የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በወገኖቹ የሚፈቀር፣ የሚከበርና አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ የሚደረግለት የህዝብና የአገር አለኝታ ነው። ክቡር ህይወታቸውን ሳይሳሱ ላገራቸው ሲሉ አሳልፈው የሚሰጡትን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች የምናከብራቸውና ልንከባከባቸው የሚገባው ልክ ያይናችን ብሌን ያህል ነው። “ክቡር ለውድ ኢትዮጵያዊ ሰማዕታት” ሲባል እንዲሁ መፈክር ለማለት ሳይሆን ከልባችን፣ ከውስጣችን፣ የመስዋዕትነታቸውን ክብር ከቶውንም ልንዘነጋው የሚቻለን ባለመሆኑ ነው። ሌላ ምክንያት የለውም። በቃ!!
የምንኮራበት መከላከያ እንዲኖረን አጥብቀን ስለምንመኝ ያገር ኩራት የሆነው መከላከያችን በክልል፣ በዞንና በጎጥ አንሶና የተዋረደ ስብዕና ተላብሶ እንዲዋቀር ኢትዮጵያውያን አይፈቅዱም። አገራችን ከምትገኝበት የጂኦ ፖለቲካል አቀማመጥ አንጻር ብሄራዊ ስብዕና ያለው፣ ህዝብንና አገርን የሚያስቀድም የመከላከያ ኃይል ሊኖረን ይገባልና፡፡ በጎጥና በዘር ፖለቲካ የተተበተበ አመለካከት ያላቸው ክፍሎች በመከላከያ ሃይላችን እንዲቀልዱበት አንፈቅድም። ክብሩንና ሞገሱን አመናምነው ወገኑን የሚወጋና የሚያፍን የማፍያ ይዘት እንዲኖረው አንፈልግም። የእስካሁኑ ይበቃል!!
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የአገሪቱን መከላከያ እንደ ጠላት በመቁጠር በታትኖ መሳቂያ አድርጎናል። አየር ኃይላችንና ባህር ኃይላችንን አፍርሶ የወጠጤዎች መጫወቻ አድርጎናል። በዚህ አሳፋሪ ታሪክ አገር አፍሯል። ተዋርዷል። ንጹሃን ትርጉም በሌለው ጦርነት ተማግደዋል። ለአገር ሲዋደቁ የነበሩ ወገኖች እንደጠላት ታይተው እንደ እቃ መጣላቸው ለታሪክ የሚተው አቶ መለስ የፈጸሙት ታሪካዊ ግፍ እንዳለ ሆኖ፣ በባድሜ ወረራ ወቅት አቶ መለስ ያደራጁት የልምድ ጦርና አመራሩ ፍጥረቱ የተበላሸ በመሆኑ ወረራውን መመከት ሲያቅተው በዳግም ጥሪ አገሩን የታደገው ይኸው ወንጀለኛ ተደርጎና “የደርግ ሠራዊት” ተብሎ የተጣለው ወገን ነበር።
ብሄር፣ ክልል፣ ቀበሌ፣ ዘርና ቂም ሳያግደው በፈንጂ ላይ እየተረማመደ አገሩን ነጻ ያወጣ ወገን ዛሬም አይታመንም። ከደጀን ድጋፉን ሰጥቶ ለድል ያበቃ ህዝብ አሁንም ለለቅሶ እንጂ ለሃላፊነት አይታጭም። ከልምድና ከውድቀት መማር የማይችለው ኢህአዴግ ይህንን ህዝብና ወገን ማስቀየሙን ገፍቶበታል። የሰሞኑ ሹመትም የሚያጠናክረው ይህንኑ ነው። ያሳፍራል። ያሳዝናል።
በቅርቡ ኢህአዴግ ሹመት የሰጣቸው ጄኔራሎች ስልጣን የተቀበሉበት አግባብ ትክክል ሆኖ አላገኘነውም። ይህን መሰል ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመት የሚቀርበው በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሲገባው ይህ አልተደረገም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሰጠው ሹመት የአንድ ብሔር (የትግራይ) አባላት የተካተቱበት፣ ፍጹም ወገንተኛ፣ ሌሎች የአገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ያገለለ፣ የኢትዮጵያ ኩራትና መመኪያ የሆነውን የመከላከያ ሃይል የሚያሳንስ ሆኖ ይሰማናል።
ታላቁን የመከላከያ ሃይል በማሳነስ ከህዝብና ከአባላቱ አመኔታ የሌለው ማድረግ ዞሮ የሚጎዳው ኢህአዴግን ሳይሆን አገራችንን ነው። የመከላከያ ሃይላችን ፍጹም ህዝባዊ፣ ሚዛናዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ሁሉም ባለቤት በሆነበት ደረጃ ባስቸኳይ ሊደራጅ ይገባል። አቶ መለስ የመተማመን ፖለቲካ በመዘርጋት ዜጎችን ወደ አንድ አመለካት ማሰባሰብ ሲገባቸው ብቻቸውን ለመምራት ካላቸው የኖረ ህልም ተነስተው አገሪቱን ተቋም አልባ በማድረግ የተወሳሰበ ችግር አውርሰውን እሳቸው አርፈዋል። የተቀሩት ከመለስ የስህተት ጎዳና በመውጣት የማስተካከያ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ “በተጀመረው ይቀጥላል” በሚል መዝሙር እያደነቆሩን ነው። ይባስ ብለው የፖለቲካውን ክፍተት ለመሙላት ህወሃት ወታደራዊና የደህንነት ተቋሞቹን እያጠናከራቸው ነው። የራሱን ሰዎች ይሾማል። የራሱን ሰዎች ያስታጥቃል። የራሱን ሰዎች በኢኮኖሚ ያበለጽጋል። የራሱን ሰዎች ከፍ ከፍ ያደርጋል። የራሱን ሰዎች ታማኝ አድርጎ አብዛኞችን ይገፋል። አሁንም እስከመቼ በዚህ መልክ ይቀጥላል?
አቋማችን አንድ ነው። ህወሃት ከብሄራዊ ክብርና ሞገስ ይልቅ ጎጥና ጎሳ ብሶበት የሚርመጠመጥበት አካሄድ ማንንም ተጠቃሚ አያደርግምና ያቁም! አገሪቱን ወደ ወታደራዊ አመራር ለመውስድ የሚያደርገውን ሩጫ ይግታ! ድርጊቱን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በህብረት ይቃወሙት! የሁሉም ስህተቶችና የመጥበብ በሽታዎች ዞሮ የሚጎዳው አገራችንን ነውና ቅድሚያ እምዬ ኢትዮጵያን ብቻ!!
Yonas says
Guys, keep up the good work !