ቀልድ ሲነሳ አስቂኝ ሶስቱ ድንቅ ተዋናዮች አለባቸው ተካ፣ ልመንህ ታደሰና አብርሃም አስመላሽ በልዩ ችሎታቸው ለእኔ እና ለብዙዎች ከፍ ያለ ቦታ አላቸው። ነፍሱን ይማረው አለባቸው ተካ ድሃ እንደደገፈ በአሳዛኝ የመኪና አደጋ አለፈ! ህይወቱን ለጥበብና በፋና ወጊ መልካም ተግባር ተሰልፎ ሲያሳልፍ ተስገብግቦ ሃብት አላካበተምና ለእሱና ለቤተሰቦቹ የረባ ጥሪት ሳይጥል አለፈ … መልከ መልካሙ ልመንህ ከምድረ አሜሪካ አዕምሮውን ስቶ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኖ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች ይንከራተታል … የሙያ አጋሮቹ ከምድረ አሜሪካ ያደረጉት ሁሉ ትብብር ቢሳካ ኖሮ ልመንህ ዛሬ ድኖ እናየው ነበር፣ ግን አልሆነምና በናኘበት ከተማ ራሱን ጥሎ ነሁልሎ ማየቱ ልብ ይሰብራል፣ ያሳዝናል! አንዳንድ ወዳጆቸ ልመንህን ለመደገፍ በግል ከሚደረገው ጥረት ባለፈ በተቀናጀ መልኩ እርዳታ እንደማይደረግለት አጫውተውኛል፣ ለዚህም ምክንያቱ የህምሙ ክፋት እንደሆነ የገለጹልኝ ሃገር ቤት ያሉ የሙያ አጋሮቹም ቢሆንም ለከፋው ህመም መላ ማጣታቸውን ይናገራሉ … ብቻ ልመንህም እንዲህ ሆኗል … አዕምሮውን የሳተ በየጎዳናው ተንከራታች … ክፉ ጊዜ ….
አዱ ገነት ተወልዶ አድጎ ለዛ ያለውን የሃገር ቤት የገጠር ቃና ንግግርን በግ ለመሸጥ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡ ከበግ ነጋዴዎች ተለማምዶ ሲናገረው ገጠር ተወልደው ያደጉትን ያስንቅ ነበር፣ ከገጠር መጥተው የገጠሩን አነጋገር ወደ ከተምኛው ለመቀየር ሲደነባበሩ አዲስ አበቤው የተገላበቢጦሽ የእነሱን የአነጋገር ዘይቤ ተክኖና ተውቦ አገር ምድሩን በፈጠራው ሲያስቀው ድንቅ ችሎታ ነበረው። አብርሃም አስመላሽ … በአንድ ወቅት ከአብርሃም ጋር ተገናኘተን ከቀልድ ያለፈ የጨዋታውን ለዛ ኮምኮሜዋለሁ! መልካም ሰብዕናም እንደ ነበረው ወዳጆቸና ወዳጆቹ አጫውተውኛል! አብርሃም አስመላሽ …
አብርሃም ወደ ጀርመን ሃገር ሄዶ ህክምና እንዲያገኝ ትልቁን ድርሻ ለተወጡት የሙያ አጋሮቹ ላደረጉት ትብብር አድናቂዎቹ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው … ዛሬ አንድ መረጃ ደረሰኝና ከምስጋናው አልፌ ብዙውን አውጥቸ አወረድኩ … አብርሃም የመሞቱን መሪር መርዶ ከሰማን እያለፈ ባለው ሳምንት ውስጥ ጥቅምት 21 በእለተ ማርያም 2013 ዓም ነው! ከዚያች ቀን ወዲህ የአብርሃምን ሬሳውን ወደ ሃገር ቤት ለመውሰድ የገንዘብ ድጋፍ እርዳታ መጠየቁን ሰምቻለሁ … እናም የጥበብ ሰዎች መጨረሻ አሳሰበኝ! … ወገን ለወገን ነውና የአብርሃም ሬሳ የሚወዳት ሃገሩ አፈር ትቀምስ ዘንድ ሁላችንም የእርዳታ እጃችን ብንዘረጋ መልካም ነው በሚል በሳውዲ ነዋሪ አሳሳቢ ከሆነው የምህረት አዋጅ ማለቅ ስጋት ወጣ ብየ ይህችን ማስታወሻ ሞነጫጨርኩ …
ከአብርሃም ሳልወጣ ቀጠልኩ. .. ከሬሳው ማመላለሻው እርዳታ በኋላስ? ብየ ለራሴ አልጎመጎምኩ … እሱም እንደ ኮሜዲ አለባቸው ከወደ ኋላ ጥሏቸው የሄዱ ቤተሰቦች እንዳሉት ሰምቻለሁ … እናም የእነሱም መጻኤ እጣ ፋንታ በእኛው ካልተደገፈ መላ አይኖረውም … በሚል ጀምሬ ምናል የኪነ ጥበብ ሰዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲህ እያለፉ ስላሉ ብርቅየ የሃገራችን ልጆችን እና ቤተሰቦችን ቢታደጓቸው? ቢያንስ ለኪነ ጥበብ አፍቃሪ አድናቂዎቻቸውን በተነሳሽነት በማሰባሰብ የድጋፍ እርዳታ ቢያሰባስቡላቸው ስል ማሰቤ አልቀረም! ቅድሚያ ድጋፉ ከሙያ አጋሮች ቢጀምር አልኩና ራሴን ያዝ አደረግኩት … ብዙ ከእርዳታ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ታወሱኝ!
የእርዳታ ነገር ሲነሳ በርካታ የከሸፉ ሙከራዎችን አይረሱኝም፣ አለም ደቻሳ ሊባኖስ በኢትዮጵያ ቆንስል በር በአንድ አረብ “ጀብራሬ” እየተጎተተች ባየናት በጥቂት ቀናት ልዩነት ራሷን ገደለች አሉን … ከወራት በኋላ ጥላቸው የሔደቻቸውን ልጆች ለመርዳት በተጠራው አለም አቀፍ አርዳታ ለተጠራው እርዳታ የተገኘው ምላሽ አያኮራም! እዚህ ሳውዲ በርካቶች ለከፋ ችግር ሲዳረጉ በግል የሚደረጉትም ሆነ በማህበራዊ ገጾች ለሚጠራ እርዳታ የሚሰጠው ምላሽ ያሸማቅቃል … ያን ሰሞን ለአመታተ በብዕራቸው አገር ያስደመሙ ሁለት ኩሩ የስነ ጽሁፍ ሰዎች በየተራ መታመማቸውን በሰማን … የጋዜጠኛ ጸሃፍት ባልደረቦዎቻችን መታመም ካንገበገባቸው ወንድሞች እርዳታ ይሰበስቡ ከነበሩት መካከል አንዱ ወዳጀ እንደ ጨው የተበተንን የዚያች ሃገር ጋዜጠኞች ዘንድ እርዳታና ድጋፍ አገኝ ብሎ ከአውሮፖ አሜሪካ በመላላክ ሲባትል ያተረፈው ድካም ብቻ ሳይሆን የሰውን ጭካኔ መሆኑን አጫውቶኛል። ይህንን አሳዛኝ ገጠመኝ ያጫወተኝ ወዳጀ መጨካከናችን አስታውሶ ያቀበለኝ መረጃ ተስፋ ባያስቆርጠኝ ሳያሳዝነኝ አልቀረም! ብቻ ጊዜው ተበላሽቶ ጨካኞችን እያወገዝን ጨቋኞች መሆናችን ዘልቆ ቢያደማም ተስፋ መቁረጥ ከቶ አይገባም …
አዎ ካለፈው ልንማር ከቻልን ዛሬ በመልካም ነገር ማስቀጠል እንችላለን! ዛሬ የብርቅየውን ኮሜዲ የአብርሃም አስመላሽን ነፍስ ይማር ስንል በስሙ ለተጠየቅነው እርዳታ እጃችን እንዘርጋ ዘንድ ግድ ይለናል! አስተባባሪዎችም ግልጽ የሆነ እርዳታ ማሰባሰብ አድርጉ፣ የስልክ የባንክ አድራሻና ሌላም ተገቢ መረጃዎችን ስጡ! አበው “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው!” እንደሚሉት ነውና የቻለ እንዳቅሙ ይርዳ … ይህ መሰሉ እርዳታ ወገንተኛነታችን እና ሰብዕናችን እናሳይበት እንደሁ ማለት እንጅ ሰው ሰጥቶ፣ ደግፎ አያጠግብም … ሰጥቶ እና ደግፎ የሚያጠግብ አንድ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው … የቻልን እንለግስ …አንድየ ሁሉንም ያያል ለሰጭ ይስጠዋል እናም እንረዳዳ! ስቀው ያሳሳቁን፣ በርተው የጠፉ የጥበብ ሰዎች እና መጨረሻቸው እንዲህ ሲሆን ማየቱ ቢያምም ከታደግናቸው ልናሽረው የምንችለው ቁስል እንዳለ አንዘንጋ ስል የማለዳ ወጌን ቋጨሁ!
ለቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ … የሟችን ነፍስህን ይማር !
ነቢዩ ሲራክ
Leave a Reply