የዋልድባ ገዳም በህዋሓት መሪዎች በዓይነ ቁራኛ የወደቀው ገና ትግሉ እንደተጀመረ ነው። የዋልድባ ገዳም የህወሓት መሪዎች እንዲወድም ሃሳብ ያቀረቡት በ1973 መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፣ አቅማራ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በወቅቱ የህወሓት መናኸሪያ ነበር። በተመቤን ውስጥ የሚገኘው ቦታ በፕሮፓጋንዳ ጽ/ቤት ተሰብስበው ወሰኑ፤ በስብሰባ የነበሩት አመራር ፖሊት ቢሮው በሙሉ ነበር። እነሱም፣ ስብሃት ነጋ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ገደይ ዘርአጽዮን፣ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን እና መለስ ዜናዊ ነበር። በወቅቱ ማ/ኮሚቴ የነበሩ ናቸው።
በዚህ ስብሰባቸው የዋልድባን ገዳም እጣ ፈንታ ወሰኑ። ዋልድባ እንዲወደም! የዋልድባ ገዳም ለብዙ መቶ ዘመናት የቅዱሳን፣ ብፁአን፣ ባህታውያን፣ ቀሳውስት፣ አባቶች፣ ደናግል፣ ዲያቆናት ወዘተ ሰፈር በመሆን በኢትዮጵያ ቅዱስና በታሪክ ትልቅ ምእራፍ የያዘ ገዳም ነው። ይህ ቅዱስ ገዳም የቅዱሳን ማረፊያ በመሆኑ በታላቅነቱ የሚታወቅ ነው። ገዳሙ የታነጸው በ12ኛው ክፍለ ዘመን በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ዮሴፍ ነው። ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡም ያረፉበት፣ የተሰባሰቡበት ቦታ እንደሆነ በርካታ አማንያን ይናገራሉ። ዋልድባ ገዳም ታሪካዊ ቅርሶች፣ የግዕዝ ብራና፣ ታላላቅ መጻሕፍት፣ ጥናታዊና ታሪካዊ መዛግብት የሚገኙበት ስፍራ ነው።
የህዋሓት ሴራ በዋልድባ ገዳም ላይ
ከዚህ ቀጥየ የማቀርበው ፀረ ዋልድባ ገዳም የሆኑትን፣ ከላይ ስማቸው የተዘረዘረውን የህዋሓት ፖሊት ቢሮ መሪዎች በ1973 በአቅማራ፣ ተምቤን የወጠኑትን ፀረ ዋልድባ ሴራ ነው። በብዙ ታጋዮች የሚታወቅ፣ በይበልጥም ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች፣ የስለላ ታጋዮች፣ የክፍል መሪዎች ወዘተ በትክክል የሚያውቁት ሴራ ነው። በስብሃት ነጋ ተነግሮናል፣ ስለዚህ ድብቅ ምስጢር አይደለም። ለሕዝብና ለተራ ታጋይ ግን ድብቅ ምስጢር ነበር።
ከላይ የተጠቀሱት የህወሓት መሪዎች የዋልድባን ገዳም በተመለከተ ብዙ ከተነጋገሩበት በኋላ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በሚከተሉትን ምክንያቶች አድርገው ወሰኑ፤
- በሰሜን ኢትዮጵያ የክርስትና መስፍፋት ዋና መሰረቱ በዋልድባ ገዳም እየተማሩ የሚወጡት ናቸው። በተለይ በትግራይ የሚገኙት አብያተ ክርስትያናት መሪዎች በዚሁ ገዳም የተማሩ ናቸው። ቀሳውስት፣ ዲያቆናት በዚሁ ገዳም የተማሩ ናቸው። ይህ ገዳም እያለ የክርስትና ሃይማኖት ከትግራይ ውስጥ ለማስወገድ አይቻልም። ለወደፊቱ ከድል በኋል ለምናቋቁመው የትግራይ መንግሥት ትልቅ መሰናክል የሚሆኑት የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶች ናቸው። ስለሆነም ዋልድባ ገዳም የክርስትና ሃይማኖት መፈልፈያ ስለሆነ ከምንጩ ማድረቅ አለብን በማለት የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባላት፣ ማለትም፣ ስብሃት ነጋ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርአጽዮን፥ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን እና በወቅቱ ማ/ኮሚቴ የነበረው መለስ ዜናዊ በገዳሙ ላይ ውሳኔ አስተለለፉ። ውሳኔውም፤
- በገዳሙ ተንቀሳቃሽ ንብረትና የማይንቀሳቀስ ንበረት ላይ ጥናት ማካሄድ፤
- የገዳሙ ሃላፊዎችን ስም ዝርዝር ማጥናትና ማሳወቅ፣
- የዋልድባ ገዳም ግምጃ ቤት ውስጥ የሚገኙትን ቅርሳ ቅርስ፣ ጥንታዊ መጽሐፍትና መዛግብት በዝርዝር ማጥናት፣
- የገንዘቡን ክምችትና ቦታውን አጥንቶ ማሳወቅ።
ይህንን ሁሉ በረቀቀ ስለላ ማጥናትና መከታተል የፖሊት ቢሮው ሃላፊነት ይሆናል ተብሎ ተወሰነ።
ለዚህ ጥናት ወደ ዋልድባ ገዳም አስርገን የምንልከው ታጋይ ቢያንስ ቢያንስ የድቁና ማእረግ ያለው፣ የቤተክርስቲያን ትምህርት ያለውና ያጠናቀቀ ታጋይ መሆን አለበት በማለት የህወሓት አመራር በአቅማራው ስብሰባ ወሰኑ። በዚህ ስብሰባ ሃላፊነቱ የተሰጠው ለስብሃት ነጋና ለግደይ ዘርአጽዮን ነበር። ሁለቱ የፖሊት ቢሮ አባላት፣ የህወሓት ሊቀመንበር እና ም/ሊቀመንበር ናቸው። በውሳኔው መሰረት ወደ ሥራቸው ተሰማሩ። ይህን የሥራ ሃላፊነት የተረከቡት የቤተ ክህነት ብቁ እውቀት ያለው ሰው ማግኘት ካባድ ቢሆንባቸውም፣ በየዞኑ የሚገኙትን የሕዝብ ግንኙነት ታጋይ ሃላፊዎችን በማነጋግር በምስጢር ደብዳቤ በመላላክ ብዙ ጊዜ ፈጁ። በ1974 መጨረሻ አካባቢ በተምቤን አውራጃ ጣንቋ አበርገሌ ውስጥ የድቁና ማእረግ ያለው ብቁ ወጣት ዲያቆን ተገኘ። አበርገሌ ተወልዶ ያደገ፣ የቤተ ክህነት ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቀዳሽ ነው። ዘመናዊ ትምህርት የለውም። የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረውና አራት ጓዶቹን አሰባስቦ ድርጅታችን ህወሓት እናንተን ለትግል ይፈልጋችኋል ተብለው ተገደው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ (02) ተላኩ። ይህ የቤተ ክህነት ድቁና ያለው ወጣት ልዩ ዳብዳቤ ለአስገደ ግብረስላሴ ተላከለት። በደብዳቤው የተካተተው ለልዩ ሥራ ስለሚፈለግ ጥሩ እንክብካቤ እንዲደረግለት የሚል ነበር።
በርሄ መብራህቱ
የ02 አስልጣኞችም በተላከው ደብዳቤ መሰረት ተንከባክበው ያዙት። የአንድ ወር ወታደራዊ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ይህ ታጋይ በርሄ መብራህቱ ይባላል። በርሄ መብራህቱ ከማሰልጠኛው ጣቢያ አስወጥተው ሰው በማያገኘው አንድ ገበሬ ቤት ደበቁት። በዚሁ ድብቅ ቦታ የሚገናኘው ከኪሮስ ሃይለ (ወዲ ሃይለ) ጋር ብቻ ነበር። ኪሮስ ሃይለ የወታደራዊ ማሰልጠኛ አስተዳዳሪ ሃላፊ ነው። አስፈላጊ እንክብካቤም አደረገለት። ከአስር ቀናት በኋላም ካንድ ትልቅ አመራር ጋር እንደሚገናኝ ነገረው። ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኝ አስጠነቀቀው። እንዲሁ እያለ ከ13 ቀናት በኋላ ስብሃት ነጋ መጥቶ እዛው ድብቅ ቤት ተገናኙ። ስብሃት ነጋና በርሄ መብራህቱ ለ9 ቀናት አብረውት በመቆየት ስብሃት ታጋይ ዲያቆን በርሄ መብራህቱ ወደ ዋልድባ ገዳም ለስለላ እንደሚላክና እገዳሙ ወስጥ ገብቶ የስለላ ጥናቱን እንደሚያካሂድ፣ ምን ምን መስራት እንዳለበት አሰለጠነው። የሚፈጸሙትን ተግባራትም በዝርዝር አስጠናው። ከሚፈጽማቸው ተግባራት መካከል፣ በዋልድባ ገዳም ያሉትን ጥናታዊ ቅርሶች፣ የብራና መጻህፍት፣ መዛግብት፣ የገዳሙን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ዋና ግምጃ ቤቱ ወስጥ ያለውን ወርቅ ወዘተ የሚቀመጥበትን፣ የዋልድባ ገዳም ሃላፊዎችን ስም ዝርዝር፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ሌሎች አስፈላጊ ናቸው የምትላቸውን ስም ማሳወቅ ወዘተ ተብሎ ተነገረው። ይህንን ጥናት ወደኛ ለማስተላለፍ ጥሞናና ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ማወቅ አለብህ። መኖሪያህ ገዳሙ ውስጥ ነው። ቀናት የፈጀ ገለጻውን ትምህርቱን ሲጨርስ ከሳምንታት በኋላ እንገናኛለን ተባለ። ግደይ ዘርአጽዮን መጥቶ ያነጋግርሃል በማለት ለጊዜው ተሰናበተው። ግደይ ዘርአጽዮን ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመሄድ ኪሮስ ሃይለን በማግኘት ኪሮስ ሃይለም ታጋይ በርሄ መብራህቱን ወደተደበቀበት ቦት ይዞ በመሄድ አገናኘው። ግደይም ለቀናት ታጋይ በርሄ መብራህቱን ስለ ስለላ ሥራው አሰለጠነው። መገናኛው የምስጢር ቃል ኮድ መሆኑን አስረግጦ አስተማረው። ከማን እንደሚገናኝ፣ የምስጢር ኮዱ ስብሃት ተመልሶ ስለሚገናኝህ ይነግርሃል በማለት ተሰናበተው።
ስብሃት ነጋ ከሳምንት በኋላ ተመልሶ መጣ። ሲመጣም በቀረጢት የተቋጠሩ እቃዎችን ይዞ መጣ። ከረጢቱን ፈትቶ ለታጋይ በርሄ መብራህቱ አሳየው፤ መስቀል፣ የቄስ ጥምጥምና ቆብ፣ የቄስ ዘንግ፣ መቁጠሪያ፣ ጭራ፣ ሙሉ የቄስ ልብስ፣ ጋቢ ወዘተ ለአንድ ቄስ የሚያስፈልገውን ሁሉ በተሟላ ሁኔታ ሰጠው። ታጋይ በርሄ መብራህቱም የመጣለትን ተረከበ። ከአሁን በኋላ ስምህ አባ ገብረሥላሴ ነው። ዋልድባ ገዳም ስትገባ አባ ገ/ሥላሴ መሆንህን አስተዋውቅ። በርሄ መብራህቱን እርሳው ተባለ፣ በጉዳዩም ላይ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው። ከኔም ሆነ ከግደይ ዘርአጽዮን ጋር የምትገናኝበት የምስጢር ኮድ ይህ ነው ብሎ ሰጠው። የሚላኩልህን መልእክቶች ተቀበል፣ የተሳሳተ ኮድ ከሆነ አትቀበል፣ የሚመጣውን ሰው ሁሉ አታነጋግር ተባለ። ከአንተ ጋር የሚገናኘው ብስራት አማረ ብቻ ነው። ሲመጣ አስተዋውቅሃለሁ። በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ትገናኛላችሁ። የተገኘውን ምስጢር ሁሉ ጽፈህና አሽገህ ትልክልናለህ። ከኔም ሆነ ከግደይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በምስጢር በአካል በድብቅ ቦታ እንገናኛለን ተብሎ መመሪያ ተሰጠው።
አሁን የለበስከውን ልብስ ለብሰህ እስከ ተከዜ ትሄዳለህ። ተከዜን ከተሻገርክ በኋላ የለበስከውን ልብስ አውልቀህ ሙሉ የቄስ ልብስህን ትለብሳለህ። የዱሮው ልብስህን ተመልሰህ እኛን ለመገናኘት ስትመጣ የቄስ ልብስህን ደብቀህ የዱሮ ልብስህን ለብሰህ እንገናኛለን። ሰው በማያገኘው ጥሩ ቦታ ደብቀው ተባብለው በዚሁ ተለያዩ። አባ ገ/ሥላሴም ዋልድባ ገዳም ገቡ።
ታጋይ በርሄ መብራህቱ (አባ ገ/ሥላሴ) ገዳም ገብተው ሰፈሩ። ከ1975 እስከ ሐምሌ 1983 ለ8 ዓመታት ዋልድባ ገዳም የኖረው ታጋይ በርሄ መብራህቱ ሰላዩ በዋልድባ ገዳም የሚታወቀው አባ ገ/ሥላሴ ሲሆን የተሰጣቸውን የስለላ ተግባር በተሳካ ሁኔታ ቀጠሉበት። በዋልድባ ገዳም አባ ገ/ሥላሴን የሚያውቋቸው የገዳሙ አባላት በርካታ ናቸው። ቢሆንም፣ ገዳሙን ለማጥቃት በህወሓት የተላኩ ሰላይ መሆናቸውን ግን አያውቁም። ስምንት ዓመት በገዳሙ ሲኖር ማንነቱ እንዳይታወቅ በጥንቃቄ የኖረ ሰላይና መልእክተኛ ነው። ታጋይ በርሄ መብራህቱ (አባ ገ/ሥላሴ) በዋልድባ ገዳም ባካሄደው የስለላ ጥናቱ ለስብሃት ነጋና ለግደይ ዘርአጽዮን በማስተላለፍ ዋልድባ ገዳምን ለካባድ ጥፋትና ውድመት የዳረገ ሰው ነው። ግደይ ዘርአጽዮን በማለሊት ምስረታ ጉባኤ በሃሐምሌ 1977 ቢባረርም፣ ሰላዩን በተገቢው መንገድ አሰጥኖታል። አባ ገ/ሥላሴ (ታጋይ በርሄ መብራህቱ) በሚያስተላልፈው የስለላ መልእክቶች በብስራት አማረ እጅ በመላክ ለስብሃት ነጋና ለውውይት ለዘርአጽዮን ይደርሳል። ከዚሁ በመነሳት የሚፈለገውን ጥቃት ሁሉ በስምንት ዓመታት ቆይታው ገዳሙ ከሚጠቀምባቸው የምንጭ ውሃ እስከ እርሻ መሬት፣ በብዛት የጋማ ከብትና ማንኛውንም ሃብት በዝርዝር አሳልፈው የሰጡና ያስተላለፉ ሰላይ ዛሬ ገዳሙ እየደረሰበት ያለው መፍትሄ የሌለው ውድቀትና ችግር የአባ ገ/ሥላሴ (ታጋይ በርሄ መብራህቱ) የስለላ ውጤቶች ናቸው። በወቅቱም ቢሆን በብስራት አማረ የሚመራው አፋኝና ሽብርተኛ ገዳይ ቡድን አድፍጠው በመጠባበቅ ብዙ ብፁአን አባቶችን፣ ቀሳውስቶችን፣ በርካታ ዲያቆናትን ደብዛቸውን አጥፍቷል። ሙታኖችን ገዳሙ ይቁጠራቸው። ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያዎቹ ስብሃት ነጋና ግደይ ዘርአጽዮን ናቸው።
ዛሬ በዋልድባ ገዳም ላይ እየደረሰያለው ጥፋትና ውድመት በስብሃት ነጋና በግደይ ዘርአጽዮን በታቀደ የስለላ መረብ ምክንያት ነው። በጠቅላላ ለጥንታዊውና ባለታሪኩ ገዳም መውደም ተጠያቂዎቹ የህወሓት ከፍተኛ መሪዎች ናቸው። ለጥፋት ውሳኔው ዋናዎቹ ተባባሪዎች፣ አረጋዊ በርሄ፣ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን እና በወቅቱ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረው መለስ ዜናዊ ናቸው። በዋልድባ ገዳም ዛሬ እየደረሰ ላለውውድመት የገዢው ስርዓት ህወሓት ሙሉ ለሙሉ በሃላፊነት ተጠያቂ ናቸው። ወንጀሎቻቸውም፤
- ታላቅና ባለ ታሪክ የሆነውን የዋልድባን ገዳም አውድመዋል፣
- ብዙ ብፁአን አባቶችን፣ ባህታዊያንን፣ ቀሳውስትን ገድለዋል፣ አጥፍተዋል፣
- የዋልድባን ገድም ጠቅላላ ሃብታና ንበረት ዘርፈዋል አስዘርፈዋል፣
- ጥንትዊ የብራና መጽሐፍት፣ የታሪክ መዛግብትን ወዘተ ዘርፈዋል፣ አስዘርፈዋል፣
- የገዳሙን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሃብትና ንብረት፣ የጋም ከብቶች፣ የእርሻ ቁሳቁሶችን ወዘተ በህወሓት ባለሥልጥናት በጉልበት ወስደዋል።
በሥልጣን ላይ ያለው ፋሽስትና ሽብርተኛ ህወሓት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቱ ሥር ከጠላት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዋልድባ ገዳም እየደረሰ ያለው ፋታ የሌለው ጥቃት ስብሃት ነጋና ግደይ ዘርአጽዮን በሸረቡት ተንኮል የዋልድባ ገድማ ጥፋት እንደቀጠለ ነው። ዛሬ የዋልድባ ገዳም በውድመት አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል። ክብሩና እና ህልውናው ተገፎ የባንዳዎችና የህወሓት አመራር የግል ንብረታቸው አድርገውታል።
የዚህ ቅዱስ ቦታ ጥቃትና ውድመት፣ ሃብትና ንብረት መዘረፍ፣ የብፁአን አባቶች ሕይወት መጥፋት ወዘተ ተጠያቂው ህወሓት ነው። የዚህ ፋሽስትና ዘራፊ መሪዎች ሁሉ ለቅዱስ ገዳሙ መጥፋት በሕግ ተጠያቂዎች ናቸው።
ድል ለኢትዮጵያ፣
ገብረመድህን አርአያ፣ 18 ኤፕሪል 2017
Leave a Reply