እንግዲህ ያረጀ የአመፅ ታሪክ ከመድገም፤ ከውጭ አገር መፍትሔ ከመኮረጅና፤ እልከኛና አንገተ ደንዳና ሆነን ለአዲሱ ጤናማ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የማንመች ከመሆን ይጠብቀን።
በአይነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነውንና የኛው በኛው ለኛው ሆኖ የሚያኮራንን አዲስ የእርቅና የመግባባት ስሌትን መፍጠር እንችላለን የሚል አስተሳሰብ ይኑረን። እንቆቅልሻችንን እንፍታና የአገር ልጅነት ግዴታችንን በታማኝነት እንወጣ። በተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተከፋፈልን ህዝብ ብንሆንም፦ ጥላቻና ንቀትን አስወግደን፤ ሁለቱም ጎራ (መንግስትና ተቃዋሚ) በጡንቻ መጠቀምን እንደ ኋላቀርነት ለመቁጠር የሚያስችል ብስለትና ድፍረት ይታይብን።
በብዙ የተለያየ ባህልና ቋንቋ የበለፀግን ህዝብ ነን። የምንከባበርበትና በእኩልነት የምንተያይባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በልዩነታችን እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን ለመገንባት እንድንችል ትህትናና ፍቅር ይብዛልን። በእርቅና በመግባባት ጥበብ ፈውስን ለምድራችን ማምጣት እንችላለን የሚል አመለካከት ምርጫችን ይሁን። ከልብ ተሳስረን እውነተኛውን ማንነታችንን እንድናውቅና እንድንለማመድ በአዲስ መንፈስ ዛሬ እንነሳ።
የተለያየ ሀይማኖት የምንከተል ህዝብ ብንሆንም አንዳችን የሌላኛውን ሀይማኖት የምናከብር ህዝብ ነን። ከዚህም ባለፈ መልኩ ሁላችንም የሁላችንም የሆነችውን ኢትዮጵያን ፈጣሪ እንዲባርካት የዘወትር ፀሎታችን ይሁንልን። የኢትዮጵያም አምላክ ተአምር ሊያሳየን ይቻለዋል የሚል ግንዛቤ ያቀራርበናል ደግሞም ተስፋችንን ያለመልማል።
በፊታችን ያለውን የአዲስ ዓመት ጉዞ በቀና አስተሳሰብ እንጀምር። ይቻላል እንበል። ዋጋ ያስከፍላል እንጂ የማይቻል ነገር የለምና። ወደ ልባችን እንመለስና በይቅርታ ሌላውን ለመድረስ እንዘርጋ። አስተዋዩና ታጋሹ ፍቅር በምድራችን እንዲያሸንፍ እንፍቀድለት! እባክዎን ስለ እርቅ የተዘጋጀውን ባለ አምስት ነጥብ ብቻ የዳሰሳ ጥናት ወደዚህ ድህረ ገፅ በመሄድ ይሳተፉ።
dereje says
እዚህ ፎቶ ላይ የምናያቸው ልጆች ሙሉ በሙሉ የሀበሻ መልክ አላቸው። እንግዴህ እነዚህን ልጆች ምናቸውን አይተንና ለይተን ነው? አንቺ ኦሮሞ ነሽ፤ አንቺ ትግሬ ነሽ ፣እንቺ አማራ ነሽ ፣አንቺ አፋር ነሽ……ወዘተ የምንላቸው? ሁሉም እኮ ሀበሾች ጥቁሮች ናቸው። ሁሉም እኮ የድሀ ልጆች ናቸው። ሁሉም ድሀ ሆኖ እኛ ወርቅ ነን ሌላው አናሳ ነው ከተባባልን ከዝንጀሮ ቆንጆ የሚሉት ተረት ሊመጣ ነው። ዋነኛው ጠላታችን እኮ ድህነት ነው።ጎሣን የሚወስነው እኮ ያደግንበት አካባቢ እንጂ ወላጅ አይደለም። ይህ እውነት ደግሞ አቶ መለስ ካሉት ” ጎሣ ወይም ዘር በአባት ይወሰናል” ካሉት አባባል ጋር ይጋጫል። ከእውነት ጋር የሚጋጭ ደግሞ ራሱ ይስበራል እንጂ እውነትን ሊቀይራት አይችልም። ለዛም ነው ከእውነት ጋር የተጋጨው የኢህአድግ የዘረኝነት አካሄድ ህዝቦችን እያጋጨ ያለው። እናም ኢህእዲግ ይህ አካሄዱ ትክክል ስላይደለ ይህ አካሄዱን ትቶ ክሌሎች ጋር ቢማከር አገራችን ውጤታማ ትሆናለች።