ደራሲ፤ አቢይ አበበ (ሌ/ጄኔራል)
ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ
ዓለም ገና ልጅ ናት አውራጃዋም ደግሞ
አርጅቶ የሚሞተው ሰው ብቻ ነው ቀድሞ
ብዙ አሳልፋለች ብዙዎች ተክታ
የሁሉንም ምግባር በየተራው አይታ። ሌ/ጄ አቢይ አበበ
እንዲህ ሆነ፤
ርዕሱን አነበብኩና ደራሲውን ስመለከት ሌተናንት ጄኔራል ይላል። የህትመት ዘመኑ ደግሞ 1955 ዓ/ም። ባለሁበት ዘመን ውስጥ ሆኜ ሳሰላው እንግዲህ መፅሀፉ ከታተመ ግማሽ ምዕተ ዓመት አልፎታል። ህትመቱስ? አስቀድሞ አሥመራ በ”ኢል ፖሊግራፊኮ ሶ. አ” ማተሚያ ቤት የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር ኤርትራ ዋና ከተማ ሲሆን እርግጥ ከ12 ዓመት በሁዋላ በ1967 ዓ/ም (ዘመነ ፅልመት) አዲስ አበባ በቼምበር ማተሚያ ቤት በድጋሚ ታትሟል። ስለምን ዘመነ ፅልመት አልነው 1967 ዓመተ ምህረትን? አንባቢ ቅኝቱን አስጀምሮ ካስጨረሰህ ምላሹን ታገኘዋለህ።
ይዘቱስ? እዚህ ላይ ነው “ጉድ እዩ!” ያልነው። (እንደ ትግሪኛ ካነበብከው “ጉድ ነው” ማለት ሲሆን፤ እንደ አማርኛው ደግሞ “ጉድ ተመልከቱ” ማለት ይሆናል።) አጀብ ቋንቋችን ማማሩ። “መፅሀፍን በሽፋኑ አትመዝነው” ያለው ማን ነበር? ደራሲንስ በስሙ በማዕረጉ ሳይሆን በድርሰቱ ጭብጥ ብቻ መፈረጅ አይገባምን?
“አውቀን እንታረም”ን ስለምን እንደፃፈው ጄኔራሉ ካወረድልን ቃል የሚከተለውን ያገኟል፤ መተዛዘንን፤ መተሳሰብን፤ ጠንካራ መንፈስን፤ ቅን ባህሪይን፤ ፍቅርን እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል። ይህም በመኻላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም። ወደ መጥፎ መንፈስ የሚመራ ሁሉ መጥፎ ነገሮችን እያራባ ሌላውን ሁሉ ከትቦ እንዳይጎዳ ያስፈልጋልና በኑሮ ውስጥ ምን ምን እንዳሉ ተረድቶ ከአሁኑ መገታት ያስፈልግ ይመስለኛል።
በአጭሩ ከገለጥኩት በሁዋላ አስፋፍቶ ማተቱን የሚመለከተው የአንባቢዎች አእምሮ እንደሚሆን በማመን፤ ለመልካም ሥራ ይውል እንደሆን በማለት ተስፋ ይህን ትንሽ መፅሀፍ ለውድ ሀገሬ ሰዎች አበረክታለሁ – ይላል ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ። ቀልብን ማራኪ፤ አእምሮን ቆንጣጭ ጅማሮ ይሏል እንዲህ ነው።
እና እንግዲህ ሌተናንት ጄኔራሉ በሠይፍ ወይ ደግሞ በጥይት ሳይሆን በሰላ ብዕሩ ማረከኝ፤ ገና በጠዋቱ ከፍልሚያው አምባ ዘልቄ እንኳን ሳልገባ አንዲት ቅጠል እንደቀረደድኩ። ጠሊቅ ሀሳቡ፤ አመራማሪና ኮርኳሪ ምልከታው በዘመን ተወልዶ በዘመን የሚሞት ሳይሆን ዘመን የሚሻገር ትውልዶችን እሚያናግር ሆነና በተለይ ደግሞ አሁን ላይ እምገኝበትን ዘመኔን እንድፈትሽ ቀፍድዶ ያዘኝ። እኔነቴን እንድከልስ እንድጠይቅ እንድመዝን አካባቢዬን እንድቃኝ። አወዳደቄን እንዳስተውለው ወይም ከመውደቅ እንድድን። እና ብዕሬን አነሳሁ። እነሆ የሆነው ይኸው ነው። ከዚህ በሁዋላ ያለው ያው “ታሪክ ነው” አይደል እሚባለው? ደግሞስ ቢሆን ጠቢቡ ወታደር የመፅሀፉን ቃል ‘አስፋፍቶ ማተቱ የአንባቢ ሥራ ነው’ አይደል ያለው? ከሆነ “ራስ ወለድ” በሆኑ ንዑስ ርዕሳን ‘ቅኝቱን’ እንዲህ አደራጅተነዋልና እንግዲህ እንቀባበል . . .
ሰው ሆይ!
ፍልስፍናን በተላበሰ አገላለፅ ስለ ሰው ሰብዕና ፤ ስለህሊና ፤ በምድር ቆይታው ሰው ራሱን በመሆንና ራሱን በመሸሸግ ስለሚኖረው ተቃርኖ ጥቂት በማይባሉ ገፆች ቋጥኝ የአስተሳሰብ ዘርፎች አስቀምጧል – ጠቢቡ ወታደር። ጥቅልና ጥልቅ የሆኑትን አገላለፆች ሁሉ የመተንተን የቅኝታችን አቅሙም ሆነ ግቡ አይደለም። እንዲያም ቢሆን ቅሉ፤ የተወሰኑትን ግና እየነቀስን እና ከዘመናችን ጋር እያዋደድን እናወርዳለን።
ጠቢቡ ወታደር እንዲህ ይላል፤ አንዳንድ ጊዜ ሁሉን ሳመዛዝን ሳወጣ ሳወርድ እዚህ ምን አደርጋለሁ እስከመቼስ አለሁበት እቆያለሁ? ጨረቃና ፀሀይ ሲፈራረቁ ማየት የሰው ልጅ ሁሉ ወግ ነው። ዛሬን አስመሽቼ ነገን ማንጋቴን አላውቅም። በዚህ ምክንያት ብተክዝና ያለኝን ጊዜ ንቄ ባሳልፈው አይሻለኝምን? እላለሁ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ለምን እተክዛለሁ፤ በአለሁበት ዓለም እምኖረው ለአጭር ጊዜ ነው። ስለምን ደስ ብሎኝ አላሳልፈውም? ለምንስ እንደሌላው ሁሉ አልሆንም! . . . ሌላው የሚያደርገውን ሁሉ ለማድረግ እኔም ይቻለኛል። ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም። የኔም ዕድል በግድ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው እያልኩ አስባለሁ – ይለናል።
እነሆ ይህንን የመሰለ መጨበጫው የረቀቀና በእዝነ ህሊና ምልከታው የመጠቀ ሀሳብ ያሰፈረው ጠቢቡ ወታደር ስለዚህች ዓለም፤ ስለ ሰው ልጅ፤ ስለ ህሊናና ስለ ህይወት ተልዕኮ ከድምሩ ህብረተሰብ ያፈነገጠ ዕይታ እንዳለው በገሀድ ያሳያል። እንዲህ የመሳሰሉትን ረቂቅ እሳቤዎችን የሚያባዝቱ በአብዛኛው በቀድሞው የሩቅ ዘመን ውስጥ የኖሩ ፈላስፎችና ተመራማሪዎች ሲሆኑ፤ በዘመናችን ደግሞ ምናልባት ጥቂት ፈላስፋዊ ነፍስ ያላቸው /ጠቢባዊ አስተሳሰባቸው የተመነደገ – በዊዝደም የተሞላ/ እና ምናልባትም ደግሞ ጥቂት ነፍሳቸው ከጥበብ ህዋ የተጣለ፤ የሰጠመ የጥበብ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ የትኛውን ነፍስ ይሆን ይዞ የነበረው? ጠቢቡ ወታደር በቁሳዊ ህይወቱ የተመነደገ ኑሮን መኖር የሚችል ሆኖ ሳለ በእንዲህ ያሉ ነፍስ ሞጋች መጠይቆች ስለምን ሲብሰለሰል ኖረ? አቢይ አበበን የሚያስጨንቀውና እንቅልፍ የሚነሳው ምን ነበር? ማለታችን መቼም አይቀርም። ለዚህ ምላሽ የቅኝታችን አንደምታ ሲጠቃለል ፍንትው ይላልና ወደዛው የሚያመራንን ፍተሻ እንቀጥላለን።
የተፈጠርኩት ጨረቃና ፀሀይ ሲፈራረቁ፤ ክረምትና በጋ፤ ፀደይና በልግ ሲወጡና ሲገቡ ለማየት፤ ዕድሜ ለመቁጠር – “ትላንት” ነበር “ዛሬ” ግን የለም ለመባል ነውን? ማለቱ ነው ጠቢቡ ወታደር – ሲመራመር። ከተፈጠርኩና በምድር መኖሬ ካልቀረ – ትርጉም ያለው ተግባር ከውኜ እና ሰው ሆኜ መኖር ይገባኛል – ነው የሚለው ጠቢቡ ወታደር። ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም – ይላል ጠቢቡ ወታደር። በዚህች ምድር ሰው አልፎ ሂያጅ ነውና ሰው በሰውነቱ ወደ ምድር በመምጣቱና ተለይቶም በመሄዱ መሬት የምታጣው ነገር የለም ነው እሚለው ጠቢቡ ወታደር። ሰው ግን መሬትን ያጣታልና በመሬት ቆይታው እርሱ ሲያልፍ መሬት ባታጣውም ታስታውሰው ዘንድ ግን መልካም ምግባር ከውኖ አሻራውን አሳርፎ እርሱን ለሚተካው ሰው እርሱ ከኖረበት የተሻለ አድርጎ ማለፍ የሰው ሃላፊነት ነው ማለቱ ነው – ፈላስፋው ወታደር። “ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም” እንደምን ያለ አመራማሪና እንደ ውቅያኖስ የተንጣለለ ባህረ ሀሳብ ነው? እንደምንስ ተተንትኖ ይዘለቃል? አንባቢ በራስህ ጊዜ ቀሪውን ተመራመረው ፤ ባህረ ሀሳቡንም ዋኝተህ ውጣው እንጂ እኛስ ከዚህ በላይ አንሞክረውም። ይልቅ ቀጣዩን ደግሞ ነቅሰንልኻል፤
ሰው ሆኖ መፈጠር ሰውነትን ለማክበርና ምድርን ለመሙላት ብቻ ሳይሆን ትዕዛዛትን ለማክበርና ሕግጋትን ለመፈፀም እንደዚሁም ዕውነትንና ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ ከልብ ለመፈቃቀርም በሆነ ነበር። ግን ሰው ተብሎ እንዲፈጠርና በምድር ላይ እንዲኖር አስፈልጎ ተፈጥሮም መሬትን የሰፈረባት ሰው ደጉንም ክፉውንም ነገሮች አስከትሎ ዓለምን ወረራት። በጊዜያችን የምናየው ሁሉ ምድር ከተፈጠረች ጀምሮ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የነበረውን እንጂ ብርቅ አድርገን የምንቆጥረው እምብዛም እንደሌለ እንመን – ይላል ጠቢቡ ወታደር።
ለመሆኑ ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ምን ማለቱ ነው? ብለን እንጠይቅና እንዲህ እንመልስ። የሰው ልጅ ወደ ምድር ሲመጣ ተቃራኒ ባህሪያትንም አጣምሮ ነው የመጣው። በዚህች ምድር ላይ ሲኖርም ለመውለድና ለመብላት ብቻ አይደለም። ህግጋትን ለማክበር፤ ፍቅርን ለመናኘት፤ በጎና ቅን ሆኖና ቅን አድርጎ መልካም ተግባርን ለመከወንም ጭምር እንጂ። ይህችን አንዴ ተፈጥሮ አንዴ ብቻ የሚኖርባትን ዓለም ጠብቆና አበልፅጎ እንጂ አጥፍቶና አራቁቶ መሄድ የለበትም ማለቱ እንጂ። ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ የሰው ልጅ ታሪክ መስራት ከጀመረ ጀምሮ በዓለም ላይ ዛሬ እኛ በደረስንበት ዘመን ሰው ሲያደርግ የምናየው ህሉ ትላንት እኛ ባልኖርንበትና ባልተፈጠርንበት ዘመንም የነበረው ሰው ሲያደርገው ነበር። ክፋት ደግነቱ፤ መግደል መቀማቱ፤ መጨከን ማዘኑ፤ መግዛት ማሰቃየቱ፤ ጦርነቱ ፤ ጥፋቱ ፤ ድህነቱ፤ ድረቁ ፤ጎርፉ ፤ ወጀቡ . . . ነበር አለ ይኖራል። የሰው ክፋቱ ጥፋቱ ጭካኔው አውሬነቱ – ስፋትና ጥልቀቱ ወርድና ቁመቱ ፤ እንደዘመኑ እንዳኗኗሩ ቢለያይም ቅሉ ፤ ማለቱ እንጂ ጠቢቡ። ‘አሁን ያለው በፊት ነበር፤ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር’ እንዲል መክብብ በታላቁ መፅሐፍ።
ሰው ሆኖ መፈጠር ሰውነትን ለማክበርም ነው ይላል ጠቢቡ ወታደር። እንዴት ማለት ነው? ራሱን ያላከበረ ሰው ነው ሌላውን ሰው የማያከብረው ማለቱ ነው። ወይም ስለራሱ በእሱነቱ ውስጥ ኢምንትነት ውስጠቱን የሚንጠው ሰው ነው በሌላው ሰው ላይ የሚታበየው፤ ተራራ አክሎ ለመታየት ተራራ የሚያከል ጭካኔና ግፍ የሚፈፅመው ማለቱ ነው አቢይ አበበ። የኢምንትነት ቫይረስ በደማቸው የሚሯሯጥ ሰዎች ሲሰባሰቡ ህመማቸውን የፈወሱ የሚመስላቸው ወይም የህመማቸው ማስታገሻ ሆኖ የሚያገኙት – በመሰል ዜጎቻቸው ወይም በሌሎች ዜጎች ላይ ዘረኝነትን ፤ ቅኝ ገዢነትን ፤ አምባ ገነንነትን ፤ ፍርደ ገምድልነትን ፤ ጥላቻንና ቂም በቀለኝነትን በመስበክ በማሰራጨትና በማስፈን ወደር የሌለው ብዝበዛና ዝርፊያ ወንጀልና እልቂት አድልዖና ኢሰብዓዊ ግፍ – የዘር ማጥፋትን ወንጀል ጨምሮ – በመፈፀም ወይም በማስፈፀም ወይም ለመፈፀም (በአደረጃጀትም ሆነ ባላሰለሰ ፕሮፓጋንዳ) በመዘጋጀት ነውና።
ማስረጃ ካስፈለገህ የጣሊያንና የስፔን ፋሽስቶችን እንዲሁም የጀርመን ናዚስቶችን ከሩቅ አገር ከሩቅ ዘመን መመልከቱ ይህም ካልበቃህ በአህጉረ አፍሪካ በምድረ ሩዋንዳ በሁርሲና ቱትሲ ጎሳ/ዘር መካከል የተካሄደውን አሰቃቂ እልቂት (የዘር ማጥፋት ዘመቻ) ወይም በጎጠኞች፤ በሃይማኖት አክራሪዎችና የሥልጣን ልክፍተኞች መካከል በሚካሄደው ጦርነት እየተፈጁ ያሉትን ሶሪያውያንንና እየወደመች ወይም እያወደሟት ያለችውን ሀገራቸውን አስተውል። ወደራስህ መመለስ ከቻልክም ከ1983 ዓ/ም ወዲህ በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የሰፈሩትን ባለተረኞች የኢምንት ሰብዕና ሰዎች ስብስብ ጎጠኛ/ዘረኛ ድርጅቶች ያካሄዱትንና በማካሄድ ላይ ያሉትን ተነግሮ የማያልቅ ምዝበራ ቶርቸር ማፈናቀል ትውልድን (ዘርን) የማጥፋት ዘመቻን መርምር።
እነሆ ደግሞም እነሱም በቀየሱት ቦይ በመፍሰስ ‘ማነህ ባለተራ’ ድርሻቸውን ለመረከብ ነባርና አዳዲስ ጎጠኞች/ጎሰኞች በ’ማንነት ፍለጋ’ “ዘመናዊ ጭምብል” የዘመኑን ጎጥ/ጎሳ/ዘር ዜማ የሚያዜሙት “አክቲቪስቶች” የሚያደርጉትን የሚደሰኩሩትንና “የሚገነቡትን” የፉክክር አጥር፤ የፉክክር ክልል፤ የፉክክር ድንበር (በጎሳ በዘር በጎጥ የመሰባሰቡን የመቧደኑን ከእድር እስከ እቁብ እስከ ሰንበት ማህበር እስከ ፖለቲካ) ሽር ጉድ – ከኢትዮጵያ እስከ አውሮፓ እስከ አሜሪካ እስከ ካናዳ እስከ እስያና አውስትራሊያ የሚሆነውን፤ የሚቦተለከውን፤ የሚታመሰውን መቃኘትም ‘የገደል ሩጫችንን’ ፍጥነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
እነሆ ዛሬ “ኢትዮጵያ” ብሎ የሚነሳው ወይም ስለ ኢትዮጵያ አደባባይ የሚወጣው ዲያስፖራ ስንት ሆኗል? በየጎጡና ዘርማንዘሩ ቆጠራና ደም የተመለመለው ሁሉ ግን በዝግ ስብሰባና በግላጭ ኮንፍረንስ በማስታወቂያ ካገር አገር እየተጠራራ ኢትዮጵያዊነትን አግልሎ በዘር /በጎሳ /በጎጥ አጀንዳ ላይ በአሜሪካ በካናዳ በአውሮፓና በአውስትራሊያ ሲዶልትና ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ሲሸነሽን – ለመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ጉዳይ (በተለይ በስደት ዓለም) የሚጠራ ኮንፍረንስና የሚገኝ ህዝብ መመናመኑን ወይም እየጠፋ መሄዱን አስተውለሃልን? ይህ እንደ ሰመመን እያማለለ የሚወስድ ወይም እንደ አረንቋ ስቦ የሚያሰምጥ የዘር ቫይረስ ‘ተስቦ’ ባልተጠበቀ ፍጥነት በየአቅጣጫው እየተራባ በመሆኑ – ጠቢቡ ወታደር እንደተነበየው (በተለይም በስደት ዓለም) ዕውነትንና ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ ከልብ ለመፈቃቀር – አልተቻለም ወይም አዳጋች እየሆነ ይገኛል – የአቢይ አበበን አገላለፅ መሬት አውርደን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በምንገኝበት ነባራዊ ዕውነታ ስንተረጉመው።
እንግዲህስ – ንግባዕኬ ሀበ ጥንተ ነገር – እንዲል የቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት – እኛም ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ። እነሆ የሚከተለውን የጠቢቡን ቃል ደግሞ ልብ ይሏል፤-
በተቀደሰ መንፈስ ለተቀደሰ ሥራ የተፈጠረው ሰው በበኩሉ ክፉ ሥራዎችንና ተንኮልን እራሱ ፈጥሮ ሲጨነቅና ሲንገላታ ፤ ሲያዝንና ሲተክዝ ፤ ሰውነቱን ሲጠላና የተወለደበትን ቀን ሲረግም ፤ በወገኑ ላይ ሲያፌዝና ወንድሙን ሲገድል ፤ በጓደኛው መንገድ ላይ ወጥመድ ሲዘረጋ፤ በጎረቤቶቹ ሲቀና በሌላው ሲመቀኝ ፤ የጊዜውንና የራሱን ጥቅም ብቻ ሲከተል ፤ዝርያውን በሀሰት ሲወነጅል ፤ የራሱን ሥራ ብቻ ሲያመሰግን ፤ ካጠገቡ ራቅ ያለውን ሲያማና ሲነቅፍ ፤ እራሱን እያታለለ ሌላውን ሲያሳስት፤ ተቆጥሮ የማያልቀውን ስንቱን ጉዳጉድ አመርቅዞና ደብቆ የያዘው ሰው እንደናንተም እንደ እኔም ያለ ነው።
አንባቢ ሆይ ፍረድ ! እርሱ በማይኖርበት ዘመን ያለህ አንተ አንባቢ አስቀድሞ የዘረዘረልህ ባህሪያት እንደኔም እንደናንተም ባለው ሰው ውስጥ ነው ይልሃል፤ ጠቢቡ ጄኔራል አቢይ አበበ። ታዲያስ? ይህ ዘመን ተሻጋሪ ትውልድን አነጋጋሪ ጠቢበኛ አገላለፅ አይደለምን?
ዛሬ እኔና አንተ በምንኖርበት ዘመን ውስጥ ለምሳሌ . . . በወገኑ ላይ ሲያፌዝና ወንድሙን ሲገድል ፤ የጊዜውንና የራሱን ጥቅም ብቻ ሲከተል ፤ ዝርያውን /ህዝብን/ በሀሰት ሲወነጅል ፤ እራሱን እያታለለ ሌላውን ሲያሳስት . . . የምናውቀው ግለሰብ ቡድን ድርጅት ወይም መንግሥት የለምን? ብዙ ሳትደክም ሀገርህን ኢትዮጵያንና ገዢዎቿን ህወሃት/ኢህአዴግን ተመልከት። ህዝብህን ኢትዮጵያውያንን ተመልከት ። የጠቢቡ ወታደር ቃል በዙሪያ ገባህ በእነ ሆድ አምላኩዎች እና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮች ሲተገበር አይታይህምን?! ይህን ግፍ ፈፃሚውና አስፈፃሚው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ከማታውቀው ዓለም የመጣ የማይታወቅ ፍጡር ሳይሆን እኔና አንተን የሚመስል ሀገር በቀል ሰው ነው።
ህወሃትን እንኮኮ የተሸከሙትና ለህልውናውም ዘብ የቆሙለት ከአማራው፤ ከኦሮሞውና ከሌላውም ብሄረሰብ የተሰባሰቡት “ኢህአዴጋውያንም” በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የተቀረፁ ሀገር በቀል ‘ሰዎች’ ናቸው። ይህ ሀገር በቀል “ሰው” ግን “ሰውቱን” አጥቷል። “ጭራቅ” የሚባል ምናብ ወለድ ጨካኝና “በላኤ ሰብ” ፍጡር ከምናብነት አልፎ “ዕውን” እንደሆነ ማወቅ ከፈለግህ ሩቅ ሳትጓዝ በሀገርህ መዲና እምብርት አዲስ አበባ ላይ በማዕከላዊ የሥቃይ ‘ቀራንዬ’ ብቻ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ህወሃት የሚፈፅመውን (ታዛዥ አገልጋዮቹ በዝምታ አልያም በመተባበር የሚያግዙትን) ጭራቃዊ ግፍና ‘ሰው በላነት’ ከመንጋጋው በተአምራት የተረፉትን የእነ ሀብታሙ አያሌውን የጣዕር ኑዛዜ ስማ!! በዘመነ ትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝ ሥር ያደገውንና ነፍስ ያወቀውን የዚህን ወጣት ትውልድን የኢትዮጵያዊነት ዕምነት ማተብና ፅናት በእነሀብታሙ አያሌው “ስቅላትና ትንሳኤ” ሰቆቃ ወፍዳ ትርከት ውስጥ ታየዋለህና!
የሀገር ፍቅርና የእናት ፍቅር ዐይንና አፍንጫ መሆናቸውን በእነ አንዳርጋቸው በእነ ሀብታሙ በእነ ኒሞና ጫሊ በእነ ሌንጂሳ አለማየሁ በእነ አቡበከር በእነ አህመድ ጀበል በእነ ካሚል ሸምሱ በእነ አህመድ ሙስጠፋ በእነ መሀመድ አባተ በእነ ካሊድ ኢብራሂም በእነ አደም በደዊ በእነ ኩርፊል ጀማል በእነ ብሩክ አጥላዬ በእነ ማስረሻ ሰጤ በእነ አቤል ከበደ በእነ ዳንኤል ሺበሺ በእነ አሸናፊ አካሉ በእነ አበበ ውርጌሳ በእነ ኑረዲን በእነ ናትናኤል በእነ አቤል ዋበላ በእነ ባህሩ ደጉ በእነ አንጋው ተገኝ በእነ ብሥራት አቢ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው በእነ በላይነህ በእነ ኡጁሉ በእነ እስክንድር በእነ ተመስገን በእነ አናንያ በእነ ዮናታን በእነ በቀለ በእነ መራራ በእነ አንዱዓለም በእነ ደመቀ በእነ ንግሥት በእነ ማህሌት ፋንታሁን በእነ ኤዶም ካሳዬ በእነ ባንቺ በእነ ሺህዎቹ የግፍ ማቃቂዎች ኢትዮጵያውያን ፍዳና ፅናት (ማየት ከፈለግህ) አሻግረህ ታያለህና … ትንታጎቹ የኢትዮጵያ ልቾች ስለ እናታቸው ክብርና ጤና በክፉ ሰዎች እጅ ቢወድቁም ቀንዲላቸው አልጠፋ አልወደቀምና!!
ክፉ ልብ ይዞ የተፈጠረ ክፉ ሰው ሁሌም የራሱን ድኩም ባህሪያት ለማየት አይቶም ለመለወጥ ከቶም አይጥርም። ክፋቱና ግፈኛነቱ ሲብስበት እንጂ ሲሻለው አይታይም። ሀገራችንና ህዝባችን እንዲህ ባሉ ክፉ ሰዎች እጅ ወድቀዋል – በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርና በሶስቱ ጉልቻ ባለሟሎቹ (ብአዴን ኦህዴድ ደህዴግ) ጨጎጎታዊ መዳፍ!! ክፉዎች ደግሞ በመጨረሻ አወዳደቃቸው አያምርም። ጠቢቡ ወታደር – አቢይ አበበ – እንዲህ አስቀምጦታል፤ ጭነቱ ምንም ባይሰማህና ባይከብድህ ፤ አወዛውዞ የሚጥልህ የማይታይህ የራስህ ምግባር ሸክም እንደሆነ አትዘንጋው።
አንጀት አርስ ቃል! ቃልም ምግብ ሆነ – ይሏል እንዲህ ነው። ጄኔራል አቢይ በዚህ አባባሉ እንደኔና እንዳተ ባሉ ግለሰቦች ምግባር ላይ ያተኮረ እንዳይመስልህ። ይልቁንም የዚህ አባባሉ ቀስት የተወነጨፈው ማህበረሰባዊና መንግሥታዊ ሃላፊነት በጨበጡት ላይ እንጂ። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ሃላፊነቱን በአግባቡና በወጉ ካልተወጣ – ህዝብን ካስለቀሰ ፤ ህዝብን ከረገጠ፤ ህዝብን ከመዘበረ ፤ ህዝብን ከፈጀ ፤ ድህነትን ጉቦኝነትን አድልዖን ዘረኝነትን ከተገበረ ካስፋፋ – እኩይ ምግባሩ በጊዜ ሂደት አወዛውዞ ከሥሩ ይመነግለዋል – ነው የሚለው ጠቢቡ ጄኔራል።
አባባሉን መሬት ላይ ስታኖረው ደግሞ እንዲህ ማለት ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ በግፍ ግፍ የሚገዛው ህወሃት/ኢህአዴግ ክፋቱ አይከብደውም። አይሰማውም። ህወሃት ጥፋቱ አይታየውም። የማይሰማው ፤ የማይታየው ፤ የማይከብደው የጥፋት ፤ የክፋት ፤ የወንጀል ምግባሩ ግን ህወሃት / ኢህአዴግን አውሎ ንፋስ እንዳርገፈገፈው ዛፍ ከሥሩ መንግሎ ይጥለዋል። ይህ ከቶም አይቀሬ ነው። ይህ ይሆን ዘንድ የተፈጥሮም ህግ ነውና።
እነሆ የጀመርነውን ንዑስ ርዕስ በሚከተለው የጠቢቡ ወታደር ቃል ብንሸብበውስ?
ሰው ሰው ሰው የማትበለጠው የማትሸነፈው የማትደመሰሰው ስምህን አክብረህ ለመኖር የምትመኘው፤ ሀብትህን ለምን ወይንም ለማን የምታከማችበትን ምክንያት የማታውቀው፤ ለጓደኛህ ውለታ የማትሰራ፤ ሌላው ላደረገልህ ምሥጋና የሌለህ ፤ ወገንህን ወደወጥመድ የምትመራ፤ ጠባይህን ሳታርም የሌላውን ጠባይ የምትነቅፍ፤ በወንድምህ የምትቀና በሀሰት ጎዳና የምትጓዝ፤ ከዐይንህ ጆሮህን የምታምን፤ የሌላው ስቃይና መከራ ደስ የሚልህ፤ በራስህ ብቻ የምትመካ፤ በዕውቀትህ የምትራቀቅ፤ ያሰኘኝን ሁሉ አደርጋለሁ አደርጋለሁ የምትል ሰው ሆይ መች ይሆን መታረሚያህ ?!
ሀገር እና ህዝብ
አንድ፤
ሀገር ያለ ሰው ምድረ በዳ ሆና ትኖር ይሆናል። ሰው ግን ያለ ሀገር ሊኖር አይችልም። ሀገር ምን እንደሆነች ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን ሀገር የምትኖርበትን ዘዴ ገና አጥርተን ያወቅነው አይመስለኝም።
የአንድ ሀገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቅና ለአንድነታችን መጠጊያ የሆነችውን እናታችንን ኢትዮጵያን ለማገልገል ለማኖርና ለኑሯችንም ለመሥራት የምንችለው በአንድ መንፈስ ስንሰለፍና በንፁህ ህሊና ፀንተን ስንተባበር ብቻ ስለሆነ ወደዚህም በቅንነት እንድንራመድ ስለሚያሻ የያንዳንዳችን መንፈስ ከደካማነት ወደ ፅኑነት መለወጥ አለበት።
መተዛዘንን፤ መተሳሰብን፤ ጠንካራ መንፈስን፤ ቅን ባህሪይን፤ ፍቅርን እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል። ይህም በመኻላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም።
ይህ የጠቢቡ ወታደር ቃል ነው። እነሆ ይህ ቃል የተፃፈውም በ1955 ዓ/ም ነው። ይህ የጠቢቡ ወታደር ቃል በዚህ ዘመን እኔንም ሆነ ትውልዴንም ሆነ ሀገሬንም ሆነ አይመለከትም የምትል የዚህ ቅኝት አንባቢ እዚሁ ላይ በጨዋ ደንብ ብንሰነባበት መልካም ይሆናል። ለምን ብትል? እኛና አንተ የምንኖረው በሁለት ዓለማት ውስጥ መሆኑ ነውና።
የጠቢቡ ወታደር ቃል የሰረሰረንና የነዘረን ዙሪያ ገባችንን ደጋግመን እንድንመረምር እኛን እኛ ባደረጉን መሰረቶችና እሴቶች እኛን ዛሬ ላይ ሆነን ለመመዘን ግፊት ለሚሰጠን ግና እነሆ በቅኝታችን አብረን እናዝግም።
ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በመፅሀፉ ያቀረበውን ሀሳብ የማስፋፋቱ ጉዳይ የአንተና የእኔ እንደሆን አስቀድሞ ነግሮናልና እነሆ እኛ በምንኖርበት ዘመን ተርጉመን የተረዳነውን እንዲህ እናወርዳለን።
ለአንድነታችን ማዕቀፍ ፤ ለእኛነታችን መለያ ፤ ለዜግነታችን መታወቂያ የሆነች ሀገራችንን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለመጠበቅ ለማራመድና እኛም አብረናት ለመራመድ አስቀድመን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የአንዲት ሀገር ልጆች መሆናችንን እንወቅ እንመንም – ይላል ጠቢቡ ወታደር በአፅንዖት።
ታዲያስ ?! ዛሬ ዘመን ቅጥ አምባሩ በጠፋ ውስብስብ ‘የማንነት’ ዘር ማንዘር አባዜ ውስጥ ገብተን የምንዳክረው አስቀድመን የአንዲት ሀገር ልጆች ፤ የአንዲት ሀገር ዜጎች – ኢትዮጵያዊ – መሆናችንን አላምን ብለን አይደለምን? እንግዲህ እኛና ሀገራችን በምንገኝበት በዚህ ምስቅልቅል ሁሉም በቅድሚያና በዋናነት ‘ኦሮሟዊ’ ‘አማራዊ’ ‘ትግራዊ’ ‘ሲዳማዊ’ … ነኝ ካለ ኢትዮጵያዊው ማን ነው? ኢትዮጵያዊነትስ ምንድን ነው? ኢትዮጵያስ የማን ናት? ሁሉም በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኔ ተበድያለሁ እያለ በዋናነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ጦር የሚሰብቅ ከሆነ፤ ከዘሬና ዘሬ ከሚኖርበት ክልል ውጪ ያለችው ኢትዮጵያ ገደል ትግባ ትፈራርስ ትበታተን ካለ፤ ጎሳዬ ከተበደለባት ኢትዮጵያ ወጥቼ / ተገንጥዬ የራሴን የዘሬን / የጎሳዬን መንግሥት አቆማለሁ ካለ እንግዲህ መጨረሻችን እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ምን ሊሆን ይችላል?
ሁለት ፤
እነሆ ደግሞ አንባቢ ሆይ የሚከተለውን በፅሞና አንብብ ፤ አስተውልም።
እርስ በርሳችን ባለመስማማትና በመቀናናት አንዱም አንዱን ጥሎ የሚመኘውን ክብር ለመያዝና ለጊዜው ብቻ በጊዜው ለመታየት፤ ወንድምና ወንድም እየተጋጩ በውስጣችን በደረሰው መገዳደልና መዘራረፍ ከዘመን ወደ ዘመን እየተላለፈ የኢትዮጵያ ልጆች ደም ያለምክንያት በከንቱ እየፈሰሰ ህዝቡም እየተቀነሰ መሬቱ ተራቁቶ ይገኛል።
ያለፈው አለፈ። ደጉም ሆነ ክፉውም ሥራዎች ታሪክ ሆነው ስለሚገኙ ባለፈው ከመፀፀትና ባለፈ ነገር ላይ ከመተቸት ያለፈውን ክፉ ነገር ሁሉ የታረመ ትምህርት አድርጎ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን መጭውን በማመዛዘን የዛሬው ተሻሽሎ ለነገ ሊተካ በሚገባው ላይ መድከም ግዴታችን ነው።
ለመሆኑ አቢይ አበበ ይህንን የፃፈው ለማንነው? እሚል መጠይቅ አእምሮህ ውስጥ አላሰተጋባምን? አዎ ዕውነት ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ለእኔ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ላንተና ላንቺ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ለኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ከአብራኳ ወጥተው በኢትዮጵያ ላይ ሰይፋቸውን ለሳሉት ጦራቸውን ለነቀነቁት ጥርሳቸውን ለሚያፋጩት ሁሉ ነው። እነሆ እንሰማው ዘንድ ሠዐቱ አሁን ነው። መስማት ከተቻላችሁ ህወሃትአውያን ሆይ ስሙ፤ ብአዴንአውያን ሆይ ስሙ፤ ኦህዴድአውያን ሆይ ስሙ፤ ደህዴግአውያን ሆይ ስሙ፤ … በሰፈራችሁት ቁና ትሰፈራላችሁና ከዛ በፊት ህሊና ካላችሁ ከህሊናችሁ ታረቁ! “ውርድ ተራሴ!” እንዲሉ አበው።
እነሆ ደግሞ ከእኒህ ዛሬ የኢትዮጵያን ማንቁርት ካነቁት ጀርባ ተደራጅተው ነገን በተራቸው በዘር ማንዘር ቅኝት ኢትዮጵያን ሊቃኙዋት ከውስጥና ከውጪ የተነሱባትና “ከድጡ ወደ ማጡ” እየደገሱላት ላሉትም ሁሉ ጆሮ ካላችሁ ስሙ፤ ምክር መቀበያ ህሊና ካላችሁ ተቀበሉ – ይላችዃል አቢይ አበበ ፤ ከመቃብር በላይ በሚያስተጋባው ጥሪው።
ያለፈው ዘመን ታሪክ አለፈ። ከመቶ ከሁለት መቶ ከአምስት መቶ ከወዘተርፈ መቶ ዓመት ጀምራችሁ እየቆጠራችሁ በሌላችሁበትና በሌለንበት የታሪክ ኡደት በዚህ ዘመን በቂም በቀል እንድንመታተር ደም እንድንፋሰስና እንድንበታተን የምታደርጉትን ድካም ሁሉ ግቱ። ያለፈውን ደጉንም ሆነ ክፉውን ሥራ የሰሩት ትውልዶች ለታሪክ አስመዝግበው አልፈዋል። እኛም እንደ ‘ዛሬ’ ትውልድነታችን ከትላንቱ ትውልድ መልካሙን እንቀጥልበት፤ ክፉውን እንዳይደገምም እናስወግደው። የትላንቱን የተዛባ አስተሳሰብና ድርጊት በእኛ ዘመን አንድገመው። በእኛ ዘመንና በእኛ ትውልድ ትላንት ከተረከብነው ትላንት ከነበረው በሥነ ምግባር በሥነ ልቡና በፍቅር በመቻቻል በአስተዳደር በአፈራረድ በመተሳሰብ በዕድገትና በብልፅግና ተራምደን እንጂ ብሰን አንገኝ። ይህንንም መሆንና ማድረግ ያለብን ስለማንም ብለን ሳይሆን ስለራሳችን ብለን ስለመቀመጫችን ብለን ስለመኖራችን ብለን ስለልጆቻችን ብለን እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ስለመቀጠላችን ብለን እንጂ!!
ሶስት ፤
እነሆ አቢይ አበበ ይህንንም ፅፏል፤-
ስለሀገሩ ተቆርቋሪ ያልሆነ ሰው ለህጓ ተገዢ አይሆንም። ድንጋጌዋንም የማያከብር አፉ ይዘልፋታል፤ አሳልፎም ለማይገባው ዘላፊ ይሰጣታል። የሀገሩንም ክብር በከንቱ የሚዘልፍ ሰነፍ ብቻ ነው። እርሱም የራሱና የወገኖቹ ጠላት ሆኖ በሚነዛው መጥፎ ምሳሌ ብዙ ደቀመዛሙርትን አስከትሎ የሀገርን ፍቅር መሰረት ለመናድ የተነሳሳ ነው።
ጎበዝ…ጄኔራል አቢይ አበበ ትንቢተኛ ነበር እንዴ? ጠቢቡ ወታደር የፃፈው እንደ ፀሀይ ብርሃን ፏ ብሎ በምድረ ኢትዮጵያ የሚታይ ሀቅ አይደለምን? እነሆ ህግ አውጥቶ ህግ የሚጥስ ፤ በህዝብ ፊት በአደባባይ ሀገርና ትውልድን የሚዘልፍ ፤ ታሪክን ‘ቧልት’ ‘ተረት ተረት’ እያለ የሚሳለቅ፤ ሀገርን አኮራምቶ ቀበሌን የሚያገዝፍ፤ ዘርፎ ለዘራፊ ሰድቦ ለተሳዳቢ አዋርዶ ላዋራጅ፤ አፈናቅሎ ላፈናቃይ የሚሰጥ መሪና መንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረው የምኒልክን ቤተመንግሥት በ1983 ዓ/ም በርብርብ ወርረው በማረኩት ህወሃት / ኦነግ / ሻእቢያ አስኳልነት አይደለምን? ከዛን ዘመን እስከዚህ በሶስቱ ፅንፈኞችና በዝርያዎቻቸው የተባለውንና የተደረገውን … ዘለፋውን የህዝብ ንቀቱን ድርጅታዊ ስድነትንና ብልግናውን ስንቱንና ስንቱን እንደምን ዘርዝሮ ይዘለቃል?
የኢትዮጵያዊ ሀገር ፍቅር መሰረቱና ፅናቱ በህወሃት / ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ ድውይ ፕሮፓጋንዳና እኩይ ምግባር ተገዝግዞ ተሰርስሮ ተሸንቁሮ ተሸራርፎ ለይቶለት ባይናድም ቅሉ አልተገዘገዘም አልተሸነቆረም አልተሸራረፈም ብሎ የሚደፍር ይኖር ይሆን? “የሀገሩን ክብር በከንቱ የሚዘልፍ የራሱና የወገኖቹ ጠላት ሆኖ በሚነዛው መጥፎ ምሳሌ ብዙ ደቀመዛሙርትን አስከትሎ የሀገርን ፍቅር መሰረት ለመናድ የተነሳሳ ነው – በማለት አቢይ አበበ የተነበየው ዛሬ በኢትዮጵያ ምድርና አልፎም በመላው ዓለም በተበተኑት ኢትዮጵያውያን መካከል የተከሰተ ክፉ ሰዎች የፈጠሩትና ክፉዎች ደቀመዛሙርትን ያፈሩበት የክፉ ዘመን ጎጣዊ በሽታ አይደለምን? የደቀመዛሙርቱ ስምና ቀለም ቢለያይም ቅሉ!!
አራት ፤
ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ‘አውቀን እንታረም’ በማለት የጎጥንና የጎሳን ጉዳይ አስመልክቶ በአፅንዖት ካሰፈርው ውስጥ የሚከተለውን ደግሞ ያስተውሏል፤
ሰው በራሱ ከተመካና ስለራሱ ብቻ ካሰበ ከሰው ጋር ሊኖር አይችልም። የራሱን ሀሳብ ብቻ ተርጓሚና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ከሆነም የማህበራዊ ዕድገት አይስፋፋም። ስለዚህም ማንኛውንም ሁሉ የጋራ ጉዳይ በማድረግ ተመልክቶ አጣርቶና ተባብሮ ለሚበጀው ነገር ብቻ መጠመድ ፍቅርን ስለሚጠይቅ አንተ ትብስ አንተ ትብስ ተባብሎ መፎካከር ቅን መንገድ ይመራልና በዚህ ዐይነት መጓዝ ግዴታ ነው።
የሚመሰገኑና የሚነቀፉ ባህሎቻችንን ለይተን አውቀን የምንተወውን ትተን የምንይዘውን ማዳበር አለብን። በየጎራው ፤ በየሸንተረሩ ፤ በየመንደሩና በየጎጡ በየጎሳውና በየክፍሉ በየሃይማኖቱ ከመመካት ለአንዲት ኢትዮጵያ ብለን የምንሰራው ሁሉ የጠቅላላው መደርጃ ጥቅም መሆኑን ብቻ እንመንበትና እንነሳ።
ሕግ እንዲከበርና እንዲፀና አዋጅም እንዲሰራ አድልዖና ልዩ አስተያየት የሚባሉት ይቁሙ። ሥልጣንም ማዕረግም ለግል ጥቅምና መከበሪያ አይሁን። ማንኛውም የሀገር ሰው በችሎታውና በሥራው ብቻ ይመረጥ እንጂ በወገንና በባለወገንነት አይደገፍ። በጥፋት የተገኘ ባለሥልጣንም ጥፋቱ ለህዝብ ተገልጦ ይነገርበት።
አንባቢ ሆይ! ይህንን ጥልቅና ምጡቅ እንዲሁም ክቡር ሀሳብ አንተው ካገርህና ከመንግሥትህ ከራስህም ተሞክሮና ህይወት ጋር እያሰናሰልክ ተርትረው እንጂ ቃኚው ለማብራራት አይዳዳውም። ነገር ግን ቃኚው ይህን ይላል፤- ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ አርቆ አሳቢና ተመራማሪ የነበረ ፤ መንፈሳዊ ቅንንት ከሀገራዊና ወገናዊ ፍቅር ጋር የሰረፀበት ከዘመኑ አብሪ ትውልድ መካከል አንዱ አንደነበር እስካሁን የነቀስናቸው ፅንሰ ሀሳባዊ ምልከታዎቹ ዋቢ አይሆኑምን? እነሆ በዚህ ከተስማማን ጥቂት አብረን እናዝግም።
አምስት ፤
እነሆ ደግሞ ቀጣዩን ወደ ውስጥህ እየተመለከትክ ልብ ብለህ አንብበው!
በአሁኑ ጊዜ ህብረት እንጂ የሀሳብ መነጣጠል ለሀገሪቱ አይጠቅምም። ደግሞም በተለዬ ጥቃትና ጭቆና የማይወደው የሀገራችን ህዝብ የሚተባበረው መከራ ሲደርስበት ብቻ ነው። ይህ ለምን ይሆናል? አንድ ክፉ ነገር በሀገሪቱ ላይ ከመድረሱ በፊት የሚደረገው መተባበር እንጂ ከደረሰ በሁዋላ በመቆጨት አይዞህ ወንድሜ መባባሉ ዋጋ የለውም።
ዛሬ የተያዘውና የሚታሰበው መነቃቀፍ ብቻ ሆኖ ይገኛል። መነቃቀፍም አርቆ ማስተዋል የሌለበት የአለ ይበሉኝና የወሬ ማዳነቂያ መደብር ሆኖ ከመገኘቱ በስተቀር ፍሬ አፍርቶ አልታየም።
አጀብ ነሽ ኢትዮጵያ! ያኔም (በ1950ዎቹ) እንዲህ ነበርሽ? ዛሬስ (በ2ሺህዎቹ መጀመሪያ) እንደ ያኔው ነሽ? ወይስ ትለያለሽ? አንባቢ በያኔውና በአሁን አንድነቱንና ልዩነቱን አንተው ዘርዝረው። እኛ ግን በዚህ ዘመን ባለው የሀሳብ መነጣጠል መነቃቀፍና ህብረት ማጣት ላይ ጥቂት እንቆዝማለን።
አቢይ አበበ አስቀድሞ ያወረደውን አንቀፅ ተረካቢ ባለቤቶች አሉ። እነርሱም በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ከህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ ፍዳ አገዛዝ እንታደጋለን እሚሉት በተቃዋሚው ጎራ የሚገኙት አያሌ ድርጅቶች ናቸው። እነሆ ከሁለት አስርታት በላይ በአንድ መድረክ ተገናኝተው በጋራ መምከር፤ በአንድ ጥላ ቆመው በጋራ መራመድና የጋራ ክንድ ማንሳት አልቻሉም። ስንት ህብረት ስንት ቅንጅት ስንት መድረክ ስንት ውህደት ተፈጥረው ፈረሱ? ለመሆኑ ‘የብሄር’ ነፃ አውጪው ድርጅት ስንት ነው? (ለነገሩ ሃያ ስድስት ዓመት ምኒልክ ቤተ መንግሥትን የተቆጣጠረው ገዢም ዛሬም ድረስ መጠሪያው ‘የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር’ አይደለም?) በኢትዮጵያ ስም የተደራጀውስ ፓርቲ ግንባር ጦር የሲቪክ ማህበር ስንት ነው? መዘርዘሩ ራሱ ያታክታል … አቢይ አበበ እንዳነጠበው – መነቃቀፉም አርቆ ማስተዋል የሌለበት የአለ ይበሉኝና የወሬ ማዳነቂያ ሆኖ ከመገኘቱ በስተቀር ፍሬ አፍርቶ አልታየም! (የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ዛሬ ላይ በየፊናቸው የሚገኙበትን ሀቅ እንደምን በመሰለ ውብ አገላለፅ ነው ያስቀመጠልን?!) እንግዲህስ በዚህ ነቁጥ እዚህ ላይ ይብቃን። አቢይ አበበ ግን ይቀጥላል፤-
የሀገሩን እድገትና ሥልጣኔ የህዝቡንም ደህንነትና ስለከፍተኛ ኑሮው ደረጃ ማደግ የማይመኝና የማያስብ በአሁኑ ጊዜ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን አንዳንድ በጎ አሳቢና ሁሉን ያወቅን ነን ባዮች ሌላውን ወገን ያላወቀና ያልገባው ተመቅኝና ልዩ ሀሳብ ያለው እንዲያውም የሀገሩ እድገት እንቅፋት ነው በማለት በሚያትቱት አሉባልታ የሚነዛው እድፍ እገባውም አልገባውም ላይ ማረፉ ስለማይቀር ለማንኛውም ወገን ሊበጀው አይችልም። የዚህም ዐይነት ሽሙጥና ማንኛውም ዐይነት አነጋገር ሁሉ ለሀገሪቷ ፈውስ የሚሰጥ መድሃኒት አይደለም።
ጥንታዊቷንም የዛሬይቱንም ኢትዮጵያችንን የወደፊትም እንድትሆን ካስፈለገ በቅን መንፈስ በፍቅርና በመተሳሰብ ደግፈን እናዘልቃታለን ብለን ካልተነሳን በቀር በአሉባልታና በመነቃቀፍ፤ በሀሰት በመነዳትና በወሬ በመሰልጠን በንፁህና በተባረከው ህዝቧ ተንኮል በመዝራት እንደዚሁም በሰው ሀገር ጉዳይ ውስጥ እየገቡ አሳቢ በመምሰል የህዝቧን መነጣጠል ለሚገፋፉ ባዕዶች ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ በመገኘት ጥቅም ይገኛል ብሎ የሚያስብ ቢኖር በተሳሳተ መንገድ መሄዱን ይረዳው። ከእንደዚህም ያሉ ሰባኪያን መራቅ የማንኛውም ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ሰው ጥንቃቄ መሆን አለበት።
ላንዲት ሀገር ከልጆቿ የበለጠ ደጋፊና አሳቢ ሊኖራት አይችልም። አሳቢ መስለው ልጆቿን በመለያየት የሚጠቀሙ እነማን እንደሆኑና የመለያየት ትርጉም ምን እንደሆነ ሀገራቸውን ወዳድ የሆኑ ሰዎች ሁሉ አእምሮ በቀላሉ ሊመዝነው ይችላል። ከሁሉ የባሰ አንድ ሀገርንና ህዝቧንም ወደ ከንቱ ምሣሌ የሚመራው ያልታመነ ተስፋ ነው።
የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊ፤ የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊት ሆይ! እነሆ ገና በማለዳ ቅኝታችንን ስንጀምር የጠቢቡ ወታደር መፅሀፍ ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ አነጋጋሪና ልጓም አስጨባጭ ብለን የመነሳታችን አንጓ ነቁጥ አንዱ አስቀድሞ የነቀስነው መልዕክት ነው። እነሆ ደግሞ እኛ ይህንን የአቢይ አበበን መልዕክት በዘመናችን የተረዳነውና የተረጎምነው እንዲህ ነው፤-
በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ ውስጥ (በዛሬይቷ ኢትዮጵያ) እየኖረ ጥንታዊቷን ለዛሬዋ መሰረት የሆነችውን ኢትዮጵያን (የአፄዎቹ የሚል ቅፅል ሰጥቷት) እንደ ማርያም ጠላት አልያም መስጊድ እንደ ገባች ውሻ በየአቅጣጫው ድንጋይ የሚወረውርባት ሜንጫ የሚያፋጭባት ትበጠስ ትቆረጥ ትበተን ገደል ትግባ እያለ የዘመተባት ሁሉ አደብ ገዝቶ ይህንን የጠቢቡን ወታደር ቃል እንዲመረምር እንዲያበራይና እንዲያጠና በኢትዮጵያዊነታችን እንጋብዛለን። የጠላቶቿ መሳሪያ ፤ የትዕቢተኛና የሥልጣን ናፋቂ አውቀናል ባዮች ጎጠኛ ምሁራንና ባዕዳን ሀይሎች መናጆና መሰላል ፤ የወንበዴና ዘራፊ እኩይና ፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ከለላ ከመሆን ታቅቦ የትላንቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ መሆኑን አምኖ ታሪኳን በታሪክነቱ ተቀብሎና አክብሮ እንደ ትውልድ እንደ ዜጋ የበኩሉንና የሚኖርበትን ዘመን ለሚኖርበት ትውልድ መልካምና ቅን ተግብሮ ከትላንቱ ልቆና ዳብሮ ደግሞ በተራው ለነገው ለማስረከብ እንጂ ያልኖረበትንና የትላንቱን “ክፋትና ጥፋት” እያመነዠከ በከንቱ ቅዥትና በቀቢፀ ተስፋ እየዳከረ ለበቀልና ለጥፋት እንዳይኖርም ሰሚ ጆሮ አስተዋይም ልቡና ላለው ወገን ሁሉ “አቤት” እንላለን።
አንድ ሀገርንና ህዝቧንም ወደ ከንቱ ምሣሌ የሚመራው ያልታመነ ተስፋ ነው – ብሏልና ጠቢቡ ወታደር – በቀቢፀ ተስፋ “ቅዥታዊ ራዕይ” እየሰበክን በከንቱ ተግባር የክቡር ኢትዮጵያውያንን ደም ከማፍሰስ ወይም እንዲፈስ ከማመቻቸት ፤የክቡር ኢትዮጵያውያንን ሠላም ከማናጋትና የአንድነትን ፍቅር ከማደፍረስ መቆጠቡ ከታሪክ ተጠያቂነትና ወንጀለኛነትም ያድናልና አውቀን እንታረም – ይላችዃል ጠቢቡ ጄኔራል።
ስድስት ፤
እነሆ ትዕግስቱና ማስተዋሉ ላንባቢ ይሁንና በእኛ በኩል ቅኝታችን ይቀጥላል።
በየአለንበት ሥፍራ ስንኖር ጥረን ግረን እንድንበላ ታዟል። ይህንንም ስናደርግ እንታያለን። ግን ድካማችንና መታከታችን ሁሉ ለምንድን ነው? ለማንስ ነው? የድካማችንስ ፍሬ ምን ይሆን?
የተለመደውን ሀተታ በመያዝ ድካማችን ለሀገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል። ነገር ግን ይህን መናገር የሚገባው በአንድ ትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት።
እንግዲያውስ እንደሚታየው ከሆነ ድካማችን ለየግል ፍላጎታችን ሆኖ የድካማችንም ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው።
እነሆ አስቀድሞ በተነቀሰው መልዕክት ውስጥ ቃላቱ በአእምሯችን ጓዳና አደባባይ እንደ ክላስተር ቦንብ (ተፈነጣጣሪ) በየአቅጣጫው ሲፈነዱ ይሰማናል። ለምን? ለምሳሌ ከ’ተቃዋሚው ጎራ’ በየመድረኩ በየጋዜጣው በየሬዲዮው በየቴሌቪዥኑ በየወዘተርፈው የሚቀርበው አብዛኛው(?) የፖለቲካ የሲቪክ የጎጥ /የዘር ድርጅት መሪ ወይም አክቲቪስት ዲስኩሩን ሲሰጥህ – የሚያስረግጠው ቃል – ድካሙና መስዋዕትነቱ ለሀገርና ለመጪው ትውልድ መሆኑን። እና ይህን ‘ተቃዋሚ አካል’ ፤ ይህን ‘በጎጥ የተደራጀ’ – ይሄ መንገድ አያዋጣንም፤ ይህ ራዕይ አያዛልቀንም፤ እልህና ከማን አንሼ ሀገር አይገነባም ለትውልድ ሠላም አይሰጥምና ታርመንና አደብ ገዝተን መኻል መንገድ ተገናኝተን (ፅንፍ ለፅንፍ ሳንቆም) ተወያይተን መላ መትተን ተያይዘን እንራመድ” ብትለው … ይፈርጅኻል፤ ይወርድብኻል፤ ‘ፔቲሽን’ እየፈረመና እያስፈረም ቢችል ከሥራህና ከምትኖርበት ሀገር እንድትባረር ‘ኡኡ’ ይላል። ለምን? የርሱ መንገድ ብቻ፤ የርሱ ራዕይ ብቻ፤ የርሱ ቀኝ ጌታ (መሪ) ብቻ የርሱ ‘አክቲቪስት’ እንጂ ጎዳናውና የዕውነት መንገዱ። ለሀገርና ለትውልድ መሥዋዕትነቱ በእርሱ ድርጅት በእርሱ መሪ ከእርሱ ጎን መቆም ብቻ እንጂ ዕውነቱ። ካልሆነ “ወይ ከኛ ወይ ከነሱ” ይልኻል – ሶስተኛና አማካይ መንገዱን ዘግቶ።
በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ዙሪያዋን ቀስፎ የያዛትና የዘመተባት ጎጠኛ አካል አደገኛነት እጅግ መረን ከመልቀቁ የተነሳ ግማሹ “የአፄዎቹን ኢትዮጵያ አናውቃትም ገደል ትግባ፤ ትበተን” ሲል፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ አጥንት እየቆጠረና ቀበሌ እየጠራ “አፄዎቹ” “የኛ ናቸው” እያለ ታሪክንና ኢትዮጵያውያንን ከርሱ ዘር ክልል ከማውጣት አልፎ የሀገር መሪዎቹን የኢትዮጵያን ሠንደቆች አውርዶና አኮስሶ በርሱ ቁመትና በርሱ ቀበሌ ለክቶ ያቆማቸዋል። ዘረኝነት እርከን ካለው እኒህ አዳዲሶቹ የዘመነ መሳፍንት ቀበሌያውያንና ጎጠኞች አክቲቪስቶች የህወሃትን የዘረኝነት መንፈስ በአዲስ ጎዳና ላይ ቀደው ወዳልታወቀ እርከን አሸጋግረውታል።
እናንት የዚህ ዘመን አዳዲስ ዘመነ መሳፍንት አክቲቪስቶችና ማህበርተኞቻቸው ሆይ! የኢትዮጵያን ነገሥታትና መሪዎች ከኢትዮጵያ ማማ ላይ አውርዳችሁ በየጎጥና ቀበሌ ኮንፍረንስና ስብሰባችሁ ግርግዳ ላይ እየሰቀላችሁ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የኢትዮጵያ ዳርቻዎች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የምናምነውን ከመሪዎቻችንና ከታሪካችን (ከትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃትም በረቀቀ መንገድ) ለመነጠልና ባይተዋር ለማድረግ የምታካሂዱብንን ከፍተኛ የሥነ ልቡና ርብርቦሽ አቁሙ!!! አፄዎቹና ታሪካቸው የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው። አባትነታቸውም በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነታቸው ለማይደራደሩ መላ ኢትዮጵያውያን እንጂ ለአዳዲሶቹ ዘመነ መሳፍንት ቀበሌያውያን አክቲቪስቶችና ማህበርተኞቻቸው አይደለም!! ጆሮ ካላችሁ ስሙ ልቡና ካላችሁ ተመለሱ መካሪ አዛውንቶች ካሏችሁም ምክር ተቀበሉ!!
እንግዲህስ ‘ንግባዕኬ ሃበ ጥንተ ነገር’ እንዲሉ እኛም ወደቀደመ ጉዳያችን እንመለስ።
በዛኛው ጎራ ደግሞ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ከነባለሟሎቹ የሚያላዝነው የሚሰብከው የሚምል የሚገዘተው ድካሙና ጥረቱ መሥዋዕትነቱ ሁሉ – ለሀገርና ለመጪው ትውልድ መሆኑን። የሚደንቅና የሚገርመው የህወሃት ኢህአዴጉን ተግባር በራስህ በቤተሰብህ በጎረቤትህ በሰፈርተኛው በሀገሬው ላይ ያደረሰውን ቁስል ያስከተለውን ሰቆቃ በደልና ኢፍትህ በአይንህ እያየኸው በሰራ አካልህ እየዳሰስከው አሌ ይልኻል፤ ይህን ሁሉ የሚያደርገው – ለሀገርና ለመጪው ትውልድ ከርሱ በላይ ተግባሪ ከርሱ በላይ አሳቢ ከርሱ በላይ ወኪል የሌለ መሆኑ።
እነሆ እንግዲህ ግራና ቀኝህን ስታስተውል ነው የጠቢቡ ወታደር ቃል እንደ ፈንጂ የሚፈነዳብህ። … ድካማችን ለሀገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል … ይህንን መናገር የሚገባው በአንድ ትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው /ህዝብ፤ ትውልድ/ የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት፤ ይላልና አቢይ አበበ።
የራሱን ትውልድ አካል እንደ ጉድ እየጠላ እየናቀ እየረገጠ እያሰቃየ እየበደለ እያንጓጠጠ እየፈጀ እየፈረጀ እያስራበ አያፈናቀለ እያሰረ እየገደለ አካል እያጎደለ በጎጥና በወንዝ እየፈረጀና እየተደራጀ ሌላውን ወገኑን እያገለለ … ስለሀገርና ስለነገው ትውልድ ወይም ስለማንነቴ ነው ድካሜና መሥዋዕትነቴ ብሎ ጩኸት አይገባኝም አይዋጥልኝም ነው ያለው ጠቢቡ ወታደር አቢይ አበበ። በአደባባይ የሚታየውና የሚሆነው አቢይ አበበ እንደታዘበው ድካማችን ለየግል ፍላጎታችን ሆኖ የድካማችንም ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው።
ሰባት ፤
ቀጣዩን የጠቢቡን ወታደር ቃል ደግሞ ያጤኗል፤
ትንሽም ብትሆን ደግ ነገር ሰርተን ካልተሸኘን እኛን የሚያስታውስ ምንም ምክንያት አይኖርም። ምናልባት እንኳ ወግ ባለው መቃብር ተቀብረን መቃብራችንም በእምነበረድ አጊጦ ስማችን በላዩ ላይ ተቀርፆ ቢታይና ቢነበብ የሚያመለክተው የስም መቃብርነቱን ነው። አለበለዚያ ግን የትም ዋሻ ውስጥ ተወርውረን አንድ ቀን መከረኛው አፅማችን ከአፈር ውስጥ ብቅ ብሎ ሲታይ የሰው አጥንት ተብሎ በተፈጥሮ ስማችን ብቻ ያስነሳን ይሆናል እንጂ የእገሌ አያሰኘንም።
አዎ ሀቅ አንጥቧል አቢይ አበበ። ሠው በዚህች ምድር ላይ በሚቆይበት ዘመኑ መልካም ነገርን ቢያደርግ ማንን ምን ይጎዳል? ፍቅርን መስበክ ፍቅርን ማስተማር በፍቅር ስለመኖርና ስለ ፍቅር ይቅር ማለትን ለወገኑ ቢያስተምርና ወገኑን በፍቅር ቢያንፅ ሀገሩ ሠላም ፤ ህዝቡ ሠላማዊ ዕድገትና ብልፅግናው የጋራ ይሆናሉ። አንድነት ይፀናል። ጥላቻ ይኮሰምናል። መተሳሰብ መተዛዘን መደጋገፍ ይጎለብታል። ይህ ሁሉ ቅን ከመሆን ይመነጫልና። ይህ ሁሉ መልካም ልቦናን ይዞ መልካም ለማድረግ ከመነሳት ዕውን ይሆናል። ኢትዮጵያውያንን በዚህ ዘመን የራቀን ቅንነት ነው። መልካም አስቦ ለመልካም መነሳት ነው የሸሸን፡፤ ከፍቅር ሳይሆን ከጠብ ስለምንጀምር ነው አድባር አውጋሩ የተጣላን። አቢይ አበበ ሊነግረን የፈለገው ይኸው ነው። በከንቱነት ኖረን በእብነበረድ ተቀበርንም አልያም ስም አልባ መቃብር ገባን…ያው አስታዋሽ የሌለው ከንቱ ህይወት ኖረን ነው ያለፍነው ማለቱ ነው ጠቢቡ ወታደር።
አቢይ አበበ ለሀገር ዕድገት ጠንቅ፤ ለመልካም አስተዳደር ዕንቅፋት፤ ለህዝብ ብልፅግና ነቀርሳ የሆኑትን ቅልብጭ አድርጎ ሲያስቀምጥና ምክሩንም ሲለግስ ደግሞ እንዲህ ይላል፤-
ምቀኝነት፤ ቅናት፤ ተንኮል፤ ሀሰት፤ ጉቦ፤ ዕምነት ማጉደልና አድልዖ እነዚህ ከቀሩ ማንኛውም ነገር ቀጥ ብሎ በንፁህ መንገድ ሊሄድ ይችላል። እነዚህን ደግሞ ለማስቀረት የሚችለው ንፁህ ህሊና ብቻ ስለሆነ ህሊናችንን ለማንፃት እንታገል።
ስምንት ፤
እነሆ እንግዲህ የመጀመሪያውን መጨረሻ ያለ ቃኚው ምልከታ እናስከትላለንና አንባቢ ሆይ ተበራቺ ፤ አንባቢ ሆይ ተበራታ።
ኢትዮጵያ ትላንት ወይም ዛሬ የተፈጠረች ሀገር የተዘረጋች ምድር አይደለችም። ከእኛ በፊት የነበሩባት ሰዎች ኖረውባት አልፈዋል። የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መሠረት ታሪካችን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአሁኑ ትውልድ እስካለነው ድረስ በሀገሪቷና በህዝቡ ላይ የደረሰውን በጥቂቱ በህሊናችን ውስጥ ብናመላልሰው ለአለንበት ሁኔታ ምክንያት ሆኖ ወደ ሁዋላ ያስቀረንን በአጭር መንገድ ልንረዳው እንችላለን።
እነማን ነበሩ? እነማንስ አሉ? እነማንስ ይኖራሉ? የተወደደችው ሀገራችን ግን ነበረች አለች፤ የምትኖረው ግን እንድትኖር አድርገን ስንይዛትና ስናገለግላት ነው እንጂ እንድትወድቅ ስናንገዳግዳት አይደለም። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ማለትም በአፍአዊ አነጋገር ሳይሆን ከእኛ ከልጆቿ የሚጠበቀው የሆነ ይሁን ማለት ትቶ ሊሆን የሚገባውን መርጦ የሚበጀውን ማድረግ ብቻ ነው።
በሥልጣን ላይ የሚገኝ ሁሉ የገባበትን ቃልኪዳን አክብሮ አስታውሶም ሀገርንና ህዝብን ፤ ማህበራዊ ኑሮን እንጂ ክብሩንና ሥልጣኑን አገልጋይ አይሁን።
ቀደም ካለው ትውልድ የምመጣ ስለሆንኩ በሀገራችን የሆኑትንና ያለፉትን የደረስኩባቸውን አጥርቼ ስለምረዳው የነበረውንና ያለውንም ሳመዛዝነው እደረስንበት ሥፍራና ደረጃ እንደምን እንደሆነ በበኩሌ ደህና አድርጌ እገነዘበዋለሁ።
ይኸውም የሀገር ፍቅር አቃጥሏቸው ደማቸውን ባፈሰሱት ብዙሃን ትጋትና ዕውነተኛ መሥዋዕትነት መሆኑ አይካድም። ባለታሪክ የሆኑት አባቶቻችን የነበረባቸውን ትግልና ድካም፤ የውስጥ ተቃዋሚ ወገንንና የውጪ ጣልቃ ገብ የባዕድ ፖለቲካ በትዕግሥት አልፈው የገነቧትን ሀገራችንን በቅርቡ ተወልደው ፤ ደርሰው ፤ ያዩዋት እንዲህ ሆና የቆየች ትመስላቸው ይሆናል። የደረሱበትንም እንደ አቅሙ የተደላደለ ጊዜ ከመንቀፍ በፊት እንዴት ኖሯል ብሎ ወደሁዋላ የነበረውን ጠይቆ፤ ተረድቶ ያለውን አመስግኖ ስለመጪው መሻሻል ትጋትን አሳይቶ የአሳብ ተካፋይና የሥራ ረዳት ሆኖ በትጋት ማከናወን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፈንታ ስለሆነ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ዕውቀትና ጉልበቱን መሥዋዕት ማድረግ ይኖርበታል።
መሥራት አስቸጋሪ ነው። ማፍረስ ግን በጣም ቀላል ነው። የፈረሰን ደግሞ መልሶ መሥራት ከሁሉ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ያንን የተከፋፈለ አሳብ ያንን የተወሳሰበ መጥፎ ልማድ፤ ያንን የተጨቆነ የህዝብ መብትና ነፃነት ፤ ያንን የተናቀ የገዥነትና የተገዥነት መንፈስ ለማጥፋት ፤ እንደዚሁም ፈርሳና ወድቃ የነበረችወን ውድ አገራችንን እንደገና ለማቋቋምና ከነፃ አህጉሮች ጎን እንድትሰለፍ ያደረጓት ሁሉ ባለውለታዎች ናቸው።
ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ዓይናችንን ከከፈትነው አንዳንዳችን ያልተደረገውን ወደ ሌላ በመተርጎምና ውለታ ቢሶች ሆነን ከመገኘት እርቀን ለሁላችንም ለሀገራችንም የሚበጀውን ብቻ በፍቅርና በህብረት አስማምተን ተደጋግፈንም እፊታችን የተደቀነውን የትየለሌ ተያይዘን በጊዜያችን ልናደርግ የምንችለውን ያህል እንወጣ።
ስለሀገራችን ክብር የተሰዉትንም አፅማቸውም በያለበት የረገፈውን ጀግኖቻችንን ሁልጊዜ እናስታውሳቸው። ስማቸውም በታሪክ ጎልቶ እንዲኖር እናድርግ። ውለታቸውም ይወሳላቸው። ምንም ጀግናን የሚፈጥረው የጊዜው ሁኔታ ነው ቢባልም አዲሱ ጊዜ የሚፈጥረው ጀግና የቀድሞው ጊዜ ጀግና ስምና ታሪክ መነሻና መቀስቀሻ እንደሚሆነው አያጠራጥርም።
እንግዲህ ከዚህም ከዚያም ጠቅሼ የደረደርኳቸው እዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሰፈሩት አነጋገሮች ሊነቀፉም ፤ ሊያስነቅፉም ፤ ሊያከራክሩም ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በማንኛውም ዓይነት ይሁን በንፁህ ህሊና ብቻ በመመራት ወደፊትም የሚጠበቅብንን በመገመት ማንኛችንም ተባብረን ለውድ ሀገራችን የዕውነት አገልግሎት ማበርከት እንዳለብን ማሳሰቤ ነውና “አውቀን እንታረም”
ማሳረጊያ፤
እነሆ የሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበን ታላቅና ክቡር መልዕክት ያዘለውን መፅሀፍ በዘመናችንና በትውልዳችን ካለው ነባራዊ የሀገራችን ፖለቲካዊና ሥነ ማህበራዊ ዕውነታ ጋር እያነፀርን የቃኘንበትን ሥራ ማሳረጊያችን ደረሰ።
የሌ/ጄ አቢይ አበበ “አውቀን እንታረም” ‘መቅድም’ ‘መነሻ’ና ‘መድረሻ’ ይዞ በሶስት ምዕራፍ በ57 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን መፅሀፉ በፖለቲካ፤ በማህበራዊ በአስተዳደርና በለውጥ ላይ ያለው አመለካከት ሰፊ የመሆኑን ያህል ጥቅልና ጥልቅ በሆኑ ንድፈ ሀሳቦችም የተሞላ ነው። አቢይ አበበ መፅሀፉን ለንባብ ያበቃው በብርጌዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይና በወንድሙ ገርማሜ ነዋይ የተጠነሰሰው የ1953 ዓ/ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ (በተለምዶ የታህሳስ ግርግር ይባላል) ከከሸፈ በሁዋላ ነበር። ከጄኔራል አቢይ ‘አውቀን እንታረም’ ሀገራዊና ትውልዳዊ መልዕክትና ተማፅኖ እንደምንረዳው ነውጥን ወይም ደም አፋሳሽ አብዮትን አጥብቆ ይቃወማል።
በኢትዮጵያ የተሞከረው የመጀመሪያው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲከሽፍ ብርጌዴር ጄኔራል መንግሥቱ እና ወንድሙ ገርማሜ ነዋይ በቤተመንግሥቱ ውስጥ አግተዋቸው ከነበሩት የሀገሪቷ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አስራ አምስቱን በጥይት ደብድበው የፈጁዋቸው ሲሆን ከእኒህ ለሀገራቸው ከደከሙ አድባራት አንዱ የጣሊያን ቦንብና መትረየስ ያልጣላቸውና ከነፃነት በሁዋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ክቡር ራስ አበበ አረጋይ ይገኛሉ።
አቢይ አበበ ከሁሉም በላይ በሌሎች ሀገራት ያለን የግራ ፖለቲካና ሥርዐተ መንግሥት እንዳለ ቀድቶ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን መነሳትን ሲቃወም ለኢትዮጵያ ሀገራችን የፖለቲካ፤ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አማራጭ አይደለም ከሚል ፅኑ ዕምነት መሆኑን በገሀድ ያመለክታል። ለዚህም ይመስላል፤ – የሚበጀንን የውጪ ፖለቲካ ከመከተላችን በፊት የሚበጀንን የውስጥ ፖለቲካችንን ማደራጀት የሚገባን እኛው ነን። የውስጥ ፖለቲካው ያልደረጀ ህዝብ ብዙውን ጊዜ ሊከተለው የሚገባውን የሌላውን ሀገር ፖለቲካ አጥርቶ ሊያውቅና ሊጠቀምበት አይችልም። የአባቶች ምሳሌ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ይላል – ሲል ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ አስተማሪ አስተውሎቱንና ምክሩን ያስቀመጠልን።
ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥቱ ተሳትፈው የነበሩትና ሁዋላም ስለዚሁ ታሪካዊ መፈንቅለ መንግሥት ሂደትና ክሽፈት መፅሀፍ የፃፉትም ሆኑ ወይም በዘመኑ የኖሩ የርሱ ትውልድ አካላትና ከርሱ ጋር የመስራት ዕድሉን ያገኙ ሁሉ ስሙንና ምግባሩን በአርአያነት የሚጠቅሱት ሲሆን ታላቅ ሰብዕና፤ ቅንነትና ፍፁማዊ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ስለመሆኑም ምሥክርነታቸው በተለያዩ መፃህፍት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። አቢይ አበበ ከአድልኦ ፤ ጉቦና ከመሳሰሉት የነፃ – የሀገርና የህዝብ ንብረትን ለግሉ ያላዋለ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ ስለመሆኑም ተመስክሮለታል።
እነ ራስ አበበ አረጋይ ያለ ፍትህና ርትዕ ከተጨፈጨፉ ከ14 ዓመት በሁዋላ በመስከረም 1967 ዓ/ም ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መቀመጫ ቤተ መንግሥት በሁለተኛው ዙር ወታደራዊ ስብስብ ስር ወደቀ። ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ/ም በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባላት ጭብጨባና በመሪው በሻለቃ መንግሥቱ ሃይለማርያም ፊርማ እድሜያቸውን ሙሉ ለውድ ሀገራቸው ደፋ ቀና ሲሉ የኖሩትንና በአብዛኛው ከመጀመሪያው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተረፉት የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን ያለ አንዳች ፍትህና ርትዕ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ በታዘዘው መሰረት በጥይት ተደብድበው ህይወታቸው ካለፈው አንጋፋና የሀገር አድባራት ኢትዮጵያውያን አንዱ ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ነው።
ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በደርግ ጥይት ተደብድቦ ሲገደል ዕድሜው 56 ዓመት ነበር። በዚህ ዘመነ ፅልመት ቀን በግፍ ግፍ ከተረሸኑት መካከል ክቡር ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ (ጠቅላይ ሚኒስትር)፤ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን (ጠቅላይ ሚኒስትር) ፤ ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ፤ ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሃብተ ወልድ እና በድምሩ ሃምሳ ሁለት የግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሲገኙ በዚህ ዕለት በድምሩ ደርግ በጥይት ደብድቦ የፈጃቸው ስልሳ ኢትዮጵውያን ናቸው።
በህዳር 14 ቀን 1967 ዓ/ም ያለ አንዳች ፍትህና ርትዕ በኢትዮጵያ ሰማይ የደም ዘመንን የጀመረው ወታደራዊው ደርግ የእኒያን አንጋፋ የኢትዮጵያ አድባራትን ታሪክና ገድል ግን ከሥጋቸው ጋር በጥይት ደብድቦ መቅበር አልቻለም። እነሆ ዛሬ ዘመን በምድረ ኢትዮጵያ ምን እሾሁና አሜኬላው ቢበዛ ከደርግ መንግሥት መሪዎችም ሆነ ከኢህአዴግ እኩይና እርጉም ባለሥልጣናት በትውልዱ እጅግ እየፈኩና እየተከበሩ ስማቸው ከመቃብር በላይ በፍቅርና በክብር የሚነሳው እኒያ ጥንታውያኑ አባቶቻችንና በደርግ ጥይት የወደቁት የጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ሰማዕታት ናቸው።
እነሆ እኛም እድሜ ሰጥቶን ከእኒያ የቀድሞው ትውልድ አባቶቻችን መካከል የሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበን ታላቅና ክቡር የኢትዮጵያዊነት መልዕክት የተላለፈበትን ምጡቅ ስራ ለማንበብ አንብበንም ከምንኖርበት ዘመን አዛምደን ለመመርመርና ለመማር በመብቃታችን ክብር ሞገስና ምሥጋና ለተከበረው አባታችን ለሌተናነት ጄኔራል አቢይ አበበ ይሁን እንላለን!! ስምህ ከመቃብር በላይ በፍቅርና በአክብሮት ከኢትዮጵያ ጋር በትውልድ ሁሉ ሲወሳ ይኖራልና!
እንግዲህ ማሳረጊያችንን የምንቀነብበው በጠቢቡ አባታችን በሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ቃል ይሆናል።
የእኛ ነገር ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንደሆነ ደህና አድርገን እናውቃለን። ስለዚህም ዞረን ዞረን የምንገባባትን ሀገራችንን ቤታችንን፤ ኖረን ኖረን የምንቀበርባትን መሬታችንን እንደዋዛ አንያት። ሁላችንም ነገ ጥለነው ለምንሄደው ነገር አንጓጓ። ሀገራችንን ካልን የሀገራችን ነገር ከሁሉ በፊት ይቅደም። ሀገራችንን ካልን ደግሞ ይዘን እናሻግራት፤ እንጠብቃት፤ ከልብም እንውደዳት፤ አንድነትም ሆነን እናገልግላት፤ ከእኛ በሁዋላ ለሚመጡትም ሀገራቸው ሆና እንድትቆይ እንድትወራረድም አድርገን እንያዛት።
ሰው በሰው ክፉ መሆን አይገባውም። በተለይም የአንድ ሀገር ሰዎች የአንድ እናት ልጆች ማለት ነንና መተዛዘን መተሳሰብና መፈቃቀርን ማወቅ ግዴታችን አድርገን እንያዘው።
ወንድም በወንድሙ ላይ በከንቱ አይነሳ። የከንቱ ነገርንም ምንጭ አይቆፍር። እያንዳንዱም ሊቅ አፉን ይክፈት፤ በጎ ምግባርናን የሀገር ፍቅርን ከመናገር ከመስበክ አይቦዝን።
ሁላችንም እናልፋለን። ይህንን የማያምን ቢኖር የነበሩ እነማን አሉ? ማለፋችንን ካመንን ስለምን በቀና መንገድ አንሄድም? ስለምንስ ቅን ሰርተን አናልፍም?
——————————– // ተ ፈ ፀ መ // —————————–
ተፃፈ፤ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ 26ኛ ዓመት ግንቦት 2009 ዓ/ም (ሜይ 2017)
ሲድኒ አውስትራሊያ
ለአስተያየት፤- mmtessema@gmail.com
- በዚህ ቅኝት ውስጥ በቀረቡት የሌ/ጄ አቢይ አበበ መልዕክቶች ላይ የሚገኙት ሰረዞችና ደማቅ ፅሁፎች የቃኚው ትኩረት ናቸው።
Merafu Ygelet says
የእውነተኛ መልዕክት ጥሪ ደወል
ለኦርቶዶክሳውያን አማኞችና አገልጋዮች እንዲሁም ለወንጌላውያን የፕሮቴስታንት አማኞችና አገልጋዮች በሙሉ የተላለፈ
ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንድንኖር ለኅብረት ጠራን እንጂ ለመቀመጫና ለወንበር አልጠራንም በመሆኑም መጽሐፍቅዱሳችን በመቀመጫ ምክንያት ለጉዳት የተዳረገውን አንድ ሰው ያስታወሰናል እርሱም ካህኑ ኤሊ ነው ከመቀመጫው ውጪ ስለሌላ ነገር ደንታ የሌለው ዔሊ ለእግዚአብሔር ለአምላኩ ተገቢ ያልሆነውን ምላሽ በመስጠት እርሱ እግዚአብሔር ነው ደስ ያሰኘውን ያድርግ እያለ በዚያው በተናገረው የአፉ ቃል ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ እርሱ ሸምግሎ ደንዝዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ ይለናል 1ኛ ሳሙኤል 3 ፥ 18 ፤ 1ኛ ሳሙኤል 4 ፥ 18 ታድያ ይሄ የናፈቅነውና በይገባኛል መንፈስ ተሟሙተንና ከሌላውም ጋር ተሻኩተን ፣ ከአንዳንዶችም ተጣልተን ፣ ስማቸውንም ሳይቀር አክፋፍተንና አሳደን ያገኘነው ወንበር በአግባቡ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ካላሳለፍንበት መልሶና ለእኛውም ጠላት ሆኖ እኛኑ ያጠፋናልና እናስብበት እላለሁኝ ከዚህ በመቀጠል ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንድንኖር ለኅብረት እንጂ ለመቀመጫ እንዳልጠራን የሚገልጹ መጽሐፍቅዱሳዊ ጥቅሶችን አስቀምጣለሁ ወደ ማንም ሳንመለከትና ማንንም ሳንከስ ፣ ጣታችንንም በማንም ላይ ሳንጠቁም 1ኛ ሳሙኤል 15 ፥ 21 _ 23 ወደራሳችን ብቻ በመመልከት እግዚአብሔር በሚፈልገው ኑሮና ትክክለኛ ኅብረት ውስጥ መግባት ይሁንልን
ጥቅሶችን እንዲያነቡ እነሆ ብያለሁ
የማርቆስ ወንጌል 3 ፥ 13 እና 14
የማርቆስ ወንጌል 10 ፥ 35 _ 45
1ኛ ዮሐንስ 1 ፥ 1 _ 4
ይህ ሃሳብ በክፍል ሁለት የሥዕል ትምህርት በአጭሩ ከተማርነው ለማስታወሻነት የተወሰደ ነው
ሰኞ በተለመደው ሰዓት ለትምህርቱ በፌስቡክ ላይቭ መስመር ላይ እንገናኝ
ተፈጸመ
Merafu Ygelet says
እግዚአብሔር ሙሴን ሁለት ኪሩብ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ ማለቱ
ክፍል ሁለት
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የክፍል ሁለት ትምህርታችንን ጀምረናል ጌታ እግዚአብሔር ሦስት ታላላቅ መመርያዎችን ለሙሴ ነግሮት ነበር
1ኛ ) ከግራር እንጨት ታቦትን ይሥሩ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን …………………..ዘጸአት 25 ፥ 10 _ 17
2ኛ ) ሁለት ኪሩብ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ በሥርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ ……………….. ዘጸአት 25 ፥ 18 እና 19
3ኛ ) በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ እኔ እንደማሳይህ ሁሉ እንደ ማደርያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ እንዲሁ ሥሩት አለ ዘጸአት 25 ፥ 8 እና 9 ተመልከቱ
ውድ ወገኖቼ ሆይ ታድያ ጌታ እግዚአብሔር ለምን ይሆን ? ታቦት ሥሩልኝ ፤ ኪሩብ ሥሩልኝና መቅደስ ስሩልኝ ሲል መናገሩ ? እኛም እነዚህ ሦስት ዓበይት ሃሳቦች በቃሉ ላይ ስለተጻፉ ዛሬም ሆነ ከዚህ በኋላ በቀረው ዘመናችን ታቦትን ፤ ኪሩብንም ሆነ መቅደስን መስራት እንዳለብን ከእኛ ይጠበቃል ? ለዚህ መልሱ አንድና አንድ ነው እርሱም ጌታ እግዚአብሔር ታቦት ሥሩልኝ ፤ ኪሩብ ሥሩልኝና መቅደስ ስሩልኝ ሲል የተናገረውና መመርያንም የሰጠው ለእነ ሙሴ ነው እኛን አይደለም ስለዚህ ታቦትንም ሆነ መቅደስንና ኪሩብን እንድንሰራ ለእኛ የተፈቀደ ነገር አይደለም እኛም እንድንሰራ አልታዘዝንም ሌላው ደግሞ እግዚአብሔር ታቦትን ፤ መቅደስን ፤ ኪሩብን ሥሩልኝ ማለቱ እስከ ዛሬ ድረስም ሆነ ከዛሬ በኋላ ባለው ለወደፊቱም ይህንኑ ታቦት ፤ መቅደስና ኪሩብ እየሠራችሁ በነዚህ ነገሮች አምልኩኝ ፤ ስገዱልኝ ፤ አክብሩኝ ለማለት አይደለም እንደውም በዚህ ነገር ውስጥ ኖረው የሚያመልኩት ሰዎች አምልኮአቸው አስጸያፊና የጣኦት አምልኮ እንደሆነ ነው ቃሉ የሚነግረን ትንቢተ ሕዝቅኤል 8 ፥ 7 _ 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር መቅደስን ፤ ታቦትንና ኪሩብን ሥሩልኝ ሲል መናገሩ በዘጸአት 25 ፥ 21 እና 22 ፤ በዘኁልቁ 7 ፥ 89 መሠረት ታቦቱ ላይ ካለው ከሥርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል አምላካችን የሆነው እግዚአብሔር ድምጹን ለማሰማት ነው በአጠቃላይ ለግንኙነትና ለኅብረት ነው ስለዚህ እነዚህ ሦሰት ዋና ዋና ነገሮች ማለትም ታቦቱ ኪሩቡና መቅደሱ የተፈለጉት ለእግዚአብሔር የግንኙነቱ መስመር መንገድ እንዲሆኑ ነው ዛሬ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የግንኙነት መንገዱም ሆነ መስመሩ ክርስቶስ ሲሆን እግዚአብሔርም በዚህ ጌታ አማካኝነት ከእኛ ጋር ሆኖአል ክብር ለስሙ ይሁንለት ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 14 ፣ የማቴዎስ ወንጌል 1 ፥ 23 ፣ ራዕይ 21 ፥ 3 እና 4 ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 3 ፥ 16 እና 17 ፣ የሐዋርያት ሥራ 7 ፥ 47 _ 50 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይህንን የተቋረጠውን ግንኙነት መቀጠል የፈለገው የመጀመርያው ሰው አዳም በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ካበላሸበት ጊዜ ጀምሮ ነበር ታድያ አዳም ሆይ ወዴት ነህ ? ሲል በገነት ውስጥ መፈለጉ እግዚአብሔር የነፍስን ጥፋት አይወድምና ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ ማሰቡን የሚያመለክተን በመሆኑ አምላካችንን በብዙ እንድናመሰግነው እንሆናለን በሐዲስ ኪዳንም ኢየሱስን የላከልን ከጠፋንበት ፈልጎ ሊያገኘንና ከራሱ ጋር ኅብረት እንድናደርግ ሊያደርገን ነው የሉቃስ ወንጌል 15 ፥ 4 _ 9 ፣ የሉቃስ ወንጌል 19 ፥ 1 _ 10 እንመልከት ስለዚህ የእግዚአብሔር መሠረታዊ ሃሳቡ ተዘጋጅተው የቀረቡለት ሥዕልና ታቦት እንዲሁም ቤተመቅደስ ሳይሆን በእነዚህ በተፈለጉትና ይሠሩልኝ በተባሉት ነገሮች በኩል ከሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ነው በሐዲስ ኪዳን ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ በኢየሱስ በኩል ዘለዓለማዊ ሆኖአል በመሆኑም ስለ ኅብረት ስናስብ ብዙ የሆኑ አዳማዊና አሮጌ የሆነ አስተሳሰባችንን እንድንለውጥ ትምህርቱ ይጠቁማል ጌታ የጠራን ለኅብረት ነውና ታድያ ውድ ወገኖቼ ሆይ ጌታ ለኅብረት ሲጠራን በማርቆስ ወንጌል 3 ፥ 14 መሠረት ከእርሱ ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ስለሚል ………………….. ከአገልግሎታችንና ከስሞቻችን በፊት በቅድሚያ ከእርሱ ጋር መኖርን መውደዳችንን እንድናስቀደም ነው እንደገናም የተጠራነው ለአገልግሎት ሳይሆን በመጀመርያ ለኅብረት ስለሆነ ከእርሱ ጋር የሚኖረን ኅብረት ትክክለኛ የሚሆነው በአገልግሎት ጉዞ ውስጥ ሳይሆን ከእርሱ ጋር በመኖር ውስጥ ነው ስለሆነም ከእርሱ ጋር በመኖራቸው ምክንያት ደቀመዛሙርት የትላንት አሮጌ አስተሳሰባቸውን ማለትም ከመካከላችን ማነው ታላቅና አንዳችን በግራ አንዳችን በቀኝ መቀመጥን ስጠን የሚሉትን ፣ ሌሎችንም ምድራዊ አስተሳሰባቸውን ጥለው ጌታን አይተነዋል ለማለት የበቁት ቅድሚያውን ይዘውና የኃላፊነቱንም ቦታ ተረክበው ስላገለገሉ ሳይሆን ከሕይወት ጅማሬያቸው አንስተው ከጌታ ጋር መኖርን ስላስቀደሙ ነው አያይዘውና ቀጥለውም በዓይኖቻቸን ያየነውን የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን ይህንን ጌታ እናወራላችኋለን ሕይወት ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን አሉን 1ኛ ዮሐንስ መልዕክት 1 ፥ 1 _ 4 ለእኛም እንዲህ ይሁንልን የክፍል ሦስት የሥዕል ትምህርት ይቀጥላል ተባረኩ ሰላም ሁኑ