• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

‘‘ፍርድ ሲዘገይ ሀገር እንደታሰረ መቆጠር አለበት’’ ተማም አባቡልጉ (የሕግ ጠበቃ)

December 12, 2013 07:52 am by Editor 1 Comment

አቶ ተማም አባ ቡልጉ ከአዲስ ጉዳይ መጽሄት ቁጥር 128 ህዳር/2006 ዕትም ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

አዲስ ጉዳይ፡ የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወደ ታህሳስ 3 ሲዛዋወር እንደ ጉዳዩ ዓቃቤነትዎ እንዲያውቁት ተደርገው ነበር?
ተማም፡ በፍጹም ለእኔ የተነገረኝ ነገር አልነበረም፡፡ ከእኔ ጋር አብሮ የሚሰራ ጠበቃ ፍርድ ቤት ድረስ ሄዶ ‘ጉዳዩ እንዴት ነው?’ ሲለኝ አይ እዚያው ነው ብዬ ሳረጋግጥለት ‘አረ ፍርድ ቤቱ ባዶ ነው’ የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ አንዳንድ ጠበቆች ጋር ስደውልም እከሌ የተባለ ጠበቃ እኮ ፍርድ ቤት በነበረበት ወቅት ከጽ/ቤት ተነግሮት ነበር አሉኝ፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ ነው ቀጠሮው መራዘሙን የሰማሁት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ በይፋ የተነገራችሁ ነገር የለም ማለት ነው?
ተማም፡ ለእኛ በይፋ ምንም የተገለፀልን ነገር የለም፡፡ በፍርድ ቤት በይፋ ተነገረ የሚባለው በቀጠሮው ቀን ችሎቱ ተሰይሞ፣ ዳኞች ተገኝተው፣ ደንበኞች ቀርበው፣ ጠበቆች ተገኝተው የተገኙት ከተመዘገቡ በኋላ ‘የዛሬው ቀጠሮ ለዚህ ለዚህ ነገር ነበረ፣ ነገር ግን ውሳኔው ስላልደረሰ ለእንዲህ ቀን ተቀይሯል’ ሲባል ብቻ ነበር፡፡ ይሁን እነጂ ጉዳዩን በንቃት የሚከታተሉት 6 የሚሆኑ ጠበቆች ቢሆኑም አንዱ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ለአንዱ ጠበቃ በቃል ከነገረው ውጪ ምንም የሰማነው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም የቀጠሮው መራዘም ለእኛም ቢሆን በይፋ በፍፁም እንዳልተነገረ መታወቅ አለበት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ መራዘም በማህበራዊ ሚዲያ አስቀድሞ ይፋ ሆኗል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ተማም፡ እኔ በፍጹም እንዴት መረጃው ሊወጣ እንደቻለ አላውቅም፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ዓይነቱ አካሄድ በጣም ስህተት ነው፡፡ አንድ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለወደፊት የሚሰየምበት ቀን እንዴት ዝም ብሎ ይገለፃል፡፡ ፍርድ ቤት የሚሰራው በመዝገብ ነው፡፡ ቀጠሮ ለ23 ከተባለ ሌላ ቀጠሮ ለመያዝ እንኳን ያ ዕለት መድረስ አለበት፡፡ ይሄ ግዴታ ነው፡፡ ዳኛው እንኳን ባይኖር ለተለዋጭ ቀጠሮውን ቀን ማስታወቂያ መለጠፍ ያለበት በቀጠሮው ዕለት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪም ሌላ ዳኛ ተሰይሞ ጉዳዩን አይቶ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ ቀጠሮ አይራዘምም፡፡ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው የቀጠሮ መራዘም አስቀድሞ መውጣቱ በጣም ስህተት ነው፡፡ አንዳንዴ ህግ ሲጣስ እየተለመደ ይመጣል፡፡ ከስራ ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት ባልደረቦች፣ ከዳኞች ሆነ ከሌሎች ጋር በስራ ምክንያት ልንተዋወቅ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በአንድ የክስ ጉዳይ ከፍርድ ቤቱ ጋር የምንተዋወቀው በመዝገቡ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያ እንዲወጣ የተደረገው መረጃ የፍርድ ቤት አካባቢ ክፍተት እንዳለ ስለሚያሳይ እርማት ያስፈልገፈዋል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ የቀጠሮው መራዘም በተለይ የሚያመላክተው የህግ ክፍተት አለ?
ተማም፡ በጣም አለ እንጂ፡፡ ‘የዘገየ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል’ እንደሚባለው የእኛ ደንበኞች የታሰሩት በሐምሌ ወር ሲሆን እስካሁን አንድ ዓመት ተኩል ሁኗቸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ ማስረጃ እና ምስክሩን አቅርቦ ከጨረሰ ሶስት ወራት አልፎታል፡፡ አሁን ደግሞ አስር ቀናት ሲጨመር መቶ ቀን ይሞላቸዋል ማለት ነው፡፡ ይሄ የፍትህ መዘግየትን ያሳያል፡፡ የታሰሩት እኮ ጥቂት ሰዎች አይደሉም፡፡ ለነገሩ በህጉ መሰረት አንድም ሰው ቢሆን ታስሮ ፍርድ ሲዘገይበት ሃገር እንደታሰረ ነው መቆጠር ያለበት፡፡ ተገቢውን ብያኔ በጊዜው ማግኘት ከቁጥር ጋር ሳይሆን ሰው ከመሆን ጋር ብቻ የተያያዘ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ አሁን ይህንን ብያኔ የሚጠብቁ ወደ 29 የሚጠጉ ደንበኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከታሰሩ 1 ዓመት ከ6 ወር አልፏቸዋል፡፡ ለብይን ብቻ ቀኑ እየተራዘመ ወደ 4 ወር እንዲጠጋ መደረጉ ብዙ ነገርን ያመለክታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለደንበኞቻችን ይህን ያህል ግድ እንዳልተሰጣቸው ያሳየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ አይሆንም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ቀጠሮው በድንገት መራዘሙ በግልዎ የፈጠረብዎት ስሜት ምን ይመስላል?
ተማም፡ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ ቀጠሮው በድንገት ይሰረዛል የሚል ግምትም በጭራሽ አልነበረኝም፡፡ የሙያ ጉዳይ አለ፤ የደንበኝነት ጉዳይ አለ፣ ይሄ ሁሉ የሚደማመር በመሆኑ የፍትህ አካሄዱ መራዘሙ አግባብ የሌለው በመሆኑ ጥሩ ስሜት አልፈጠረብኝም፡፡ አድስ ጉዳይ፡ ቀጠሮው መራዘሙ በደንበኞችዎ ላይ የተለየ ችግር ይፈጥራል የሚል ስጋት አለዎት?
ተማም፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቀጠሮ መራዘሙ ራሱ እውነቱን ለመናገር በጣም ትልቅ ችግር ነው፡፡ በተለይ እንደ ህግ ባለሙያ አንዳንዴ ሕጋዊ አካሄዶች ሳይተገበሩ ሲቀሩ በጣም ባዶነት ይሰማሃል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ እስኪ ይሄን ጉዳይ ቢታብራሩት?
ተማም፡ ምን አለ መሰለህ? ባለሙያ ተብለህ ተምረህ በሕግ ጉዳዮች ላይ የምትሳተፈው በትክክለኛው መንገድ በህጉ መሰረት ነገሮች ይሄዳሉ ብለህ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕግ የሚሄድበት መስመር አለው፡፡ ይሄ ተገቢ አካሄድ ሳይከበር ሲቀር ትርጉም የማጣት ስሜት ያድርብሃል፡፡ ብዙ እንዲህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ያሉ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ በምን ምክንያት?
ተማም፡ የህግ ትልቁ መርህ የሕግ አተገባበር እንደ ፀሐይ መውጫና መግቢያ የማይለዋወጥ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም መብትህን አውቀህ ስትንቀሳቀስ በእርግጠኛነት ሕገ-ወጥ የሆነ ነገር አይደረግብኝም የሚል ጠንካራ ሐሳብ መያዝ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ሲቀር ተጠራጣሪ ያደርግሃል፡፡ በዚህ የተነሳም በምንም ነገር ላይ እርግጠኛ ያለመሆን ነገር ይፈጠራል፡፡ ይሄ በመሆኑ ደግሞ መጥፎ የባዶነት ስሜት እንዲሰማን ያደርግል፡፡ ወደ እኛ ደንበኞች ጉዳዩን ብንወስደው እንኳን ነገሩ ይህንን ያህል የሚጓተት ከሆነ ለብያኔ ብቻ ቀጠሮ መራዘሙ በራሱ ‘ጉዳቱ ደርሶብናል’ የሚል ስሜት በውስጣቸው አሳድሮባቸዋል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ለቀጠሮው መራዘም የሚወሱ ምክንያቶች አይኖሩም?
ተማም፡ ይህን ያህል የተማረ ህዝብ ባላት ሀገር የአቅም ችግር ነው የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን ማንሳት በአሁኑ ወቅት ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን በሚያህል ወደ መቶ ሚሊዮን እየተጠጋ የመጣ ሕዝብ ያላት ሀገር የፍርድ ቤት አደረጃጀቷን የተቀላጠፈ እና የተሻለ ማድረግ እንጂ የተለያዩ ምክንያቶችን መደርደር ተገቢ አይደለም፡፡ ሰዎች እኮ ታስረዋል፡፡ ለማሰር በቂ የሆነ ሰው ኖሮህ ካሰርክ ለመበየንም በቂ የሆነ የሰው ኋይል ሊኖርህ ይገባል፡፡ ይሄ የማይሆን ከሆነ ደግሞ አስቀድመህ አለማሰሩ የተሻለ ነበር፡፡ ምክንያቱም የህግ ልዕልና መከበር ስላለበት ነው፡፡ በሌላም በኩል ፍትህ ማግኘት የዜጎች መብት ነው፡፡ ከነዚህ ደንበኞቻችን ደግሞ ፍትህን የተጠሙ በመሆኑ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አፋጣኝ ፍትህን ይሻሉ፡፡ እንደ ሌላ ሆኖ መታየት ግን መኖር የለበትም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ የቀጠሮው በድንገት መራዘም የፖለቲካ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል?
ተማም፡ እኔ እውነቱን ለመናገር በእርግጠኝነት ‘ፖለቲካዊ ነው? አይደለም?’ የሚለውን ለማወቅ አልችልም፡፡ ነገር ግን ፍትህ የሚሰጥበት ቀጠሮ የተራዘመበት አካሄድ ፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ በመነሳት ትርጉም መስጠት ይቻላል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ከዚህ በኋላም ብያኔው ሊዘገይ ይችል ይሆናል የሚል ስጋት ያላቸው አሉ፡፡ የእርስዎስ ስሜት ምን ይመስላል?
ተማም፡ በእኔ በኩል ተገቢ ያልሆኑ አካሄዶችን መልመድ አልፈልግም፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ብዙ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም እኔ ግን እንዲሁ በየዕለቱ ከሚታዩ ችግሮች በመነሳት ከድምዳሜ ላይ መድረስ አልፈልግም፡፡ ለሀገራችንም ለሁሉም ቢሆን የሚበጀው ህግና ስርዓት አክብሮ መሄድ በመሆኑ በእኔ በኩል ህግን የተከተለ አካሄድ ይኖራል የሚል ተስፋ ነው ያለኝ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ከፍርድ ቤቱ ብያኔ እርስዎ ምን ይጠብቃሉ?
ተማም፡ እንደ ሕግ ባለሙያ እና ጉዳዩን በጣም በቅርበት እንደተከታተለ ጠበቃ መጀመሪያውኑም ቢሆን ደንበኞቼ በቀረበባቸው ክስ አጥፍተዋል ብዬ አላምንም፡፡ ብዙ ሰውም አያምንም፡፡ ወደ ኋላ ላይ በተግባር የታየውም ይሄው ነው፡፡ የተሳሳቱ ነገሮች ማስተካከል ይገባል ብዬ ስለማምን ከብያኔው ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ነገር ይገኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ደንበኞቻችን በሕጉ መሰረት በአግባቡ ተዳኝተው በነፃ ተሰናብተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ይቀላቀላሉ የሚል ተስፋ ነው ያለኝ፡፡ ማመን የምፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ በፍርድ ቤቱ ወቅት በአቃቤ ሕግ የቀረበው ማስረጃ ምን ይመስላል?
ተማም፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩህ ከፍርድ ቤቱ የሚጠበቀው ብይን ተከላከሉ ተብሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠት አልያም በነፃነት ማሰናበት መሆኑ ይተወቃል፡፡ ዓቃቤ ህግ ማስረጃ እና ምስክሮች ተሰምተው በማለቃቸው አሁን እኛ መከላከያችንን ማቅረብ ከመጀመራችን በፊት በነፃ ይለቀቁ የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ የቀረበው ማሥረጃ ይቅርና በደንኞቻችን ላይ የተመሰረው ክስ በራሱ ሕግን የመጣስ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ነው፡፡ እንደ እኔ ከሆነ የቀረበው ማስረጃ ሰዎቹ የተሰጣቸውን አደራ መጠበቃቸው እንጂ ሌላ ያጠፉት ነገር የለም፡፡ ወንጀል በድርጊት የሚከወን እንጂ በሕግ የተሰጣቸውን መብት በስራ ላይ ማዋል አያስከስስም፡፡ ለዚህ ነው እኔ መከላከያ ማቅረብ ሳያስፈልግ ደንበኞቻችን ይለቀቃሉ የሚል እምነት ያሳደርኩት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ የክሱ ጭብጥ በአጭሩ ሊገልጹልኝ ይችላሉ?
ተማም፡ በእኛ ደንበኞች ላይ የቀረበውን ክስ ገጽ ሃያ ላይ ስትመለከት ብዙ ዝርዝር ነገሮችን ካወራ በኋላ ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ እንደቆዩም ካስታወሰ በኋላ ከመንግስት የካቲት 26 ቀን መልስ እንደሰጣቸው ይገልጻል፡፡ በኋላ ግን መልስ እንዳልተሰጣቸው ሆኖ መቆየታቸው አግባብ አለመሆኑ፤ አንድ ወታደር ለመደብደቡ እና አንድ አውቶብስ መኪና ለመጎዳቱ ራሳቸው ጉዳት አድራሽ ሳይሆኑ መንስዔ ሆነዋል የሚል ነበር፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ኮሚቴው የመንግስትን ምላሽ የመቀበል ግዴታ ነበረበት?
ተማም፡ አይደለም! መንግስት መልስ ሰጥቼያለሁ ቢልም እነርሱ እኮ መልሱ በአግባቡ አልተሰጠንም የማለት መብት አላቸው፡፡ ይሄ በግልፅ መታወቅ ያለብት ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ በመንግስት ሚዲያዎች ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት መታሰቡ ይነገራል፡፡ ይሄ ጉዳይ ክሱ ላይ አለ?
ተማም፡ በፍፁም የለም፡፡ የኛ ደንበኞች የተከሰሱት ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው ነገሮች ብቻ ነው፡፡ ዙሪያ ጥምጥም እየተሄደ ከበሮ እየተመታ የሚነገረው በሙሉ አሳዛኝ ነው፡፡ ሌላው የሚያሳዝነው ነገር ወታደሩን ሰውዬ መትቷል የተባለው ሰው እንኳን በገንዘብ ነው የተቀጣው፡፡ አሸባሪ አልተባለም፡፡ ተከሳሾቹም ቢሆኑ እኮ መቱ አልተባሉም፡፡ ያን ድርጊት እነርሱ አነሳስተዋል ነው የተባሉት፡፡ የመታው ሰው በገንዘብ ተቀጥቶ እነርሱ በአሸባሪነት ተከሰዋል፡፡ እንዴት አድርገው እነርሱ ሰውን ለአድማ አነሳሱ የሚለውን ማስረዳቱ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ በክሱ ዝርዝር መደምደሚያ የሚለው በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ፣ በእነርሱ ምክንያት ወታደር ተመታ መኪና ተሰበረ ይላል፡፡ ማን መታ ለሚለው ሆነ መቶ ሺ ብር አካባቢ በአውቶብሱ ላይ ደረሰ ለተባለው ጥፋት ጉዳት ያደረሱት የኛ ደንበኞች አይደሉም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ ከመንግስት የተሰጠውን ምላሽ ኮሚቴው መቀበል ነበረበት?
ተማም፡ በማንኛውም ጉዳይ ሲደራደሩ የነበሩ ሰዎች በሕጉ መሰረት በተቻለ አቅም አንደኛው መልስ ሰጥቼያለሁ ቢል ሌላኛው ወገን አልተመለሰልኝም ማለት መብቱ ነው፡፡ በጉልበት ካልሆነ በቀር መልሼልሃለሁ ተቀበል ብሎ ነገር በሕጉ መሰረት አግባብነት የለውም፡፡ እኛም ለዚህ ነው በደንበኞቻችን ላይ የቀረበው ክስ መንግስት ‘በግድ የሰጠነውን መልስ ተቀበሉ’ የሚል አንድምታ ይኖረዋል የምንለው፡፡ ዋናው ነገር ግን መንግስት ያኔ ምላሽ ሰጥቺያለሁ ቢልም የተካሄደ ምንም ዓይነት የሕዝቡን ጥያቄ የፈታ አማራጭ አልነበረም፡፡ በሌላም በኩል ሕዝቡም በምላሹ ተደስቻለሁ አላለም፡፡ በዚህ የተነሳም እነርሱ ተገቢውን መልስ የመረጠን ሕዝብ አላገኘም ለማለት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው ከመንግስት ተሰጠ የተባለውን መልስ እንዲሁ የመቀበል ግዴታ የለበትም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡ በስተመጨረሻ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚሳስብዎት ነገር ካለ?
ተማም፡ በእኔ በኩል ኢስላማዊ መንግስት እየተባለ ከደንበኞቻችን ጋር ለምን እንደሚወሳ አይገባኝም፡፡ አንደኛ ይሄ አካሄድ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት በፍፁም አያስኬድም፡፡ ሌላኛው ትልቅ ጉዳይ ደግሞ ይሄን ዓይነቱ ነገር ደጋግሞ ማውሳት አላስፈላጊ ጥላቻን ሊዘራ ይችላል፡፡ በተለይ ግን ይሄንኑ ኢስላማዊ መንግስት የመመስረት ጉዳይ ከደንበኞቻችን ጋር አያይዞ ማቅረቡ ትርጉም አልባ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእነርሱ ላይ በቀረበው ክስ ላይ በፍጹም እንዲህ ዓይነት ሓሳብ አለመኖሩ መታወቅ አለበት፡፡

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Interviews Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. hassen says

    August 28, 2014 11:58 pm at 11:58 pm

    አላህ ይርዳቸው.

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የአየለ ጫሚሶ ቅንጅት ፈረሰ January 18, 2021 02:31 pm
  • ህወሓት ተሠረዘ!!! January 18, 2021 01:32 pm
  • ዓሲምባ፣ ሣልሳዊ ወያኔና ባይቶና ከመፍረሳቸው በፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተነገራቸው January 18, 2021 01:00 pm
  • ቤተሰቦች አስከሬን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገረ January 14, 2021 06:48 pm
  • ስብሃት፤ “ከሞትን ቆይተናል፤ … አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችን” እየተፈጸመ ነው January 14, 2021 01:37 pm
  • “ተመልሰን እንነሳለን” ያሉት ህወሓቶች ተመልሰው ወደማይነሱበት ተሸኙ January 13, 2021 01:12 pm
  • አፋር ነፃ አውጪ (ኡጉጉሙን) ለመጠቀም የታቀደው የህወሃት ሤራ ከሽፏል January 13, 2021 01:10 pm
  • ህወሃትን ወደ ጅቡቲ ለማሻገር ሲሰሩ የነበሩ የአፋር ታጣቂዎች በሰላም ወደ ክልሉ ገቡ January 13, 2021 06:47 am
  • በታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ January 13, 2021 06:10 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? January 13, 2021 04:10 am
  • ለትምህርት እንዲሆነን January 11, 2021 01:20 pm
  • “ከተቀበሩበት የጃርት ጉድጓድ ነው ያወጣናቸው” መቶ አለቃ ስዩም ቱርቦ January 11, 2021 12:11 pm
  • የተደመሰሱና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወንበዴው አባላት ይፋ ሆነ January 7, 2021 01:16 pm
  • ዐቢይና መኮንኖቹ በመቀሌ፤ “ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” December 13, 2020 02:36 pm
  • ወንበዴው ህወሓት ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች አስቀምጧል December 8, 2020 01:05 am
  • ማይካድራ – የትህነግ የዘር ማጥፋት ጥግ ቋሚ ምስክር December 8, 2020 12:57 am
  • የወልቃይት ጠገዴ እናቶች ሰቆቃ ሲታወስ December 8, 2020 12:50 am
  • የደብረጽዮን ዋሻ December 7, 2020 11:30 pm
  • ባለ ከዘራው ኮሎኔል December 7, 2020 05:15 pm
  • ሰላማዊ ሕይወት በማይጨው December 7, 2020 04:12 pm
  • ተጠርጣሪ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊሶች የመያዣ ትዕዛዝ ወጣባቸው December 7, 2020 11:46 am
  • ከ3 ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች በወልዲያ ጉምሩክ ሊያሳልፉ የሞከሩ 4 ግለሰቦች ተያዙ! December 7, 2020 11:18 am
  • ወንበዴዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው ተያዙ December 7, 2020 10:50 am
  • ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሶማሌ ክልል ተመሠረተ December 7, 2020 10:31 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule