የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና የስነ ጽሁፍና ፎክሎር መምህሩ ብርሃኑ አሰፋ (ዶ/ር) ሀገራችን ኢትዮጵያ ረዥም ዘመናትን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ የመጡ በየአከባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ባህላዊ የግጭት አፈታትና የእርቅ ተቋማት አሏት ብለዋል።
ለአብነት በወሎ አከባቢ ያሉትን ብናነሳ በራያና አከባቢው ዘወልድ፣ በተሁለደሬና አከባቢው አበጋር፣ በምዕራብ ወሎ አማሬና በሀብሩ አከባቢ ሸህ ለጋን መጥቀስ ይቻላል ያሉት መምህሩ በየአከባቢው ያሉት የግጭት አፈታቶቹ እንደየአከባቢው ባህል፣ ልማድ፣ እምነት እና የአኗኗር ኹኔታ መጠሪያቸውና የአከዋወን ኹኔታቸው ቢለያይም ግጭትን የመፍታትና እርቅን የማውረድ እሳቤያቸው ተመሳሳይ ነው ብለዋል።
እነዚህ የግጭት መፍቻ ተቋማት በማኅበረሰቡ እምነትና ስነ ልቦና ላይ የተመሰረቱና አስታራቂዎቹም በማኅበረሰቡ ከፍተኛ ግምትና ተቀባይነት የተሰጣቸው በመኾናቸው ውጤታማነታቸውና የእርቁ ዘላቂነት ተመራጭ ያደርጋቸዋልም ብለዋል።
መምህሩ ሀገራችን በየወቅቱ እያጋጠሟት ላሉ የግጭት ችግሮች እነዚህን ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶችን በመጠቀም ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ብሄራዊ የምክክርና የእርቅ መድረኩም እነዚህን ታላላቅ የግጭት መፍቻ ተቋማትን የሚመሩ አስታራቂ ሽማግሌዎችን በማካተት ቢካሄድ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።
በተለይም ወጣቱ በምዕራባውያን በእቅድ የተመራ የባህል ወረራ ተወስዶ እነዚህን ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በተገቢው ስለማያውቃቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባህሎቹን በማጥናትና በማስተዋወቅ ሚዲያዎችም በተገቢው ለሕዝቡ በማስገንዘብ ባህሎቻችንን ትውልዱ እንዲያውቃቸውና ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንዲገለገልባቸው ሊሰሩ ይገባል፤ መንግስትም ለእነዚህ ተቋማት ተገቢውን እውቅና ሊሰጥ ይገባል ብለዋል ዶ/ር ብርሃኑ አሰፋ። (አሚኮ)
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply