• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

በግብረሰዶም ተጠርጣሪዎች ላይ የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ የምስክርነት ቃል ሰጡ

August 5, 2013 09:26 am by Editor 1 Comment

ሁለት የ10 እና የ11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የግብረሰዶም ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ ስድስት መምህራን ክስ ላይ፣ ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በተጨማሪ አንዲት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የሙያ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ በማየት ላይ ያለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰባተኛ የወንጀል ችሎት፣ ስማቸው በሚዲያ እንዳይገለጽ የከለከለላቸው የሳይኮሎጂስትና የሳይካትሪ ባለሙያዋ፣ በተጠርጣሪ መምህራን የግብረሰዶም ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባሉትን ሁለት ወንድ ሕፃናት፣ ለሦስት ጊዜያት አግኝተው እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹንም ሆኑ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው የተባሉት ሕፃናትን እንደማያውቋቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ሕፃናቱን ከአራት ወራት በፊት ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ታዘው ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዋ ከሕፃናቱ ጋር ቃለ መጠይቁን ያደረጉት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ጠቁመው፣ መጀመሪያ ከእናቶቻቸው ጋር ቀጥለው ደግሞ ሕፃናቱን ለብቻቸው ማነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕፃናቱን መጀመሪያ ከወላጆቻቸው ጋር ያነጋገሯቸው ስለማያውቋቸው ለመለማመድ መሆኑንና ቀጥለው ለብቻቸው ቤተሰቦቻቸውን ሳይፈሩ እንዲያነጋግሯቸው ማድረጋቸውን የገለጹት ባለሙያዋ፣ በምክር ወይም ድርጊቱን በማስጠናት የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጧቸው፣ ቃለ መጠይቁን ያደረጉላቸው እያጫወቱና ዘና እንዲሉ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠዋት ቁርሳቸውን ከበሉበት እስከ ማታ ከትምህርት ቤት ተመልሰው ወደ ቤታቸው እስከሚገቡበት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ያደረጉትን አንድ በአንድ እንዲያስረዷቸው በመጠየቅ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ባለሙያዋ የሚፈልጉትን በጨዋታ ዓይነት ተጎጂ የተባሉት ሕፃናት ምንም ሳይፈሩ የጠየቋቸውን ሁሉ በአግባቡ እንደመለሱላቸው አክለዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያትም ያንኑ ጥያቄ ሲጠይቋቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ማስረዳታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ሕፃናቱ እንዴት ቀናቱን ሊያስታውሱ እንደሚችሉ ተጠይቀው ባለሙያዋ ሲመልሱ፣ ሕፃናቱ ቀኑን በትክክል ባያስታውሱም ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ጊዜ በዓል ካለ ወይም በዚያን ጊዜ የማይረሳ ነገር ካለ እሱን በማስታወስ እንዲያስታውሱት ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ከተጠቂዎቹ አንዱ ቀኑን በደንብ አስታውሶ እንደነገራቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ያሏቸውን ሰዎች ስምና ድርጊት እንዳስረዷቸው ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት ከድርጊቱ በኋላ የሚያሳዩት ባህሪ ካለና የጉዳዩ ባለቤት በሆኑት ሕፃናት ላይ ያዩት የባህሪ ለውጥ ወይም ምልክት ካለ እንዲያስረዱ ተጠይቀው፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት አራት ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡ ፈሪ፣ ኃይለኛ (ተደባዳቢ)፣ ብቸኛ መሆንን መፈለግና ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ፍላጎት የማሳየት ባህሪያት እንደሚያመጡ አስረድተዋል፡፡ ሌላው በትምህርት ላይ የሚያሳዩት ሁኔታ ሲሆን፣ በአንድ ትምህርት ላይ ብቻ ጎበዝ የመሆንና ሌላውን የመጥላት ወይም ፍላጎት ያለማሳየትና ደብተራቸውን ጥሎ የመምጣት ባህሪም እንደሚያመጡ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡

ተጠቂ ከተባሉት ሁለቱ ሕፃናት አንደኛው የወሲብ ፍላጎት እንዳለውና እሱም እንዳረጋገጠላቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ይኼ ስሜት ሲመጣበት ከማን ጋር ለማድረግ እንደሚፈልግ ጠይቀውት፣ ከወጣት ወንዶችና እንደ አስተማሪዎች ካሉ ወንዶች ጋር ማድረግ እንደሚፈልግ፣ ወንድ ሕፃናትና ትልቅ ሰው እንደማይፈልግ እንዳስረዳቸው ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ጥያቄ ያቀረቡለት በጥናት ሕፃናት የሚጠቁት በአብዛኛው በሚያውቁትና በቤተሰብ፣ ወይም ዘመድ መሆኑን ስለተረጋገጠ በቤታቸው ውስጥ ወንድሞችና አባት ስለሚኖሩ ከነሱ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሕፃናት ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው ወዲያውኑ የቤተሰብ እንክብካቤ፣ አማካሪ ዘንድ በመውሰድ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ ድርጊቱ እንዳልተፈጸመ ሆኖ እንዲሰማቸው ወይም ጥፋቱ የእነሱ እንዳልሆነ እንዲያስቡ ስለሚያደርጋቸው በቀጣይ ከሚደርስባቸው ተፅዕኖ ማዳን እንደሚቻልም ባለሙያዋ አብራርተዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እያደጉ ሲሄዱ እነሱም ወደ ተመሳሳይ ተግባር እንደሚያመሩ፣ ኃይለኞች እንደሚሆኑ፣ ከቤት ወጥተው ተስፋ በመቁረጥ ወደማይሆን ነገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡

መምህራኑ የተጠረጠሩባቸው ሁለቱም ሕፃናት ‹‹ትምህርት አስጠልቶኛል፤ ባልሄድ ደስ ይለኛል፤›› እንዳሏቸው ባለሙያዋ ጠቁመው፣ በጥናትም የተረጋገጠው ሕፃናት ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ብቸኝነትን እንደሚመርጡ፣ ፈሪና ኃይለኛ እንደሚሆኑ መረጋገጡንና በእነሱም ላይ ምልክቱ ተግባራዊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንደኛው ተጠቂ ብዙ ትምህርት ቤቶችን እንደቀያየረና በሄደባቸው ትምህርት ቤቶች ጥቃቱ እንደደረሰበት በመጥቀስ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች እንዴት ሊያውቁት እንደሚችሉ ጠይቀውት ከሆነ ባለሙያዋ እንዲያስረዱ ሲጠይቋቸው፣ በተለይ አንደኛው ተጠቂ ከፍተኛ የወሲብ ስሜት ስላለው፣ ተጠግቶ ስለግብረሰዶም እንደሚያወራቸው ነግሯቸዋል፡፡ ስሜታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ተጠቂዎች አንገት ሥር የመሳም፣ የመነካካት፣ በብልት አካባቢ መመልከትና መቀመጥ እንደሚያዘወትሩ ባለሙያዋ አክለው፣ በአንደኛው ሕፃን ላይም ይህንን ምልክት ማየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ድርጊቱ በቤተሰብ ቢፈጸም በሌላ ሰው የማሳበብ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበትን አጋጣሚ በሚመለከት ለባለሙያዋ ጥያቄ ቀርቦ፣ ‹‹እውነት ነው፣ አድራጊውን በመፍራት በሌላ ሰው ላይ ያሳብባሉ፤›› ካሉ በኋላ፣ በሁለቱ ሕፃናት ቤተሰብ ዙሪያ ስላለው ሁኔታ ሲጠየቁ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑን ብቻ መናገራቸውን አውስተዋል፡፡

ስድስት መምህራን በአንድ ሕፃን ላይ ተፈራርቀው ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ልጁ ያለምንም ጉዳት ወደ ጨዋታ የሚሄድበት ሁኔታ ካለ እንዲያስረዱ ባለሙያዋ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አንዳንድ ጊዜ ሊገጥም እንደሚችል፣ ግን የልጁ ሁኔታ እንደሚወስን ካስረዱ በኋላ፣ ይኼ የአካል ጉዳትን የሚመለከት በመሆኑና እሳቸውም በዚህ ዙሪያ ማብራራት እንደማይችሉ ተናግረው፣ የሕክምና ባለሙያ ማብራሪያ ሊሰጥበት እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ተፅዕኖው አብሯቸው አድጎ ትዳር በሚመሠርቱበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትልባቸው ገጠመኛቸውን በማስረዳት አደገኛነቱን ተናግረዋል፡፡

ሕፃናቱ የግብረሰዶም ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ምርመራ በማድረጋቸው፣ ፍርድ ቤቱ የምርመራ ውጤቱን ተከትሎ በሰጡት ማስረጃ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሆስፒታሎቹ መታዘዛቸው ይታወሳል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ‹‹ባለሙያ የለኝም›› ብሎ ምላሽ ሲሰጥ፣ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግን ባለሙያ ሳይልክ በመቅረቱ፣ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲልክ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. የአካዳሚው መምህራን የተጠረጠሩበትን የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል አስመልክቶ ለመዘገብ በፍርድ ቤቱ የተገኘ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ የሚታየው በዝግ ችሎት መሆኑን ገልጾ እንዲወጣ በማዘዙ ችሎቱን ሊከታተል አልቻለም፡፡

ዘጋቢው በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በመዋል መረጃውን ከችሎቱ ታዳሚዎች በማግኘት ውሎውን በተመለከተ ‹‹ጋዜጠኞች ችሎት እንዳይገቡ ተከለከሉ›› በማለት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ችሎቱ ዝግ የሆነው በሌሎች መዝገቦች እንጂ በግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል የተጠረጠሩትን እንደማያካትት አስታውቆ፣ ችሎቱ በግልጽ መካሄዱን በመግለጽ ማስተካከያ እንዲያደርግ አዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ችሎቱ ዝግ እንዲሆን የተደረገው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ እንደሚገኘው አንዳንድ ክሶች (ጉዳዮች) በዝግ ችሎት መታየት ስላለባቸው፣ የሪፖርተር ዘጋቢ ከችሎት እንዲወጣ የተደረገው በዝግ ችሎት መታየት ለሚገባቸው ጉዳዮች እንጂ፣ በግብረሰዶም ወንጀል ተጠርጥረው ለተከሰሱት ባለመሆኑ፣ ዘገባው ስህተት እንዳለበትና ይኼው እንዲገለጽ በድጋሚ አዟል፡፡

የሪፖርተር ዘጋቢ በዕለቱ ለብይን ተቀጥሮ የነበረውን የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለመከታተል በሰዓቱ ችሎቱን ታድሟል፡፡ ችሎቱ በዝግ እንደሚታይ በመግለጽ ታዳሚዎች እንዲወጡ ዳኛዋ ሲያዙ ዘጋቢው ወደኋላ በመቅረት ለፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ መሆኑን በመግለጽ መታደም እንዲችል ሲጠይቅ አልተፈቀደለትም፡፡ ውጭ ቆይቶ በተደጋጋሚ ለመግባት ሲሞክር የችሎት ፖሊሶች ‹‹ዝግ ነው›› በማለት ሊያስገቡት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ችሎቱ እስከሚያበቃ እዚያው ቆይቶ ከችሎቱ ታዳሚዎች ባገኘው መረጃ መሠረት ሲዘግብ፣ ችሎቱ ጉዳዩን በዝግ ማየቱን በዘገባው አካቷል፡፡ ዘጋቢው የዕለቱን ችሎት በአግባቡ እንደዘገበ ቢታወቅም፣ ፍርድ ቤቱ መስተካከል እንዳለበት በማዘዙ በድጋሚ ለመዘገብ ተገደናል፡፡

ሌላው ፍርድ ቤቱ እንዲታረም ያዘዘውና ሪፖርተርም ስህተት መሆኑን አምኖ ተስተካክሎ እንዲነበብ አንባቢዎቹን የሚጠይቀው፣ የግብረሰዶም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል በተባሉት ሁለት ወንድ ሕፃናት ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ የታዘዙትን የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያን በሚመለከት ስለተሠራው ዘገባ ነው፡፡

በወቅቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ሠራተኛ ሆኖ ሳለ፣ የሪፖርተር ዘጋቢ ግን ቀደም ብሎ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት ቆጥሯቸው የነበሩትን የሥነ ልቡና ባለሙያን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በተፈጠረው ስህተትም ፍርድ ቤቱንና አንባብያንን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Law Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. Ermisha Beyene Petros says

    November 18, 2017 11:54 am at 11:54 am

    ግብረሰዶም ፈጽመዋል በሚል ጥርጣሬ ክስ የተመሠረተባቸው መምህራን ነፃ ወጡ
    December 01, 2013
    •ተጠርጣሪዎቹና የችሎት ታዳሚዎች በእንባ ተራጩ
    https://www.google.co.uk/url?sa=t&rct=j&q=&esrc=s&source=web&cd=1&cad=rja&uact=8&ved=0ahUKEwjoxZW43cfXAhXDrxoKHdnvAZ0QFggoMAA&url=https%3A%2F%2Fwww.facebook.com%2Fpermalink.php%3Fstory_fbid%3D1431909613690818%26id%3D1411286192419827&usg=AOvVaw3GJWTVsP_rfsUtSx3tV9zd

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • በአዲስ አበባ የተወረረው መሬት፣ ባለቤት አልባ ቤቶችና ሕንጻዎች ይፋ ሆኑ January 26, 2021 11:16 am
  • የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አክቲቪስቶችን በሕግ ተጠያቂ አደርጋለሁ አለ January 26, 2021 10:32 am
  • የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማኅበር 81ኛ የምስረታ በዓል January 26, 2021 07:17 am
  • በጋምቤላ ህወሃትንና ኦነግ ሸኔን ትረዳላችሁ ተብለው የታሰሩ እንዲፈቱ ተጠየቀ January 25, 2021 03:07 pm
  • “…ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው” – ዶ/ር ሙሉ ነጋ January 25, 2021 01:02 pm
  • የሶማሌና ኦሮሚያ መሥተዳድሮች ወሰንን በተመለከተ የሰላምና የጋራ ልማት ስምምነት አደረጉ January 25, 2021 12:50 pm
  • 125ተኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት ሊከበር ነው January 25, 2021 09:34 am
  • በመቀሌ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የህክምና ግብዓቶች ክምችት መኖሩ ታወቀ January 25, 2021 02:47 am
  • ዊንጉ አፍሪካ (wingu.africa) በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የመረጃ ማዕከል ሊገነባ ነው January 24, 2021 01:23 pm
  • ኢትዮጵያ ድሮኖችን ማምረት ልትጀምር ነው January 24, 2021 02:40 am
  • የአየለ ጫሚሶ ቅንጅት ፈረሰ January 18, 2021 02:31 pm
  • ህወሓት ተሠረዘ!!! January 18, 2021 01:32 pm
  • ዓሲምባ፣ ሣልሳዊ ወያኔና ባይቶና ከመፍረሳቸው በፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተነገራቸው January 18, 2021 01:00 pm
  • ቤተሰቦች አስከሬን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገረ January 14, 2021 06:48 pm
  • ስብሃት፤ “ከሞትን ቆይተናል፤ … አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችን” እየተፈጸመ ነው January 14, 2021 01:37 pm
  • “ተመልሰን እንነሳለን” ያሉት ህወሓቶች ተመልሰው ወደማይነሱበት ተሸኙ January 13, 2021 01:12 pm
  • አፋር ነፃ አውጪ (ኡጉጉሙን) ለመጠቀም የታቀደው የህወሃት ሤራ ከሽፏል January 13, 2021 01:10 pm
  • ህወሃትን ወደ ጅቡቲ ለማሻገር ሲሰሩ የነበሩ የአፋር ታጣቂዎች በሰላም ወደ ክልሉ ገቡ January 13, 2021 06:47 am
  • በታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ January 13, 2021 06:10 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? January 13, 2021 04:10 am
  • ለትምህርት እንዲሆነን January 11, 2021 01:20 pm
  • “ከተቀበሩበት የጃርት ጉድጓድ ነው ያወጣናቸው” መቶ አለቃ ስዩም ቱርቦ January 11, 2021 12:11 pm
  • የተደመሰሱና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወንበዴው አባላት ይፋ ሆነ January 7, 2021 01:16 pm
  • ዐቢይና መኮንኖቹ በመቀሌ፤ “ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” December 13, 2020 02:36 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule