ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በታህሳስ ወር በተካሄደው ቅንጅታዊ የኮንትሮባንድ መከላከል ስራ ግምታዊ ዋጋቸው ብር 274 ነጥብ 8 ሚሊየን የሆኑ የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ህገወጥ ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በሌላ በኩል ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ወጪ የኮንትሮባንድ አይነቶች መያዛቸውን በታህሳስ ወር የኮንትሮባንድ መካከል ስራዎች ሪፖርት ተመላክቷል።
በአጠቃላይ በወሩ ብር 344 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚያወጡ ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል።
በገቢ ኮንትሮባንድ የተያዙት ዕቃዎች በተለይም በጅጅጋ፣ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በሞያሌና ኮምቦልቻ ቀዳሚውዎቹን ስፍራዎች የሚይዙ ናቸው።
በወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ሃዋሳ፣ ሞያሌ፣ ጅማ እና ጅጅጋ ቅ/ፅ/ቤት ከፍተኛ መጠን ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ የያዙ ናቸው።
የተያዙት ዕቃዎችም ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ የተያዙት አደንዛዥ ዕፆች፣ ህገወጥ ገንዘብ፣የተለያዩ የግብርና ምርቶች፣ ማዕድናት እና የቁም እንስሳት ሲሆኑ በገቢ ኮንትሮባንድ ደግሞ ልባሽ ጨርቆች፣ ኤሌክትሮኒክሶች፣ የምግብ ምርቶች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ መድኃኒትና ሌሎችም ዕቃዎች ተካተዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ህዝብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የጤና ጠንቅ የሚያስከትለውን ኮንትሮባንድ ፍሰትን ለመቀነስ ውጤታማ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፆአል። (ኢትዮ ኤፍ ኤም)
Leave a Reply