መቼም ሰው ይናገራል። እኔ ደግሞ ጆሮ ፈጥሮብኛልና እሰማለሁ። የምሰማውና የማዳምጠው ግን ይለያያል።
ባለፈው ሰሞን ቁጥር 00 ሰውዬ ሲናገሩ ሰማሁ፣ “የዛሬ አሥር አመት ከ80 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ እናስይዛለን” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ።
እና አዳመጥኩ፣ “የዛሬ አሥር አመት ከ80 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ እናስይዛለን፣ ምክንያቱም አሁን እየቀጠርናቸው ያለነው ቻይናውያን፣ ህንዳውያን፣ ብራዚላውያን፣ ወዘተርፈዋውያን . . . የዛሬ አሥር አመት ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ፣ በቁጥርም ከ 80 ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ” ብዬ አዳመጥኩ።
ያገሬ ህዝብ ደግሞ የቀን ሥራ እንኳን ሳይቀር እየተቀማ ለቻይና ሲሰጥበት፣ ተግቶ ይጸልያል። “የባሰ አታምጣ” እያለ። እኔ ደግሞ አዳምጣለሁ፣
“የባሰ አታምጣ”ን መሥማት ደከመኝ
“የተሻለ አምጣ” የሚል ናፈቀኝ” ብዬ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ። እኔም አዳመጥኩ። በጫወታዬ ላይ ቁጥር ከ 00 በላይ መቁጠርም ሞክራለሁ። ግን የሚናገሩት ተመሳሳይ ስለሆነ መለየት ቸግሮኝ ነው አንድ አይነት ቁጥር የሰጠኋቸው። እና ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ። “እኛ ስለእድገታችን ስንተነብይ ቁጥሩን ለጥጠን ተናግረናል። አሁንም ቢሆን ለጥጠን እንናገራለን።” ሲሉ ተሰማ።
እኔም ደግሞ “አዎን ለጥጠን እንናገራለን። ቃም፣ ቃም አርገን መርቀን ሥንል በጎ፣ ከፍ፣ ከፍ ያለ ቁጥር ብንመኝ ምናለበት? ቢሳካ ባይሳካ ምን ችግር አለው? ማን ይጠይቀናል?” ብዬ አዳመጥኩ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ፣ “ቻይናዎች አውሮፕላኑ የነሱ እንደሆነ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። የነሱን ዜጋም የቀጠርነው ለዚህ ነው።”
እኔም “ከቻይናው ባንክ በወለድ የተበደርነውን መክፈል ባለመቻላችን በሰሊጥ፣ በኑግና በሌሎችም ጥሬ ምርቶች ከፍለን፣ ከፍለን፣ ከፍለን፣ እዳው አላለቀም። እንግዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እየሸራረፈን፣ ለምሳሌ የነሱን ዜጋ በመቅጠር አይነት ለመክፈል አስበን ነው” ብዬ ለማዳመጥ እየከጀልኩ ነው።
ጌቱ ኃይሉ የጸሃዮቹ (http://tsehayochu.com/)መጽሃፍ ደራሲ ነው።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply