• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ!

August 12, 2016 03:34 am by Editor 2 Comments

አንድ

በነገረ አስተሳሰብ ወይም በአስተሳሰብ ሕግ (ሎጂክ) ትምህርት ላይ አንድ የማስታውሰው ምሳሌ አለ፤ ‹‹ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚነሣው ጠያቂው አውቃለሁ ብሎ ከያዘው እውቀት ወይም እምነት ነው፤ ስለዚህም ጠያቂው የሚፈልገው ጥያቄ ለማስተላለፍና መልስ ለማግኘት አይደለም፤ ጠያቂው የሚፈልገው በጥያቄ መልክ የራሱን ‹‹እውቀት›› ወይም እምነት ለተጠያቂው ለማስተላለፍና ተጠያቂውን የጠያቂው ደቀ መዝሙር ለማድረግ ነው፡፡

ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤ ‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄው ትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው፡፡

‹‹ወልቃይት የማን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ትክክል አይደለም፤ የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው፤ ጠያቂው የሚፈልገው መልስ የአማራ ነው፤ የጎንደር ነው፤ የትግሬ አይደለም፤ የሚል ነው፤ ነገር የሚገባው ተጠያቂ ጥያቄውን ጠያቂው በፈልገው መልክ አይመልስለትም፤ ሊመልስለትም አይገባም፤ ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው የሚል መልስ አይፈለግም፤ የማይፈለግበትም ምክንያት ‹‹ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው፤›› ማለት ወልቃይትን ከጎሠኛነት አጥር ስለሚያወጣ ነው፤ የትግራይ አይደለም፤ የአማራ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ነው፤ አሁን ትግራይና አማራ የኢትዮጵያ ናቸው፤ ይህ ከተባለ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ነው? ወይስ የአማራ? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት የጎሠኛነት ጥያቄ ነው፤ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ አይደለም፤ ጥያቄው የማይረባ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት የጎሠኛ ጥያቄ በመሆኑ የወያኔን የጎሠኛ መመሪያ የሚያከብር መሆኑ ነው፡፡

ትልቁና መሠረታዊው ጥያቄ በአማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ አገዛዝ ወደትግራይ ክልል መግባቱ ነው፤ እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም አውራጃ ነው፤ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የጎሣ ዓይነት ወይም የጎሣ ስብጥር አይደለም፤ የፈለገውን ዓይነት አንድ ጎሣ ወይም የብዙ የጎሣ ስብጥር ሊኖርበት ይችላል፤ ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት አውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ የአስተዳደር ለውጡ የተፈጸመው የፌዴራል መዋቅሩን ሥርዓት በጣሰ መንገድ አንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ወረራ አካሂዷል ነው፤ ይህ ወረራ ሕጋዊ አይደለም፤ ይህ ወረራ ሊቀለበስ ይገባል፤ ዋናው መቋጠሪያ ይኸው ነው፡፡

ግን ጉዳዩን የጀመርነው ከመሀሉ ነው፤ ሲጀመር ወያኔ ከኦሮሞ ቡድኖች ውስጥ ኦነግን መረጠና አማርኛ ተናጋሪውን አለ እያለ እንደሌለ ቆጠረው፤ በዚያን ጊዜ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎቹም ኢፈትሐዊነቱን አልተናገሩም፤ ዋና የፖሊቲካ ጉዳይ አድርገው አላነሱትም፤ ለምን? እነሱ በሎሌነት በመመረጣቸው በደስታ ተውጠው ስለነበረ ጌቶቻቸውን ለማስቀየም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ግን ወያኔ በእጁ ያሉትን ምርኮኞች ከአደራጀ በኋላ ኦነግ ተባረረና በኦሕዴድ ተተካ፤ የኦነግ መሪዎች አገር ውስጥ ሆነው ለመታገል የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው በስልክ ‹‹ትግሉን›› መምራት መረጡ፤ ወያኔ አነግን በብዙ መንገድ ተጠቅሞበታል፤ አንደኛና ዋናው አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን ለመለያየትና በቅራኔ ለማጋጠም፤ ሁለተኛ የኦሮሞ መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ለወያኔ ትሑት አገልጋይ ከመሆን ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አረጋገጠላቸው፤ ኦነግንና እስላማዊ ኦነግን አፋጅቶ በኦሕዴድ አጋዥነት ሁለቱንም ከትግል መድረኩ አስወጣቸው፡፡

አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤ ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡

ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት፡፡

ሁለት

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ርእስ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 96ና 97 መሀከል ካርታዎች አሉ፤ ከነዚህ ካርታዎች አንዱ የኢጣልያ ምሥራቅ አፍሪካ (AFRICA ORIENTALE ITALIANA) 1928-1933 ዓ.ም. የሚል ነው፤ በዚያ ካርታ ላይ ፋሺስት ኢጣልያ ትግራይን በሙሉና አፋርን በሙሉ በኤርትራ ክልል ውስጥ አድርጎት ነበር፤ በደቡብም የኢጣልያን ሶማልያ ወደሰሜን ገፍቶ ኦጋዴንን በሙሉና ግማሽ ባሌን ጨምሮበት ነበር፤ ምዕራቡን ክፍል — ወለጋን፣ ኢሉባቦርን፣ ጋሞ ጎፋን፣ ሲዳሞን በአንድ ላይ አስሮ ጋላና ሲዳማ የሚል ስያሜ ሰጥቶት ነበር፤ ሀረር ሰሜን ባሌንና አርሲን ጠቅልሎ ነበር፤ ወያኔም ከፋሺስት ኢጣልያ የወረሰውን አስተሳሰብ ይዞ የጎሣ ክልሎችን ፈጠረ፤ በዚያን ጊዜ ግማሹ እልል እያለ ግማሹ እያጉረመረመ ተቀበለ፤ በዚህም ሥርዓት አንድ ትውልድ በቀለና በጫትና በጋያ አደገ፡፡

ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ፤ ሲያብጡ ቦታ ይጠብባል፤ ስለዚህ ወደቤኒ ሻንጉልና ወደጋምቤላ በመዝለቅ ሁለት ዓላማዎችን ማሳካት ይቻላል፤ አንደኛ ትግራይ ሰፊ ይሆንና በእርሻ ልማት የሚከብርበት ተጨማሪ መሬት ያገኛል፤ ሁለተኛ ጠላት ብሎ የፈረጀውን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የውጭ ንክኪ እንዳይኖረው ያፍነዋል፤ ከሱዳንም ጋር ጊዜያዊ ወዳጅነትን በመሬት ይገዛል፤ የወያኔ የእውቀትና የብስለት እጥረት ከብዙ ትንሽም ትልቅም ኃይሎች ጋር ያላትማቸዋል፤ ሱዳንን በመሬት በማታለል ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከግብጽ፣ ከሳኡዲ አረብያ፣ ከየመን፣ ከሶማልያ … መለየት የሚችሉ ይመስላቸዋል (ልክ አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን እንደለዩት)፤ የተዘረዘሩት አገሮች ሁሉ በሱዳን ላይ ከወያኔ የበለጠ ጫና ማድረግ የሚችሉ ናቸው፤ አሜሪካን ለብቻው ብቻ ሳይሆን ከነዚህ አገሮች ጋር አብረን ስንገምተው የወያኔን ደካማ ሁኔታ ለመገንዘብ ቀላል ነው፤ በአካባቢያችን ከአሉት አገሮች ሁሉ ወረተኛ የውጭ አመራር ያለው ሱዳን ነው፤ ሱዳን የኤርትራን መገንጠል የደገፈው በአሜሪካ ጫና መሆኑን አንርሳ፤ ለማንኛውም አሁን በወልቃይት የተጀመረው ውጊያ ከቀጠለ የወያኔና የሱዳን የጓዳ ጨዋታ ያበቃለታል፡፡

ጉዳዩ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡

ሦስት

ወደየጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ስንመለስ፡– ጥያቄው በቁሙ የወልቃይት-ጸገዴ ተወላጆች እንዳቀረቡት ሲታይ የወያኔ አገዛዝ ሃያ አምስት ዓመታት የደከመበት የጎሠኛ ሥርዓት ቢያንስ በአስተሳብ ደረጃ የተሳካ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎሠኛ አስተሳሰብ ገና እንዳልወጣ የሚያረጋግጥ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በጎሣ ሥርዓት እየገዛ በጎሣ ሥርዓት የሚሸነፍ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፤ ወያኔ ይህንን አዲስ ክስተት ገና አልተገነዘበውም፡፡

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከመለስ ዜናዊ ጋር ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተን ስንከራከር አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል!

በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በሚንገላታበት ጊዜ ደ ክለርክ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ መሪ ማንዴላን ከእስር አስወጥቶ እንደአኩያው በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው የሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች መተማመን የደቡብ አፍሪካን ችግር ለጊዜው ፈታው፤ ማንዴላ በክብር ሞተ፤ ደ ክለርክ በክብር ይኖራል፤ የሚያሳዝነው በወያኔ አመራር ውስጥ እንደደቡብ አፍሪካዊው ደ ክለርክ ያለ ሰው እንኳን ሊኖር ሊታለምም አይቻልም፤ እንኳን በወያኔ ውስጥ በአገሩም እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይኖር አረጋግጠዋል፡፡

የተጀመረውን ግብግብ ኢትዮጵያ ካላሸነፈች ማንም አያሸንፍም!

ኢትዮጵያ የድንክዬዎች አገር ሆናለችና የገጠማትን ችግር እግዚአብሔር በጥበቡ ይፍታላት!

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

ነሐሴ 2008

(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions, Politics Tagged With: Full Width Top, mesfin, Middle Column, Woldemariam

Reader Interactions

Comments

  1. Jijjaw says

    August 12, 2016 06:26 am at 6:26 am

    በረከት የማን ነው?

    ሰላምዎርቅ AKA በረከት ስምኦን
    ሲያልቅ አያምር እንዲሉ የሰሞኑ የወያኒ ፕሮፐጋንዳ ቅጥአምባሩ ጠፍቷል። ራሳቼውን በሚያራክሱበት አይጋ ፎረም አንዴ መስዋትነትን ሊላጊዜ ደግሞ ታሪክን ይህም አላስኬድ ሲል ወንድ ከሆንክ ሞክራት በሚል “አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ” ትርክት አኛን “ትምክህኞችን” አርፈን እንድንገዛ እንድንዘረፍ ሃገራችንን እንድናስረክብ በትግርኛ አማርኛ ሰልጠን ያሉት ደግሞ በትግሪኛ እንግሊዘኛ ይቼከችካሉ። አንድ ሰው ሃሳቡን ለመግለጽ ሁለት ሶስት ፓራግራፍ ቢበቃውም የቡድን ስራ መሆኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ ሃያ አርባ ገጽ ይከትባሉ በአንድ ቀን አዳር። አማራ ሆኖ ስለብአዴንና አማራ የነሱን ትርክት የሚተርክ ሰው ባለመኖሩ [ ሰው እንጂ በቍሙ የሞተ ሰው አላልኩም ] አንዴ ሙሉአለም ሌላ ጊዜ መኮነን ወዘተ በሚል ስም ራሳቼውን ከሳሽ ገላጋይ ተሳዳቢ አራሚ አድርገው ይፈጋሉ: የሚሆን መስሏቼው። ውሼት ህልውናው የሆነው ወያኔ ስለሚለው ብዙ ጊዜ ባይጠፋ ጥሩ ነው። እንደኔ ከእንግዲህ ከነዚህ ፋሺስቶች ጋር አብረንም መኖር ያለብን አይመስለኝም። የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉት አስበው አቅደው አንጂ ተሳስተው ወይም ካለማዎቅ አይደለም። በጣም በድለውናል በጣሙንም ታግሰናቼዋል። አማራም ሆነ ኦሮሞ ራሳችንን ችለን መኖር የምንችል ህዝቦች ነን። ከተግባባን በአዲስ ስርአት አብረን እንዘልቃለን። ካልሆነም ይህን ደመኛ ጠላት አስዎግደን በጥሩ ጉርብትና እንኖራለን።ያለፈ ታሪክ እስረኛ ሆነን ለመኖር ማናችንም አንፈቅድም። ነጻነቴን ለማግኘት እንደ አንድ አማራ ከኦሮሞ ጓዶች ጋር በዚህ ደረጃ ተገባብቼ ለጋራትግሉ ህይዎቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። ወያኔ ጠላት ነው። እኔም ከዛሬ ጅምሮ አገሪ በጠላት ቅኝ እንደተያዘች፡ አምኛለሁ። ከዚህ ወራሪ ጋራ የሚሰሩ ሁሉ ጠላቶቼ፡ ናቼው። ይህን ወራሪ የሚታገሉ ሁሉ ወዳጆቼ ናቸው።
    በረከት እባክህን ከምትጠላው ህዝብና ድርጅት ጋር አትኑር። ሂድና የሰገድክላቼውን ፋሽስቶች በጊዜ ተቀላቀል። ሞትህ የሚያምረው ከህውሃት ጋር ነው። አስረግጨ የምነግርህ ቢኖር ምንም ያህል ጭካኔ ከትግላችን አያስዎጣንም።
    ሞት ለዎያኔ!

    Reply
  2. በለው! says

    August 12, 2016 03:22 pm at 3:22 pm

    የእኛ ቤት ጉድ!
    ” አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤” አፍ ያለው ጥሬ ይቆላል!
    “ኢዴኃቅን ካጠፋን በኋላ ገብሬውን አማራ በፓለቲካው ያደራጀናቸውና ያነቃናቸው እኛ ነበርን የግድ የአማራ ብርሔር ባይሆኑም “በአመለካከቱ “የሚወክሉት መረጥንለት ብሎ ለገሠ መለሰ ዜናዊ ሲያናፋ አማራ አልነበረም !።
    ” ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ “ታማኝ ጓዶች !”
    “ሰዶ ማሳደድ ሲያምርህ አገርህን በክልል ለውጥ ”
    *** በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡”
    እንደማጎብደድና ጭነት የመቻል አቅማቸው ልክ አዲስ ታሪክ እየፈጠረ ታሪክ ሰሪ (መሰሪ) በክልል አስሮ በጫካ ማኒፌስቶ አደንዝዞ በጡትና ወሸላ ሥር ባዶ ሆዱን ፡በባዶ እግሩ ባዶ ቂጡን እየመታ ሲያስጨፍረው በሕገ መንግሥታዊ ጥቅማጥቅም ልቡ ተደፍኖ ዓይኑ ታውሮ ፱፭ ዓመት ትውልድ መከነ ባከነ ።

    “ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት!። “እያነቡ እስክስታ !”

    >> አሁን አማራ አለሁ እራሴን ወክዬ ሀገሬን ስጡኝ ቤተሰቤን ኦሮሞውን አትንኩ! አለ ኦሮሞ ቀበሌና መንደር የኔ(ኬኛ) ከማለት ጎንደር የእኔ ነው! አለ ውስጠ ወይራው “ኢትዮጵያ የእኔ ናት!” ማለቱ ነው ።አራት ነጥብ።

    = ኦሮሞ ከስህተቶቹ ተምሮ በሰላምና የዲሞክራሲ ግንባታ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ ታሪካዊ ለውጥ እና የሕዝብን አመኔታን ያገኝ ይሆን ? ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የኦሮሞ አደለችም የሚል ሻቢያ እና ህውሐት ይፈጥራሉን?
    ** አለሁ! ያለው አማራ በእርግጥም አንድ ሆኖ በዳግማዊ ብአዴን ሳይጠለፍ ይዘልቅ ይሆን ? ሞረሽ ወገኔ .. ቤተ ንፉጋን ..ቤተ አምሐራ የሚልም ዓርማው ምንም የኢትዮጵያ ሠንደቅ የሌለው ጭልፊት ይሁን ሲላ ወይም ንሥር ማንነቱንና ምንነቱን ያልተለየ በድረ ገፆች ላይ ሲያንዣብብ ይታያል :ያለው ከብዶናል ወንዝና ተራራ እየቆጠርን ጨርቅ በቀለም እየነከርን መንደራዊ ብሔርተኝነትን ቀፍቅፈን በጎጥ በነገድ ሻክላ እንዳንተባተብ አደራ በለው!

    የተማረ እያስተማረ ያልተማረ ይማራ
    ብርታትና ድል ለተገፋው አማራ!

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የሲኖዶሱ ውዝግብ አካሄድና መጪው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ February 6, 2023 02:03 am
  • የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ፤ ተጠባቂው ዕርቅ ፍንጭ እያሳየ ነው February 3, 2023 05:17 pm
  • የብላቴ: የውጊያ ማርሽ ቀያሪ ሠራዊት መፍለቂያ ማዕከል February 3, 2023 10:06 am
  • በኢትዮጵያ 27 በመቶ የሚሆነው የአእምሮ በሽተኛ ነው ተባለ February 3, 2023 09:47 am
  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule