ዕለቱ ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 ቀን 1996ዓም ነበር – ልክ የዛሬ 15 ዓመት። የአኙዋክ ወንዶች እንዲገደሉ ዕቅዱ የወጣው አስቀድሞ ነበር። በቅርቡ ህይወቱ ያለፈውና በወቅቱ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበረው ኦሞት ኡባንግ ኡሎም ቢሮ በ1996 ዓም የተገኘ በአማርኛ የተጻፈ ባለ 16 ገጽ ማስታወሻ እንደሚያመለክተው “መስከረም 13፤ 1996ዓም የዚያን ጊዜ ጠ/ሚ/ር በነበረው መለስ ዜናዊ ቢሮ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ መለስ ራሱ፣ ምክትል ጠ/ሚ/ር አዲሱ ለገሠ፣ የህወሓት ከፍተኛ ሹም ስብሃት ነጋ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር በረከት ስምዖን፣ የጋምቤላ ደኅንነት ዋና ኃላፊ ኦሞት ኡባንግ ኡሎም፣ ፌዴራሉ ደኅንነት ጽ/ቤት የመጣና ስሙ ያልታወቀ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አባይ ፀሃዬ፣ ኤታማዦር ሹም ሳሞራ ዩኑስ፣ መከላከያ ሚኒስትር አባዱላ ገመዳ፣ የወታደራዊ ስለላ ሹም ብርጋዴር ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ተገኝተው ነበር።
“በዚህ መለስ ዜናዊ በመራው ስብሰባ ላይ የነበረው ዋና አጀንዳ የጋምቤላን የፀጥታ ሁኔታ መወያየት ነበር። ሆኖም በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር ታኅሣሥ 3 ቀን 1996ዓም መጨፍጨፍ ስላለባቸው አኙዋኮች ዕቅድ የወጣውና አፈጻጸሙም የተወሰነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከስብሰባው በኋላ በኅዳር ወር አጋማሽ አካባቢ የሚገደሉት ሰዎች ዝርዝር በኦሞት ኡባንግ ኡሎም ተዘጋጀ። ይህ የመጀመሪያው ዝርዝር አምስት መቶ አሥራሁለት ስም ሊስት የያዘ ነበር። በታኅሣሥ ወር ሊስቱ ላይ የሠፈሩት ስሞች ከዚህም ይበልጥ እንደነበር ግምት አለ። ምክንያቱም በጋምቤላና በአዲስ አበባ በእስር ላይ የነበሩ አኙዋኮችም በኋላ ተካትተው ነበር።
“የዕቅዱ አፈጻጸም ላይ አኙዋኮች እንዲጨፈጨፉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሰጠው ጸጋይ በየነ (በጋምቤላ የሠራዊቱ ኃላፊ) ሲሆን ፈቃዱን ያገኘው የፌዴራል ጉዳዮች ከፍተኛ ኃላፊ ከነበረው ገብረአብ በርናባስ ነበር። የፖሊስ ኃላፊው ታደሰ ኃይለሥላሴም የማስገደል ትዕዛዝ በመስጠቱ ውስጥ ነበረበት። ሌሎች የፖሊስ ሠራዊት አባላትም በግድያው ላይ ተሳትፈዋል፤የስም ዝርዝራቸውና ሌሎች የወንጀል ጉዳዮች በማስረጃ የተረጋገጠ ነው።
በዚያ በደም በተጠመቀው ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 ቀን 1996ዓም እና ከዚያም ቀጥሎ ባሉት ቀናት 424 የአኙዋኮች ሲጨፈጨፉ ኢትዮጵያን በግፍ ሲገዛ የነበረው ህወሓት/ኢህአዴግ የሰጠው መልስ የጎሣ ግጭት ነው የሚል ነበር። በዚያኑ ዕለት ከጋምቤላ ሃያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ያልታወቁ ኃይሎች ስምንት የስደተኛ ካምፕ ሠራተኞችን ይዞ በሚጓዝ መኪና ላይ ጥቃት ይሰነዝሩና ይገድሏቸዋል። ቀጥሎም ገዢው ኃይል ያሠማራቸው የሠራዊቱ አባላት እጅግ የተበላሸውን የስምንቱን ሰዎች አስከሬን በጋምቤላ ከተማ አደባባይ አምጥተው በማስቀመጥ ለትዕይንት ያውሉታል። ይህንንም በማድረግ ጥቃቱን ፈጻሚዎቹ አኙዋኮች ናቸው በማስባል የመሃል አገር ሰዎች (ሚሊሻዎች) በአኙዋኮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ያነሳሷቸዋል። በቁጣ የተነሱት ሚሊሻዎች ህወሓት/ኢህአዴግ ባሰማራቸው የሠራዊቱ አባላት እየታገዙ አኙዋኮችን መጨፍጨፉን ተያያዙት። አስቀድሞ የተነደፈው ዕቅድ በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ በሦስት ቀናት ብቻ 424 አኙዋኮች አብዛኛዎቹ የተማሩ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የማኅበረሰቡ መሪዎች፣ ከወጣት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ወንዶች በሙሉ ተጨፈጨፉ።
በቀጣይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የቻይና ኩባንያ በአኙዋክ ምድር የተገኘውን ነዳጅ ለማጥናት በመፈለጉና አኙዋኮች ደግሞ ከመሬታቸው ላይ አንፈናቀልም በማለታቸው ጭፍጨፋው ለመካሄዱ አንደኛ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል። በቀጣይም ህወሓት/ኢህአዴግ ደርግን በእጅጉ ሲነቅፍበት የነበረውና የደርግን አሠራር ለዓለም በክፉ እንዲነሳ ያደረገበትን የመልሶ ማቋቋምና የመንደር ምሥረታ እሱም መልሶ በአኙዋኮች ላይ ፈጸመ። የመሠረት ልማት በክልሉ ለማፋጠንና ተሰበጣጥሮ የሚኖረውን ሕዝብ በአንድ ለመርዳት በሚል ሽፋን አኙዋኮችን ዕትብታቸው ከተቀበረበት ምድር በማፈናቀል በመንደር ምሥረታ ስም በአንድ በመሰብሰብ መሬቱን ለልማት በሚል ለሳውዲ ስታር፣ ለካሩቱሪ እና በአብዛኛው ለትግራይ ተወላጆች በሔክታር አንድ ዶላር ሒሳብ ቸበቸበው። በግፍ እየተነጠቀ የሚሰጠው መሬት አግባብነት የለውም፤ ችግር እየፈጠረ ነው ተብሎ መለስ ዜናዊ ሲጠየቅ የመለሰው “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልሸጥነው መሬት ነው” በማለት ነበር የመለሰው።
መለስ ዜናዊ ለፍርድ ሳይቀርብ አልፏል። የእርሱ ቀኝ እጅ በመሆን የራሱን ወገኖች ያስጨፈጨፈው ኦሞት ኡባንግ ኡሎም በቅርቡ በስደት በሚኖርበት በፊሊፒንስ በውርደት አልፏል። ከጭፍጨፋው በኋላ ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓም ጀምሮ ሟቹ መለስ ዜናዊ በላካቸው አስገምጋሚዎች ለሳምንት በጋምቤላ በተካሄደ አውጫጪኝ ኦሞት ኦባንግ ኡሎም “የአኙዋክ ተወላጆችን አስጨፍጭፈሃል” የሚል መነሻውና ዓላማው ግልጽ ያልሆነ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። በወቅቱ ግምገማው ላይ የነበሩ እንዳሉት ለዚህ ጥያቄ ኦሞት ሲመልስ “እኔ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ከሆንኩ መሳሪያና ወታደር የሰጠኝ መለስም ይታሰራል” በማለት መልስ መስጠቱን ይመሰክራሉ። አሁን ግን ሁለቱም አልፈዋል፤ ሆኖም እስካሁን ወንጀላቸውን አምነው ያልተቀበሉ የወቅቱ ሹመኞች አሉ፤ በኃላፊነት የሚጠይቃቸው የመንግሥት አካል አልተሰማም፤ በመንግሥት ደረጃ በአኙዋክ ላይ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ ምርመራ እንዲካሄድ የቀረበ ዕቅድ የለም፤ እስካሁንም አንድም የክስ ፋይል በማንም ላይ አልተከፈተም።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የዛሬ አስራ አምስት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ሲያስታውስ የትኛውም ወገን በበቀልና በምሬት በመነሳሳት የከፋ ጥቃት የመፈጸም ክፉ ስሜት ውስጥ በመግባት ቀድሞ ከወደመው የበለጠ ጥፋት እንዳይፈጸም አበክሮ ይመክራል፤ ያስጠነቅቃል። በቀል በቀልን ይወልዳል፤ ጥላቻም ጥላቻን። በዚህ አዙሪት ውስጥ እርስበርስ ደም ከመደፋሰስና ግፍን ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ በስተቀር ማንም ምንም አያተርፍም። ለልጆቻችንም የምናወርሳቸው ይህንን ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱ ግፍ ደግሞ እንዳይፈጸም ለዕርቅ፣ ለሰላም እና አብሮነት እንዲተጉና ከዚህ ስህተት እንዲማሩ ነው። ይህንን ስንል ግን ለርትዓዊ ፍትሕ (restorative justice) እንዲሰፍን እውነት በይፋና በግልጽ መነገር አለበት ብለን እናምናለን።
ለዚህም ነው በመስከረም ወር 2011ዓም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የልዑካን ቡድን ወደ ጋምቤላ በመሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚህ በግፍ ለተጨፈጨፉት 424 አኙዋኮች የመታሰቢያ ፕሮግራም በጋምቤላ ከተማ ያካሄደው። ይህ ከ15 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ የሙታን መታሰቢያ ሥነሥርዓት ይህ ግፍ እንዳይወሳ የሚፈልጉ በርካታ ቡድኖችን ያስቆጣና ፕሮግራሙም እንዳይካሄድ ዕንቅፋት እስከመፍጠር እንዲደርሱ ያደረገ ነበር። እነዚህ ቡድኖች የአኙዋክ ሕዝብ በግፍ ያጣውን ወገኖቹን በሥርዓት አልቅሶ እንዳይቀብር ከማድረጋቸው አልፈው አንድ ጊዜ እንኳን መታሰቢያ እንዳይደረግላቸው ሲከለክሉ የኖሩ ናቸው።
የልዑካን ቡድናችን ጋምቤላ በደረሰበት የመጀመሪያ ቀን ያደረገው ቀዳሚ ያደረገው ተግባር ከዳልዲም ጋር በመተባበር የከተማውን ሕዝብ በመሰብሰብ ለግፍ ሰለባዎቹ የመታሰቢያ ሥነሥርዓት ማድረግ ነበር። ሰኞ መስከረም 7፤ 2011ዓም ከሰዓት በኋላ በጋምቤላ ከተማ በሚገኘው አዳራሽ በተከናወነው ሥርዓት ላይ ቁጥሩ እስከ አምስት ሺህ የሚሆን ሕዝብ እንደተገኘ ግምት አለ።
በዚህ እጅግ የተከበረ ሥነሥርዓት ላይ የታኅሣሥ 3 ጭፍጨፋን የሚወሳ አጭር ቪዲዮ ቀርቧል። በመቀጠልም በግፍ የተገደሉት 424 አኙዋኮች ስም በአራት የአኙዋክ ወጣቶች እንዲነበብ ተደርጓል። እነዚህ ስም፣ ዘመድ፣ ወገን ያላቸው ሰለባዎች እንዲሁ በቁጥር ብቻ ተጠርተው የሚታወሱ ሳይሆኑ በስም የሚታወቁና በማንነታቸው ሁልጊዜ የሚወሱ ሊሆኑ ይገባቸዋል በሚል ነበር የእያንዳንዱ ስም በአዳራሹ ለተሰበሰበው ህዝብ የተነበበው። ይህ ሁሉ እንዳይሆን ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ ተከናውኗል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላማዊው የአኙዋክ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ወገኖቹ እንዴት እንደተጨፈጨፉ ሲመለከትና የወገኖቹን ስም ሲነበብ ሲሰማ በበቀል መንፈስ እንነሳና እርምጃ እንውሰድ ሳይሆን ያለው በአዳራሹ ውስጥ በእንባ እየታጠበ ሥነሥርዓቱን እየዘመረ ነበር ያጠናቀቀው።
ከዚህ ሥነሥርዓት በኋላ የጋራ ንቅናቄችን ዋና ዳይሬክተርና ራሳቸውም በዚህ ጭፍጨፋ በርካታ ዘመዶቻቸውን ያጡት አቶ ኦባንግ ሜቶ ለአኙዋክ ሕዝብ ባደረጉት ጥሪ ዘመኑ የብቀላና የደም መፋሰስ ሳይሆን የዕርቅና ይቅር የመባባል ነው ነበር ያሉት። ስለዚህ አኙዋክም ሆነ ኑዌር ወይም የመሃል አገር ሰው በሙሉ ይህንን ግፍ ሲቃወም ዋና ዓላማ ማድረግ ያለበት ከእንግዲህ እንዳይደገም ጠንክሮ መሥራት ሲሆን ለፍርድ መቅረብ በሚገባቸው ላይም የራሱን ፍርድ ሳይሆን የሕግ የበላይነትን መከተል ነው ያለበት በማለት የሰላም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይም በተደረጉ ስብሰባዎች የጋራ ንቅናቄያችን ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተገናኘ ሲሆን በዋንኛነት ያስተላለፈው መልዕክትም በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በሁሉም የአገራችን ቦታ የወገናችን ደም የፈሰሰ በመሆኑ ይህ የሚያቆምበት ሥራ መሠራት ያለበት ጊዜው አሁን መሆኑን ነው። ስለዚህም በመላው የአገራችን ክፍል ሰላም ወርዶ ሕዝባችን ያለአንዳች መጠላላትና ብቀላ በሰላም ለመኖር እንዲችል ያለፈውን የግፍ ዘመን በይቅርታና በዕርቅ ልንደመድመው ይገባል የሚል የፀና እምነት የጋራ ንቅናቄችን አለው።
የደምና የግፍ ዘመናችንን የምናስታውሰው በደል ፈጻሚዎቻችን ላይ ደግመን በደል በመፈጸምና በመበቀል ሳይሆን ያለፈውን ጠባሳ በማስታወስ እንደገና በቀሪው ሕዝባችንና በመጪው ትውልድ ላይ እንዳይፈጸም የመከላከያ ጋሻ ለማበጀት ነው። አዲስና የግፍ ውጤት የገባው ትውልድ ለመፍጠር ነው። ተበቃይ ሳይሆን ይቅር ባይና አዛኝ ትውልድ ለማምጣት ነው። ግፍን በግፍ ለመመለስ ቀላል ነው። ገዳይን መግደል ከሁሉ የሚቀል ተግባር ነው። እጅግ የሚከብደውና ጀግንነት የሚጠይቀው ግን ይቅር ባይነትና ዕርቅ ነው።
ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቱን ትውልድ ለመፍጠርና አዲሲቷን ኢትዮጵያ በፍቅር ለመገንባት የአኙዋክ ምድር የዕርቅ ማስጀመሪያ ቦታ ሊሆን ይገባል እንላለን። ይህንን ስንል ግን ሌላው የአገራችን ክፍል ለዚህ ብቃት የለውም እያልን እንዳልሆነ ሊታወቅልን ይገባል። ይልቁንም የአኙዋክ ምድር ለዘመናት ስንናፍቅ የኖርነውን ሰላምና ዕርቅ እንዲሁም ይቅርባይነት ለመተግበር የተመቻቸ ቦታ ሆኖ ስላገኘነው ነው። በኢትዮጵያ ካሉት በቁጥር እጅግ ዝቅተኛ የሆነው የአኙዋክ ሕዝብ ይህ ሁሉ ግፍ ደርሶበት፣ በበርካታ ሺህ የሚቆጠረው ተሰድዶና አገር አልባ ሆኖ አሁንም ኢትዮጵያዊነቱ በተመለከተ የሚደራደር ሕዝብ አለመሆኑና ለዕርቅና አብሮነት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ የሚያሳይ በመሆኑ ነው።
የጋራ ንቅናቄችን አሁን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከግቡ እንዲደርስ በጽኑ ይፈልጋል፤ አጥብቆም ከለውጥ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ይተጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይቅር ባይነትና ዕርቅ በተለይም ርትዓዊ ፍትሕ (restorative justice) በአገራችን እንዲሰፍን የሚቻለውን ሲያደርግ እንደቆየ ሁሉ አሁንም በዚህ መስመር ይገፋበታል። ይህ የተቀደሰ ሃሳብ የሚጀመርበት አንድ የማስጀመሪያ ታሪካዊ ቦታ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ስለዚህ የአኙዋክ ምድር በኢትዮጵያ የዕርቅ ማስጀመሪያ ቦታ ሊሆን ይገባል ይላል!
ፈጣሪ የአገራችንን ሰላም ያጽናልን፤ ሕዝቧንም ይባርክ።
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአሜሪካ አገር በሕግ የተመዘገበ ድርጅት ሲሆን በትርፍ አልባ የሲቪክ ድርጅትነት በ501(c)(3) ምደባ ሥር የተካተተ ነው። ለተጨማሪ መረጃ የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በስልክ ቁጥር፤ 0940-802589/202-725-1616 ወይም በኢሜል፤ obang@solidaritymovement.org ማግኘት ይቻላል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Sergute Selassie says
ትክክል!
Dagmawi Kana says
Please, find people who can tell the atrocities perpetrated by these same jackals on the Tigrian people since 1967Ethc. Then we will know well what TPLF is. It is time to arouse the Anger of the Tigrian people too.
Fictor king says
አሉባልታ ስለሚበዛው መረጃም እውነትም ነው ማለት ያስቸግራል። ደራሲው ግን የመፃፍ ችሎታው በአንፃራዊነት ጥሩ ነው። መረጃ የለውም እንጂ ቢኖረው ጋዜጠኛ ቢሆን ያዋጣው ነበር
ፍርድ says
ለፍርድ አይቀርቡም እንዴ አዛዦች?
sinknesh mekonnen says
እግዚኦ የማይሰማ ነገር የለም፡፡ ወይ ሀገሬ ምን ዓይነት ትውልድ ነው ትውልድን የሚበላው? ሰላም ለአኙዋክ ህዝብ እንመኛለን፡፡
Bek says
The so called “Fictor king” you can see the pictures posted with the articles. What do you think of that ?????????????