
አልሸባብ ጋልሙዱግ በሚባል ክልል ከሶማሌ ጦር ጋር ባደረገው ውጊያ ሶስት የሶማሊያ ጦር ካምፖችን በቁጥጥሩ ስር አድርጓል።
አል ሸባብ ከሶማሊያ ጦር ጋር አምስት ሰዓታት ያህል የቆየ ከባድ ጦርነት ካካሄደ በኋላ ከጥቃቱ የተረፉ የሶማሌ ብሄራዊ ጦር የ”ጎርጎር ኮማንዶ” መኮንኖችና ወታደሮች እንደተናገሩት በውጊያው ከ230 በላይ የሶማሊያ ወታደሮች መሞታቸውን እንዳረጋገጡና ስፍር ቁጥር የሌላቸው መቁሰላቸውን ገልፀዋል።
የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር በቦታው ያሰፈራቸው ወታደሮቹ 4 ሻለቃ የ”ጎርጎር ኮማንዶዎችን” ሲሆን 15 የአል ሸባብ አሸባሪዎች ጋር ባደረገው ውጊያ ከፍተኛ ሞትና የአካል ጉዳት አስተናግዷል።
የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር በአል ሸባብ ከበባ ውስጥ ሆኖ ምንም ዓይነት የሽፋን ኃይል ማሰማራት አልተቻለውም ተብሏል።
ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ በአል ሸባብ የሽብር ቡድን ላይ ዘመቻ ጀምሬያለሁ ካሉበት የቅርብ ጊዜ መግለጫቸው ወዲህ ብቻ የተገደሉ ወታደሮች ቁጥር ከ 4,000 በላይ ሲደርስ ከ300 በላይ የሶማሊያ ጦር አዛዦችም በሽብር ቡድኑ መገደላቸውን ዘገባዎች አስታውሰዋል። (Esleman Abay)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች የሚባለው እንዲህ ያለው ነገር ሲከሰት ነው። የመቋዲሾው መሪ ኢትዮጵያ ጋር ለመግጠም ተዘጋጅተናል ይላል። ጥቁሩ ዓለም ጨለማ ሃሳቢ ነው። የአረብና የነጭ መንጋ ወደባቸውን ሲወር ትንፋሽ ያላሰሙት አሁን እንሆ ገና ላም አለኝ በሰማይ ወሬ ከወደ አዲስ አበባና ከሃርጌሳ ተሰማ ተብሎ ይህን ያህል መፎከር ምን የሚሉት እብደት ነው። ሱማሊያ ሃገር መሆኗ የቀረው በ 1991 ነው። ያው የአፍሪቃ መከራ ሁሌ የሚታከከው የቅኝ ግዛት ወሰንን ተከትሎ ሌላውን ገመና እየደረበ በመሆኑ በእንግሊዞች ስር የቆየችው ሶማሊላንድ ከቀረው የሱማሊያ ክፍል ተለይቼ ሃገር ሆኛለሁ ካለች ዘመናት አለፉ። በእነዚህ አስርተ አመታት መልካም ነው በሚባል ደረጃ ቁራሿን ሃገር አስተዳድረዋል። እያስተዳደሩም ይገኛሉ። እርግጥ ነው ሃገርነታቸውን ሌሎች ሃገሮች አልተቀበሉትም። እንደ እውነቱ ከሆነ የዓለም ፓለቲካ ገጣባ ነው እንጂ የሱማሊላንድ ጥያቄ ከኤርትራው ጥያቄ የሚለይ አይደለም።
ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁ በማለት የያንየው እብድ ሲያድ ባሬ ኢትዮጵያን ወሮ ብዙ እልቂት እንደ ደረሰ ሁሉ አሁንም እንደ ግብጽና ሌሎች የነጭ እቃ ተሸካሚና ተላላኪ ሃገሮች የሱማሊያና የኢትዮጵያን ግጭት ይፈልጉታል። ለዚህ ነው ቱርክ ኢትዮጵያንም ሱማሊያንም የምታስታጥቀው። እሳቱን በጋራ ይሙቁት በለው ነው። ጥቁር እንደ ቅጠል ሲረግፍ ደስ ይላቸዋል። ግን ይህ ብቻ አይደለም የግብጽ መንግስት ድንፋታ የኤርትራው መሪና የመቋድሾው መሪ የካይሮ ቆይታ ሁሉ ለጥቁር ህዝቦች ያሰበ ሳይሆን ለራስ ጥቅም ነው። የአረቡ ራቢጣ ኢትዮጵያን እንደ እሳት ነው የሚፈራው። በመሆኑም መቋዲሾን ደግፎ መግለጫ መስጠቱ የሚጠበቅ ነው። ልብ ላለው ግን ሱማሊያ እንድትበታተን፤ ዛሬ እነ አል ሸባብና ሌሎች በውጭና በሱማሊያ ውስጥ አክራሪ የእስልምና እይታ እንዲይዙ ያደረጉት ከአረብ ሃገር የሚመነጨው የእስልምና ትምህርት ነው። በሃይማኖት አክራሪዎች የተነሳ የስንቱ ቤት ፈረሰ? የስንቱ ሃገር ተፍረከረከ? ቤቱ ይቁጠረው። የእምነት አክራሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዪች ብቻ አይደሉም። ስመ ክርስቲያኖችንም ይጨምራል።
በቅርቡ የሚኒሴቷዋ የሶማሊያ ተወላጅ የኮንግረስ ተወካይ ከአሜሪካ ይልቅ ሶማሊያን አስቀድማ መናገሯ ምን ያህል የትሮጃን ፈረሶች አሜሪካን እንደ ወረራት ያሳያል። እንደ እኔ ቢሆን ያላትን ሁሉ ሰብስቦ፤ ከነ ነጭ ባሏ መቋድሾ ማድረስ ነበር። ምን አልባትም ሸረኛውና ዘረኛው ዶላንድ ትራምፕ ከተመረጠ ልትሸኝ ትችል ይሆናል። ይህ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ተወሽቆ ሳይመርጡ መለፍለፍ መከራን ያመጣል።
ባጭሩ የመቋድሾው መንግስት በቋፍ ላይ ያለ፤ በተመድ ወታደሮች የኢትዮጵያን ጨምሮ በድጋፍ የቆመ በመሆኑ ኢትዮጵያን የመውጋት አንድም አቅም አይኖረውም። ይህ ሲባል ግን በዚህም በዚያም ተወንጫፊ ከአረብና ከነጩ አለም እየሰበሰበ ሃገር አያተራምስም ማለት ግን አይደለም። ግብጽ ለሶማሊያ አንድነት አብራ እንደምትዋጋ አስታውቃለች። ጥሩ ነው ይምጡ። ድሮስ እነ አሉላ አባነጋ ቂጥ ቂጣቸውን ብለው አይደል ከኤርትራ መሬት ያባረሯቸው? ግን ዛሬ ያን ታሪክ ማን ወደ ኋላ ተመልሶ ያየዋል። በዘሩና በቋንቋው ሰክሮ ይወላገዳል እንጂ! እውነተኛ የፓለቲካ ሰው፤ አፍሪቃዊ፤ ኢትዮጵያዊ መጠየቅ ያለበት ግን UAE ወደቡን ተረክባ ስታስተዳደር፤ ጅቡቲ ለፈረንሳይ ለቻይና ለአሜሪካ ወዘተ ወደብ ሲፈቅድ ለምን ያኔ የተቃዋሚ ድምጽ አልበረከተም? መልሱ የአረቡና የነጩ ዓለም ጥላቻ በኢትዮጵያ ላይ በመሆኑ ነው። ይህ አልገባኝም የሚል ወያኔ 3 ጊዜ ወረራ ሲያደርግ ከላይና ከሥር ጦርነቱን በይፋ ይመሩት የነበሩት አሜሪካኖች ናቸው። እናስብ ስንት ብልሃት ተጠቀሙ ሰውንና አመራሩን ለማስበርገግ? ስንት ጊዜ ተመድ በትግራይ ጉዳይ ተሰበሰበ ትዝ ይበለን። ጠላቶቻችን እልፍ ናቸው። የኢትዮጵያን ል ዕልና ያኔም ዛሬም አይፈልጉትም። እነርሱ የሚፈልጉት እቃ ተሸካሚና ተላላኪ መንግስት ነው። ወያኔ በዚህ በኩል የተሳካለት ባለ ሁለት የፊት ገጽታ ባለቤት ነበር። ለሃገርና ለውጭ ዓለም የሚያሳየው መልኩ ለየቅል ነበር። ግን ሁሉ ነበር ሆነ። ኢትዪጵያ መተንፈሻ ወደብ በግድም በውድም መፈለጓ ምርጫ ሳይሆን የግድ ነው። በቃኝ!