… ቋንጣ ዜና አመጣሽ አትበሉኝና፤ ሰሞኑን ከፌስቡክ ጠፍቼ በከረምኩበት ወቅት የአራት አመት ከስድስት ወር ልጅ የደፈረው ዋልጌ በአራት ወር “ሲቀጣ”፣ ምስር ወጥ የሰረቀው ሰው ደግሞ አመት ከአራት ወር እስር ተፈርዶበታል ሲባል ሰምቼ በንዴት ስንተከተክ ከርምኩ፡፡
ከዚያ ደግሞ እነ አብርሃ ደስታ ሲፈቱ በደስታ ተፍነከነኩ፡፡
…ልጅ ሆኜ እናቴ ሰው ቤት ይዛኝ ሄዳ ለየኔ ቢጤ ምግብ ለመስጠት የሚሰስት ሰው ስታይ፤ “አበስኩ ገበርኩ…!ደግሞ ለሞተ…ለበሰለ ምግብ መስቆንቆን ምንድነው!” ትል ነበር፡፡
እነሆ ፍትሃችን፣
“የበሰለ” እና “የሞተ” ምግብ ለሰረቀው ሰውዬ ፣ አመት ከአራት ወር!
“ያልበሰለች” እና “ታዳጊ” ልጅ ለደፈረው ሰውዬ፣ አራት ወር ሆኗል፡፡
እነሆ ፍትሃችን፣
እንዲህ እንዲህ የሌሎችን መብት ግጥም አደርጎ የሚጥስን ማበረታቻ በሚመስል የአራት ወር “ቅጣት” ሲያልፍ ፤ ለሌሎች መብት የሚታገልና የራሱን መብት የሚጠይቅን ደግሞ ለአመታት በእስር ያማቅቃል፡፡
እነሆ ፍትሃችን፣
ደስ ባለው ሰአት፣ ነፃነትን “አምጣ” ብሎ ቀምቶ ፣ ደስ ባለው ሰአት መልሶ “እንካችሁ” ይላል፡፡
ቢሆንም ቢሆንም፣ በእነ አብርሃ ደስታ መፈታት ተደስተናል፡፡
በሰበብ- አስባብ አስሮ ያለ ለምክንያት መፍታት እንደ ዲሞክራሲያዊነት መገለጫ ተቆጥሮ የሚደረግብን ዘመቻ ግን እጅጉን አድክሞናል፡፡
ሰሞኑ የቡሄ ነው፡፡ እናውቃለን፡፡
…. ግን እባካችሁ እንደ ጅራፍ ራሳችሁ እየገረፋችሁ ራሳችሁ አትጩሁብን!
Leave a Reply