ሕግ በረጅም ገመድ ያሰረው ጃዋር!
ቅድሚያ “ኢትዮጵያዊ ፣ አባ ሜንጫ፣ አክቲቪስት፣ ተንታኝ፣ ፖለቲከኛ፣ አሁን ደግሞ “ሐጂ” ሆንኩ ያለው ጃዋር ማነው ነው? የሚለው ድብልቅልቅ ጉዳይ መመልከት ያሻል። ወይም የተለያዩ ማንነት ያለበት ጥያቄ መመለስ ግድ ነው።
ጃዋር ወደ ፖለቲካ ሲመጣ በዳያስፖራ ያሉትን አገር ወዳዶች ለማማለል ፍጹም ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ በንግግሩ ሁሉን አስደምሞ ነበር ብቅ ያለው። ነገሮች መስመር ሲይዙለትና ደጋፊ ሲያገኝ እነዚህኑ ወደ ላይ የሰቀሉትን መሳደብና ኢትዮጵያን ማበሻቀጥ ጀመረ። በወቅቱ ተው ብለው አዛውንቱ የዳያስፖራ ምሁራን መከሩት። ወደላይ እየወጣ ስለነበር ይልቅ እኔን ብትሰሙ ይሻላል አላቸውና አልፏቸው ተስፈነጠረ።
በቀጣይ ለኦሮሞን ትግል “አዲስ ትንፋሽ ነኝ” በማለት ራሱን መሪ አድርጎ ሾመ። የቀድሞ የኦሮሞ ታጋዮችን በተለይም ዕንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን በየሚዲያው እስኪበቃቸው አብጠለጠላቸው፣ ተናገረባቸው፣ ጻፈባቸው፣ ተፋባቸው። እነርሱን አበሻቅጦና አራክሶ የራሱን መንገድ በእነሱ ውርደት ላይ ገነባ።
ትምህርቱ ከሚዲያ ጋር የተገናኘ ስለሆነ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመዘወር ረገድ የሚዲያን ጥቅም ጃዋር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ስለገባው በክፉም በደጉም ሚዲያ ላይ ላይ ውሎ አዳሩን አደረገ። ባገኘው አጋጣሚና በዘረጋው መዋቅር ሚዲያ ላይ ተሰቅሎ ኦሮሞን የሚወክል ሚዲያ ለመክፈት በበርካታ የኦሮሞዎች ወጣቶችና ምሁራኖች ሲቀነቀን የነበረውን ሃሳብ ጃዋር እንደ ጊንጥ ተጣበቀበት። ለሱ ብቻ በሚታየው መዳረሻው ሰንኮፉን ተክሎ አጋር፣ ተባባሪ በመምሰል ቡድኑን ተቀላቀለ። ሰንኮፉ አይታይምና ትኩስ ኃይል ያገኙ የመሰላቸው ሁሉ በእልልታ ተቀበሉት።
የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ሲመሠረት ጃዋር አንድ ሰው ነበር እንጂ ሚዲያው የግሉ ሃብት አልነበረም። ሆኖም የመለስ ዜናዊ አድናቂ እንደሆነ በገሃድ የሚናገረው ጃዋር አብረውት ሚዲያውን የጀመሩትን ቀስ በቀስ ቅርጥፍ አድርጎ በላቸው፤ የተቀሩትንም ከጫወታ ውጪ አደረጋቸው። ይህ ራሳቸው አብረውት ሚዲያ የጀመሩት የመሰከሩት ዛሬ ድረስ አየር ላይ ተሰንቆ ቁጭ ያለ ሃቅ ነው። እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ጉዳይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ መስራቾችም ይፋ እንዳደረጉት በመዋጮ ከመሃል ፖለቲከኞች፣ አመራር ውስጥ ያሉ አካላትና ድርጅታቸው የሚደገፉት “የሕዝብ” የተባለ ሚዲያ ነበር።
ጃዋር ከሚዲያ ምሥረታ በፊት የተወናቸው ሁለት ተውኔቶች አሉ። የመጀመሪያው የድምጻችን ይሰማ የሙስሊም እንቅስቃሴን መቀላቀል ነው። ሙስሊም ኦሮሞ ስለሆነ አልከበደውም። ሆኖም ዓላማው ሙስሊሙን የለውጥ እንቅስቃሴ ለውጤት ማድረስ ሳይሆን ትግሉን ቀልብሶ ለራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ነበር።
በሙስሊሙ እንቅስቃሴ እንዲሳብ ያደረገው አንዱ ነገር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ የዕዝ ሠንሠለት ተከትሎ የነበረው አደረጃጀትና ትዕዛዝ አፈጻጸም ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ በድምጻችን ይሰማ አንቂዎች የተሠራው መስተጋብር ከውጪ እስከ አገር ውስጥ ከተሞች ከዚያም ሲያልፍ እስከ ትንንሽ ወረዳና የገጠር ቀበሌ ተሰናስሎ የሚደማመጥ ነበር። ለምሳሌ ሃሙስ ማታ ለጁምዓ ተብሎ የተጠራ ተቃውሞ አርብ ጠዋት ከሶላት በፊት ከተቀየረ ሁሉም ሙስሊም በተዋረድ መቀየሩን ሰምቶ ይተገብራል። የሚወጣው መፈክር እንዲሁ ከተቀየረ ያለአንዳች ችግር ወዲያውኑ በኔትዎርኩ እንዲቀየር ይደረጋል።
እንዲህ ያለውን መስተጋብር ሲመኝ የነበረው ጃዋር ሙስሊሙን ያገዘ መስሎ እንቅስቃሴውን ተቀላቀለና ትልቅ ፋዎል ሠራ። አስቦበት ይሁን ወይም ለዓላማው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። ሆኖም የዛሬ ፱ ዓመት አካባቢ ፈርስት ሒጅራ በጠራው ትልቅ ስብሰባ ላይ ጃዋር እሱ ባደገበት ቦታ ሙስሊም ያልሆነ በሜንጫ አንገቱ ይቀነጠስ እንደነበር በመናገር ተመሳሳይ ጥሪ አሁንም እንዲደረግ አወጀ። በውጤቱም የሙስሊም ትግል ቀዝቃዛ ውሃ ተደፋበት፤ ታላላቅ የሙስሊም መሪዎች እጅግ አዘኑ፤ አሁን ስም ጠቅሶ መናገሩ ባያስፈልግም በሚዲያ ላይ ያልወጣ ብዙ ነቀፋ አወረዱበት።
ጃዋር ግን ይህንን ከመናገሩ በፊት በዚያን ወቅት በየሚዲያው እየወጣ ትግሉ የሙስሊም ብቻ ሳይሆን የኦሮሞም ነው በማለት የክርስቲያን ኦሮሞዎችን ድጋፍ ለማግኘት ሲታትር ነበር። እንዲያውም ኦሮሞ እስከ ጎንደር ድረስ ነው ያለው፤ ሙስሊምም እንደዚያው፤ ስለዚህ የጎሣና የሃይማኖቱን ጥምረት ማፋፋም ያስፈልጋል ሲል በስፋት ተሰምቷል። አስልቶ በዋጠውና ብር በገፍ ባመረተበት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በኩል “ደጋፊ ለማግኘት የብሄርና የሃይማኖት ቅሰቀሳ ተመራጭ ነው” ሲል አምልጦት ይሁን አውቆ በራሱ ላይ በቁሙ ኑዛዜ አሰምቷል።
የድምጻችን ይሰማ ትግል ከተቀዛቀዘ በኋላ ጃዋር አቅጣጫውን በመቀየር “ኦሮሞ ፈርስት” በሚል አሜሪካን እና አውሮጳን በመዞር ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመረ። የጎሣ ፖለቲካ ጠላት ፈጥሮ ጥላቻን የሚሰብክ በመሆኑ ጃዋር እጅግ ብዙ ገንዘብ እንደሚያስገኝለት ስላወቀ ገፋበት። በዚህ ወቅትም አንድ ሌላ የታወቀበትንና የበርካታ ጽንፈኞችን ቀልብ የገዛበትን ንግግር በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሲስተጋባ ተሰማ። ትንሽዋን ኦሮሚያ ከታላቋ ኢትዮጵያ አስበልጦ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” ወይም “ኢትዮጵያ አውት ኦቭ ኦሮሚያ” የሚል መፈክር አሰማ።
በቀጣይ የኦሮሞ ሚዲያ የመክፈቱን ዓላማ ይጋሩ ከነበሩት መካከል የኦ-ፕራይድ አዘጋጅ መሃመድ አዴሞ እና ሌሎች አብረውት ሲያዘጠዝጡ ከረሙ። ትንንሽ ከሚባሉ የአሜሪካ ከተሞች ሳይቀር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር የሰበሰበው ጃዋር ወዳጆቹን በካልቾ አላቸውና ኦ.ኤም.ኤን. የራሱ አድርጎ ጠቀለለው። ከዚህ በፊት እነ አልጃዚራ ለጃዋር በሚዲያ ገንኖ መውጣት ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል። መሃመድ አዴሞ ከአሜሪካ ለአልጃዚራ የሚዘግብ እንደነበር ልብ ይሏል።
ከኦኤምኤን ምሥረታ በኋላ የተነሳውን የኦሮሞ ተቃውሞ (ኦሮሞ ፕሮቴስት) ጃዋር በፍጥነት ተቀላቅሎ ትግሉን ጠለፈው። ሲጀመር የነበረው ስምምነት አገር ውስጥ ያሉት የኦህዴድ ሰዎች መዋቅሩን ሊከፍቱለትና መረጃ ሊያቀብሉት፤ እሱም የሚላክለትን መረጃ ፍሰቱን ጠብቆ ለሕዝብ እንዲያቀርብ ነበር። በሌላ አነጋገር ከመሃል አገር ከመንግሥት መዋቅር የሚወጣውንና የሚላክለትን መረጃ ተቀብሎ እንዲበትን ነበር በለውጡ መሃንዲሶች የተቀጠረው።
ማኪያቬሊያዊና መለስ ዜናዊ ስልት የሚከተለው ጃዋር እሺ ለማለት ብዙም እልጨነቀውም። ትግሉ ሲጀመርና የሟቾች ፎቶ እየተላከለት ባለበት የመጋቢት ወር አካባቢ የሦስት ወይም ሁለት ወጣቶችን አስከሬን ፌስቡኩ ላይ ለጥፎ፤ “ጨምራችሁ ግደሉ ዋጋው በእኛ ላይ ነው” በማለት ለሰው ሕይወት ምንም የማይጨንቀው አውሬ መሆኑን መሰከረ። ማለትም እሱ ማኪያቶውን ሜኔሶታ እየጠጣ በግፍ የሚገደሉ ወጣቶችን ፎቶ ለመለጠፍና የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በዕቅድ መዘጋጀቱን ፍንትው አድርጎ አረጋገጠ። በምስኪኖች አስከሬን ዝናና ስም ተክሎ ብር አጋበሰ፤ አመረተ።
ኢህአዴግ ምርጫ ሊያደርግና መሪ ሊሾም ባለበት ወቅት ላይ ዐቢይ አህመድ እንደሚመረጥ ግልጽ እየሆነ ሲመጣ ጃዋር ባይሳካለትም በዐቢይ ምትክ ለማ መገርሳ እንዲመረጥ ትልቅ ውስወሳ አድርጓል። እንዲያውም በዚያን ወቀት በኦኤም ኤን ላይ ከሕዝቅኤል ገቢሳ ጋር ሆኖ የፓርላማው ሕግ ተቀይሮ ለማ ከክልል ተመራጭነት ወደ ፌደራል ፓርላማ እንዲገባ መደረግ አለበት ብለው ብዙ ጥረት አድርገው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ለውጥ መጥቶ ጃዋር ወደ አገር ሲመለስ ዋነኛ ዓላማው በወቅቱ አዲሱ አረጋ ይዞት የነበረውን የኦሮሚያ ገጠር አደረጃጀት ዋና ቢሮ መምራት ነበር። ዓላማው የገባቸው የኦህዴድ ሰዎች ሥልጣኑን ሲነፍጉት ነቀለ። በከፈተው ሚዲያና ይዞት በገባው ግማሽ ቢሊዮን ብር በርካታ የአገር ውስጥ የሚዲያ ቡድኖች ከፈተ። እነዚህም በአማርኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ፣ በአገው፣ ወዘተ የሚዘግቡና በእርሱ ድጎማ የሚደረግላቸው ነበሩ። ጉለሌ ሚዲያን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ዛሬ ደግሞ ኡቡንቱ!! በነገራችን ላይ ኡቡንቱ አዲሱ የጃዋር ፈረስ እንዲሆን ታስቦ የተከፈተ የድህረ እስር ሚዲያ ነው።
ጃዋር አልሞና አስቦ በከፈታቸው የሚዲያ አውታሮች የሚረጨው መርዝ ኢትዮጵያን አፈናት። ምድሪቱ በዘር ፖለቲካ ጦዘች። ሰዓት እየከፋፈለ አንዴ ቅማንት ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤጀቶ እያለ አገርና ህዝብን አወከ። የሲዳማ በደል እንዲወራ ያደርግና ሲዳማዎን ከወላይታዎች ጋር ያባላ ጀመር። ከዚህ ሌላ ያለማቋረጥ ስለ አገውና ቅማንት ሕዝብ እንዲወራ፣ አጀንዳ እንዲሆን፣ ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በኦኤምኤን እንዲሰራጭ እርፍት እስኪያጣ ደከመ። ከሚሴ ገብቶም ሁከት ነዛና አብረው ለዘመናት የኖሩ ወገኖችን እሳት አደረገ።
በአንድ ወቅት አገር ቤት የገባ ሰሞን በራሱ ሚዲያ ቀርቦ ስለ ለውጡ ብዙ ከተናገረ በኋላ በቀጣይ ስለሚሆነው ወይም መሆን ስለሚገባው ነገር የተናገረውን አሁን ደግሞ ቢሰማው ራሱ ጃዋር ይደነቃል። ቃል በቃል ያለው “አሁን ዐቢይ የሚመራው የሽግግር መንግሥት ነው … ማንም ያለ ምርጫ በሽግግር መንግሥት ስም ሥልጣን በአቋራጭ መሞከር አይችልም” ነበር ያለው።
ይህንን ሲል የነበረው ጃዋር ወዲያውኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግሥት እንዳለ ሲናገር ቆየ፤ አንዱ አራት ኪሎ ያለው ሲሆን 2ኛው ደግሞ የቄሮ መንግሥት እንደሆነ አስታውቆ ራሱን ሾመ። የመደበኛው መሪ ዐቢይ ከሆነ የቄሮው ደግሞ ራሱ መሆኑ ነው። በዚሁ ጊዜ “ብንፈልግ አራት ኪሎን መቆጣጠር አያቅተንም” ሲል በገሃድ ገለጸ።
በዚህ ልክ የሥልጣን ጥማቱን በአደባባይ ሲናገር የነበረው ጃዋር የመጨረሻ የሚባለውን መተግበር ግድ ሲሆንበት በቅድሚያ የፖለቲካ ድርጅት መቀላቀል አስፈላጊ መሆኑን በመረዳቱ መረራ ጉዲናን ከነፓርቲው በበቀለ ገርባ አሻሻጭነት ጠቀም ባለ ብር ገዛው። በስፖርቱ ቋንቋ ለጠቅላይ ተጫወተበት። ቀጥሎም የኦሮሞ ፓርቲዎች ውኅደት ብሎ የዳውድ ኢብሣን ኦነግና የከማል ገልቹን ፓርቲ ከኦፌኮ ጋር ለማጣመር ሌላ ድራማ ተወነ። ዳውድ የጥምረቱ መሪ ተብሎ ተሾመ፣ የፊርማ ሥነሥርዓት ተደረገ፣ ዳውድ ዲስኩር ሰጠ። በነጋታው ግን ጃዋር ዳውድን “እውነት መሰለህንዴ?” ማለት ሲጀምር ከማል ገልቹ ከውህደቱ ወጣ፣ በዚያው ሁሉም ፈረሰ።
ጃዋር እየተገለባበጠ ያደረገው ሙከራው ሁሉ የእንቧይ ካብ እየሆነበት ሲመጣ የመጨረሻውን ውሳኔ መተግበር ግድ ሆነበት። ሥልጣን እንዳሰበው በቀላሉ የሚያዝ እንዳልሆነ እንዲያውም በጣም እየራቀው እንደመጣ ሲያይ ኦፐሬሽን ሃጫሉን ተገበረ። ሃጫሉ ኦኤምኤን ላይ ወጥቶ የተናገረው እሱ ባልገመተው መንገድ ቀለበት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ነበር። የሃጫሉ መገደል የሚቀሰቅሰው ቁጣ ለጃዋር የአራት ኪሎን በር ወለል ብሎ የተከፈተ እንዲመስለው አደረገ። ሃጫሉ ከተገደለ በኋላ በአስከሬኑ ላይ የተፈጸመው ድራማ እና ፖለቲካ ያለ ቅንብር፣ ያለ ዕቅድ ነው የሆነው የሚለውን የሚያምን የጃዋርን ማንነት የማያውቅ ወይም ፖለቲካ ያልገባው ነው። በተለይ ከግድያው በኋላ በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሐመድ፣ ሃምዛ ቦረና፣ … ዞን እና ቀጣና ተከፋፍለው መረጃ እየበተኑ ዕልቂት እንዲነሳ፣ አገሪቷ እንድትናወጥ በማድረግ የፈጸሙት ተግባር ቢሳካ እሳቱ ዛሬ ድረስ የሚንቦገቦግ በሆነ ነበር።
ከሃጫሉ ግድያ በፊት የቁማሩ ካርድ እያለቀበት ሲመጣ ጃዋር አንድ ድራማ ተውኖ ነበር። የኦሮሞ ወጣቶች እንዲነሱ ታፍኛለሁ፣ ታግቻለሁ፣ ብሎ አገር በማናወጥ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ፤ ንብረት ያወደመ እጅግ አሰቃቂ የግፍ ድራማ ተጫውቷል። ግን መንግሥትን ገልብጦ ሥልጣን ማማ ላይ መውጣት አልተሳካም። ይልቁኑ ከዚያች ቀን ጀምሮ በሩቅ ሸብ የተደረገበት ገመድ ጠበቀ። ገመዷ ጠብቃ ሳለ በሃጫሉ አስከሬን ሥር ቁማር ፈጸመ። አስከሬን ከቤተሰብ ነጥቆና አስነጥቆ ከበቀለ ገርባና ከጀርባ ካሉት ጋላቢዎች ጋር ሆኖ አዲስ አበባን በነውጥ ሊያበራይ የያዘው እቅድ እንደ ጭስ ተነነበት። የጠበቀውም ገመድ አነቀውና “ብዙ ዓመት ሳወራ ኖርኩ። እስኪ ላዳምጥ ብዬ ዝም ብዬ ተቀመጥኩ” ብሎ የሚናገር እንደበተ ልስልስ ሆኖ የወጣበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ተከረቸመ።
ዐቃቤ ሕግ ክስ አቋርጦ ጃዋርን ከእስር እንዲወጣ ከፈቀደለት በኋላ ለወራት ምንም ነገር ሳይናገር ቢቆይም በእነዚህ ወራት አንድ የፈጸመው ወሳኝ ተግባር አለ። ረመዳንን ጠብቆ ለሐጂ ለሐጂ ዑምራ ወደ መካ ነበር የሄደው። (መዘርዘር ባያስፈልግም) ከሃይማኖቱ ጋር በጣም ተጻራሪ (ሃራም) የሆኑ ተግባራትን ሲፈጽም የኖረው ጃዋር ባልታሰበ ሁኔታ ሐጂ ማድረጉ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ለመፈጸም ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ከአሜሪካ ወደ አገር ቤት ከመጣ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቆይ ለሐጂ ብዙ ትኩረት ያልሰጠው ጃዋር በዚህ ወቅት ማድረጉ የጤና እንደሆነ አድርጎ መቀበል አይቻልም። ጃዋር ይህንን ሃይማኖታዊ ተግባር የፈጸመው እንደ ሌሎች ሃይማኖቱን ናፍቆ፣ ሥርዓቱን አክብሮ ለመቀደስ እንዳልሆነ ከduty free ብሉ ሌብል (Blue Label) ዊስኪና ኤሌክትሮኒክ ኮንዶም የሚያግዙለት የነበሩ ቀኑ ሲደርስ ምስክርነት የሚሰጡበት ጉዳይ ይሆናል። እናም አያ ጃዋር “ሐጂ” የሚለውን ማዕረግ የተጎናጸፈው ፊቱን ወደ ሃይማኖታዊ ፖለቲካ ሊገለብጥ እንደሆነ በርካታ ጠቋሚዎች አሉ።
“ኦሮሞ ሲነካ እስልምና ይነካል፤ እስልምና ሲነካ ኦሮሞ ይነካል” ብሎ የተናገረው ጃዋር የኦሮሞንና የሙስሊሙን ድጋፍ አቀናጅቶ መያዝ ለአራት ኪሎ እንደሚያበቃ ጠንቅቆ ያውቃል። ትልቁ ችግር ሁለቱን አጣምሮ ረጅም ርቀት ማስኬድ እጅግ ከባድ መሆኑ ላይ ነው። ምክንያቱም ሙስሊም ያልሆኑትና እንዲህ ያለውን ክፉ ሂሳብ የሚጠየፉ፣ ሙስሊምም ሆነው በልዩነት ለመጠቀሚያነት ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የማይወዱ አብዛኞች፣ ከሁለቱም ወገን ሆነ ኦሮሞ ያልሆኑት ወገኖች፣ ቀና አሳቢዎች ጋር ሲደመሩ የሐጂ ጃዋርን ሂሳብ ጠኔ ያንፈራፈረው የትህነግ ጭፍራ አማራ ክልል ገብቶ እንደዘረፈው አሻሮ ዓይነት ያደርገዋል።
እኔ ከታሰርሁ ይቺ አገር ድብልቅልቋ ይወጣል፤ ቄሮ ይነሳል፤ ዳያስፖራው በውጪ ታላላቅ ከተሞችን በሰልፍ ያናውጣል፤ ለዚህ ነው የማልታሰረው፤ ወዘተ የሚሉ ድንፋታዎችን ሲያሰማ የኖረው ጃዋር እስር ቤት የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈጽሞ እንደማያውቀው በበቂ ሁኔታ አስተምሮታል ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ በራሱ የሚፈጥረው የቅስም መሰበር ስሜት በቀላሉ የሚለቅ አይደለም። ስለዚህ ጃዋር ማሰብ አለበት። ከፖለቲካ እንደማይወጣ ኦፌኮ ባደረገው ስብሰባ የፓርቲው ምክትል ሆኖ በድጋሚ መመረጡ አንድ ማሳያ ነው። የኦፌኮ መንገድ ግን ወደ አራት ኪሎ እንደማያደርሰው እርሱም የኦፌኮ ሰዎችም ጠንቅቀው የሚያውቁት ነው። ስለዚህ ማሰብ የሚጠይቅና በጥንቃቄ የሚተገበር አቅጣጫ ቀያሪ ሥልት መነደፍ አለበት።
ጃዋር በቅርቡ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ከቢሮ ዕይታ ጀምሮ ሌላ ሰው ሆኖ ነው የቀረበው። ከኦሮሚያና ኦነግ ባንዲራ ውጪ በቢሮው የማይታይ የነበረው ጃዋር አሁን ግን በመካከል የኢትዮጵያን ሠንደቅ አድርጎ በረጋ መንፈስ ሲናገር ተደምጧል። በደም ፍላት፣ በሁሉን አውቃለሁ ባይነትና በትዕቢት ሲናገር የሚታወቀው ጃዋር እስርቤት ያጎናጸፈውን ሽበት እያብረቀረቀ የኢትዮጵያ አዲስ መሢሕ ሆኖ ነው የታየው። አዲስ ሆኖ ሲቀርብ አሁንም ግን ጠቅላዩን ለማናገር እንደሚመኝ አልሸሸገም። በአንድ ወቅት “ተደምረሃል ወይ?” ተብሎ የተጠየቀው ጃዋር የመለሰው “የመደመሪያውን ካልኩሌተር የሠራነው እኛ ነን” ብሎ ማለቱን እዚህ ላይ መጠቆም ግድ ይላል።
በቅርቡ ከዑቡንቱ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ የሰሙ የኦሮሞ አክቲቪቶች ነን የሚሉ ብዙም አልተደሰቱም። “ጃዋር ተሸጧል፣ ከድቶናል፣ ከመንግሥት ጋር እየሠራ ነው” በማለት ነቀፋ እያወረዱበት ነው። “ቄሮ!” ብሎ ሲጮህ ብቅ ይሉ የነበሩት ጀሌዎቹም አሁን በኩታ ገጠም እርሻ ተጠምደው ስንዴ እያመረቱ ነው። ከእስር ከወጣ በኋላ የኦሮሚያ የፖለቲካ መልክዓ ምድር ከጠበቀው ውጪ ሆኖ ተቀያይሯል። በበቀለ ገርባ በኩል ሲዘውረው የነበረው ሸኔም አከርካሪው ተመትቶ ለመሞት እያቃሰተ ነው። ስለዚህ ጃዋር የቀረው አንድ የትግል መስክ ብቻ ይመስላል – ሃይማኖት ተኮር ፖለቲካ!!
በኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ ለማስነሳት እየታሰበ ያለው ግጭት ከሃይማኖት ጋር እንደሆነ አስቀድሞ ሲነገር የቆየ ነው። ወሎዬውን ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ እንድሪስን ከሥልጣናቸው ለማውረድና በሌላ ለመተካት የተሄደበት መንገድ አንዱ ጠቋሚ ነው። እነ አህመዲን ጀበል እየሠሩ ያሉት ሤራ፣ በጎንደር የተፈጸመው፣ ወዘተ አሁን ያለውን መንግሥት ለማስወገድ ለብዙዎቹ የከሰሩ ፖለቲከኞች እንደ አማራጭ የሚታይ መፍትሔ ነው። የጃዋርን ንግግር ሙስሊም ያልሆኑ ኦሮሞዎች የተቃወሙትን ያህል የሌሎች ብሔረሰብ ሙስሊሞች ግን በአብዛኛው መደገፋቸው የጃዋር ቀጣይ የትግል መስክ ወዴት እያጋደለ እንደሆነ የሚሰጠው ፍንጭ አለ። ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በአውሮጳው የገለቶማ ጉዞ ላይ አማርኛ በስበስባ አዳራሾች መሰማቱ ሌላው ቀልብ የሚስብ ጉዳይ ነው።
በዚህ ሁሉ መሃል ግን ጃዋር አጣብቂኝ ውስጥ ነው። ብሩን ሆጭ አድርጎ የገዛው የመረራ ጉዲና ፓርቲ ጠንካራ የሚባለው ደጋፊው ያለው ሸዋ ውስጥ ነው። የሸዋ ኦሮሞ ደግሞ ባብዛኛው ክርስቲያን ነው። በኦፌኮ ሥር ሆኖ የሸዋን ኦሮሞ ከሙስሊም ጋር አጋብቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ካሰበ በራሱ አንገት ላይ ገመዱን ሸመቀቀው ማለት ነው። አሁን በአውሮጳና አሜሪካ በሚያደርገው የ“ገለቶማ” ጉዞ ላይ ቀድመው ሲደግፉት ከነበሩት ኦሮሞዎች አቋሙን በተመለከተ ከረር ያሉ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል ተብሎ ይጠበቃል። እጅግ ቢጠነቀቅ እንኳን ቢንስ ባንዱ ስብሰባ ፋዎል መሥራቱ እንደማይቀር የበፊት ታሪኩ ይመሰክራል። ከዚሁ ጋር ተዳምሮ ጃዋር በታሠረበት ወቅት በዳያስፖራ ያለው የእርሱ ደጋፊ እንደሚገባው ሳይጮኹለትና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድምፅ ሳይሆኑለት በመቅረታቸው “ለካስ ብገደልም ኖሮ” የሚል ቂም አስቋጥሮታል የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ።
በገለቶማ ስብሰባዎች ላይ ጃዋር መንግሥትን የሚደግፍ ነገር መናገር ከቀጠለ “እስቲ ዓቋሙን እንፈትሽ ” በማለት መሃል ላይ ቆመው እየጠበቁት ያሉትን ጥለውት እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል። ሸኔን አስመልክቶ የእርሱ ፓርቲ ያለው ዓቋም ግልጽ አይደለም፤ እነ መረራ አንዴ መንግሥት ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ድርድር ያድርግ ይላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሸኔ የሚባል ነገር የለም ይላሉ። የሸኔ አብዛኛው ደጋፊ ደግሞ በዳያስጶራ የሚገኘው እንደሆነ ይገመታል። ይህንን እና መሰል ጥያቄዎችን ሲመልስ ጃዋር የሚሠራው ፋዎል ጉዞውን ጨርሶ ቦሌ ሲደርስ የቃሊትን መንገድ የሚጠርግለት ይሆናል። አንዳንዶች ጃዋር ከዐቢይ ጋር ተስማምቶ በይቅርታ ነው የወጣው እንደሚሉት ሳይሆን ጃዋርም፣ እስክንድርም፣ በቀለም፣ … የተለቀቁት እስራቸው ተቋርጦ ነው። የተቋረጠ ክስ በማንኛውም ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ግልጽ ነው።
ስለዚህ የሐጂ ጃዋር ቀጣዩ ጉዞ ለራሱም ግልጽ የሆነለት አይመስልም። ፖለቲካውን እስላማዊ ማድረግ ግን አንዱ አማራጩ እንደሆነ ብዙ ፍንጮችን አሳይቷል። ይህ መንገድ ደግሞ የጸዳና መዳረሻው የታወቀ ሳይሆን መርገጫ እስኪጠፋ ድረስ በተቀበረ ቦምብ የተሞላ ምድር ነው። የመንግሥት ሕግ የማስከበር ዓቅሙ ከበፊቱ በእጥፍ የጨመረ መሆኑ በይፋ በታየበት፣ ነፍጥ አንስተው ሲያምሱ የነበሩ ቀላቢያቸው በረሃብ ታንቆ፣ የሊጥና የአሻሮ ሌባ፣ የእንኩሮ ቀማኛ መሆኑን ሲያዩ የቻሉ በሰላም እጅ እየሰጡ፣ ያልቻሉም እየቀመሱ ስንበት ላይ በሆኑበት በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ የሃይማኖት ጭምብል ለብሶ መንከላወሱ ሰላም በጠማው ሕዝብ ላይ መቆመር ነውና በድጋሚ ፈቃድ የሚሰጥ አይኖርም።
በሌላ በኩል ጃዋር አሁን በቁጥጥር ሥር ለምትገኘው መዓዛ መሐመድ ለምትባለው የዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ቅልብ፣ “ጃዋርን ቃሊቲ ልትጠይቀው ሄዳ የአንድነት ኃይሎች ጉድ አደረጉኝ” ሲል የነገራትን አቤቱታ በማሰላሰል፣ የአንድነት ኃይሎች የተባሉት የቂሊንጦ ፍቅረኞችን ቀረቶ ደጋግመን እየሰማን፣ ልደቱ አያሌው ጃዋርን እስር ቤት ጠይቆ ስለመከረው ምክር የትህነግ ሳንባ በሆነው ርዕዮት ሚዲያ የሰጠውን ሃተታ (በነገራችን ቴድሮስ የሚባለው ማየት የተሳነው ጠያቂ ምሥጢር ለመጠበቅ በሚመችህ መልኩ መመለስ ትችላለህ ያለውን ከዋጋ አስገብተን)፣ ወያኔ ያኮላሻቸው “ወያኔ ይሻላል” በሚል በገሃድ እየመሰከሩና አማራ ሆነው በአማራው ላይ ወያኔ ባደረሰው ግፍ የሚያሳለቁትን እየቃኘን የሁሉንም የሥልጣን ተመኚዎችና የሽግግር መንግሥት ተስፈኞች አሜሪካ መሰባሰብ ያልታቀደ ግጥምጥም ነው ማለት እንደማይቻል በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ያስፈልጋል – ልክ የጃዋር ፖለቲካዊ ሐጂነት ያጋጣሚ እንዳልሆነው ሁሉ!
ግርማ ጃለታ ከጀርመን
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Semaneh says
አቶ ግርማ ጃለታ፤
የከበረ ሠላምታየን ከኦታዋ ካናዳ ከከፍተኛ አክብሮት ጋር አቀርባለሁ። ይህን የመሰለ የፖለቲካትንታኔ ዎን (analysis) በጥሞና አነበብሁት። በእውነት ስለእውነት ትንታኔዎት እጅግ ትክክልናኛ፤ አስተማሪና ሐቀኛ ብቻ ሳይሆን ሃገር አድንም ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ይህን ጽሑፍ ለጠቅላይ ሚ/ር ዶክተር ዓብይና አማካሪዎቻቸው በቀጥታ እንዲደርስ ቢአደርጉ ጥሩ ነው። ከብዙ ጥፋት ሊታደጋቸው ይችላልና።
በተረፈ የኢትዮጵያ አምላክ ጤናውንና ሠላሙን ይስጥዎት።
እንደአቅሚቲ እኔም አልፎ አልፎ ጽሑፎችንና ገንቢ ሃሳቦችን አቀርባለሁ። በዘሃበሻ ድህረገጽ ላይ semaneh jemere ብለው ቢፈልጉ ያገኙአቸዋል። ሚመችዎት ከሆነ በኢሜል ያግኙኝና እንወያያለን፤ ስልክም እንለዋወጣለን።(stjtamrat@hotmail.com)
ኢትዮጵያ እርስዎን በመሰሉ አስተዋዮች ትሻገራለች። እንበርታ። ሰማነህታ. ጀመረ
ማስታወሻ፤ ጎልጉል ድሕረ ገጽ ይህን የመሰለ ጽሑፍና ትንታኔ ስላስነበበን ምስጋና ክብር ይድረሳቸው። ብዙ ጊዜ እደተገነዘብሁት ድረ ገጹ የሚአስነብበን እጅግ ጠቃሚ ሃሳቦችንና ትንታኔዎችን ስለሆነ ምስጋና ሲአንሳቸው ነው። ጎልጉሎች በርቱና በጽናት ጎልጉላችሁ ሐቁን አውጡ፤ አንቁን፤ አስተምሩን።