• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

“በአገራችን ባይተዋር ከመሆን በላይ ውርደት የለም”

November 5, 2012 11:39 am by Editor 4 Comments

ይህንን ዘገባ ሳሰናዳ በ1997 ምርጫ ወቅት አዲሱ ገበያ አካባቢ አልሞ ተኳሾች የገደሉባቸውን ልጃቸውን ስም እየጠሩ “ምን አደረካቸው? ምን አጠፋህ? አንተኮ ትንሽ ነህ? ማንን ልጠይቅ? ማንን ላናግር? ልጄ … የኔ ባለተስፋ፣ እኔ ልደፋ፣ እኔ መንገድ ላይ ልዘረር፣ ምነው ለኔ ባደረገው? የማን ያለህ ይባላል…” የሚሉ ልብን ዘልቆ የሚገባ ሃረግ እየደጋገሙ እብደት የተቀላቀለው ለቅሶ አልቅሰው ያስለቀሱን እናት ታወሱኝ፤ ብዙዎች በተመሳሳይ አንብተዋል።ደረታቸውን ደቅተዋል። አሁን ድረስ የልጅ፣ የአባት፣ የወንድም፣ የእህት፣ የዘመድና ወዳጅ ብሎም የአገር ልጅ ሃዘን የሚያቃጥላቸውን ቤታቸው ይቁጠራቸው።

“ኢትዮጵያ ለእኛ አስፈላጊ አገር ናት። ኢትዮጵያዊ በመሆናችን ለአገራችን ትልቅ ቦታ መስጠት አለብን። ምክንያቱም አስፈላጊ ናትና። እዚያ እስከተወለድን ድረስ /መሰረታችን ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ ለማለት ነው/ ለአገራችን መቆም አለብን። መለስ የተባለው መጥፎ ሰው ይዝትብናል። ህዝባችንን ይገድላል። ስለዚህ ለመብታችን መታገል አለብን። ወደ አገራችን ለመመለስ መታገል አለብን” ስትል ስሜቴን የጎተተችውን ህጻን ያገኘሁት ኦስሎ ነው። ስምንት ዓመት፣ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ!

“ስለ መንግስትና ስለመለስ ነግሬያት አላውቅም። መለስ ስለመሞቱና ስለመኖሩ ትወቅ አትወቅ አላውቅም። ይህንን ደብዳቤ ብዕር ተውሳ እዚሁ ጎኔ የጻፈችው ነው…” የኦስሎ ነዋሪው አባት አቶ እንግዳ ታደሰ ውስጣቸው ዘልቆ የገባውን ስሜታቸውን መደበቅ በማይችሉበት ሁኔታ የተናገሩት ነበር። አዎ፣ እሳቸው በወላጅነት፣ ሌሎች በመልክቱ ጥንካሬ ስለመራዳቸው የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ምስክር ነው።

ይህ የሆነው ኦክቶበር 31/2012 ኦስሎ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ነው። አቶ ኦባንግ ሜቶ በተጋባዥነት የተገኙበት ይህ ውይይት ሲጀመር የማህበሩ ሊቀመንበር ወ/ሮ ዙፋን አማረ “ውድ ወንድማችን፣ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ፣ኢትዮጵያዊያን ርዳታ በጠየቁበት ሁሉ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ የቦታ ርዝማኔ ሳያግድህ ፈጥነህ ትደርሳለህና ሁላችንም ላንተ ታላቅ አክብሮት አለን” አሉ። ኦባንግ መድረኩን ተረክበው “የማደርገው ሁሉ ለህሊናዬና ነው። ማድረግ የሚገባኝን አደርጋለሁ። ግዳጄም ነው። ምስጋና አያስፈልግም ዛሬ ንግግር ሳይሆን ምክር እሰነዝራለሁ” የሚል ምላሽ ሰጡና ስለ መደራጀት አበክረው ተናገሩ።

አቶ ኦባንግ ለምን ኦስሎ ተገኙ?

መሰረታዊ ለውጥ ይከናወን ዘንድ ሁሉም ተባብሮ አንድ ወጥ ትግል ማድረግና ስደትን እስከ መጨረሻ ለማስቀረት መስራት አለብን የሚለው በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ዋና ጸሃፊ ቢኒያም ካሳ፣ ኦባንግ ሜቶ ኦስሎ ስለመጡበት ዓቢይ ምክንያት ያስረዳል። ለማንኛውም የስደት ማመልከቻ መልስ የሚሰጠው የኖርዌይ የስደተኞች ጉዳይ መ/ቤት (UDI: Norwegian Directorate of Immigration) ለጉዳዩ መነሻ የሚያደርገው ስደተኛው ስለጠየቀበት አገር ተጨባጭ ሁኔታ የተጻፈውን (Land Information) ተብሎ የሚጠራውን ሰነድ ማስረጃ በማድረግ በመሆኑ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያለው መረጃ አሁን ካለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ስለማይጣጣም የስደት ማመልከቻ አቅራቢዎች ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አድርጓል።

ይህንን የተዛባና አንድ ወገን የሚያቀርበውን መረጃ ማስተካከል ይቻል ዘንድ ማህበሩ ይህንን መረጃ ከሚያዘጋጀው አመራሮች፣ የስደት ማመልከቻ የመጀመሪያ ውሳኔ የሚሰጠው ዩ.ዲአ.ይ፣ የስደት ማመልከቻ ውሳኔ ይግባኝ ሰሚ ቦርድ (UNE: The Norwegian Immigration Appeals Board) እና በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ከተነገረለት የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው ስደተኞች መብት መከበር ከሚሰራው “ኖሽክ ፎልክ የልፕ” ጋር በየደረጃው ውይይት ተደርጓል። አቶ ኦባንግ በቂ መረጃ፣ ተሞክሮ፣ ተቀባይነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታዋቂ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር የቀረበ የስራ ግንኙነት ስላላቸው ተጋብዘው በውይይቶቹ ላይ እንዲገኙ መደረጉን ቢኒያም ያስረዳል።

የስብሰባው ውጤቶች ምን ይመስላሉ?

ስብሰባዎቹ የተከናወኑት በሶስት ተከፍለው ነበር። በቅድሚያ ዩኤንኢ የስደት ማመልከቻ ውሳኔ ይግባኝ ሰሚ ሁለት ተወካዮች፣ ከላንድ ኢንፎ ሶስት ተወካዮች በተገኙበት በጣምራ የተከናወነው የመጀመሪያው ውይይት ሲሆን፤ በመጀመሪያ የስደት ማመልከቻ ተቀብሎ ውሳኔ ከሚሰጠው ከዩዲአይ ሶስት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከቱ አካላት ጋር በተናጠልና “ኖሽክ ፎልክ የልፕ” በሚል ስያሜ ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛ ለመዋጋት ከተቋቋመው ድርጅት ጋር ነበር።

በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል የሆነው ሙሉአለም ደረጀ “እስካሁን ባለው እውነታ የስደት ማመልከቻ የሚቀበለው ዩዲአይም ሆነ ይግባኝ ሰሚው ቦርድ ለውሳኔያቸው መሰረታዊ መነሻቸው የሆነው የላንድ ኢንፎርሜሽን በየጊዜው መሻሻል ይገባዋል። በዚህ መሰረት አቶ ኦባንግን በመያዝ ባካሄድናቸው ውይይቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ረገጣው መባባሱን፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት መታፈኑን፣ የተለየ አመለካከት ማራመድ አለመቻሉን፣ መቃወም እንደሚያስወነጅል፣ በተለያዩ ደረጃ ወገኖች እየታሰሩና እየተገረፉ መሆኑንን በተለያዩ አቅጣጫዎች በማሳየት ግንዛቤ ማስጨበጥ” መቻሉን ይናገራል።

ሌላው የማህበሩ ስራ አስፈጻሚና የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ ጌዲዮን ደሳለኝ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የሚያካሂደው አፈናና ማሳደድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረና እየከፋ በመሄዱ ስደቱ እየተባባሰ ነው። አዲስ የሚመጡ ስደተኞች እኛ የገጠመን ችግር እንዳይገጥማቸው ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማስረዳት አግባብ ይሆናል። በዚሁ መነሻ ከተጠቀሱት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት መጨረሻ ለስራቸው ግብአት የሚሆን መረጃ ማግኘታቸውን እንደተነገራቸው ያስረዳል።

ላንድ ኢንፎርሜሽን ፖሊሲ አውጪ ተቋም ባይሆንም ስለ ኢትዮጵያ ግን ወቅታዊና ታማኝ መረጃ ማዘጋጀት እንዳለበት በሚያሳስበው ውይይት ላይ አቶ ኦባንግ በጥልቀት በመረጃ አስደግፈው በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃ ያሉትን የውይይቱ ተሳታፊዎች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሰጡት መግለጫ ውጤት ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳለውም ጌዲዮን አስታውቋል።

አቶ ኦባንግም በዝርዝር ስለውይይቱ ባይገልጹም መረጃውን ለሚያጠናቅሩት ክፍሎች በቂ ግብአት የሚሆን ስራ ስለመሰራቱ ይስማማሉ። በተከታታይ ለሚሰሩ ስራዎች መሰረት በማኖር ከዓመት በፊት የተጀመረው ሥራ ውጤት እንዳዩበት ያስገነዘቡት ኦባንግ በቅርቡ አንድ ለውጥ ይኖራል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ኦባንግ ሜቶ ምን ይላሉ?

“አማራጭ ቢኖረን ስደትን አንመርጥም ነበር። በአገራችን ግፍ ባይፈጸምብን ኖሮ አገራችን እንኖር ነበር” በሚል አስተያየታቸውን የሚጀምሩት ኦባንግ አጥብቀው የሚናገሩት ስለመደራጀት አስፈላጊነት ነው። ባካሄዱት ውይይቶች መግባባት እንደነበር ያስታወቁት አቶ ኦባንግ አስርና ከአስር ዓመት በላይ በስደት ካምፕ ውስጥ ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት ወገኖች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ደጋግመው አስታውቀዋል። በርካቶች ለስነልቦና ችግርና ለአእምሮ ቀውስ መዳረጋቸው ያበቃ ዘንድ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

እኤአ 2005 ላይ በተባበሩት መንግስታት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የወጣው መመሪያ (guideline) አሁን ካለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የማይስማማና ሊቀየር የሚገባው በመሆኑ ድርጅታቸው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አግባብ ካላቸው ክፍሎች ጋር እየሰራ መሆኑንን አቶ ኦባንግ ጠቁመዋል።

በየደረጃው የተደረጉት ውይይቶች እጅግ አስፈላጊና መደረግም የሚገባቸው እንደነበሩ ያስታወሱት ኦባንግ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ። ግን ብዙ መስራት ያስፈልጋል። ጀምረናል አናቆምም” ብለዋል። ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ፣ የሰው ልጆች መብት የሚከበርባትና ለዜጎቿ ሁሉ እኩል የሆነች አገር አድርጎ የሳላት በ2005 ላይ የተዘጋጀው መመሪያ ይቀየር ዘንድ ትግሉ የሁሉንም አካላት ያላሰለሰ ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነም አስምረውበታል።

ከዩዲአይ ጋር በተደረገ ውይይት አጠንክረው ወቀሳ የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ “የኖርዌይ መንግስት የችግሩ ምንጭ አይደለም። ችግሩ የኛ የራሳችን መንግስት ነው። እኔ ሰብአዊ መብት ላይ የምሰራ ሰው ነኝ። የፖለቲካ መሪና የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም። ግን አሸባሪ ተብዬ ተከስሻለሁ። እኔ አንድ ያለው ችግር ማሳያ ነኝ። እኔ ላይ የተደረገው አይነት ውሳኔ በርካቶች ላይ ተወስዷል። ይህንን የኢትዮጵያ መንግስት ተግባር አታውቁም ማለት አልችልም” ሲሉ ስለ ኢትዮጵያ መንግስት ዓለምአቀፍ እውቅና ያላቸው ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያወጡትን ሪፖርት እንደ ግብአት ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ራሷን ካጠፋች ልጆቿ የተሻለ እድል ይገጥማቸዋል በሚል ራስዋ ላይ የፈረደች እናትን ታሪክ በማውሳት ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ያሳዩት አቶ ኦባንግ “አንዳንድ ጊዜ አሁን በስደት ከሚኖሩት ኑሮ ይልቅ ሞት የሚመርጡ እንዳሉ መረጃ አለኝ” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በስፋት ምሳሌዎችን በማጣቀስ አቅርበዋል።

ኦባንግ በሶማሊያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን የስዊዲን ጋዜጠኞች ለማሳያነት ተጠቅመዋል። “ጎረቤቶቻችሁ” ነበር ያሉት። “ጎረቤቶቻችሁ ወደ ኦጋዴን የገቡት በስፍራው በመገኘት መንግስት የፈጸመውን ወንጀል ለማጋለጥ ነበር። በርግጥ ድንበር ያለፈቃድ ማቋረጣቸው ህጋዊ ባይሆንም አሸባሪ ግን አያሰኝም። እንግዲህ የኛ መንግስት እንዲህ ያለ ነው” ነበር ያሉት። አያይዘውም እንግዲህ ከዚህ መንግስት መንጋጋ አምልጠው የመጡትን ነው ለመመለስ ስምምነት የተፈጸመው በሚል ውሳኔው ዳግም ሊመረመር እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ከስብሰባው በኋላ ከአስር እስከ አስራ ሁለት ዓመት ያለ ትምህርት፣ ያለ ሥራና ያለ አንዳች ለውጥ በካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች አስመልክቶ በተለይ ከጎልጉል ለቀረበላቸው ጥያቄ “የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ካምፕ መኖሪያቸው ዘንድ በመዘዋወር የመጎብኘት አቅድ አለን” ሲሉ አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ እነዚህ ወገኖች ያሉበት ሁኔታ ማንኛውንም ዜጋ እረፍት የሚነሳ በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተዋል። በመጨረሻም “የኖርዌይ መንግስት አንድ ሊያደርገን አይችልም። እኛ አንድ ቤተሰብ ነን። ተያይዘን የአገራችንን መልክ በመቀየር ስደትን እናስቁም። እባካችሁ ራሳችሁን ውደዱ፣ሌሎችንም ውደዱ፣ ራሳችሁን አክብሩት፣ የኢትዮጵያ አምላክ ከእኛ ጋር ነው። ተስፋ አትቆረጡ። ተስፋ መቁረጥ ሞት ነው የኔ ዋንኛው ግብ የስደት ወረቀት ማግኘት ሳይሆን ነጻነት እንዲሰፍን ድልድይ መሆን ነው” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

አስተያየት ሰጪዎች

በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በተጠራው የወገኖች ውይይት ላይ የተገኙ አስተያየት ሰጥተዋል። ሁሉም አንድ እምነት አላቸው። ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለመመለስ የተደረገው ስምምነት ሊቀለበስ ይገባዋል። “አገሬ ውድ እቃ አለኝ” ስትል ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የልጇ ጠረንና ናፍቆት እንዳንገበገባት የገለጸችው ስርጉት በሴቶች በኩል የመደራጀት ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን አስምራበታለች።

አቶ ልዑል የተባሉ አስተያየት ሰጪ በብሄራዊ ጉዳይ ላይ ልዩነት ከሌለና መድረስ ለሚፈለግበት ዓላማ አስፈላጊ ከሆነ ተቀራርቦ መስራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።የማህበሩ ዋና ጸሃፊ ቢኒያም ካሳ “ታስረናል፣ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች ሰላባዎች ነን።የፖለቲካ መሪዎች ታዋቂ ስለሆኑ በተለያዩ መገናኛዎችና ተቋማት ከፍተኛ ሽፋን ያገኛሉ።በአገራችን ሁኔታዎች ከመጥፎ ወደባሰ መጥፎ ሲሄዱ እዚህ በስደትም ጉዳያችን በተመሳሳይ ወደባሰ መጥፎ ተቀይሯል” በማለት አገርና ጸሃይ የሞቀው የኢህአዴግ መራሹ አገዛዝ ገበና ይጋለጥ ዘንድ ተባብሮና ተደራጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ያሳስባል።

ጌዲዮን ደሳለኝ አብሮት ለሚሰራው ቢኒያም ድጋፉን ይሰጣል። ላንድ ኢንፎ አሁን መጠነኛ መሻሻል የሚያመላክቱ መረጃዎችን እያቀረበ ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም። ኢህአዴግን በመቃወም ፊትለፊት የተጋለጡና በተለያዩ ደረጃ እንደየ ፖለቲካ ዝንባሌያቸው የሚታገሉ እስከ ነጻነት ድረስ ከለላ አግኝተው ይኖሩ ዘንድ ተያይዞ መታገል ግድ ነው። “ተቀምጠን መፍትሄ አናመጣም” የሚለው ጌዲዮን “ያለን አማራጭና ችግር አንድ ነው። አሁን እየተደረገ እንዳለው ዲፖርቴሽንን መዋጋት። አገራችን ነጻ እንድትወጣ ጸንቶ ትግሉ የሚጠይቀውን ሁሉ በማድረግ መታገል፡፡”

መሉዓለም ደረጀ በበኩሉ “በመሬት ላይ ያለው እውነት ይታወቃል። አገራችን ያለችበትና ኢህአዴግ የቆመበት የአስተዳደር መሰረት የተሸፈነ አይደለም” በማለት አስተያየቱን የሚያጠቃልለው አሁንም የመደራጀትን አስፈላጊነት በማውሳት ነው። “ካልተደራጀን አንጠነክርም። ስንደረጅ ድምጻችን ይሰማል። ህግና ስርዓት ጠብቀን በጀመርነው መስመር እንተሳሰር፡፡”

በወገኖች ምክክር ወቅት የተገኙት ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያዊያን ድምጽ ነህና እናመሰግናለን ሲሉ ኦባንግ ሜቶን አድንቀው “ከልቤ ልንገራችሁ” በማለት አስተያየታቸውን ጀመሩ “አንድ ቀን ደስተኛ ሆኜ አላውቅም። ከቤተሰቦቼ ጋር እኖራለሁ። ጥሩ ስራ አለኝ። መኪና አለኝ። ቤት አለኝ። ለኑሮ የሚያስፈልገው ሁሉ አለኝ።ሁሌም የሚሰማኝ ጉድለት ነው። የመኖሪያ ወረቀት ማግኘት የህይወትና የማንነት መልስ አይደለም። የመኖሪያ ፈቃድ ያለውም የሌለውም ሁላችንም አንድ ጀልባ ላይ ነን። በዋንኛነት አገራችሁን ነጻ ስለ ማውጣት አልሙ…” ሲሉ ልምዳቸውን አካፈሉ።

“አገር ውስጥ ባይተዋር ከመሆን በላይ ውርደት የለም” ያሉት ዶ/ር ሙሉዓለም፣ የተወሰኑ ጮሌዎች የድሃውን ቤት እያፈረሱ ህንጻ ይገነባሉ። ሃብት ይሰበስባሉ። ሌሎች እንዳይተነፍሱ አፍነው ይጨፈጭፋሉ” በማለት የስርዓቱን አስከፊነት በመጠቆም “ድህነታችንን ችለነው የምንኖርበት አገር ልንመሰርት ይገባል” ብለዋል። በማያያዝም በስደት ካምፕ ውስጥ ስለሚገኙ ወገኖች በጥልቀት ማሰብና የምክር ድጋፍ ሊያገኙ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነ አመልክተዋል።

“እኔ ዝም ብዬ መኖር እችል ነበር። የራሴ የሆነው ፍጹም እምነቴ አርፌ እንድቀመጥ አይፈቅድልኝም። በአረብ አገራት ወገኖቻችን፣ እህቶቻችን ራሳቸውን እያጠፉ ነው። በባህርና በየብስ በየጊዜው የሚሞቱት ወገኖቻችን ናቸው። በግብጽ ሲና በረሃ ወገኖቻችን የሰውነት ክፍላቸው እየተወሰደ ነው። ዘግናኝ ተግባር እየተፈጸመባቸው ነው። ማልታ፣ ጃፓን፣ እስራኤል፣ሜክሲኮ … ይህንን የምዘረዝረው ሁላችንም ለወገኖቻችን ስቃይ ያገባናል እንድንል ነው” ይህ አቶ ኦባንግ ሜቶ የመጨረሻ መልዕክት ነው።

በኖርዌይ ከ5800 በላይ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ይኖራሉ። 2500 የሚሆኑት የኖርዌይ ዜግነት  አላቸው፤ 1400 የሚጠጉ የመጀመሪያ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን 1400 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወረቀት አልባ ናቸው ተብሎ ይገመታል። ከነዚህ ውስጥ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው የሚባሉት 700 የሚያህሉት እንደሆኑ ማህበሩ መረጃ ይሰጣል።

ዝግጅት ክፍሉ፦ ይህ ሪፖርት ሁሉንም ወገኖች አላካተተም። በተለይም በኖርዌይ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማነጋገር ከተለያዩ ወገኖች የሰበሰብናቸውን አስተያየት ጋር በማጣመርና የኖርዌይ ኢትዮጵያዊያን መገናኛ ድር አመራሮችን ሃሳብ በማከል ተጨማሪ ዘገባ እናቀርባለን።

ምስጋና፦ ሪፖርቱን ለማጠናከር እንችል ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር ላደረጋችሁልን ድርጅቶችና በኦስሎ ነዋሪ ወገኖች ምስጋናችን ከፍተኛ ነው። ፎቶ በመስጠት የተባበሩንን አቶ ፍቃዱ ብዙነህን ከልብ እናመሰግናለን!!

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Full Width Top, Land Information, Middle Column, UDI: Norwegian Directorate of Immigration, UNE: The Norwegian Immigration Appeals Board

Reader Interactions

Comments

  1. GEDION says

    November 5, 2012 03:16 pm at 3:16 pm

    በመጀመርያ የከበረ ሰላምታና ምስጋና ለጎልጉል ድህረ ገፅ አዘጋጆች፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዎይ እየደረሰባቸው ያለው ስቃይ ቀላል የሚባል አደለም፥ ምናልባትም እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ስለሆንን እንጂ ይሄን የረጅም አመት ስቃይ ማንም አይችለውም ባይ ነኝ፥

    ለማንኛውም የ Solidarity Movement for a New Ethiopia ዋና ሃላፊ አቶ ኦባንግ ሜቶን ወደኦስሎ አመጣጥና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዎይ በተመለከተ ያቀናበራችሁት ቅንብር አስደስቶኛል፥ በርቱ

    ጌዲዮን ከኦስሎ

    Reply
  2. nu nu says

    November 5, 2012 10:58 pm at 10:58 pm

    ባለፉት 21 አመታተ የህገራችን ፖለቲካ ሀዝባችን እያመሰና የንፃነት የሰላም የበልፅግና ተስፋችንን እየቀበረ አንደንታቸነና አከብሮታችንን አየቦረቦረ ኢትዮጵያችንን አንደገደል ላይ ቄጠማ ከገራ ቀኝ አያላተመው በመኖርና ባለመኖር ጥያቄ ከምንወዳት ከሀገራች ወጥተን በየሀገሩ ተበትነናል ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ችግር አያወቁ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉበት ምከንያት ብዙ ድክመት ስላለበን ይመስኛል ብዙ መስራት ቅንጀት ይጎለናል እኛ ሀብረት ቢኖረን ወያኔ ከሀገራችን አሳዶን እዚህ ያለንበት ደረስ መጥቶ አያሳደደነም ነበር አንደሚገባኝ ከሆነ አነዚህን ሆድ አደር ተኩላዎች ከውስጣችን ጎተተን አስካላወጣን ድረስ የበይ ተመልካቸ ሆነን ነው የምንቀሪው አነሱ የምያምትለነን አንጀራና በርበሪ ተቀበለን ኪሳቸውን አንሞላልን ሊቀር ይገባል . ሌላው ድርጅቶች በስደተኞች ጉዳይ ጥሪ ተደርጎላችው ሳይሆን ጉዳያችው ሊሆን ይገባል ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር ግሩም ዘለቀ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረት ልዩ ወገናውያውነት ሊኖራችው ይገባል .ኦባንግ ሳላመሰገንሀ አላልፍም እኛ ተስፋ ሳንቆርጥ ጠንከረን መስራት ይጠበቅበናል እንበርታ !!!

    ኑ ኑ ከትሮንድሃም

    Reply
  3. dawit says

    November 5, 2012 11:21 pm at 11:21 pm

    ከሁሉም በላይ ያስጨነቀኝ የህጻኗ መልዕክት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ያስደነገጠኝ በየካምፑ ያሉ ወገኖች ናቸው።አቶ ኦባንግ እንዳሉት እነዚህ ወገኖች እንዴት እንዳሉ መመልከትና መጎብኘት እጅግ ወሳኝ ተግባር ይመስለኛል።መጎብኘት ራሱ ታላቅ ተስፋ ነውና ለዓመታት ያለ ትምህርትና ስራ አንድ ቦታ ለኖሩት ወገኖች መድረስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለምና ሁሉም ሊተባበር ይገባል።እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉም ይተባበሩ ዘንድ የተላለፈ መልዕክት ይመስለኛልና እንተባበር።ይህንን ላስታወሱ ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና አለኝ።

    Reply
  4. ቤንጃሚን says

    November 6, 2012 11:01 pm at 11:01 pm

    እኛ አንድ ቤተሰብ ነን። ተያይዘን የአገራችንን መልክ በመቀየር ስደትን እናስቁም። እባካችሁ ራሳችሁን ውደዱ፣ሌሎችንም ውደዱ፣ ራሳችሁን አክብሩት፣ የኢትዮጵያ አምላክ ከእኛ ጋር ነው። ተስፋ አትቆረጡ። ተስፋ መቁረጥ ሞት ነው የኔ ዋንኛው ግብ የስደት ወረቀት ማግኘት ሳይሆን ነጻነት እንዲሰፍን ድልድይ መሆን ነው” {አቶ ኦባንግ ሜቶን}
    “እኔ ዝም ብዬ መኖር እችል ነበር። የራሴ የሆነው ፍጹም እምነቴ አርፌ እንድቀመጥ አይፈቅድልኝም። {ዶክተር ሙሉዓለም}
    ከዚህ አባባል ምን እንማራለን ???
    አቶ ኦባንግ ሜቶን,ዶክተር ሙሉዓለም,እንዲሁም በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ኮሚቴ ለምትሰሩት ስራ ልትበረታቱ ይገባል እናመሰግናለን !!!!!!!
    ጎልጉሎች እንኳን ደህና መጣቹህ !
    ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!

    ቢንያም ከክርስቲያንሳንድ

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule