የአሜሪካ ምርጫ ሲጠናቀቅ ተሸናፊው ሚት ሮምኒ ደጋፊዎቻቸው በተሰበሰቡበት አዳራሽ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡- “… ሁለታችንም ለምንወዳት አገራችን የምንመኘውን ለማድረግ በተለያየ አቅጣጫ ሞከርን፤ … ሕዝባችን ደግሞ የሚፈልገውን መሪ መረጠ፤ … ስለዚህ ፕሬዚዳንቱን ደውዬ አነጋሬያቸዋለሁ፤ ባገኙትም ድል እንኳን ደስ አለዎ ብያቸዋለሁ፤ … በተለይ ለእርሳቸው፣ ለቀዳማዊ እመቤት እና ለልጆቻቸው ሁሉ መልካሙን እመኛለሁ፤ … አገራችን ከባድ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፤ … ባለቤቴና እኔ ለፕሬዚዳንቱና ቤተሰባቸው ከልብ እንጸልያለን፤ በሥራቸው ስኬት እንዲያገኙና ታላቋን አገራችንን በመምራት የሚያከናውኑት ሁሉ የተሳካ እንዲሁን እመኛለሁ፡፡” ይህንን ካሉ በኋላ ወደተለመደው ህይወታቸው ሄዱ – የፖለቲካ ገዳም ገቡ፡፡ ይህ ንግግር ወደራሳችን እንድንመለከት የሚያደርግ ነው፡፡ የእኛስ ፖለቲከኞች ዕድሜ ልካቸውን የፖለቲካ አክሮባት እየሰሩ አንደ ፓርቲ ሲያቋቁሙ፤ ሌላ ሲያፈርሱ፤ አንዱን ሲጠልፉ ሌላውን በሾኬ ሲሉ … ከመቆየት ይልቅ የሚሞክሩትን ሞክረው አልሆን ሲል በክብር ለተከታዩ ቦታ ለቅቀው ወደ ፖለቲካ ገዳማቸው የሚገቡት መቼ ይሆን?
የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በድጋሚ መመረጥ ብዙ የተጠበቀ ቢሆንም የአሜሪካ ሚዲያ እንደተለመደው በሕዝቡ ውስጥ በፈጠረው የ“አፍጥጣችሁ እዩኝ” ፍላጎት ምክንያት አንድን ምሽት በስሜት ውጥረት እንዲያልፍ አድርጓል፡፡ “ተስፋ” እና “ለውጥ” የተሰኙ ልብን የሚያማልሉ ቃላትን በመላው ሕዝብ ዘንድ በማስረጽ የዛሬ አራት ዓመት እጅግ ከፍተኛ በሆነ የሕዝብ ድጋፍ የተመረጡት ባራክ ሁሴን ኦባማ እንደገና ለተጨማሪ አራት ዓመታት ተመርጠዋል፡፡ አራት ዓመት መለስ ብለን ስንቃኘው የታሰበው “የለውጥ ተስፋ” ተግባራዊ ሆነ ወይስ ተጨማሪ አራት ዓመታትን “አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ” በእንግሊዝኛ የሚያስዘፍን ነው?
በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኦባማ መመረጥ ከቀለምም ሆነ ከዘር አኳያ የሚሰጠው ቀቢጸ ደስታ እንዳለ ሆኖ ፕሬዚዳንቱ የሚከተሉት የአገር ውስጥ ፖሊሲ በቀጥታ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ግን የኦባማ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽዕኖ ማድረጉ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ታሪካዊው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲፈጸም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ምርጫውን ያልደገፈ፣ ያላለቀሰ፣ ያላጨበጨበ፣ ያልዘፈነ፣ … ይኖራል ለማለት እጅግ ያዳግታል፡፡ የልዕለኃያል ሰብዕና የተሰጣቸው ኦባማ በአምባገነን መሪዎች ተጠፍረው የሚገኙ የኢትዮጵያንና መሰል አገራት ችግር በቀጥታ ትዕዛዝ ያስወግዳሉ ብሎ ከማሰብ ባለፈ እንዲያውም የአሜሪካ ፖሊሶች አቶ መለስን ለፍርድ ሲያስጎትቱ የሚያሳይ የተሻሻለ ፎቶ እስከመሰራትና በድረገጾች እስከመበተን የደረሰበት ጊዜም ነበር፡፡ አገርቤትማ በኦባማ ስም ያልተከፈተ ሻይ ቤት፣ ዳቦ ቤት፣ ጆተኒ ቤት… የለም፡፡
ዓመታት እያለፉ ሲሄድ የብዙዎች ተስፋ መጨለም ሲጀምር የሚሰጡትም ማስተባበያዎች በዚያው መልኩ እየጨመረ ሄደ፡፡ “በመጀመሪያው ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ ችግር የገጠመውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማሻሻል ኃላፊነት ስላለባቸው በውጪ ጉዳይ ላይ እምብዛም ላይጠመዱ ይችላሉ” የሚሉ ራስን የማታለያ መላምቶች ተሰጡ፡፡ ኦባማ ግን በአምባገነኖች ላይ ከንግግር ያለፈ በተግባር የታገዘ የፖሊሲ አቋም ሳይዙ ቀጠሉ፡፡ አቶ መለስም በየዓመቱ በሚደረገው የቡድን 7፣ 8፣ 20፣ 22፣ … ብቻ የተገኘው የቡድን ስብሰባ (የቡድን አባቶችን ሳይጨምር) ላይ ከኦባማ ጋር ሲጨባበጡ፣ ሲሳሳቁ፣ … መታየታቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን “ዱሮውንም … ” የሚያስብል መራራ ክስተት እየሆነ መጣ፡፡ የዚያኑ ያክልም “የራሳችንን ችግር ራሳችን ነን እንጂ መወጣት ያለብን ኦባማ ነጻ ሊያወጣን አይችልም” የሚል የመከላከያ አስተያየት እንደተለመደው ቀጠለ – “አልተሸወድንም” ለማለት ነው፡፡ ገንዘቡና ዕርዳታው ግን አላቆመም፡፡
ቀጠለና የንግግር ተሰጥዖ የፈሰሰባቸው ፕሬዚዳንቱ ጋና ላይ ታሪካዊዉን ንግግር ባደረጉ ጊዜ “መለስ ጉድህ” ተባለ! “ሕግ የበላይ ባልሆነበት ጭከናና ጉቦ (ሙስና) በሰለጠኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር የሚፈልግ አንዳችም ሰው የለም፡፡ ይህ ዴሞክራሲ አይደለም፤ ይልቁንም ይህ የጭቆና አገዛዝ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አገዛዝ ያከትም ዘንድ ጊዜው አሁን ነው” አሉ ኦባማ፡፡ አፍሪካም በደስታ ሰከረች፡፡ በዚህ ደስታ እንደተለመደው “የለውጥ ተስፋ” ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ኦባማ “ምነው አልበዛም እንዴ” የሚያሰኝ ንግግር በዓለም ፊት አደረጉ፡፡ በኒውዮርክ ከተማ የምዕተዓመቱ የልማት ዕቅድ (ትልም) ሴፕቴምበር 22፤ 2010ዓም በተካሄደ ስብሰባ ላይ ኦባማ ከመለስና “አብዮታዊ ዴሞክራሲያውያን” በላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አደነቁ፡፡ ማስረጃም አከሉበት፡፡ “ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ይቻል ዘንድ የለውጥ ማዕበልን (ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማለታቸው ነበር) ፈትተን መልቀቅ አለብን፡፡ ይህም ድህነትን በማስወገድና ዕድልን በመፍጠር ደረጃ ዓለማችን እስካሁን ካየችው ሁሉ ለየት ያለ ነው፡፡ ይህ ኃይል ደቡብ ኮሪያን ከዕርዳታ ተቀባይነት ወደ ዕርዳታ ለጋስነት ያሸጋገረ ነው፡፡ በብራዚልና ሕንድ የኑሮ ሁኔታን ያሻሻለ ነው፡፡ በአፍሪካ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ፣ ማላዊና ሞዛምቢክ ያሉ አገራትን የምዕተዓመቱን የልማት ትልም ተግባራዊ እንዳያደርጉ የተጋረጠባቸውን ሁሉ በመቋቋም እውነተኛ ዕድገት እንዲያስቆጥሩ ያደረጋቸው ነው” በማለት በኒውዮርክ ሰዓት ከሰዓትበኋላ 11 አካባቢ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የተራበ ሆዱን በእህል ሳይሞላ አሸልቦ ባለበት ኦባማ ቀለዱበት፡፡ በእንቅልፍ ተታልሎ ጉዱን ያልሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይነቃ እነ አቶ መለስ ከኦባማ ንግግር የሰሟትን ቃል አሻሽለው “ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” ብለው በህልሙ ቂቤ አጠጡት፡፡ ከመፍጠናቸው የተነሳ “ትራንስፎርሜሽን” ለሚለው የባዕድ ቃል የአማርኛ ትርጓሜ እስኪያገኙ መጠበቅ ያልቻሉ ይመስላል፡፡ የልማት አርበኛ፣ የልማት ሰራዊት፣ … የሚሉት የልማት ክተት አዋጆች የተጎሰሙትም በዚሁ ቅጽበት ነው።
ተስፋ ያልቆረጠው ለውጥ ናፋቂ አሁንም ከአሜሪካና ኦባማ ተዓምር ሲጠብቅ “አሁንስ በቃኝ” የሚያሰኝ “የተስፋ ለውጥ” ተሰጠው፡፡ ከአምስት ወራት በፊት በሺካጎ ከተማ ከቡድን ስምንት ስብሰባ በፊት በእርሻና ምግብ ሰብል ራስን መቻል ርዕስ በተደረገ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ አቶ መለስን በስም ጠርተው በአፍሪካ ለብዙዎች ህይወት ሰለባ የሆነውን ረሃብ በመታገል ደረጃ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ አፍሪካዊ መሪ በማለት ከሌሎች ሁለት አፍሪካዊ መሪዎች ጋር በማሞገስ አስጨበጨቡላቸው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም ኢትዮጵያ በግብርናና ምግብ ዋስትና ላይ በምታካሂደው በሳል ኢንቨስትመንት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በአሁኑ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ተረጂዎች ከመሆን ተላቅቀዋል በማለት አቶ መለስ በስብሰባው ላይ የተጠሩበትን ምክንያት በማስረጃ ጠቀሱ፡፡ በማስከተልም “ፕሬዚዳንቱ በእርግጥ ኢቴቪን በደንብ ይከታተላሉ” የሚያሰኝ ንግግር በማድረግ ስብሰባውን አጠቃለሉ፡፡ የመለስ መንግሥት በሚከተለው የግብርና ፖሊሲ የገበሬው ህይወት እየተቀየረ መሆኑን በመጥቀስ ሲናገሩ “በነዚህ ስትራቴጂዎች ምክንያት በኢትዮጵያ ያለ ገበሬ (ከመንግሥት) ብድር በማግኘቱ ምርቱን ለማሳደግና ተጨማሪ ሠራተኞችን ለመቅጠር ችሏል፤ በመሆኑም ይህ ገበሬ እንዲህ ይላል ‘በዚህ ደመወዝ ምክንያት ሕይወቴ ተቀይሯል፤ አሁን ልጆቼ ትምህርትቤት መሄድ ይችላሉ’” በማለት ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ልማታዊ ፕሬዚዳንት የሚያስብል ንግግር ኦባማ አደረጉ፡፡
የኦባማን እንደገና የመመረጥ ጉዳይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ይሰጡ የነበሩ በአሜሪካ የነጻ ሚዲያ ውጤቶች በሁለቱም ዕጩዎች መካከል ምንም ዓይነት ለውጥ እንደሌለ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ የዛሬ አራት ዓመት በአሜሪካም ሆነ አሜሪካ በዓለም ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉት ኦባማ በተለይ በውጭ ጉዳይ ረገድ ከቡሽ ያልተለየ ፖሊሲ መከተላቸው ተራማጅ የሆኑና የኦባማን የመጀመሪያ ምርጫ በጽኑ ይደግፉ የነበሩ ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አራቱ ዓመታት ከመጋመሳቸው በፊት ነበር ተስፋ የቆረጡት፡፡
በዘመነ ቡሽ እስረኞችን በማሰቃየት መረጃ የመቀበልን አካሄድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት አጥብቀው የተቃወሙት ኦባማ ሥልጣን በያዙ ማግስት በጦር ወንጀለኝነት የሚፈለጉ የቡሽ ባለሥልጣናት በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ እንዳይከሰሱ አስደረጉ፡፡ በተለይ በስፔን ተከፍቶ የነበረ የክስ ፋይል በአስተዳደራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንዲዘጋና ክሱ እንዲቆም አስደረጉ፡፡ በተመረጡ በአንድ ዓመት ውስጥ የጓንታናሞ ቤይ እስርቤትን እንዲዘጋ አደርጋለሁ ብለው በምርጫ ዘመቻ ወቅት ብቻ ሳይሆን ቤተመንግሥታቸው ከገቡ በኋላ ቃል የገቡት ኦባማ እስርቤቱን እስካሁን ሳያዘጉ አራት ዓመት ቆይተው እንደገና ለአራት ዓመት ወደ ቤተመንግሥታቸው ተመልሰዋል፡፡
የኖቤል የሰላም ሽልማት የተሰጣቸው ኦባማ የአሜሪካንን ወታደራዊ ቁጥጥር (ሚሊቴራይዜሽን) ገፍተውበታል፡፡ በአፍሪካ የአፍሪኮም መስፋፋትና በበርካታ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ ወይም እያስነሱ በአሜሪካ ወታደሮችና ልዩ ኃይል ቁጥጥር ሥር ማዋል የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በአሸባሪዎች ላይ በሚደረገው ጦርነት ሰበብ ሰው ዓልባ ጀቶችን በመላክ አካባቢዎችን በቦምብ ማጥቃት (drone attacks) የኦባማ አስተዳደር ዓይነተኛው መለያው ሆኗል፡፡ በቡሽ የ8ዓመታት ዘመን በፓኪስታን አካባቢ 52 ጊዜ የተደረገውና የ200 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይኸው ሰው ዓልባ ጀት የቦምብ ጥቃት በኦባማ ዘመን 300 ያህል ጊዜ የተደረገ ሲሆን የሦስት ሺህ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉት ህጻናት ናቸው፡፡
ተመሳሳይ ጥቃት የመሰንዘሪያ ቦታ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘጋጀ እንዳለ ያለፈው ዓመት በአሜሪካና አውሮጳ በሚገኙ ዋና ዋና ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ አቶ ኃይለማርያም በዲንነት ያስተዳደሩት በነበረው የአርባምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ (አሁን ዩኒቨርሲቲ) በሚገኘው የአየር ማረፊያ አጠገብ የአሜሪካ ወታደሮች ለበረራ የሚያስችላቸውን ቤዝ መስራታቸውንና እያስፋፉትም እንደሆነ የመከላከያ ባለሥልጣናትን እንዲሁም ለግል ጉዳይ የሚመላለሱ ተጓዦችን ጠቅሶ ዋሺንግተን ፖስት ቢዘግብም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደተለመደው “የውጪ ወታደራዊ ቤዞችን አናስተናግድም” በማለት ክደዋል፡፡ እንደ ወታደራዊ ፖሊሲ ተንታኞች አስተያየት ይህ አካሄድ በመጪዎቹ አራት የኦባማ ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በምርጫ ወቅት ሚዲያው በሚነዛው የወሬ ማዕበል ምክንያት ሰዎች በጥፍራቸው የቆሙ እስኪመስላቸው በንቃት ምርጫውን የሚከታተሉ ይመስላል እንጂ ስሌቱ የሚያሳየው ግን ሌላ ስዕል ነው፡፡ በዴሞክራሲ በልጽገዋል ከሚባሉ 40የሚሆኑ የአውሮፓና ሌሎች አገራት አንጻር በአሜሪካ ለምርጫ የሚወጣው ሕዝብ ሲነጻጸር አሜሪካ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በቁጥር ደረጃም ካየነው መምረጥ ከሚችለው ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በየጊዜው አይመርጥም፡፡ በ2000ዓም መምረጥ የሚችለው ሕዝብ 195ሚሊዮን አካባቢ የነበረ ሲሆን የመረጠው 107ሚሊዮኑ ብቻ ነበር፡፡ ቀሪው 87ሚሊዮን አካባቢ የሚሆነው ድምጹን አልሰጠም፡፡ በ2004 እና በ2008 የምርጫ ወቅትም እንዲሁ 80ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሳይመርጥ ቀርቷል፡፡ በዚህ ዓመቱ ምርጫም ቁጥሩ አልተቀየረም፡፡ በሌላ አነጋገር በአሜሪካ መምረጥ ከሚችለው ሕዝብ ውስጥ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሕዝብ የሚያክል መራጭ በምርጫ አይሳተፍም፤ አይመርጥም፡፡ ከዚህ ምርጫ በፊት በተደረገ የሕዝብ አስተያየት መሠረት 60በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን የአገራቸውን ፖለቲካ እንደማይከታተሉና ፖለቲከኞች የሚገቡትን ተስፋ ፈጽሞ የማይፈጽሙ ውሸታሞች በመሆናቸው በማንም ላይ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ዓለም የአሜሪካንን ምርጫ የዴሞክራሲ ተምሳሌት አድርጎ ከራሱ አገር ፖለቲካ አስበልጦ ይከታተላል፡፡ ምስጋና ለኮርፖሬት የሚዲያ አውታሮች!
የየትኛውም ፓርቲ ዕጩ ተመረጠ ለውጥ የማምጣቱ ሁኔታ ላይ እምብዛም ተስፈኛ ያልሆኑ መራጮችም ሆኑ የፖለቲካ ምሁራን ምርጫ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የሚኖረው ለውጥ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ለዓብነት ያህልም በውጪ ጉዳይ ላይ ባተኮረው ሦስተኛው የፕሬዚዳንታዊ ክርክር ወቅት ኦባማና ተቀናቃኛቸው ሮምኒ የአንድ ፓርቲ ተወካዮች እስኪመስሉ በተነሳው አጀንዳ ላይ በአብዛኛው መስማማታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አሜሪካ በፍልስጤምና እስራኤል ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በየትኛውም ፓርቲ ፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን አለመቀየሩ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሪፓብሊካንና የዴሞክራት ፓርቲዎችን “ሁለት ጭንቅላት ያለው አንድ የፓርቲ አካል” በማለት አንዳንዶች የሚገልጹዋቸው፡፡ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ብዙም እምነት የሌላቸው አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኞችም አልፈው ተርፈው በኦባማና በሮምኒ መካከል ያለውን ልዩነት በጥይት ወይም በስቅላት መገደል ከመምረጥ ተለይቶ አይታይም በማለት ይገልጹታል፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎቹ ሁለት ሳይሆኑ ሁለት እንዲመስሉ ሆነው የተሰሩ ነገርግን አንድ ፓርቲ ናቸው – ይህም ሪፓብሊክራት (Republicrat) ይባላል እስከማለት ይደርሳሉ፡፡
በመሆኑም በሚዲያው አደንቋሪነትም ይሁን በራስ ፍላጎት በርካታ ሰዓታት ተቃጥለውና ስድስት ቢሊዮን ዶላር ፈስሶ የአሜሪካ ምርጫ ተጠናቅቋል፡፡ በኦባማ የአራቱ የሥልጣን ዓመታት ወቅት አቶ መለስን ወዳጅ በማድረጋቸው የተበሳጩ በርካታ ኢትዮጵያውያን “ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሠይጣን ይሻላል” በሚል ይመስላል ኦባማ መመረጥ እንዳለባቸውና አኩርፎ ቤት ከመቀመጥ ይልቅ ውጡና ምረጡ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም ከነመኖራቸውም ፈጽሞ በማይታወቁት የሦስትዮሽ ኮሚሽንና (trilateral commission) የውጪ ግንኙነት ካውንስል (council on foreign relations) የሚመራው የአሜሪካና በአጠቃላይም የምዕራቡ ዓለም የውጪ ፖሊሲ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ኦባማ ለአገራችን ረብ ያለው ነገር እንዲሠሩ ፖሊሲ ይነድፍላቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸውና በወቅቱ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳድረው የነበሩት ሴናተር ቤሪ ጎልድዎተር በተለይ የሦስትዮሹን ኮሚሽን በተመለከተ With No Apologies በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ “የዓለምን የፖለቲካ፣ የገንዘብ፣ የእውቀትና የሃይማኖት ሥልጣን ማዕከላት በረቀቀና በተቀናጀ ዘዴ ለመቆጣጠር” የሚሠራ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተግባር በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚወጣውን የውጪ ፖሊሲ አስፈጻሚ ከመሆን እንደማያልፍ ግልጽ ሆኖ ሳለ ኦባማ ለኢትዮጵያ የተለየ የውጪ ፖሊሲ ነድፈው ወያኔ/ኢህአዴግን ጠራርገው ያስወግዳሉ ብሎ ማለም የህልመኛውን አእምሮ ጤንነት አጠያያቂ የሚያደርግ ነው፡፡
ስለሆነም ታዋቂው የጋና ምሁር ጆርጅ አዪቴ በተደጋጋሚ እንደሚሉት ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ሽግግር የትኛውንም ዓይነት ተሃድሶ ከማድረግ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የእውቀት ተሃድሶ ነው፡፡ ሕዝብ እንደሚገባው በእውቀት ከነቃ የዴሞክራሲና የመብቱን ጉዳይ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ይህንን ተከትሎ የሚከሰተው የእውቀት ተሃድሶ ወደ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊ፣ ሕገመንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ … ተሃድሶ ይመራል፡፡ የእውቀት ተሃድሶ ሳይደረግ ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር አንዱን አምባገነን በሌላ የመተካት ሂደት እንጂ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም ይላሉ፡፡ ሕዝብ የእውቀት ተሃድሶ ካካሄደ በሥልጣን ላይ ከተቀመጠው አምባገነን ያልተሻሉትን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ማንነት ጠንቅቆ ማወቅ ይችላል፡፡ በፖለቲካ ብልጣብልጥነት ሊያካሂዱበት የሚችሉትን አሻጥር አስቀድሞ ያውቃል፤ ዕድልም አይሰጣቸውም ምክንያቱም ሕዝብ የሚፈልገው ትክክለኛ ሥርዓት እንዲመሠረት እንጂ አንዱን አምባገነን በሌላው ለመተካት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ምሁሩ ከፖለቲካ ተሃድሶም ይሁን ከሌላ ማንኛውም ተሃድሶ በፊት የእውቀት ተሃድሶ መደረግ አለበት የሚሉት፡፡ በጋና ተግባራዊ አድርገውት ውጤት እንዳመጣና ጋና ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና ለመሸጋገር መቻሏን እንደማስረጃም ይጠቅሳሉ፡
ከዚህ አኳያ ለአገራችን ልንመኝም ሆነ ልንጠብቅ የሚገባን ተስፋ ሊመሰረት የሚገባው በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ምርጫ ላይ ከሆነ በየአራት ዓመቱ “ማን ያውቃል” እያልን ከመጠበቅ ያለፈ ውጤት ለማምጣት ይከብዳል፡፡ “ኦባማ መጀን” ብለን፣ ኦባማንም ተስፋ አድርገናቸው አራት ዓመታት አስጠበቁን፤ አሁን ደግሞ ሌላ አራት ዓመታት ለመጠበቅ ከፈለግን “እግዚኦ ኦባማ” ማለት ምርጫችን ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ከማንኛውም ተሃድሶ በፊት የእውቀት ተሃድሶን ተግባራዊ ለማድረግ እንደራጅ፡፡ የአገራችን ጉዳይ በእነማን እጅ እንዳለ እንወቅና ከእነዚህ ተቋማት ጋር በእውቀትና በቅንጅት ፊትለፊት እንግጠማቸው፡፡ ከፖለቲካ መሪዎቻችን ሳይሆን ከሕዝባችን ለሕዝባችን የሆነ ለውጥ እናምጣ፡፡ ይንን ማድረግ የማንችል ከሆነ ፖለቲካውን ተወት እናድርገውና “ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪ እጆቿን ትዘረጋለች” በማለት በየሃይማኖታችን ጸሎት (ዱዓ) እናድርስ፡፡ ይህንንም ማወቅ እኮ ትልቅ እውቀት ነው፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
dawit says
“ኦባማ መጀን” ውብ ጽሁፍ ነው።ከየአቅጣጫው የጎተታቸው ጉዳዮች መድረሻቸው የት ነው?በሚል ተከታተልኩት እናም ደረስኩበት።ኦባማ በመጀመሪያ ሲመረጡ ያለቀሱና “ኢትዮጵያ ጸሃይ ወጣላት” በማለት አስተያየት የሰጡ ነበሩ። ልጅቸውን ኦባማ ብለው የሰየሙ አቶ ገለታ የሚባሉ ሰውም አውቃለሁ። ጸሃፊው እንዳሉት ኦባማ ጠጅ ቤት፣ ኦባማ ጫማ አዳሽ፣ ኦባማ በለጬ… ተብለው የተሰየሙ የመንደር ንግድ ቤቶች አሉ። ሃሳቡ ኦባማ በቀለማቸውና በዘር ግንዳቸው ብቻ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸው ከሚዲያው እስክስታ ጋር ተዳምሮ የተፈጠረ ባዶ ተስፋ ነበር። ዋናው ጉዳይ ኦባማ መጀን ከማለት ራስን አደራጅቶ መታገል ነው በሚለው ሃሳብ ላይ አዲስ የመወያያ አጀንዳ መትከል አግባብ ነው። የጋናው ምሁር የተሞከረ፣ የሰራና፣ ውጤቱ የሚጨበጥ ሃሳብ ሰንዝረዋልና ያ የእወቀት ተሃድሶ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ።
Tsinat says
አቦ ይመቻቹ! ድንቅ ጽሁፍ ነዉ:: ለዚህ ጽሁፍህ ብቻ የኮፒ ራይት ህጋቹን ብታነሱና በየቦታዉ ቢበተን መልካም ይመስለኛል::
Miron yilma says
Betam des yamel hasab yayaze,melkto yameyarka beyawalho katlobet God Bless our Ethio
dawit says
@Tsinat እኔም ባነሳኸው ጥያቄ እስማማለሁ።ጎልግሎች እባካችሁን ይህንን ጽሁፍ የሚበተንበትን መንገድ ብትፈልጉ ለማለት እወዳለሁ።በሌላ በኩል ግን ለጽሁፉ እውቅና በመስጠት መበተን እንደሚቻል አስቀድማችሁ በመግለጻችሁ ለጥያቄው መልስ እንደማትነፍጉን ለማሳሰብ እወዳለሁ።
አ.በ. says
ወቅታዊ ፀሁፍ። እውነት ይሄ ሁሉ ሰው ካለፈው ሳይማር አሁንም አሜሪካን አ ብኢሎ ሲጠብቅ መየት ያሳዝናል ያሳፍራልም።
inkopa says
AT LAST!! …..
THANK YOU GOLGUL.
Editor says
ለ Tsinat and dawit:
በቅድሚያ እናንተ የዘወትር አንባቢዎቻችንም ሆነ ለሌሎች ለምትሰጡን አስተያየት ያለንን ልባዊ ምስጋና ለመግለጽ እንወዳለን::
ጽሁፎቻችንን በተመለከተ ያለን አሠራር ማንም ሰው የትም ቦታ መለጠፍም ሆነ ለፈለገው ማስተላለፍ – ማሰራጨት ይችላል:: ግን ለጽሁፎቻችን እውቅና እንዲሰጣቸው እንፈልጋለን ይህንንም የምናደርገው ጽሁፎቻቸንን በተመለከተ ለሚመጣው ነገር በሙሉ በሃላፊነት ለመጠየቅ ስለምንፈልግና ዝግጁ ስለሆንን ነው:: ስለሆነም የኛን ጽሁፎች ድረገጻችንን እንደ ምንጭ በመጥቀስ ዜና መሥራት ይቻላል ወይም ጽሁፉን እንዳለ በማሰራጨት ምንጩ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል:: ይህ ዓይነት የጋዜጠኛነት የሙያ ሥነምግባር ተግባራዊ ይሁን ነው የምንለው::
ለምሳሌ Associated Press አንድ ዜና ቢያወጣ ያንን ዜና እንደራስ አድርጎ ማውጣት ተገቢ ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚያስከስስም ነው:: ግን ያንን ዜና ከሌሎች መረጃዎች ጋር በማጣቀስ APን እንደ ምንጭ አድርጎ በመጥቀስ መሥራትም ይቻላል:: ይህንን ማድረግ የሚያቅት ከሆነ ደግሞ ዜናውን እንዳለ በማተም APን ምንጭ ማድረግ ይቻላል:: ይህ ሲሆን ተጠያቂነትና በተመሳሳይ የሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ ማግኘት የሚችሉት እንዲሀ ዓይነት አሠራር ሲለመድ ነውና በሚዲያው ላይ ያሉትም ሆኑ ሕዝባችን ባጠቃላይ ይህንን ይልመድ ነው የምንለው:: ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለነጻነት ስናስብ እነዚህንም የነጻ ሕዝብ እሴቶችን ወደጎን ማድረግ አይገባም ብለን በጽኑ ስለምናምን ነው:: በጊዜው ካልተለማመድናቸውና “አሁን ወያኔን እናስወግድ” በሚል ፈሊጥ ብቻ ከተውናቸው ወደፊት በአስማት አይከሰቱም ለማለት ነው::
ስለዚህ እናንተን ውድ አንባቢዎቻችንም ሌሎችንም ለማሳሰብ የምንፈልገው ይህንኑ እንደሆነ እንድትረዱን እንወዳለን:: ስለዚህ ጽሁፎቻችንን ይህንኛውንም ጨምሮ በተገቢው መሠረት በማሰራጨት በኩል ፍጹም ነጻነት እንዲሰማችሁ እንወዳለን:: አስቀድመንም ለዚህ መልካም ሥራችሁ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን::
የሚታረም ነገር ካለንም ላኩልን እንታረማለን – ለዕድገታችን በጣም ወሳኝ ነውና::
አርታኢ/Editor
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ/Golgul: the Internet Newspaper
http://www.goolgule.com
editor@goolgule.com
Amare says
ይህ ጽሁፍ አማርኛ እየተንገዳገደ ባለበት ሰዓት የቀረበ በመሆኑ እኔን ያረካኝ አማርኛ እያገገመ መሆኑን ማየቴ ነዉ። ሌላዉ ለለዉጥ የዕዉቀት ተሐዲሶ አስፈላጊነትን ሊያሳየን መሞከሩ ነዉ። በጀመረ እጁ ይህ የተባለዉ የዕዉቀት ተሐዲሶ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ያሳየናል ብዬ እገምታለሁ።
ደካማ ጎኑ ግን የአሜሪካንን ሚና አስመልክቶ እስከአሁን ያለዉን የተዛባ አመለካከት በሌላ የተዛባ አመለካከት መተካቱ ነዉ_አሜርካ የችግሮቻችን ሁሉ ፈች አድርጎ መመልከትን አሜርካ ለችግሮቻችን መፍቻ ምንም ሚና እንደማትጫወት አድርጎ መመልከት። አደገኛ አካሄድ።
የተባለዉ የዕዉቀት ተሐዲሶ እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት? ብለን እንጠይቅ። ተግባራዊም እናድርግ። ቄራ አካባቢ እንደሚራኮቱ ቁራዎች እርስ በርስ የሚናቆሩ “ፖለቲከኞች” ቁርጥም (ባይወገድም) ይቀንሳል። አምባገነንነትን አስወግዶ ጤናማ ህበረተሰብ ለመፍጠር የአሜርካ ሚናም እስከምን ድረስ እንደሆነ ለመገመት እንችላለን።
Fasil says
yehenee tsehuf liyanbu ymichelut betam tikitoche nachew. hizbu limar yemichelebet kelal ena fetan menged memechachet alebet.