አንድ ሽማግሌ የነገሩኝ ታሪክ ትዝ አለኝ።
ሰውዬው ጀግና ነኝ፣ አንበሳ በጡጫ ነብርን በእርግጫ እገላለሁ እያለ ይጎርራል። በኋላ ራሱ ደጋግሞ ያወራውን ጉራ እውነት ነው ብሎ ራሱ አመነው። አምኖም አልቀረ በጉራው የተሳቡ፣ በወሬው የተሰባሰቡ፣ አድናቂዎቹን አስከትሎ በረሃ ወረደ።
እሱ ጀብድ ሊሠራ ሌላው ጀብድ ሊያወራ፣ ምን ለምን አብረው አዘገሙ። አድናቂዎቹን ከፍ ያለ ኮረብታ ላይ አስቀመጠና “ዛሬ ሶምሶንን በዓይናችሁ ታያላችሁ” አላቸው። እነርሱም አድንቀውና አዳምቀው እንዴት እንደሚያወሩት እያሰቡ ወደ አንበሳ መንጋ የሚወርደውን ጀብደኛ በማዶ ይመለከቱ ያዙ።
ወረደ ጀብደኛው። አንበሶች ሰብሰብ ብለው ተኝተዋል። በሩቁ ድንጋይ ወረወረባቸው። ሁሉም አንበሶች ቀና ቀና አሉ። አንዱ በድንጋይ የተመታ ደቦል ዘሎ ወጣበትና በቅጽበት ሌሎች ገነጣጠሉት። ታሪኩም ከጄት ፈጥኖ ከውኃ ቀጥኖ በዚሁ ተጠናቀቀ። አድናቂዎቹ ግራ ተጋቡ። ምን ብለው ያውሩ? ለዘመናት ተወርቶለት ለደቂቃ የተጠናቀቀውን ጨረባ ምን ብለው ይተርኩት።
በመጨረሻም ለኛም ለታሪካችንም አይበጅም አሉና መከሩ። ለቅጽበት ያለቀውን ጨረባ ለዘመናት በመተረክ ሊያካክሱት ወሰኑ። ወደ መንደሩ ተመለሱና ያላዩትን ፈጥረው፣ ያልሰሙትን ቀምረው እያዳነቁ አወሩ።
‘ጀግናው’ አንበሶችን ገድዬ ካልጨረስኩ አልመለስም አለ ተብሎ ተወራ። መንደርተኛውም አደነቀ። ከወራት በኋላም አንበሶችን ጨርሶ ነብሮችን ጀምሯል ተብሎ ተወራ። መንደርተኛውም አዳነቀ። ከወራት በኋላም ነብሮችን ጨርሶ ከዘንዶ ጋር እየታገለ ነው ተባለ። ተደነቀ።
ሰውዬው ከሞተ ዘመናት ቢያልፉትም አዝማሪውና ገበያተኛው ግን የራሱን ታሪክ እየፈጠረ መዝፈኑን ቀጥሏል። አንዳንዶችም ለጀብደኛው ስንቅ እናዘጋጃለን ብለው ብዙ እህልና ከብት ሰብስበዋል። አንዳንዶችም ስለ እርሱ ሕልም አልመናል፣ ራእይ አይተናል እያሉ ታዋቂ ሆነዋል። ሌሎችም የጀብደኛው ወኪሎች ነን ብለው በየሠርግና በየልቅሶ ቤቱ፣ የክብር ሥፍራ ይወስዳሉ። ሌሎችም የሌለውን ሰውዬ አንድ ቀን ይመጣል ብለው በምኞት ይጠብቃሉ። አንዳንዶችም አይተን መጣን ብለው፣ ሌሎችም ሰው ነገረን ብለው የሌለውን ጀብደኛ ‘ገድል’ መንደር መጥተው ያወራሉ። ቢያንስ ለወሬው ሲባል ጠላና ጠጅ ጋባዥ አያጡም።
የሞተ ጀብደኛ ተጎዳ እንጂ …
ዳንኤል ክብረት
Leave a Reply