እ.ኤ.አ. ቅዳሜ ኖቬምበር 02, 2013 ዓ.ም. በጀርመን ሚዩኒክ ከተማ ወያኔ ሊያደርግ ያሰበው የአባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች በተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ሊከሽፍ ችሏል።
ከዚህ በፊት በጀርመን ፍራንክፈርት ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች እክል የገጠመው የወያኔ የቦንድ ሽያጭ ኮሚቴ አካሄዱን በመቀየር የቦንድ ሽያጩ ይጀመራል ተብሎ ከታሰበበት ጊዜ ሶስት ሰዓት ያህል በማዘግየት ለተቃውሞ የመጡትን ሰዎች ተስፋ ለማስቆረጥ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ከመቅረቱም በላይ በወቅቱ በነበረው ቅዝቃዜና ብርድ ሳይበገሩ የፕሮግራሙን መጀመር በትዕግስት በቅርብ ርቀት የተከታተሉት እነዚህ ተቃዋሚዎች የመግቢያ ትኬት ሽያጭ ሲጀመር በአንድ ጊዜ ቁጥራቸው ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ የኦነግ አባላት፣የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አባላት፣የኢህአፓ አባላት፣የ‘‘ድምፃችን ይሰማ‘‘ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የፖለቲካና ሲቪክ ማህበር አስተባባሪነት በር ላይ የነበሩ የወያኔ የደህንነት ሰዎችን በመጣስ ወደ አዳራሹ የገቡ ሲሆን በወቅቱ የመግቢያው በር ላይ በተፈፀመ ግርግር የሚዩኒክ ፖሊሶች በስፍራው በመገኘት የወያኔ ደህንነቶችን ከመደብደብ ታድገዋል።
በአዳራሹ ውስጥ ለገቢ ማሰባሰቢያ በሚል ተዘጋጅቶ የነበረ ምግብ እንዲሁም ከለስላሳ መጠጦች እስከተለያዩ ዊስኪዎችና ቮድካዎች የነበሩ ሲሆን ተቃዋሚዎቹ ‘‘የሀገራችን ንብረት ነው‘‘ በማለት ከምግቡም ከመጠጡም በመቋደስ ወያኔ በተከራየው አዳራሽ ውስጥ ለሁለት ሰዓታት ያህል በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ በተለይም በዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው አፈናና እንግልት፣የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣የእምነት ነፃነት አለመከበርና በመሳሰሉት ላይ ውይይት በማካሄድ እንዲሁም ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ እየፈፀመ የሚገኘውን አፈናና የግፍ አገዛዝ በአባይ ግድብ እና በልማት ስም ለመሸፈን የሚያደርገውን መሠሪ ተግባር በማውገዝ ተጠናቋል።
(በየነ መስፍን ከጀርመን)
Leave a Reply