ታላላቅ ረሀቦች ተብለው በዓለም ታሪክ ከሚዘከሩት ውስጥ የቻይናውያን ረሀብ ኣይዘነጋም። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1958-1961 ድረስ ቻይና ውስጥ ከፍተኛ ረሀብ ተከስቶ ወደ ሰላሳ ሚሊዮን ህዝብ ረግፏል። ብዙ ምሁራን እንደሚሉት ለዚህ አስከፊና ቻይናውያን ሊረሱት ለማይችሉት ረሀብ አንደኛ ተጠያቂ ማዖ ዚዳንግን ነው። የኮሙኒስት ፓርቲ መሪ የነበረው ማዖ ዚዳንግ በሶቪየት ህብረት በነጆሴፍ ስታሊን አብዩት ፍቅር የከነፈ ሲሆን ቻይናን በአምስት ዓመታት ውስጥ ከሁዋላ ቀር ግብርና አውጥቼ ወደ ኢንዱስትሪ እለውጣታለሁ በማለት Great Leap Forward ታላቁ የግስጋሴ ርምጃ የተሰኘ የአምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፎ አመጣ። እቅዱ የግል የመሬት ባለቤትነትን የሚጻረርና የወል እርሻን የሚያራምድ ነበር። በዚሁ እቅድ መሰረት ቻይናውያን በፍጥነት እየተደራጁ የወል እርሻ ሥራን ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ እቅዱ እንደተቋመጠለት ሳይሳካ ቀርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገላቢጦሽ ችግር አመጣና ቻይናውያንን አስርቦ ቁጭ አለ። ዛሬ ላይ ያን ረሀብ የGreat Leap Forward ረሀብ ይሉታል።
በማዖ ዚዳንግ ጊዜ ቻይናውያን በጋራ እርሻ ከጀመርን ነው የምናድገው ተብለው የግል እርሻ በሰፊው ማካሄድ ተከልክሎ ስለነበር አልፎ አልፎ ጓሮ አካባቢ ትንሽ አትልክት ቢጤ ከማሳደግ ውጭ መሬት ሁሉ የጋራ ሆኖ በጋራ ማረስ ተጀመረ። ከፍተኛ የሰው ኃይል ደግሞ ከግብርናው ተቀንሶ ወደ ብረት ማቅለጥ ሥራ እንዲሄድ ታዞ የብረት ማቅለጥ ሥራ ተጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ እቅዱ ቀቢጸ ተስፋ የሞላውና የግል መብቶችን የጣሰና የግል ንብረት ባለቤትነትን የሰበረ በመሆኑ ከፍተኛ ሶሺዮ ኢኮኖሚክ ኪሳራን አመጣና ወዲያው ከሸፈ። እንደታሰበው ምርታማነትን ሳያሳድግ ቀርቶና በተቃራኒው ሄዶ ብዙ ሰው ጨረሰባቸው። ታዲያ ቻይናውያን እድለኛ ሆነው የድህረ ማዖ መሪዎች ለዛች ኣገር የኢኮኖሚ እድገት የተሻለ ፖሊሲ አምጥተው ማደግ ችለዋል። እነሆ ዛሬ ቻይና ድህነትን ለመቀነስ ባደረገችው ጥረት ከዓለም አንደኛ ናት። በዓለማችን ታሪክ ውስጥ መጠናቸው ይብዛም ይነስም ከፓሊሲና ከመልካም ኣስተዳደር ብልሹነት የተነሳ ሰዎች በረሀብ አልቀዋል።
ዩክሬን ውስጥ ከ 1932-1933 ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በርሀብ ያለቁት ጆሴፍ ስታሊን ባወጣው የኣምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደሆነ ብዙ ምሁራን ይስማማሉ። ከ 1932-1933 ጊዜ ውስጥ፣ በዚህች ኣጭር ጊዜ ወደ ኣስር ሚሊዮን የሚጠጉ ዮክሬናውያን በረሀብ ኣልቀዋል። ህጻናት ዋይ ዋይ እያሉ፣ አረጋውያን እያቃሰቱ በሳይቤሪያ በረሀ ሳይቀር በየሜዳ የቀሩበትን ይህን ክፉ ጊዜ ዮክሬናውያን በቋንቋቸው ሆሎዶሞር (Holodomor) ሲሉ ይዘክሩታል። በአማርኛ በረሀብ መግደል ወይም ሰውን በችጋር መጨረስ እንደ ማለት ነው። ረሀቡ ሰው ሰራሽ ነው፣ የስታሊን የአምስት ዓመት ትራስንስፎርሜሽን እቅድ ውጤት ነው ብለው የዩክሬን ሰዎች ኣምርረው ኮንነውታል። በርግጥም ዮክሬናውያን ይህን ለማለት ይገባቸዋል። በጣም የከፋው ነገር ደግሞ ከፖሊሲው መክሸፍ ባሻገር ረሀብ በተከሰተበት ወቅት ስታሊን የውጭ ርዳታ እንኳን እንዳያገኙ በተለያየ መንገድ ተጽእኖ ፈጥሮ ነበር። ረሀብ ያለባቸው አካባቢዎችም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ እንዳይዘዋወሩ በመከልከሉ የጉዳቱን መጠን ኣስፍቶታል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፕሮሸንኮ በርሀብ የሞቱትን ሰዎች በመታሰቢያ ሀውልቱ ስር ሲያስቡ።
በርግጥ ይህ አሁን የምናወራው ረሀብ ከብዙ ዓመታት በፊት ያለ ነው። ዛሬ የሰው ልጅ አይራብም። ቢያንስ እጅግ ብዙው ዓለም በምግብ ኣይቸገረም። ወደኛው ቤት ስንመለስ ግን በሃያ ኣንደኛው ክፍለ ዘመን እንደነ ስታሊንና ማዖ ዚዳንግ የኢትዮጵያ መንግሥት ያመጣው የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተባለው በመጨረሻ ይሄውና ኣስር ሚሊዮን ህዝብ ለረሀብ ኣጋልጦ ቁጭ ብሏል። ዩክሬናውያን ስታሊን በችጋር ገደለን ሲሉ ሆሎዶሞር እንዳሉት እኛም የመንግሥት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ኢትዮጵያውያንን ኣስርቦ እየገደለብን ነው።
ለዚህ ረሀብ ምክንያቱ ምንድን ነው? ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት ሮጦ ድርቅ እኮ ኣውስትራሊናያ ካሊፎርኒያም ገባ … አልሰማችሁም እንዴ?. . . ይላል። የውቅያኖስ ውኃ ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣ የኣየር ንብረት ችግር ኤሊኖ የተባለ የአየር መዛባት ያመጣው ችግር ነው ብለው ያብራሩልናል። ኤሊኖ ሆኖብን ነው እንጂ የኣምስቱ ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ኣገራችንን ትራንስፎርም ኣድርጓል ይሉናል። ብንራብም በጥንድ ቁጥር እያደግን ነው ሲሉን ደግሞ ግራ የተጋባው ዜጋ እነዚህ ሰዎች የሚያወሩት ስለ ሌላ ሀገር ይሆን? እያለ ይደመማል። ወይስ እኔ የምኖርባትን ይህቺን ኢትዮጵያን የሚመለከት ነው? እያለ ይገረማል።
ኣስር ሚሊዮን ህዝብ ረሀብ ላይ ወድቆ ስናይ ማንን ነው የምንወቅሰው? ተፈጥሮን ነው? በርግጥ ኢትዮጵያ አፈርና ውኃ የላትም ወይ? የሚል ጥያቄ እናነሳለን። በመሰረቱ የአገራችን ረሀብ መቶ እጅ ከፖሊሲ ችግር የመጣ ነው። ከአመራር ችግር የመጣ ነው። ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ከምሥራቅ ኣፍሪካ ሀገራት የውኃ ገንዳ የምትባል አገር ናት። ውኃ ሞልቷታል እየተባለች በሌሎች ኣፍሪቃ ሀገራት ይቀናባታል። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ከሀገሪቱ ሆድ ሞልቶ የሚተርፍ ነገር ማምረት የሚያስችል ለም መሬትም አላት። ይሁን እንጂ ድሮም ቢሆን የብዙ ገበሬዎችን ህይወት ካበላሸው የመሬት ፖሊሲ ጀምሮ ያለንን የከርሰ ምድር ውኃና ወንዞች በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላችን እነሆ ዝናብ ጸጥ ሲል ለረሀብ ተጋልጠን ቁጭ እንላለን። አፈርና ውኃ እያለን መራባችንን ስናይ በርግጥ የኛ ሀገር ረሀብ ከአመራር ችግር ጋር ብቻ መያያዙን በሚገባ ያሳየናል።
አሁን ያለንበት ዘመን የሰው ልጅ የሚራብበት ዘመን አይደለም። ቴክኖሎጂ አድጎ ረሀብን ጉልበቱን ሰብሮታል። የከርሰ ምድርን ውኃን አየሳቡ፣ መስኖ እያለሙ፣ የተለያዩ የእርሻ ግብዓቶችን እየተጠቀሙ አገሮች የምግብ ዋስትናቸው ከቶ ኣሳሳቢ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ኣሁን ይህ ዘመን ስለ ምግብ ሳይሆን ስለ ቴክኖሎጂ፣ ስለ የተሻለ ህይወት፣ ስለሌሎች ፕላኔቶች የሚታሰብበት ዘመን ነው። በዚህ ዘመን የሚራብ ህዝብ መንግሥት የሌለውና በጦርነት ምክንያት ህዝቡ ማምረት ካቆመ ነው። መንግሥት ያለበት አገር አይራብም። ለምሳሌ ያህል ሶርያን ብናይ ፕሬዚደንት ኣሳድ ወደ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ክፍል መቆጣጠር ኣልቻለም ነበር። ይህ ሰፊ የሀገሪቱ ክፍል ከኣሳድ እዝ ውጭ ቢሆንም ኣሳድ ደማስቆ ላይ ቁጭ ብሎ ግድ የለውም። ኣንዳንድ ከተሞች እርዳታ እንኳን እንዳይደርስላቸው የጦርነት ቀጣና ሆነው ብዙ ሰው በአጥንቱ እስኪቀር ተርቧል። ኣሳድ ሰማኒያ በመቶ የሶሪያን ግዛት ኣጥቶ፣ በሶሪያውያን ስደት በተባበሩት መንግሥታትት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ፣ ኣውሮፓውያን፣ ዓለም ባጠቃላይ ተጨንቀው ስደተኛውን ምን እናድርገው? እያሉ ኣስሬ ስብሰባ ሲጠሩ፣ ዓለም በሶሪያ ስደት ስትናወጥ ኣሳድ ደማስቆ ቤተመንግሥቱ ቁጭ ብሏል። ይገርማል። ዲክቴተርስ ምን ያህል ግድ የለሽ እንደሆኑ ከግል ጥቅም ባሻገር ለብዙሀኑ እንደማያስቡ ያሳይል።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ ያለፈው ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአገሪቱ ውስጥ በመስኖ ሊለማ ከሚችለው ኣምስት በመቶ እንኳን ሳያለማ ገበሬውን እንደ ጥንታዊ ዘመኑ የዝናብ ጥገኛ ኣድርጎ ለኪሳራ መዳረጉ ሳይበቃው እንደገና ሁለተኛ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተብሎ መጣ። እቅዱ የገበረውን የመሬት ችግር የማይፈታ ሆኖ ይታያል። የኣምስቱ ዓመት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ልክ እነስታሊን የወደቁበትን ይመስል በኢትዮጵያም በውጤቱ ኣገሪቱን ወደ ተሻለ ህይወት ከመምራት ወደ ርሀብ ሲወስዳት ይታያል። ረሀቡ ደግሞ የእለት እንጀራ ብቻ ሳይሆን የሚጠጣ ውኃንም ይጨምራል። የከርሰ ምድር ውኃችንን ለእርሻ ልማት መጠቀም አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን እቅዱ የመጠጥ ውኃ እንኳን ኣሳጣን። ይሄ ተሀድሶ ሊባል አይችለም። ዛሬ አንዳንድ ቦታዎች የሚታየው የጀሪካን ሰልፍ መንግሥትን ኣያሳፍረውም። ይህ ረሀብና በምግብ ራስን አለመቻል የተከሰተው ከመንግሥት የፖሊሲ ችግር ጋር የተያያዘ ነው የሚያስብለን ዋነኛ ምክንያት ኣንደኛ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ገበሬ ውስጥ ወደ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ገበሬ ከፍ ያሉ ቦታዎች የሚኖር ሲሆን ይህ ገበሬ የመሬት ባለቤትነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር የበሬ ግንባር የምታክልን መሬት እያረሰ ይኖራል። በአማካይ አንድ ሄክታር መሬት ነው የሚያርሰው። መንግሥት ይህንን ሰፊ ህዝብ በዚህ መልኩ እንዳይንቀሳቀስ ኣፍኖ ይዞ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅታ ቦታዎች አካባቢ ያለውን ለም መሬት ለመሬት ቅርምት ዳርጓል። እነዚህ ሁለት መሰረታዊ የግብርናው ችግሮች ያለንን ሪሶርስ ተጠቅመን ረሀብን እንዳናሸንፍ ኣድርጎናል። ለረሀብ ኣጋልጦናል። በሌላ በኩል መንግሥት የምከተለው የእድገት ኣቅጣጫ ግብርና መር ነው ይበል እንጂ በተግባር ግን በብልጭልጭ (glitz economy) እድገት የተለከፈ ነው። ለታይታ የሚሆኑ ነገሮችን ሰርቶ “በጥንድ እያደግን ነው” አጨብጭቡ ማለት ለስልጣን እድሜ ይቀጥላልድ ክመትን ይሸፍናል ብሎ ያምናል።
በመሰረቱ አገሮች ሁሉ የዝናብ ሁኔታ ስለተመቻቸላቸው ኣይደለም ከርሀብ ያረፉትና ዜጎቻቸውን ያላሥራቡት። ለምሳሌ ግብጽን ብንወስድ ይህቺ ኣገር በዝናብ ኣትደገፍም። የሷ ድጋፍ መስኖ ነው። ከሀገሪቱ መሬት ዘጠና እጅ የሚሆነው በረሀ ነው። ለምንም ኣይሆንም። ለእርሻ ከሚሆነው ጥቂት መሬቷ ውስጥ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሚሆነው በመስኖ የሚለማ መስኖን የተደገፈ ነው። በመሆኑም በየዓመቱ አንጋጣ የምትጠብቀው የለምና ያለ ኣሳብ ከመስኖ ልማቶቿ ቀለቧን ታፍሳለች። ራሷን ከመቻል ኣልፋም እነሆ ዛሬ ለእኛ ለርሀብ ማስታገሻ የሚሆን ወደ ኣንድ ሚሊዮን ዶላር ለገሰች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛው ግብርና መር ፖሊሲ ኣለኝ በሚል ነው። ግብርናን ተገን ኣድርገን ነው ወደ ኢንዱስትሪ የምናድገውና ጥርመሳ ውስጥ የምንገባው ይሉናል። በመርህ ደረጀ ብዙ ሰው ይስማማል። በርግጥም በኛ ሁኔታ ግብርና መር የልማት ስትራተጂ ነው የሚያስፈልገን። ታዲያ በተግባር ግብርና መር ማለት ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ሩብ ምእተ ዓመት የስልጣን ዘመን በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬት ጥርግ ኣርጎ መጠቀም ሲቻል ነበር። እስካሁን የለማው ኣምስት በመቶ ኣለመሙላቱ የሚያሳየው ግብርናው ላይ ትኩረት ኣለመደረጉ ነው። ወሎ ውስጥ በመስኖ ሊለማ የሚችል በብዙ ሺህ ሄክታር የሚለካ መሬት እያለ ዝናብ ሲጠፋ ረሀብ ከተፍ ኣለ። በጣም በቂ የሆነ የከርሰ ምድር ውኃ እያለን ያንን እየጎተቱ ኣውጥቶ ኣካባቢን ኣረንጓዴ ማድረግና ቢያንስ ረሀብን ማጥፋት ሲቻል ግብርናው መር መንግሥት ኣልሞከረውም። ውኃ ያዘለ መሬት ላይ ቆመን በውኃ ጥምና በርሀብ አለቅን።
በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይ በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ይህ ሁሉ ሕዝብ በፖሊሲ ችግር ተርቦ እያለ መንግሥት ኣለመደንገጡ ነው። ይሄ ኣሳዝኖኛል። ልክ ስታሊን የዩክሬንን ህዝብ ኣፍኖ እንደጨረሰው መንግሥትም የቁጥር ጨዋታ ይዟል። ረሀቡን ለመሸፈን ይሞክራል። ኣንዳንዴም ረሀቡ በቁጥጥሬ ስር ነው ይላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ኣሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ ረሀቡ ኣሳሰበን የሚለገሰው እርዳታም በቂ ኣይደለም እያሉ ኣሳብ ይዟቸዋል። እንዴውም በቅርቡ የተባበረችው ኣሜሪካ ድርቁ ለሰኪዩሪቲዋ ኣሳስቦኛል ብላለች። በርግጥ ኣርቆ ኣሳቢ መሪዎች ስላሉ ነው። ድርቅና ረሀብ ኣገርን ሊፈታ ይችላል። እየተባባሰ የመጣው ሥራ ኣጥነትና ስደት ሲደመር ርሀብ የአገርን ሉዓላዊነት የሚደፍሩ ኣገርን የሚያፈርሱ እምቅ ችግሮች ናቸው። ይህንን ጦማር እየጻፍኩ ባለሁበት ሰዓት እንኳን ሁለቱ የዓለማችን ታላላቅ መሪዎች ማለተም ፕሬዚደንት ኦባማና የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ አሜሪካ ውስጥ በተሰበሰቡበት ወቅት ፕሬዚደንት ኦባማ እንዲህ አሉ፣ “ከሀምሳ ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው የሚባለው ድርቅ በኢትዮጵያ ያስከተለውን የምግብ እጥረት ለመርዳት አስቸካይ ርምጃ ወስደናል።”
በዚህ ደረጃ ትኩረት ያገኘና ዓለምን ያሳሰበ ድርቅ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ኣሳሳቢ ኣይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርና መር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ኣለኝ የሚለው መንግሥት በሁለተኛው ዙር ላይ ኣስር ሚሊዮን ህዝብ ሲያስርብ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምን እንደሚያደርጉ ኣላውቅም። ለህዝባዊ ተቃውሞ ኣንዱ ትልቁ መነሻ የድህነት መጨመር ሲሆን በተለይ በረሀብ ሰዎች ከተጎዱ ደግሞ ከበድ ያለ የለውጥ ትግል መኖር ኣለበት። ኣሜሪካም ሆነች ካናዳና እንግሊሊዝ፣ ስዊድን፣ አውስትራሊያ፣ ኖርዌይ፣ ጀርመንና ሌሎች ለጋሽ አገሮች ድርቁና ረሀቡ ያሳሰባቸውን ያህል እንዴት የኛው መንግሥት ኣላሳሰበውም የሚለው ነገር እንደገና እጅግ ገራሚ ነው።
ለማናቸውም ዋናው የአገራችን ረሀብ ችግር ያለንን ውኃ ስቦ እያወጡ ማልማት ኣለመቻል ጋር የተያያዘ ነው። የተራብነውም ውኃ ወይ ከመሬት ውስጥ ወይ ከወንዞቻችን ስበን ማልማት ባለመቻላችን መሬታችንን ለመሬት ነጣቂ በማስረከባችን፣ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ባለመመለሱ ሲሆን ይህም በቀጥታ የመንግሥት ችግር ነው። ከፍታ ቦታዎች ላይ ያለው ድሀ ገበሬ መሬቱን በከርሰ ምድርና በመስኖ ውኃ እያለማ እንዳይጠቀም ካለመታገዙም በላይ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ሀምሳ ዓመት ሙሉ ቆይቶ እነሆ ሰማኒያ በመቶ የሚሆን ገበሬ በበሬ ግንባር በምታህል መሬት ላይ ታስሮ ይገኛል። ኢትዮጵያ ታሪካዊ ኣገር እንደመሆኑዋ ለጋሽ ኣገራት በቀና ልብ እርዳታውን ቢያጎርፉትም ግብርናው ከጥንቱ ኑሮው ንቅንቅ ኣላለም። ገበሬው ወገናችን ዛሬም የዛሬ ሶስት ሺህ ዓመት ያርስ እንደነበረው ያርሳል፣ በሳር ቤቶች ውስጥ ይኖራል፣ ሁለ ገብ እርሻን ተጠቅሞ ኣነሰችም በዛች ያችኑ ከጓዳው እያገኘ ለመኖር ይጥራል እንጂ የገበያ ሰው ኣልሆነም፣ የዛሬ መቶ ሁለት መቶ ዓመት የነበረው ግብርና ሲስተም ዛሬም ይኖራል። በእግሩ ይሄዳል፣ በቤቱ ውስጥ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች አያቱ ይጠቀምባችው ከነበሩት አይለይም። የታየው ለውጥ ህዝብ ብዛት ሲጨምር የመሬት ጥበት ካልሆነ ግብርናውና ገበሬው ኣልተለወጡም። ተጀምሮ የነበረ መሰረተ ትምህርት የደርግ በመሆኑ በታጋዮች ተደመሰሰና ስሙን መጻፍ ጀምሮ የነበረው ገበሬ ወደ ጥንቱ ማይምነቱ ተመለሰ።
ለዚህ ረሀብ የዳረጉን ጉዳዮች በዓጠቃላይ ኣንደኛ የመሬት ፖሊሲውና ርዳታን በአግባቡ አለመጠቀም ናቸው። በኣሥራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ተነስቶ የነበረው የመሬት ላራሹ ጥያቄ መነሳት ኣለበት የሚያስብለን ይሄ ነው። ርሀባችን ሰው ሰራሽ በመሆኑ የመንግሥት ለውጥ የግድ ያስፈልገናል። ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ ኣገራት በእርዳታ መቀበል ከፍተኛውን ቦታ ይዛለች። ብዙ እርዳታ እናገኛለን። የኢትዮጵያ መንግሥት ዓመታዊ ባጀት ከሀምሳ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነው ከለጋሾች በሚገኝ ርዳታ የቆመ ነው። ይህቺ ኣገር በዚህ ልክ ርዳታን ተገን ኣድርጋ የምትኖርበት ጊዜ በታሪክ ኣልነበረም። አጼ ኃይለ ሥላሴ እርዳታ ያደርጉ እንደነበር ይነገራል። ደርግ ሲመጣ በተወሰነ ደረጃ ርዳታ መቀበል የጀመርን ሲሆን ኣሁን ስልሳ በመቶ ባጀታችን በእርዳታ የቆመ ሆኖ ቁጭ ብሏል። እርዳታ ለጋሾቹ የሚረዱት ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል ነበር። ይህ ሁሉ እርዳታም እየተገኘ ግብርናው ፈቀቅ አለማለቱ ያሳዝናል ሳይሆን ያስቆጣል። በዚህ ያልተቆጣን በምን ልንቆጣ። ዛሬ በኦሮሚያ፣ ጋምቤላና አማራ አካባቢ ያሉ ተቃውሞዎች በርግጥ ፍትሀዊ ናቸው ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሊደገፉ ይገባል። በዚያ በድሀ ገበሬ ስም የሚመጣው እርዳታ ብዙ መስኖ ልማቶችን ሊሰራ ሲችል ተዘርፎ ይሸሻል። የኢትዮጵያ ኣንዱ ትልቅ ችግር ገንዘቡ መዘረፉ ብቻ ሳይሆን የተዘረፈው ገንዘብ መሰወሩ ነው። ዓለም ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ኤክስፐርት የነበሩት ዶክተር አክሎግ ቢራራ ሲናገሩ ሙስና ኢንዶኔሽያም ውስጥ ነበር ይላሉ። ኢንዶኔሽያም ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ይታይ የነበር ቢሆንም ዘራፊዎቹ ገንዘቡን ዘርፈው ሲያበቁ እዚያው ኣገራቸው ውስጥ የንግድ ተቋማት ነው የሚከፍቱበት የነበረው። ኣንዳንዶቹ ሆስፒታል፣ ኣንዳንዶቹ ሆቴል፣ ኣንዳንዶቹ የግብርና ሥራ ይሰሩበት ነበር ኣሉ። ይሄ መቼም ሳይሻል ኣይቀርም። የኢትዮጵያን ጉዳይ ስናይ ኣንደኛ ፖለቲካው ራሱ የብሔር በመሆኑ እነ ኤፈርት የሕዝብን ንብረት ወስደው ምን እንደሚያደርጉት ኣይታወቅም። ኦዲት ተደርጎ ለህዝብ ይፋም ኣይሆንም። የኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀብትም ኣይደለም ተብሏል። ሕወሓት በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ከትግሉ ጎን ለጎን እየነገድኩ ያደለብኩት ነውና ንብረትነቱ የትግራይ ሕዝብ ነው ይላል። ይህንን ሲል አያስጠላውም። የሚገርመው ደግሞ ይሄንን የግሌ ነው ብሎ በአንድ እጁ ይዞ በጉጂ ኦሮሚያ አካባቢ ያለውን ወርቅ ደግሞ የጋራችን ነው ብሎ በሌላ እጁ ይዝቃል። ይህን ሲያደርግ አያስጠላውም። ጉጂዎች የሚጠጣ ንጹህ ውኃ እንኳን ኣያገኙም። ስለዚህ በእንዲህ ዓይነት የመንግሥት እምነቶች ግብርናው ኣያድግም። ርሀብም ይህ መንግሥት አስካለ ይቀጥላልና ድሮ መሬት ላራሹ ብለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደታገሉ የዛሬው የአለማያ የግብርና ሳይንስ ተማሪ፣ የኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ የጅማ፣ የዲላ፣ የጎንደር ወዘተ….. ሊነሱና የገበሬውን ኣባታቸውን የመሬት ፖሊሲ ጥያቄ ሊያስመልሱ ይገባል። ዛሬም መሬት ላርሹ ብለን ለውጥን ማምጣት አለብን። አለበለዚያ የተባበረችው አሜሪካ እንዳሳሰበችው ይህቺን አገር ረሀብና ስደት ሊፈታት ይችላል። ለለውጥ መነሳትና መታገል አለብን። ውኃና አፈር እያለን፣ እርዳታ እያገኘን ሕዝባችንን ያሥራበ መንግሥት ላይ ጥያቄ ካላነሳን በታሪክ ተጠያቂ እንሆናለን። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply