የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ይድነቃቸዉ ተክሉ በወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ አባፍሯንሷ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ነዉ።
ከ10 በላይ የተለያዩ የሳይንሰና የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ስራ ባለቤት ሲሆን ከነዚህ የፈጠራ ስራዎች መካከል የእናቶች ጉልበትና ጊዜ ማስቀረት የሚያስችል የእንጀራ መጋገሪያ ቴክኖሎጂ ፈጥሯል።
ይህ የእንጀራ መጋገሪያ ቴክኖሎጂ እራሱ ያቦካል ፣ እራሱ ያሟሻል፣ እራሱ ይጋግራል እንዲሁም እንጀራዉ ሲደርስ እራሱ ከምጣዱ ላይ ያወጣል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ባዘጋጀዉ 3ኛዉ ዙር የሳይንስና የሒሳብ ትምህርቶች ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽንና ዉድድር ላይ እናቶችን ከጭስ የሚገላግለዉ የእንጀራ መጋገሪያዉና ሌሎችም በርካታ ቴክኖሎጂዎች ይዞ የቀረበዉ የአባ ፍሯንሷ ፈርጥ ይድነቃቸዉ ተክሉ በውድድሩ 1ኛ ደረጃ በመውሰድ አጠናቀዋል።
ታዳጊዉ በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ላይ እና ማህበረሰቡ በስፋት የተቸገረበት ቴክኖሎጂ ለመቅረፍ ትኩረት አድርጎ በመስራት የፈጠራ እዉቀቱን እያሳደገ ይገኛል።
ከተማሪ ይድነቃቸዉ የፈጠራ ስራዎቹ መካከል አዉቶማቲክ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን በቅርቡ በተካሄደዉ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ዉድድሮች ላይ ይዞ የቀረበ ሲሆን ይህ አዉቶማቲክ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽኑ የ12 ሰዉን ስራ ተክቶ የሚሰራ፣ 12 ምጣድ ያለዉ ሲሆን በአንድ ሰአት ዉስጥ 460 እንጀራ መጋገር የሚችል ማሽን ነዉ።
ታዳጊዉ የፈጠራ ሰዉ 10 የአካባቢ ማህበረሰብ ችግር የሚቀርፉ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ (water level indicator) በመሬት ላይ ሆነን ጣራችን ላይ ያለዉን የዉሃ ሮቶ መጠን የሚነግረን ቴክኖሎጂ ፣ አዉቶማቲክ የእንጀራ መጋገሪያ ፣ አዉቶማቲክ በር ሰዉ በሚመጣ ሰአት በራሱ ጊዜ የሚከፈት ሲሆን ሌላዉ ደግሞ ሮሆቦት ሲሆን ይህ ሮሆቦት አንድ ሰዉ የመኖሪያ ቤቱን ሴኪዩርድ ለማድረግ ቤት ዉስጥ በመቀመጥ ሮቦሆቱን በአንድ ስልክ እያንቀሳቀሰ በሌላ ስልክ ቪዲዮ ሮሆቦቱን የሚያየዉ ነገር በፎቶና በቪዲዮ መረጃ የሚሰጠን ነዉ።
ሌላዉ ከታዳጊ ይድነቃቸዉ የፈጠራ ስራዎች መካከል ቤት ዉስጥ ወይም ግቢ ዉስጥ ሰዉ ሲንቀሳቀስ የሚበራ መብራት እንዲሁም በዉሃ ዳቦ መጋገር የሚያስችል ማሽን ሲሆን ይህ ማሽን ከፍተኛ ሀይል ሳይፈልግ በዉሃ ሙቀት ዳቦ መጋገር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፣ ጸሃይ ባለ ጊዜ በሶላር በመብራትና በጎማዉ ቻርጅ የሚያደርግ መኪና ሲሆን ይህ መኪና ቤት ዉስጥ ስንሆን በመብራት፣ ጸሃይ ባለ ሰአት በሶላር እንዲሁም ረጅም መንገድ በምንጓዝበት ወቅት ከፍተኛ ፍጥነት ላይ በሚሆንበት ሰአት የፊት ጎማ መካኒካል ሲስተም ወደ ኤሌትሪካል ሲስተም በመቀየር መኪናዉን መልሶ ቻርጅ ያደርገዋል።
የእንጀራ መጋገሪያ ቴክኖሎጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደዉ የፈጠራ ስራዎች ዉድድር 3ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።
ታዳጊዉ እየሰራዉ ያለዉን የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች የበለጠ ዉጤታማ እንዲሆን መንግስት ፣ ወላጆቹና የትምህርት ቤቱ ባለድርሻ አካላት የግብዓት ችግሮችን መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻም የእናቶች ጊዜ፣ ጉልበትና አይናቸዉ በጢስ እንዳይጠፋ የፈጠረዉን የእንጀራ መጋገሪያ ቴክኖሎጂና ሌሎችም የፈጠራ ስራዎቹ ወደ ምርት እንዲቀየር መንግስት፣ ባለሀብት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል መልክታችን ነው። (የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Semaneh T. Jemere says
ውድ ጎልጉል፡
በዛሬው እለት ይህን የፈጠራ ዜና ስታበስሩ የተሰማኝን ደስታ ስገልጽላችሁ በታላቅ ትህትና እና የኩራት ስሜት ነው። በዛሬው እለት ያልሁበት ምክንያት ትላንት May 8, 2022 የዓለም የናቶች ቀን በመሆኑ ከዚህ የበለጠ ስጦታ ለታታሪዋ እናት ምን ሊኖር ይችላል ስል እራሴን ጠየቅሁት። ለወጣቱ ፈጣሪና ተመራማሪ አድናቆተ እና ምስጋናዬን በእናቴ፤ በባለቤቴ፤በልጆቸና እህቶቼ ስም አቀርባለሁ።
ከዚህ በማያያዝ የፈጠራው ስራ በኢትዮጵያ የሳይንስናን ቴክኖሎጂና የደረጃ መዳቢ ድርጅት እውቅና አግኝቶ ከሆነ መቸ ነው ወደ ተግባር፤ ሽያጭና ማከፋፈል የሚጀመረው እላለሁ።
ይህ ፈጠራ የእናቶችን ድካም ብቻ ሳይሆን የሚቀንሰው፤ የደን መጨፍጨፍን የቀንሳል፤ የእናቶችን ጤንነት ያሻሽላል፤ ባህላዊ አስራርን ያዘምናልና ወደ ተግባር የሚውልበትን ቀንና ጊዜ ብታሳውቁን ደስ ይላል። የህዳሴው ግድብ ሃይል ማመንጨት በጀመረበት ጊዜ በመምጣቱ ፈጠራውን ወቅታዊ ያደርገዋል። በተለይ እኛ በዳያስፖራ የምንገኝ ሰዎች ማሽኑን እየገዛን አነስተኛ ገቢ ላላቸው እናቶች በስፖንሰርሽፕ መልክ ገዝተን ማበርከት የሚቻል ይመስለኛልና አጣርታችሁ አሳውቁን።
ሌላው ይህ ወጣት ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልገው እርዳታ ካለ ብታሳውቁን ብዙ መርዳት የሚፈልጉ ሰዎችና ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ፈጠራ በቀላሉ እንዳይታለፍና የአንድ ሳምንት ዜና ማሞቂያ ሆኖ እንዳይቀር አደራ እላለሁ። እነስታይን ፈጠራውን ወደ ተግባር በመቀየር ነው ዓለምን የቀየረው። የዚህ ወጣት ፈጠራም እንዲሁ ከተበረታታ ውጤቱና ጥቅሙ ለወጣቱ፤ ለሕዝባችንና ለሃገር ነውና እንደግፈው። እራስን በራስ የመቻል ማሳያም ነውና ቸለንዳይበላ አሁንም አደራ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ለማያስፈልግ ሰው ሰራሽ ጸጉር ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ሳስበው ሁሌም እቆጫለሁና ይህን ከንቱ ወጪ ወደዚህ ፈጠራ አዙራ ብታስፋፋውና በተግባር ብታውለው ምንያህል በተጠቀመች እላለህ። ይታሰብበት!
ለጊዜው ወጣቱን እጅጉ እያደነቅሁ በርታልን እላለሁ። አመሰግናለሁ
ሰማነህ ታምራት ጀመረ
ኦታዋ ካናዳ May 9, 2022
Editor says
ውድ ሰማነህ ታምራት ጀመረ
በቅድሚያ ጊዜዎን ወስደው ይህንን የመሰለ ምላሽ ስለላኩልን ከልብ እናመሰግናለን። እርስዎ እንዳሉትም ሁለቱም የዜና ዘገባዎች በጣም ጠቃሚና የሚያስደስቱ ናቸው።
የሚያሳዝነው እጅግ መልካም እና የሚያስደስት እሴት ያላት አገራችን ብዙ ሊወራላት የሚገባ ነገር እያላት ጠላቶቻችን በሚሰጡን አጀንዳ እርስበርስ እየተናቆርን መጥፊችንን በግድ የምንደግስ መሆናችን ያሳዝናል። ሆኖ ደግሞ እንደ እርስዎ ያለ እሾኹን ብቻ ሳይሆን አበባውንም የሚያይ አንድ ሰው መገኘቱ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነው።
በእርግጥ እርስዎ በዚህ ልክ ጻፉልን እንጂ በዝምታ ደግሞ ያገራቸውን ሁኔታ የሚከታተሉና መልካሟን የሚመኙ እንደ እምነታቸው የሚጸልዩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች አሏት። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የተዓምር አገር የሆነችው።
ለመልካሙ አስተያየትዎ በድጋሚ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
አርታኢ
Kidus says
ውድ ጎልግል አቅራቢዎች፡ የወጣቱ የእንጀራ መጋገሪያ የፈጠራ ሥራ በጣም የሚደነቅ ነው። እኔና ጓደኞቼም እንጀራ ማከፋፈል ስራ በአ.አ ከተማ እንሠራለን። ስለዚህ ይህን ወጣት ብታገናኙን እና ተነጋግረን ማሽኑን ቢሠራልን፡ ለኛም ለሱም ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንልን ተስፋ አደርጋለሁ። እና ውድ ጎልጉል አዘጋጆች እባካችሁን የወጣቱን እንዳልካቸው ተክሉን የምናገኝበትን ስልክ ወይም ሌላ መንገድ ካለ ብታጋሩን በማለት በትህትና እንጠይቃለን።