
ሕገ-መንግሥቱን በጣሰ መልኩ በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ በኢፌዴሪ መከላከያ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የኦፕሬሽናል ጉዳዮች ኃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየርን ተከትሎ ሠራዊቱ በህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ሲውል የነበረው የአብዮታዊ ሠራዊት መገንቢያ ሰነድ ሠራዊቱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ እንዳላደረገው ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ አስታውሰዋል።
ስለሆነም በአገራዊ ሪፎርሙ አዲስ የሠራዊት መገንቢያ ሰነድ አገልግሎት ላይ መዋሉን ጠቁመው÷ አሁን ላይ ሰራዊቱ ያለ ምንም ፖለቲካ ወገንተኝነት ህዝብንና ሀገርን ህልውና እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ሠራዊቱ “የማንም ፖለቲካ ፓርቲ መጠቀሚያ አይደለም፣ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲና አክቲቪስት ጫጫታ ከተልዕኮው አይደናቀፍም ሲሉም ነው የተናገሩት።
ሠራዊቱ ጠንካራ ውስጣዊ አደረጃጀት እንዳለው የጠቆሙት ጄኔራሉ ከዚህ አንጻር ፖለቲከኞች በየትኛውም የፖለቲካ ቅስቀሳቸው ላይ የመከላከያ ሠራዊቱን የሚመለከት አጀንዳ ማራመድ የለባቸውም ብለዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ህገ-መንግስቱን የተከተለ መሆኑንም ጀኔራል ብርሃኑ አብራርተዋል።
በህገ መንግስቱ መሰረት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ እንጂ ‘ሽግግርና ባለአደራ’ በሚል ትርምስ አይደለም ሲሉም ነው የተናገሩት።
ከዚህ አንጻር ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለምና እንደፈለኩ እሆናለው የሚል አካሄድ ህገ-ወጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ-መንግሥቱን በጣሰ መልኩ ‘በሃይል ፍላጎቴን’ አሳካለሁ በሚል የትኛውም አካል ላይ ሠራዊቱ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ገልጸዋል።
ጀኔራል ብርሃኑ አክለውም የኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየርን ተከትሎ ሠራዊቱ በህገ-ወጥ ገንዘቦች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ሠራዊቱ ህገ-ወጥ በሚል ሰበብ ገንዘብ እየነጠቀ እንዲወስድ ፈቃድ ተሰጥቶታል በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ አካላት እንዳሉም ነው የገለጹት።
ሠራዊቱ ከተገነባበት እሴት ይህን እንዲያደርግ ፈጽሞ አይፈቅድለትም ብለዋል።
በህገ-ወጥ መልኩ ሲዘዋዋር የተያዘ ገንዘብ በአንድ ቋት ተሰብስቦ የጸጥታ መዋቅሩን ለማጠናከር እንደሚውል በማብራራት።
ሆነ ብለው በተደራጀ መልኩ የሀገር ኩራት የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ስም ጥላሸት የሚቀቡ አካላት እንዳሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ከውስጥ ምንጭ አገኘነው በሚል ሰበብ የመከላከያ ሠራዊት ስም የሚያጠፉ ጽሁፎችን ያሳተሙ ግለሰቦች መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ድርጊቱ ከባድ ወንጀል ቢሆንም በትዕግስት መታለፉን ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ በመሰል ተግባር የሚሳተፉ ማናቸውንም አይነት ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቀቀዋል።
ሠራዊቱ በአሁን ወቅት ማናቸውንም አይነት ተልዕኮዎችን በብቃት ማከናወን በሚያስችል ሙሉ ቀመና ላይ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
really yours documents