
በኦሮሚያ በየጊዜው እያጋጠመ ለሚገኘው የህይወትና ንብረት ውድመት በህወሓት ጁንታና ተላላኪዎቹ የሚፈፀም መሆኑንና ይህንንም ለማስወገድ ብሎም የቡድንን ዕድሜውን ለማሳጠር በ‹ጂ ፒ ኤስ› ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ ኢንዶክተሬሽን መምሪያ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ ኢንዶክተሬሽን መም ሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር እንዳለ ቁምላቸው ለበሪሳ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የህወሓት ጁንታ እና የኦነግ ሸኔን ሴራ ለማክሸፍና ዕድሜ ለማሳጠር ‹‹ጂ ፒ ኤስ›› ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ አካላት ዜጎችን ለምን እንደሚገድሉ እን ደማያውቁ በመጠቆም በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋልም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል። ቴክኖሎጂው እነዚህ አካላት ያሉበትን ቦታ ለመከታተል የሚያስችል እንደሆነም አመልክተዋል።
በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ በሠላማዊ መንገድ እጅ ለማይሰጡና የኃይል አማራጭ ለመጠቀም የሚሞክሩት ላይ ደግሞ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል ።
እነዚህ ጸረ ሠላም አካላት አባ ቶርቤ በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሱ መሆኑን አመልክተው፣ ኦሮሚያ ክልልን የግጭትና ጦር አውድማ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ሠላማዊ ዜጎችን መግደል ሥራቸው አድርገው መቆየታቸውንም አመልክተዋል።
ማንኛውንም የፖለቲካ አመለካከት ያለው አካል በዴሞክራሲያዊ መንገድ የፖለቲካ አስተሳሰቡን ለህዝብ መሸጥ ይጠበቅበታል ያሉት ኮማንደር እንዳለ፤ ከዚህ ውጪ ሰላም በማደፍረስና ሠላማዊ ዜጎችን በመግደል ስኬታማ መሆን እንደማይቻል አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነና የዜጎችን ሠላም ለመጠበቅ የተቋቋመ ነው ያሉት ምክትል ኮማንደር ፣ በየትኘውም ሁኔታ የዜጎችን ሰላም ችግር ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን አይታገስም ብለዋል። መንግሥትም ለዜጎች ሠላምና ደህንነት መቃወስ ምክንያት የሆኑ እንደ የህወሓት ጁንታና፣ አባ ቶርቤ፣ ሸኔና ሌሎችንም ወደ ህግ ለማቅረብ ከመቼውም በላይ ጠንካራ ሥራ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply