የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737-800 ማክስ አውሮፕላን የመከስከስ አደጋ በደረሰበት ስፍራ ለሚገነባው ሀውልትና ፓርክ የወጣውን ዓለም አቀፍ የንድፍ ውድድር የኢትዮጵያዊው አርክቴክት አለበል ደስታ ድርጅት አሸናፊ መሆኑ ታውቋል።
በምስራቅ ሸዋ ዞን ግምቢቹ ወረዳ ለሚሰራው ይሄው የመታሰቢያ ሀውልት እና ፓርክ በ4 ሄክታር መሬት ላይ ሊገነባ የታሰበ ሲሆን ቦታው የማስታወሻ፣ የአረንጓዴ ቦታና የውጪ መሰብሰቢያ ስፍራ ያካተተ ነው ተብሏል።
የአርክቴክት አለበል ደስታ ድርጅት ውድድሩን በማሸነፉ የ10 ሺህ ዶላር ሽልማት ሲያገኝ ሁለተኛ የወጣው ባይቦን አማካሪ አርክቴክቶችና መሀንዲሶች ድርጅት 7ሺህ ዶላር እንዲሁም በረከት ተስፋዬ አማካሪ አርክቴክቶችና መሀንዲሶች ድርጅት ሶስተኛ በመውጣት የ5 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል።
አርክቴክቱ ከዚህ ቀደምም በመስቀል አደባባይ የተካሄደውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአለ ሲመት መድረክ ንድፍ እና ግንባታ በማካሄድ እውቅና ያተረፈ ባለሞያ ነው።
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር 302 መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ተንስቶ ወደ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ለመጓዝ የተነሳው በረራ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ተከስክሶ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። (ኢብኮ፣ አዲስ ዘይቤ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply