ነው። ትርክቱ ቀድሞም በተቃዋሚዎች ቢቀነቀንም፣ ገዢ ትርክት እንዲሆን አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በአጭሩ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያስተሳስረን ነገር ካለ ኢኮኖሚ ነው የሚል እምነት አንፀባርቋል። ለዚህም ይመስላል፣ ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው “የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክአ ምድር አሰፋፈር የነበረን እና ያለን…” በማለት የዘውግ ቡድኖች የተለያየን መሆናችንን ካስታወሰን በኋላ፣ የሚያስተሳስረን ቁሳዊ ጥቅም ብቻ መሆኑን ሲነግረን ደግሞ “አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ለመገንባት” የሚል ቃልኪዳን በብሔር ብሔረሰቦች መሐል መደረጉን ይነግረናል።
ኢሕአዴግ ይህንን አቋሙን ሲያራምድ ፖለቲካው ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳረፍ ከሚችሉ ወገኖች ጋር ትልቅ ግጭት ውስጥ ገብቷል። ይሁን እንጂ ገና በዘውግ የመደራጀት መብት ከመፈቀዱ በርካታ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ተፈጥረዋል። ከግንባር ቀደሞቹ የዘውግ ድርጅቶች ውስጥ፣ በ‘ኢትዮጵያዊነት’ አይደራደርም የሚባለው የአማራ ሕዝብን የሚወክለው ‘መአሕድ’ ብዙ አባላትን ይዞ መነሳቱ ደግሞ ትንግርት ነበር። (በርግጥ ለዚህ የተሰጠው ዋነኛው ትንታኔ ሕወሓት ጣቱን አማራ ላይ ቀስሮ “ትግሉ የተደረገው የብሔር እና መደብ ጭቆናን ለማስወገድ ነው” እያለ ሲደሰኩር ስለነበር ነው የሚል ነው፡፡) ይህ በእንዲህ እያለ፣ መጀመሪያ፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በ1989 ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት ለመግጠም ሲገደድ ሥሙን እንኳ ይጠየፈው የነበረውን ‘ኢትዮጵያዊነት’ን በራሱ ዜማ ለመዘመር ተገደደ። ከዚያም፣ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ‘ቅንጅት’ በከተሞች፣ እንዲሁም በአማራ እና በደቡብ ክልሎች ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ እና ‘ኢትዮጵያዊነት’ን በውስጠ ታዋቂነት ማንገቡ ተቀባይነት አስገኝቶለታል የሚል ትምህርት በመቅሰም፣ ‘በአዲስ አበባ የኢሕአዴግ አባላትን ብሔር ሳይጠይቁ ከመመልመል’ ጀምሮ ‘የባንዲራ ቀን’ ከማክበር፣ ያስተሳስረናል ያለውን ‘የኢትዮጵያ ሕዳሴ’ን እስከማወጅ ደረሰ።
ነገር ግን በዘውግ መደራጀት፣ በዘውግ መፈራረጅ፣ በዘውግ መወጋገን እያደገ መጣ እንጂ አልቀነሰም። ይልቁንም አስተሳሰቡ እንደቀድሞው በገጠር ከመወሰን ይልቅ የወትሮው የከተሜው ዘውግ-ጥዩፍነትን በማሸነፍ በከተማም ፖለቲካዊ ርዕዮትነቱ ጨመረ። ለዚህ ዐቢይ ምክንያቱ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካውን በዘውግ ለመዘወር መምረጥ ሲሆን፣ በምላሹ የሚቀነቀነው የአንድነት ኃይሉ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ንቅናቄ ደግሞ ራሱን ታሪክ ናፋቂ፣ የሚሰነዘሩበትን ትችቶች የማይቀበል፣ ዘመኑን ያልዋጀ መስሎ መታየት እሳቱ ላይ ነዳጅ ጨምሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ‘ኢትዮጵያዊነት’ አሁን የሚታወሰው በዘፈን፣ በእግር ኳስ እና አትሌቲክስ ሜዳ ብቻ የሚመስልበት ጊዜ መጣ። የዘውግ ንቅናቄዎች የበለጠ ተቀባይነት ማግኘት እውነታ ጋር የተጋፈጠው ድኅረ-ዘውጌ (post-ethnic) ነኝ ባዩ የከተሜ ልኂቅ በዚህ ተደናገጠ። በዚህ ድንጋጤም ይመስላል ቀድሞ (በተለይ በደርግ ጊዜ) በመንግሥት አስገዳጅነት ይቀነቀን የነበረው ‘ኢትዮጵያዊነት’ አሁን በኪነት ሰዎች፣ በሬዲዮና ቲቪ አቅራቢዎች (ወይም በመገናኛ ብዙኃኑ) የለትተለት አጀንዳነት የተተካው። ዛሬ ዛሬ ከመቼውም ግዜ በበለጠ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለው መፈክር ብዙ ጠቃሽ አግኝቷል። አሁንም ቢሆን ግን፣ የ‘ዘውጌ ይቅደም’ ንቅናቄ ከገጠር ከተማ በዘለቀበት ፍጥነት፣ ‘የኢትዮጵያዊነት’ መፈክር ከከተሜዎች አልፎ ብዙኃን ገጠሬዎች ጋር ደርሷል ማለት አይቻልም።
ከዚህ ሒደት መረዳት የምንችለው እና መጠየቅ ያለብን ጉዳዮች፣
1) ብዙኃኑ እና ገጠሬው ኢትዮጵያዊ ቀድሞም ይሁን አሁን ‘ዘውጌ ይቅደም’ ባይ መሆኑን(?)
2) ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለው አስተሳሰብ መጀመሪያ መንግሥታዊ ፕሮጀክት፣ ከዚያ በኋላ ከተሜው ጋር ተቀባይነት ያገኘ ንቅናቄ መሆኑን(?)
3) ምናልባትም ከከተሞች ዴሞግራፊ መቀየር (ገጠር-ከተማ ፍልሰት) ጋር ተያይዞ፣ ወይም በፖለቲካ ጨዋታው መቀየር ምክንያት፣ ከተሜውም ዘውጌኝነትን እያራመደ መምጣቱ፣
4) ‘ኢትዮጵያዊነት’ ይቅደም የሚለው ንቅናቄ የጨመረ ቢመስልም፣ ለ‘ዘውጌ ይቅደም’ ንቅናቄ የተሰጠ ግብረ መልስ መሆኑን ነው።
ይህ ግን ‘ኢትዮጵያዊነት’ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ አይመልስልንም። “‘ኢትዮጵያዊነት’ በዜግነት የሚገኝ ነገር ነው” ማለት የንቅናቄውን መንፈስ አለመረዳት ነው። ‘ኢትዮጵያዊነት’ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ነገር ነው፡፡ በተለይ በብዙኃኑ እና በልኂቁ መካከል የተለያየ ነገር ነው፡፡ በብዙኃኑ ዓይን ‘ኢትዮጵያዊነት’ ሲባል የሚመጣባቸው ቀደምት የሥልጣኔ ምንጭነት (ለምሳሌ አኵሱም)፣ አኩሪ የትውፊት ባለቤትነት (ለምሳሌ ገዳ)፣ የጀግንነት እና ነጻነት ምሳሌ (ለምሳሌ አድዋ)፣ ሃይማኖታዊ ባለታሪክነት (ለምሳሌ የክርስትና እና የእስልምና ወደአገር ቤት አገባብ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መከባበራቸው) እና የመሳሰሉት ናቸው ትዝ የሚሏቸው፡፡ ይህ ግን እያደገ የመጣውን እና ልኂቃኑን የሚወክለውን ‘ኢትዮጵያዊነት’ የተሰኘ የፖለቲካ ንቅናቄ አይወክልም፡፡ ሆኖም ልኂቃኑ እነዚህን አንድ ሕዝብ የወል ሥነ ልቦና እንዲኖረው የሚያስፈልጉትን የኩራት ምንጮች መጠቃቀሳቸው አይቀርም፡፡ ነገር ግን የወል የኩራት ምንጮችን መጠቃቀሳቸው ብቻውን አሁን የሚያራምዱትን የፖለቲካ ንቅናቄ ሐቀኛ እና ትክክለኛ አያደርገውም፡፡
የንቅናቄው አራማጅ ነን የሚሉት ልኂቃንም ቢሆኑ ራሳቸው የተለያዩ መሆናቸው በራሱ ብያኔውን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ቢሆንም በአንድ ባሕሪ ሁሉንም መግለጽ ይቻላል። ይኸውም ሁሉም ‘ዘውጌ ይቅደም’ ሳይሆን ‘ኢትዮጵያዊነት ይቅደም’ መባል ነው ያለበት ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ በማንኛውም ሁኔታ የመገንጠል ጥያቄ መነሳት የለበትም ብለው ያምናሉ። ስለዚህ በነርሱ ብያኔ ‘ኢትዮጵያዊነት’ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚገኝ ‘ማንነት’ ነው ማለት ይቻላል። እንደነዚህ ልኂቃን ከሆነ፣ አንድ የኢትዮጵውያን ፖለቲካ ስብስብ ከአገረ-መንግሥቱ የምናገኘው ጥቅም ስለሌለ (ወይም እየመጡ በሔዱ ፖለቲካዊ ስርዓቶች እንጨቆናለን፣ በሀብታችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ አይደለንም፣ ወዘተ…) ስለዚህ ተገንጥለን የራሳችንን ዕድል እንወክላለን የሚል አቋም ማራመድ ሲጀምሩ ገና የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ንቅናቄ ልኂቃን ‘ኢትዮጵያዊነት’ን ከነዚህ የፖለቲካ ስብስብ አባላት ይነጥቃሉ፡፡ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ነጠቃው አንዳንዴ “በቀደሙት ስርዓተ መንግሥታት እኔ የምኮራበትን ያክል አልኮራችሁም” በሚል ሊሆንም ይችላል፡፡
‘ዘውጌኝነት’ ለ‘ኢትዮጵያዊነት’ ዘመዱ ወይስ ባዳ?
የዘውግ ንቅናቄ ሥር የሰደደ “ኢትዮጵያዊ” አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላል። ማመን ከምንፈልገው በላይ በታሪካችን ውስጥ በወንዝ እና በቀዬ መቧደን የተለመደ ነበር። እርግጥ በዋነኝነት አገሪቷ በሁለት ዐብይ ቡድኖች ተከፍላ ነበር – የገዢና የተገዢ መደብ በሚል። ገዢዎቹ በእያንዳንዱ አካባቢ የመንገሥ ዕድል ያለው ልዑል ለማፍራት ከየአካባቢው ገዢ ወይም ጦረኛ ልጅ ጋር በጋብቻ ይዛመዱ ነበር። ምክንያቱም የአካባቢው ተወላጅ ጋር ሳይዋለዱ በአካባቢው ቅቡልነት ማግኘት እንደማይችሉ ያውቁ ነበር። በጦር ጀግንነት መኳንንትነት ቢገኝም፣ ምስፍንና በውልደት ብቻ ነበር የሚገኘው። የቀድሞ ነገሥታት የጦር ጀግና ሲያምፅባቸው በጋብቻ ይዛመዱታል። ይህም ዘር እንደመሸለም ስለሆነ አመፅ ያስታግሳል። ይህ በዘር ላይ የነበረ ጥገኝነት የሚያስረዳን የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የተፈጠረው በዘውጌኛ አስተሳሰብ መሆኑን ነው። ሌላው ቀርቶ የቀድሞ ጸሐፍት እና ሊቃውንት ከሥማቸው ቀጥሎ “…ዘ ብሔረ ቡልጋ (ዘጌ)(ወዘተ)…” በሚል የትውልድ ቀበሌያቸውን መጥቀስ የተለመደ ነበር፡፡ የድሮው ዘውጌኝነት ከዛሬው ስርዓት ልዩነቱ አንድም የዘውጎቹ አረዳድ እና ባሕሪ ከዛሬው የሚለይ በመሆኑ (ማለትም በፊት ሸዋ፣ ጎጃም፣ አርሲ ወዘተ የነበሩት ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ… መባላቸው) እና፣ አንድም ደግሞ የዛሬው ስርዓት የዘውጌኝነቱን ችግር (define and rule እንዲሉ) እየተቸ በተግባር ግን ራሱን ከቀድሞው በበለጠ ያውም በሕግ የተወሰነ የዘውገኛ አደረጃጀት እና በአፈፃፀም ደግሞ የሚባባስ የዘውግ መድልዖ ውስጥ መዝፈቁ ነው።
ከኢትዮጵያ እና ከ‘ኢትዮጵያዊነት’ የቱ ይቀድማል?
ነገሥታቱ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አልፎ አልፎም ቢሆን ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጂ እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ ጠንካራ ፖለቲካዊ ኅልውና የነበራት አቢሲኒያ ነበረች። አቢሲኒያ መሠረቷ ክርስትና የሆነች አገረ መንግሥት ነበረች። ከዛሬይቱ የደቡብ፣ እና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነትም የጠነከረ አልነበረም። ደቡቡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደሰሜን በፍልሰት፣ ሰሜኑ (አቢሲኒያው) በ19ኛው ክፍለ ዘመን በጦር በማስገበር ሲቀላቀሉ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተፈጠረች። የዚህ ኢትዮጵያን በዛሬ መልክና ቁመቷ የመፍጠር የመጨረሻ ርምጃ የወሰዱት ዳግማዊ ምኒልክ ቢሆኑም፣ አገሪቱ በአዋጅ ኢትዮጵያ ተብላ የተጠራችው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ግዜ ነው። (እርግጥ ነው ዳግማዊ ምኒልክ “ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” የሚል ሐረግ ማኅተማቸው ላይ ስለነበር ያኔም ኦፊሴላዊ መጠሪያ ነበር ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡) የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ከተፈጠረ በኋላ፣ ኢትዮጵያም ኦፊሴላዊ ሥሟ ከሆነ በኋላ ነው ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለው ሐሳብ የተፈጠረው እንጂ በተቃራኒው አይደለም።
የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት መሥራቾች አቢሲኒያውያን እንደመሆናቸው፣ ኢትዮጵያን ከደቡቡ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያዊው የበለጠ መውደዳቸው አይገርምም። አሰባሳቢ ነው ከመባሉ በቀር ገና አግባቢ ትርጉም እና ተግባር ያልተገኘለት ‘ኢትዮጵያዊነት’ም ቢሆን አቢሲኒያውያን በራሳቸው ስሜት እና ግንዛቤ የፈጠሩት ንቅናቄ እንደመሆኑ ለነርሱ የበለጠ ቢስማማቸው አይገርምም። በተቃራኒው፣ የደቡብ እና የምሥራቅ ሕዝቦች ከአቢሲኒያውያን ተቃራኒ ስሜት ቢያንፀባርቁ ሊገርም አይገባም። ምንም እንኳ ብዙዎቹ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ አራማጆች ከዚህ ውጪ አማራጭ የለም የሚል አቋም ቢያራምዱም፣ “‘ኢትዮጵያዊነት’ የተባለው ማንነት ወይም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሁሉንም ካላስማማ፣ ኢትዮጵያ ያለኢትዮጵያዊነት መኖር ትችላለች ወይስ አትኖርም?” የሚለው ጥያቄ መከተል ይኖርበታል።
ከ‘ኢትዮጵያዊነት’ እና ከኢትዮጵያውያን የቱን እንምረጥ?
አሁን ‘ኢትዮጵያዊነት’ “በልካችን አልተሰፋም፤ ወይ እንደገና በልካችን ይሰፋልን አልያም አውልቀን እንጥለዋለን” የሚሉ ኢትዮጵያውያን መጥተዋል። በሕግ ‘ኢትዮጵያዊ’ የተባሉ በሙሉ ይህ በተለምዶ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚባለው የተለያዩ ፖለቲካዊ ትርጉም የሚሰጠው ማንነት እንዲሰማቸው የሚያስገድድ የሕግም፣ የሞራልም ግዴታ የለም፡፡ በሌላ በኩል ‘ኢትዮጵያዊነት’ ይቅደም የሚሉችን ‘ዘውጌ ይቅደም’ ከሚሉት የማበላለጡ መነባንባዊ እምነትም ውኃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ይልቁንም አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔ ይዞ መቅረብ የተሻለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ዘመኑ 21ኛው ክፍለዘመን ነው፡፡ መንግሥት ወይም ብዙኃን ወይም ልኂቃን የፈለጉትን ነገር ያገኙት ላይ ሁሉ በዘላቂነት መጫን አይችሉም፡፡ የአንድ ግለሰብም ቢሆን ልዩነቱ የሌሎችን መሠረታዊ መብት እስካልጣሰ ድረስ ይከበርለታል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ፌዴራላዊ ሆናለች፡፡ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ አራማጆች የሚጠቁሙት ሦስት ዋና-ዋና መፍትሔዎች (ሀ) ፌዴራሊዝሙን አፍርሶ ማዋሐድ፣ (ለ) የዘውግ ፌዴራሊዝሙን አፍርሶ በመልክአ ምድር ደግሞ ማዋቀር፣ (ሐ) ፌዴራሊዝሙን እንዳለ በማኖር የክልሎችን ሥልጣን (በተለይ የመገንጠል መብትን) መቀነስ ናቸው፡፡ የትኛውንም አማራጭ መፍትሔ መትከል ሕወሓት/ኢሕአዴግን ታግሎ ከመጣል በላይ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም መፍትሔው የሕዝብ ይሁንታን ማግኘት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደተለመደው የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ንቅናቄ አራማጆችም ይሁኑ የትኞቹም ከዚህ በፊት የታዩት ኃይሎች “ሁሉም ሕዝቦች ያቀረብነውን መፍትሔ ስለሚበጃቸው መቀበል አለባቸው” ባይ ቢሆኑም ሳይፈተኑ ተቀባይነት የሚያገኙበት ጀምበር ጠልቋል፡፡
‘ኢትዮጵያዊነት’ ለሶማሌ ተወላጆች፣ ለጋምቤላ ተወላጆች፣ ለአዲስ አበቤዎች እና ለሁሉም ዕኩል ስሜት፣ ዕኩል ዕድል እና ዕኩል ጥቅም እንዲሰጥ የሚያስችለው ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በባሕል፣ በመልክአ ምድር፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪክ የተለያየ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከላይ የጠቀስነው ‘ኢትዮጵያዊነት’ አብረው እንዲዘልቁ አይጋብዛቸውም፡፡ ሁነኛው መፍትሔ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ምቾት ሲባል፣ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የዜግነት መብቶችን በማክበር መርሕ ላይ እንዲመሠረት ማድረግ ነው፡፡ ይህ መርሕ መንግሥትና ሕዝብ፣ እንዲሁም አንዱ ወገን ከሌላው በጠመንጃ ቁራኛ በሚጠባበቁበት አፍሪካ ውስጥ ብቸኛው ልዩነትን አቻቻይ ተስፋ ሰጪ መርሕ ነው፡፡ የዜግነት መብቶችን ሙሉ በሙሉ ማክበር እና ማስከበር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትሕን ያመጣል፡፡ ፍትሕ ካለ ነጻነት፣ ዕኩልነት እና ወዳጅነትም ይኖራሉ፡፡
በፈቃዱ ኃይሉ
በለው! says
…ህወሓት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን መውደቅና መበታተን በመስመክ ከጫካው ማኒፌስቶ እስከ ከተማው ሕገመንግስት ድረስ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እራቁታቸውን እንዲጨፍሩ ያደረገ ተዓምረኛ ቡድን ነው።የሚሂድበትና የሚደርስበትን የማያውቁ ሁሉ የሄደበትን መሬት ሲጠርጉ፡ የተቀመጠበትን ወንበር ሲያደላደሉ፡ የቆመበትን ሁሉ ሐውልት ይሁን ሲሉ፡ ሲያስንጥሰው መሐረብ ሲያቀብሉ ያልተናገርውን ያለሰራውን ፈጠረው የሚያንቆለጳጵሱ እየታዘበ፡ እየለካ፡ እየገመገመ፡ አብዛኛውን አራግፎ ሌሎቹንም ሲያስረና ሲያሳድድ ብቻውን ያለተቃዋሚ ቆመ። … ** አሁን የአድርባይን አፍርስ፡ ሰርዝ፡ ደልዝ፡ቱማታ ተወና “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው ሲል” አዳሜ የውሸት እየተቃወመች በጥቅማጥቅም ታስራ፡ ትሰራና ትሠረስር የነበረች አውርቶ አደር ካድሬ፡ ጋዜጣ በል፡ ጣፊ፡ ጉዷ ፈላ …”ነጭ ልብስ ጋዜጠኛ አይለብስም! ነጭ ቀለም የምርኮኛ ነው!፡ በታክስ ከፋዩ(ጭቁን ሕዝብ ግብር) ፲ የኢትዮጵያ ከፍታ ቀን አይከበርም ጥቁር እለብሳልሁ”…ነጭ የባሕል ልብስ የሰሜኑ ሕዝብ ባሕል አይጫንብንም! …ኢትዮጵያ ፈርስት (ትቅደም!) የደርግ ነው! በ፳፩ኘው ክ/ዘመን ክልል/ሕዝቤ/ነገዴ እንጂ(የጋዜጠኛ፡ ፖለቲከኛ የፓርቲ ማንነት) እንጂ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም! የለም የሚሉ በውጭ ሀገር ዚግነት የተደበቁ፡ የካናዳ ዜግነታቸውን በኋላ ኪስ የደበቁ ኢትዮጵያ እስክትፈርስ የሚጠባበቁ እንደ ኢትዮጵያ ፈርስት ድረ ገጽ አዘጋጅ ቢኒያም ከበደ …በፍቃዱ ዘብሔረ ኅይሉ/ዘነበችም የግንቦት ፱(ዞን ዘጠኝ)ዜግነት ይዞ ማጓራት ጀመረ።
++መቼም ሴት ወልዶት ወንድ ባሳድገው አያምርም፡ ሴት ወልዷት ወንድ የሆነች የሐረር ወርቅ ጋሻውን ይላከበት!!
**ሌላው ህወአት/የኢአዴግ ድንቅ ሥራ..ይህ ቃሊቲ እሥር ቤት የሚልካቸው ሁሉ ሲወጡ ኢትዮጵያ ጠል እንዲህ መርዝ የበላች ውሻ ተላካፊ የሚሆኑት ለምን ይሆን!?…ታምራት ላይኔ፡ስዬ አብርሃ፡ ብርሃኑ ነጋ፡ብርቱካን ሚደቀሳ፡አብርሃ ደስታ፡በቀለ ገርባ፡ግንቦት ፱ (ዞን ፱) ለፍልፈው የገቡበትን ሲወጡ የቀባጠሩትን ማንበብና ማድመጥ ነው።
*በፍቃዱ ዘኅይሉ የመንዚቷ ልጅ…የብዙ ሚሽነሪስት መጽሐፍ ከማንበቡ የተነሳ ሲተርከው እንደውጭ ዜጋ ሆኖ ነው።
“ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” “ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!” “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!” “ኢትዮጵያዊነት መልካምነት!” “ኢትዮጵያ!” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ..የሐበሻ ቢራ ማስታወቂያ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለውን ቃል ማዕከል ያደረገ እና ስለኢትዮጵያ ‘ገናና ታሪክ’ የሚያወሳ ዓይነት ነው።ሌሎቹም ቢራዎች ተቀራራቢ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን ይዘው ብቅ-ብቅ ማለት ጀመረዋል። የቴሌቪዥን ትዕይንቶች፣ የግጥም ምሽቶች፣ ሌሎችም የጥበብ ሥራዎች ከመቼውም ግዜ በላይ ‘ኢትዮጵያዊነት’ን እያንቆለጳጰሱ ነው። በምላሹም ቀላል የማይባል ጭብጨባ ይቀበላሉ። እሱ እጅ ክሚቆርጡት ጎን ነበር አደለም እንዴ? ….ለመሆኑ የግለሰቡ ቅናትና ምቀኝነት እንዲህ የኢትዮጵያ ሥም መንቆለጳጰስ ዛሩን ቀስቀሶ ያንቀጠቀጠውና ያስጓራው ኢትዮጵያ ያለ«ኢትዮጵያዊነት» ልትኖር አትችልምን? ሊል የተቀባዠረበት ምኑን ቢረግጡት ነው !? ያው እንግዲህ ቃሊቲ የጋቱት ብሔርተኝነትና ልዩነት(ግንጠላ) ነዋ!
** ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ላይ ሕዝብ ካለ፡ የሚለብሰው የራሱ ፈጠራ ልብስ፡ የራሱ አመራረት፡ አዘገጃጀትና አመጋገብ ካለው፡ የራሱ ቀን ቀመር በራሱ መግባቢያ ቋንቋ ካለው፡ የራሱ ግዛት ሰንደቅና መንግስት ካለው ዛሬ አርግዘው ሄደው ከሚወልዱበት ሀገር፡ ተስለውና ለምነው ዜግነት በምራጫ ከሚሰጣቸው ከሌላው ሀገርና ዜግነት ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንደምን ያንሳል? ዜጋ የሌለው ሀገር ከምድር ውጭ ሌላ ጠፈር ወይንም ሀገር የሌለው ሰው ዜግነት አልባ፡ የኮንቴነር ውስጥ ነዋሪ (ጂብሲ)..ኤሊያንስ መሆኑ ነው።የህወሓት/ኢህአዴግ ማኒፌስቶ (ሕገ መንግሥቱ) በመግቢያው “የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክአ ምድር አሰፋፈር የነበረን እና ያለን…” በማለት የዘውግ ቡድኖች የተለያየን መሆናችንን ካስታወሰን በኋላ፣ የሚያስተሳስረን ቁሳዊ ጥቅም ብቻ መሆኑን ሲነግረን ደግሞ “አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ለመገንባት” የሚል ቃልኪዳን በብሔር ብሔረሰቦች መሐል መደረጉን ይነግረናል።”… የዘውግ ቡድኖች የተለያዩት አበላል ላይ እንጂ ኢትዮጵያን ለመበላት በጋራ ነበር…አንድ የጋራ ኢኮኖሚ የሚገነቡ ወሮ በሎች አንዱ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ መር ዘውገኛ ሲሆን ሌላው እስታዲየምና ቢራ ፋብሪካ ከፈቶ አፉን ከፈቶ አይቀርም በእርግጥ እናንተም የብልጥ ዕቃ ይወድቃል ብላችሁ ኢትዮጵያ ትቅደምን ነቅፋችሁ፡ ኢትዮጵያ ትውደም ደስ ብሏችሁ ነበር፡ አሁን የኢትዮጵያ ከፍታ ሲነሳ እናንተ ወደቃችሁ!?”የቷ ኢትዮጵያ? የምን ኢትዮጵያ? አለ ዶ/ር በያን አሶባ….ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም!አለ ጸጋዬ እረጋሳ…ዘበፍቄ
…*ከኢትዮጵያ እና ከ‘ኢትዮጵያዊነት’ የቱ ይቀድማል?”ከ‘ኢትዮጵያዊነት’እና ከኢትዮጵያውያን የቱን እንምረጥ?
__ እምዬ ቃሊቲ ..ኢትዮጵያ ሀገር…ኢትዮጵያዊነት(ዊ/ት) ዜግነት መሆኑ ቀረ ማለት ነው!? ይህ እራስ ገዝ፡ ክልል(ጋጣ)ሀገር ሆነ ማለት ነው። ለነገሩ ተስፋዬ ግብረእባብ ገዳ ሆኖ የለምን? ደቡቡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደሰሜን በፍልሰት፣ ሰሜኑ (አቢሲኒያው) በ19ኛው ክፍለ ዘመን በጦር በማስገበር ሲቀላቀሉ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተፈጠረች። ..‘ኢትዮጵያዊነት’ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ነገር ነው፡፡ በተለይ በብዙኃኑ እና በልኂቁ መካከል የተለያየ ነገር ነው፡፡ በብዙኃኑ ዓይን ‘ኢትዮጵያዊነት’ ሲባል የሚመጣባቸው ቀደምት የሥልጣኔ ምንጭነት (ለምሳሌ አኵሱም)፣ አኩሪ የትውፊት ባለቤትነት (ለምሳሌ ገዳ)፣ የጀግንነት እና ነጻነት ምሳሌ (ለምሳሌ አድዋ)፣ ሃይማኖታዊ ባለታሪክነት (ለምሳሌ የክርስትና እና የእስልምና ወደአገር ቤት አገባብ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መከባበራቸው) እና የመሳሰሉት ናቸው ትዝ የሚሏቸው፡፡ ይህ ግን እያደገ የመጣውን እና ልኂቃኑን የሚወክለውን ‘ኢትዮጵያዊነት’ የተሰኘ የፖለቲካ ንቅናቄ አይወክልም፡፡” ሊሂቃን ተብዬዎቹ እነማን ናቸው? ጃዋር?ጂነዲን? ተስፋዬ ግብረእባብ?ጸጋዬ አራናሳ? ህወአት/ኢህአዴ ሲቪል ሰርቪስ ጥርብ ድንጋዮች? ድንቄም! ይህ እንኳን አብሮ ሊያኖር አብሮ ኳስ የማያጫወት ጎጠኛ ሥርዓት የተወተፉ አድርባይ ምሁራን ይሆኑ?
*** ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማንቆለጳጰስ ሃጥያት የሆነው፡ ልዩነት እንዲሰበክ ሀገር እንድትፈርስ ጋዜጠኞች ሌት ተቀን የሚቀበቀቡት እውነታው ለውጭው ስደተኛ/ፈላሽ፡ ዲያስፐር ልሂቃን ሹምባሽ፡ የፖለቲካ ተንታኞችና በታኞች ልዩ ኢትዮጵያዊነት ለመፍጠር ሲባል ሲሞጣሞጡ ነው፡፡ ድሃው ወጣት ንብረት እንዲያወድም…እንዲታሰር፡ እንዲገደል፡ ከውስጥም ከውጭም እንዴት እንደተበተብን በፍቃዱ ዘብሔረ ኅይሉ ኢትዮጵያን እንጂ ኢትዮጵያዊነትን አትቀበሉ ይለናል።”ጉድ በል! ሰላሌ ኢትዮጵያዊ አደለህም ተባልክ” አለ አቤ ቶክቻው።