አሜሪካ የሽብር ህጉ አሰጋኝ አለች
በሳምንቱ አጋማሽ በእነ አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ መጽናቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃውሞ አሰምቷል። ቪኦኤ ድምጻቸውን ያሰማቸው የሚኒስቴሩ ተጠባባቂ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ቬንትል “ውሳኔው በጸረ ሽብር ህጉ ላይ ያለንን ስጋት ያጠናክረዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና በእነ እንዷለም አራጌ ላይ የተላለፈው ፍርድ በመጽናቱ አሜሪካ በጥልቅ ቅር ተሰኝታለች” ያሉት ቃል አቀባዩ ውሳኔው መንግስት የሚተቹትን ሁሉ ለፍርድ እንደሚያቀርብ አመላካች ነው ብለዋል።
ሰዎች በነጻነት የመናገርና የማሰብ መብት እንዳላቸው የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ያሰፈረችውን የሰብአዊ መብቶችንና የዲሞክራሲ መብቶችን ማክበር የወደፊቱ ግቧ እንደሆነ አመልክተው “ኢትዮጵያ እነዚህን መሰረታዊ መብቶቻቸውን ስለተጠቀሙ ያሰረቻቸውን በሙሉ እንድትፈታ ደጋግመን እንጠይቃለን” ብለዋል። አሜሪካ በሽብርና ከሽብር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ኢህአዴግን በግንባር ቀደም የምታግዝና ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ የምታቀርብ አገር መሆኗ የሚታወቅ ነው።
የእስክንድር ነጋ ባለቤት ሰግታለች
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር ነጋን ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ወይም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ለማዛወር መታሰቡን ባለቤቱ ሰርካለም ስጋቷን እንደገለጸች ሪፖርትር አስታውቋል። ጋዜጣው ዝርዝር ባያቀርብም እስክንድር ወደ ዝዋይ ከተዛወረ ባለቤቱና ልጁ እሱን ለመጠየቅ እንደሚቸገሩና ምን አልባትም ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። እነ እስክንድር ነጋ ላይ የ18 ዓመት ፍርድ ያጸኑት ዳኛ ዳኜ መላኩ ናቸው።
ዳኜ መላኩ ውሳኔውን ካሳወቁ በኋላ ከፍተኛ የሃዘን ስሜት ችሎቱ ውስጥ ይታይ ነበር። ፍርደኞቹ ወደ እስር ቤት ሲመለሱ ድምጽ አውጥተው ስሜታቸውን የገለጹላቸው እንደነበሩ ሪፖርትር በደፈናው ግለጿል። እስክንድር እጁን ወደ ፈጣሪው በማንሳት “እውነት ተደብቃ አትኖርም” ሲል መናገሩን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል”፡፡
የሽብር ህጉ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል ተባለ
ባለፈው አርብ በዓለም ተከብሮ የዋለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ሂውማን ራይትስ ዎች “የኢትዮጵያ የሽብርተኞች ህግ የፕሬስ ነጻነትን አውድሟል” አለ። እስረኞች እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል።
ከመግለጫው በተጨማሪ የድርጅቱ የናይሮቢ ጥናት አቅራቢ ላቲቪያ ቤደር የሽብር ህጉ በረቂቅ ደረጃም ሆነ ህግ ሆኖ በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የመናገር መብትን የሚነፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል። ለቪኦኤ ቃላቸውን የሰጡት ላቲቪያ ድርጅታቸው የምዕራቡን ዓለም የኒዖ ሊብራል ሃሳብ አቀንቃኝ ስለሆነ ነው በተደጋጋሚ ኢህአዴግን የሚቃወመው በሚል ስለሚሰነዘረው ለተጠየቁት “ይህ በማንኛውም መልኩ ርዕዮተ አለማዊ ጉዳይ አይደለም፤ ጥሪያችን ስለ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መከበር ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናደርገው የመብት ጥሪ ነው። በኢትዮጵያ ይበልጥ የሚያሳስበን ጸረ ሽብር የተባለ ሀግ ጸድቆ ጋዜጠኞችን ለማፈን ጥቀቅም ላይ መዋሉ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሂይውማን ራይትስ ዎች አጥኚ ላቲቪያ ቤደር ድርጊቱን ከመቃወም ባለፈ ጫና በመፍጠር የታሰሩት የፖለቲካ አስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ለቪኦኤ በሰጡት ቃል እንዳስታወቁት “አገራቱን በሚረዱ ወዳጅ አገሮችና ለነጻነት የሚቆረቆሩ ተጽዕኖ ፈጥረው እስረኞቹን እንዲያስፈቱ በየጊዜው እንወተውታለን” ብለዋል። በፕሬስ ነጻነት ቀን ይፋ እንደሆነው በኢትዮጵያ 11 ጋዜጠኞች በሽብር ህግ ተከሰዋል። ስድስቱ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ አምስቱ ወህኒ ቤት የሚገኙት ናቸው። ከአምስቱ መካከል ሶስቱ ተፈርዶባቸዋል። ሁለቱ ዮሴፍ ጌታቸውና ሰለሞን ከበደ የፍርድ ሂደታቸውን እየጠበቁ ነው።
ኤርትራ ካሰረቻቸው ጋዜጠኞች መካከል የተገደሉ አሉ
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካሰሯቸው ከ10 በላይ ጋዜጠኞች መካከል እስር ቤት በሚያሳዝን መልኩ የሞቱ እንዳሉ ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡለት የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ሃላፊ ተናግረዋል። ሃላፊው ለቪኦኤ የናይሮቢ ዘጋቢ እንደነገሩት ኤርትራ ውስጥ የታሰሩት ጋዜጠኞች ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
እስረኞቹ ቤተሰቦቻቸውን አያገኙም፣ የት እንዳሉ በውል አይታወቅም፣ በዜግነት ስዊዲን የሆነው ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ ሁሉም እስረኞች በህይወት ስለመኖራቸው ቤተሰቦቻቸው ተስፋ በቆረጡበት ወቅት ሃላፊው ጉዳዩ ለአፍሪቃ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለቀረበ ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከታህሳስ 2006 ጀምሮ ኢትዮጵያ ያሰረቻቸውን ተስፋ ልደት ኪዳኔና፣ ተስፋ እግዚ የተባሉትን ሁለት የኤርትራ ተወላጆች ጉዳይም ሃላፊው አንስተዋል “ጋዜጠኞቹ በኮሚኒካዶ ታስረዋል” ያሉት ሃላፊው እስረኞቹ በጠበቃ መወከልና በቀይ መስቀል ሊጎበኙ እንደሚገባ አመልክተዋል። ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤርትራ ዘልቆ ከገባ በኋላ ነበር። በወቅቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለና ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ መለስ ጦሩ የያዘውን ቦታ ለቆ እንዲወጣ ማዘዛቸው አይዘነጋም።
በተዛማጅ ዜና በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2012 ብቻ 121 ጋዜጠኞች መገደላቸውን በመግለጽ ለጋዜጠኞች ጥበቃ እንዲደረግ ዩኔስኮ ጥሪውን አቅረቧል። ዩኔስኮ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ ነው።
የአቶ አስግደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታሰረ
የህወሀትን የበረሀ ትግል ታሪክ የሚዘክረውን ገሀዲ ቊጥር አንድ፣ ሁለት እና ሶስት የሚሉ መጽሀፎችን ከመጻፍ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በማጋለጥ የሚታወቁት አቶ አስገደ ገብረስላሴ ሁለተኛ ልጅ ታስሯል።
የ28 አመቱ የማነ አስገደ ገብረስላሴ የሶፍት ዌር ኢንጂነረግ ምሩቅ ሲሆን፣ በውቅሮ በመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ነበር። አዲሱን ስራውን ሲጀምር አቶ አስገደ ልጅ መሆኑ በመታወቁ በቅጣት ወደ በረሀ ተመድቦ እንደነበር አባቱ አቶ አስገደ ገልጸዋል።
እናቱ ሻለቃ ግደይ ወ/ሚካኤል ልጃቸውን አያቱ ወደ ሚኖሩበት አዳህላይ ወደምትባል ቀበሌ ለህክምና መውሰዳቸውን ተከትሎ በቀበሌው የሚገኘው ትምህርት ቤት በመቃጠሉ የህወሀት ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው “ትምህርት ቤቱን ያቃጠለው አቶ አስገደ የሚባል የአረና ትግራይ ድርጅት አባል ልጅ ነው” በማለት ሊወነጅሉ ሲሞክሩ ህዝቡ “ሀሰት ነው ” በማለት በመቃወሙ ባለስልጣናቱ ሳይሳካላቸው እንደቀረ አቶ አስገደ ገልጸዋል። ስብሰባው ከተበተነና ህዝቡ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ ፖሊሶቹ ልጃቸውን አስረው መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በእስር ላይ የሚገኘው የ26 አመቱ አክህፎም አስገደ 06 እየተባለ ከሚጠራው ድብቅ እስር ቤት ወጥቶ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወሩን አቶ አስገደ ገልጸው፣ አለም ባደረገው ጫና ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸውን በአይናቸው ለማየት እንደቻሉ እና ከወር በኋላም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አክለዋል።
አቶ አስገደ በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ቤርሙዳ እየተባለ የሚጠራ እስር ቤት መኖሩን አውስተዋል። “የእነሱ ልጆች በህዝብ አንጡራ ሀብት ይማራሉ፣ የኛ ልጆች ይህን የተበላሸ ኑሮ ችለው በኖሩ በእንዲህ አይነት እስር ቤት ማሰቃየት ከዚህ በላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም ብለዋል። (ዘገባው የኢሳት ነው)
Leave a Reply